Monday, September 3, 2012

የእኛ ጀግንነት




ጀግንነት እና እኛ ኢትዮጵያውያን ከተያያዝን የማንላቀቅ ለሌሎችም ስንሸልመው የኖርን የጀግንነት ወራጅ ሕዝቦች ነን፡፡ ከጀግንነት ጋር ጥልቅ ፍቅር ውስጥ የወደቅን ሕዝቦች መሆናችንን ለማሳየት የታሪክን ምስክርነት መጠየቅ አያስፈልግም፡፡

በቅርብ ጊዜዎች እንኳን ጀግንነትን ለብዙዎች ስንሸልም ተመልክተናል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የልማት ጀግንነት ለገበሬዎች እና ድህነትን ድል ላደረጉ ሁሉ ሲሰጥ የነበረ ስያሜም ሆኖም ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በዘመናችን ከድፍረት ጋር የተያያዘ ጀግንነትን ስለምናደንቅ እና ስለምናበረታታ ጥንት ጥንት የጦር ሜዳ ጀግነነትን አሁን ደሞ የተለየ ድፍረትን በጀግንነት ምሳሌነት ከመጥቀስ ባሻገር የሚያግባባን የጋራ ትርጉም ያለው አይመስልም፡፡

ሰሞኑ እና ጀግንነት


የቀድሞው /ሚር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማርና) ከሞታቸው ጋር ተያይዞ በሰሞኑን ጀግንነትን የመሾም ታሪካችን ውስጥ ከፍተኛ ስፍራን የያዙ መስለዋል፡፡ በእርግጥ በጥቂት ፖስተሮች እና ህትመቶች ላይ ይታይ የነበረው የአቶ መለስ የጀግና ስፍራ ከሞታቸው በኋላ በእርግጠኝነት እና በስፋት በሁሉም ቦታ እና ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ህልፈታቸው ከተሰማበት ማግስት አንስቶ ስራ የጀመረው የፕሮፖጋንዳ ማሽንም አገራዊ ሃዘኑን ለፖርቲ ስብእና ግንባታ መጠቀም መሆኑ በሚያስታውቅ ሁኔታ የጀግናው ሞት ምን ያህል እንዳሳዘነን ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ ይህ የሚዲያው ተግባር እና ተያያዥ ሕዝባዊ ምላሾችን አስመልክቶ ውይይቱ ለሌላ ጊዜ ይቆየንና የአቶ መለስን ጀግና ያስባሉ ጉዳዮችን በትኩረት ብንመለከት ቢያንስ ቢያንስ ጀግና ባሰኛቸው ነገር ላይ መነጋገር የወደፊት ጀግኖቻችንን ሹመት በአትኩሮት ለማየት ይረዳን ይሆናል፡፡

ልማታዊ መሪ (የግድብ እና የመንገድ አባት)

አቶ መለስ ዜናዊ የመንግስትን ስልጣን ከተረከቡ 1983 ጀምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ መንግስታቸው ከሚታወቅበት ጉዳዮች አንዱ መንገዶች እና ህንፃዎች በብዛት መገንባታቸው ነው፡፡ ይህ የመንግስት ስኬት በተለይ ካለፉት መንግስታት ጋር ሲነጻጸር የሚያስመሰግነው ቢሆንም መንገድ የሰራልን መሪያችን ጀግና ነው የሚያስብል ድምዳሜ ላይ ማድረሱን እጠራጠራለሁ፡፡ ለነገሩ ፓርቲውም ቢሆን ስለስኬቶቹ ሲጠየቅ መጀመሪያ የሚያነሳው መንገድን ስለጥፋቶቹም ሲወቀስ መልሶ የሚያነሳው መከላከያ ያው የመንገድ እና የህንፃዎች ግንባታን ነው፡፡ በቅርብየአባይ መደፈርነገሩን ወደዚያ ወሰደው እንጂ ላለፉት 20 ዓመታት ፓርቲያቸው የመንገድ ግንባታን ግብር የሚሰበስብ መንግስት ኃላፊነት ያልሆነ ይመስል ለተለያየ ፕሮፖጋንዳ ሲጠቀምበት ከርሟል፡፡

