Monday, September 24, 2012

ሰለጠቅላይ ሚንስቴር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፦ ያልተባሉና ያልተነገሩ


በቀድሞ ተማሪያቸው
I.      መግቢያ፡-

የጠቅላይ ሚንስተር አቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሞት ተከትሎ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያልተጠበቀና ያልታሰበ ወደስልጣን መምጣት ብዙዎችን ያስገረመ ጉዳይ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የዚች ሃገር  ጉዳይ  ያገባኛል ያሉ ብዙ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማሀበራት እና ሌሎችም የሳቸው ሹመት ለሃገሪቱ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችልና ምናልባትም ፈጣሪ ለዚች ሃገር ለውጥ ያስቀመጣቸው ሊሆኑ ሁሉ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገውባቸዋል፡፡ እኔም ከነዚህ ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡



ስለ ጠቅላይ ሚንስተር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ ድህረገጾችና ጋዜጦች ብዙ የተባሉና የተጻፉ ሲሆን አብዛኞቹ የሳቸውን በጎና ጥሩ ጎኖች የሚዳሰሱ ናቸው፡፡ ከዚህም መካከል ሰውየውን ጥሩ ሃይማኖተኛና፣ ፈርሀ እግዚአብሔር ያላቸው፣ የመልካም ስነምግባር ባለቤት፣ ቅንና ተንኮል የሌለባቸው፣ ጥሩ አስተማሪና አስተዳዳሪ የነበሩ፣ ቤተሰባቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ፣ ሰውን የማይጎዱ፣ ምንም አይነት ሱስ የሌለባቸውና ሙስናን የሚጸየፉ ወዘተ… የሚሉ ናቸው፡፡ እኔም ከሞላ ጎደል በነዚህ የሰውየው ባህሪያቶች እና ገለጻዎች እስማማለሁ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሰሞኑን በፉርቹን ጋዜጣ እና  በቪኦኤ ራዲዮ ጣቢያ በአርባ ምንጭ  የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (አሁን አርባ ምንጭ ዩንቨርስቲ) ሁለት የቀድሞ የስራ ባልደረቦቻቸው (መምህራን የነበሩት ዶክተር ዮሴፍና ዶክተር ስለሺ በቀለ) እና አንድ የቀድሞ ተማሪ (አቶ ኤርሚያስ) ስለዚሁ ጉዳይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እነዚህም አስተያየቶች ስለ አቶ ኃይለማርያም ጠንካራና በጎ ጎኖች የሚያወሱ ሲሆኑ አሁንም የዚህ ፅሑፍ ጸሐፊ ከሞላ ጎደል በተሰጡት አስተያየቶች ይስማማባቸዋል፡፡

እንደማንኛውም ዜጋ እና የርሳቸው የቀድሞ ተማሪ በአቶ ኃይለማርያም ሹመት እኔም በበኩሌ ከመገረምም አልፌ ከተደሰቱና የለውጥ ጭላንጭል ከተያቸው ወገኖች ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ከባለሙያነታቸውም፣ የአካደሚ ሰው ከመሆናቸው፣ በቅርብም ቢሆን በፖለቲካውና በመንግስት ስልጣን ከነበራቸው ተሳትፎ እና ልምድ እንዲሁም ከዳራቸው /Background/ አንጻር ይቺን ሃገር ሊመሩ፣ ሰላም እና ለውጥ ሊያመጡና ሊያሳድጉ ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከዚህም አንጻር ይህንን ጹሑፍ በዚህ ሰዓት መጻፍ አልፈለኩም ነበር፡፡ ነገር ግን በምዕራቡ ዓለምም እንደተለመደው አንድ መሪ ወደስልጣን ሲመጣ ለዚያውም የዘጠና ሚሊዮን ህዝብ መሪ ቀርቶ እያንዳንዱ በጎና ደካማ ጎን ከልጅነት ጀምሮ አስተዳደጉና ገጠመኙ ባህሪና የሥራ ፀባ በአጠቃላይ የህይወት ታሪኩ በደንብ ተደርጎ እንደሚዳሰስና ትንተና እንደሚሰጥበት እናውቃለን፡፡

