ዞን 9 ኢ-መደበኛ የአራማጆች እና የጦማሪያን ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ማኅበረሰባዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ የተለየ እና ወገናዊ ያልሆነ ተረክ ለመፍጠር እየሰራ የሚገኝ የወጣቶች ስብስብ ነው፡፡ ይህንን የምናደርግበት ዋና አላማ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሪቷ ጉዳይ ያገባኛል ብለው ውይይት የማድረግ ባህል እንዲያሳድጉ በማድረግ ሀገሪቷን በሁሉም መስኮች ወደተሻ ለደረጃ የሚያደርሱ ሃሳቦች እንዲወለዱ ለማመቻቸት ነው፡፡
የተከበራችሁ የዞን9 ነዋሪዎች፣ በ2005 ዓ.ም ሊደረጉ ከታቀዱት አራት የበይነ መረብ ዘመቻዎች አራተኛው እና የመጨረሻው ዘመቻ ነገ ሐሙስ ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም እስከ ቅዳሜ ጳጉሜን 2 ቀን 2005 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል፡፡ አራተኛው ዘመቻ ‹‹#ኢትዮጵያዊ_ሕልም፤ ኑ አብረን እናልም!›› በሚል ርዕስ መላው ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያ ሆና ማየት የሚፈልጉትን እና እዚያ ለመድረስ መደረግ አለበት የሚሉትን የሚያካፍሉበት ይሆናል፡፡
የረጅም ታሪክ፣ የውብ ባሕል እና ማንነቶች ባለቤት በሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ ዜጎቿ እርስ በርስ ተስማምተው እና ሁሉንም ዕኩል ባሳተፈ መልኩ ሀገሪቷን ለመገንባት ከሚያስችሉት ግብዓቶች መሐከል የጋራ ሕልም መኖሩ ዋነኛው ነው፡፡ ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ አራተኛው የበይነመረብ ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያ ያላቸውን የወደፊት ተስፋ እንዲጋሩ መድረክ ለመፍጠር ይጥራል፡፡
የዘመቻው ዋና ዓላማዎችም፤ ሁሉንም አካታች፣ ለሁሉም ምቹ፣ ለሁሉም ዕኩል ዕድል የምትሰጥ ኢትዮጵያን ለማመለካከት፣ የቋንቋ እና ባሕላዊ ኅብርን አስፈላጊነት እና ጥቅም ለማመላከት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍትሕን ለማምጣት የሚበጁ አመለካከቶችን ለማስረጽ፣ ሃይማኖታዊ መቻቻልን ለመስበክ እና በተለይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊኖርባት የሚፈልጋት፣ ተሰዶ የማይወጣባት፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዕኩል የሚታዩባት፣ የሚጠቀሙባት እና የሚጠቅሟት ኢትዮጵያን ማለም እንዲቻል ማድረግ ይሆናሉ፡፡
ዘመቻው በዋነኛነት የሚካሄደው ‹‹ፌስቡክ›› እና ‹‹ትዊተርን›› በመጠቀም ይሆናል፡፡ ዜጎች ለሀገሪቷ ያላቸውን ሕልም በተመለከተ እራሳቸውን እንዲጠይቁ እና እንዲወያዩ የሚያስችሉ የተለያዩ ጽሑፎች በጦማራችን ይወጣሉ፡፡ በሁለቱ ማኅበራዊ አውታሮች ላይ ለዚሁ ዘመቻ ሲባል የተዘጋጁ አጫጭር ጽሑፎች ይሰራጫሉ፡፡ ዘመቻውን የሚመለከት ‹ባነር› ተዘጋጅቶ ዘመቻው በሚቆይባቸው ቀናት የተለያዩ ፕሮፋይል ምስሎችም ተዘጋጅተው የሽፋን ምስል እና የፕሮፋይል ፎቶ ይሆናሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ ምቹ፣ ሁሉም ዜጎቿ ካለምንም የጥላቻ ስሜት እርስ በርስ ተደጋግፈው ሰብኣዊና ቁሳዊ የሀገር ግንባታ ላይ ብቻ የሚያተኩርበት እና የበለጠ የምታኮራ ሀገር ሆና ማየት የምትፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚህ ዘመቻ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሕልማችሁን እንድታጋሩ እና የሌሎችን ሕልም እንድትጋሩ እንጋብዛለን፡፡
ስለሚያገባን እንጦምራለን!!!
ዞን9
No comments:
Post a Comment