Monday, September 17, 2012

እኛና ሶማሊያ




ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት አሁን ሶማሊያ ተብላ የምትጠራውን ሀገር አብዛኛውን ግዛት ያስተዳድር የነበረው አሕመድ ግራኝ በሰሜን የሚያዋስኑት ባብዛኛው ክርስትያንያዊ ከሆኑ አስተዳደር ግዛቶች ላይ ያካሄደው አስከፊ ወረራ አሁን ኢትዮጵያ ተብላ በምትጠራው አገራችንና በጎረቤት አገር ሶማሊያ መካከል ጊዜ እየጠበቀ ለሚያገረሸው ጦር መማዘዝ እና ቁርሾ የመጀመርያው አድርገው ይወስዱታል አንዳንድ ተንታኞች፡፡ 

ሁለቱ አገሮች ዘመናዊ በሆነ ማዕከላዊ መንግስት መተዳደር ከጀመሩበትና ሶማሊያ ከቀኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ ሁለት ጊዜ በይፋ ጦር ተማዘዋል፡፡ ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት ጋር አብሮ ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግስት ካጣች በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ለደህንነቴ ስጋት እየፈጠሩ ነው ያላቸው ታጣቂዎች ላይ በተለያየ ወቅት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ጥቃቱን የሚፈፅመው ድንበር አካባቢዎች ላይ ወይንም ድንበር አልፎ ከገባም ጥቃቱን ፈፅሞ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነበር ለቆ የሚወጣው፡፡ ጥቅሙን የሚያስጠብቁ የጎሳ ሪዎችንም ያስታጥቃል በሚል የኢትዮጵያ መንግስትን ክስ የሚያቀርቡበትም ጥቂት አልነበሩም፡፡

እንደ ኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር በሰኔ ወር 1998 ዓ.ም የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረት በሚል እራሱን የሚጠራ ቡድን የሶማሊያን ዋና ከተማ ሞቃዲሹንና አብዛኛውን የአገሪቱን ደቡባዊ ግዛቶች ተቆጣጠረ፡፡ እንደ ብዙዎች ዕይታ በዚያድ ባሬ የሚመራው መንግስት ወድቆ አገሪቷ መንግስት አልባ ከሆነች በኋላ ሶማሊያ ለመጀመሪያ ጊዜ አንፃራዊ ሰላም እና ሰፊ ግዛት የሚያስተዳድር መንግስት ያገኘችው ሕብረቱ ሞቃዲሹን በቁጥጥር ስር ሲያውል ነበር፡፡

ሕብረቱ በማዕከላዊ እና ደቡባዊ የሶማሊያ ግዛቶች ያገኘውን የበላይነት በሰሜን የሀገሪቱ ግዛቶች መድገም አልቻለም፡፡ ለዚህም ተጠያቂ ያደረገው በአካባቢው ታጣቂዎችን ትረዳለች ያላትን የኢትዮጵያን መንግስት ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቅዱሳዊ ጦርነት (ጂሃድ) ኢትዮጵያ ላይ ማወጁን ሕብረቱ በይፋ አስታወቀ፡፡

ጦርነት የታወጀባት የኢትዮጵያ መንግስትም ይህ አደጋ ግልጽ እና በጊዜ መፍትሔ ሊሰጠው የሚገባ ነው ሲል ፓርላማውን ሞግቶ ‹‹ማንኛውን አስፈላጊ እርምጃ›› እንዲወስድ የአብላጫ ድምፅ ይሁኝታ አገኘ፡፡ በታህሳስ ወር 1999 ዓ.ም ከሕብረቱ ኃይሎች ጋር በሶማሊያ ግዛት ውስጥ ውጊያ እንደጀመረ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ አደረገ፡፡

ዓመት ከፈጀ ውጊያ በኋላ በኢትዮጵያ ወታደሮች የሚደገፈው የሶማሊያ ሽግግር መንግስት ሞቃዲሹን ተቆጣጠረ፡፡ በወቅቱ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ውጊያው በጦርነት በተሞላው ሕይወታቸው ካዩት ውጊያዎች ሁሉ ከፍተኛ የሆነ አለመመጣጠን የጎላበት እንደነበር ተናግረው ነበር፡፡ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን እንዳጡ ግን ለመናገር ኃላፊነት (ግዴታ) እንደሌለባቸው ለማስረዳትም ሞክረው ነበር፡፡

ጊዜ በገፋ ቁጥር እና የኢትዮጵያ ጦር ወደሶማሊያ ዘልቆ እንዲገባ ምክንያት የነበረው የሕብረቱ ኃይሎች የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታ ከነበረው ከኪስማዩ ግዛት ተሸንፈው ከተባረሩ በኋላ ‹የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ለቆ የሚወጣው መቼ ነው?› የሚለው ጥያቄ በተደጋጋሚ መሰማት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን ዓላማዬን ጨርሻለሁና ለቅቄ ልውጣ የሚል አዝማሚያ አልታየበትም ነበር፡፡ 

