ነብዩ ኃይሉ
ላለፉት 21 አመታት የምኒሊክ ቤተመንግስት
ለአንድና ለሁለት ቀን ግፋ ሲልም ለአንድ ሳምንት ካልሆነ ጌታውን አጥቷቸው አያውቅም፡፡ አቶ መለስ በግንቦት ወር በቡድን ስምንት
ጉባኤ ከተካፈሉ በኋላ ግን ማንንም አምነው የማይርቁትን ቤተመንግስት በህመም ምክንያት ትተው ብራስልስ ከረሙ፡፡ ህመማቸው እና አማልክቱ
ጨክነውም ዳግም ወደ ምኒሊክ ቤተ መንግስት በቁማቸው ሳይመለሱ ቀሩ፡፡ እናም ቤተመንግስቱ ላለፉት ሦስት ወራት ኦና ሆኗል፡፡
አገሪቱን ማን የት ተቀምጦ እንደሚመራት
ብዙም ግልጽ ባይሆንም፣ ኃለማርያም ደሳለኝ በተጠባባቂነት አገሪቱን እየመሩ እንደሆነ ሲገለፅ ሰንብቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ባለፈው
አርብ መስከረም 4 ተጀምሮ ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2005 ዓ.ም የተጠናቀቀው የገዢው አብዮታዊ ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ኃይለ
ማርያም ደሳለኝን በሟቹ ሊቀመንበሩ ምትክ ቢያስቀምጥም፣ ሰውየው እስከወሩ ማገባደጃ ቃለ መሀላ ፈፅመው ወደ ቤተመንግስት አይገቡም፡፡(በዚህ
ሳምንት መጨረሻም ይሆናል የሚልም ግምት አለ) ሁኔታው ኢህአዴግ ኃይለማርያምን
ቤተመንግስት ከማስገባቱ በፊት ማጠናቀቅ የፈለገው ስራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡
ኢህአዴግ ከ21 ዓመት በኋላ ከህወሓት
ውጪ የሆነን ግለሰብ ለፓርቲው ሊቀመንበርነት በመሾሙ በፓርቲው የውስጥ ፖለቲካዊ የኃይል አሰላለፍ ላይ ለውጥ መጥቷል ለማለት ያስችላል?
የአቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ተክለ ስብዕናስ እንደ መሪ ውሳኔዎችን ለመስጠት የሚያስች ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች ቀጣዩ ፅሁፍ ምላሽ
ለመስጠት ይሞክራል፡፡
የኢህአዴግ
የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አሳይቶ ይሆን?
ኢህአዴግ ላለፉት አመታት ከህወሓት ተፅእኖ
ስር ተለይቶ አያውቅም፡፡ የአራት ፓርቲዎች ስብስብነቱም አፋዊ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ ህወሓት ያቀደው፣ ህውሓት ያቦካውና የጋገረውን
ተቀብሎ ከማስተጋባት ውጪ ህወሓትን የሚገዳደር አንድም አባል ድርጅት ያልነበረው ኢህአዴግ፣ ለህወሓት አንደኛ፣ ለብአዴን ሁለተኛ፣
ለኦህዴድ ሦስተኛ እንዲሁም ለደኢህዴን የአራተኛነት ደረጃ የሰጠ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ ነበረው ተብሎ ሲታማ ከርሞአል፡፡
የህወሓትም ሆነ የኢህአዴግ ጭንቅላት ተደርገው
የሚወሰዱት መለስ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ግን የኢህአዴግ ውስጣዊ የኃይል አሰላለፍ እንዲቀያየር የሚያስገድድ ሁኔታ የተ፡፡ ለፓርቲው
ቅርብ የሆኑ ወገኖች እንደሚገልፁት ህወሓት በአቶ መለስ ላይ ከተገቢው በላይ በመተማመመን ተተኪ ሰው ባለማዘጋጀቱ በኢህአዴግ ውስጥ
የነበረውን ተፅእኖ በቀላሉ ለማጣት ተገዷል፡፡ በከሰተ ይመስላል፡፡ብአዴን ውስጥ አዳዲስ ፊቶች በፊት እንዲመጡ ባይደረግም ቅሉ ፓርቲው
ከአቶ መለስ በኋላ አለቅነቱ ለኔ ይገባኛል የሚል የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረጉንም እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ኦህዴዶች በስልጣን
ሽኩቻ ላይ ብዙም አልተሳተፉም፤ ከብአዴን ጋር የነበራቸውን ዘመን ያስቆጠረ የመቀናቀን አዝማሚያ ላለማድረግ የተገደዱ ይመስላል፡፡
አሁን ከሞላ ጐደል ኢህአዴግ ውስጥ ብአዴን ጠንከር ያለ ባይሆንም መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል የበላይነት ይዟል፡፡ ኢህአዴግ መንግስት
