Friday, July 19, 2013

የስደተኛው ማስታወሻ ከአውሮጳ


(ክፍል ፭)

ውዴ:-

ባለፈው ከሳሚ ጋር ስለመጠለያ ጣቢያ ስንጨዋወት ስሙን መቀየር ስላልፈለገው ጓደኛቸው ያጫወተኝን እየነገርኩሽ ነበር ያቆምነው፡፡የሳሚ ታሪክ ይህንን ይመስላል፡፡ እሱን አንብቢና ስደተኛ በአውሮፓ የሚጠብቀውን ህይወት ገምቺ፡፡
 
ከዚያ
ጊዚያዊ ካምፕ የመቆያዬን ጊዜ ጨርሼ ወደተመደብኩበት ቋሚ መኖርያ ስሄድ ካገሬ ሥሰደድ ያልተሸኘሁትን አይነት ሽኝት በዚያ ካምፕ ባገኘኋቸው ወገኖቼ ተደረገልኝ። በውድቅት ሌሊት የምሔድበት መኪና የሚቆምበት ቦታ ድረስ መጥተው መልካም ምኞታቸውን ገለጡልኝ። እኔም አፀፋውን መለስኩና ወደዚያ ከተማ ሄድኩ። ከነዚህ የአጭር ጊዜ ወዳጆቼ ጋር እስከአሁን እንደዋወላለን። ወዴት እንደሄዱ ሳላውቅ ደብዛቸው የጠፉም ሞልተዋል።

ከትልቁ ጊዚያዊ መጠለያ ወደዚያ ስንሄድ አንድ አበሻ ብቻ ነበር የማውቀው። እሱም ከኔው ጋር ተመድቦ በአንድ ባቡር አብሮኝ የነበረ ነው። እዚያ የደረስነው ጥር አጋማሽ ላይ ስለነበር የነበረው አየር እጅግ ይገርም ነበር። መሬት የሚባል ነገር አይታይም። በሙሉ ነጭ ነው፣ ዛፉም የእግዜር ስሪት አይመስልም፣ ከመንጣቱና ከቅርፁ የተነሳ ሰውሰራሽ ይመስላል። ብርዱ ለመግለፅ በሚያስቸግር መልኩ ተስፋ ያስቆርጣል።

ከባቡር እንደወረድን የመጠለያው ሰራተኞች ፎቷችን ያለበትን ወረቀት ይዘው ስለነበር ገና ከደረጃው ስንወርድ በስማችን እየጠሩ ተቀበሉን። ወደውጭ ባየሁት ነጭ መልክዓምድርና የሚያቃጥል ቅዝቃዜ የተፈጠረብኝን ስጋት ለማርገብ ስለከተማውና ስለምንኖርበት ቦታ እየተርበተበርኩ እንደምንም ብዬ በምችላት ጥቂት እንግሊዝኛ መጠየቅ ጀመርኩ። ሁኔታዬን የተረዳው ሰራተኛምአይዞህ ሁሉም ሲመጣ እንዳንተው ይሆንና ትንሽ ሲቆይ ይለምደዋልአለኝ።

ከመኪናው አስገብቶን 30 ደቂቃ ነዳው። ግራ በመጋባት አብሮኝ ካለው ልጅ ጋር ተያየን። ወዴት ነው የምትወስደን ብለን ጠየቅነው።እዚሁ ነው! የናንተ መጠለያ  ከከተማው ወጣ ይላል፣ አይዟችሁ ባካባቢው የሚኖር ማሕበረሰብ ስላለ የገበያ ችግር የለምአለን።

ሶስት የዶከካቸው ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃዎች እንደመልክዓ ምድሩ ነጩን በረዶ ተሸከመው ተኝተዋል። በመካከላቸው ባለ ክፍት ቦታ ላይ እንደጨው ክምር የተቆለለ በረዶ ሶስተኛውን ሕንፃ ሸፍኖታል። የሰውየው መኪና እየተንደረደረ ሄዶ እዚህ ግዙፍ የበረዶ ክምር ስር አረፈ። አወረዱንና ቢሮው ወደሚገኝበት ወደመኻለኛው ሕንፃ አስገቡን። በስርዓት አስተናገዱን። የመጠለያውን ሕግ አነበነቡልን፣ ለሶስት እንድንኖር ብቻውን ይኖር ወደነበረ ወደ አንድ ኤርትራዊ ክፍል አመላከቱን። የክፍሉን ቁልፍና የምንበላውን እንድንገዛ ገንዘብ ሰጡን። ሁሉን ጨርሰን ቢሯቸውን ለቀን ወደውጭ ወጣን።