እኔም የዚህ ጽሑፍ ጻሐፊ አቶ ኃይለማርያምን ከ1985-1989 ዓ.ም ለአምስት አመታት ያህል በተማሪነት የማውቃቸው ስሆን ከላይ ከዘረዘርኳቸው በብዙ ሰዎች ከተባሉት በጎ ጎኖች ውጭ ያሉትን እና በተለያዩ ሚዲየዎች ብዙ ያልተነገሩትነና ያልተባሉትን ለመጻፍ እወዳለሁ፡፡

II.     የአቶ ኃይለማርያም ወደ አካዳሚክ ስልጣን አመጣጥ፡-

አቶ ኃይለማርያም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ1984 ዓ.ም ከፊላንድ ታምፒር /Tampere/ ዩኒቨርስቲ በውሃና አካባቢ (ሳኒተሪ) ምህንድስና /Water & Environmental (Sanitary) Engineering/ ይዘው እንደተመለሱ በወቅቱ በአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዲን በነበሩት እና በ1997 ዓ.ም ምርጫ ወቅት ደግሞ የኢዴፓ ሊቀመንበር እና የቅንጅት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር በነበሩት በዶክተር አድማሱ ገበየሁ ረዳት ሬጅስትራር ሆነው ተሹመዋል፡፡

በዚያን ጊዜ የኢንስቲትዩቱ ሬጅስትራር የነበሩት የስታስቲክስ ምሩቅ የሆኑት አቶ የማነ ናቸው (አሁን በሕይወት የሉም)፡፡ እንደ አቶ ኃይለማርያም በተመሳሳይ ጊዜ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዝ ሀገር ይዘው የመጡት አቶ አባቡ ተክለማርያም (አሁን ዶክተርና በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ) እና አቶ ስለሺ በቀለ ( አሁን ዶክተርና አፍሪካ ህብረት ውስጥ የሚሰሩ) በምክትል ዲንነት እና በምርምርና ህትመት /Research & Publication/ አስተባባሪነት በቅደም ተከተል ተሹመዋል፡፡  ይህ ሹመት በወቅቱ ረዳት ሬጅስትራር ለነበሩት ለአቶ ኃይለማርያም ስላልተዋጠላቸው ቅሬታን ፈጥሮባቸዋል፡፡ አንድም በትምህርት ደረጃም ሆነ በሥራ ልምዳቸው /Seniority/ ከማይበልጧቸው የሚያንሰ ሹመት ማግኘታቸው ሲሆን ሌላው ደግሞ የብሔር አድልዎ ተደርጎብኛል በሚል ስሜት ነው፡፡ ዶክተር አድማሱ የሚፈልጋቸውንና የራሱን ብሔር ተወላጆች  (አማራ) ሲሾም እኔ ከደቡብ አካባቢ ስለሆኩ ጎደቶኞል በሚል ስሜት መሆኑ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ ኃይለማርያም ዶክተር አድማሱ ከኢንስቲትዩቱ የሚነሳበትን መላና ዘዴ ይፈልጉ ነበር፡፡ በኋላም በታህሳስ ወር 1985 ዓ.ም በወቅቱ የተ.መ.ድ ዋና ፀሐፊ የነበሩት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሪ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ተከትሎ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተነሳው የተማሪዎች አመጽ ዶክተር አድማሱ አመጹን ደግፈሃል እና አበረታተሃል በሚል ምክንያት ከዲንነቱና ከሃላፊነቱ ተንስቷል፡፡ አመጹን ከማይደግፉ ተማሪዎች ኢንፎርሜሽን በመውሰድና ለደህነንትና ፖሊስ አካላት በማቀበል (ዶክተር አድማሱ ለአንድ ቀን ታስሮ ነበር) ዶ/ሩ ከቦታው እንዲነሳና እንዲባረር ያደረጉት አቶ ኃይለማርያም እና በወቅቱ የኢንስቲትዩቱ አስተዳደርና ፋይናንስ ኃላፊ የነበረ አንድ የህወሀት አባል ናቸው፡፡

በዶክተር አድማሱ ምትክ በወቅቱ ምክትል ዲን የነበሩት አቶ አባቡ ተጠባባቂ ዲን ሆነው  ሲሾሙ አቶ ሃለማርያም ደግሞ ምክትል ዲን ሆኑ፡፡አሁን የአቶ ኃይለማርያም  ዋናው የስልጣን ግልበጣ ሴራ ይጀምራል፡፡ አቶ አባቡ ለትምህርታዊ ወርክሾፕ ወደ እንግሊዝ ሃገር በሄዱበት ጊዜ አቶ ኃይለማርያም  በሰሜን ኦሞ ዞን እና በክልሉ ባለስልጣናትና ቁልፍ  የፖለቲካ ሰዎች በመታገዝ እሳቸው የአካባቢው ብሔር ተወላጅ እያሉ እንዴት የሌላ ብሔር (አማራ) ሰው ስልጣን ይይዛል ብለው ሎቢ /Lobby/ በማስደርግና በተደረገ ማግባባት ወ/ሮ ገነት ዘውዴ (በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትር) አቶ አባቡን በማውረድ አቶ ኃይለማርያምን የኢንስቲትዩቱ ዲን ያደርጎቸዋል፡፡ ይህም የሆነው አቶ አባቡ በውጪ ሃገር በነበሩበት ጊዜ ሲሆን ወደ ኢንስቲትዩቱ ግቢም አንደተመለሱ ስብዕናቸውን በሚነካ መልኩ በአንድ ቀን ውስጥ በኃላፊነት ይዘውት የነበረውን መኪና እንዲያስረክቡና የዲኑን መኖሪያ ቤትም ለቀው እንዲወጡ በቀደሞ ምክትላቸው በአቶ ሃይለማርያም ታዘው ነበር፡፡ ይህም አቶ ሃይለማርያም ምን ያህል ሥልጣን እንደሚወዱና ለሥልጣን ጓጉተው እንደነበር ያሳያል፡፡

በነገራችን ላይ አቶ ሃይለማርያም ፖለቲከኛ ለመሆን ያሰቡትም፣ ግኝኙነትም የጀመሩት፣ ወደ ፖለቲካ ውስጥም የገቡት በዚሁ አጋጣሚ ነበር፡፡ ይህም ማለት ማለትም በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ያለውን የስልጣን ፍትጊያ ለማሸነፍ እና ዲንም ለመሆን ከነበራቸው ፍላጎትና እሱንም በድል ለመወጣት ከደቡብ ፓርቲ (ደኢህዴን) ድጋፍ ለማግኘት ብለው ነበር፡፡ በተጨማሪም የዞኑና የክልል ፖለቲከኞች አቶ ኃይለማርያም የዲንነቱን ቦታ እንዲያገኙ በወቅቱ እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማርያምን ፖለቲካ ውስጥ ያስገባቸው ዋናው ምክንያት እና ዛሬ ለደረሱበትም ትልቅ ቦታ መነሻ የሆነው ያ የኢንስቲትዩቱ ዲን የመሆን ፍላጎታቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡
     
III. የአቶ ኃይለማርያም የአመራር መንፈስ

የኢንስቲትዩቱ ዲን ከሆኑ በኋላ ስልጣናቸውን በደንብ ለማደላደል የሚፈልጓቸውንና የሚቀርቧቸውን ሰዎች በተዋረድ ይሾሙም ነበር፡፡ አቶ ኃይለማርያም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን አባል የሆኑበት  ቤተክርስቲያን ግን ከዋነኞቹ ወንጌላዊ አብያተክርስቲያናት ለየት ያለና በሦስቱ ስላሴዎች የማያምን የኢትዮጵያ ሃዋርያ (Apostolic) ቤተክርስቲን (በተለምዶ only Jesus የሚባሉት) ነው፡፡ እናም በወቅቱ ስልጣን ሲሰጡ የሃዋርያ ቤተክርስቲያን አማኝ ካለ ቅድሚያ ይሰጡና ያዳሉ ነበር፡፡ እርሳቸውም አብዛኛውን ጊዜ የሚያስተምሩት የ/Water supply & West Engineering /ኮርስ ሲሆን እኔም በእሳቸው ሁለት ኮርስ ተምሬአለሁ፡፡ በጣም ጎበዝና ጥሩ የአካደሚክ  ዕውቀት የነበራቸው ሰው እንደሆኑ ልመሰክርላቸው እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ የማልክደው ሀቅ ቢኖር በአስተዳደጋቸው ይሁን፣ ከአሁን በፊት በደረሰባቸው ነገር ለሰሜን አካባቢ ሰው (በተለይ ለአማራ ብሔር ተወላጆች) ትንሽም ቢሆን ጥላቻ ነበራቸው፡፡ ምዕራባውያን የበታችነት ስሜት(ኢንፌሪየሪቲ ኮምፕሌክስ)  እሚሉት አይነት ነገር ይሰማቸው ነበር፡፡ ይህንንም በተለያየ አጋጣሚ ያንጸባርቁት ነበር፡፡ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ የቀድሞ ገዢዎች፣ ሰሜነኞች፣ ጨቋኞች እያሉ የጨቆኝና የተጨቋኝ አይነት ክርክር /Argument/ ያበዙ ነበር፡፡ በተጨማሪም በአስተዳደራቸው ጊዜም ቢሆን የተወሰነ አምባገነንነት ይታይባቸው ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በኢንስቲትዩቱ ባህል መሰረት  በየአመቱ ከ1-3ኛ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ለረዳት አስተማሪነት ይቀጠራሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ዲን ከሆኑ በኋላ ግን መቀጠር ያለበት እሳቸው ከሚፈልጉት ብሔር ውጪ ከሆነ በተለያየ ዘዴ እንዳይቀጠሩ ያደርጉ ነበር፡፡  በዚህ ሁኔታ ብዙ እዛው ቀርተው ማስተማር የነበረባቸውና ዛሬ ትልቅ ቦታ የደረሱ የቀድሞ ተማሪዎች ምስክር ናቸው፡፡ ይህም ምን ያህል አቶ ሃይለማርያም እርሳቸው ጨቋኝ ነበሩ ከሚሏቸው ብሄሮች ጋር ችግር እንደነበረባቸው ያሳያል፡፡

