Thursday, July 18, 2013

በጭቆናና በበደል የተፈተነ የፍትህ እና እኩልነት አባት - ዶ/ር ቢሂምራዎ ራምጂ አምበድከር (ክፍል ፬)

በማናዬ በላይ

      VII.        የአምበድከር እና ጋንዲ አለመግባባት
    ማህተመ ጋንዲ ከአምበድከር በብዙ እድሜ የሚበልጥ ቢሆንም ሁለቱም የህንድ አይከኖች በተመሳሳይ ወቅት በህንድ ፖለቲካ ስርዓት ዉስጥ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በትምህርት፣ በአንደበተ ርቱዕነት፣ በፍልስፍና አምበርከር ከጋንዲ ብዙ ርቀት የተጓዘና ለዉድድር የሚቀርብ ባይሆንም በወቅቱ በፖለቲካ ተቀባይነት እና በድጋፍ ጋንዲ ከአበድከር እጅጉን የበዛ ድጋፍ ነበረዉ፡፡ በዛ ወቅት ከጋንዲ የተለየ ሀሳበ መያዝ በራሱ ከህዝብ ጋር ከማጋጨት በተጨማሪ በወቅቱ በህንድ እንደ ፋሽን ተይዞ ለነበረዉ ፖለቲካዊ ግድያ ሊዳርግ ይችላል፡፡ የከፍተኛ ካስት አባል መሆኑ እንዲሁም ህንድ ጀግና በተጠማችበት ጊዜ የመጣ መሆኑ ጋንዲን ለእዉቅናዉ ጠቅሞት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ጋንዲን ተቃዉመዉ ሃሳባቸዉን በግልፅ ከሚያንፀባርቁ ግለሰቦች መሀከል ዶ/ር አምበድከር ዋንኛዉ ነበር፡፡
    ጋንዲ የሁሉም ሂንዲ ሹድራን ጨምሮ ወኪል ነኝ ብሎ ስለሚያስብ ከሱ ዉጭ ያለ ማንኛዉንም መሪ አይቀበልም አምበድከር በበኩሉ የሹድራና እና የሌሎች ካስት ሂንዱ ጥያቄ አንድ ካለመሆኑ ባሻገር የሚጋጭ በመሆኑ ጋንዲ ሊወክለን አይችልም የሚል ቆራጥ እሳቤ ነበረዉ፡፡ በዚህ መሰረት እንግሊዞች ይህንን ተቀብለዉ ይመስላል ለንደን ላይ በ1930-32 ስለ ህንድ ፖለቲካል ስርዓት ለመወያየት ለተከናወነዉ ስብሰባ አምበድከር የሹድራ መሪ ሆኖ እንዲሳተፍ ደብዳቤ ይደርሰዋል ይህንን ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋንዲ ጥሪ አምበድከር እና ጋንዲ ቦምቤ ተገናኝተዉ የተወያዩ ሲሆን ዉይይቱ ባለመስማማት የተቋጨ ነበር፡፡

    ዶ/ር አምበድከር ለሹድራ ጭቆናና የበታችነት ዋንኛ ተጠያቂ አድርጎ የሚያቀርበዉ የካስት ስርዓቱን ሲሆን ለዚህ መወገድም አበክሮ ይሰራ ነበር፡፡ የሹድራን የአገልጋይነት እና የበታች ሆኖ የመኖርን ስርዓት ሕግ በሚመስል መልክ የሚገልፀዉ የማኑስምሪትን (የሂንዱ የሐይማኖት መጻሕፍ) በማቃጠል በወቅቱ እንደ ታቡ የማይወራበትን የሂንዱ ሐይማኖት መሰረት የሆነዉ ካስት ይወገድ ዘንድ በግልፅ በመስበክ፤ ይህንንም ለማሳካት የፖለቲካ ስልጣን ወሳኝ መሆኑን በማመን ወደ ፖለቲካዉ ገብቶ ጫና በመፍጠር በመጨረሻ ዉጤታማ የሆነበትን ሕገ መንግስት ለማፀደቅ በቅቷል፡፡