እንዲመሰርት የሚያስችለውን ትልቁን የፓርላማ መቀመጫ የሚያዋጣው ኦህዴድ ሀገሪቱ ያላትን ሁለት ከፍተኛ የስልጣን ማዕረጐች ለማግኘት
አለመቻሉ አስገራሚ ባይሆንም በፓርቲው ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመካከለኛ አመራር ላይ እየተጠናከረ ከመጣው በኢህአዴግ ውስጥ ስልጣን
ይገባናል የሚል ጥያቄ አንፃር የኦህዴድ አመራሮች ፈተና ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ደኢህዴን አቶ ኃይለ ማርያምን ስላስመረጠ
ብቻ በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ደረጃ በማሻሻል የበላይነቱን አረጋገጠ ለማለት ባይቻልም ተጠቃሚነቱን አረጋግጧል ለማለት ግን ያስደፍራል፡፡
ይህ በሲቪል አስተዳደር ላይ የተደረገ
የአሰላለፍ ለውጥ ሁሉን አቀፍ እንደሆነ ተደርጐ ከተወሰደ እና የህወሓት የበላይነት እንዳበቃለት ከተቆጠረ ግን ስህተት ላይ መጣሉ
አይቀርም፡፡ ይህ ስህተት የገዢውን አብዮታዊ ፓርቲ ትክክለኛ ማንነት ካለመረዳት ይመጣል፡፡ በተግባር እንደሚታየው ኢህአዴግ ፍፁማዊ
አምባገነንነቱን ለማስጠበቅ የተለያዩ ክንፎችን ዘርግቷል፡፡ አንደኛው የሲቪል አስተዳደር ክንፍ ሲሆን ሁለተኛው ወታደራዊና የደህንነት
ክፍል ሲሆን ሦስተኛው የፓርቲውን ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የሚያሳየው የንግዱ ክንፍ ነው፡፡ እነዚህ ክንፎች አመጣጥ ነው በሁሉም የበላይነቱን
ተቆናጠው የነበሩት ህውሓቶች የመለስን ሞት ተከትሎ ከሌሎቹ ኢህአዴጋውያ በበለጠ ስልጣን በማጣት ስሜት ዙሪያው ቢጨልምባቸውም ኢህአዴግ
ግን አሁንም ከቁጥጥራቸው ውጪ አይደለም፡፡ በኢንዶውመንት ስም ባቁዋቋሟቸው የንግድ ድርጅቶች [ህውሓቶች] የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የመዘወር
አቅም አላቸው፡፡ የህውሓቶች ዋስትና ይህ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በኢህአዴግ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለውንና ስርዓቱ
እንደ አፈና መሳሪያነት የሚጠቀምበትን ወታደራዊና የደህንነት ኃይል በበላይነት መቆጣጠራቸው ለህወሓቶች በሲቪል አስተዳደሩ ያጡትን
የኃይል ሚዛን ያስጠብቅላቸዋል፡፡
በቅርቡ ይፋ የተደረገው ወታደራዊ ሹመት
ወትሮም በብሔር ስብጥር ፍትሀዊነት ማጣት የሚታማውን የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የከፍተኛ መኮንንነት ስፍራዎች የህውሓት ሰዎች
በበላይነት እንዲቆጣጠሩት ተጨማሪ ሀይል ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህ እርምጃ ህውሓቶች ያለብዙ ፍትጊያ ሲቪል አስተዳደሩን እንዲለቁ የተሰጣቸው
ማስተማመኛ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም፡፡ በብሔር ስብጥሩ ከፍተኛ አለመመጣጠን የታየበት ወታደራዊ ሹመት ኃይለማርያም ቤተመንግስት
ከመግባታቸው በፊት በጥድፊያ መደረጉ እና በትግራይ ክልል ብዙሀን መገናኛዎች እየተላለፈ ካለው “ሶስተኛውን የወያኔ እንቅስቃሴ እንጀምራለን”
የሚል አንድምታ ካለው መልእክት ጋር ሲዳመር የኢህአዴግ የውስጥ ሽኩቻ ሀገሪቱን ለትርምስ እንዳይዳርጋት ያሰጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አቶ ኃይለማርያም በሚያዋቅሩት
ካቢኔ ውስጥም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በአማካሪነት ደረጃ ለህውሃቶች ሁነኛ ቦታዎች እንደተዘጋጀላቸው ቃል መገባቱን ከታማኝ
ምጮች የተገኙ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ህውሓቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቅርብ ርቀት ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው እንደሚሆን
