Monday, August 20, 2012

ዳኛቸውና ገዢ ሐሳቦቹ

እንዳልካቸው ኃ/ሚካኤል እና አቤል ዋበላ

ከዶ/ር ዳኛቸው ጽሁች መሀከል ጥቂቶቹ

የቄሳር እና አብዮት መጽሐፍ ዳሰሳ
አንዲት ኢትዮጵያ ሬድዮ
ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ
ግልጽ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  አዲስ ጉዳይ መጽሔት
ሰብል እርሻ በጅብ ማረሻ  ፍትሕ ጋዜጣ
ዳኛቸው ስለ ብርቱካን   አዲስ ነገር ጋዜጣ

ብሔራታ ወልማታ- ሸገር ራዲዮ ጋር ያደረው ቃለ ምልልስ
የአገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ስፋት እና ጥልቀት ስናስተውል ብዙዎቻችንን በቀቢጸ ተስፋ እንባክናለን፡፡ ይህን ለማሻሻል የተጀመረ ተዋስኦ አለመኖሩ ደግሞ ሀዘናችንን እጅግ ያበረታዋል፡፡ በተማሩትና በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ ዙሪያ እንኳን ትንፍሽ የማይሉ ነገር ግን ማዕረጋቸው ላጠራር የከበደ ሰዎች በየመስኩ ተደርድረዋል፡፡ብዙዎቹ ልሂቃን ትውልድን በሚገራና አቅጣጫ በሚያሳይ መልኩ አርአያ አለመሆናቸው አገሪቱ  በሐሳብ ክፍተት እንድትዳክር አድርጓታል፡፡ ዞን ዘጠኝም የነገዋ ኢትየጵያ መጻዒ ተስፋ የሚያሳስባቸው ወጣቶች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን የራስንም የአቻንም መደናበርን ለመቀነስ ወይም ሐሰሳን ለመደገፍ ስናስብ አገሪቱ ካሏት ጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነው ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ ላይ አይናችን አረፈ፡፡ (በዚህ ጽሑፍ ላይ እኚህን የተከበሩ ምሁር ‹አንቱ› ሳንል የቀረነው፣ ለንባቡ ቅልጥፍና እንዲመች በማሰብ መሆኑን አንባቢዎች እንድታውቁልን፡፡)

ከዚህ በፊት ለአደባባይ የዋሉት ሥራዎቹ እጅግ ቢማርኩንም ወጥ የሆኑ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ይህንን የሐሳብ ኦና (idea vacuum) ለመሙላት ከሚታትር መምህር  የበለጠ ለመቅሰም በአንድ ወዳጃችን እርዳታ አገኘነው፡፡የዳኛቸው ሐሳቦች እጅግ የሚገዙ ለአብዛኛው ሰው ቅርብ የሆኑና በቀላሉ በሚገቡ ናቸው፡፡ ሀገራዊ ስነ ቃሎችና ስነጽሑፎችን በማጣቀስ፣ የሀገራችንን የቅርብና የሩቅ ታሪኮች ከፍልስፍና ንድፈ ሐሳብ ጋር በማጣመር  የመተንተን አቅም አለው፡፡ ይህንን ታላቅ ምሁር ከአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ ውጭ ላለው የህብረተሰብ ክፍል በማስተዋወቅ አዲስ ነገር ጋዜጣ ጉልህ ሚና ተጫውታለች፡፡ በወቅቱ በእስር ቤት የነበረችውን የአእምሮ እስረኛ ዘሪ ብርቱካን ሚደቅሳን እስራት ኢፍትሕዊነት አስመልክቶ በጻፋቸው ተከታታይ ሑፎች ወደ አደባባይ ብቅ ያለው ዶ/ር ዳኛቸው በብዙ አካዳሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙርያ ገዢ ሐሳቦችን እያካፈለ ይገኛል፡፡እኛም ከነዚህ ብዙ ጉዳዮች ውስጥ የተወሰኑትን  በመምረጥ ትውልድ ሊያተኩርባቸው እና የምር ሊያነባቸው እና ሊያዳምጣቸው የሚገ መሆናውን ለመጠቆም እንዲህ አቅርበነዋል፡፡  