    የጋንዲ እሳቤ ከዚህ የተለየ ነበር እሱ የካስት ስርዓት የህንድ ማኅበረሰብ እሴት አድርጎ የሚያስብ የማኅበረሰብ በደል ያልቆጨዉ ለመሰረታዊ ለዉጥ ሳይሆን በጥቃቅን ነገሮች ጥያቄዎን ለማድበስበስ  የሚጥር ነበር፡፡ እንደ ምሳሌ ጋንዲ መሰረታዊ ችግሩን ለማስወገድ ከመስራት ይልቅ አይነኬ የሚለዉን የዚህ ማኅበረሰብ ስያሜ በሀሪጃን (የአምላክ ልጆች) በሚል እንዲቀየር እንዲሁም ካስትን ከማስወገድ ይልቅ ከካስት ዉጭ ያሉትን የመጨረሻዉን ሹድራ ካስት ሰጥቶ ማመሳሰልን የሚሰብክ ነበር (አይነኬዎች በመጨረሻዉ ዝቅተኛ ቫርና ያሉት እና ካስት የሌላቸዉን ሂንዱ ይጨምራል)፡፡ ጋንዲ ለካስት ስርዓት ይህንን ያህል ተቆርቋሪ ሆኖ የሚታገለዉ በወቅቱ የነበረዉን ፖለቲካዊ ተአማኒነት ላለማጣት እንጂ አምኖበት አልነበረም፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነዉ ጋንዲ ከሶስተኛዉ ከነጋዴ ስራ የሚመደቡ የካስት አባል ቫይሲያ አባል ሲሆን የኖረዉ ግን የብርሀሚን ካስት የሚሰራዉን ፕሪስት በመሆን ከመሆኑ ባሻገር ልጁም ቢሆን ይሰራ የነበረዉም ከንግድ ዉጭ የጋዜጠኝነት ስራ ነበር ይህም በሂንዱ የሐይማኖት መጻሕፍት ከፍተኛ ቅጣትን የሚያስከትል ነዉ፡፡ ጋንዲ በዚህ ስርዓት እንደማያምን የሚያሳየዉ ሌላዉ የሚሰጣቸዉ መግለጫዎች እና ጽሑፎች ሲሆን በወቅቱ በጋንዲ መስራችነት ይታተም የነበረዉ ያንግ ኢንዲያ በኋላም ሀሪጃን የእንግሊዝኛ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ የአይነኬነትና ካስት ተቃዋሚ ሆኖ መግለጫ ይሰጥና በአካባቢዉ ቋንቋ ጉጂራቲ በሚፅፈዉ ጽሑፍ ደግሞ አክራሪ ሂንዱ በመሆን ለካስት ስርዓት እንደሚታገል ይገልፅ ነበር፡፡ 

    ጋንዲ በወቅቱ ተደማጭነቱን ተጠቅሞ ከሚያደርገዉ ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በወቅቱ ሹድራ ተለይተዉ በራሳቸዉ ዉክልና ያገኙ ዘንድ በዶ/ር አምበርከር ተደጋጋሚ ጥያቄ በራምሴ ማክዶናልድ የተሰጠዉን ዉሳኔ ተቃዉሞ በተደጋጋሚ ለጠ/ሚሩ የጻፈዉ ደብዳቤ ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲያዉቅ በወቅቱ በእጁ የነበረዉን ትልቅ መሳሪያ ተጠቀመ፡፡ ጋንዲ ይህ ዉሳኔ ካልተቀየረና ሹድራዎች ከሂንዱ ተለይተዉ የተለየ የምርጫ ክልል ከተሰጣቸዉ እስክሞት እፆማለሁ በማለት በ1932 ያዉጃል፡፡ በዚህ ወቅት ከያቅጣጫዉ በአምበድከር ላይ ጫና ይደርስበታል ጋንዲ ከሞተ ህንድ በእርስ በርስ ጦርነት እንደምትታመስ ግልፅ ሆነ፡፡ አምበድከር ጋንዲ መጣ ጋንዲ ይሄዳል የኔ ህዝቦች ግን ለዘላለም ኗሪ ናቸዉ በሚል ለአምስት ቀናት በእንቢተኝነት ቢቆይም በወቅቱ የነበረዉ የሀገሪቱን ዉጥረት መቋቋም ባለመቻልና የሚመጣዉን ዉጤት በመፍራት ከኮንግረስ መሪዎች ጋር ከስድስት ቀን የጋንዲ ፆም በኋላ ፖና ፓክት ተብሎ የሚጠራዉን ስምምነት ፈረሙ፡፡ በዚህ ስምምነት የተለየ ምርጫ ለሹድራ መሰጠቱ ቀርቶ በሂንዱ ዉስጥ ሪሰርቬሽን እንዲሰጣቸዉ ተስማሙ፡፡ እንደ አንዳንዶች ገለፃ ይህ ባይሆን ኖሮ ህንድ አሁን ካለችበት ማኅበራዊ ችግር ቀድማ ትወጣ ነበር፡፡ ችግሩ መልኩን ቀይሮም ቢሆን አሁንም አለና (ከፍተኛ ሂንዱዎች አሁንም የፖለቲካ ስርአቱ ተቆጣጣሪ ናቸዉ)፡፡ ጋንዲ ለካስት ስርዓት ለረጂም ጊዜ ሲታገል ከቆየ በኋላ በመጨረሻ በ1946 አቅራቢያ ካስት ያለፈበት ስርዓት ነዉ በሚል ከአምበድከር ጋር አብሮ ቆሞ ሲታገል ነበር፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የአምበድከረን ሀሳብ መቀበሉ አሁን ላለዉ የተሻለ የህንዳዉያን ንቃተ ህሊና እና ፖለቲካ ለዉጥ አስተዋፅኦ ነበረዉ፡፡ ለአብዛኛዉ ህንዳዊ ጋንዲ ማለት ብዙ ነዉና እሱ ካለ አለ ነዉ ሌላዉ አፉን ሊዘጋ ይገባል፡፡

    በእድገት እሳቤ ላይም ቢሆን ዶ/ር አምበድከር እና ጋንዲ የተለያየ እሳቤ ነበራቸዉ፡፡ ጋንዲ ወደ ተፈጥሮ እንመለስ የሚል ኋላ ቀር አስተሳሰብ አራማጅ ከመሆኑ ባሻገር ሆስፒታል፤ ባቡር ትራንስፖርት፤ ኢንዱስትሪ አላስፈላጊ ናቸዉ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ዶ/ር አምበድከር በበኩሉ ወደ ተፈጥሮ እንመለስ ጥሪ ማለት ወደ ባዶነት፣ ወደ ሰቆቃ እና ረሀብ አብዛኛዉን ማኅበረሰብ መክተት ነዉ ይል ነበር፡፡

    በእርግጥ በብዙዎች አዕምሮ ሊመጣ የሚችለዉ ታዲያ ለምን ጋንዲ በአለም ላይ ታዋቂ ሆነ የሚል ነዉ፡፡ በወቅቱ ህንድ ጀግና የተጠማችበት ጊዜ ነበር፡፡  እንዲሁም የህንድን ፖለቲካ ስርዓትን የተቆጣጠሩት የከፍተኛ ካስት አባል ሂንዱዎች አስበዉበት ለዚህ አላማ ማለትም ጋንዲን ታዋቂ ለማድረግ የሰሩት ፕሮፖጋንዳ እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል፡፡ የህንድ ማኅበረሰብ አሁን ስለ ዶ/ር አምበርከርም ይሁን ጋንዲ ትክክለኛ ግንዛቤ አላቸዉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለጋንዲ የሚያደርጉትን ለአምበድከርም ያደርጋሉ፡፡ የዶ/ር አምበድከር ወሳኝ ቀናት እንደ ዉልደት፤ ሞት ፤ ቡድሂዝምን የተቀበለበት ቀን በመላዉ ህንድ በአብዛኛዉ ማኅበረሰብ ይከበራል፡፡ የተወለደበት የሞተበት፤ ሰላማዊ ትግል ያከናወነበት ቦታ ዋንኛ የቱሪስት ቦታዎች ሆነዋል፡፡ ችግሩ ያለዉ በሌላዉ ዓለም ሲሆን አብዛኛዉ ማህበረሰብ ህንድን ከጋነዲ ጋር እንጂ ከዶ/ር ባባሳሂብ አምበድከር ጋር አያይዞ አያነሳትም፡፡ ይህም ሥነ-አመክንዮ ያለዉ አይመስልም፡፡

    ---
    ‹‹በጭቆናና በበደል የተፈተነ የፍትህ እና እኩልነት አባት - ዶ/ር ቢሂምራዎ ራምጂ አምበድከር›› በሚል ርዕስ ማናዬ በላይ በአራት ተከታታይ ክፍሎች ያቀረበልን ጽሑፍ በዚሁ ተጠናቋል፡፡
    ---
    ጸሐፊውን ለማግኘት bemanishe@gmail.com ላይ ይጻፉላቸው፡፡

    No comments:

    Post a Comment