Monday, July 9, 2012

Ethiopia፤ የግል ፕሬሱ ለአቅመ አማራጭነት ብቁ ነውን?



ጠቅላላ ሁኔታ
በኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቻ ያለ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የክልል ቴሌቪዥኖችም ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ይዞታ ስር ናቸው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመንግስት ልሳን ወደመሆኑ አመዝነዋል፡፡ ለግል የተሰጡ  በጣት የሚቆጠሩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ቢኖሩም በኤፍ.ኤም. የተወሰኑ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጪ ያለው ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ንብረትነቱ ጥቂት የገዢው ፓርቲ አባላት በመሆኑ ለገዢው ፓርቲ የመወገን አዝማሚያ አለው፡፡ ከዚህ እውነታ በመነሳት ለማንም በማይወግኑ የግል ይዞታዎች ውስጥ የሚገኘው ነፃ ፕሬሱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ጽሁፍ ‹ነፃ ፕሬሱ ምን ያህል አማራጭ ሚዲያ መሆን ይችላል?› ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት የተለያዩ መስፈሪያዎችን በመጠቀም ለመመለስ ይሞክራል፡፡

ከየካቲት 2001 እስከ ህዳር 2004 ድረስ 224 ያክል የሕትመቶች ውጤቶችን ለማዘጋጀት 211 ድርጅቶች እንደተመዘገቡ የብሮድካስት ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 137ቱ መጽሔት እና ቀሪዎቹ 87ቱ ጋዜጦች ናቸው፡፡ ከአንድ ክልል በላይ ከሚሰራጩት ሕትመቶች ውስጥ 75 ያህሉ ‹የተቋረጡ/የተሰረዙ›› መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ በገበያ ላይ ከሚውሉት የግል ሕትመቶች መካከል ሳምንታዊዎቹ ሃያ አይሞሉም፡፡ (በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ፡- ሪፖርተር፣ The Reporter፣ አዲስ አድማስ፣ ሰንደቅ፣ ኢትዮ ቻናል፣ ነጋድራስ፣ መሰናዘሪያ፣ ፍትሕ፣ ፍኖተ ነፃነት፣ የኛፕሬስ፣ The Sub Saharan Informer፣ Fortune፣ Capital እና ፕሬስ ዳይጀስት (ሁሉም ሳምንታዊ)፤ ከመጽሔቶች፡- ሙሐዝ (ወርሃዊ)፣ አዲስጉዳይ (ሳምንታዊ) እና አዲስ ታይምስ (ወርሃዊ) - በኢኮኖሚ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑ ሕትመቶች ናቸው፡፡)

በእንግሊዝኛ የሚታተመውና ንግድና ማስታወቂያ ላይ አተኩሮ የሚሰራው፣ ብቸኛው ዕለታዊ የግል ጋዜጣ The Daily Monitor ይሁን እንጂ ዕለታዊ ስርጭቱ 2000 አይሞላም፡፡ የአገሪቱ ኦፊሴላዊ ቋንቋ በሆነው አማርኛ ቋንቋም ሆነ በሌሎች የክልል ቋንቋዎች የሚታተም አንድም ዕለታዊ፣ የግል ጋዜጣ በአገሪቱ የለም፡፡

