Friday, April 26, 2013

#Ethiopia: የስደተኛው ማስታወሻ ከአውሮፓ


(ክፍል ፪)

ናፍቆት

እስክትመጪ ያልኩሽ ስትመጪ ከምትደናገሪ ቀድመሽ እንድትዘጋጂ ብዬ ነው፡፡አንቺ ብቻ ሳትሆኚ ማንም ለመሰደድ የሚቋምጥ ሁሉ እስኪሰደድ የስደትን እውነተኛ ገፅታ ይወቅ ለማለት ነው! እስኪመጣ ይወቅ! እስክትመጣ ትወቅ! እስኪመጡ ይወቁ! ስለ አውሮፓ አእምሯችሁ የሚነግራችሁ ወሬ ውሸት ነው።ስለአውሮፓ ሰዎች የሚነግሯችሁ ሃሰት ነው። አትመኗቸው፤ እወቁና ራሳችሁ  ፍረዱ፤ እወቁና ተዘጋጅታችሁ ወደ አውሮፓ ለማለትም ጭምር ነው፡፡

ከአገርሽ እንደወጣሽ ብዙ ፈተና ይጠብቅሻል። አንዱ ፈተና ናፍቆት ነው። የማይናፍቅሽ ነገር የለም፤ አንተ ብቻ ነህ የምትናፍቀኝ አንተን ካገኘሁ ምንም አይናፍቀኝም የምትይውን አነጋገርሽን የምታፍሪበት እዚህ መጥተሽ ያቺ ለማየት የምተፀየፊያት ሽሮ ከሁሉ በላይ ስታሳሳሽ ነው። አምርረሽ የጠላሽው ወይም እጅግ የሰለቸሽ ሁሉ እየፀፀተሽ ይናፍቅሽ ይጀምራል። የምትወጃቸውንማ ማናገር እስኪያቅትሽ ድረስ ሲቃውን አትችይውም። ቤተሰብሽን፣ ጓደኞችሽን ስታናግሪ ያኔ እኔን ከተለያየን ከሶስት ሳምንት በኋላ ስደውልልሽ እንደሆንሽው ትሆኛለሽ። ናፍቆት አንደበትሽን ይሸብበዋል፣ ናፍቆት ቃልሽን ያጠፋዋል፣ ናፍቆት አልቃሻ ያደርግሻል። ስለዚህ መለስ ቀለስ የምትይበትን የስደት መንገድ መምረጥ ይኖርብሻል።

እኔን ናፍቆት እንዴት እንዴት እንዳረገኝ ልንገርሽ፦ እንደገባሁ ትውልደ ፓኪስታን ከሆነ አንድ ጎልማሳ ላይ የተከራየኋት ጠበብ ያለች ቤት ነበረችኝ። ረከስ ያለችውን መርጬ ነበር የተከራየሁት። ሳሎን እና ኩሽና የጋራ ሲሆን መኝታ ቤት እና ሽንት ቤት የግል ነበር። ከዚህች ቤቴ በተቃራኒው የከተማው ክፍል የሚገኘውን ዩኒቨርሲቲ ለመድረስ ከአንድ ሰአት በላይ እጓዝ ነበር።