የአደባባይ ተዋስኦ /public discourse/

ዶ/ር ዳኛቸው የዲሞክራሲ ባህል እንዲዳብር ከተፈለገ ጫፍ አልባ ውይይት (endless conversation) ያስፈልጋል ይላል፡፡ በንግግር ተዋስኦ የሚመጣው ችግር በበለጠ ንግግር ማሸነፍ ይገባል ሲልም ይከራከራል፡፡ አንዳንዶች ያለገደብ ውይይትን መፍቀድ  ለብዙ የምግባር ችግሮች (ዘለፋ፣ ስድብ እና ልቅ ወሲብ ቀስቃሽ ምርቶች ለመሳሰሉት..) ይዳርጋል ይላሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይህ ግን እቀባ/ እግድ በመጣል  ሊፈታ አይችልም፡፡ ከነጻ ንግግር የሚመጣን ችግር ለመፍታት የበለጠ ነጻ ንግግር (more free speech) መፍቀድ ይገባል፡፡ ብሔርን ብሔርን ያጋጫል፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ያላትማል የሚል ሰባራ ሰንጣራ ምክንያት በመት ነጻ ንግግርን/ማሰብን ለማለፍ ወይ ለማገድ መሞከር ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ የውይይት ባህል መዳበር እንዳለበት ሲያሰረዳ ደግሞ አውሮጳውያን የዲሞክራሲ ባህል ጉዞን ሲጀምሩ በዘመነ አብርኆት (enlightenment) ወደ አንድ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ የነበውን ወግ እና ባህል ፈትሸዋል፡፡ ሰፋ ያለ የውይይት ዘመንን በማለፍ ከዲሞክራሲ ባህል ጋር ተለማምዋል ከዲሞክራሲ አሰራር ጋር የሚጣረሱ ግባራትን እና ጽንሰ ሳቦችን ሁሉ ለማጥራት ችለዋል ይለናል፡፡

ኢትዮጵያ እና የአደባባይ ተዋስኦ ባህላችን

አውሮጳውያን የአደባባይ ተዋስኦ ባህላው እጅግ የጠነከረ እንደሆነ የሚመሰክረው ዶር ዳኛቸው ለዚህም  በዘመነ አብርኆት የዲሞክራሲ ባህላቸውን እንዳያዳብሩ የሚያግዱ ጽንሰ ሳቦችን በይፋ በውይይት ማስወገድ በመቻቸው እንደሆነ ያስረዳል:: ከነዚህ ጽንሰ ሳቦች ውስጥ ተጠማኒያዊነት ይሰኛል፡፡

ኢትዮጵያ ባህል ተወሰነ መልኩ ማኒያነዊነት (Manichaeism) እንደተጫነው የሚጠረጥረው ዶ/ር ዳኛቸው  ለዚህ እንደማስረጃ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገድላትን ይጠቅሳል፡፡ ማኒያነዊነት አስተምህሮ መነሻው  በሦስተኛ ክፍለ ዘመን በተነሳ እና ራሱን ከዞራስተር፣ ቡዳህና ክርስቶስ ቀጥሎ የመጣ የመጨረሻው ነብይ አድርጎ በሚቆጥረው በማኒ ነው፡፡ ማኒያዊነት የኖስቲክዝም (Gnosticism) ከፍተኛ ተጽእኖ ቢኖርበትም መሰረታዊ አስተምህሮው መላውን ጠፈር በክፉና ደግ አምላክ ትግል እንደተፈጠረች በመጥቀስ ነገሮችን ሁሉ ቅዱስና ርኩስ ብርሃንና ጨለማ በማለት ምነታዌ አድርጎ ይከፋፍላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአገራችን መኖሩ የዴሞክራሲ ባህልን እንዳንገነባ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡  

