Thursday, September 13, 2012

“አራማጅነት” በኢትዮጵያ




ኤዶም ካሣዬ የኢትዮጵያ አካባቢ ጋዜጠኞች ማሕበር አባል የሆነች ለአካባቢ ተቆርቋሪ ጋዜጠኛ (Environment Journalist) ነች፡፡ ምንም እንኳን በአጋጣሚ ያለችበት አካባቢ በቆሻሻ የተበከለ ቢሆንም እንኳን የወረቀት ቁርጥራጭ፣ የማስቲካ ልጣጭ፣ ያገለገለ ሶፍት ጨምሮ ምንም ዓይነት አገልግሎት የሰጠ ቁስ መንገድ ላይ አትጥልም፤ አብረዋት ያሉትንም እንዲጥሉ አትፈቅድም፡፡ በየቦታው የቆሻሻ ማስወገጃ ከረጢት (bin) ወይም ገንዳ በቀላሉ ስለማይገኝ በቦርሳዋ እንዲህ ዓይነቶቹን መወገድ ያለባቸው ኮተቶች ማጨቅ የተለመደ ጉዳይዋ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የፋቀችውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ካርድ እዚያው የገዛችበት ሱቅ ትታ ነው የምትወጣው፡፡ የላስቲክ ማሸጊያ ካላቸው ቁሳቁሶች ይልቅ የወረቀት ማሸጊያ ያላቸውን መግዛት ትመርጣለች፣ በጋዜጠኝነት ሙያዋ በተገኘው አጋጣሚ ስለ አካባቢ ነክ ጉዳዮች ትጽፋለች፣ አባል በሆነችበት የተፈጥሮን አድን ኢትዮጵያ ማኅበር አማካይነት በየዓመቱ ለችግኝ ተከላ ትሳተፋለች፣ የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ ከሚንከባከቡ የአካባቢ ሰዎች ጋር ትገናኛለች፡፡

በአካባቢ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሕይወት መስኮች እንደ ኤዶም ጥልቅ ስሜት ያላቸው በርካታ ሰዎችን ከፍ ሲልም ማህበረሰቡንም እዚህ ደረጃ ለማድረስ ከሚያስፈልጉ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች መሀከል አራማጅነት(Activism) በዋናነት ይጠቀሳል::

አገራችን፣ 80 በመቶ ሕዝቧ በዝናብ ውሃ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ አንፃር የአካባቢ ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳዋ ነው፤ ሆኖም በቁጥር የሚዘረዘሩ የአካባቢ ጉዳይ ‹አራማጆች› የሉባትም፣ ኢትዮጵያ ፈርጀ ብዙ የባሕል አብዮት እንደሚያስፈልጋት ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ፣ ነገር ግን በተግባር እንቅስቃሴ አብዮቱን ለማራመድ የተዘጋጁ ሰዎች አይታዩም፡፡ ኢትዮጵያ እና መንግስቷ ከሰብአዊ መብት በደል ጋር በተደጋጋሚ ስማቸው ይነሳል፣ ነገር ግን ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ዓይን የሚገቡ አራማጆች የሉንም፡፡

“አራማጅነት” ምንድን ነው?

Activismን አንዳንዶች አራማጅነት፣ ሌሎች አቀንቃኝነት፣ አንዳንዶችም ተሟጋች እያሉ ይተረጉሙታል፡፡ እኛም በዚህ ጽሑፍ “አራማጅነት” የሚለውን ብንመርጥም ሌሎቹንም እንደየአገባቡ አስፈላጊነት ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ሌላው አቀንቃኝነት በተለይ advocacyን ይወክላል የሚል ነገር ቢኖርም፣ በሁለቱም (activism and advocacy) ውስጥ ተመሳሳይ ሚናዎች ስለሚኖሩ በጥቅሉ አራማጅነት ያልነውን ተከትለን እንሄዳለን፡፡

አራማጅነት ቀጥተኛ የማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወይም አካባቢያዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት ነው ሲል ዊክፔድያ ይበይነዋል፡፡ የዚህ ለውጥ ‹አራማጆችን› (activistsን) ደግሞ ለአንድ ጉዳይ ድጋፉን ወይም ተቃውሞውን በተግባር የሚያሳይ ሰው ነው ይለዋል፡፡ ‹አራማጅነት› በጉዳዩ ላይ ሕዝባዊ ንቃትን (awareness) ማስጨበጥ፣ ደብዳቤዎችን ለፖለቲከኞች እና ለጋዜጦች ከመጻፍ ጀምሮ እስከ ማስተባበር እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እስከማድረግ (የተወሰኑ ሸቀጦችን አለመግዛት፣ ሰልፍ መውጣት፣ የጎዳና ተቃውሞ፣ አድማ እና ሌሎችም) ድረስ የሚዘልቁ የተለያዩ መገለጫ ተግባራቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡

አራማጆች ለምን?