ጉዞው ረጅም ቢሆንም ለውጪው ዓለም አዲስ በመሆኔ ምክንያት በየመንገዱ የማየው ትዕይንት የጉዞውን ርዝመት እንዳይታወቀኝ አድርጎኝ ነበር። ሁሉም ነገር ይገርመኝ ስለነበር አንዱን አይቼ ሳልጨርስ ሌላው እየተተካ እንዲችው እየተቁለጨለጭኩ ነበር የምመላለሰው። ጠዋት ጠዋት በምድር ውስጥ ባቡር ላይ ተጠቅጥቀውና ተኮራርፈው ከሚጓዙት ፈረንጆች ውስጥ ጋዜጣ የማያነብ ሰው ማግኘት ይከብዳል። ይህን ሳይ ባቡሩንም፣ አንባቢውንም፣ ጋዜጣውንም እመኛለሁ። አገሬ ላይ እንዲህ አይነት ትዕይንት መቼ ይሆን የማየው እያልኩ። ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደ ልደታ በምድር ውስጥ ባቡር እየሄድኩ እለታዊዋን አዲስ ነገር ጋዜጣን እያነበብኩ ብጓዝ፤ ማይጨው አደባባይ ወርጄ መስመር ስቀይር ከባቡሩ ጉርጓድ መውጫ በር ላይ እንደ ስሙ የዘመነውን አዲስ ዘመንን ገዝቼ ወደ ልደታ ለመሄድ ስሸጋገር እያልኩ እመኝ ነበር። (ይህን እየተመኘሁ ትምህርት ቤት ደርሼ ኢሜሌን ስከፍት አንዱ ወዳጄ አንድ መልዕክት አስቀምጦልኝ አገኘሁ። የሰላም ያርገው ብዬ ብከፍተው ‘ዘጓት’ ይላል፤ የምድር ውስጥ ባቡሩን ብንሰራው እንኳ ጋዜጣውን ርሳው ማለቱ ነበር።)


ምኞት ብቻ ሆኜ ሁሌ ስለአገሬ ሳስብ ስለምውል የባሰ የአገሬ ሰው እየናፈቀኝ ሄደ፣ በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራቶች ውስጥ አማርኛ ያወራሁት በስልክ ብቻ ነበር። ስጓዝ ከምመኛቸው ክስተቶች ባሻገር የአገሬን ሰው ለማግኘት አይኔ ይቅበዘበዛል። አንድ ሁለቴ አበሻ የመሰሉኝን ሰዎች ሰላምታ አቅርቤ ተሸውጃለሁ። ነብር ዝንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊነቱን አይለቅም የሚለውን ነገረ መጽሃፍ ቅዱስ አውቃለሁ ብዬ ሰላምታ ሳቀርብ ሰምቼ በማላውቀው ቋንቋ መልስ አገኘሁና አረፍኩት። ይጥቆርም ይቅላም፣ ይርዘምም ይጠርም፣ ይወፍርም ይክሳም፣ ሴት ብትሆንም ወንድ፤ ሳይናገር ሳይጋገር የማየው ሰው ከሃበሻ ምድር እንደፈለሰ ለማወቅ አልቸገርም የሚል ትዕቢት ነበረብኝ። ከሁለቱ ሙከራዎቼ ቡሃላ ግን ትዕቢቴም ተነፈሰና ሙከራዬን አቆምኩ። ስለሆነም ወደዘወትር ምኞቴ ተመልሼ ያየሁትን ጥሩ ነገር ሁሉ፤ ይህ ኢትዮጵያ በኖረ፣ ይህን አገሬ ስመለስ እሰራዋለሁ እያልኩ መጓዜን ቀጠልኩ።

በነዚያ የትኩስነት ወራት ባንዳቸው ቀን ሁሉን ነገር እየተመኘሁ አንድ ፌርማታ ላይ ቆሜ በብቸኝነት እየተከዝኩ አውቶቡስ እጠብቃለሁ። ከክፍል እንደወጣን ከባድ ዝናብ ይጥል ነበር። ዝናቡ እስኪያባራ ስጠብቅ ዘወትር የምጓዝበት ባቡር ጥሎኝ ሄደ። የሚቀጥለው እስኪመጣ ላለመጠበቅ በአውቶቡስ ልሄድ ወስኜ እየጠበቅኩ ስላንቺ አስባለሁ። ባትመጪና እኔ ብመለስ እያልኩ እመኛለሁ። አንቺን አስጥሎ ያሰደደኝ እውነት አሁን አሁን አልጥምህ እያለኝ ተቸግሬያለሁ። የትምህርቱ ቀላል መሆን አሁንን እንዳላስብ አድርጎ ስላለፈውና ስለወደፊቱ እንድጨነቅ አድርጎኛል።

