Wednesday, July 4, 2012

አባይን መልሱልኝ!

በሶልያና ሽመልስ

አባይ……. አባይ……..  አባይ…….. አባይ
የአገር አድባር  ያገር ኩራት ……..የአገር  ሲሳይ


ቲቸር ታደሰ ከማልረሳቸው  የአንደኛ ደረጃ መምህራን መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ታዲያ የስድስተኛ ክፍልን የህብረተሰብ ትምህርት ለየት የሚያደርገው የቲቸር ታደሰ ከክፍል ሥራ እና ከንባብ በተጨማሪ ይዘዋቸው ይመጡ የነበሩት ከክፍለ ጊዜው ጋር የተገናኙ ጨዋታዎች እና የጠቅላላ እውቀት ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ታሪክ ቀመስ ትረካዎችን ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሲያነቡልንም አስታውሳለሁ፡፡ (አዲስ ዘመንም የሚነበብ ታሪክ የሚጽፍበት ወቅት ነበረው ማለት ነው?) ታዲያ በአብዛኛዎቹ ክፍለ ጊዜዎች መጨረሻ ላይ ስለቀድሞ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ታሪክ እና ስለተያያዥ ጉዳዮች ሲያወሩ የአባይ ጥቅም ላይ አለመዋልን  በቁጭት ማንሳታቸው አይቀርም ነበር፡፡
ከሚሽነሪ ት/ቤቱ ጥብቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት  በመነሳት ምንም አይነት መንፈሳዊ ያልሆነ ሙዚቃ መዝፈን የሚያስቀጣ ቢሆንም ቲቸር ታደሰ ግን በኅብረተሰብ ትምህርት በሬድዮ  ክፍለ ጊዜ ማጠናቀቂያ ላይ በተደጋጋሚ የሚመጣውን፤
አባይ……. አባይ……..  አባይ…….. አባይ
የአገር አድባር ያገር ኩራት ……..የአገር  ሲሳይ

በጋራ እንድንዘምር ይፈቅዱልን ነበር፡፡ የኅብረተሰብ ትምህርት እና ልጅነት ሲነሳ አብሮኝ የሚከሰተው የአባይ ትዝታን የምጋራው እኔ ብቻ ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ ዓይነቱ የተለየ ቢሆንም  ሰለአባይ ስንማር  እና ሲነገረን  የኖርናቸውን ነገሮች በማስታወስ የአንደኛ ደረጃ የህብረተሰብ ትምህርቱ  እና የአባይ  ትውስታ የሚቀላቀልበት የኔ ቢጤ ወዳጅ መቼም አላጣም፡፡


የአሁኑ አባይ የማን  ነው?

"የታላቁ የህዳሴ ግድብ"  ግንባታ ከተጀመረ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን የምንጨርስበትን ጊዜ የማናውቅ/የናፈቅን/የጠረጠርን ይመስል የጀመርንበትን ቀን በትልቅ ድግስ እና ግርግር አሳልፈነው ነበር፡፡ ሰሞኑን ታዲያ አራት ኪሎ መንገድ ላይ የሚገኘው "የፓርቲያችን" ጽ/ቤት አቅራቢያ ሳልፍ ያየሁት ትልቅ ቢል ቦርድ /ፖስተር መነሻ ሆኖኝ ከዚህ በፊት ይሰማኝ የነበረውን የልጅነቴን አባይ የመነጠቅ ስሜት ወደ አደባባይ ለማምጣት መረጥኩ፡፡አባይን እንደ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ የምንቆጥረው ሰዎች መቼም ጥቂት የምንባል አይደለንም፡፡ ታዲያ በኢህአዴግ ጽ/ቤት ህንጻ ላይ የተሰቀለው ትልቅ ቢል ቦርድ የታላቁን የህዳሴ ግድብ እና አባይን ከጀርባው ያደርግና ከላዩ ላይ ትልቅ የፓርቲውን አርማ በብሔር ብሔረሰቦች ባንዲራ  አጅቦ የተለመደውን የግድቡን ግንባታ ቅስቀሳ የመሰለ መፈክር ያስቀምጣል፡፡ ይህ አባይን የፓርቲ የማድረግ አባዜ እነ ኢቴቪን እና ፋናን በመሳሰሉ የፓርቲ ልሳኖች ሲገለጽ ከርሞ አሁን ቢልቦርዱ ጠቅልሎ ስለገለጸልኝ  ነው፤ ‹አባይ የማን ነው?› የሚለውን ጥያቄ ያነሳሁት፡፡ እሺ! ኢህአዴግን ያልመረጠስ? የፓርቲ አባል ያልሆነስ? አባይ የእርሱ አይደለምን? የአባይን መገንባት ሲፈልጉ የኖሩት ኢህአዴግ እና ተቀጥጽላዎቹ ብቻ ናቸው? ይህ ህዝባዊ የጋራ መገለጫን ነጥቆ የፖለቲካ ጨዋታን ማድመቂያ ማድረግ የተለመደ የፓርቲው አካሄድ ቢሆንም (የባንዲራ ቀንን ያስታውሱዋል) የህዳሴው ግድብ ነገር ግን ከፓርቲ አመራሮች ጨዋታና የኢቲቪ ፕሮፖጋንዳ ባለፈ የእያንዳንዱ ካድሬ ንግግር ማሟሻ እና መለማመጃ ሆኖ ከራቀን ቆይቶዋል፡፡
በየትኛውም የሲቪል ሰርቪስ ስራ ውስጥ የቢሮክራሲው አንዱ አካል እየሆነ የመጣው ግድብ የእኛ ያልሆነ እና ለፓርቲው ብቻ የተሰጠ ይመስል በባለቤትነት የያዙት ካድሬዎች ብዛት ሳያንስ በየግርግዳው ላይ አባይን የሚያሞግሱ ፉከራዎችን (የማይገናኙ ጉዳዮች ማገናኛም ጭምር ሆኖ) ለማግኘት  አቅራቢያዎ የሚገኝ ወረዳ ጽ/ቤት ጎራ ማለት ይበቃል፡፡ ገፋ ሲልም ለግል ጉዳይዎ አገልግሎት ለማግኘት የሄዱበት የሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤት የህዝብ አገልጋይ ከአገልግሎቱ በላይ ስለግድቡ ለደቂቃ አለመቋረጥ  ሲጨነቅ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡

ከአገር ኩራትነት እና ግርማነት ቁልቁል ወርዶ የካድሬ ጉዳይ፣ የፖስተር ማድመቂያ፣ የንግግሮች መክፈቻ እና መዝጊያ ሲሆን “ኧረ ተው አባይ እኮ የእኛም ነው” የምንለው ለማን ነው?

ለሰከንዶች እንዳይቋረጥ…

ሰሞኑን የምንሰማቸው ካድሬያዊ ንግግሮች አቅጣጫ የሳቱት አባይን የእኛ ጉዳይ እንዳልሆነ በማስመሰላቸው ብቻ አይደለም፡፡ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ፍሬ ነገሮችን በመቀላቀል የግድቡ መገንባት ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ አድርገው ማቅረባቸውም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ የክ/ከተማ (ወረዳ)  ስራ አስፈጻሚ “የግድቡ ግንባታ ለደቂቃ እንዳይቋረጥ የእኛ ድርሻ ከፍተኛ ነው” የሚል ንግግር በስበሰባው ማጠቃለያ ላይ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ጉዳዩን የሚገርም የሚያደርገው በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ሰጪው እና በግድቡ ግንባታ መቋረጥ እና አለመቋረጥ  መካከል ጨርሶ ግንኙነት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን  የግድቡ መቋረጥ እንደ አንድ የሚያሰጋ እውነት ሆኖ መቅረቡም ጭምር ነው፡፡ “መቋረጥን ምን አመጣው?” ብለን ብንጠይቅ የግድቡን ተገንብቶ ማለቅ በውስጠ አዋቂ የመጠርጠር ስሜት እየተሰማን እና እያሳየን እንዳለን ያሳብቅብናል፡፡ይህ በቅጡ ያልተቃኘ ካድሬያዊ ፕሮፖጋንዳ እንዲባል የሚፈለገውን(መባል ያለበትን) መልእክት መሳቱ እኛን ከማሰልቸቱ እና ወደ ዳር ከመግፋቱ  ባሻገር ያለው ትልቁ ችግሩ ነው፡፡ እስቲ አሁን አባይ እንዳይቋረጥ ሥራህን በስርዓት መስራት አለብህ የሚል ኩርኩም የሚደርስበት  ሲቪል ሰርቫንት (የደሞዙ ነገር ሳያንስ) አባይን ቢያኮርፈው ይፈረድበታል፡፡

“እስቲ እንነጋገር፥ የደሞዙን ነገር…”
ታላቁ ሩጫ እንደቀድሞው ለዛው ቢሆን ኖሮ የሚዘፈንለት አንድ ነገር አባይና የደሞዛችን ነገር፣ አባይ እና የመዋጮው ነገር ይመስለኛል፡፡ የመንግስት ሠራተኛው ፍቃዱ ሳይጠየቅ ሌላው ሰው ደግሞ በሰበብ አስባቡ በተጽእኖ ስር ሆኖ የሚቆረጥበት ገንዘብ ሌላው አባይን ከእኛ የነጠቀ ጠላታችን ነው፡፡ አስተዋፅዖው እና መዋጮው  በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ቢሆን ኖሮ አንድ ሠራተኛ በፍቃዱ ወዶ  የሚያዋጣው  5 በመቶ የደሞዙ ድርሻ ተገዶ መቶ በመቶ ከሚያወጣው በተሻለ የጋራ የባለቤትነት ስሜት ይፈጥርለት ነበር፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው? በየወሩ የደሞዙ ዕለት ያለፍላጎቱ እና ያለ ነጻ ፍቃዱ የሚቀነስበትን ብር እያሰበ የሚያዋጣና ኑሮ የሚያንገዳግደው ደሞዝተኛ የአባይን ባለቤትነት በጥያቄ ማየቱ የሚገርም አይሆንም፡፡ በዚያ ላይ ደሞ የካድሬ አለቃ እና የኢቲቪ የጋራ ፕሮፖጋንዳ ሲጨመርበት የአባይን የጋራነት ለመርሳት በጣም ቅርብ ይሆናል፡፡

“አባይን የደፈረ…”

አሁንም የፈረደበት አባይ ከፓርቲው አርማ ጀርባ ከመሆን አንስቶ እስከ ሊቀመንበሩ ፎቶ ማድመቂያነት ድረስ አባይን የደፈረ  መሪ ቅጽል ይዞ አደባባይ ከከረመ ቆይቶዋል፡፡ አባይን የመገንባት ፕሮጀክት ጥሩ ሆኖ ሳለ ያላለቀውን ፕሮጄከት እውቅና በሙሉ ለአንደ ግለሰብ ሰጥቶ በየአደባባዩ ማናፈስ (እንዲናፈስ መፍቀድ እና ማበረታታት) ፓርቲ የሚታማበትን የአንድ ግለሰብ ግነት እና አምልኮ እንደተጨማሪ መገለጫ ተደርጎ ቢቆጠርበት ብዙ አያስገርምም፡፡ ይህ ሊቀመንበሩን እና የአባይ ግንባታን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ አድርጎ የማሳየት አባዜ ፓርቲውን እና ኢትዮጲያዊነቱን በሁለት ልብ ለይቶ ለሚይዝ ኢትዮጲያዊ አባይን የመራቅ እና የመነጠቅ ስሜት ቢፈጥርበት ለምን ሆነ ብሎ መፍረድ ከባድ ይሆናል፡፡ በፓርቲው ህዝባዊ  ህትመቶች ላይ የሊቀመንበሩን ፎቶ ላለማስቀመጥ የሚጠነቀቀው ኢሕአዴግ አባይን በ21 ዓመት መሪው ፎቶ ጀርባ እያስቀመጠ የጋራ አባያችንን ለግሉ ሲያደርግብን አቤት የሚባለው ለማን ነው?

“በኅብረተሰብ ክፍለጊዜ የዘመርኩለትን ኢትዮጵያዊውን አባይ መልሱልኝ!”

የእኔ አባይ ከሁሉም ሰው ጋር የምግባባበት የዘር ግንዳቸውን እና  የፖለቲካ አቋማቸውን ከማላውቃቸው  የልጅነት ጓደኞቼ ጋር የዘመርኩለት ነው፡፡ እባካችሁ ያንን አባይ መልሱልኝ!! የእኔ አባይ ባለመጠቀሜ የተቆጨሁበት አፈሩን ለምን አናስቀረውም? ብዬ ከጓደኞቼ ጋር በልጅነት አንደበት የተወያየሁበት ነው፡፡ እባካችሁ መልሱልኝ!! የእኔ አባይ የጋራ፣ የሁሉም የሆነው በቲቪ ሲመጣ በፏፏቴው የምደነቅበት አባይ ነው፡፡ እባካችሁ ኩራቴን መልሱልኝ!! የእኔ አባይ የማንም ፓርቲ ያልሆነ ጥቅም ላይ ለመዋል ኃላፊነት የሚሰማው፣ በፕሮፖጋንዳ ያልተለወሰ እውነተኛ ልማት ሲጠብቅ የነበረ ህዝባዊ ሃብት ነው፡፡ እባካችሁ መልሱልኝ!!  አባይን የአንድ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳይ፣ የአንድ ፓርቲ ልሳን መገለጫ፣ የአንድ ፓርቲ ኩራት አድርጋችሁ ለፊትለፊት ገጽታ ግንባታ ብቻ አትጠቀሙበት፡፡ የጋራ አባያችንን ወንዛችንን መልሱልን፡፡ ያኔ ሳናማርር አዋጥተን በጋራ እንገነባዋለን!! "እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" ነው ያለው ያ……ልማታዊ ጋዜጠኛ!!!!???

No comments:

Post a Comment