በተጨማሪም  አቶ ኃይለማርያም ዲን በነበሩበት ወቅት መታየትም የሚፈልጉ ሰው ነበሩ፡፡ በተቻላቸው መጠን ዜና ሊሆን የሚችል ነገር እየሰሩ በተለያየ አጋጣሚ ስማቸውንና አርባምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን በኢቲቪና በሬዲዮ እንዲታወቅ ያደርጉ ነበር፡፡ ይሄም በደቡብ ፓርቲና በመንግስት ባለሥልጣናት አይን ውስጥ እንዲገቡና ለፓርቲው ከፍተኛ ሃላፊነት እንዲመለመሉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ነው የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሸሙት እና የፓርቲውም ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት፡፡

IV. አቶ ኃይለማርያም ያለፉባቸው ፈተናዎችና ያጋጠሟቸው ተግዳራቶች

አቶ ኃይለማርያም በህይወታቸው ፈጽሞ ሊረሱት የማይችሉትና ምናልባትም እግዚአብሔር ረድቷቸው የተወጡት፤ ያን ወቅት በብቃት ባያልፉ ኖሮ ይቅርና የቀድሞ የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት ከዚያም አልፎ የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ቀርቶ ከመምህርነት ሙያቸውና (ነገር ግን ዶክትሬታቸውን ሊይዚ ይችሉ ይሆን እንጂ) ከአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አይወጡም ነበር የሚያስብል አንድ ተግዳሮት ደርሶባቸው ነበር፡፡ እሱም በ1988 ዓ.ም ሁለተኛ ሴሚስተር መጀመሪያ አካባቢ በኢንስቲትዩቱ የተነሳው የተማሪዎች አመጽ ነው፡፡ ይህም አመጽ በዚያን ወቅት በነበረው የአቶ ሃይለማርያም  አስተዳደራዊና የኢንስቲትዩቱ አካዳሚካዊ ችግሮች ላይ ተንተርሶ የተቀሰቀሰ ሲሆን አቶ ኃይለማርያምን፣ ምክትላቸውን እና አስተዳዳርና ፋይናንስ ኃላፊውን ከስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ነበር፡፡

