Friday, July 20, 2012

መለስ ወደ ውጭ - መለስ ከውጭ


መጋቢት 25/1982 ዓ.ም ዋሽንግተን ዲሲ 14ኛው መንገድ ቦታውም የህወሀት ፅ/ቤት፡፡ አንድ ያለማቆም ሲጋራ የሚያጨሱ በፅ/ቤቱ በባዶ እግራቸው ዘና ብለው ቁጭ ያሉ፣ እንግሊዘኛቸው የሚያምር በኢትዮጵያዊ የንግግር ዘይቤ የተካኑ ወጣ  ከቀድሞው የCIA ኤጀንት እንዲሁም አፋቃሬ ኢትዮጵያዊው (Ethiopianist) ፖል ሄንዝ ጋር ለውይይት ቁጭ ብለዋል፡፡ በንግግራቸው መጀመሪያም ወጣ ፖል ሄንዝን እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፡

‹‹አንተ የፃፍካቸውን ብዙ ነገሮች አንብቢያለሁ በሁሉም ነገሮችህ እስማማለሁ ነገር ግን ለምን ማራክሲስቶች እያልክ ትጠራናለህ?››

ፖል ሄንዝም፡ 
 ‹‹ምክንያቱም እናንተ እራሳችሁን ማርክሲስቶች ነን እያላችሁ ስለምትጠሩ ነው፡፡ አልባኒያን እንደ ሞዴል አድርገን የተቀበልን ነን ትላላችሁ፡፡ ለስታሊንም ተለየ ፍቅር እንዳላችሁ ሪፖርቶች ያሳያሉ‹‹ ይሏቸዋል፡፡

 ወጣ ቀበል አድርገው: ‹‹እኛ ማርክሲስት-ሌኒኒስት እንቅስቃሴዎች አይደለንም፣ በትግራይም ማርክሲዝም እና ሌኒኒዝምን ተግባራዊ አናደርግም፡፡ አዎ አንዳንድ አባላት ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊሆኑ ይችላሉ እኔም በተማሪነት ዘመኔ ነበርኩ፣ አሁን ግን አለም ላይ ምን እየተካሄደ እንዳለ እናውቃለን፣ የውጭ ርዕዮተ አለምም ለኛ መፍትሄ ይሆናል ብለን አናምንም፣ የራሳችን ባህል እና ወግ የጠበቀ ስርዓት መፍትሄ ነው ብለን እናምናለን›› በማለት ተኮት ተው ያደጉበት ማርክሲዝም በካፒታሊዝሙ አለም መሪ ዋና ከተማ ቀበሩት::


የ ያኔው ወጣት  የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው::
ታዳጊው መለስ

ካርል ማርክስ 'የግል ሀብት የህብረተሰብ ችግር ነው፣ ሀብታም ደግሞ የህብረተሰቡ ሳንካ ነው' ማለቱን እጅግ በጣም ትክክለኛ ሀሳብ ነው ብሏል ያ ትውልድ ፡፡ የዊንጌቱ መለስም ዩንቨርስቲ ሲገቡ ይሄን ሀሳብ በልቦናቸው አዋሉት፡፡ የሀብታሞች መንግስት ነው ያሉትን ንጉሳዊ ስርዓትም ከጓዶቻቸው ጋር በጩኸት አፈረሱት፡፡ የንጉሱ ስርዓት መገርሰስ ግን ለመለስ በቂ አልበረም ይልቅስ ወደ ስልጣን የቀረበው ወታደራዊ መንግስት የትግራይን ህዝብ ጥያቄ አልመለሰም እንዲያውም የትግራይ ህዝብ  ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ተገንጥሎ የራሱን ሀገር መመስረት አለበት፣ ሌኒን እና ስታሊም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለጭቁኑ ህዝብ ዋነኛ የነፃነት መሳሪያ ነው ይላሉ ብለው በማመን ተኻህትን ተቀላቀሉ በተኻህት የመጀመሪያ ማንፌስቶም ‘ነጻ ትግራይን’ ለመመስረት ከጓዶቻቸው ጋር ተስማሙ የማንፌስቶውንም መዝጊ‹‹ኢም ሪያሊዝም ይንኮታኮታል›› በማለት የምዕራቡን ካፒታሊስት ስርዓት አጣጣሉ፡፡ የቀድሞው  ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ (ተሓህት) የበኋላው ህወሀት በትግል አስር አመታትን ካሳለፈ በኋላ አቶ መለስ ወደ ስልጣን ማማ የሚያወጣቸውን አንድ መንገድ ቀየሱ በህወሀት ውስጥ አንድ ተጨማሪ ሊግን ማቋቋም ሊጉንም ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ኦፍ ትግራይ (ማሌሊት) አሉት ሊቀመንበርነቱንም ተቆናጠጡ፡፡
መለስ በትግል ወቅት

