Sunday, June 16, 2013

ኢትዮጵያ እና ዴሞክራሲ


ሞክራሲ ምንድን ናት? የሞክራሲ መናስ እንዴት ትወርዳለች? እንደምንስ ትፀናለች? የዲሞክራሲ ዋነኛ ጠላቶችስ እነማን ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች ለረጅም ዘመናት በየእለቱ አዲስ መልስ እየተሰጠባቸው እና አዲስ ጥያቄ እየፈጠሩ አንድ እና ወጥ መግለጫ ሳያገኙ ቀጥለዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ጥያቄዎች ጠቅለል አድርጎ ይገልፅልናል የምንለው የአሜሪካው 16ኛ ፕሬዘደንት፣ አብርሃም ሊንከን ታዋቂውን የጌትስበርግ ንግግራቸውን ያጠቃለሉበት “[…] that government of the people, by the people, for the people, shall not perish from the earth.” የተባለው ሀሳብ ነው፡፡ ከሕዝብ ለሕዝብ፣ በሕዝብ የሆነውን ስርዓትም ዘመናዊ ፀሃፍት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንደሆነ እና የዴሞክራሲ ምንጯ ሕዝብ፤ ጠላቷም የሕዝብ ጠላት እንደሆኑ ይተነትናሉ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዴሞክራሲ አይሰራም፤ ቀልድ ነው፤ “Democracy can't work. Mathematicians, peasants, and animals, that's all there is, so democracy, a theory based on the assumption that mathematicians and peasants are equal, can never work.” ከሚሉት ከነሮበርት ሔንላይን እስከ “Democracy is the worst system, except for all the other systems” በማለት የዲሞክራሲን አስከፊነት ግን ምርጫ አልባነት እስከሚናገሩት ድረስ እናገኛለን፡፡ እንግዲህ ይህ በሀሳብ መለየት ነው እንጅ ዴሞክራሲማ እጅግ ተመራጩ ስርዓት ነው በሚል እሳቤ ነው የምንቀጥለው፡፡

ችግሩ የት ላይ ነው?

ዴሞክራሲን ለመግለጽ ሊቃውንት አንድ ቁርጥ ያለ ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ምክንያት ሁሉም የራሱን ትርጉም በመስጠት ለአመቸው ተግባር ሲያውለው ይታያል፡፡ ከሀገር ሀገር፤ ከጊዜ ጊዜ አንዴ እየሰፋ፤ አንዴ እየጠበበ እጅግ የበዙ እና የተለያዩ ትርጉሞችን ይዞ በሩን አሁንም ለሌላ የትርጉም ጋጋታ ክፍት አድርጎ አዲስ ስያሜን ይጠብቃል - ዴሞክራሲ፡፡ ይሄን የበዛ የትርጉም ልዩነት የተመለከተው ጆርጅ ኦርዌል ‘Politics and the English Language’ በተባለው መጣጥፉ ‹‹ዴሞክራሲ ስምምነት ላይ የተደረሰበት ትርጉም ያጣ ቃል ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ትርጉም ለመስጠት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ከሁሉም አቅጣጫ ውግዘት ይደርስበታል፤ ምክንያቱም ሁሉም በውስጡ የራሱ ትርጉም አለውና ያ ትርጉም እንዲፈርስበት አይሻም… እንደ ዴሞክራሲ ያሉ ቃላት ለእያንዳንዱ ሰው የራሳቸው ትርጉም አላቸው›› በማለት ገና በ1930ዎቹ ዴሞክራሲ ትርጉም ያጣ፤ ሁሉም በየጓዳው እየመዘዘ የሚጠቀምበት ትርጉም አልባ ቃል እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ለዚህም ይመስላል የፖለቲካ ሳይንቲስቱ Robert Dahl በዴሞክራሲ ፋንታ ‘እውነተኛውን የዲሞክራሲ ትርጓሜ’ ወይም ‘Polyarchyን’ እንጠቀም ዘንድ የሚመክረን፡፡ ዴሞክራሲን እንዲህ ነው ብለን ብይን እንዳንሰጠው በተለያዩ ችሎቶች የተለያዩ ብይኖች ተሰጥተዋል እና ዴሞክራሲ ‘One of the most Misused and Abused term’ ይባል ዘንድ እውነት ሆኗል፡፡ ችግሩም የዴሞክራሲ ስመ ብዙነት፤ የዴሞክራሲ ትርጉመ የትየለሌሽነት ላይ ይወድቃል፡፡

The Ethiopian ‘D’ Syndrome    
              
ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ዋለበትን ጊዜ ይህ ነው ብሎ ለመናገር የጠለቀ ጥናት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ በወጡት ዓለማቀፍ ህጎች እና መርሆች በመንተራስ በፀደቀው የ1955ቱ ሕገ መንግስት ላይ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚል ስያሜ የዜጎች መብቶች ተቀምጠው እናገኛለን፡፡ ያም ቢሆን የንጉሱ ስርዓት ራሱን ዴሞክራሲያዊ ብሎ ጠርቶ አያውቅም - ደግ አደረገ፤ ፈላጭ ቆራጭ ነበርና፡፡ 

የንጉሱ ስርዓት ማብቂያ ላይ ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት ‹የመጀመሪያዎቹ› የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ዴሞክራሲያዊ ብለው ከመጥራት ይልቅ ሕብረተሰባዊ፣ አብዮታዊ፣ ወ.ዘ.ተ የሚሉ ቃላትን ተመራጭ ያደርጉ ነበር፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆኑን የንጉሱን ስርዓት መገርሰስ ተከትሎ ብልጭ ብላ በነበረችው ‹የነፃነት ጮራ› በመጠቀም እስከ ቀይ ሽብር ማብቂያ ድረስ ለምልመው ከነበሩት ፓርቲዎች ውስጥ የዋነኛዎቹን ስያሜ ብንመለከት፤ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ አብዮታዊ ሰደድ፣ የወዛደር ሊግ (ወዝሊግ)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) እና ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሊሽናዊ ድርጅትን (ማሌሪድ)፤ እንዲሁም እነዚህ አምስት ድርጅቶች በጋራ የመሰረቱትን የኢትዮጵያ ማርክሳዊ ሌኒናዊ ድርጅቶች ህብረት (ኢማሌዲህ) በአንድ ወገን ስናገኝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን (ኢህአፓ)  እናገኛለን፡፡ 

ከነዚህ ዋነኛ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱም ዴሞክራሲን የስም ማሸብረቂያ ሲያደርጋት አይታይም፤ አልደፈረም፡፡ ደርግ በአፈሙዝ በዙሪያው ያሉትን ፓርቲዎች አንድ ባንድ ካስወገደ በኋላ የወዛደሩን ፓርቲ  የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ ኮሚሽን (ኢሰፓኮ) በኋላ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲን (ኢሰፓ) መሰረትኩ አለ፤ እስከዚህ ጊዜ ድረስም ዴሞክራሲን ተዳፍሮ ለስም መጠሪያነት አላዋለም ነበር፡፡ ነገር ግን ወታደራዊው መንግስት በዙሪያው ነፍጥ ያነገቡ ሀይላት እየገፉ ሲመጡበት እና የምስራቁ ርዕዮተ ዓለም ሲዳከም ተመልክቶ ‹በአዎጅ ሀገር አስተዳድራለሁ› የሚለውን ቀረርቶ በማቆም፤ ለሕዝቡ ‹ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስት› እነሆ አልኩ ሲል፤ በዛውም የሀገሪቱን ብሄራዊ መጠሪያ ዴሞክራሲ በተባለችው ምትሃተኛ ቃል አስጊጧት ነበር - ‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ›፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ግንባር ከጅምሩ ራሱን ዴሞክራሲያዊ ብሎ በመጥራት የፖለቲካውን ገበያ የተቀላቀለ ሲሆን፤ እርሱን ከመሰረቱት አራት ፓርቲዎች ውስጥ ከሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) በቀር ሶስቱ ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ)፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ያችን ‹ወርቃማ ቃል› መለያቸው አድርገዋታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም  በኢህአዴግ አጋርነት ቀሪዎቹን አምስት ክልሎች ከሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ውስጥ ከሀረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሀብሊ) በቀር አፋርን፣ ሶማሌን፣ ጋምቤላን እና ቤንሻንጉል ጉምዝን የሚያስተዳድሩት አጋር ፓርቲዎች ስያሜያቸውን በምትሃተኛዋ ዴሞክራሲ ያደመቁ ሁነው እናገኛቸዋልን፡፡ 

ተቃዋሚ ፓርቲዎቻችንም ‹ዴሞክራሲ› ለተባለው ቃል ያላቸው ፍቅር የበዛ ነው፡፡ ዴሞክራሲን በስያሜነት ያልተጠቀመ የተቃዋሚ ፓርቲ የህዝብን ይሁንታ አያገኝም የተባለ ያክል፤ የተቃዋሚው ሰፈር በዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የዴሞክራሲ ግንባር፣ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ወ.ዘ.ተ በሚሉ የዴሞክራሲ ቅጽል የተዋቡ ናቸው፡፡

ይሄን እይታችንን ወደ ሀገሪቱ መጠሪያነት ስንወስደው ደግሞ፤  የሀገራችን ብሄራዊ መጠሪያ ከዴሞክራሲ ጋር የተፋቀረ ሆኖ እናገኝዋለን፡፡ ወታደራዊው መንግስት አስራ ሶስት ዓመታትን ዘግይቶ ባወጣው ሕገ መንግስቱ ንቆ ትቶት የነበረውን ዴሞክራሲ ለስርዓቱ መጠሪያነት ‹የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ› በማለት አውሎታል፡፡ ወታደራዊውን መንግስት የተካው ኢሕአዴግ በበኩሉ የወታደራዊውን መንግስት ሕገ መንግስት ቀይሮ  ባወጣው አዲስ ሕገ መንግስት ‹የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን› እንደመጠሪያነት ተጠቅሞ በአፍሪካ ራሳቸውን ‹ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ› ብለው ከሚጠሩት ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ከአልጀሪያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር በሶስተኝነት ተሰልፏል፡፡ እንግዲህ የሀገሪቱ መጠሪያ ዴሞክራሲያዊ ከተባለ ሩብ ምዕተ ዓመት አስቆጥራለች ማለት ነው፡፡ 

እንግዲህ ያንድ ወጣት እድሜ ያስቆጠረው የዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ብሄራዊ መጠሪያ እውን መሬት ላይ ያለችውን ኢትዮጵያን ይወክላል ወይ? ትንሹም ትልቁም ‹ዴሞክራሲ› የተሰኝችውን ቃል እየመዘዘ ስሙ ላይ ሲለጥፍ፤ እውን ራሱን ለዴሞክራሲ ፅንሰ ሀሳብ አስገዝቶ ነውን ነውን? ወይስ እንዲሁ ማታለያ ነች? ነው ጥያቄው፡፡

‹‹ዴሞክራሲ ሆይ፣ ዴሞክራሲ ሆይ የሚለኝ ሁሉ…››

አስማተኛው ወይም ሻማኑ ምትሃቱ እውን ይሆን ዘንድ፤ መናፍስቱ ስራቸውን ይጀምሩ ዘንድ በማይገባ ቃል ያነበንባል (‹በልሳን› ይናገራል እንበለው ይሆን?)፤ ይህም ማነብነብ ‘Abracadabra’ ይባላል፡፡ የቃሉ አመጣጥ ከቁምርዓነ ፅሁፎች (The writings of ‘Q’) አንዱ  በሆነውና በSerenus Sammonicus ከተፃፈው ፅሁፍ  ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሳሞኒከስ ስለዚህ ምስጢራዊ (Cabbalistic) ቃል የአጠቃቀም መመሪያ ያስቀመጠ ሲሆን፤ የማነብነቡ ሚስጥርም መናፍስቱን መጥራት እንጅ ምትሃቱን ማዝነብ አይደለም፤ የምትሃቱ ባለቤቶች መናፍስቶቹ ናቸው፡፡ 

እኛም ሀገር ዴሞክራሲ ወደ ሳሞኒከሱ ‹አብራካዳብራ› የተቃረበ ነው፡፡ የፖለቲካ አስማተኞቻችን የሳሞኒከስን መመሪያ ተከትለው በሚመስል መልኩ፤ ዴሞክራሲን በፓርቲ መጠሪያነት፤ ዴሞክራሲን በፓርቲ ፕሮግራም አድማቂነት፤ ዴሞክራሲን በሕዝብ ግንኙነት መሪ ቃልነት ይጠቀማሉ ፤ ሕዝቡም እንደመናፍስቱ ወደነሱ ይቀርባል፤ በዙሪያቸውም ይሰበሰባል፤ ያኔ አይኑን ያውሩታል በሕዝቡ ስም ይነግዳሉ፡፡ ይህም ማለት ፖለቲከኞቻችን ዴሞክራሲን እንደ ማር ገምቦ (Honeypot) ይገለገሉባታል እንደማለት ነው፡፡ ህዝቡ ማሩን ፍለጋ በማሩ ዙሪያ ይኮለኮላል፤ ማሩን ግን አያገኝም፡፡ 

የዘመናዊ ሕገ መንግስታት ፈር ቀዳጅ የሆነው የአሜሪካ ሕገ መንግስት አንድም ቦታ ዴሞክራሲ ወይም ዴሞክራሲያዊ የሚሉ ቃላትን አይጠቀምም፡፡ በተነፃፃሪ ባለፉት 25 ዓመታት ያየናት ኢትዮጵያ  ከሕገ መንግስታቶቿ እስከ ፓርቲ ፕሮግራሞች ድረስ ዴሚክራሲን ያልተጠቀመችበት ቦታ ማግኝት ከባድ ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ አብዝታ ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ስላለች አሜሪካ ደግሞ በሕገ መንግስቷ አንድም ቦታ አላስተናገደችውምና፤ ኢትዮጵያ የተሻለች ዴሞክራሲ ናት ማለት በፍፁም አይደለም፡፡ ይልቁንም የህዝቡን ፈቃድ የሚያደርግ እንጅ፤ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ የሚል ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡


በተኩላው ‹ርዕዮተ ዓለም›  የተበላው፤ በጉ ዲሞክራሲ

በቅርብ ዓመታት ታሪካችን ውስጥ ያስተዋልነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሂደት ውስጥ የዴሞክራሲና የገላጭ ቅፅልን ጋብቻ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ብቻውን መቆም አይችልም በሚል ሀሳብ ከፖለቲከኞች እስከ ምሁራን ድረስ የመረጡትን ወይ የሚተነትኑትን ዴሞክራሲ ለማስረዳት በቅፅል ያደምቁታል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ሊብራል ዴሞክራሲ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ፣ ሕዝባዊ ዴሞክራሲ፣ የድርድር ዴሞክራሲ ወ.ዘ.ተ እያሉ የሚቀጥሉ የዴሞክራሲ ክምር እናያለን፡፡ ዴሞክራሲ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ በገላጭ ቃል በማጀብ ለመግልፅ እየተሞከረ ነው ማለት ነው፤ ‹እኔ ከ እገሌ የምለየው በያዝኩት ልዩ ቅጽል› ነው ብሎ እንደመከራከር ማለት ነው፡፡ 

እንግዲህ ዴሞክራሲ በራሱ እንዳይቆም ሁሉም የራሱን ትርጉም በመስጠት ትርገም አልባ አድርጎታል ካልን ዘንድ፤ ቅፅል እየጨመሩ ማብራራቱ ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን ባለው ተሞክሮ በሀገራችን ዴሞክራሲ በቅጽል ሲታጀብ የሃሳቡ ባለቤት ግለሰብ ወይም ፓርቲ ቅፅሉን ለማግዘፍ ያደረገው እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ ሰዎች ራሳቸውን ‹አብዮታዊ ዴሞክራት› ብለው ሲጠሩ ‹አብዮተኞች ነን› ማለታቸው ሆኖ እናገኝዋለን፤ ‹ሶሻል ዴሞክራት ነን› ሲሉ፤ ‹ረጅም የመንግስትን እጅ (Big Government) በኢኮኖሚው ውስጥ ማየት እንፈልጋለን› ማለታቸው ሆኖ ይታያል፤ ‹ሊብራል ዴሞክራቶች ነን› ሲሉ ደግሞ፤ ‹መንግስት እጁን ሰብስቦ ይቀመጥ› ማለታቸው ሆኖ እናገኝዋለን፡፡ በዚህ መሃል ዴሞክራሲ የተባለችውን ቃል ርዕዮተ ዓለም የተባለ አቧራ ሸፍኗት እናገኛታለን፡፡ እንግዲህ ዴሞክራሲን ከአቧራው መሃል አውጥቶ በዙፋኗ ማስቀመጥ ነው ተስፋ የሚደረገው የድኸነት መንገድ፡፡ ከአቧራው መሃል ማን ያወጣታል? ለሚለው ጥያቄ፤ ማን ሊያወጣት አይችልም?  ለሚለው ጥያቄ ዊንስተን ቸርችል “Democracy is no harlot to be picked up in the street by a man with a tommy gun” ያለውን ሀሳብ እንደመልስ ብንወስድስ?

No comments:

Post a Comment