ስገባ አንድ ሕንፃ ብቻ ነበር ያየሁት፤ ስለ ሶስት ሕንፃዎች ሲነግረኝ ግር አለኝ እዚህ ከመምጣትህ በፊት ሌላ ቦታ ኖረህ ነበር ማለት ነው?’ብዬ ጠየቅኩት።

አዎ፤ እዛ ሶስት ወር ኖሬ አመመኝ ብዬ ነው ወደዚህ የቀየሩኝ። አውቆ መታመም እችልበታለሁ፤ በስደተኛውም ዘንድ  አውቆ ማበድና መታመም የተለመደ ነው። አመመኝ ብዬ ጠብ ስል ደንግጠው ወደዚህ መደቡኝ። ቦታ በጣም ከባድ ነበር። ሰው የምርጫዎቹ ጥርቅም ነው ይባል ነበር። እዛ ተመድቤ የሄድኩ ቀን ግን እንዳልሆነ ታረዳሁ። እኔና ጓደኛዬም እንደተራራ በተከመረው በረዶ ስር ቆመን ተኮራረፍን፣ አብዝተን ተከዝን፣ ተስፋ ቆረጥን። ተስፋ ከመቁረጣችን የተነሳ የሚያቃጥለውን ብርድ ረስተን እውስጡ ተገትረን ቀረን። ወደምንሔድበት ግራ ገባን። ራቅ አድርገን ስናይ ከጎናችን ያለውን የበረዶ ክምር አብዝቶ የሚበልጥ ነጭ ተራራ እይታችንን ይገድበዋል። ቀና ስንል የከፋው ሰማይ ምን እንደያዘንኳ እንዳያስታውቅ ሆኖ በቅርብ ርቀት በጉም ተጠቅጥቋል። የሚታዩን ሶስቱ ሕንፃዎች ድኃዋ አገራችን ላይ ለእህል መጋዘንነት የሚታነፁትን አይወዳደሩም። ውስጣቸው ያሉት ስደተኞች ለምንም ግድ ያላቸው አይመስሉም። ይወጣሉ ይገባሉ። በረዶውን በትልቅ ጫማቸው እየሰነጠቁ ያልፋሉ ያገድማሉ እኛም ላይ እንደትንግርት ያፈጣሉ።

ያንን መጠለያ ካለፈው የሚለየው የጥገኝነት ጥያቄ መልስ የሚሰጠን በዚህ ቦታ ተቀምጠን በመጠበቅ ነበር። ብዙ ጊዜ እንደሚያስጠብቁን ሳስበው ደግሞ ቦታው የበለጠ እየቀፈፈኝ ሄደ። ከዚህ የባሰ የሚያስጠብቁ አገሮች እንዳሉ ግን እሰማ ነበር። እዚያ የሚኖሩት ስደተኞች እንደበፊቱ ከብዙ አገር የመጡ አይደሉም። ከአፍጋኒስታን፣ ከኤርትራ፣ ከሶማሌ፣ ከኢራን፣ ከኢራቅና ከኮንጎ የተሰደዱ ይበዛሉ።

ቢሆንም ግን በዚያኛው መጠለያ አበሻው እራሱን አግሎ ለብቻው ነው የሚኖረው። እዚያ መጠለያ የሄድን ቀን ከቆምንበት የበረዶ ክምት ስር እንደተገተርን አንድ አበሻ መጣና ጨበጠን። ስሙንም ነገረን። ከመጣሁ ሰባት ወሬ ነው ሲለን እንደጀግና በተደሞ ተመለከትነው። እዚህ ነጭ ጫካ ውስጥ፣ የበረዶ ግግር መኃል ሰባት ወር! ጓደኛዬም አብሮኝ ተገረመ። መልስ አግኝቶ እንደሁ ስንጠይቀው አላገኘሁም አለን። እንዲያውም አመትና አመት ተኩል እምደሚያስጠብቁ አረዳንና እዛው ጥሎን ሄደ። 

