Sunday, July 22, 2012

ጋዜጣና መጽሔቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ - ሰባት


(ከሐምሌ 9፣ 2004 እስከ ሐምሌ 15፣ 2004)

ሪፖርተር  በረቡዕ ዕትሙ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸው ተሰማ›› የሚል ዜና አስነብቦናል፡፡ ‹‹በ21 ዓመታት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤንነት ችግር በ19ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ያልተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመልካም ጤንነት ላይ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የውጭ ሕክምና ክትትላቸውን ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ …››

** ** **
‹‹የሚኒስትር ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ከሳዑዲ ዓረቢያ የሃይማኖት አታሼ ቢሮ ገንዘብ ይዘው ሲወጡ ተያዙ›› የሚል ዜና ያስነበበን ሰንደቅ ጋዜጣ ነበር፡፡ ‹‹…[ወ/ሮ ሃቢባ ሐምሌ 10፣ 2004] …ግምቱ ከሃምሳ ሺ እስከ መቶ ሺ ብር የሚገመት የታሰረ ገንዘብ እና በዓረብኛ የተጻፉ መጽሐፍት ይዘው ሲወጡ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡…››

** ** **

ፍትህ ጋዜጣ ከጋዜጦች ሁሉ ተለይቶ በዚህ ሳምንት አልወጣም፡፡ የጋዜጣው ከፍተኛ አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በፌስቡክ ገጹ ችግሩ ከአሳታሚው አለመሆኑን እንዲህ ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹ዛሬ አርብ ነው፤ ፍትህ ግን አንባቢያን ጋር አልደረሰችም፡፡ በእርግጥ ትላንት የጋዜጣው የሽያጭ ሰራተኛ ብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ተገኝቶ ለ30 ሺህ ኮፒ 80385 (ሰማኒያ ሺህ ሶስት መቶ ሰማኒያ አምስት) ብር ከፍሏል፡፡ የፍትህ ህትመት ክትትልም እኩለ ሌሊት ላይ ማተሚያ ቤት ቢደርስም የህትመት ክፍል ሀላፊው ‹‹ፍትህን እንዳታትሙ ተብለናል›› በሚል ጋዜጣዋ ሳትታተም አደረች፡፡

‹‹በዛሬው ዕለትም የማተሚያ ቤቱን ምክንያት ለማወቅ ወደ ብርሃና ሰላም ከጥቂት ባልደረቦቼ ጋር ሄድኩኝ፡፡ ሆኖም ምክትል ስራ አስኪያጁ ከሌሎች የድርጅቱ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ስብሰባ ቢጤ አድርገን እንድንወያይ ጠየቁን፡፡ ተወያየን፡፡ በፊት ገፅ ላይ ያለ አንድ ዜና ማንሳት እንዳለብን ከመጠቆም ባለፈ እዚህ ጋር የማልገልፀውን እጅግ አሰፋሪ የሆነ መደራደሪያ አቀረቡ፡፡ እኛም የሀገሪቱን ህግ ጠቅሰን ተከራከርን፡፡ ያለስምምነት ከሰዓት 8፡30 ላይ ተወያይተው ውሳኒያቸውን ሊያሳውቁን በቀጠሮ ተለያየን፡፡ ቀጠሮውንም ተቀብለን ስንወጣ ከተሰበሰብንበት የም/ስራ አስኪያጁ ትንሿ አዳራሽ በር ላይ የፍትህ ሚንስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ዓቃቢ ህግ ተቀምጠው አየናቸው፡፡ በር ላይ ደግሞ በመልክ የምናውቃቸው በርከት ያሉ የፀጥታ ሰራተኞች እንደተለመደው አጀቡን፡፡ ይህንን በዕምሮአችን ይዘን ወደቢሮአችን ተመለስን፡፡ ሰዓቱ እስኪደርስ ለምሳ ወጣን፡፡ ምሳ ለመብላትም ካሳንችስ አካባቢ አንድ ምግብ ቤት ገባን፡፡ ተመግበን ስንወጣም አደባባይ ላይ የመኪናዬ ጎማዎች ፈንድተው አገኘን፡፡ ከዛም ከሰዓት በኋላ በቀጠሮአችን ሰአት ም/ስራአስኪያጁ ቢሮ ስንደርስ ‹‹እንዲታተም ተፈቅዷል›› የሚል መልስ ተሰጠን፤ እናም ጋዜጣዋ አሁን እየታተመች ነው፡፡ ነገ ጠዋት ትወጣለች ብለንም እንጠብቃለን፡፡››

ተመስገን እንዲህ ቢልም ፍትህ ጋዜጣ ቅዳሜም ገበያ ላይ አልዋለም፡፡ ይህንንም ተከትሎ ተመስገን ይህንን ጽሁፍና የደብዳቤ ኮፒ አያይዟል፡፡ ‹‹በትላንትናው ዕለት ለስርጭት መብቃት የነበረባት ፍትህ የጠቅላይ ሚንስትሩን መታተም ተከትሎ በተፈጠረው የስልጣን ትግል እያሸነፈ በመጣው አክራሪ ሀይል ተስተጓጉላ የነበረ ቢሆንም በማግስቱ እንድትታተም ተፈቅዷል ተብሎ ታተመች፡፡ ትላንት ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይም ሙሉ በሙሉ ታትማም አለቀች፡፡ ነገር ግን አንባቢያን እጅ ልትደርስ አልቻለችም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ (በዛው ኃይል ትዕዛዛ ይመስለኛል) በአቃቢ ህግ ብርሃኑ ወንድምአገኝ ‹‹ለሀገር ደህንንት የሚያሰጋ ዘገባ በጋዜጣው ላይ መታተሙ መረጃ ስለደረሰን እንዲታገድ ወስነናል›› በሚል የተፈረመ የዕግድ ደብዳቤ ማተሚያ ቤቱ እንደደረሰው ገለፀልን፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ሰዓት 30 ሺህ የፍትህ ጋዜጣ እትም በብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት ተቆልፎበት ይገኛል፡፡
…እንዴት ነው ነገሩ? ‹‹ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ›› እየሆነ ነው? ይህ ሁኔታ ወደስልጣን እየመጣ ያለው ሀይል የባሰ እንደሆነ ምልክት እያሳየስ ይሆን? ለማንኛውም መጨረሻውን አይተን የራሳችንን እርምጃ እንወስዳለን፡፡ (ማተሚያ ቤቱ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል የላከውን ደብዳቤ እዚህ ይመልከቱ)››
-- -- --
በተያያዘ ዜና፣ ‹አልቁዱስ› የተባለው የሙስሊሞች ጋዜጣ የሚታተምበት ማተሚያ ቤት በመታሸጉ ‹ዘገነርስ› የተባለው የአርብ ስፖርት ጋዜጣም ሳይታተም ቀርቷል፡፡ አርብ ዕለት ይወጣ የነበረው ‹ነጋ ድራስ›ም በዚህ ሳምንት ገበያ ላይ አልዋለም፡፡

** ** **

አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊ ገጹ ‹‹አዲሱ የመንግስት ቤቶች የመሸጫ ዋጋ ይፋ ሆነ›› ይላል፡፡ አነስተኛ ገቢ ያቸው ዜጎች በ26ሺ ብር የቤት ባቤት ይሆናሉ፣ በቀጣዩ ዓመት 10ሺ ቤቶች ይገነባሉ፡፡ ‹‹… በነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ ለመታቀፍ የቤቱን ሽያጭ ዋጋ 40 በመቶ በመቆጠብ 60 በመቶውን ከባንክ በሚገኝ ብድር የቤት ባለቤት ለመሆን እንደሚቻልም ሚኒስትሩ ተናግረዋል…››

** ** **

‹‹Meles Back in Town›› (መለስ ወደከተማ ተመልሰዋል) የሚል የፊት ገጽ ዜና ያስነበበን Fortune ነው፡፡ በዝርዝሩም፣ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጫ በተሰጠ ማግስት (አርብ ዕለት) ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደአዲስ አበባ መግባታቸውንና የጤንነታቸውም ሁኔታ በጣም እየተሻሻለ መምጣቱን ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ ዘግቧል፡፡


ሌላም፣ ሌላም
  • ኢትዮጵያን አይዶል ክብሩን ያጣ ፕሮግራም ነው፣ ባለሙያዎቹ ምንም ነገር የማያውቁ ናቸው ተብያለሁ - አቶ ይስሐቅ ጌቱ (የኛ ፕሬስ)
  • የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መራራ የዕድገት ሽሙጦች፤ 140 ሺ ቶን ጫት በየዓመቱ ይቃማል፣ 7 ቢሊዮን ብር ለጫት ፍጆታ ይውላል - መሰናዘሪያ
  • አንድነት በሰላማዊ ትግል ለሚመጣ ችግር ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አለ፤ ለጠ/ሚስትሩ መልካም ጤንነት ተመኝቷል፡፡ - አዲስ አድማስ
  • ከኮሌስትሮል ነፃ የሚባለው የፓልም ዘይት ነፍሰገዳይ መሆኑን ያውቃሉ? - ኢትዮ ቻናል
  • ንግድ ባንክ የሚድሮክ የሚድሮክ ኩባንያዎችን በ942 ሚሊዮን ብር ብድር አንበሸበሸ - ሪፖርተር (እሁድ)

ርዕሰ አንቀጾች