ግሪኮች  አንድ  ፓለቲካዊ ፍልሰፍናቸውን የገለጹበት ብሒል አላቸው፡፡ አንተ መንግስትን ማማት አትችልም ምክንያቱም አንተ ራስህ  የመንግስት ነጸብራቅ ነህና ግዛትና ባህሉ (state and culture) ተዋህዶ የሚኖር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አምባገነን መሪዎችን በማየት የኛ ናቸው ለማለት ስንቸገር ይታያል:: እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ሐሳብ ግን እነዚህን አምባገነኖች የሰራቸው የኛው ማኅበረሰብ ባህል ነው፡፡ ለዚህ እንደማስረጃ መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ መለስ ዜናዊና ኢሳያስ አፈወርቂን እንደምሳሌ ያቀርባል፡፡ በውጭ ትምህርት መልክ ለመደበቅ ቢሞከርም የኢትዮጵያዊ ባህል ማሳያ ናቸው፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ በሀገራችን የተከሰተው ውዥንብር ማንሳት ይቻላል፡፡ Politics is the art of compromising (ፖለቲካ ማለት የማመቻመች ጥበብ ነው፡፡) በባሕላችን ያለው ማኒያዊነት ግን ይህን እንድንረዳ አልፈቀደልንም፡፡ መንግስት ፍጹማዊ ድል ለመጎናጸፍ  የቅንጅት መሪዎችን በመወንጀል ሰብስቦ አሰረ፡፡ ቅንጅት ደግሞ ህዝቡ ተሰልፎ የሰጠውን መብት ሙሉ በሙሉ አልተሰጠኝም በማለት አልቀበልም የምፈልገው ፍጹማዊ ድልን ነው አለ በማለት ዶ/ር ዳኛቸው ይተነትነዋል፡፡

የዘመን መንፈስ

እንደ ሔግሊያን አመለካከት በአንድ ሀገር መንግስትን የሚበይነው (assign) የሚያደርገው መንፈስ አለው፡፡ ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ እጓለ ገብረ ዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በተሰኘ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ አውሮጳ፣ በጀርመን ሀገር ሳሉ ላዩት ለዚያ ዘመን ወጣት መንፈስ መጽሐፋቸውን እንደመታሰቢያ ሲያቀርቡ  “በከፍተኛ መንፈስ ለተነሳው ወጣት እጅ መንሻ  እንዲሆነኝ…”  ማለታቸው  በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ስለነበረው ለመማር፣ ለማወቅ፣ አገርን ለመለወጥ የሚያስብ መንፈስ እንደነበረ እንረዳለን፡፡ እያንዳንዱ ስርዓት የራሱ መንፈስ አለው፡፡ ከዚህ መንፈስ ውጭ ከዚያ ስርዐት መጠየቅ አስቸጋሪ ነው፡፡

እንደ ዶ/ር ዳኛቸው ትንተና የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስተ ሦስት የዘመን መንፈሶች ነበሩበት፡፡ የመጀመሪያው ምንሊክ እንደወለላ ትተዋት የሄዷትን አትዮጵያ ማያያዝና አሐዳዊ ስርዓትን መዘርጋት ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግም ከቅኝ ገዢዎችና ኢምፔሪያሊሰቶች ትንኮሳ ሉዓላዊት ኢትዮጵያ መጠበቅና  የተከበረ የውሃ በርን በበሰለ ዲፕሎማሲ አንድ ጥይት ሳይተኮስ ማሰገኘት ነበር፡፡ ሶስተኛው ደግሞ  ዘመናዊት ኢትዮጵያን መገንባት ሲሆን ይህም የሞሶሎኒን አማካሪዎች አስደንገጦ “ለተፈሪ አስር አመት ከሰጠኸው ኢትዮጵያን ዘመናዊ ያደርጋታል፤ ቶሎ ብለህ ኢትዮጵያን ውረር፤ ኋላ አልሰለጠነችም ብሎ ለመውጋት አስቸጋሪ ነው” የሚል መልእክት እንዲስተላለፉ አስገድዷቸዋል፡፡ የዘመናቸው መንፈስ ያዘዛቸው ይሄን ነው፡፡  ወታደራዊው መንግስት አገርን ለማያያዝ ካደረገው ጥረት ውጪ የረጋ የተጨበጠ መንፈስ አልነበረውም፡፡ ኢህአዴግም ለወጉ ዴሞክራሲ፣ ፌደራሊዝም፣ ሕገ መንግስት የመሳሰሉ ነገሮችን ቢያወራም መንፈስ ግን ያን አላሸከመውም፡፡ በዲሞክራሲ በኩል፣ በነጻነት በኩል፣ በመብት በኩል መመልከት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ነው፡፡ አሁን እንደተረዳደሁት ይላል ዶ/ር ዳኛቸው  ዴሞክራሲዊነት እንዲያብ፣ ሕገ መንግስታዊነት እንዲመጣ፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መንፈስ እንዲነሳ ኢህአዴግ መታለፍ (supplant) አለበት፡፡ አሁን ኢሕአዴግም ይህን የተረዳ ይመስላል በሚዲያው ስለልማት፣ ስለዕድገት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስለማሰለፍ ብቻ ነው የሚያወራው፡፡

ወንበር በሌለበት ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና!?

ሁለት ዓይነት ፍልስፍናዎች አሉ የመጀመሪያው በእንግሊዘኛው small p የሚጽፉት ፍልስፍና (philosophy) ሲሆን ሁሉም ሰው ይህ ፍልስፍና አለው፡፡ ገንዘብ አወጣጥ፣ ልብስ አስተጣጠብ፣ የምግብ አበሳሰል የመሳሰሉት…  ለነገሮች ያለው አዝማሚያ ማለት ነው፡፡ ‘ብዙ ገንዘብ ለሰው ማበደር አልወድም፤ ይህ ፍልስፍናዬ ነው’ ማለት ይቻላል፡፡ በcapital P የሚጽፉት (Philosophy) ግን የተወሰኑ መመራመሪያ መንገዶችን አበጅተው መሰረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚደረግ እንቅስቃሴ  ነው፡፡ አርስቶትል በሜታፊዚክስ እንዲህ ብሏል “እኛ ብቻ ነን እውነት ላይ  ለመድረስ መፈላሰፍ አለብን ያልን ለሌላ ነገር አይደለም፤ ግብጾችን እዩ ስልጣኔ አላቸው ግና ከኋላ ሌላ ዓላማ አላቸው፣ ፐርሺያንም ተመልከቱ እኛ ብቻ ነን ፍልስፍናን ለፍልስፍና ስንል የተከተልን” ብሏል፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ፍልስፍና ስንመጣ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዓመታት የዘለቀ በሀይማኖታዊ አሻራ የቀለመ የትምህርት ዘይቤ አለ፡፡ ይህ የትምህርት ስርዓት በከፋፈላቸው ውስጥ ፍልስፍና የሚያስተምር የትምህርት ዘርፍ የለም፡፡ ከዋሸራ ጀምሮ ባሉ አድባራት እኔ መምህር እገሌ ፍልስፍና አስተምራለሁ ብሎ ወንበር የተከለ መምህር የለም፡፡ ወንበር ማለት የትምህርትና ስልጠና ተቋም (institution) ማለት ነው፡፡ በቅርቡ የተነሳ የሳይንስ ታሪክ ምሁር በመካከለኛው ዘመን የነበረ የእስልምና ሳይንስ የት ደረሰ ብሎ ይጠይቃል፡፡ በመስቀል ጦርነት ወቅት ምዕራባውያን እና ሙስሊሞች ሲዋጉ ምዕራባውያኑ በወታደሮች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከርኩስ መንፈስ ጋር በማያያዝ በጠበል እና በጸሎት ለመፈወስ ሲተጉ የሙስሊም ሀኪሞች ግን በተቃራኒው በሰውየው ላይ ደረሰውን የጎራዴው ጋር እና ሌሎች ሁኔታዎች ጋር በማያያዝ ሳይንሳዊ ግምት ለመስጠት ጥረት  ያደርጉ ነበር፡፡ ከላይ ያነሳነው  የታሪክ ምሁር እንዲያ ተስፋ ሰጭ የነበረው የእስልምና ሳይንስ ወዴት ጠፋ ብሎ ይጠይቅና የምዕራብ ክርስትና በመካከለኛው ዘመን ለነበረው እውቀት፣ ፍልስፍናና ወንበርን ስትሰጠው እስልምና ግን ወንበር ባለመስጠቷ የያ ተስፋ ሰጭ (promising) ሳይንስ ሊጠፋ ችሏል፡፡ በኢትዮጵያም እንዲሁ ወንበር ስላልነበረ ፍልስፍና አለ ለማለት አይቻልም ባይ ነው - ዶ/ር ዳኛቸው፡፡

የዘርዓ ያዕቆብን እንደ ብልጭታ (Bleeps) ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህን ከምዕራባውያን ተማረው ለማለት  አይችልም፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሀገር እንዳደረጉት እንዲሁ ጋልበውት (በባህል፣ በሀይማኖት) እንደሄዱት በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሁኔታ አልገጠማቸውም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሲደርሱ የራሳችን የሆነ  ቅዳሴ (Liturgy)፣ ትርጓሜ (hermeneutics) የንባብ ባህልና ስነ ጽሑፍ እንዳለ ሲያዩ እንደደነበሩ (shoked እንደሆኑ፣) ይህም ድንጋጤያቸው እስከ ቅርብ ጊዜ አብሯቸው እንደቆየ እንደሚገምተው ዳኛቸው ሐሳብ  በዘመኑ የነበረው ተጋላጭነት (exposure) ይህን በራሱ እንዲጠየቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህ እንደ መነሻ የሚያገለግለው በዘርዓያዕቆብ ዘመን የመንበረ ጳውሎስ ትርጓሜን፣  የእስክንድርያንም፣ የኢትዮጵያውያን ሊቃውንትን ትርጓሜ አጠናው ማለቱን ይጠቅሳል፡፡ ይህንንም ቅዱስ  ላሊበላ  በኢየሩሳሌም የነበረውን ቆይታና  ልዑል ተፈሪ መኮንን በአውሮጳ በፓሪስ ከተማ ለሦስት ወራት ያደረጉት ጉብኝት  የፈጠረባቸውን ተጽእኖ በተወሰነ መልኩ ያስረዳል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ዘርዓያዕቆብ  ያለ  ሰው ከኢትዮጵያ ሊወጣ አይችልም ብለው የጻፉ  ምሁራን አሉ፡፡ ፕሮፌሰር ሳምነርና መምህር አለማየሁ ሞገስ ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሚዛን የደፋ ሐሳብ እንዳላቀረቡ የሚስማማው ዳኛቸው መኖሪያውን በካናዳ ያደረገው የፍስሐ ታደሠ ክርክር ሳቢ የሆነ አዲስ ሐሳብ ይዞ እንደመጣ ይቀበላል፡፡ እንደፍስሐ ሐሳብ የዘርዓ ያዕቆብ ያነሳቸው ንባብ፣ ሐሰሳ፣ ስለመጠየቅ፣ ስለአእምሮ ሲያነሳ የኢትዮጵያውያንን ሊቃውንት አይመጥነንም፡፡ ስንት ብዙ ውስብስብ (sophisticated ) ጽሑፎች እያሉ እንዲህ ሊባል አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት ብዙ ጠይቀዋል ከዚህ በላይ ያውቃሉ ባይ ነው፡፡ እድሜ ከሰጠን ወደፊት ፍስሐ ታደሠ ያለበት ተዋስኦ እንደገና እንደሚኖር ዳኛቸው ፍንጭ ይሰጣል፡፡ እሰከዚያው ግን ዘርዓያዕቆብን እንደኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነው የምንወስደው፡፡
                                
ማኅበራዊ ጅማት ወይም ውል /social fabrics or contract/

የአገር አመሰራረትን አስመልክቶ ሁለት ዓይነት እሳቤዎች (schools) አሉ፡፡ የመጀመሪያው አገርን እንደ ተክል፣ እንደሚያድግ አበባ፣ ስር፣ ቅርንጫፍ ያለው ቀስ እያለ እየተከማቸ (sedimented) የሚያድግ  ሲሆን  ማኅበራዊ ጅማት (social fabrics)፣ ጥቅል የጋር ትውስታ  (collective memory)፣ ወግ (norm) የመሳሰሉት ገንዝብ ያደረገ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አገር እንደጭቃ ተድቦልቡላ እንዲሁ በዘፈቀደ የተፈጠረ ነው ባይ ናቸው፡፡ ለዚህ ትልቋ ምሳሌ ዩኤስ አሜሪካ ናት፡፡ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮችም በቅኝ ግዢዎች ነው እንዲህ ባለ ሁኔታ የተመሰረቱት፡፡ እንደዳኛቸው ሐሳብ ኢትዮጵያ በጠነከረ ማኅበራዊ ጅማት የተገነባች አገር ነች፡፡ ጉዳዩ በአካል ጨብጠህ የምትይዘው ዓይነት ነገር አይደለም ሜታፊዚካልም ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ እጅግ ጠንካራ ነገር ይናገራል፤ ለዚህ እንደምሳሌ በቦስተን ዩንቨርሲቲ ሳለ የገጠመውን ያነሳል፡፡ በኒው ዮርክ ከተማ ለሦስት ቀናት መብራት ይጠፋል ከዚያ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያና ወንጀል ይከሰታል፡፡ በዚያን ወቅት ከሶቪየት ተባሮ በአገረ አሜሪካ ያለ ሶልኒስተን የሚባል የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት በሀርቫርድ የኒቨርስቲ ንግግር እንዲያደርግ የተጋበዘው ሶሊንስተን እንዲህ ሲል አሜሪካኖቹን ልካቸውን ነገራቸው፡፡ ሀገራችሁ ጨቅላ ናት፣ ሦስት ቀን መብራት ቢጠፋ እርስ በርስ አንገት ለአንገት  እነዴት ትያያዛላችሁ፤ ሀገሬ ራሺያ ግን ታላቅ ሀገር ናት፡፡ ነገ ዛሬ አምባገነኖች ቢይዟትም ስርዐቱ ነገ ይወድቃል፡፡  በጠንካራ ማኅበራዊ ጅማት የተገመደች ናት፡፡

አሁን ዛሬ ላይ ሆነን ዶ/ር ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሐፋችን ነው፡፡ ለብዙ ተዋስኦች ጤናማ ገዢ ሐሳቦች አሉት፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክንም አብጠርጠሮ ያውቀዋል፡፡ ፍልስፍና ለእርሱ ክህሎት ነው፡፡ ልክ እንደ ፈረንሳያዊው ፈላሰፋ ሰ በሀገረኛ የስነጽሑፍ ውጤቶች አጅቦ ታላላቅ የፍልስፍና ቲዎሪዎቹን ለብዙዎች በሚገባና በሚማርክ መልኩ ያቀርባል፡፡ እኛ ከባህሩ በጥቂቱ እንዲህ ተመልክተናል፡፡ የበረታ እንዲዋኝበትም ሲሻው ጠጥቶ እንዲሰክር ፈቅደናል፡፡ ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም፡፡

No comments:

Post a Comment