የሕትመት ውጤቶቹን ስርጭት በተመለከተ በሚያዝያ ወር፤ 2004 በወጣው መረጃ መሰረት ከፍተኛ ስርጭት ያስመዘገበው ፍትሕ ጋዜጣ ሲሆን ሳምንታዊ አማካዩ 21,750 ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው አዲስ አድማስ በበኩሉ 12,000 ቅጂዎች አማካይ ስርጭት ሲያስመዘግብ ፕሬስ ዳይጀስት እና መሰናዘሪያ የተባሉት ጋዜጦች 230 እና 960 ዝቅተኛ አማካኝ ቅጂዎችን አሳትመው አሰራጭተዋል፡፡ ከመጽሄቶች ደግሞ አዲስጉዳይ በ20,000 ቅጂ ከፍተኛ ስርጭት አግኝቷል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ሎሚ መጽሔት 12,000 ቅጂ በማሰራጨት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህንን መረጃ ያገኝነው ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ሲሆን ትክክልኝነቱን ማረጋገጥ አንችልም:: ምክንያቱም አሳታሚዎቹ የማይስማሙባቸው ቁጥሮች እንዳሉ ሁሉ፣ በመረጃው ላይ የአማርኛውን የእንግሊዝኛ መጽሔት እስከማለት የተደበላለቀ ነገር አለ፡፡ አለመታደል ሆኖ እንጂ እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ነጻ የሆኑ እንደ ኒልሰን ሬትንግ ያሉ ሳምንታዊ የሚዲያ ውጤቶችን ተነባቢነትን (Readership) እና ስርጭትን (Circualation) የሚለኩ ኩባንያዎች አሉ:: በርግጥ የሚዲያው ሕልውና በሚያጠራጥርበት ሁኔታ፣ አንባቢ የሚቆጥር ነፃ ኩባንያ ማቋቆም ይከብዳል፡፡
ጋዜጦች (ከሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚው እና ሕግ አስፈጻሚው ቀጥሎ) 4ተኛው መንግስት የሚል ቅጽል የተሰጣቸው ቢሆንም ይሄ ደረጃ ግን በኢትዮጵያ የግል መገናኛ ብዙሐን ዘርፍ ገና እንዳልተደረሰበት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የግል ፕሬሱ (የገበያ/commercial ወይም የሐሳብ/thought) ተጽዕኖ የሌለበት፣ ዜና እና አስተያየትን የለየ፣ ሕፀፅ ሐታች (critical analysis) ጠንካራ ተቋም እንዳልወጣው ያለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ውጤቶች ይዘክራሉ፡፡ ሃሌሉያ ሉሌ የተባለ በኢትዮጵያ የግል/ነጻ ሚዲያ ላይ የማስተርስ ዲግሪ ማሟያ ምርምሩን ያካሄደ ወጣት ተማራማሪ ይህን በማስመልከት “the private press has neither been a vital information channel for the general public nor has it had a pivotal function as a watchdog of government performance” (‹‹የግል ፕሬሱ አንድም ለብዙሐኑ ዐቢይ የመረጃ ምንጭ አልሆነም አሊያም ደግሞ የመንግስትን ብቃት ታዛቢ ማንፀሪያ ችካል ማኖር አልቻለም፡፡››) ብሏል፡፡ ጥያቄው ‹‹ለምን?›› የሚለው ነው፡፡

የግል ፕሬሱ ጥንካሬ

ምንም እንኳ የግል/ነጻ ሚዲያው የተቃውሞ ፖለቲካን ይደግፋል የመንግስትን ስኬታማነት የመዘገብ አንጀት የለውም የሚል ትችት ከተለያዩ ወገኖች ቢቀርብበትም እንደ ተቋም ከተቋቋመበት ግዜ አንስቶ በበርካታ ረዶች ሊያልፍ ተገዷል:: ለአብነት ጦሰኛውን ምርጫ 97 ተከተሎ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ተዘግተዋል:: ጋዜጠኞቻቸውም ለእስር እና ለስደት ተዳርገዋል:: ከዚህ ያመለጡትም ቢሆኑ በበርካታ ሀገራት እንዲቀር በተደረገው የፕሬስ የስም ማጥፋት ወንጀል (Criminal Defamation) ተጠርጥረው ክሱን ለመከላከል ወደ ፍርድ ቤት ይመላለሳሉ:: ከዚህም በላይ ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ የመጣው የህትመት ዋጋ ተቋቁመው አማራጭ የመረጃ ምንጭ ለመሆን የሚሞክሩት መፍጨርጨር በራሱ ሊደነቅ ይገባዋል::