እንግዲህ አቶ መለስ ከተማሪነት ጊዜያቸው ጀምሮ ደርግ እስከ ወደቀበት ጊዜ ድረስ ለአለማቀፉ ህብረተሰብ የነበራቸው አስተሳሰብ በካቲታሊስት-ሶሻሊስት ንጽርኦተ አለም (World Outlook) አስተሳሰብ የተቃኘ ነበር፡፡ 

የአለም ጭቁን ህዝቦች ነፃ የሚወጡት የግል ሀብት ሲጠፋ (On the abolishing of Private property) ነው የብሄሮችን ነፃነት በቡድን መብት አስተሳሰብ አማካይነት መመለስ አለበት፣ ይሄም በሩሲያ መሪነት የምስራቁ አለም ርዕዮት ስለሆነ ለምስራቁ ጎራ መልካም አመለካከት ነበራቸው:: በመጨረሻም የአልባንያን ሶሻሊዝምም እንደ ትክክለኛ ሞዴል በመውሰድ የሀገሪቱ አዳኝ አድርገው ተቀበሉ የያኔው መለስ፡፡

ከቀብር መልስ  

ከላይ በመግቢያችን አንደጠቀስነው አቶ  መለስ በዋሽንግተን ቆታቸው ማርክሲስትነታቸውን ቀብረዋል፡፡መለስ ማርክሲስትነታቸውን ከቀበሩ በኋላ ደርግ ወደቀ፣ የሀገሪቱን አመራርነትም ተረከቡ፣ ፍቅራቸውንም ከምእራቡ አለም ጋር አደረጉ፡፡ ምእራቡ አለም ሀገሪቱን ከህዝብ ብዛቷ አንፃር እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ ማዕከል መሆኗን ከአካባቢው መረጋጋት ጋር ብሎም ለመካከለኛው ምስራቅ የወደብ መቆጣጠሪያ (Light House) አድርጎ ማሰቡ ግንኙነቱን ከኢትዮጵያ ጋር ለማጠናከሩ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኝው ችሏል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የፀረ-ሽብር ትግሉ (War on Terror) እና የኢትዮጵያ የሱማሊያ ጎረቤት መሆን ኢትዮጵያን እንደ ጠቃሚ አጋር ለማየት አስቻለው አለማቀፉን ህብረተሰብ፡፡

አቶ መለስም ይሄን የአለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም የምዕራቡን ፍላጎት የተረዱ ይመስላሉ፡፡ ለዛም ነው ‹‹ሁሌም ከእናንተ ጋር ነን›› ብለው ምዕራቡን በፍቅር የከተቡት፡፡ በዛ ላይ የንግግር ተሰጥኦአቸው (Oratory) ታክሎበት የምእራቡን አይን እንዲያማልሉ አስችሏቸዋል፡፡ 
የ G-20 ስብሰባ ሶል ፣ ደቡብ ኮሪያ

 
የቀድሞው የእንግሊዝ  ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በአንድ ወቅት የአፍሪካ ተራማጅ መሪዎች (The New Progressive Leaders of Africa) ዝርዝራቸው ውስጥ መለስን ከቀዳሚዎቹ ስፍራ አሰልፈዋቸዋል፡፡

በዚህ የጫጉላ ወቅት መለስ ሁሌ ከምእራቡ አለም ጋር የሚነ ታርካቸው ጉዳይ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ከአለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት (Bretton Woods Institution) የሚቀርብላቸው ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ያለአግባብ ይታሰራሉ፣ ዲሞክራሲንም አስረዋል፣ ህግ ስርዓት ፈረሰ ወ.ዘ.ተ ይሏቸዋል የሰብዓዊ ተቋማቱ በሌላ በኩል ደግሞ አለም አቀፍ ንዘብ ተቋማቱ የፋይናንስ ተቋማትን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት አድርጉ፣ ሞኖፖሊዮችን ለቀቅ አድርጉ፣ የኢኮኖሚውን አወቀቀር አስተካክሉ (Structural Adjustment) ወ.ዘ.ተ ይሏቸዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ የመለስ መልስ ለዘብተኛ ነበር፡፡ ዲሞክራሲን በቻልነው መጠን እያሳደግነው ነው፣ ህገመንግስቱን እያስፈፀምነው ነው በርግጥ በአፈፃፀም ደረጃ አንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች ይከሰታሉ እነሱም በቀጣይ የማስፈፀም አቅማችን ስናዳብር የሚስተካከሉ ናቸው እያሉ የሰብኣዊ ተቋማቱን ቁጣ ለማብረድ ይጥሩ ነበር እንዲሁም ጊዜው ገና ነው፣ ልማታችንን ተደራሽ ካደረግን በኋላ ለግል ባለሀብቶች ኢኮኖሚው ሙሉ ለሙሉ ክፍት ይሆናል እያሉ የምዕራቡ አለም በተስፋ ፈገግ ያስብሉት ነበር መለስ በዚህ 14 ዓመት በዘለቀ የምዕራቡ አለም ፍቅራቸው ዘመን፡፡

መለስ እንደገና፣ ከቀለም አብዮት እሰከ ኒዮ ሊበራሊዝም

ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም አዲስ አበባ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቢሮ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ወንበሮች በሙሉ ጭንቀት በወረራቸው የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሀላፊዎች እና ሰራተኞች ተሞልቷል፡፡ ሁሉም በያለበት አዲስ ስለተረቀቀው የማህበራት እና ሲቪል ሶሳይቲ አዋጅ መንፈስ ላይ ይወያያል፡፡ የውይይቱ ዋነኛ ማጠንጠኛዎችም ሁለት አንቀፆች ናቸው፡፡ ‹‹ከ10 በመቶ በላይ አመታዊ ባጀቱን ከውጭ ለጋሽ የሚቀበል ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በፓለቲካዊ አድቮኬሲ ስራ እንዲሁም ትኩስ (Sensitive) የሆኑ የማህበረሰቡ አካላት ጋር የተያያዘ ስራ መስራት አይችልም›› የሚለው እና ‹ሁሉም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከበጀታቸው ከ30 በመቶ ያልበለጠውን ገንዘብ ብቻ ነው  ለስራ ማስኬጃ ማዋል የሚችሉት›› የሚሉት አንቀፆች የታዳሚውን ቀልብ ስበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም የእነዚህን ሁለት ጉዳዮች ምንነት ለማስረዳት ነው በቦታው የተገኙት፡፡ ንግግራቸውንም እንዲህ ሲሉ በጠነከሩ ቃላት ጀመሩ፡

‹‹ገንዘብ ከውጭ፣ ሰው ከሀገር ውስጥ በመደባለቅ ኢትዮጵያዊ ሲቪል ሶሳይቲ መፍጠር አይቻልም፡፡ከጡጦ በሚንቆረቆር ገንዘብ ዲሞክራሲ ይኖራል ለማለት የማይቻል ነው፡፡ በዲሞክራሲ ተዋናይ ለመሆን የውጭ ገንዘብ ያስፈልጋል የሚለው አባባል አደገኛ ድንቁርና ወይም ስድብ ነው፡፡ በውጭ ገንዘብ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተንጦ ቅቤ አይወጣውም፡፡›› በማስከተልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደናግጦ የሚመለከታቸውን ታዳሚ እያማተሩ ‹‹በሞግዚት ዲሞክራቲክ መሆን አይቻልም፡፡በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ ሀገር ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር እና ሰብዓዊ መብት በጡጦ ሊጠባ አይቻልም፡፡ ጡጦ ካላስፈለገው ባለጡጦ አያስፈልገውም፡፡በውጭ ገንዘብ እና አይዲያ ላይ የተመሰረተ የዲሞክራሲ እድገት በእባብ አንቁላል ላይ የተመሰረተ ርቢ ማለት ነው፡፡የማይመለከታችሁ ቢላዋ ይዛችሁ እሰው አንገት አካባቢ እስካላሽከረከራችሁ ድረስ መስራት ትችላላችሁ፡፡ ቀይ መስመሯን ስትሻገሩ የጨዋታው ህግ ይቀየራል፡፡ በቢላዋ ጉዳይ ጥያቄ ወይም ኮምፕሮማይዝ የለም፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለዚህ ዛቻ መሰል ንግግር ያበቃቸው ምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አለማቀፋዊ ፍቅር እንደገና ምዕራቡን አለም እንደተፋታ ለማየት እንችላለን፡፡ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንደ አንድ የፓርቲ መሪ ግለሰብ ምርጫ 97ን ተምረንበታል ይላሉ፡፡ ከቀዳሚዎቹ የምርጫ 97 ትምህርቶች መካከል የሲቪል ሶሳይቲው ሚና መሆኑ ምርጫውን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የተከታተለ ሁሉ የሚስተው ጉዳይ አይደለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በፓርቲቸው እምነትም ሲቪል ሶሳይቲው ውጭ ሁነው በሚዘውሩት እና የራሳቸው የተለየ አጀንዳ ባላቸው ሀይሎች እየተደገፈ ተቃዋሚዎቹን በጭፍን ረድቷል ይሄ እርዳታም መንግስትን በምርጫ ከማስወገድ ባለፈም በህዝባዊ አመጽ  ወይም በተለምዶ ቀለም አብዮት ተብሎ በሚጠራው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንድ ወቅት 'የቅጠላ ቅጠል' አብዮት ብለው ያሾፉበት እና በምስራቅ አውሮፓ ተሞክሮ የታየውን አይነት ለውጥ እስከማካሄድ ድረስ ይዘልቃል ባይ ናቸው፡፡ ለዚህም ዋነኞቹ አንቀሳቃሾች አንዳንድ የምዕራብ ሀይላት ናቸው በማለት መለስ ስልጣን በመያዛቸው ዋዜማ የተጋቡትን የምዕራብ ፍቅር ተጣሉት፣ አኮረፉት፡፡

ይባስ ብሎ በዛው በመጋቢት 2000 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ፅሁፋቸውን የመጀመሪያ ድራፍት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ለውይይት አቀረቡ፡፡ የፅሁፋቸው ዋነኛ ማጠንጠኛም የምዕራቡን አለም ፖለቲካል-ኢኮኖሚ በማጣጣል ለአፍሪካ የሚበጃት ከምስራቁ ተሞክሮ መውሰድ ነው በማለት እነ ደቡብ ኮሪያን፣ ቻይናን እና ሲንጋፖርን እየጠቀሱ አዲስ ወዳጅ ፍለጋ ፊታቸውን ከምዕራቡ አለም መለስ አድርገው ወደ ምስራቁ ማማተር ያዙ፡፡ ማርክሲስቶች ኢምቴሪያሊዝም ይውደም ባሉበት ድምፀት መለስም ኒዮ ሊብራሊዝም ይውደም ማለትን አዘወተሩ፡፡

ግለሰቡ መለስ

መለስ አቋማቸውን ህዝቡ ላይ ካሰረፁ በኋላ በግላቸው ስብእናቸውን ለመገንባት መሯሯጣቸው አልቀረም፡፡ ለዚህም ዋነኛ ተጠቃሽ የሚሆነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካን ይወክላሉ፣ ልዕለ-ሰብነት አላቸው የሚለውን አመለካከት በአለማቀፉ ህብረተሰብ ውስጥ ሊተክሉ መቻላቸው ነው፡፡

ወደስልጣን እንደገቡ በርቀት ትምህርት ከእንግሊዙ ኦፕን ዩንቨርስቲ በቢዝነስ አዲሚንስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ ሲይዙ ዩንቨርስቲው የመለስን ውጤት ‹‹One of the best result in Open University’s History›› ሲል ነበር የገለፀው፡፡ በማስከተልም ከሮተርዳሙ ኢራስመስ ዩንቨርስቲ ሌላ ማስተርስ በኢኮኖሚክስ በመያዝ ስብዕናቸውን ያዳበሩ ሲሆን እንደ ጆሴፍ ስቲግሊትዝ እና ጀፍሪ ሳክስ ከመሳሰሉ ትልልቅ ስብእናዎች ጋር በመሻረክ እንዲሁም ፈጣን እና ቀልጣፍነታቸውን በመጠቀም ለአለማቀፉ ህብረተሰብ መለስ እንደ ታላቅ ምሁር ሁነው ቀርበዋል:: ለዚህም ትክክለኛ አመላካች የሚሆንልን የእንግሊዝ የአለምአቀፍ ልማት ሀላፊ የነበሩት ክሌር ሾርት በአንድ ወቅት ስለ መለስ ሲናገሩ፡ ‘the most intelligent politician I’ve met anywhere in the world’. በማለት ነበር፡፡ ይህ የመለስ ስብእና በተለይም በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ጎልቶ የሚንፀባረቅ ምስል ነው፡፡ ለዛም ይመስላል አፍሪካን በመወከል መለስ ቅድሚውያን የሚይዙት፡፡

የመለስ ካሮት እና ዱላ
<<Meles Zenawi is the cleverest and most engaging Prime Minister in Africa – at least when he talks to visiting outsiders. When he speaks to his fellow Ethiopians, he is severe and dogmatic. But he entertains western visitors with humor and irony, deploying a diffident, self-deprecating style which cleverly conceals an absolute determination to control his country and its destiny, free of outside interference.>>
ይህ ከላይ ተጠቀሰው ፅሁፍ የሮያል አፍሪካ ሶሳይቲ ሊቀመንበር የሆኑት ሪቻርድ ዳውደን መለስ ዜናዊ ኢትዩጵያን እንዴት እየመሯት ነው? (How Meles Zenawi Rules Ethiopia?) ያሉት ፅሁፋቻው መግቢያ ነው፡፡  

መለስ አለማቀፉን ህብረተሰብ ሲቀርቡ ተለሳልሰው ይቀርባሉ፣ቃል ይገባሉ፣ ጊዜ ስጡን ይላሉ ነገሩ ከረር ሲልባቸው ዱላቸውን ይመዙና እኛ ለማንም የውጭ ሀይል አንንበረከክም ብትፈልጉ በሊማሊሞ ማቋረጥ ትችላልችሁ እያሉ ሊያስፈራሩ ይሞክራሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ምርጫ 2002 ነው፡
መለስ ከይናው ፕሬዘደንት ሁጅን ታኦ ጋር በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም ላይ

‹‹ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ከአለም አቀፍ ዲሞክራሲ ተቋማት ቃል በቃል የተገለበጠ የምርጫ ስነምግባር ደንብ አለ በሱ ላይ እንፈራረም እና ምርጫውን በሰላም እናስኪደው›› አሉ በፓርቲያቸው አማካኝነት፡፡ ‹‹አይ ምህዳሩ እንዲህ በጠበበት ሁኔታ ስለ ስነምግባር ማውራት ከባድ ነው መጀመሪያ ምህዳሩን ለቀቅ ያድርጉት›› ሲባሉ አሻፈረኝ አሉና ምርጫ አካሄዱ ውጤቱንም አለማቀፉ ህብረተሰብ እንደማይቀበለው ባወቁ ጊዜ አለማቀፉን ህብረተሰብ በተለይም ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን የሚያወግዝ ሰልፍ በመላው ኢትየጵያ ጠሩ ‘NO, to TROJAN HORSE’ የሚል የእንግሊዘኛ መፈከር አሸክመውም ካሮቱን አልበላም ያለውን አለማቀፉ ህብረተሰብ በዱላ ዳሰስ አደረጉት፡፡

አለማቀፉ ህብረተሰብም በአካባቢው ካለው ሌሎች ፍላጉት አንፃር መለስን በድፍረት ተው ማለት አልፈለገም ከላይ ጠቀስናቸው ሪቻርድ ዳውደን አንድ የአሜሪካን ዲፕሎማትን ጠቅሰው ‹‹ይህ የሙባረክ አባዜ (Mubarak Syndrome) ነው›› ይላሉ ማለትም “We only talked to Mubarak about Egypt’s role in the region, never about what was happening inside Egypt. It’s the same with Ethiopia.” ፡፡

መለስ ለነገ

ከማርክሲዝም ወደ ካፒታሊዝም (በእርሳቸው ቋንቋ ወደ ነጭ ካፒታሊዝም) ከዛም ምንነቱን ያልለየለት 'የልማታዊ መንግስት' ርእዮተአለም አራማጅ ነኝ እያሉ ያሉት መለስ የሀገሪቱን የውጭ ፖሊሲዎች በግል ፍላጎታቸው ስር አድርገዋል ይሏቸዋል ተችዎቻቸው፡፡ ለምን እንዲህ አደረክ ሲባሉ የሚያኮርፉት መለስ የግል ወዳጆቻቸው የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሆኑ ነው ጥረታቸው እንጅ ሀገራዊ ጥቅምን(National Interest) ያገናዘበ አይደለምም ሌላው ትችት ነው፡፡ እንግዲህ መለስ ስልጣን አስረ ቡ እንበልና የመለስ የውጭ ግንኙነት ውርስ (Legacy) ምን ሊሆን ይችላል?