አራማጆች የሚያስፈልጉባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፤ ዋነኛው የትኛውም ጠንካራ መንግስት ማኅበረሰቡ ውስጥ ፈጣን የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ነው፡፡ በአገራችንም ቢሆን የፀረ ኤችአይቪ፣ የትራፊክ ጽ/ቤት፣ የሴቶች ጉዳይ እና ሌሎችም ቢሮዎች ቢኖሩም ችግሮቹን መቆጣጠር ቀርቶ ለመቆጣጠር የቀረበ ሙከራ የተደረገበት ጊዜ አልታየም፡፡ ይህም የሚሆነው መንግስት የአስፈፃሚዎች አቅም ማነሱ፣ የአደረጃጀቱ ዴሞክራሲያዊነት ማነሱ፣ የትምህርት ፖሊሲው በማሕበራዊ ንቃት ዘርፍ ያነሰ ትኩረት መስጠቱ እና ሌሎችም ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ክፍተት የሚሸፍኑ አራማጆች እና አራማጅነት በሰፊው ይፈለጋሉ፤ በተለይም ለታዳጊ አገራት፡፡

ምን አይነት አራማጅነት?

‹‹አራማጅነት›› ማለት መንግስትን/ተቃዋሚዎችን መደገፍ ወይም መቃወምም አይደለም፡፡ ይልቁንም ለማኅበረሰቡ ጤናማ የአእምሮ እና የቁስ ዕድገት እሴት የሚጨምሩ ለውጦች እንዲመጡ፣ ለውጡን ማሕበረሰቡ በእውቀት መር አካሔድ እንዲያመጣው መሥራት ነው፡፡

በአገራችን ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለሕዝቡ ለውጥ ለማምጣት፣ ዴሞክራሲ ለማስፈን፣ መልካም አስተዳደር ለመዘርጋት እና ወዘተ እየሰራን ነው ይላሉ፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የራሳቸውን ግብ አስቀምጠው መንቀሳቀሳቸው ምንም ችግር ባይኖርበትም አገራዊ ለውጥ የሚመጣው ግን በፓርቲ መስራቾች እና በአባሎቻቸው ብቻ አይደለም፡፡ እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው በፖለቲካ ፓርቲዎች መፈራረቅ ብቻ ሳይሆን (በእርግጥ ይህ ከተቻለ ተግባራዊ ትምህርቱ የሚናቅ አይደለም) ነገር ግን በሕዝባዊ አስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡

አራማጅነት በሌሎች አገራት

በሌላው ዓለም፣ በተለይም ያደጉ አገራት ውስጥ አራማጆች በማሕበራዊ ለውጥ አማጪነት ሁነኛ ሚና አላቸው፡፡ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር የጥቁሮች መብት በሀገረ አሜሪካ እንዲከበርዴዝሙን ቱቱ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ላይ፣ ኬንያዊቷ ዋንጋሪ ማታይ የአካባቢ ጥበቃ እና የፖለቲካ መብት ተቆርቋሪ በመሆን ዓለም አቀፍ እውቅናን ለማትረፍ የበቁ እና በጉዳዩ ዙሪያ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ናቸው፡፡

“አራማጆች” እና “አራማጅነት” በኢትዮጵያ፤ ጥቂት ምሳሌዎች

(፩) አንድ ሰሞን፣ ጋሽ አበራ ሞላ በሚለው ስሙ ይበልጥ የሚታወቀው የክራሩ ኤክስፐርት ስለሺ ደምሴ በከተማ ንፅህና እና አረንጓዴነት ዙሪያ ከፍተኛ የአራማጅነት ሚና ተጫውቷል፡፡ በወቅቱ ባደረገው ቅስቀሳ መላውን የአዲስ አበባ ወጣት በማነሳሳት ለአጭር ጊዜም ቢሆን አዲስ አበባን ከቆሻሻ ገንዳነት ወደ አረንጓዴ መዝናኛነት የመለወጥ ተስፋ አሳይቷት ነበር፡፡ የጋሽ አበራ ሞላ ፕሮጀክት አሁንም የቀጠለ ቢሆንም የአራማጅነት ሚናው ግን የሞተ ይመስላል፤ ለዚህም ነው ቀድሞ እናየው የነበረውን ያህል ለውጥ አሁን ማየት ያልተቻለን፡፡

(፪) ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) መወለድ ምክንያት የሆኑት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ አራማጅነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ የተሻለ የሰሩ ሰው ናቸው፡፡ ይህ ሚናቸው ግን በምርጫ 97 የፓርቲ አባል ሁነው ከመጡ በኋላ የቀነሰ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ በግለሰብ ደረጃ በአገር ውስጥ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሆኖ የሚታይ ግለሰብ እምብዛም የለም፡፡

(፫) እስከመጨረሻው ዘልቆ የሆነ ውጤት ባያመጣም፣ በ1994 በአቶ ልደቱ አያሌው (ፓርቲ ኢዴፓ አስተባባሪነት) ‹‹ኢትዮጵያን የአሰብ ወደብ ባለቤት ለማድረግ›› በየከተማው ፊርማ የማሰባሰብ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደራጁ ንቃት ለማስጨበጥ ያደረጉት ሙከራ ፖለቲካዊ ተራማጅነት (political activism) ሊባል ይችላል፡፡

(፬) ታማኝ በየነ በሙያው አርቲስት ቢሆንም ኢሕአዴግ በአገዛዝ አፍላ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአንድ አቋሙ ይታወቃል፡፡ የዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች አራማጅ ተብሎ ሊጠራም ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እርሱም ስደተኛ በመሆኑ መረጃ የሚሰጣቸው፣ ወይም የሚያቀነቅንላቸው ሰዎች ባመዛኙ በዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ለተሻለ ግንዛቤ የተሻለ ተግባራዊ አማራጭ ያላቸው ብቻ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባለመሆናቸው በኢትዮጵያ የሚያመጣው ለውጥ የሚጠበቀውን ያህል የጎላ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

(፬) ዘውዱ ጌታቸው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ እንቅስቃሴ ማሕበር (ተስፋ ጎህን) የመሰረተ ሰው ነው፡፡ ምንም እንኳን አሁን በጉዳዩ ላይ ለመስራት እንደአሸን የፈሉ በርካታ ማሕበራት ቢኖሩም፣ ዘውዱ ጌታቸው ማሕበሩን በመሰረተበት ሰዓት ማኅበረሳባችን ስለጉዳዩ የነበረው ግንዛቤ ለማውራት እስከመጠየፍ ይደርስ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ዘውዱ ጌታቸው እና ማሕበሩ የሰሩት ሥራ ሁሉንም ሰው ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ እስከ ተጠቂዎቹን ድጋፍ እና ሟቋቋም ድረስ ዘልቋል፡፡

(፭) ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ‹‹በኢትዮጵያ አትንዱ›› የሚል ዓለም አቀፍ ባጅ ያሰጠንን የትራፊክ አደጋ አስከፊነት ግንዛቤ በማስጨበጥ ከመንግስት ተቀጣሪነታቸው ውጪ የሚሰሩት ሥራ እንደአራማጅነት የሚያስቆጥራቸው ነው፡፡

(፮) በግለሰብ ደረጃ ጎልተው የወጡ ግለሰቦች ባይኖሩም፣ በኢትዮጵያ ሴት ጠበቃዎች ማህበርም ሲሰራ የነበረው (ከጥብቅና መቆም በላይ) የማንቃት እንቅስቃሴው፣ ማሕበሩን ከአራማጅነት ተርታ ያሰልፈው ነበር፡፡

ሌሎችም ጥቂት ምሳሌዎች ልንጨምር ብንችልም ለ80 ሚሊዮን ሕዝብ ግን በስንት ጭንቅ ትውስ የሚሉ እና በጣት የሚቆጠሩ የዘርፍ አቀንቃኞች ብቻ አይበቁትም፡፡

የሌሉን

በአገራችን በጣም አስፈላጊ ሆነው ሳሉ ጭራሹኑ የተዘነጉ የሚመስሉም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
  • የፀረ ሙስና አራማጆች የሉም፣
  • በትምህርት ጥራት ዙሪያ የሚሰሩ አራማጆች የሉም፣
  • በፕሬስ፣ በመደራጀት እና በጥቅሉ በሕገመንግስታዊ መብቶች መከበር ዙሪያ የሚሰሩ አራማጆች የሉም፣
  • ፀረ-እፅ (anti-drug) በተመለከተ፣
  • የፍትሐዊ የንግድ ስርዓት፣
  • የከተማ ንፅህናን በተመለከተ፣
  • የሴቶች መብትን በተመለከተ፣
  • በጎዳና ተዳዳሪነት እና ፀረ-ድህነት ላይ፣
  • የኢንተርኔት ነፃነትን በተመለከተ እና  
  • በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በቂ አራማጆች የሉንም፤ ይሁን እንጂ ችግሮቹ ስር የሰደዱ እና በመንግስት አቅም ብቻ የሚፈቱ አይደሉም፡፡

አራማጆች እና ውጤታቸው

በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰችው ጋዜጠኛ የአካባቢ ተቆርቋሪነቷን በግለሰብ ደረጃ እየተገበረችው ቢሆንም በዙሪያዋ ያሉ ሰዎችን መጠነኛ ግንዛቤ ከማስጨበጥ የበለጠ ሕዝብ ጋር በመድረስ ለውጥ የምታመጣበትን ሥራ እየሰራች አይደለም፡፡ ስለዚህ እሷን አራማጅነት ደረጃ ላይ ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ እየዘረዘርነው በመጣነው ማብራሪያ መሰረት እሷ የአካባቢ ጉዳይ አራማጆች ፍሬ ናት፤ በሆነ ጉዳይ አራማጅ/አቀንቃኝ/ተሟጋች የምንላቸው፣ ከራሳቸው አልፈው የማኅበረሰቡን አባላት ልክ እንደ ተጠቀሰችው ጋዜጠኛ ዓይነት በጉዳዩ ዙሪያ ተቆርቋሪነት እንዲያዳብሩ እና ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ለማድረግ የሚሰሩትን ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ አገራችን እንኳን በዓለም ዙሪያ የሚጠቀሱ ቀርቶ በአገር ውስጥ እንኳን ከአንድ ጉዳይ ጋር አወዳጅተን የምናስታውሳቸው አራማጆችን አላፈራችም፡፡ ለዚህ ተጠያቂ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፤ አንደኛው የሲቪክ ማሕበራቱ አዋጅ ነው፡፡

ይህ አዋጅ በአራማጅነት ላይ ትልቅ ቡጢ ያሳርፋል፡፡ ግለሰቦች ለውጦች እንዲመጡ የአራማጅነት ሚናን እንዲወስዱ የፋይናንሻል አቅም ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የሲቪክ ማሕበራቱ በአገር ውስጥ ድጋፍ ካልተዳደሩ በቀር ይህንን ድጋፍ የማድረግ መብት የላቸውም - በተለይ በመብት ጉዳይ፡፡ ይህም፣ አገር በቀሎቹን የየሰብአዊ መብት ጉባኤን እና የሴት ጠበቃዎች ማሕበር ላይ ያደረሰው ማሸመድመድ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ መሰረታዊ ፍላጎቶቹ ያልተሟሉለትን ሕዝብ ሲቪክ ማሕበራትህን ራስህ አስተዳድር ማለት ለችግሩ ተባባሪ ከመሆን የተሻለ እርምጃ አይደለም፡፡

ሌላኛው እና ሳይጠቀስ የማይገባው ምክንያት፣ የግለሰቦች የደህንነት ስጋት ነው፡፡ ግለሰቦች በሚያራምዷቸው አስተሳሰቦች እና አመለካከቶች እየተመለመሉ የሹመኞች ጥርስ ውስጥ የሚገቡበት ስርዓት ውስጥ መሆናችን የማይካድ ነው፡፡ ይህ ድባብ ግለሰቦች ለውጥ ማምጣት በሚፈልጉበት እና በሚችሉበት መስክ ተሟግተው ከመጠመድ ይልቅ በጥላው ተሸፍነው ማለፍን ይመርጣሉ፡፡

ጠቅላላው ነባራዊ እውነታ ይህ ቢሆንም፣ ዕድሉን ለማግኘት እየታገሉ በተለያዩ ምክንያቶች ግባቸውን ያልመቱ በርካታ አራማጆች መኖራቸውን ግን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ጽሑፍ የዞን ዘጠኝ የ2005 የመጀመሪያው ጽሑፍ እንደመሆኑ፣ በዚሁ አጋጣሚ ዓመቱ በርካታ ግለሰቦች እና ተቋማት ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚሰሩበት ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታችንን እንገልፃለን፡፡

No comments:

Post a Comment