የግል ፕሬሱ ድክመቶች

የግል ፕሬሱ ምርጫ 97 ተከትሎ በደረሰበት የማዋከብ እና ሕልውናን አደጋ ላይ እስከሚጥል ሁኔታ ድረስ የተወዳዳሪነቱን አቅም ለማሽመድመድ የሚዳርጉ ፈተናዎች ደርሰውበታል፡፡ የተረጋገጠ የመረጃ ምንጭ (verification) እጥረት ሞቅሞቅ የማድረግ (sensationalism) አባዜ፣ ፅንፈኝነት (extremism) እና ቀጣይነት/ዘላቂነት(sustainability) የለውም ለማለት በሚያስደፍር ይዞታ ላይ ነው፡፡
በተለይም የፕሬሶች ዘላቂነት ጉዳይ አንገብጋቢ ወደመሆኑ እየተሸጋገረ ነው፡፡ ቀደምት የተባሉት ጋዜጦች ቢዘጉም፣ ተሳካላቸው የሚባሉት እነሪፖርተር፣ አዲስአድማስ እና ፎርቹን ጋዜጦች የመጀመሪያ ዓመቶቻቸው ላይ የነበራቸውን የእድገት ፍጥነት ባለበት አቁመው፣ ወይም እያቆለቆሉ በማዝገም ላይ ናቸው፡፡ ሪፖርተር ዕለታዊ ጋዜጣውን ማሳተም ይጀምራል ተብሎ ሲጠበቅ የእንግሊዝኛ እትሙን ሳምንታዊነት እንኳን በኪሳራ ለመደጎም ተገድዷል፡፡ አዲስ አድማስ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ አሳትማለሁ ብሎ በሰፊው ካስተዋወቀ በኋላ ትቶታል፤ የአማርኛውም ጋዜጣ ቢሆን ከበፊት የስርጭት ብዛቱ በከፍተኛ ሁኔታ ወርዷል፡፡ በተቋማዊ አደረጃጀቱ የተሻለ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው አዲስ ነገር ጋዜጣም ከሁለት ዓመታት በላይ መጓዝ አልቻለም፡፡ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣም ሲዘጋም 17 ሰራተኞቹን ሜዳ ላይ ጥሎ ነው፡:
በሌላ በኩል የግል ፕሬሱን እየተፈታተነ የሚገኘው ውስጣዊ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ አዎንተኝነት (Confirmest) ላይ ማተኮር ቀዳሚ ተጠቃሽ ችግር ነው፡፡ ይህ  ከምርጫ 97 በኋላ በይዘታቸው ለስላሳ የሆኑ ወይም የመንግስትን ቀልብ በማይስቡ ስፖርትና ፋሽን ዙሪያ፣ በተለይም ደግሞ በቴዲ አፍሮ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሚያጠነጥኑ ወሬዎችን (የቴዲ አፍሮ አባዜ ወይም The Teddy Afro Mania ብንለው እንመርጣለን)  ጉዳዮች እያሳደዱ የሚያወጡ መጽሔቶች መበራከት፡፡ ከዚህ አለፈ ሲባልም ደግሞ ከስንት አንዴ በሚከሰት ጉዳይ ላይ (ለምሳሌ አንድ ጠንቋይ በወንጀል ፍርድ ቤት ሲቀርብ የሰውዬውን ስም የሚያስነሳ ማንኛውንም ታሪክ እያግበሰበሱ ማተም፣ አንዲት ሴት ጾታዊ ጥቃት ሲደርስባት ከጉዳዩ’ጋ ግንኙነት የሌላቸውንና ከተአማኒነትም አንፃር ምንም ዓይነት ተጨባጭነት የሌላቸውን የፍቅር ግንኙነቷን የሚመለከቱ አሉባልታዎችን ሳይቀር እያሳደዱ ማተም) ለአንባቢው በማያገባው ነገር ተጠምዶ፣ በሚመለከተው አገራዊ ጉዳዮች ላይ  ጥልቅ መረጃ ሳያገኝ እንዲቀር ምክንያት ሆኗል፡፡
 
ሚዲያዎቹ በዚህ ረገድ አንድን ግለሰብ ወይም ሁኔታ ሲያወድሱም ሆነ ሲያጠለሹ በፍፁማዊ መንገድ እንደሆነ ከመታማት አልተረፉም፡፡ ሌላው ቀርቶ፤ ጋዜጦቹና መጽሔቶቹ በቋንቋ ጠቃቀም ገጽ መሰናዶ (layout design) እንኳን ሳይቀር የማንበብ ፍላጎትን ለመሳብ የማይሞክሩ ከመሆናቸውም ባሻገር ብቸኛ ትኩረታቸውን እና ስልታቸውን በማስታወቂያ ገንዘብ ማጋበስ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸው እና ስለማሕበራዊ አበርክቷቸው (social contribution) የሚጨነቁ አለመምሰላቸው፣ በተለይም መጽሔቶቹ አብዛኛው ይዘታቸው ከኢንተርኔት የተገለበጠ መሆኑ ለሕትመት ሚዲያው ወጥ አስተዋፅዖ ጉድለት ራሱን የቻለ ሚና አለው፡፡  

