Thursday, July 12, 2012

ስለምንስ ከምሁራን መካከል ትፈልጉኛላችሁ? !

የትምህርት ጉዞው የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ ተማሪዎች በምረቃ ቀን የሚለብሱት ጋወን ፣ አስመራቂ ቤተሰቦቻቸው ወደ ምረቃው ቦታ የሚገቡበት የመግቢያ ትኬት ከየትምህርት ክፍላቸው እየወሰዱ ነው፡፡ አንድ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ተግባር ግን ይቀራል፡፡ የአንድ ሙሉ ቀን ስልጠና፡፡ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በመጡ ባለሙያዎች ከምረቃ በኋላ ሊሰማሩባቸው ስለሚችሉባቸው የስራ አይነቶች፡፡

ገነትም ከነዚህ ሰልጣኞች መካከል አንዷ ስትሆን በ3 አመት የዩንቨርስቲ ቆይታዋ Applied Biology ያጠናች ስትሆን ከተቻለ አንድ ፋርማሲ ሰራተኛ ውስጥ አለዚም መምህር እሆናለው የሚል ህልም ነበራት፡፡ በስልጠናው የሰማችው የስራ መስክ ግን አልተዋጠላትም፡፡ ተደራጅቶ የባልትና ውጤቶችን መሸጥ፣ የከተማ ግብርና ላይ መሰማራት፣ የኮብል ስቶን ማንጠፍ ስራ፣ፓርኪንግ ወ.ዘ.ተ፡፡

ይህ በ2004 ዓ.ም ተማሪዎቻቸውን ያስመረቁ የሁሉም የመንግስት ዩንቨርስቲዎች እና ተማሪዎች ሰሞነኛ ቆይታ ነው፡፡

ትምህርት

የሰው ልጅ ሁሉን ያውቅ ዘንድ አይቻለውም ስለዚህም ስለ ክዋክብቱ መረዳቱ የበዛለት ላላወቀው እሱም ስለ ስነ ተዋልዶ እውቀቱ ከሌለው ከአዋቂው የሚቀስምበት ስርዓት ነው ትምህርት፡፡ አንድ ሰው አቃቂ ምሁር ይባል ዘንድ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች የዕውቀት ላቂያ ይኑረው ያኔም አዋቂ ይባላል ይለናል የRenaissance Man Theory፡፡ ለዛም ይመስላል በአብርሆት ዘመን (15-18 Century) የነበሩ ምሁራን ሁሉን አቀፍ እውቀት ነበራቸው ልንል የምንችለው፡፡ የፍልስፍና፣ የሂሳብ፣ የስነ-ክዋክብት፣ የስነ-ሰብ ወ.ዘ.ተ እውቀቶችን አንድ ምሁር አቅፎ ሊይዝ ይችል ነበር፡፡

ይሄ ትክክል አይደለም ይልቅስ በህብረተሰቡ ውስጥ እምርታ ይመጣ ዘንድ የስራ ክፍፍል (Division of Labor) ወሳኝ ነው ብሎ ስኮትላንዳዊው የስነ-ምጣኔ ምሁር አዳም ስሚዝ የሀሳብ ሽግግር ካደረገ ወዲህ፡፡ እያንዳንዱ ህብረተሰቡ አካል አንድ የስራ መስክ ላይ በተለየ(Specialize) አድርጎ ጥናት ካደረገ እና ከተማረ በዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያመጣል በሚል የትምህርት ስርዓቶቹም በዚህ ሀሳብ መቀረፅ ጀመሩ፡፡ ባጫ ምህንድስና ፣ አበበ ህግ ፣ አይዳ እርሻ ወ.ዘ.ተ እየተማሩ በያዙት ሙያ ላቂያን ማሳት ይችላሉ የሚለው የ Specialization Theory አሁን ድረስ በትምህርቱ ዘርፍ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡


ሱፍ ለባሽ ምሁር

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ መቶ አመት እንኳን አልደፈነም ፡፡ የመጀመሪያው ዘመናዊ የመንግስት ትምህርት ቤት በ1908 ነው የተቋቋመው እስከ ጣልያን ወረራም ብዙ ተማሪዎችን ማስተማር አልተቻለም በአብዛኛውም ከውጭ ተምረው የመጡ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ እንደ ምሁር የሚቆጠሩት፡፡ ከነዚህ በውጭ ተምረው የመጡ 120 ተማሪዎች ውስጥ ጣልያን በተለምዶ የሚያዚያ 28ቱ ጭፍጨፋ ተብሎ በሚጠራው ድርጊት 75 በመቶዎቹን እንደ ገደላቸው የመንግስትን ሪፖርት ጠቅሰው Mrgery Perham, The Government of Ethiopia ባሉት መፅ ሃፋቸው ያስረዳሉ፡፡

እንግዲህ በጣሊያን ወረራ 75 በመቶ የተማረ ሀይሏን (በነገራችን ላይ የተማረው ሀይል 75 በመቶ ማለት 90 ምሁራን ብቻ ማለት ነው) ካጣች በኋላ እስከ ንጉሱ የስልጣን ዘመን ማክተሚያ ድረስ የተማሪዎች ቁጥር (በውጭም በሀገር ውስጥም ተምረው የመጡት) በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡
  • አለ ከተባለ የፈረንሳይ ህግ ትምህርት ቤት ህግ ተምሮ የሀረርጌ አውራጃ አስተዳዳሪ የእልፍኝ አሽከር፣
  • Literature 4 ዓመት ሙሉ እነ ሸክስፒርን፣ እነ ሞንታኝን፣ እነ ዳንቴን እንዲያም ሲል እነ ቶልስቶይን ሲያጠና ከርሞ በንግድ ሚኒስቴር የወርሃዊ የዋጋ ጥናት ባለሙያ መሆን፣
  • የምጣኔ ሀብት ትምህርትን እንደ ውሃ ጨልጦ በበጌምድር አውራጃ የደምቢያ ወረዳ የመንግስት ሹም ወ.ዘ.ተ እየሆኑ ነበር እነዚህ እውቀትን እና አለባበስን ከአውሮፓ የቀዱ ምሁራን ወደ ስራ አለም የሚሰማሩት ፡፡

በርግጥ አቢዮተኛ ው ያ ትውልድም የዚህ ሱፍ ለባሽ ምሁር አካል ነበር፡፡

የተማረ ሁሉ ያስተምር

ደርጉ መጣ ሁሉንም ነገር ወደ ጦር ግንባር ከማለቱ በፊት የትምህርት ዘመቻ ጀመረ 'ማሃይምነት አይነስውርነት' ነው በሚል የሚያሸማቅቅ መፈክር የገጠሩን ህዝብ ስሙን ይፅፍ ዘንድ ፊርማ በእርሳስ ይፈርም ዘንድ አስቻለው፡፡ ነገር ግን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪወች የተማሩትን ትምህርት የት አደረሱት ከተባለ፡፡ ግማሾቹ አቢዮት ጠባቂ፣ ግማሾቹ የቀበሌ ሹም ፣ ወታደር ቤትም የገቡ አሉ፡፡

ይልቁንም ደርጉ ተማሪዎችን ከነ ኢህአፓ ጋር 'ንክኪ' አላቸው በሚል በጥርጣሬ ነበር የሚመለከታቸው፡፡ ይባስ ብሎም ከሀገር በፊት የምን ትምህርት ብሎ በተለምዶ ‘ምሁሩ ጦር’ የሚባለውን ወታደር ከዩንቨርስቲ አፍሶ ብላቴ ጦር ማሰልጠኛ ከተተ፡፡ የተማሩት ትምህርትም አላማው ጠፋባቸው ለነዚህ ምሁር ወታደሮች፡፡

ስለምንስ ከምሁራን መካከል ትፈልጉኛላችሁ? !

ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ ከሰራቸው አመርቂ ስራዎች አንዱ ትምህርትን በነፃ ተደራሽ ለማድረግ ያደረገው ጥረት እና ያም ያመጣው ውጤት ነው፡፡ አጠቃለይ የትምህርት ፖሊሲ በ1986 ዓ. ም ከወጣ በኋላ ብዙ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተሰርተዋል፣ የትምህርት ቤቶች የቅበላ አቅም በብዙ እጥፍ ጨምሯል፣ ከ30 በላይ የመንግስት ዩንቨርስቲዎች ተገንብተዋል፡፡

ነገር ግን የትምህርት ፖሊሲውን ሁለት ዋነኛ ተግዳሮቶች አንቀው ይዘውታል፡፡

1. የትምህርት ጥራት ጉዳይ፡

መንግስትም እንደሚለው ዋነኛው የትምህርት ፖሊሲያችን ፈተና የጥራት መጓደል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ:

  • ዩንቨርስቲ የChemistry ምሩቅ ተማሪዎች Chemistryን Khemistry እያሉ እንደሚፅፉ ይነገራል፡፡
  • አራቱን የሂሳብ ስሌቶች የመለየት ችግርም የምሩቃኑ ሌላው ጣጣ ነው፡፡
  • በሶሲዎሎጅ ተመርቀው ካርል ማርክስ ሲባል እሱ ደግሞ ማነው? ማለትም ያስደነግጣል፡፡
  • ህግ ተምረው የCivil Right እና የCivil Code ልነትን አለማወቅም ይወራል፡፡

አዎ ጥራቱ ችግር ውስጥ ነው፡፡

2. ሁለተኛው እና አዲሱ የትምህርት ፖሊሲው ችግር ሰዎች ተምረው በተማሩበት ትምህርት መስክ ሊሰሩ አለመቻላቸው ነው፡፡

የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን የ2011 ዓ.ም የከተማ ስራ አጥነት 18 በመቶ እንደሆነ መረጃው ያስረዳል ፡፡ሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ደግሞ መጠኑ ከዚህ እንደሚልቅ ይገልፃሉ፡፡

እንግዲህ ከዩንቨርስቲ የሚወጡት ምሩቃን ከነዚህ ስራ አጦች ቁጥር ላይ የሚደመሩ ናቸው፡፡ ይሄን ቁጥር ለመቀነስ ይመስላል መንግስት ሰሞኑን እንደምንሰማው ወጣቶችን በተለያዩ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ እያደረገ የሚገኝው፡፡

  • ችግሩ ግን አንድ ሰው Computer Science ተምሮ የኮብል ስቶን ጠረባ ላይ የመሰማራቱን ጥቅም ስናሰላስለው ነው፡፡
  • ችግሩ ግን አንድ ወጣት በPhysics ተመርቆ በከተማ ግብርና ተግባር ላይ ሲሰማራ የተማረውን ትምህርት ተግባር ላይ እንዴት ሊያውለው ይችላል? ያልን እንደሆነ ነው፡፡
  • ችግር የሚሆነው Afan Oromo & Literature የተማረች ወጣት በባልትና ውጤት ስራ ላይ ተሰማርታ ስናይ ነው፡፡

ይሄ ስኬት ነው እንዴ ለመሆኑ?



Nelson Mandela በግለ-ታሪካቸው ላይ ስለ ትምህርት ሲናገሩ :

"Education is the great engine of personal development. It is through education that the daughter of a peasant can become a doctor, that a son of a mineworker can become the head of the mine, that a child of farm workers can become the president of a nation."

አሁን ወዳለው ሀገራችን የትምህርት ውጤት ስንሄድ ማንዴላ እንደሚሉት ትምህርት የገበሬውን ልጅ ዶክተር ፣ የማዕድን ቆፋሪውን ልጅ የሀገር መሪ የሚያደርግ መሳሪያ ነው ያሉትን የትምህርት Upgrade የማድረግ ሚና Downgrade በማድረግ የተተካ ያስመስለዋል፡፡ አለዚያማ ስለ ፓለቲካል ህልዮት ሲማር የከረመ ወጣት እንዴት የብየዳ ስራ ላይ ይሰማራል?፡፡

ገነት ‹‹ስለ ስራ አስበሽ ታወቂያለሽ?›› ተብላ ስትጠየቅ ‹‹እኔ የምማረው እናቴ ተመርቄ ስታየኝ ደስ እንዲላት ነው እንጅ ስራ መስራት አልፈልግም›› ትላለች፡፡ እንግዲያውስ ገነቶችን ከምሁራን መካከል መፈለግ ምን ሊረባ?

No comments:

Post a Comment