Wednesday, July 25, 2012

ማን ስልጣን ላይ ተወለደና?

በናትናኤል ፈለቀ



Murder at 1600 ዊስሊ ስናይፕስ (Wisely Snipes) የተሰኘ ጥቁር አሜሪካዊ የሚተውንበት ልብ አንጠልጣይ ፊልም መጠሪያ ነው - Murder at 1600፡፡ 1600 (Sixteen hundred) የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች መኖሪያ የሆነው ዋይት ሀውስን በር ይዞ የሚያልፈው መንገድ መጠሪያ ነው፡፡

ፊልሙ የሚያጠነጥነው ስናይፕስ ዋይት ሀውስ ውስጥ ተገድላ የተገኘች ሴትን ነፍሰ ገዳይ እና የአማሟት ሁኔታ ለማጣራት በሚያደርገው ውጣ ውረድ ላይ ነው፡፡ ነፍሰ ገዳዩን ለማግኘት ስናይፕስ በሚያደርገው ክትትል በግድያው የፕሬዝዳንቱ እጅ እንዳለበት የሚጠቁሙ የጥርጣሬ መረጃዎች ያገኛል፤ ይህ ያልተዋጠላቸው የፕሬዝዳንቱ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ስናይፕስን ደውለው ያስጠሩትና የዋሽንግተንን ማስታወሻ ሃውልት አሻግሮ የሚያሳየው ፓርክ ውስጥ የጠዋት ስፖርት እየሰሩ ስናይፕስን የክትትሉን ትኩረት ወደ ሌላ ተጠርጣሪዎች እንዲያዞር ወይንም ከነጭራሹ ቢተወው እንደሚሻል ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ስናይፕስ ግን የሚመለስ አልሆነም፤ እንደውም መረጃዎች የጠቆሙት ሰው እና ስልጣን ድረስ እንደሚሄድ አስረግጦ ይነግራቸዋል፡፡ ይህን ጊዜ ቺፉ ቆጣ ብለው ‹‹ፕሬዝዳንትነቱ ተቋም ነው (ግለሰብ አይደለም) እዛ እንድትደርስ አልፈቅድልህም›› ይሉታል፡፡

ስልጣን ተቋማዊ (Institutionalized) ሲሆን ምን ማለት ነው?

በታዳጊ ሀገራት ያሉ የመንግስት የአስፈፃሚ ቅርንጫፍ አናት ላይ የሚገኙ ባለስልጣናት ብዙ ጊዜ ሲፈፅሙ/ሊፈፅሙ ሲሞክሩ ከምናያቸው የፖለቲካ ቅሌቶች መካከል ስልጣን ላይ ለተጨማሪ ዓመታት ለመቆየት ሕገመንግስቱን ማሻሻል (ሴኔጋል እና ቬንዙዌላ የቅርብ ምሳሌዎች ናቸው)፣ ምርጫ ማጭርበርበር (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዚንባቡዌ)፣ በምርጫ ቢሸነፉም ስልጣን አለቅም ማለት (ኮትዲቩዋር) ይገኙበታል፡፡  እነዚህን የመሰሉ አሳፋሪ ድርጊቶች የሚፈፅሙት ታዲያ ስልጣንን የሚያዩት እንደህዝብን ማገልገያ መሳርያ ሳይሆን እስከ እለተ ሞታቸው የፈለጉትን እየፈለጡና እየቆረጡ የሚኖሩበት የግል ንብረታቸው አድርገው ስለሆነ ነው፡፡ ማቲያስ ባሰዶው እና አሌክሳንደር ስትሮህ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሙያዎች የፖለቲካፓርቲዎች ተቋማዊነት በታዳጊ ሀገራት በፈተሹበት ጥናት ተቋማዊነትን ሲተረጉሙ ‹ድርጅቶች እሴቶችን የሚመርጡበት እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡበት ሂደት ነው› ሲሉ ይገልፁታል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደማንኛውም ድርጅት ትውልድ ተሻጋሪነታቸውን ለማረጋገጥ ግልፅ የሆነ ስልጣንን (ቢያንስ ፓርቲ ውስጥ) ለተተኪዎች የሚያስተላልፉበት መመሪያ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህንንም ሽግግር የሚያበረታታ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ ብቻ እንደሆነ የሚያረጋግጥ የውስጠ ፓርቲ እሴት ያስፈልጋል፡፡ ኃላፊነትን ለመረከብ በጥሩ ሁኔታ የተኮተኮተ ተተኪ ማዘጋጀት እና ተተኪውም ብቁ መሆኑ ሲረጋገጥ ስልጣን (የፓርቲውንም ይሁን የሀገር) ማስረከብን አማራጭ የሌለው ምርጫ የሚያደርግ ባህል መፍጠርን ያካትታል ማለት ነው - ተቋማዊነት፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ማድረግ ያልቻለ እንደ ትልቅ ውድቀት የሚቆጠርበት በተለይም ስልጣን አልለቅም ብሎ ችክ ማለትን አሳፋሪ የሚያደርግ እሴት መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡
አምባገነኖች እና ተቋማዊነት!