የግል ፕሬሱ ተግዳሮቶች

የግል ፕሬሱ ካለፈው ልምድ ያዳበረው ድባብ እና ሌሎች ውስጣዊ የኢኮኖሚ እና የአስተዳደር ብቃት ማነስ ከሚጥልበት ችግር በተጨማሪ በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነውበታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል፡-
  • የባለሙያ እጥረት፤ በጋዜጠኝነት ሙያ የተመረቁ ወይም ለሙያው ፍቅር ያላቸው ጋዜጠኞች በሙያው ከመሰማራት ይልቅ ወደ ዝብ ግንኙነት መሰማራተቸውና፣ ከሕትመት ሽያጩ ለሚገኘው ትርፍ (ወይም በጽሁፉ ስለሚገኘው ጊዜያዊ ክፍያ) ብቻ ሲሉ የሚሰሩ ጸሐፊዎች መበራከት፣
  • የሽብርተኝነት ክሶች፤ በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ባለው የሽብረተኝነት ክስ ጋር በተያያዘ ወደ ሙያው የሚገቡ ወጣቶች የፍርሃት ቆፈን የሚጻፍ እና የማይጻፉ ጉዳዮችን እንዲለዩ ማድረጉ በሌላ ቋንቋ የራስን ጽሁፍ በራስ ቅድመ ምርመራ (self-censorship) ውስጥ ማሳለፈ መበራከቱ
  • ት ዋጋ መናር ከ5 መታት በፊት አንድ ባለ 16 ገጽ ሳምንታዊ ጋዜጣ ለማተም በአማካይ 90 ሳንቲም ብቻ ያስወጣ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ተመሳሳይ ገጽ ያለው ጋዜጣ ለማተም ከ2.90 ብር በላይ እንደሚጠይቅ ያደረገነው ምርምር ያሳያል
  • ሙያዊ ስነምግባር ማነስ፤ ማስታወቂያ ልስጥህና ዜና ስራልኝ ለሚሉ ማባበያዎች መንበርከክ እና ዜና መሰል ማስታወቂያዎች (advertotials) መስራት:: ለምሳሌ ‹አዲስ መኪና የሚገጣጠም ፋብሪካ መከፈቱን እና የመገጣጠሚያው መከፈት ለአገሪቱ ትልቅ ሚና እንዳለው የሚያስተዋውቅ ዜና ከሰሩ በኋላ፣ ዜናውን ተከትለው በሚወጡ ተከታታይ እትሞች ላይ የመገጣጠሚያውን ኩባንያ ማስታወቂያ ማውጣት› የሚመስሉ ተግባራት መበራከት እና
  • የፕሬስ  እና የረ ሽብር ሕጉ፤ የፕሬስ ሕጉ እና የፀረ ሽብርተኝነት ሕግጋት በጋዜጠኞች ደሕንነት እና በስራቸውም ላይ ክፉ ጥላውን አጥልቷል፡፡ የስም ማጥፋት፣ የዜና ምንጭን የመጥቀስ አስፈላጊነት፣ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ የሚናገሩትን መዘገብ እና የመሳሰሉትን በሕጉ መሰረት ለመጻፍ ለሚፈልጉ፣ የመንግስትን እርምጃዎች ከማወደስ በቀር ለመተቸት ወይም ስህተቶችን ለማጋለጥ የሚያስችል ምንም መፈናፈኛ መንገድ አልቀረላቸውም፡፡

አማራጭ መፍትሄዎች
  • የዜጎች ጋዜጠኝነት (Citizen Journalism) የአዲሱ ዘመን ቴክኖሎጂ ካመጣለን ትሩፋቶች ውስጥ  አንዱ በሪክ ነጋሪዎች(Story Tellersጋዜጠኞች ግለሰቦች) እና ተራ ግለሰቦች መሀከል ያለውን ሰፊ መስመር ማጥበቡ ነው:: ይህንንም በመጠቀም ዜጎች ያዩትን የሰሙትን እና አስተያያቶቻቸውን ፌስቡክን ዩ ቲዩብንትዊተርን  ብሎጎችን እና ሌሎችንም የዜጎች ጋዜጠኝነት መደበ አለፎችን (Citizen Journalism platforms) በመጠቀም ዜጎች ከፍተኛ ተዳራሽነት ባለው የተንቀሳቃሽ ስልክ አማካይነት እንዲናገሩ መፍቀድማበረታት እና ምቹ ስርዓት መፍጠር ችግሩን ለመቅረፍ አሌ የማይባል አስተዋፅዖ ያበረክታል፣
  • ነፃ ጋዜጠኞችን መፍጠር፤ ጋዜጠኞች ከስጋት ነፃ የሚሆኑበት ስርዓት ሊዘረጋላቸው ይገባል፡፡ ይህንን ከግብ የሚያደርሱ፣ ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገቱ፣ ነፃ የጋዜጠኞች እና የጋዜጦች ማሕበራት መመስረት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ረገድ ነፃ ሊባል የሚችል የጋዜጠኞች ማሕበር ተዘርግቷል ማለት ባይቻልም፣ አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማሕበር (ኢፕአማ) ላይ እንደአዲስነቱ ተስፋ ጣልት ይችላል፣
  • የፕሬስ አሳታሚዎች ተቋማዊ አደረጃጀትን ማጠናከር፤ ጋዜጠኞች ሲሰደዱ ወይም ሲታሰሩ የሚዘጉ ወይም የሚበተኑ በጥቂት ጋዜጠኞች ላይ ብቻ ጥገኛ/ተመርኳዥ የሆኑ ተቋማትን ወደ ራስመር ተቋምነት ማሳደግ፣ በአክስዮን የሚመሩ ተቋማትን ማቋቋም፣ ጋዜጦች ከመንግስት የማተሚያ ቤቶች እንዲወጡ የአሳታሚዎች ማተሚያ ቤት ማቋቋም እና ወዘተ. መፍትሄዎች ናቸው፡፡

መደምደምያ
የግል ፕሬሱን በደመስማሳው ለማየት እንደሞከርነው በብዙ መልኩ፣ በተለይም ‹‹በገዢው ፓርቲ ልሳንነት›› እያገለገሉ ያሉትን የመንግስት ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ እና ጋዜጦችን በስርጭት አድማስም ሆነ በይዘት ለመቀናቀን አሊያም ተመጣጣኝ የሆነ ሚዛን ለመድፋት የሚያስችል አቅም አላዳበረም፡፡ የአቅም እጥረቱ ከባለሙያነት (professionalism)፣ ተቋማዊ አደረጃጀት፣ ከፋይናንስ አንፃር ብቻ የሚመነጭ ሳይሆን ሚዲያው በማይቆጣጠራቸው አገር አቀፍ ስርዓታዊ እንከኖች እና አዋጆች ሳቢያም የተወለደ ነው፡፡

መንግስትም በበኩሉ፣ ከሚያወጣቸው አዋጆች፣ ከአገዳቸው ጋዜጦች እና በጋዜጠኞች ላይ ከመሰረታቸው ክሶች በመነሳት የፕሬሶቹን አማራጭ ድምጽነት የፈለገው እንደማይመስል መናገር ይቻላል፡፡ ምናልባትም ይሄ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የአውራ ፓርቲ መርሕ’ጋ የተወዳጀ አካሔድ ሊሆን ይችላል፡፡ በማንኛውም አካሔድ ግን ነፃ ፕሬሶች የአውራ ፓርቲውን መስመር በማስተካከልም ቢሆን የሚኖራቸው ሚና የማይታበል ነው፡፡

በተቃራኒው መንግስት በ21 ዓመት ጉዞው ለነፃ ሚዲያ የሚመች ስርዓት ዘርግቻለሁ እያለ ይከራከራል፡፡ የግል ፕሬሱ ግን አራተኛ መንግስት በመሆን ደካማ ስርዓቶችን ማውገዝ፣ ዐቢይ ማሕበራዊ ጉዳዮችን ለውይይት ማብቃት (agenda setting) እና ተጠያቂነትን በቀዳሚነት መምራት አልቻለም፡፡ ለዚህ አቅም አለመዳበር እና የወደፊት ዕጣ ፈንታው መንግስትም ሆነ ሌሎች የግል ፕሬሱ ዋነኛ ተጫዋቾች/stakeholders (አሳታሚዎች፣ ጋዜጠኞች…) ተጠያቂዎች/ኃላፊዎች ናቸው፡፡

2 comments:

  1. የእውነት በጣም አሪፍ ዳሰሳ ነው።የተገኘውን መንገድ ሁሉ በመጠቀም ህብረተሰቡ ለመረጃ ባይተዋር የማይሆንበትን ሆኔታ መፍጠር ይገባል።የመገናኛ አውታሮች ለህብረተሰብ የንቃተ ህሊና እድገት ቀላል የማይባል አስተዋጾ አላቸውና።

    ReplyDelete
  2. …እደጉ ተመንደጉ፤ ግራ ቀኝ እያያችሁ መንገድ ተሻገሩ፤ ዳር ዳሩን ሂዱ፤ የትራፊክ መብራት አክብሩ፤ ከግንቦት 7 ዓለም ያውጣችሁ፤ ከዲያስፖራ የፖለቲካ ሲንድረም ይሰውራችሁ…http://www.naodlive.com/2012/07/blog-post_10.html

    ReplyDelete