እኔና አንቺ የተፈጠርነው ለመፈቃቀር ነበር፤ በሚገባ ተፈቃቀርን። እነዚያ የማታውቂያቸው አለቆቼ ለምን ይሆን የተፈጠሩት? እነሱን ሳስባቸው ይገርመኛል። ልጆች ወልደዋል፤ ሚስት አላቸው። ታዲያ ከአጋራቸው ጋር ይፈቃቀራሉ ማለት ነው? እኔ እንደሚመስለኝ  መፈቃቀር ሲያቅተን ነው የሰዎችን ፍቅር ለመበጠስ የምንነሳው። መፈቃቀር ሳንችል ስንቀር ነው ለምድር አሜኬላ የምንሆነው። እኔ አንቺን ያፈቀረው ልቤ ሌላ ሰው ላይ ክፋትን ይፈፅማል ብዬ አላምንም። አንቺን ያፈቀርኩ ዕለት ጥሩ ሰው መሆኔን አውጅኩ። አንቺን ያፈቀርኩ ዕለት ለማንም ይማልጎረብጥ ጥሩ ዜጋ መሆኔን አረጋገጥኩ። አንችን ከማፍቀሬ በፊት ግን በልምዴና በዕውቀቴ መጠን የምመራ ከንቱ ሰው ነበርኩ።

የማፍቀርን ጥቅም የረሱትን እነዛን አለቆቼን እያሰብኩና ልቦና እንዲሰጣቸው እየተመኘሁ አውቶቡስ ጥበቃዬን ቀጥያለሁ። እንደድንገት አይኔን ወደጎኔ ላክ ሳደርግ የብርጭቆ ቂጥ የሚመስል መነፅሩን ገርግዶ አንድ አይነ ውሃው ከአበሻ ወገን የሚመስል ሰው ከጎኔ ቆሞ እሱም እንደኔ አውቶቡስ ይጠብቃል። ልብ ብዬ ሳየው የማውቀው የማውቀው ሲመስለኝ በድፍረት ወደ ልጁ ሄድኩና ሰላምታ ሰጠሁት።
ለሰላምታዬ ምላሽ በአማርኛ ሲመልስልኝ ልጨብጠው የዘረጋሁትን እጄን አስረዝሜ ተቃቀፍን፡፡ ሳሚ እባላለሁ አለኝ ስሜን ነገርኩት። ከዚያም ብርቅ ሆነብኝ መሰል ብዙ ጥያቄዎች ጠየቅኩት። ከሶስት ጓደኞቹ ጋር እንደሚኖር ሲነግረኝ ወደሚሄድበት ይዞኝ እንዲሄድ ለመንኩት። ትንሽ አቅማማና እሺ አለኝ። እያወራን ተያይዘን ወደመኖሪያቸው ሄድን።

አውሮፓ ላይ የአገርሽን ሰው ለማግኘት ያለሽ እድል እንደ አመጣጥሽ ይወሰናል። ጥገኝነት ልትጠይቂ ከመጣሽ በቀላሉ ከወገኖችሽ ጋር ትገናኛለሽ። እንዲያ ሲሆን አንቺን የሚናፍቅሽ ናፍቆት እኔን ገጥሞኝ ከነበረው የአማርኛ ናፍቆት ይለያል። ያን ቀን ያገኘሁት ልጅ ሌላ ቦታ ጓደኛ ለመጠየቅ ሄዶ እየተመለስ ነበር። አብሬው ስጓዝ እጅግ ደስ ብሎኝ ነበር። ለምን ደስ እንዳለኝ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ። አገርሽ ላይ ተቀምጠሽ ይህን እያነበብሽናፍቆት ነውብልሽ እንደምፀት እንደምትቆጥሪው ይገባኛል።

ከሳሚ ጋር በተስማማነው መሰረት ሰፈሬ መውረዱን ተውኩትና አብሬው ሄድኩ። መኖሪያቸው ከከተማው ጥቂት ወጣ ይላል። እንደደረስን እንደ ተማሪ ዶርም ከተደረደሩ ክፍሎች ውስጥ አንዱን ከፍቶ ገባን። በክፍሉ ውስጥ ሁለት አልጋዎች አሉ። ማንም ሰው ክፍሉ ውስጥ አልነበረም። ማንም አለመኖሩን ሲያይ ስልኩን አወጣና ደወለ።
የት ነው ያላችሁት?’በስልኩ ውስጥ ትንሽ አወራና ስልኩን ዘጋ።ቦርሳህን እዚሁ አስቀምጠውና እንሂድ ከጓደኞቼ ጋር ላስተዋውቅህአለኝና ለብሶት የነበረውን የብርድ ጃኬት አውልቆ ወደ በሩ አመራ። ሕንፃው ባለ አንድ ፎቅ ነበር። የነበርንበት ክፍል አንደኛው ፎቅ ላይ ስለነበር ወደ ምድር ወረድንና የጓደኞቹን ቤት አንኳኳ። ከውስጥ ደራ ያለ ወሬ ይሰማል፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ በማወቄ የበለጠ ደስ አለኝ።

የሚገርመው ይህን ያህል ሰው እንደምወድ ያወቅኩት ከአገሬ ስወጣ መሆኑ ነው። አንቺም ዛሬ አገርሽ ላይ ሁሉንም ባይሆንም የፈለግሺውን መውደድና ማድረግ ትችያለሽ፤ ግን በእጅ የያዙት ወርቅ ስለሆነ ምንም አታደርጊም። እዚህ ስትመጪ ግን እንዲህ በሆንኩ ኖሮ፣ ያን ባደርግ ኖሮ፣ ይህን በጎበኘሁ ኖሮ እያልሽ መቆጨት ብቻ። በዚህች አጭር የህይወት ጉዞ እንደ ኢትዮጵያዊ ተፈጥረሽ እሱን ንቀሽ ያልሆንሽውን ለመሆን እየጣርሽ የሰውን ስታባርሪ እንዲሁ ማለፍ የሚያስቆጭ አይመስልሽም?

ሳሚ ከሶስቱም ልጆች ጋር አስተዋወቀኝ። ስናወራ አመሸንና መሸትሸት ሲል ስልካቸውን ተቀብዬ እየፈነደቅኩ ወደ ቤቴ አመራሁ።

የምቾት ውስጥ ፍዳዎች

መንግስቱ ሃይለማርያም በዘመናቸው የነበረውን ወጣትና ማህበረሰቡን ሲተቹ ‘ወደ ማሰልጠኛ ሲወሰድ ገና ጦር ሜዳ ሄጄ ጥይት ይገለኛል ብሎ በማሰብ ከሚበር መኪና ላይ እየዘለለ እየወረደ የሚሞት ወጣት ነው የሚላክልን’ ብለው ነበር። ብሄራዊ ውትድርና በደፈናው እንደመቅሰፍት ተቆጥሮ ስለነበር ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ዘመቻው እንዳይሄዱ ለማድረግ በምድር ውስጥ፣ በጎተራ፣ በድብኝትና በቋት ውስጥ ይሸሽጓቸው እንደነበር ይነገራል። ውትድርናን አንዴ ማህበረሰቡ አውግዞታልና በዘመኑ የነበረውም ወጣት ተልዕኮውን ለመጥላት ምክንያት አላስፈለገውም። ለዚህም ነበር ተልዕኮውን ለማምለጥ ሲባል በያንዳንዱ ሰው ይደረግ የነበረው መስዋዕትነት ከተልዕኮው በላይ ሲያስከፍል የነበረው።

ውዴ- የአሁኑ ዘመን እርስ በርስ ጦርነት የለም፣ ብሄራዊ ውትድርናም የለም። ማህበረሰቡ በደፈናው የሚጠላውም ልጆቹንም የሚያስደብቅ ነገር ዘንድሮ የለም። ግን ልጆቹን እንደወጡ እያስቀረ ያለ ክፉ መቅሰፍት መልኩን ቀይሮ መጥቷል። ይህም መቅሰፍት ስደት ነው። ዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጫካዎች፣ ወደ ሰሜን አፍሪካ በረሃዎች እና ወደ ምስራቅ አፍሪካ በባሕር ላይ በጅምላ ማለቅ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የተለመደ ክስተት መሆኑን በየሚዲያው ላይ ትሰሚያለሽ፡፡ወጣቱም ቢሆን በስደቱ ውስጥ ስላለው አደጋና እልቂት ማሰብም ሆነ ላለመሰደድ የሚጠቅሰው ምክንያት አያስፈልገውም። በቃ ሁሉም በጭፍን መሰደድን ይመርጣል። ባገኘው ቀዳዳ ተጠቅሞ ነቅሎ አገር ጥሎ ይኮበልላል።

ለምሳሌ ባለፈው የተፈጠረውን ክስተት ላስታውስሽ፡፡
2004 አጋማሽ ላይ የተፈጸመ አሳዛኝ ስደት ነው። በተሳቢ መኪና ላይ በተጫነ ኮንቴይነር ውስጥ ታጭቀው ከናዝሬት የተነሱት 70 የሚሆኑ ወገኖቻችን ወደጅቡቲ ያመራሉ። ጅቡቲ ደርሰው ከዚያም ወደ አረብ አገር ለመሻገር አልመው። ስለሁኔታው ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ተሳቢውን መከታተል ይጀምርና በአንድ የአፋር በረሃ ውስጥ ደርሶበት መኪናውን ያስቆመዋል። የፖሊስን መምጣት ቀድሞ ያስተዋለው ሹፌር መኪናውን አቁሞ ይሸሻል። የክልሉ ፖሊስ በአፋር በረሃ ውስጥ ተሳቢውን ሲደርስበት ከኮንቴይነር ውስጥ ካሉት ሰዎች ውስጥ 11 የሚሆኑት ጅቡቲን ለዘላለም ሳያዩዋት አልፈዋል። ፖሊሶቹ የኮንቴይነሩን በር ለመክፈት ጥቂት ደቂቃዎችን ቢዘገዩ ኖሮ ደግሞ ሁሉም መንገደኞች በመታፈን ያልቁ ነበር።

አሁንም በተመሳሳይ ወቅት ሌላ አሳዛኝ ክስተት ሰምተናል። የጉዞአቸው አላማ ከአገራቸው ተነስተው ደቡብ አፍሪካ መድረስ የነበረው ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች በታንዛንያ በኩል ህገ-ወጥ በሆነ ሁኔታ ወደ ማላዊ ያቋረጡት በጀልባ ነበር ይሁንና 28 ሰዎች ብቻ የመጫን አቅም ነበራት የተባለችው ጀልባ ላይ ወደ 60 የሚጠጉ ስደተኞች በመጫናቸው ጀልባዋ መገልበጧ ነበር በወቅቱ የተዘገበው። ይህች ኢትዮጵያውያንን የጫነች ጀልባ በማላዊ ሃይቅ ላይ በመገልበጧ 47 ኢትዮጵያን ወንዶች፣ ሴቶችና ህጻናት ሞቱ። የአካባቢው ነዋሪዎችም የኢትዮጵያውያኑን አስከሬን ከሃይቁ ዳርቻ ጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ በጥድፊያ  ቀበሩት። ኢትዮጵያዊ ክብር አያስፈልገውም ብለው ማስ ማስ አድርገው የቀበሩትን አስከሬን ለኢትዮጵያውያኑ ክብር የነፈገ ድርጊት ነው ያለው ቀይ መስቀል እንደ አዲስ ስራዓትን የጠበቀ ቀብር እንዲፈጸምላቸው ቢያደርግም ኢትዮጵያውያኑ ግን እንደወጡ ቀርተዋል።

አለም ዓቀፍ የስደተኞች ማሕበር (IOM) እንደሚለው በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ በአመት ከሁለት በላይ ኢትዮጵያውያን ያልቃሉ። በጥቅምት ወር 2005 መጨረሻ አካባቢም ከሶማሊያ ቦሳሶ ወደብ ሁለት ስደተኞችን የጫኑ ጀልባዎች ይነሱና ጉዟቸውን ወደ የመን ሸጉዋ ያደርጋሉ። ሁለቱም ጀልባዎች ሸቡዋ ወደተባለው የየመን ጠረፍ እየተቃረቡ ሳለ አንዱ በመስጠሙ ምክንያት 72 ኢትዮጵያውያን አስከሬን በባሕሩ ላይ ተንሳፎ እንደተገኘ ታውቋል። በዚህ የመስመጥ አደጋ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በትክክል የማይታውቅ ሲሆን 72 የተባለው ባህሩ ላይ ሬሳቸው ተንሳፎ እና ባህሩ ወደዳር ተፍቷቸው የተገኙት ብቻ ናቸው፡፡

በደርግ ዘመን እንደ ሃጢአት ተቆጥሮ የነበረው ብሄራዊ ውትድርና በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ እንደ ጀብድ ሲቆጠር አይተናል።  የትኛው ጦርነት ምክንያታዊ እንደሆነ መጠየቅ የማያስፈልገው የእኛ ሰው ጥሩን ከመጥፎ የሚለየው እንዴት እንደሆነ ግራ ያጋባል። በመንግስት በኩል የሚነገረውን በማመን ነው እንዳይባል ‘ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር’ የሚለው የደርግ ድምፅ አይሰማም ነበር። ስለዚህ የእኛ ሰው ጦርነትን እንደመጥፎ ይቆጥራል ማለት ይከብዳል።


ውዴ- በየጦር ግንባሩ ይሞት ከነበረው ያልተናነሰ ወጣት በስደት መንገድ ላይ እንደወጣ በሚቀርበት ጊዜ ላይ እንደደረስን ይሰማኛል፡፡ ታዲያ ይህ እየታወቀ ልጆቹን ወደ ጦርነት ሲልክ እንዲያ ሲያለቅስ የነበረ ማህበረሰብ ወደ ስደት ሲልክ እንዲህ የሚስቀው ለምን ይሆን? በጦርነቱ ውስጥ መሞት፣ መማረክ አሊያም ማሸነፍ ይኖራል፤ በስደቱም ውስጥ መሞት አለ፣ በአካል ሳይሞቱ በመንፈስ መሞት አለ፣ ታስሮ መሰቃየት፣ መጠረዝ፣ በምቾት እየኖሩ ራስን ማጣት የመሳሰሉት እንግልቶች አሉ። ጦርነት ገዳይ እንደሆነ እሙን ነው ነገር ግን ስደቱም የዕድል ጉዳይ ካልሆነ በቀር ገዳይ ነው። ከብዙሃኑ ስደተኛ ጥቂት የታደሉ ይሳካላቸው ይሆናል እንጂ በዘፈቀደ ተሰደው ሰው የሚሆኑ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ታዲያ ይህ ፀሃይ የሞቀው ዕውነት እያለ ስደትን እንደበጎ ቆጥሮ ሁሉም ሰው ለምን አልሰደድ እንዲል ያደረገው ማን ይሆን?

ውይ የጀመርኩልሽን ታሪክ ረስቼ በገዛ ራሴ ብሶት ውስጥ ይዥሽ ጠፋሁ አይደል? ኢትዮጵያውያን እንደኑሯቸው የተለያየ የስደት መንገድ አላቸው። ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የሚሄዱት የስደት መንገድ፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው የሚጓዙበት የስደት መንገድ እና በድህነት አረንቋ ውስጥ የተዘፈቁ የሚሄዱበት የመሰደጃ መንገድ ለየቅል ነው።  የመንገድ ፈተናው እንደገቢያቸው ቢለያይም የስደት መዳረሻቸውን ከረገጡ ቡሃላ ግን ፈተናው ለሁሉም እኩል ይሆናል። በቦይንግ ተንፈላሶ የተሰደደውም በባሕር ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ እያለ የተሰደደውም እኩል የሚዳኙበት የስደት ህይወት ላይ እኩል ይቀመጣሉ። አብዛኞቹ ከአገራቸው የተሰደዱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ቢገምቱትም በውል የሚያውቁት ግን ጥቂቶች ናቸው። የስደት ምክንያታቸው በአገራቸው ተስፋ መቁረጣቸው ቢሆንም የብዙዎቹ ተስፋ መቁረጥ ግልፅ አይደለም። ምን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ሳያውቁት እንዲሁ ተስፋ ይቆርጡና አንዳንዶቹ የተደላደለውን ኑሯቸውን በትነው ለስደት ይነሳሉ፣ አንዳንዶቹ ጅምር ልፋታቸውን አጨናግፈው ለስደት ይዳረጋሉ የተቀሩት ደግሞ የበይ ተመልካች መሆን ያቅታቸውና አገር ጥለው ይፈረጥጣሉ። ግን ከነዚህ አንዱም ለመሰደድ እንደምክንያት ስለማይቆጠር ሁሉም የስደት ህይወትን ተደላድሎ ለመጀመር ፈተና ይሆንባቸዋል።

ኢትዮጵያውያን በአምባገነናዊ ስርዓት ስር እየማቀቁ፣ እጅግ ባልተስተካከል አስተዳደር ውስጥ እየተጎሳቆሉ፣ በሙስና የተበከለ ስርዓት ውስጥ እየዳከሩ፣ በከፋ ድህነትና ርሃብ ውስጥ እየኖሩ እንደሆነ ቢታወቅም እነዚህ ምክንያቶች ግን አንድን ዜጋ ለስደት ሊዳርጉት እንደማይችሉ ይነገራል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰኔ 1943 ስለጥገኝነት ያስተላለፈው ድንጋጌ ማን ጥገኝነት እንደሚገባው በግልፅ አሳውቋል። በዚህ ድንጋጌ መሰረት ሰዎች የጥገኝነት መብታቸው ይከበርላቸዋል። በዚህ አንቀፅ መሰረት የኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ማመልከቻ ሲዳኝ ስደታችን ከድንጋጌው ጋር ተያያዥነት የለውም ተብሎ በተለያዩ አገሮች መንግስታት ይታመናል። የምንሰደደው አገራችን ላይ ለመኖር ፈርተን ሳይሆን የተሻለ ሕይወት ሽተን እንደሆነ እና መንግስታችንም አንፃራዊ ሰላምና ዲሞክራሲን እንደመሰረተ ይነግሩናል።ከዚህ በሁዋላ የምነግርሽ ያጋጠሙኝ ታሪኮችም እነዚህን ህግጋትና አስተሳሰቦች የመሸወድና እንደማንኛውም ሰው ተቆጥሮ የመኖር ትግሎች ናቸው፡፡ ጥገኝነት የማግኘት ጥበቦች የሚል መጽሃፍ የሚያጽፉ ብዙ ገጠመኞች እዚህ አሉ፡፡ ሁሉም ግን ኢትዮጲያዊነት የት ደረስ እንደረከሰ የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ እነሳሚ አብረው የሚኖሩበትን ቦታ እና ጓደኞቹን እየለመድኩኝ ስመጣ ብዙ ታሪኮቻውን ለመስማት እድሉን አግኝቻለው፡፡ ይህንን አይነቱን ውስጥን የሚነካ ታሪክ ለአንቺ ካልነገርኩ ለማን እነግራለሁ?

(ይቀጥላል)
----
ክፍል አንድን እዚህ ክሊክ በማድረግ ይመልከቱ!
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው tizusola@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

No comments:

Post a Comment