ይገመታል፡፡ እዚህ ጋር ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ ኃይለማርያም ምን ያክል በዙሪያቸው ያለውን የኃይል ሚዛን ትግል አልፈው በራሳቸው
ውሳኔ ሰጪነት መስራት ይችላሉ? የሚለው ነው፡፡
ኃይለማርያም
እና ኢህአዴግ
አቶ ኃይለማርያም በኢህአዴግ ውስጥ የጐላ
ደርሻ ካላቸው ግለሰቦች ተርታ የተሰለፉት ከሁለት አመት በፊት የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ ሲመረጡ ነበር፡፡ ሰውየው
ከአስተዳደር ጋር የተገናኙ ስራዎች ላይ ረጅም አመት የመስራት ልምድ ቢኖራቸውም ከፖለቲካ ተክለ ሰብዕናቸው ይልቅ (technocrat)
ገራገር የቴክኒክ ሰውነታቸው ያመዝናል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጠውም ከሁለት አመት በፊት በምክትል ጠ/ሚኒስትርነትና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት
ሲሾሙ “ስራው ላይ ልምድ ስለሌለዎት ለመስራት አይቸገሩም ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት ማላሽ “ከቅርብ አለቃዬ[ከአቶ መለስ]
ምክር እየጠየኩ እሰራለሁ” ማለታቸው ነው፡፡ የያኔው ገራገር ፖለቲከኛ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬም ፖለቲካዊ ብስለት ያገኙ አይመስሉም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በሰጧቸው አስተያየቶች መለስን በምንም አይነት ሁኔታ መተካት እንደማይችሉ ጠቅሰው
ሀገሪቱን “በጋራ” ለመምራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአንድ ፖለቲከኛ አስፈላጊና ወሳኝ
የሆነው በራስ የመተማመንና ራስን ተፎካካሪ አድርጐ የማቅረብ ብቃት ጨርሶ እንደሌላቸው ነው፡፡ ፖለቲካ፣ መተጋገዝ፣ መተባበርና መመካከርን
የሚጠይቅ የጋራ ስራ ቢሆንም፣ ሁልጊዜም ቆራጥነትና በራስ የመተማመን ግላዊ ጥንካሬን የግድ ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ህገመንግስት ስልጣንን ሁሉ አከማችቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ
ይሰጣል፡፡ በመሆኑም አቶ ኃይለማርያም ህገመንግስቱ ሳይሳሻሻል “በጋራ” አመራር ለመስጠት መዘጋጀታቸው የሚያዛልቅ የብልህ ውሳኔ
አይመስልም፡፡ “በጋራ” የሚወስኑትም ከማን ጋር እንደሆነ ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ ከነበረው የወንጀልና የመብት ጥሰት
ታሪክ እና አሁንም ሊወስዳቸው በሚችላቸው አደገኛ እርምጃዎች ፈጠነም ዘገየ በፍትህ ፊት የሚዳኝ ስርአት ከመሆኑ አንፃር አቶ ኃይለማርያም
“በጋራ” ውሳኔ ለመስጠት መዘጋጀታቸው የኋላ ኋላ ጦስ ተቀባይ ሊያደርጋቸውም ይችላል፡፡ አምባገነንና ወንጀለኛ ስርዓትን መምራት
የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳያገናዝቡ “መለስ የጀመሩትን” እንደሚያስቀጥሉ ቃል መግባታቸው ከቀደመው የአቶ መለስ አገዛዝ ያልተሻለ አገዛዝ
እንደሚኖራቸው አያጠያይቅም፡፡
የሦስተኛው አለም ፖለቲካ በአብዛኛው በጠንካራ
አመራር (Bold leadership) ላይ የመመስረት ታሪክ እንደመያዙ፣ ኢህአዴግ ከጅምሩ በሴራ የታሸ ፖለቲካን ከማዘውተሩ እና
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ውጥረት ላይ ያለ ከመሆኑ አንጻር የአቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ተክለ
ስብዕና ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡
የኃይለማርያም ፈተናዎች
ኢህአዴግ አቶ ኃይለማርያምን ወደ ፊት ያመጣበት ሂደት በፓርቲው የጋራ
መግባባት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የኦህዴድ ተመጣጣኝ ቦታ አለማግኘት እንዲሁም የደህንነትና የወታደራዊ ስልጣኖች ተከማችተው ለህወሓት
መሰጠታቸው ጊዜ ጠብቀው እንደሚፈነዱ ቦንቦች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
ኦህዴድ በአቶ ኃይለማርያም ካቢኔ የሚሰጠው ቦታ በአመራሮቹና በፓርቲው
መካከለኛ አመራሮች መካከል እየተባባሰ ያለውን አለመግባባት ሊያረግበው የሚችል አይመስልም፡፡ በመሆኑም ኦህዴድ ከስድስት ወር በኋላ
በሚደረገው የኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ምን አይነት አቋም እንደሚወስድ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ህገመንግስት ለጠ/ሚኒስትሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥነት
ስልጣንን ያጎናፅፋል፡፡ አቶ ኃይለማርያም ከመከላከያ ሰራዊቱ አዛዦች ጋር ቅርበት ያላቸው ያለመሆኑ፣ የህውሓት ከኢህአዴግ ኃላፊነት
መራቅን ተከትሎ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በወታደራዊና በደህንነት መዋቅር የመቃወም አዝማሚያ ሊከሰት የመቻሉ አጋጣሚ አይኖርም የማይቻል
ነው፡፡
አለም አቀፉ ማህበረሰብ የኃይለማርያምን ወደ ማማው መውጣት እንደ በጐ
ጅማሮ መቁጠሩ የማይቀር ቢሆንም ሰውየው በቂ ዲፕሎማሲያዊ እውቀትና የዳበረ ልምድ ያላቸው ስላልሆኑ የአቶ መለስን ያክል የፋይናንስ
ድጋፍ በማግኘት ስራቸው በመቆም ላይ ያሉትን የአባይ ግድብንና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል መቸገራቸው የማይቀር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያልተረጋጋና በርስ በርስ
ጦርነቶች እንዲሁም በተጐራባች ሀገሮች መሀከል በቋፍ ላይ ባሉ ግጭቶች የተወጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም ነፍጥ ያነገቱና በጐረቤት
ሀገራት የሚደገፉ ቡድኖች የመኖራቸው ጉዳይ፣ የኢትዮጵያ ጦር ሱማሌ ውስጥ ከመገኘቱና ከኤርትራ ጋር ካለው ወታደራዊ ፍጥጫ ጋር ሲዳበል
በየትኛው ወቅት ምን ሊከሰት እንደሚችል ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዋጋ ግሽበት
እና ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር፣ በአፈና እና በግድያ ያልበረደው የኢትዮጵያውያን የነፃነትና የመብት ጥያቄ እንዲሁም የኢህአዴግ መንግስት
በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ ያስጀመረው የሙስሊሞች የተደራጀ ተቃውሞ ትክክለኛ ምላሽ የማያገኙ ከሆነ ሊያቀጣጥሉ
የሚችሉት ስርአቱ በምንም አይነት መንገድ ሊወጣው የማይችለው ህዝባዊ ንቅናቄ ሊፈጥር እንደሚችል ለመገመት ነብይነት ግድ አይልም፡፡
ከላይ ከተብራሩት ተጨባጭ ፈተናዎች አንፃር የምኒሊክ ቤተመንግስት ለአቶ
ኃይለማርያም ደሳለኝ የምቾት ስፍራ ሊሆንላቸው የሚችል አይመስልም፡፡
Thanks for this very insightful analysis and for putting things in perspective of the recent developments. Creating alliances through marriage, and thus keeping a finger on the button using ones spouse has been used as a strong political tool since the beginning of time. In this particular instance, please note that, W/o Roman, Ato Hailemariam's wife, happens to be from Tigray Region. She has been seen to wield some influence as a confidante, in the Ministry of Health of Ethiopia, where she works. Is that not a factor important enough to put into the equation?
ReplyDelete