Saturday, July 14, 2012

ጠቅላያችን የማን ናቸው?

 
ሰሞኑን የጠቅላያችን ጤና በጽኑዕ መቃወስ የሚያወሱ ጭምጭምታዎች ከተለያየ አቅጣጫ እየተናፈሱ ይገኛሉ፡፡አንዳንዶቹ እንደውም ስለ ድህረ መለስ ኢትዮጵያ እና ስለተተኪዎች የምር መነጋገር ይዘዋል፡፡እንደው አያድርገውና! ድንገት ጸጥ ቢሉ መቃብራቸው ላይ የሚነበብ አጭር የህይወት ታሪካቸውን የመጻፍ ሃላፊነት  ቢሰጠን ምን እናደርግ ይሆን? አንድ የኔ ብጤ ተርታ ሰው ቢሆን ብዙም አያስቸግርም፡፡ የእርሳቸው ለመጻፍ   ግን  የህይወት ታሪክ  እና  ሌላውን መደበኛ ታሪክ (history and biography) ማጣቀስ ተገቢ ነው:: ለዚህ ደግሞ ሁነኛው የትምህርት ዘርፍ የስነ ማኅበረሰብ ጥናት (sociology ) ነው፡፡

እንደ የስነ ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች  ትንታኔ ሰው በዕለት ተዕለት ጉዳዮቹ ወስጥ የተለያዩ ማኀበራዊ ማነቆዎች ያጋጥሙታል፡፡አንድ ማእከላዊ ሰው (average person) እነዚህ ያገጠሙትን እክሎች(traps)  አልፎ የግሉን ችግሮች ከትልቁ ስዕል (ከሚኖርበት ማኀበረሰብ ፣ ከዓለም ታሪክ) ጋር ለማያያዝ ይከብደዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ከራሱ ትንሽ ዓለም (መንደር ፣ ጎሳ ፣ ት/ቤት ፣ መ/ቤት) አንጻር  መረዳት ይቀናዋል፡፡ ጥቂቶች ነገር ግን የመንፈስ ልዕልና (quality of mind)  ያላቸው ግላዊ ጉዳዮችን ከማኅበረሰብ ጋር አጣምሮ ለማየት የሚያስችል ማኀበረሰባዊ ነጽሮት (Sociological imagination) አላቸው፡፡

ስነ ማኅበረሰባዊ ነጽሮት  ብዙ ፍሬዎች አሉት፡፡ የራስን የህይወት ልምድ ከታሪክ አጋጣሚና ከማኅበረሰባዊ መዋቅሮች ጋር በማገናኘት እድል ፈንታ ጽዋ ተርታን ለመለካት ይጠቅማል፡፡ እንዲሁም  በማኅበረሰብ ውስጥ የራስን ሚና መለየትና ራስን ለአንድ ስፍራ ለማጨት ያስችላል፡፡  በዚህ ዘርፈ ብዙ ማኀበረሰብ ውስጥ የኔ ስፍራ  የት ነው?  የሚለውንም  ጥያቄ ለመመለስ የሚደረግም ሐሰሳ ነው፡፡ በዚህ ነጽሮት ተጠቅመው የራሳቸውን፣ የቤተሰባቸውን፣ የመንደራቸውን ችግር የፈቱ ሰዎች ‘የራሳቸው ናቸው’ ለማለት ይከብዳል፡፡ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የፈጠሩት ደግሞ የሁሉ ሰው (global citizen or cosmopolitan person) ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእኛም  ማኅበረሰብ ውስጥ እንደዚህ ህዝበ አዳም የኔ የሚላቸው አልፎ አልፎ ይታያሉ፡፡ በየእደሩ፣ በዕቁብና በጽዋ ማኅበራት ከማዕከላዊነት አልፈው ከቤተሰባቸው በላይ ለአከባቢያቸው ማኅበረሰብ የሚተጉ ሰዎች አልጠፉም፡፡ እንደዛሬ የመቅለል ዘመን ሳይመጣ፣  የረባ ሚኒስቴር ሳይጠፋ በፊት   በዓለም አቀፍ ተቋማት በማገልገልም የዓለምን ህዝብ የጠቀሙ ጠንካራ ዲፕሎማቶችም  ነበሩን፡፡ እንግዲህ ይህን መሰረት አድርገን ነው የጠቅላያችንን አጭር የህይወት ታሪክ ለመጻፍ ጥረት የምናደርገው፡፡ በነጽሮታቸው መጠን ለማኅበረሰባቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦና ይህን ተከትሎ ከማኅበረሰቡ የሚሰጥ  “የኔ ነህ  ፣ጀግናዬ  ነህ፣” ከሚል ማዕረግ፡፡ በአንድ ቃለ መጠይቅ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ስለጠቅላያችን ጭንቅላት ምጥቀት ሲናገሩ “ገንዘብ ለማግኘት ብፈልግ እርሱን ከዚህ አስወጥቼ  ሌላ ስራ እንዲሰራ ነው የማደርገው” ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዳይሆንብን እርሱን ትተን በርዕሰ መንግስትነት ለሁለት አሥርት ዓመታት ካስተዳደሯት ኢትዮጵያ ተነስተን ‘የኢትዮጵያ ናቸው/ አይደሉም ?’ ብለን እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ

ብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን እርሳቸውን የኔ ብለው ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ በግድ አስገድደው ያንተ ነኝ ካላሉት በቀር ሁሉም እርሳቸውን መሪዬ ናቸው ብሎ ለመቀበል አይፈልግም፡፡ እርግጥ ነው ሙሉ ወጣትነታቸውን በጫካ ያሳለፉት አቶ መለስ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ የመወሰን  “እምዬ መለስ” ተብሎ የመጠራት ብዙ እድል በእጃቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን የሚያዩበት መነጽር በእጅጉ ስለተንሸዋረረ የኔ የሚያስብል ግብር ሳይኖራችው ሁለት አሥር ዓመታት አለፉ፡፡ ታሪኳን ወደ ሰማንያ አመት፣ ባንዲራዋን ወደጨርቅነት፣ ልጆቿን ለርሀብ እና ለስደት የዳረጉ በመሆናቸው ከኢትዮጵያ ማህጸን የተፈጠሩ፣ አፈሯን ፈጭተው ያደጉ ስለመሆናቸው ብዙዎች እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል፡፡ የሚጠበቅባቸውን አለመፈጸማቸው ሳያንስ የሀገሪቷን መጻዒ ተስፋ እንዳይፋፋ ምሁራንን የሌሉበት፣ ጋዜጠኞች የሚታሰሩበት ማድረጋቸው ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ያደርጋቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በፓርቲያቸው ካድሬዎች አገላለጽ አቶ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የማይሆኑበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

የትግራይ

በወርሃ የካቲት በ1968 ዓ.ም. የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ድርጅት(ት.ህ.ነ.ኣ.ድ)  የትግሉን መግለጫ ባሰፈረበት የመጀመሪያ እትሙ የትግላቸው ዐብይ ምክንያት ከቀን ቀን እየተባባሰ የሚሄደው የኢኮኖሚ ብዝበዛ በሰፊው የትግራይ ህዝብ (ትግርኛ ተናጋሪዎች፣ አፋር (ጠልጠል)፣ አገው ፣ ሳሆ፣ ኩናማ ወ.ዘ.ተ.) ላይ ድሕነት ርሃብና ውርደት እየተደደጋገመ እንዲደርስ በማድረጉ የሥራ ማጣት ችግር ሽርሙጥናና ስደትን ማስከተሉ መሆኑን ያትታል፡፡ ይህ ያልጠራ ንደፈ ሐሳብ ብዙዎቹን በማጓጓቱ ብዙዎቹ የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ገብረዋል፡፡ ይህ ግን እነአደይን በብዙ ከተሞች እጃቸውን ለምጽዋት ከመዘርጋት አላዳናቸውም፡፡ በስደትና በሴተኛ አዳሪነትም የራሳቸውን ድርሻ ያነሳሉ፡፡ አንዳንዶች ስርዓቱ ለትግራይ ተወላጆች የተለየ ጥቀማ ጥቅም እንደስገኘ ሽንጣቸውን ገትረው ቢከራከሩም በእለት ተዕለት የሚያጋጥመን እውነታ ይህን አይነግረንም፡፡ በጭንጋፉ ስርዓተ ትምህርት ያለፉ፤ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ በሆነው የኑሮ ውድነት የሚዳክሩ የትግራይ ተወላጅ ወዳጆቼ በዙሪዬ በከበቡኝ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ሰውየው የትግራይ ናቸው ለማለት ይከብደኛል፡፡ እርግጥ ነው እርሳቸውም ቢሆኑ ብሔራቸውን ሲጠየቁ ‹‹እኔ በእሳት ተፈትኖ ካለፈው የትግራይ ሕዝብ ነው የወጣሁት›› ቢሉም ትግራይ የኔ አትላቸውም፡፡

ባላባታዊ መደብ በመደብነት እንዳይኖር ቢዋደቁም አሁንም ኢትዮጵያ (ትግራይ) ጥቂቶች የሚምነሸነሹባት ሆናለች፡፡ ወሰን አልባ ርሃብ እና እርዛቱን ለመቋቋም የትግራይ ክልል እየተረዱ ዜጎች ዛሬም የሴፍቲ ኔት መርሐግብር ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህ ያንገበገበው ትግራዋይ ዘለዓለማዊ ኢትዮጵያዊ እንዲህ እያለ ማንጎራገር ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ ለየካቲት 11 ብዙሓት አኖታት ኣብሻያት ወይድማ አዴታት ..ንዘላዓለም ዘይምሎሱ መንእሰያት ህባተን ይኹን ደኣምብር ንውሕዳት ህይወት ቁማርተኛታት ሸሻይ ኾይና አላ፡፡

የቀዳማዊቷ

አቶ መለስ የልጆቻቸው ናቸው ለማለትም አያስደፍርም፡፡ እርግጥ ነው የፈለጉትን እንደሚበሉ፣ ያሻቸው ነገር እንደማይጎልባቸውም ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህን አንድ  የመርካቶ ነጋዴም ያደርገዋል፡፡ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ዐብይ ተክለማሪያም የጠቅላያችን በአንድ ቃለ መጠይቅ  ስለልጃቸው ሰመሃል መለስ ዜናዊ አስረስ “ልጆት በአደባባይ ፖለቲካ ህይወት እንድትሳተፍ ይመኛሉ?” ለሚል ጥያቄ  የሰጡትን  “እንደ ዕድል ሆኖ እኔ ስለእርሷ አልወስንም ነገር ግን መወሰን ብችል ከዚህ ዓይነት ህይወት (ከፖለቲካ) ራቂ ብዬ እመክራት ነበር፡፡” የሚል መልስ ተከትሎ ‘የአባት ውርስ’ በሚል ጽሑፉ ጠቅላያችን ልጃቸው ወደ ቦለቲካ እንዳትገባ አንደ ጥሩ አባት  የከለከሉበትን ምክንያት ከተነተነ በኋላ አለመግባቷ ከዚህ እንደማያድናት አስረግጦ እንዲህ ይላል፡፡

“የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደገኛ ቢሆን፣ ውስን ቢሆን፣ ክብረ ቢስነት ቢበዛበትም እንኳ በከፊልም ቢሆን አቶ መለስ ራሳቸው ተጠያቂ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ሰመሃል ፖለቲከኛም ሆናም ሆነ ሳትሆን የምታልፍበት ሁኔታ የአባት ውርስ እንጂ የተፈጥሮ እና የአምላክ እዳ አይደለም፡፡”

አዲስ ነገር ጋዜጣ 2ኛ ዓመት ቁጥር 101 መስከረም 16 200 ዓ.ም.

ይህ ከወዳጅ ከዘመድ ከሀገር ልጅ የማያኖር የአባት ውርስ ስንገነዘብ ጠቅላያችንን የልጆቻቸው እዳ እንጂ መኩሪያ እንዳልሆኑ እንረዳለን፡፡ከነርሱ ይልቅ ቀዳማይቷ እመቤት አዜብ መስፍን የኔ ቢሏቸው ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ስርዓት እንደርሳቸው የተመቸው የለም፡፡ ከጅማ እስከ መተማ እንደሚነግዱ፣ Boeing 777 ለመሸመት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው፣ ለጌጣጌጥ መግዣ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያወጡም ብዙዎቻችን ሰምተናል፡፡ እነዚህን እውነት አዘል ሀሜቶች ያደመጠ ሰው የሰውዬውን አጭር የህይወት ታሪክ ቢጽፍ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፡፡

“ወዲ ዜናዊ ምንም ያልነበራትን የወልቃይት ጠገዴ ኮረዳ ከምንም አንስተው ለብዙ አመታት ተዋግተው ፣ ላይ ወጥተው  ታች ወርደው፣ ቀን እረፍት ሌት እንቅልፍ አጥተው፣ ቢሊኒየር ለማድረግ ባደረጉት ግብግብ ለደም ካንሰር፣ ለጭንቅላት እጢና  ለከፍተኛ ጭንቀት በመዳረጋቸው በተወለዱ...”

ይሄስ ማርያምን ደስ አይልም ፤ እባክዎ የመጨረሻውን ምዕራፍ ያሳምሩት፡፡ ህመም እስክንድር ነጋን በማሰር፣ ብራሰልስ በመመላለስ አይድንም፡፡ ንስሐ ይፈልጋል፤ መመለስ ይፈልጋል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መታረቅ፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር መታረቅ፣ ከአዲሱ ትውልድ ጋር መታረቅ ይፈልጋል፡፡ የሚያድግ ልጅ አይጥላኽ አይደል የሚል የኢትዮጵያ ሰው፡፡

No comments:

Post a Comment