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ለሀገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ብቸኛ አማራጭ አድርገው ለሚያዩት ሶማሊያዊያንና ጉዳዩ ያገባናል ለሚሉ የውጭ ኃይሎች የኢትዮጵያ ጦር በሸሪፍ ሼክ አሕመድ የሚመራው የሽግግር መንግስት ሞቃዲሹን እንዲቆጣጠር በማገዙ ደስተኛ እንደነበሩ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ጦሩ በሶማሊያ የነበረውን ቆይታ ባራዘመ ቁጥር አብዛኛው ሶማሊያዊያን ቅሬታቸው እየበረታ ሄደ፡፡ እንደውም አንዳንድ አክራሪ (አክራሪ ያሰኛቸው ምን ይሆን? የኢትዮጵያ መንግስት…??) የሚባሉ ታጣቂ ቡድኖች ከሽግግር መንግስቱ ጋር ለመደራደር የኢትዮጵያ ጦር አገሪቱን ለቆ መውጣቱን እንደቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ጀመሩ፡፡

በዚህ መሀል ነበር ተሸንፎ የተበታተነው ሕብረቱ ኃይል ከመካከለኛው ምስራቅ ጠንከር ያለ ‹የእንርዳህ› ጥሪ የቀረበለት፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያ የአገሪቷን አለመረጋጋት እና መንግስት አልባነት እንደሽፋን ተጠቅሞ እግሩን ወደ ሶማሊያ ማስገባት የሞከረው አል-ቃይዳ ሶማሊያዊያን ከመካከለኛው ምስራቅ መጤ አክራሪ የእስልምና አስተምህሮት ይልቅ ከባህላቸው ጋር የተዋሀደውን እስልምና በመምረጣቸው ሳይሳካለት ቀርቶ ነበር፡፡ ዓለም አቀፋዊ ጅሃድ ሶማሊያውያን ሕይወታቸውን ለመስጠት የሚፈቅዱለት ጉዳይ ሆኖ አላገኙትም ነበር፡፡ ከዓሥር ዓመት በኋላ ግን አል-ቃይዳ ጥሩ እድል ተፈጠረለት፡፡ ‹ከክርስቲያን አገር› የመጡ ወታደሮች ላይ ለመተባበር ለሶማሊያውያን ጥያቄ ሲያቀርብ እንደቀድሞ ላለመቀበል ምንም ምክንያት አልነበራቸውም - ሶማሊያዊያኑ፡፡

ታድያ የ1999ኙ የሶማሊያ ወረራ ከሁለት ዓመት ተልዕኮ ቆይታ በኋላ ተጠናቆ የኢትዮጵያ ጦር በጥር ወር 2001 ዓ.ም ወደ አገሩ ሲመለስ ሶማሊያ ውስጥ አል-ሸባብ ለሚባል ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ላለው እስላማዊ አክራሪ ቡድን ማንሰራራት ምክንያት ሰጥቶ ነበር፡፡
ሶማሊያውያን ወጣቶችን (ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ አባላቱ እድሜ ከ20 ዓመት በታች ነው፡፡ ‹አገራችንን ከክርስቲያኖች ወረራ እንከላከል› በሚል ስሱ (sensitive) መመልመያ መቀስቀስ የቻለው አል-ሸባብ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማሊያን መልቀቃቸውን ተከትሎ ድሮም ቢሆን በቅጡ ያልተደራጀውን የሽግግር መንግስት ጦር በቀላሉ በማባረር በዛ ያሉ የአገሪቱን ግዛቶች በጁ አስገብቷል፡፡

የኢትዮጵያ ጦር ከመውጣቱ በፊት በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ወደ ሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል የሰላም ስምምነት አካል ያልሆነውን አል-ሸባብን ለመቆጣጠር አልቻለም ነበር፡፡

የአል-ሸባብን ማንሰራራት እና እያደር መጠናከር ተከትሎ፣ መጀመሪያ የኬንያ ጦር በስተደቡብ በኩል ‹ድንበር ጥሰው ዜጎቼን እያፈኑ› ያስቸገሩ ታጣቂዎችን ፍለጋ በሚል ምክንያት ከዚያም የኢትዮጵያ ጦር ‹የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይልን እንዲረዳ› ከኢጋድ አባል ሀገራት የቀረበለት ጥያቄን ተቀብሎ በሕዳር ወር 2004 ዓ.ም በይፋ ወደ ሲማሊያ ድጋሚ አመራ፡፡ ይህ ጦር አሁንም እዛው ያለ ሲሆን መቼ እንደሚመለስም በይፋ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

የሶማሊያ መፍትሔ - ችግሩን በሚገባ መረዳት

ሶማሊያውያን 275 አባላት ያሉት ብሔራዊ ምክር ቤት መርጠዋል፡፡ ምክር ቤቱም ከማዕከላዊ መንግስቱ መውደቅ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በሶማሊያ ምድር በተደረገ ምርጫ ሀሰን ሼክ መሐሙድን የአገሪቷ ፕሬዝዳንት አድርጎ መርጧል፡፡

ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትልቅ ወጣ ውረድ ያለው ኃላፊነት ነው የተሰጣቸው፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ የተረጋጋ ሰላም አግኝታ የማታውቀው ሶማያን ሰላም መስጠት ከኃላፊነታቸው ሁሉ የላቀው ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ሁሉንም ሶማሊያውያን የሚያግባባ ሐሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሁሉንም ሶማሊያውያን ማለት አል-ሸባብንም ይጨምራል፡፡ ሶማሊያ ውሰጥ የተረጋጋ ሰላምን ለማምጣት የአል-ሸባብን መውደቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያዩ ሁሉ ስህተት እየፈፀሙ ነው፡፡ ምን አልባት አል-ሸባብን ወግቶ ማሸነፍ እና ወታደራዊ ድርጅቱን ቅርፅ ማሳጣት ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሁለት አደጋዎች ተከትለው የመምጣታቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡

አንደኛ፤ ተደራጅቶ በመዋጋት የተሸነፈው አል-ሸባብ የትግል ቅርፁን ቀይሮ ወደ ሰርጎ ገብ ጥቃት መጣልና ወደ ሰፊ አጥፍቶ ጠፊ ጥቃቶች ፊቱን ሊያዞር ይችላል፡፡ የሶማሊያ የመከላከያና ፖሊስ ኃይል ደግሞ እየተሸሎከሎከ ጥቃት የሚፈፅም ኃይልን ተከታትሎ ሊያድን የሚያስችል በቂ አቅም ስለሌላቸው የሰላም መፍትሔውን በዕጅጉ ሊያርቀው ይችላል፡፡

ሁለተኛ፤ ሶማሊያ ውስጥ እስካሁን እንዳየነው የአንድ ታጣቂ ኃይል መውደቅ በሌላ ታጣቂ ኃይል ይተካል፡፡

ስለዚህም ሶማሊያውያንን ወደ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት አል-ሸባብን ማካተት ምርጫ የሚኖረው ጉዳይ አይመስልም፡፡ ምን አልባት አል-ሸባብ እራሱ ወደ ድርድር አልመጣም ብሎ አሻፈረኝ ሊል እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም፡፡ ይህንንም ለማሸነፍ ግን አማራጮች አሉ፤

በመጀመርያ የአል-ሸባብ ጠንካራ መመልመያ የሆኑትን የውጭ ኃይሎች በተለይም የኢትዮጵያ ወታደሮችን ወደ አገራቸው በመመለስ (በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ያለው ኃይል ሲቀር) አል-ሸባብን የመመልመያ ምክንያት ማሳጣት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደድሮ የመመልመል አቅም የማይኖረው አል-ሸባብ የተለሳለሰ አቋም ሊይዝ ይችላል፡፡

ሁለተኛውና ተያይዞ መሰራት ያለበት ለሶማሊያዊያን ወጣቶች ጠብ-መንጃ አንግቶ ከመዋጋት የተሻለ ምርጫ መስጠት ነው - የሶማሊያን መልሶ ግንባታ ቢያንስ ቢያንስ አንፃራዊ ሰላም ባሉባቸው ቦታዎች በማፋጠን፡፡ ይህ ደግሞ አሁን አደራጅቶ የያዘውን ወጣት ልብ ወደ ቀድሞ ለአል-ቃይዳ አስቸጋሪ ወደነበረው ሶማሊያዊ አስተሳሰብ በመመለስ አል-ሸባብን የኃይል መሰረት በማናጋት ያዳክመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚና

አሁን ሶማያ ለደረሰችበት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ማንም ሊከፍለው ያልደፈረውን መስዕዋትነት ከፍለዋል፡፡ አሁን ተራው እግራችንን ወደ ሶማሊያ እንድንሰድ ከዳር ሆነው ያበረታቱን ምዕራባዊያን ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን መፍትሔዎች ለማስፈፀም ፍላጎቱ እንጂ አቅሙ የለንም (በተለይም መልሶ ግንባታውን በተመለከተ)፡፡

‹‹እስከ አሁን መስዕዋትነት የከፈልንበት የሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት ዋጋ እንዳያጣ እና አሁን የተገኘው ተስፋ በጥዋቱ እናዳይጨልም አጥብቀን እንፈልጋለን፤ ስለዚህም ለመሳርያ መግዣ ለማዋል የማትሰስትን የፈረጠመ የገንዘብ አቅማችሁን ተጠቅማችሁ ለሶማሊያ መልሶ ግንባታ ማዋል የሚገባችሁ ጊዜ አሁን ነው›› የሚል ኮስተር ያለ የውለታ ምላሽ ጥያቄ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን እንጠብቃለን፡፡

No comments:

Post a Comment