ግብር ከፋይ ሕዝብ መንገድ ሲሰራለት እነደችሮታ አንዲቆጥረው ሲደሰኮር መክረሙን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የአባይ ፕሮጄክት መጀመርን ሙሉ ዕውቅናን ለጠ/ሚኒስትሩ መስጠት የጥረታቸው የሚገባ ዋጋ ነው:: (ይህ እንግዲህ የመነሻ ዓላማውን፣ የፕጄክቱን ስኬታማት ዕድሎች፣… የመሳሰሉትን ክርክሮች ሳይጨምር ነው፡፡) ይህ የሚገባው ዕውቅና እንዳለ ሆኖ ነገር ግን የመንግስት ኃላፊነቶቹን የሚወጣ መሪን ኃላፊነትህን ስለተወጣህ ጀግና ነህ ብሎ ማወደስ የለመደብን፣ የማጋነን እና በነፈሰበት የመንፈስ ዘይቤ ውጤት ይመስላል፡፡ የአባይን የመገደብ ፕሮጄክት ብቻውን ለሟች /ሚር ተገቢ ዕውቅና ቢሰጣቸውም ሌሎቹን ልማታዊ ቅጥያዎች መንግስታዊ ኃላፊነታቸው/ሥራቸው መሆኑን ባንረሳ ጥሩ ነው፡፡

ልማቱ ከተነሳ አይቀር በልቶ ማደር ብርቅ የሆነባቸው የከተማ ነዋሪዎች፣ የቤት ኪራይ እና የደሞዝ መጠን አንድ የሆነበት ጊዜ፣ ትራንስፓርት ችግር የሚያስለቅስበት ወቅት፣ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም ያልተቻለበት ዘመን የእርሳቸው አመራር ውጤት መሆኑንም መዘንጋት አያስፈልገንም፡፡

የኢትዮጵያ/የአፍሪካ ተወካይ

ኢቴቪ፣ መሰሎቹ እና ሐዘንተኞቹ በተደጋጋሚ ያነሱት የነበረው የአቶ መለስ የመጀመሪያ ሰሞን የጀግነት መገለጫ በአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ዙሪያ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አቶ መለስ ስለአገራቸው በቅንነት እና እንደመሪ በሚያኮራ መልኩ የተናገሩት ብቸኛ ንግግር ይሄ ነወ ለማለት እደፍራለሁ:: ኢቴቪም ቢሆን የአገር መሪ እንዳጣን ሊያስታውሰን ሲሞክር ደጋግሞ ሲያሳየን የነበረው ይሁንኑ ንግግር ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ ያለውን የአቶ መለስን ስብዕና ሰስናስታውስ ደጋግሞ የሚታወሰኝብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችተያያዥ ጉዳዮች እና ከእሳት የተፈተነ ብሔር መምጣታቸውን በኩራት የተናገሩበት ንግግራቸውም ጭምር ነው፡፡

አፍሪካ ህብረት እና ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ቦታ ዛሬ በመለስ ዘመን ያገኘነው አዲስ ቦታ አይደለም፡፡ (አቶ መለስም ቀደም ሲል በገለጽኩት ንግግራቸው ላይ ይህንን ያምናሉ)፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት (በቀድሞ አፍሪካ አንድነት) ውስጥ የነበራትን ቦታ ይዛ እንድትቀጥል ማድረጋቸው እንደ አንድ መሪ የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ጀግና የሚያስብል ማዕረግ ግን የሚያላብስ አልነበረም፡፡ እንደውም እንደአለመታደል ሆኖ ነው እንጂበየስብሰባው የሚዞር መሪያላት አገር ተብሎ ከመታወቅ ይልቅ በፈጣን የዴሞክራሲ ስርአት እና ተያያዥ ፍሬዎቹን የሚያጣጥሙ ሕዝቦች አገር ተብሎ መታወቅ ይበልጥ ያምርብን ነበር፡፡

የአቶ መለስ አለም አቀፍ የተግባቦት ችሎታ የማይካድ ቢሆንም የግል ስብእናቸውን ገንብቶ እኛን ለኢቴቪ ፕሮፖጋንዳ ከመዳረግ ውጪ እንደ አገር ኢትዮጵያን የጨመረላት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እንደውም ይህ የተግባቦት ችሎታቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶቸን እና ጭቆናን ለመደበቅ እነደመሳሪያ ሆኖ ማገልገሉን አናንሳ ካልን ነው፡፡ ከአፍሪካ መሪዎች በተሻለ የማሳመን ችሎታቸው የሚታወቁትን አቶ መለስን አፍሪካ ተወካይ አድርጋ ብትመርጥ አይገርምም:: የአፍሪካ መሪዎች ብዙዎቹ አምባገነኖች ናቸው፡፡ ሕዝቦቻቸውን በማማረር በሚታወቁ የአፍሪካ መሪዎች መካከል በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት ሕዝቦቻቸውን የሚያሰቃዩ መሪዎችን መወከል የምርጦች ምርጥ መሆን አይደለም፡፡ አቶ መለስ የዴሞክራሲያዊ አገራትና የሚኮራባቸው ስኬታማዎች መሪዎች ተወካይ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር በየአመቱ ብዙ ሺህ ሰዎች የሚሰደዱባት፣ በየአገሩየሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችዋን በየቀኑ የምትቀበል አገር መሆንዋን የአቶ መለስ ተወካይነት አላስቀረውም፡፡ ምክንያቱም ይህ በእርሳቸው አስተዳደር ዘመን ኢትዮጵያ ያለችበት እውነታ ነውና!

የዴሞክራሲያ አባት/የአንድነት አባት

ይህንን ወደቀልድነት የሚያደላ የአቶ መለስ ቅጥያ ጀግንነት የሰማሁት ከኢቲቪ እና መሰሎቹ ነበር፡፡ እንደሰማሁት መጀመሪያ የተሰማኝ የነበረውየዴሞክራሲን እና የአንድነትን ትርጉም ለመረዳት ምን ያስፈልገናል ወይስ አይገባቸውም ተብለን ይሄን ያሕል ተንቀን ነውየሚል ጥያቄ ነበር፡፡ አንዳንዴ ሳስበው አቶ መለስን በግል ከየትኛውም ሚዲያ ውጪ ብናጨዋውታቸው ራሳቸው የአንድነት እና የዴሞክራሲ አባት ነኝ የሚሉ አይመስለኝም፡፡ ዴሞክራሲ ሒደት ነው ብለው ይሸፋፍኑት ይሆናል እንጂ፡፡

አቶ መለስ የዴሞክራሲን ማስፈን ፍላጎት እና ተግባራዊነት የተቀላቀለባቸው መሪ ነበሩ፡፡ (ይህንን ለመረዳት ሕገ መንግስቱን እና ተግባራዊውን ሁኔታ ማወዳደር ይበቃል) የፓርቲያቸውም ሆነ የግለሰብ ባህሪያቸው ዴምክራሲን እሴታቸው አድርጎ አይቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ አለማቀፋዊ ተቀባይነትን ለማግኘት ከሚሞከሩ የጨዋታ ምርጫና ሚዲያ ውጪ የተቃውሞ ድምጾች መገለጫም ሆነ ቁጥር ቀን በቀን እየቀነሰ ሄዶ አሁን ዜጎች መንግስትን የምትተች ትንሽ ንግግር እንኳን ሲያደርጉ አካባቢያቸውን ዞር ዞር ብለው ለማየት እና ድምጻቸውን ለመቀነስ የተገደዱበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ እንግዲህ የአቶ መለስን 1997ቱን የኢትዮጵያን የሰላማዊ ዴምክሲያዊ ሽግግር ዕድል የገደሉበትን፣ ነፍስ ያስጠፉበትን ተግባራቸውን እንርሳ ካልን ነው፡፡

የአቶ መለስ መንግስት ባለፉት 21 ዓመታት ከፈጠራቸው ታላላቅ ጠንካራ አገራዊ ጥፋቶች መካከል አንዱ እንደአገር ልዮነቶቻችን ላይ አንድናተኩር የመደረጋችን ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህ የሃይማኖት እና የብሔር ልዩነትን በዕውቅና እና መብት መስጠት ሽፋን በማስፋፋት የማንነታችን መነሻ ኢትዮጵያዊነት መሆኑን የረሳንበት ደረጃ ላይ አድርሶናል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ይህ በጋራ መሃከል ላይ እስክንመጣ ድረስ የሚቆይ አገራዊ የቤት ሥራ የአቶ መለስ አመራር ውጤት ሆኖ እያለ አቶ መለስን የአንድነት አባት ማለት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲከኛ እስረኞች ያሉባትን ሃገር፣ የፓለቲካ ስደተኞች የበዙባትን ሃገር፣ ሽምግልና የፓለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት መቀለጃ እና መሳሪያ በሆነበት ዘመን፣ አቶ መለስን የዴሞክራሲ አባት አድርጎ መሳል በሕዝቦች ላይ መቀለድ ነው፡፡

አንደበተ ርቱዕ?

የአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት ሰሞኑን አንዱ የጀግንነታቸው ምክንያት ሆኖ ተገልጧል፤ (ለነገሩ ወደ በኋላ ትንሽ ደበዘዘ እንጂ የድሮም ዝናቸው መሰረት አንደበተርዕቱነት ነበር)፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ሐሳባቸውን በመግለጽ በኩል ጠንካራ ነበሩ፡፡ ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ እና ሁኔታ ቢለያይም (ፓርላማ ላይ ሌላ፣ ከአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ሌላ፣ ከሃገር ውጪ ስብሰባ ላይ ሌላ፤ የአገር ውስጥ ስብበሳ ላይ ሌላ) በራስ መተማመን መንፈስ ሐሳባቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አያውቁም ነበር፡፡ በሃገር ውስጥ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ ግን አቶ መለስ የመሪነት ስልጣናቸውን እንደፈለጉ ለመናገር መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡

አቶ ለመለስ በፓርላማ ይጠየቃሉ እንደፈለጉት ይመልሳሉ፤ እርሳቸው ለመለሱት መልስ ክርክር እና ተጨማሪ ምላሽ የመስጫ ጊዜ ኖሮ ስለማያውቅ ከማሰካካት ባለፈ የክርክራቸውን ቀሽምነትን እና ጥሩነት ከሌሎች ጋር በመከራከር ተፈትኖ አያውቅም፡፡ በዚህ ብዙ ዕድሎች የሰጠን ምርጫ 97 እንኳን እርሳቸውን በአደባባይ ሲከራከሩ ሊያሳየን አልቻለም ነበር፡፡ በተለይ በአገር ውስጥ ጉዳዮች ዙሪያ የአቶ መለስ አንደበት አንድም ቀን ለክርክር ቀርቦ አያውቅም፡፡ እሳቸው ይናገራሉ ሌሎች ያዳምጣሉ፡፡ እንደውም ሞታቸው የሚቆጨው ከአንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋር ለቀጥታ ክርክር ቀርበው ሳይከራከሩ በመቅረታቸውም ጭምር ነው፡፡ የአቶ መለስ አንደበተ ርቱዕነት በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚመሰከርለት ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያዊ ምስክር ሆነን እና አፋችንን ሞልተን እናወራለት ዘንድ እሳቸው ብቻ ሲናገሩ መክረማቸው ቀርቶ በአገራዊ ውይይቶች ከሌሎች ጋር ሲያወሩ፣ ሲወያዩ እና ሲከራከሩ የማየት እድሉ ቢኖረን ይህንን የጀግንነታቸው መገለጫ አንደበተ ርቱዕነታቸውን ነው ብለን አፋችንን ሞልተን እናወራ ነበር፡፡

ለእኔ በግሌ አቶ መለስ የምኮራባቸው ጥሩ መሪ አልነበሩም፡፡ እዚህ ቅሬታ ላይ የሰሞኑን ቅጥ ያጣ ፕሮፖጋንዳ ሲጨመርበት ደግሞ እንደ ሰው ያዘንኩትን ሐዘን በኢቴቪ እና በመሰሎቹ እንዳልቀማ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ ሐዘኑን ፓለቲካ ሲያደርጉብን ከርመው እኛ ፓለቲካዊ ስናደርገው የሚወቅሱን ካሉ ለአቶ መለስ ማዘን እና ፕሮፖጋንዳውን ባለመቀላቀል እንዲረዱኝ ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ አልታደልንም እንጂ ኢቴቪን ወደ አንድ ጽንፍ ሲጎትተን የሚያመጣጥንልን ሌላ ሚዲያ ቢኖረን ኖሮ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ለመነጋገርም አንነሳም ነበር፡፡

አቶ መለስ ታታሪ፣ ለአላማቸው ጽኑ፣ ጠንካራ ሰራተኛ፣ የፓርያቸው ምሰሶ ነበሩ፡፡ የእርሳቸው ዓይነት አንድ ሁለት ሰው አንደተተኪ እንኳን ሳያበቁ ማለፋቸው የአመራራቸውን ድክመት ያሳያል፡፡ እርሳቸው የጥቂት ዓመታት መሪ ቢሆኑ ኖሮ በቂ ጊዜ ሳይኖራቸው ነው ብለን እናስተባብልላቸው ነበር ነገር ግን 30 ዓመት በላይ በመሩት ፓርቲ ውስጥ ለሚተካቸው መጥፋት መልሶ ራሳቸውን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚሁ አጋጣሚ የሰሞኑን የመንግስት ባለስልጣናት አቶ መለስን ሲያወድሱ የፓርቲያቸውን ባዶ ሜዳ መቅረትም እየነገሩን ነበር፡፡ የአቶ መለስ ታታሪነት አንጂ ተተኪ ያለመኖር ታሪክ የሚኮራበት መሆን አልነበረበትም፡፡

ለታታሪው ኢትዮጵያዊ አቶ መለስ ዜናዊ ነፍስ ይማር፡፡ በፕሮፖጋንዳ ብዛት ራሳቸውን እያጠፉ ላሉት ኢቴቪና ዘመድ አዝማድ ሚዲያዎችም ነፍስ ይማር!

No comments:

Post a Comment