በወቅቱ ተማሪዎች በፖሊስ ተንገላተዋል፡፡ ከ20 የማያንሱ በተማሪ የተመረጡ መሪዎች ለ21 ቀን በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ እስርቤት ታስረዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም የዞኑን አስተዳዳሪና ፖሊስ ሃላፊ እያመጡ የተማሪ መሪዎችን አስፈራርተዋል፡፡ የተማሪዎቹን ህጋዊና አግባብ ያለውን ጥያቄን በማጣመም ተማሪዎቹ ምንም ዓይነት ችግር የለባቸውም፤ ችግራቸው ሌላ ብሔር (ወላይታ) አይገዛንም፤ ዲን አይሆንም ብለው ነው በማለት ተማሪውን ከአካባቢው ህበረተሰብ ጋር ለማጣላትና ለማጋጨት ሞክረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተማሪው በረብሻው ምክንያት ግቢውን ለቆ ሲወጣ እንኳን የከተማው ህዝብ እንዳይተባብረው አድረገዋል፡፡ ተማሪው ከግቢው ወጥቶ ወደ አካባቢው ከሄደ ከአንድ ሳምንት በኋላ ትምህርት ሚኒስቴር በሚዲያ ጥሪ አድርጎ ተማሪዎቹ ተመልሰው ወደ ግቢ እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ዶክተር ተክለሃይማኖትን (በዚያን ጊዜ ምክትል ትምህርት ሚኒስትር) መጥተው ተማሪውን አወያይተውና አረጋግተው ትምህርት እንዲጀመር ሲደርግ፣ የተማሪውን ጥያቄ ባልመለሰ መልኩ ምንም አይነት የኢንስቲትዩቱ ባለስልጣን አቶ ሃይለማርያምን ጨምሮ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በስልጣን እንዲቆዩና እንዲቀጥሉ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ታላቅ ባለውለታ ምናልባትም ዶክተር ተክለሃይማኖት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ወቅቱ ብዙ የዪነቨርስቲ ተማሪዎች ያምጹ የነበረበት ጊዜ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር ከሞላ ጎደላ የተማሪዎቹን ጥያቄ ለመመለስ የየግቢውን ዲኖችና ፕሬዝዳንቶች ያነሳባት ጊዜ ነበር፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ አዳማ ድረስ ሄደው በተማሪዎች ጥያቄ መሰረት የናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅ ዲንን በወቅቱ ከሃላፊነት አንስተዋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ግን ያን ማዕበል በዶክተር ተክለሃይማኖት እገዛና ትብብር አልፈዋል፡፡ ማን ያውቃል ፈጣሪ ይህን ትልቅ ቦታና ስልጣን ስላየላቸው ይሆን?

ከዚህ በተረፈ በተማሪዎች ረበሻ ወቅት አቶ ሃይለማርያም ከስልጣን እንዲወርዱ በጣም ሲጥርና ተማሪዎችን ሲያስተባብር የነበረ አንድ የተማሪዎች መሪ እንደነገረኝ ተማሪው ትምህርቱን ጨርሶ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ውጪ አገር የትምህርት እድል ለማግኛት የድጋፍ ደብዳቤ /Recommendation Letter/ እንዲጽፉለት ሲጠይቃቸው ተማሪው ባደረገው ነገር ምንም ቂም ሳይዙና ቅር ሳይላቸው በደስታ ጥሩ የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈውለት በዚያም መሰረት በውጪ ሃገር እስኮላር ሽፕ አግኝቶ 2ኛ ድግሪውን ተምሮ እንደመጣ አጫውቶኛል፡፡

V. ማጠቃለያ

ከዚያ በኃላ በነበሩ ጥቂት አመታት አቶ ኃይለማርያም በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ያላቸውን የሥልጣን ማዕከል ያደላደሉበትና በመሀልም እሳቸውን ከአካዳሚክ ሀላፊነት ወደ ፖለቲከኛነት የሚወስዳቸውን ሽግግር የፈጸሙበት ወቅት ነበር፡፡ የተማሪዎቹም አመጽ ከተደረግ ከ3 ዓመት በኋላ አቶ ሃይለማርያምን ዛሬ ወደ ደረሱበትን ስልጣን ትልቅ ቦታ አንድ ብለው ወደጀመሩበት የስልጣን ጉዞ ወደ ደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት ቢሮ ተሹመው ሄዱ፡፡ ከሐዋሳው ሹመት በኋላ የቆዩበት ሁኔታና ወደአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚንስቴር ቢሮ እንዴት ሊመጡ እንደቻሉ እንደቻሉ ከዚያም አሁን እስከተሾሙበት ቁጥር አንድ የሀገሪቱ የሥልጣን እርከን እንዴት እንደደረሱ በዛም ያለፉባቸውን ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ደግሞ ሌላ እንደ እኔ ለማየትና ለመታዘብ እድሉ የገጠመው ሰው ከዚህ ይቀጥልበት፡፡


እስከዚያው ቸር ይግጠመን፡፡
ጠቅላይ ሚንስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኃይለማርያም የቀድሞ ተማሪ

 ጸሐፊውን ለማግኘት በዚህ civil.at.aait@gmail.com አድራሻ ይጠቀሙ፡፡  

1 comment: