Friday, July 5, 2013

Re: ስለምንስ ከምሁራን መካከል ትፈልጉኛላችሁ? !





የትምህርት ጉዞው የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ ተማሪዎች በምረቃ ቀን የሚለብሱት ጋወን አስመራቂ ቤተሰቦቻቸው ወደ ምረቃው ቦታ የሚገቡበት የመግቢያ ትኬት ከየትምህርት ክፍላቸው እየወሰዱ ነው፡፡ አንድ ከዚህ በፊት ያልተለመደ ተግባር ግን ይቀራል፡፡ የአንድ ሙሉ ቀን ስልጠና፡፡ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በመጡ ባለሙያዎች ከምረቃ በኋላ ሊሰማሩባቸው ስለሚችሉባቸው የስራ አይነቶች፡፡

ገነትም ከነዚህ ሰልጣኞች መካከል አንዷ ስትሆን 3 አመት የዩንቨርስቲ ቆይታዋ Applied Biology ያጠናች ስትሆን ከተቻለ አንድ ፋርማሲ ውስጥ ሰራተኛ ሆና ለመቀጠር አለዚያም መምህር እሆናለው የሚል ህልም ነበራት፡፡ በስልጠናው የሰማችው የስራ መስክ ግን አልተዋጠላትም፡፡ ተደራጅቶ የባልትና ውጤቶችን መሸጥ፣ የከተማ ግብርና ላይ መሰማራት፣ የኮብል ስቶን ማንጠፍ ስራ፣ ፓርኪንግ ..ተ፡፡

አሁን ስልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ተማሪዎችን ከሚያስተምሩት የዩንቨርስቲ መምህራን አንዱ የሆኑት አቶ ዳዊት ገብሩ (ስማቸው የተቀየረ) ግን የምሩቃኑ ብቃት አሳስቧቸዋል፡፡ አቶ ዳዊት የሚያስተምሩት የሞራል ፍልስፍና ትምህርት ሲሆን፤ ሰሞኑን የመጨረሻ ፈተና ለተመራቂ ተማሪዎቻቸው የፈተኑት ሲሆን አንድ የፈተና ወረቀት ግን ይጠፋባቸዋል፡፡ የመጥፋቱን ምክንያት ሲያጣሩም ኩረጃን ለመቀነስ በማሰብ ተማሪዎች ከሌላ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ጋር ተደባልቀው የሚፈተኑ በመሆናቸው እና ፈተናው የጠፋባት ተማሪ የማታውቀውን የሶሻል አንትሮፖሎጅ ፈተና ተፈትና በመውጣቷ መሆኑን ይደርሱበታል፡፡ አቶ ዳዊት ተማሪዋን አስቀርበው ለምን እንዳልተፈተነች ሲጠይቋት፤ እንግሊዝኛ ማንበብ እንደማትችል እና የተፈተነችው ፈተናም የሞራል ፊሎሶፊ ፈተና እንደሆነ አስባ እንደተፈተነች ትናገራለች፡፡

የዲግሪ ምሩቋ የምትፈተነውን ፈተና አለማወቋ አቶ ዳዊትን ግራ ከማጋባትም አልፎ ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል፡፡ እናም ትምህርት ወዴት ወዴት? ብለን እንጠይቅ ዘንድ ተነሳን፡፡
 
ትምህርት

የሰው ልጅ ሁሉን ያውቅ ዘንድ አይቻለውም ስለዚህም ስለ ክዋክብቱ መረዳቱ የበዛለት ላላወቀው እሱም ስለ ስነ ተዋልዶ እውቀቱ ከሌለው ከአዋቂው የሚቀስምበት ስርዓት ነው ትምህርት፡፡ አንድ ሰው አቃቂ ምሁር ይባል ዘንድ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች የዕውቀት ላቂያ ይኑረው ያኔም አዋቂ ይባላል፤ ይለናል Renaissance Man ሕልዮት፡፡ ለዛም ይመስላል በአብርሆት ዘመን  የነበሩ ምሁራን ሁሉን አቀፍ እውቀት ነበራቸው ልንል የምንችለው፡፡ የፍልስፍና፣ የሂሳብ፣ የስነ-ክዋክብት፣ የስነ-ሰብ .. እውቀቶችን አንድ ምሁር አቅፎ ሊይዝ ይችል ነበር፡፡

ይሄ ትክክል አይደለም ይልቅስ በህብረተሰቡ ውስጥ እምርታ ይመጣ ዘንድ የስራ ክፍፍል (Division of Labor) ወሳኝ ነው ብሎ ስኮትላንዳዊው የስነ-ምጣኔ ምሁር አዳም ስሚዝ የሀሳብ ሽግግር ካደረገ ወዲህ፡፡ እያንዳንዱ ህብረተሰቡ አካል አንድ የስራ መስክ ላይ በተለየ (Specialize) አድርጎ ጥናት ካደረገ እና ከተማረ በዘርፉ ትልቅ አስተዋፅኦ ያመጣል በሚል የትምህርት ስርዓቶቹም በዚህ ሀሳብ መቀረፅ ጀመሩ፡፡ ባጫ ምህንድስና አበበ ህግ አይዳ እርሻ .. እየተማሩ በያዙት ሙያ ላቂያን ማሳት ይችላሉ የሚለው Specialization ሕልዮት፤ አሁን ድረስ በትምህርቱ ዘርፍ ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡

ሱፍ ለባሽ ምሁር

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ታሪክ መቶ አመት እንኳን አልደፈነም ፡፡ የመጀመሪያው ዘመናዊ የመንግስት ትምህርት ቤት 1908 ነው የተቋቋመው እስከ ጣልያን ወረራም ብዙ ተማሪዎችን ማስተማር አልተቻለም በአብዛኛውም ከውጭ ተምረው የመጡ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ እንደ ምሁር የሚቆጠሩት፡፡ ከነዚህ በውጭ ተምረው የመጡ 120 ተማሪዎች ውስጥ ጣልያን በተለምዶ የሚያዚያ 28 ጭፍጨፋ ተብሎ በሚጠራው ድርጊት 75 በመቶዎቹን እንደ ገደላቸው የመንግስትን ሪፖርት ጠቅሰው Mrgery Perham, The Government of Ethiopia ባሉት መፅሃፋቸው ያስረዳሉ፡፡

እንግዲህ በጣሊያን ወረራ 75 በመቶ የተማረ ሀይሏን ካጣች በኋላ እስከ ንጉሱ የስልጣን ዘመን ማክተሚያ ድረስ የተማሪዎች ቁጥር (በውጭም በሀገር ውስጥም ተምረው የመጡት) በብዙ እጥፍ ጨምሯል፡፡ ነገር ግን አውሮፓን አይቶ የመጣው ምሁር ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ ከዋና ፈተናዎች አንዱ በተማረበት መስክ ስራ ያለማግኝቱ ነው፡፡ አለ ከተባለ የፈረንሳይ ህግ ትምህርት ቤት ህግ ተምሮ የሀረርጌ አውራጃ አስተዳዳሪ የእልፍኝ አሽከር፣ Literature 4 ዓመት ሙሉ እነ ሸክስፒርን እነ ሞንታኝን፣ እነ ዳንቴን እንዲያም ሲል እነ ቶልስቶይን ሲያጠና ከርሞ በንግድ ሚኒስቴር የወርሃዊ የዋጋ ጥናት ባለሙያ መሆን፣ የምጣኔ ሀብት ትምህርትን እንደ ውሃ ጨልጦ በበጌምድር አውራጃ የደምቢያ ወረዳ የመንግስት ሹም .. እየሆኑ ነበር እነዚህ እውቀትን እና አለባበስን ከአውሮፓ የቀዱ ምሁራን ወደ ስራ አለም የሚሰማሩት ፡፡

በርግጥ   ትውልድም  የዚህ ሱፍ ለባሽ ምሁር አካል ነበር፡፡

የተማረ ሁሉ ያስተምር

ደርጉ መጣ ‹ሁሉንም ነገር ወደ ጦር ግንባር; ከማለቱ በፊት የትምህርት ዘመቻ ጀመረ ‹መሃይምነት አይነስውርነት ነው› በሚል መፈክር የገጠሩን ህዝብ ስሙን ይፅፍ ዘንድ ፊርማ በእርሳስ ይፈርም ዘንድ አስቻለው፡፡ ነገር ግን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚወጡ ተማሪወች የተማሩትን ትምህርት የት አደረሱት ከተባለ፤ ግማሾቹ አቢዮት ጠባቂ፣ ግማሾቹ የቀበሌ ሹም ወታደር ቤትም የገቡ አሉ፡፡

ይልቁንም ደርጉ ተማሪዎችን ከነ ኢህአፓ ጋር 'ንክኪ' አላቸው በሚል በጥርጣሬ ነበር የሚመለከታቸው፡፡ ይባስ ብሎም ከሀገር በፊት የምን ትምህርት ብሎ በተለምዶምሁሩ ጦርየሚባለውን ወታደር ከዩንቨርስቲ አፍሶ ብላቴ ጦር ማሰልጠኛ ከተተ፡፡ የተማሩት ትምህርትም አላማው ጠፋባቸው ለነዚህ ምሁር ወታደሮች፡፡

ስለምንስ ከምሁራን መካከል ትፈልጉኛላችሁ?!

ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ ከሰራቸው አመርቂ ስራዎች አንዱ ትምህርትን በነፃ ተደራሽ ለማድረግ ያደረገው ጥረት እና ያም ያመጣው ውጤት ነው፡፡ አጠቃለይ የትምህርት ፖሊሲ 1986 . ከወጣ በኋላ ብዙ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተሰርተዋል፣ የትምህርት ቤቶች የቅበላ አቅም በብዙ እጥፍ ጨምሯል፣ 30 በላይ የመንግስት ዩንቨርስቲዎች ተገንብተዋል፡፡

ነገር ግን የትምህርት ፖሊሲውን ሁለት ዋነኛ ተግዳሮቶች አንቀው ይዘውታል፡፡

1.
የትምህርት ጥራት ጉዳይ፡

መንግስትም እንደሚለው ዋነኛው የትምህርት ፖሊሲያችን ፈተና የጥራት መጓደል ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታዩንቨርስቲ Chemistry ምሩቅ ተማሪዎች Chemistry Khemistry እያሉ እንደሚፅፉ ይነገራል፤ አራቱን የሂሳብ ስሌቶች የመለየት ችግርም የምሩቃኑ ሌላው ጣጣ ነው፤ በሶሲዎሎጅ ተመርቀው ካርል ማርክስ ሲባል እሱ ደግሞ ማነው? ማለትም ያስደነግጣል፤ ህግ ተምረው Civil Right እና Civil Code ነትን አለማወቅም ይወራል፡፡
አዎ ጥራቱ ችግር ውስጥ ነው፡፡

2.
ሁለተኛው እና አዲሱ የትምህርት ፖሊሲው ችግር ሰዎች ተምረው በተማሩበት ትምህርት መስክ ሊሰሩ አለመቻላቸው ነው፡፡

የማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን
2011 . የከተማ ስራ አጥነት 18 በመቶ እንደሆነ መረጃው ያስረዳል ፡፡ሌሎች አለማቀፍ ተቋማት ደግሞ መጠኑ ከዚህ እንደሚልቅ ይገልፃሉ፡፡


እንግዲህ ከዩንቨርስቲ የሚወጡት ምሩቃን ከነዚህ ስራ አጦች ቁጥር ላይ የሚደመሩ ናቸው፡፡ ይሄን ቁጥር ለመቀነስ ይመስላል መንግስት ሰሞኑን እንደምንሰማው ወጣቶችን በተለያዩ የጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ እያደረገ የሚገኝው፡፡ ችግሩ ግን አንድ ሰው Computer Science ተምሮ የኮብል ስቶን ጠረባ ላይ የመሰማራቱን ጥቅም ስናሰላስለው ነው፡፡ ችግሩ ግን አንድ ወጣት Physics ተመርቆ በከተማ ግብርና ተግባር ላይ ሲሰማራ የተማረውን ትምህርት ተግባር ላይ እንዴት ሊያውለው ይችላል? ያልን እንደሆነ ነው፡፡ ችግር የሚሆነው Afan Oromo & Literature የተማረች ወጣት በባልትና ውጤት ስራ ላይ ተሰማርታ ስናይ ነው፡፡
ለመሆኑ: ይሄ ስኬት ነው እንዴ?

Nelson Mandela
በግለ-ታሪካቸው ላይ ስለ ትምህርት ሲናገሩ :

"Education is the great engine of personal development. It is through education that the daughter of a peasant can become a doctor, that a son of a mineworker can become the head of the mine, that a child of farm workers can become the president of a nation."

አሁን ወዳለው ሀገራችን የትምህርት ውጤት ስንሄድ ማንዴላ እንደሚሉት ትምህርት የገበሬውን ልጅ ዶክተር የማዕድን ቆፋሪውን ልጅ የሀገር መሪ የሚያደርግ መሳሪያ ነው ያሉትን የትምህርት Upgrade የማድረግ ሚና Downgrade በማድረግ የተተካ ያስመስለዋል፡፡ አለዚያማ ስለ ፓለቲካል ህልዮት ሲማር የከረመ ወጣት እንዴት የብየዳ ስራ ላይ ይሰማራል?፡፡

ገነትስለ ስራ አስበሽ ታወቂያለሽ?›› ተብላ ስትጠየቅ ‹‹እኔ የምማረው እናቴ ተመርቄ ስታየኝ ደስ እንዲላት ነው እንጅ ስራ መስራት አልፈልግም›› ትላለች፡፡ የሞራል ፍልስፍና ፈተናን ከሶሻል አንትሮፖሎጅ ጋር ጋር መለየት አቅቷት ፈተናውን ሳትወስድ ቀረችው ምሩቅ ለስህተቷ የምትሰጠው ምላሽ ፈገግታ ነው፡፡ እንግዲያውስ ገነቶችን ከምሁራን መካከል መፈለግ ምን ይሆን እርባናው?




No comments:

Post a Comment