"What would I do if I leave the Presidency? Chop Onions?” Hosni Mubarak

ከላይ እንደ ተጠቀሰው አምባገነኖች ስልጣን ላይ ለመቆየት ምንም ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፤ ድርጊታቸው ምንም ያክል አሳፋሪ ቢሆንም፡፡ አንባገነኖች እራሳቸውን ብቸኛ ነፃ አውጪ፣ ሰላም አስከባሪ፣ አልሚ …ወ.ዘ.ተ አድርገው ነው የሚቆጥሩት ወይም እንዲቆጠሩ የሚፈልጉት፡፡ ለዚህም ነው መልካም ስራ በመስራት ትንሽም ቢሆን ህዝባዊ ተቀባይነት የሚያገኙ ሰዎችን ከኃላፊነታቸው ዞር ከማድረግ አንስቶ ‹‹በህጋዊ›› እርምጃም ከጨዋታ ውጪ የሚያደርጓቸው፡፡ ሰዎች በአምባገነኑ ጥርስ ውስጥ ለመግባት የሚጠበቅባቸው ጥሩ ስራ ሰርተው በህዝብ ዘንድ ጥሩ ስም እና አመኔታ መገንባት ብቻ ነው፤ የአምባገነኑ ፓርቲ ወይንም ጎሳ አባል፣ አብሮ አደግ፣ ወይንም የተፎካካሪ ፓርቲ አባል መሆን ልዩነት ያለው የሚከተለው ቅጣት ላይ ነው እንጂ ህዝብ እንዲወደውና አመኔታ እንዲጣልበት የሚፈቀደው ለአምባገነኑ ለእራሱ ብቻ ነው፡፡ አምባገነኖች በወዳጅ ሀገሮችም ዘንድ እንደብቸኛ የወዳጅነቱ ጠባቂ ሆነው መቅረብ ነው የሚፈልጉት - እነሱ ከሌሉወ ዳጅነቱ ገደል እንደሚገባ፡፡

ይህን ትንተና ለመደገፍ የቀድሞ የግብፅ ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሆስኒ ሙባረክ እና የሊቢያ መሪ የነበሩትን ሙአመር ቃዳፊን ማየት ይበቃል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በየሀገራቸው ለረጅም (ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ) በስልጣን የቆዩ ሲሆን ሀገሮቻቸው የሚያስፈልጋቸው ዴሞክራሲ ከምዕራቡ ዓለም ለየት ያለ እንደሆነ ሲሰብኩ የኖሩ ነበሩ፡፡ የአረቡ ዓለም ፀደይን ተከትሎ ሁለቱም ስልጣናቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ የተለመደውን የአምባገነኖች ብሔራዊ መዝሙር ነበር የዘመሩት፤ እስከዛሬ እኔ ሆኜ ነው እንጂ ይህች ሀገር በብዙ ችግሮች የተተበተበች ናት፣ ያለ እኔም በቀጥታ የእርስ በእርስ ጦርነት ነው የምትታመሰው፣ በኋላ ሙባረክ/ቃዳፊ ምን በደለን የምትሉበት ቀን ይመጣል የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ነበር የሚያቀርቡት - የሚሰማቸው አላገኙም እንጂ፡፡ የሚገርመው ከጥቃቅን የማስዋቢያ ለውጦች በስተቀር የሁሉም አምባገነኖች ክርክር አንድ ነው - የእናት ሆድ ዥንጉርጉር የሚለው አባባል ለአምባገነኖች የሚሰራ አይመስልም፡፡ በስተመጨረሻ መውደቂያቸው ሲቃረብ አምባገነኖች የሀገሪቷን ችግሮች አጋንነው ሲደረድሩ ለሃያና ሠላሳ ዓመት በአመራራቸው ስር ስለነበረች ሀገር ሳይሆን ስለሌላ መልካሙዋን ማንሳት ስለማይፈልጓት ፀበኛ ሀገር የሚያወሩ ነው የሚመስለው፡፡

አምባገነኖች ሁልጊዜም ቢሆን እንደስልጡን መሪ መታየት ይፈልጋሉ፡፡ ጎልማሳ እያሉ ስልጣን እንደያዙ ምንም የማይወጣለት ብሔር ብሔረሰኖችን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚያጎናፅፍ ሕገመንግስት ሲያፀድቁ እና በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ ሊባል የሚችል ህዝባዊ ምርጫ ሲያካሂዱ የተሰጣቸውን የ‹‹ተራማጅ››ነት ዝና ስልጣን ላይ ከድፍን ሃያ ዓመት በላይ ከቆዩ በኋላ በልማታዊነት እንደገና ዝናዋን መልሰው ሊጎናፀፉ ይፈልጋሉ፡፡ አንድ አሁን በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት አምባገነኖች እራሳቸውን ለማሞኘት የሚሄዱትን ርቀት አሳንሶ መመልከት በርግጠኝነት መሳሳት ነው፡፡

ከአንባገነኖችበኋላስ?

አምባገነኖች የፖለቲካ ስልጣንን የግል ንብረታቸው አድርገው በመመልታቸው ተተኪ ማዘጋጀት ይቅርና ሊተኩ ይችላሉ የሚባሉትን ሰዎች ብቻ አይደለም ሐሳቡንም ጭምር ማጥፋት ከተቻላቸው ይሞክሩታል፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው አንባገነኖች እራሳቸውን እና እራሳቸውን ብቻ ለሀገሪቱ አማራጭ የሌለው ምርጫ አድርገው፤ እኔ ከሌለሁ ምንም አይኖርም በሚል ስልታዊ የፍራቻ ድባብ ውስጥ የሚመሩት ሀገር ዜጎች ሁሉ እንዲገቡ በማድረግ የስልጣናቸውን እድሜ ማራዘም ነው ግባቸው፡፡ እንደሳቸው ማነው አቻችሎ የሚገዛን? እሳቸው ባይኖሩ እኮ እስከዛሬም አልቀን ነበር ብለን እንድናስብ ነው የሚፈለገው፤ ስለሆነ ሳይሆን ለዓላማቸው ስለሚረዳቸው ብቻ፡፡

ወደገደለው

አቶ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ አልተወለዱም፡፡ ፈጣሪም እሳቸውን ብቻ ለቦታው የሚመጥኑ አድርጎ እንዳልሰራቸው ምስክር ከራሳቸው ሌላ የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡ እንደውም
  • አስፈራርቶ እና በጠብ-መንጃ ተማምኖ ከሚገዛን ልምድ ያለው አምባገነን አንድ ሀገራዊ ራዕይ ፈጥሮ የሚመራን ጀማሪ ይሻለናል፣
  • ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን ሳስር እና ሳንገላታ አያገባችሁም፣ ገንዘባችሁን በሊማሊሞ በኩል ይዛችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ ሃያ አንድ ዓመት ማሸነፍ ያቃተን የምግብ እህል ተረጂዎች ጉዳይ ግን የጋራችን ነው ብሎ ሀገሪቷን ከሚያዋርድ መሪ በግልፅ ቋሚ የውጭ እገዛ የምንፈልግበትን ሀገራዊ ጉዳይ ለይቶ ከሁሉም ወዳጅ ሀገራት ጋር ተስማምቶ የሚሰራ መሪ ይሻለናል፣
  • ስልጣን ላይ ለመቆየት ንፁሀን ዜጎችን ከሚገድል/ከሚያስገድል ይህን ተግባር እፈፅማለሁ፣ ሀገሪቷን ከእህል ተረጂነት አላቅቃለሁ አለበለዚያ ግን ስልጣን የናንተ ነውና እለቃለሁ የሚል፣ ብሎም የሚፈፅም መሪ ይሻለናል፡፡

No comments:

Post a Comment