ይሄ ደግሞ ምን ጋግርታም ነው፣ እንግዶች ነን፣ እቤት እንግባንኳ አይልምንዴእያልን እየወረድንበት ባይናችን ሸኘነው። እየዘፈነ ጥሎን ሄደ። አማትረን አማትረን ያገኘነው ሰው ሰው አልሆን ሲለን ተያይዘን ጉዞ ጀመርን፣ ወደሱፐር ማርኬት። ባናውቀውም ይሆናል ብለን ወደገመትንበት አቅጣጫ መራመድ ጀመርን። መኪናዋ ይዛን ስትመጣ በረዶው ላይ የተወችውን የጎማ ምልክት ተከትለን መራመድ ጀመርን።

በነጩ ምድር ላይ ኮቴያችንን ሲል እየሰማን በፀጥታ ስንራመድ ሱፐር ማርኬት አገኘን። በቃ እንዲህ ጀመርነው ኑሮውን። ገዛዝተን ስንመለስ የተመደብንበት ክፍል ውስጥ የሚኖረውን ልጅ ከቤት አገኘነው። ቁጭ ብሎ እኛን ይጠብቃል። እንግዳ ይመጣብሓል ተብሎ የተነገረው ቀደም ብሎ ስለነበር አልጋችንን ብቻ ሳይሆን ምግባችንንም አዘጋጅቶልን ነበር የጠበቀን። አበሻዊ አቀባበል ሲገጥመን የገዛነውን ከነፌስታሉ ገለል አድርገን ክሽን አድርጎ ያሰራውን ዶሮ መብላት ጀመርን። እኛ ስለመጠለያው እየጠየቅነው፣ እሱ እየመለሰ በልተን ጨረስን። አንድ ኢትዮጵያዊና ብዙ ኤርትራዊ በመጠለያው እንደሚኖር ነግሮን ማታ ሊያስተዋውቀን እንደሚወስደን ነግሮን ክፍሉን ጥሎልን ውልቅ አለ። እኛም አመስግነን አልጋችንን ማንጠፍ ጀመርን።

ከኤርትራዊ ጋር ኖረኻላ? እንዴት ናቸው ኤርትራውያን? እንዴት ነበር አንተ የነበርክበት መጠለያ?’ ስለ ኤርትራውያን ስደተኞች ለማወቅ ያለኝን ጉጉት በጥያቄ መዓት በማቅረብ ገለፅኩለት።

እንዲህ ሲል መተረክ ጀመረ። እዚያ መጠለያ ውስጥ ሶስት ኢትዮጵያውያኖች ብቻ ነበርን። አንዱ ያ ጋግርታሙ ስለሆነ እንደሌለ ቁጠረው፣ አንዱ አብሮኝ የሄደው ልጅ ሲሆን ዘመድ አለው መሰል ወዲያው መጠለያውን ለቆ ወደከተማ ሄደ። እኔም ኬዜ ኤርትራዊ ስለሆነ ለመምሰል ጥረት አላደርግም። ኤርትራዊ ነኝ ማለት እንዴት እንደሚከብድ ይገርምሃል፤ ስጠየቅ ወይ ዝም እላለሁ ወይ ኢትዮጵያዊ ነበር  የምለው። ታዲያልህ ለሶስት ወራቶች ስኖር የገጠሙኝ ስደተኞች በአብዛኞቹ ኤርትራውያን ናቸው። ከተሰደድኩ ቡኃላ በመንገድ ላይም ከዚያም ቡኃላ በጣም በርከት ያሉ ኤርትራውያንን ተዋውቄያለሁ። ሲወዱንና ስንወዳቸው አይቻልሁ። የጋራ መጠሪያችን የሆነውን አበሻን እየተጠቀምን አንድ ለመምሰል እንጥራለን።

ኤርትራውያን ጉዳያቸው ተቀባይነት ስላለው ደስተኞች ናቸው። ከተመደብኩበት መጠለያ ውስጥ አዘውትረን ካርታ እንጫወታለን፣ ሌላ ነገር የለም፣ ወጣ ሲሉ ዙሪያው ነጭ ውኃ ነው፣ ንፋሱ ሳያቋርጥ ይነፍሳል። አገሪቱ ኃብታም ብትሆንም እዚያ ባቋቋመችው የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ቤተ መፅሃፍትም ሆነ ኢንተርኔት የለም።

40 ደቂቃ በእግሬ ተጉዤ ከማገኛት ተለቅ ካለች ከተማ በሁለትም በሶስትም ቀን እየተመላለስኩ ስለአገሬና ስለአለም የሚደረገውን ክስተት የማውቃትን ቪኦኤን ከኢንተርኔት እየከፈትኩ እከታተላለሁ። በተረፈ በምልክት ከምግባባቸው ከኤርትራ ከተሰደዱ ስደተኞች ጋር እየተጫወትኩና እየተዋደድኩ ጊዜዬን እኖራለሁ። ከአዲስ አበባ፣ ከወለጋ፣ ከሓረር ወይም ከሌላ የኢትዮጵያ ክፍል የተሰደደ ሰው እዚያ ባይኖርም ችግር አልገጠመኝም። አበሾቹ ኤርትራውያን አሉልኝ።  በጅምላ አበሻ አይደለን? እንዋደዳለን።

‘አንተ ትግርኛ እንደማትችል ነግረኸኛል፣ እነሱ አማርኛ ይችሉ ነበር? እንዴት ትግባባላችሁ?’ብዬ ጠየቅኩት።

በቋንቋችን ባንግባባም በትግርኛና በአማርኛ መካከል ባሉት ጥቂት መወራረሶች እየተረዳን እንግባባለን። ቁምነገር ስለማናወራ ብዙም አልተቸገርኩም። ካልጋ ወርደን ሳሎን ነው ስራችን። እንቅልፍ ሲያልቅ ምግብ፤ ከምግብ በኋላ ጫወታ። እንዲህ እንዲህ እያልኩ ጥቂት ሳምንታትን ካሳለፍኩ በኋላ አንድ አማርኛንና ትግሬኛን አቀላጥፎ የሚናገር አምቼ ከጫወታው ማሕበር ተቀላቀለ። ነገር ግን ትግሪኛን ቢያንስ እንድግባባበት በማሰብ የሱን እርዳታ ላለመጠቀም ወስኜ ሲያወሩ ባንክሮ ማድመጥ ጀመርኩ። ካልገባኝ እያስደገምኩ ራሴን ትምህርት ቤት ውስጥ እንዳለሁ ለመቁጠር ሞከርኩ። ኢትዮጵያዊ ባለመኖሩ አልቆጨኝም። መተሳሰቡ መዋደዱ ስላልቀረብኝ አልከፋኝም። ቢያንስ አንድ ቋንቋ ለመግባቢያ ብጨምር ብዬም ተስፋ አደረኩ።

ከወደውጭ የሚሰማው ውሽንፍር ለመውጣት አያስመኝም። ውሎ ውሎ ከቤት ኑሮ ኑሮ ከመሬት እዚያ አይሰራም። ውሎ እቤት አዳር እቤት ነው። እንዲህ እያልን በጋራ ቀኑን እየገፋን እየተጫወትን ባለበት ባንድ ምሽት አንዱ ወጣት እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ወደምንጫወትበት ክፍል ዘው ብሎ ገብቶ አንድ ነገር ተናገረ።

በትግርኛ የተናገረውን እንኳን ሊገባኝ ቃላቱንም አልሰማሁትም። ልጁ ተናዶ በጣም ይፈጥን ስለነበር ለመከተል ከበደኝ። ከዚያ ቡኃላማ ነገሩ ተባባሰ። ጫወታው ፈረሰ፤ አባይ ደፈረሰ ሆነ ነገሩ። ካርታቸውን በትነው ተነሱ። ግራ መጋባቴን ያየው አማርኛ የሚችለው ወደኔ ጠጋ አለና ስለሁኔታው ሲነግረኝ ፈገግ አልኩኝ።

ኢትዮጵያ አሰብን ልትወስድ ኤርትራን ወረረችነበር የሰሙት ሰበር ዜና። ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ድንበር ዘልቃ በመግባት ጥቃት ፈፀመች የሚለውን ዜና ነበር አንሻፈው የሰሙት።

ኢትዮጵያዊ በመሆኔና በፈገግታዬ ምክንያት አንድ ላይ አበሻ መባላችንን ረሱት። ኬዜም ኤርትራዊ እንደሆነ ዘነጉት። ቋንቋቸው የሚችለውን ያህል ኃይለ ቃል እየወረወሩ አማረሩ። እኔም ከደቂቃዎች በፊት የነበረኝን አበሻነት ሳልቀይር ፈገግ እንዳልኩ ቀጠልኩ። ምን ያስቅሃል አይነት የቁጣ ግልምጫቸውን እያሻሩኝ ቤቱን ለቀው ወደብርዱ ገቡ። ሁሉ ፍቅራቸው በአንድ ጊዜ በኖ ጠፋ። ሁሉ አክብሮት በዚህች ባልተረጋገጠች ወሬ ምክንያት እንዳይሆኑ ሆነ።

ወሬውን አቋረጥኩት ‘ዜናው ትኩስ ነበር? እንዴት ያልተረጋገጠ ወሬ አልከው?’

ከሳምንት በፊት የተከሰተ ክስተት ነበር። እንግዲህ በሳምንት ውስጥ ወሬውን ሳይሰሙ ከሳምንት በኋላ ከአሰብ ጋር አያይዘው ሲሰሙት ገርሞኝ ነዋ! የሆነው ሆኖ ከመጣሁ እንደዚያ ሲሆኑ አይቼ አላውቅም። መደሰትና መዝናናት የሚያዘወትሩት ኤርትራውያን ወዳጆቼ ለመጨፈር ክፍሉ ውስጥ ያሉትን ጠረጴዛና ወንበሮች ጥግ ጥግ ማስያዝ የሚጀምሩት ምክንያት ፈልገው ነበር። ኮሽ ባለ ቁጥር ከበሮ ያነሳሉ። መደሰት መጫወት ነው። ስደትን አቅደውና አስበው ስለጀመሩት ይሆን ወይም በሌላ መሰደዳቸው ሲቆጫቸው አይታዩም። ለመሰደድ ምክንያት የሆናቸውን መንግስታቸውን ሲቃወሙ አይሰሙም። ፖለቲካ እንዲገባቸው የሚሞክሩት ከኢትዮጵያ ጋር ሲሆን ብቻ ይመስላል። አብዛኞቹ ፖለቲካ ከተነሳ መጀመሪያውም መጨረሻውም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ያደርጉታል።

አማርኛ ሙዚቃን አዘውትረው ይሰማሉ፤ እንትናንም ጨምሮ፤ አማርኛን የማይረዱትም ጭምር። የአማርኛ ሙዚቃ ፍቅራቸው ቋንቋውን በማይረዱት ይብሳል። አንዳንድ ጊዜ በአማርኛ ያልተዜሙ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችንም እንደአማርኛ ቆጥረው ትርጉሙን እንድነግራቸው ይጠይቁኛል። እኛ ለመለየት የምንቸገራቸውን ዘፋኞች እነሱ ክብር ሰጥተው ያደምጧቸዋል። ሙዚቃ ቋንቋ ነው ይሉሃል ይህ ነው።

የሆነው ሆኖ ያን ቀን ጠሉኝ፤ እየገላመጡኝ ጥለውኝ ሄዱ። በሰዎች መካከል ያለ ፍቅር እንዲህ በቀላሉ የሚናድ ከሆነ ፍቅሩ የውሸት ነበር ለማለት ምንም አያስፈራም። ለነገሩ እኛስ እርስ በርሳችን ከዚህ ባንብስ ነው? ከመብላትና ከመጠጣት ውጪ ምን ቁም ነገር ኖሮን ያውቃል? ምናልባት በአንድ አይነት ቋንቋ ፖለቲካውን እንተነትነው ይሆናል እንጂ መች ለቁምነገር ታደልን። ይህም በስመ አበሻ ዝም ብሎ ሊዋደድ ሞክሯል እንጂ ከእንጫወትና ከእንብላ ያለፈ መተሳሰብ በአበሻው ውስጥ እንደሌለ ያሳያል።

ሁለት አመት ባልሞላው የስደት ህይወቱ ይህን ያህል ልምድ ማዳበሩ እየደነቀኝ ልሸኘው ተነሳሁ። ሸኝቼው ስመለስ ስለሱ እያሰብኩ ነበር ወደ ቤቴ የገባሁት። ሁሉን እያባከነች ያለችው አውሮፓ ሳሚንም እያባከነችው እንደሆነ ገብቶኛል።

(ይቀጥላል)
----
የስደተኛው ማስታወሻ ቀደምት ጽሑፎች፡- ክፍል አንድ.... ክፍል ሁለት.... ክፍል ሦስትክፍል አራት
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸውethioswe13@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment