Saturday, February 2, 2013

ስለግብ ጠባቂዎች እስኪ እንነጋገርበኤፍሬም ማሞ

ለአሁኑየዋሊያዎቹን በአፍሪካ ዋንጫ 31 ዓመት በኋላ ተሳትፎ እንደመጨረሻ ግብ አድርገው ወስደው፣ አይ በእግር ኳስ የሚሆነው አይታወቅም ምናልባትም ወደሚቀጥለው ዙር ሊያልፉ ይችሉ ይሆናል ከሚሉት ወገን ነገርኩ፡፡ የልምድ ማነስ ያመጣውን ችግር ያው በሜዳ ላይ እስተውለነዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመወከል በደቡብ አፍሪካ ላደረጉት የልብ ጥረት ሁሉም የቡድን አባላት ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ሞቅ ያለ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ብሎ ማስብ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ግን ጥቂት ስለበረኞቻችን እንነጋገር፡፡ አንድ በረኛ የሚፈጽመው አስደናቂ የግብ ሙከራን የማዳን እንቅስቃሴ የቡድን አባላትን የማነቃቃቱን ያህል በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉ ኳሶች ከመረብ ማረፋቸው ደግሞ ተስፋ መቁረጥን የመዝራት እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡በአህጉራዊ ውድድሮች በሶስት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ጠባቂዎቿ ከሜዳ በቀይ ካርድ የተወገዱባት አገር ማየት እንዲህ የተለመደ ክስተት አይመስለኝም፡፡ ጀማል ጣሰው በዛምቢያው ጨዋታ ወደ ጎል ያላነጣጠረች ኳስን ይዞ ከመጣ ዛምቢያዊ ሲላተም ከቀይ ሌላ ዳኛው የሚያሳዩት ካርድ አልነበረም፡፡ የሲሳይ ባንጫም በናይጀሪያው ጨዋታ በቀይ መወገድ ሊወገድ የሚችል ስህተት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

በረኞቻችን በአገር ውስጥ ክለብ

ታዲያ በረኞቻችን ይህንን ሁሉ ስህተት እንዲህ በመሰለ ታላቅ አህጉራዊ ውድድር መፈጸም ምንጩ ከየት ነው ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው በደቡብ አፍሪካው የአሃጉራዊ የእግርኳስ ውድድር የቀረቡት ግብ ጠባቂዎች በአገራቸው የክለብ እግር ኳስ ያላቸው ሚና ከወንበር ማሞቅ አንጅ የግብ መጠበቅ ተግባር ላይ አይደለም፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዘሪሁን ታደለ ለኡጋንዳዊው ሮበርት ኦዶንከራ የአንደኛ ደረጃ ግብ ጠባቂነትን ቢያስረክብ ብዙ የማቅማማት እድል አይኖረውም፡፡ አንድ ክለብ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶ ያስመጣውን ተጫዋች አስቀምጦ የአገሬውን ተጫዋች ያሰልፋል ብሎ መጠበቅ የዋህ ቢያሰኝ ነው፡፡

የቡና ገበያ እግር ኳስ ቡድንም ዘካሪያ ኦንያነጎን ከኬንያ አስመጥቶ ለአገር ልጆች የግብ ጠባቂነት ሚና ወንበር ማሞቅን አድርጓል፡፡ ጀማል ጣሰውም ከደቡብ አፍሪካዊው ሞካሲ ጃኮብ ተመርጦ በጨዋታ የመሰለፍ እድሉን ያገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡

የደደቢት የእግር ኳስን የተጫዋቾች ዝርዝር ላየ ጃኮብ ሞካሺ የተሰኘ እንግዳ ስም ለቁጥር አንዱ ቦታ ተሰጥቶ ያያል፡፡ ይህ ከደቡብ አፍሪካ የፈለቀ ግብ ጠባቂ ለአገር ልጆች በተጠባባቂ ወንበር መቆየት ተጠያቂ መሆኑን ልብም የሚለው አይመስለኝም፡፡

የሃገራችን ስመ-ጥር የእግር ኳስ ቡድኖች እንዲህ ከውጭ ሃገር የግብ ጠባቂዎች ጋር ፍቅር በፍቅር የሆኑት በአገር ልጆች የግብ አጠባበቅ ክህሎት ማነስ ወይስ እነሱን በሚያበቃው ስልጠና ክፍተት? ጥናት አድራጊዎች ጉዳዩን ቢዳስሱት የተሻለ ነው፡፡

መፍትሔውስ?

ታዲያ መፍትሄው ምን ይሆን ለሚለው ጥያቄ ግን ሩቅ ሳንሄድ ወደ ግብጽ ሃገር እናገኘዋለን፡፡ ሳልሃዲን ሰዒድ ለአገር ውስጥ ብዙሃን መገናኛ በሰጠው ቃለ-ምልልስ በግብጽ ሃገር የክለቦች ውድድር ላይ የውጭ ሃገር ተጫዋችን ማስመጣት የተከለከለ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ በዚህኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቀንቷት ያልተሳተፈችው ግብጽ ስመ ጥር በረኞችን በማፍራት ከአሃጉሩ ቀደምት አገሮች መሆኗ የታወቀ ነው፡፡

ይህ መልዕክት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ባለስልጣናት ይድረስና ከግብጽ በተገኘው ልምድ አንጻር ተቃኝቶ የአገር ውስጥ የእግር ኳስ ቡድኖች የግብ ጠባቂነቱን ስፍራ ለአገር ልጆች ቢለቀቅላቸው መልካም ይሆናል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው እንዳስተዋልናቸው አይነት ስህተቶቸን የማስወገጃው አንዱ መንገድ በረኞቻችን አስፈላጊውን የጨዋታ ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ ይሆናል፡፡ ሁነኛ አሰልጣኝ ፈልጎ የግብ ጠባቂነትን ክህሎት እንዲዳብር ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን፣ የመጫዎቻ ሜዳዎቸን ማመቻቸት፣ የታዳጊዎችና ወጣቶች ስልጠናን ማጠናከር፣ የአስፈላጊ ቁሳቁሶች አቅርቦት፣ የአስተዳደር ጉደፈቶችን መቅረፍ፡ ተያያዥ ግን ጠቃሚ ግብዓቶች መሆናቸው እንደማይዘነጉ አምናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment