Monday, July 29, 2013

ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ


በታዬ ዘሐዋሳ

በሃገራችን በነበረው ፖለቲካዊ ቀውስ ወይም አመለካከት የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስደት እንደሚኖሩ ይታወቃል:: የሚኖሩበትም ሃገር ብዛትና ስብጥር በራሱ ከሌሎች ሃገራት ዜጎች የተለየን ያደርገናል ብዬ አስባለሁ:: እንደ ሃገራቱ ስብጥር እና ብዛት ሁሉ የሃበሻ አመለካከትም እጅግ ብዙ ነው:: ይህ ብዛት ያለው ስብጥር ደግሞ ወጥ የሆነ አመለካከት እንዳይኖረን አድርጓል:: ክፍፍላችንም እንደዚያው ብዙ ነው:: ፍረጃችንም ጭምር:: የዛኑ ያክልም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ለመፈራረጅ ወይም ለመሞጋገስ ከንፋስ የፈጠነ ነው:: ፍረጃው ከተለያዩ አካላት ይጀመር እንጂ አብዛኛዎቹን ፍረጃዎች በማዳነቅና በማሟሟቅ ረገድ የሁሉም ድርሻ አለበት:: አንዲት የፌስቡክ ወዳጅ ስለፍረጃዎች ብዛት እና ጥልቀት ትዝብቷን አካፍላን ነበር:: ከነዚህ የርስ በርስ ፍረጃዎች ውስጥ የሚከተሉት በስፋት የምናስተውላቸው ናቸው:-

 . ኢቲቪ ወይም ኢሳት
 . ኢህአዴግ ወይም ተቃዋሚ
. አይጋ ፎረም ወይም ኢትዮጲያን ሪቪው
. አዲስ ዘመን ወይም ፍትህ
. ኢትዮጲያ ወይም ሞት ወይም ገንጣይ ተገንጣይ
. እምየ ሚኒሊክ ወይም አፄ ዮሃንስ
. ኢትዮጲያ ፈርስት ወይም ኦሮሞ ፈርስት
. ልማት ወይም ሰብአዊ መብት
. ንኡስ ከበርቴ ወይም ደሃ
. ኪራይ ሰብሳቢ ወይም ልማታዊ
. ሰለፊስት ወይም አህባሽ
. የውጪ ሲኖዶስ ወይም የሃገር ውስጥ ሲኖዶስ
. የምርጫ ትግል ወይም የትጥቅ ትግል
. ጠባብ ወይም አገር ወዳድ
. ባንዳ ወይም ጀግና
. የባንዳ ልጅ ወይም የጀግና ልጅ
. X ወይም Y እያለ ይቀጥላል::

ይህን የፍረጃ ብዛት እና አይነት ለግዜው በዚህ እናብቃው:: የፅሁፌ መነሻ ርዕሥ በርካታ ሃሳቦችን ማስነሳት እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራን በተመለከተ የተለያዩ ሃሳቦችን ማንሳትና ማወያየት እንደሚችል ግልፅ ነው:: አነሰም በዛም እነዚህን ሃሳቦች እያነሱ መወያየትም ሆነ መተራረም ስለ ድክመታችን አውቀን የማስተካከያ እርምጃ እንድንወስድ ይረዳናል:: ድክመቱን በገደምዳሜ እያየን የምናልፈው ከሆነ ግን ለሃገራችንም ሆነ ለህዝባችን ፋይዳ አናመጣም:: መፅሃፉ እንዳለውም አስቀድሞ በአይናችን ያለውን ምሰሶ ማውጣት ስንችል ነው የጓደኛችንን ጉድፍ ማየት የምንችለው:: ነገር ግን የኛ ዳያስፖራ እሱ ያለው እንጂ ሌላው የሚለው ትክክል አይደለም ብሎ የማሰብ አዝማሚያ ያሳያል:: እናም ምናልባት የኔ ሃሳቦች ከተወደደው ዳያስፖራ ሃሳብ ጋር ካልተስማሙ የማይስማሙበትን ሁኔታ ለመስማት ዝግጁ መሆኔን አስቀድሜ ልግለፅ:: የባህርያችንን ጥልቀት ለማሳየትም ይመስላል "ኢትዮጵያ የገባ አንድ ፀሃፊ በማግስቱ ስለ ኢትዮጵያውያን ከአንድ በላይ መፅሃፍ ሊፅፍ ይችላል:: በሁለተኛው ቀን ምናልባት ከተሳካለት ለጋዜጣ የሚሆን መጣጥፍ ሊፅፍ ይችላል:: ሳምንት ሲቆይ ግን ሰው ስለ ኢትዮጵያውያን አንድ አረፍተ ነገር እንኳ መፃፍ አይችልም" አለ የሚባለው:: ለማንኛውም ለዛሬ የሚከተሉትን "እዛም እዛም የረገጡ" ሃሳቦችን ላንሳ:: ነገር ግን የማነሳቸው ሃሳቦች ከጥቂት ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ጋር ግንኙነት የሌላቸው እና እንደማይመለከታቸውም ባውቅም ብዙሃኑን ይወክል ዘንድ እነዚያን ጥቂቶችም የፅሁፌ አካል አድርጌያቸዋለሁ:: ለዚህ አስቀድሜ ይቅርታ እጠይቃለሁ::

1)  የእርስ በእርስ ፍረጃ መፍትሄ ይሆነናል?

ፍረጃ በማንኛውም ልኬት ቢለካ ወደምንፈልገው የልማት ግብ ሊያደርሰን አይችልም:: ክፍፍሎችንና ፍረጃዎችን እየተከተልን ስንጨቃጨቅ እና ስንፈራረጅ ዓለም ጥሎን መሄዱ አይቀርም::  የፍረጃችንን ጥልቀት የሚያሳይ አንድ ትዝብት ላንሳ:: አንዱ የውጭ ሃገር ዜጋ ስለኛ ክፍፍል እና ፍረጃ ከሃበሻ ጋር ሲወያይ "እናንተ ኢትዮጵያውያን በእስካሁኑ ሂደት በብሄር፤ በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በሀይማኖት እና በመሳሰሉት ተከፋፍላችኋል:: አሁን የቀራችሁ ነገር ቢኖር በስማችሁ ፊደል ቅደም ተከተል መከፋፈል ነው፡፡" አለ የሚባል መራራ የቀልድ እውነታ አለ:: በብዛት እንደምንታዘበውም አብዛኛው ስለወቅታዊው ፖለቲካ የሚያወራልን ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድነትን ወይም ህብረትን የሚሰብክልን የራሱ ብሄር ከፍታ ቦታ ላይ ሊሆን እንደሚችል ካሰበ ብቻ ነው:: የርሱን ብሔር የተመለከተ ሌላ ታሪክ ወይም ድርጊት ከተነገረ ከርሱ በላይ የዘር ፖለቲካን አራማጅ የለም:: ፍረጃውም በአይነት በአይነት ተደርድሮ ይቀርባል:: ይህንን አይነት አካሄድን የሚያሳየን ደግሞ በተለያዩ ግዜያት ጣል በሚደረጉ አመለካከቶች ስር የሚሰጡ አስተያየቶችን መመልከት ስንችል ነው:: እንደዚህ አይነት አመለካከትና አካሄድ ምናልባት የምንፈራውን ከማፋጠን ያለፈ ፋይዳ የለውም:: ስለ አንድነት ሲሰብክ የነበረ ኦሮሞ ስለ ኦሮሞ እርሱ የማያምንበት ተፅፎ ሲያነብ ለዛ ፅሁፍ መልስ ወይም ማስተካከያ እና መከራከሪያ ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ የፀሃፊውን ዘር እያነሱ ጥንብ እርኩሱን በማውጣት ፍረጃ የሚያወጣለት ከሆነ ምኑን ስለ አንድነት ሰበከው? ስለዘር ፓለቲካ ጎጂነት አሳምሮ አቀነባብሮ የሚሰብከን ሰው ስለትግሬ መጥፎነት በማውራት እና በመፈረጅ ካጠናቀቀው የቱ ላይ ነው አንድነትን የሚያሳየው? አንድነት ሃይል ነው እያለ የሚያስተምር ሰው ስለ አማራ ጨቋኝነት እያነሳ እና አማራውን እየፈረጀ ሌላው ብሄር አማራን እንዲጠላ ከሰበከ የቱ ላይ ነው አንድነቱ ያለው? አንድ ነን እያለ ትግሬን አትመኑ ካለን፣ አንድ ነን እያለ አማራ በድሎናል በማለት ያለፈ ታሪክ ካወራ፣ አንድ ነን እያለ ኦሮሞ የመጣው ከዚያ ነው ካለ የቱ ጋር አንድነቱ ያለው? የሚወራው አንድነትስ የማን ነው? አንድነቱ ከግለሰቦች ካልጀመረ እንዴትስ አንድነት ይሆናል? ይህን ትዝብት ለግዜው እዚህ ልግታዉና ወደ ቀጣይ ሃሳብ ላምራ::

2)  ምን ያህል ዳያስፖራዎች ናቸው ሃገራቸውን የሚወዱት?

የግሌ መልስ "ምናልባት 20% የሚሆኑት ይወዱ ይሆናል" ባይ ነኝ:: ሃገርን የመውደድ ልኬቱ በኔና በነሱ ሊለያይ ይችላል:: ለኔ ሃገርን መውደድ ማለት የግል ፍላጎትን እና ምቾትን ለሃገር አሳልፎ መስጠት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት እራስን አሳልፎ እስከመስጠት ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት መከራን እና ችግርን መሸሽ አይደለም:: አንድ ሰው ፖለቲከኛ ሲሆን ለግል ጥቅሙ ሳይሆን ለህዝብና ለሃገር ሊሰራ ቆርጦ ተነሳ ማለት ነው:: ሆኖም ግን አንድ ችግር ሲያጋጥመው የሚኮበልል ከሆነ ቀድሞውኑ የተነሳው ለራሱ ግላዊ ጥቅም እንጂ ለሃገርና ለህዝብ አልነበረም ማለት ነው:: ከዚህ የፖለቲከኞች ቁማር ጋር በተያያዘ የበርካቶችን ታሪክ ማንሳት ይቻላል:: ነገር ግን ከዚህ በፊትም ብዙ ስለተባለ ልለፈው:: በኔ አመለካከት ፖለቲከኛ ለያዘው አላማ ሞትን የሚጋፈጥ እንጂ የሚሞዳሞድ ወይም ወደ ባእድ ሃገር የሚፈረጥጥ አይደለም::

ሌላው በዚህ ርዕስ ስር የማነሳው ሃሳብ ሰልፍን ይመለከታል:: በተለያዩ ሃገሮች ላይ ሃበሾች ሰልፍ ሲወጡ ይታያሉ:: ለምንድን ነው ሰልፍ የሚወጡት? ሀገራቸውን ስለሚወዱ ወይስ በሌላ ምክንያት? ከላይ እንዳልኩት 80% ምክንያታቸው ሌላ ነው:: ሃገሩንና ህዝቡን የሚወድ ሰው በሩቁ ሆኖ "ሊመታችሁ ነው ተጠንቀቁ" "ሊገላችሁ ነው ሽሹ" ወይም "ገደላቸው ገረፋቸው" እያሉ በባዶ ሜዳ መፈክር ማሰማት አይደለም:: ሃገሩን የሚወድ ሞትንም ቢሆን ተጋፍጦ ለሃገሩ ለውጥ ያመጣል እንጅ በተንደላቀቀ ኑሮ ላይ ሆኖ እንዲህ እኔ እንደምጽፈው መፈክር እያዘጋጁ መሰለፍ አይደለም:: ከተሰላፊዎቹ መካከል በርካታ የሃገሪቱ አንጡራ ሃብት ፈሶባቸው በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ ነገር ግን ብር ስላነሳቸው ብቻ ወይም የተንደላቀቀ ኑሮ ስላማራቸው ብቻ በባእድ ሃገር ከሙያቸው ጋር ፍጹም ግንኙነት የሌለው ስራ እየሰሩ የሚኖሩ ነገር ግን ለሃገር ተቆርቋሪ የሚመስሉ አሉ:: በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ የህክምና ባለሞያዎች ሃገር ቤት ያለ ወገናቸው በበሽታ እያለቀ እነርሱ ግን ብር ፍለጋ ብቻ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ገብተው የሾፒንግ ካሸር ወይም የጽዳት ሰራተኛ ሆነው የሚሰሩ አሉ:: እውን እነዚህ ሰዎች ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ይወዳሉ? በምርምር ስራቸውና የማስተማር ስራቸው አንቱ ተብለው ሲኖሩ የነበሩ ምሁራን ወደ ፈረንጅ ሃገር መጥተው ከሙያቸው ጋር የማይገናኝ ስራ እየሰሩ ነገር ግን ሰልፍ የሚወጡ እውን ሃገራቸውን ወደው ነው? ሃገርን መውደድ ማለት የደሃ ገንዘቧን አውጥታ ያስተማረችኝን ሃገር ቢያንስ በሙያዬ ሳገለግላት እንጅ ሰባራ ሳንቲም ባላወጣብኝ ሃገር ላይ ሳገለግል አይደለም:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን ከድንቁርናና ከበሽታ መታደግ ማለት ነው:: ሃገርን መውደድ ማለት ወገንን እና ሃገርን ከጥፋት መታደግ እንጂ መታሰርን ወይም መሞትን መሸሽ አይደለም:: የዛሬ የኛ በገንዘብ ተቸግሮ ሃገሪራችንን ማገልገል ማለት የነገውን ትውልድ እንዳይቸገር ማድረግ ነው:: የአንድ ሰው መታሰር ወይም መሞት ሚሊዮኖችን መተካት እንጂ መሞት አይደለም:: ይህንን የሰልፍ ጉዳይ በተመለከተ በእርግጠኝነት መናገር የምንችልባቸው በርካታ ሰዎችን ማንሳትና መነጋገር እንችላለን:: እነዚህ ሰዎች ባሉበት ሃገር የፖለቲካ ጥገኝነት ጠይቀው ውሳኔ እስኪተላለፍላቸው ድረስ ሰልፍ ያስተባብራሉ:: ሰልፍ ይወጣሉ:: ነገር ግን የነዚህን ሰዎች መቃወም ሳይሆን መፈጠራቸውን እንኳ የኢትዮጵያ መንግስት እንደማያውቀው እራሳቸውም ይረዱታል:: የግል ጥቅማቸውን ለማሳካት ሲሉ ብቻ ሰልፈኞች ናቸው:: አንድ ከፌስቡክ ጓደኞቼ መሃል ታሪኳን የማውቀው እህትን ጉዳይ ላንሳ:: ይህች እህት 2010 ኢትዮጵያ እያለች የተሳካላት አስጎብኚ ነበረች:: ሃገር ቤት እያለች የመንግስት ደጋፊም ነበረች:: ነገር ግን በአንድ ወቅት ከጎብኚዎች ጋር ተመሳጥራ ተሰደደች:: ሆኖም በተሰደደችበት ሃገር ላይ በቶሎ ፈቃድ ማግኘት ስላልቻለች ያላት አማራጭ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ መስራት እንዲሁም መስራቷን ለማሳየት የተለያዩ ፎቶዎችን መነሳት፣ ሰልፎችን ማስተባበር ነበረባት:: አደረገችው:: እንዲህ አይነት በርካታ ሰዎችን ማንሳት እንችላለን:: ነገር ግን መራራ ሃቅ ስለሆነ የሚጋፈጠው የለም:: ሲነካም የሚያጉረመርመው ብዙ ስለሆነ ለውይይት ሲቀርብ አይስተዋልም::

እናም በፈረንጅ ሃገር የምንኖር ሃበሾች በእውነቱ እራሳችንን ወይም አጋሮቻችንን መመርመር አለብን:: አንድ ሰው የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት አስቦ ሰልፍ ሲጠራን ተግበስብሰን መሄድን ማቆም አለብን:: እውነተኛ የሀገር እና የህዝብ ፍቅር ካለን ግን አካሄዳችንን ማስተካከል አለብን:: እውን ሃገሬን እወዳለሁ? ማለት አለብን:: ለምንድን ነው ሃገሬን የምወደው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን:: የተማርነው ደግሞ ሃገራችንን ከወደድን ገንዘብን እና ምቾትን ትተን ወደ ሃገራችን ተመልሰን ሃገራችንን ማገልገል አለብን:: "አሳሪ ወይም ገዳይ አለ" ብለን ከፈራን ግን ሃገራችንን ሳይሆን እራሳችንን ነውና የምንወደው ዝም እንበል:: ፓለቲካው ላይ ያሉትን ሰዎች ስናይ የተማረ ባለስልጣን በስንት መከራ ነው የምናገኘው:: ለምን ሲባል ደግሞ የተማረው ሆዳም እና ምቾት ፈላጊ ስለሆነ ነው:: እውን ሃገራችንን የምንወድ ከሆነ የራሳችንን አካሄድ ማሰብ አለብን:: ለራሳችን የግል ምቾት ተቆርቋሪ ሆነን ሳለ ለሃገር አሳቢ መስለን እኛ የማንደፍረውን ወይም የሸሸነውን ነገር ሌላው እንዲያደርገው መምከርና የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ ባለህበት እርገጥ እንዲል ማድረግ የለብንም:: ሃገሩን የሚወድ የራሱን ምቾት ወዲያ ጥሎ በፈለገው አካሄድ ለአላማው መቆም አለበት:: መሸሽ ወይም በውጭ ሆኖ ሰልፍ መውጣት ሃገርን መውደድ አይደለም:: ሃገራችን የተማሩ ልጆቿን ጣልቃ ገብነት ትፈልጋለች:: ያልተማሩ እና ለሆዳቸው ያደሩ እየመሯት ታድጋለች ማለት የህልም እንጀራ ነው:: ቢሆንማ ኖሮ ባለፉት 40 አመታት ብቻ የብልጽግና ማማ ላይ በወጣን ነበር:: መስሪያ ቤቶቻችን በተማሩ ሰዎች መሞላት አለባቸው:: ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የተማረው የሰው ሃይል አላማ ሲኖረውና በሆድ ማሰብን ትቶ በጭንቅላቱ ማሰብ ሲጀምር ነው:: "ምንም ብጎሳቆል የተሻለች ነገን በሀገሬ ላይ ለማየት በሙያዬ ልሰራ ይገባኛል" ማለት ስንችል ነው:: መሸሽ ወይም ሃገር ጥሎ መኮብለል መፍትሄ አያመጣም::

3) ማነው ሙሰኛው?

ሌላው ርዕሴ ሙስና ነው:: ሙስና ሲባል አብዛኛውን ግዜ የሚመጣብን የመንግስት ባለስልጣናትን ሙስና ብቻ ነው:: ከሰሞኑ ትውስታ ብናይ እንኳ ከአንድ ባለስልጣን ቤት ብቻ በርካታ ገንዘብ እንደተገኘ ሰምተናል:: ይህንን ድርጊት መንግስት አጥብቆ እንዲገፋበት በተቻለን አቅም ሁሉ አስተያየት በመስጠት ስናበረታታ ነበርን:: ጠቅላይ ሚኒስትራችንም በተለያዩ ግዜያት በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት አስረግጠው ቃል ገብተውልናል:: እርሳቸው በቃላቸው የሚፀኑ ከሆነ መላው ህዝብ እንደሚተባበራቸውና የፀረ-ሙስና ትግሉ ተፋፍሞ እንደሚቀጥል የታወቀ ነው:: ይህ እንዳለ ሆኖ ግን "እውን የመንግስት ባለስልጣናት ብቻ ናቸው ሙሰኞች?" በማለት መጠየቅ እወዳለሁ:: የመንግስት ባለስልጣናትን በሙስና ስንከስ ህብረተሰቡንም አብረን መክሰስ አለብን:: ሙስና በተፈጥሮው የሰጪና የተቀባይ ሂደት እንጂ የተቀባይ ብቻ አይደለም:: ዋነኛው ጥፋተኛ ሰጭው አካል ነው:: ካለው ስግብግብነት የተነሳ በገንዘቡ መደራደርን የመረጠ የህብረተሰብ ክፍል ሰጪ ባይሆን ተቀባይም አይኖርም:: በማንኛውም ልኬት ቢታይ ሙሰኞች የሚቀበሉት ከሰጪ ላይ በሰጪ ፍላጎት እንጂ አስገድደው አይደለም:: ላስገድድ የሚሉትማ በወቅቱ በህግ ቁጥጥር ስል ይውላሉ:: በባህሪያቸው ሙስናን የሚጠየፉና የተመሰገኑ ሰዎችን በስልጣን ላይ ስላስቀመጥንም ሙስናን መከላከል አይቻልም፡፡ የሰጪዎች አመለካከት እስካልተቀየረ ድረስ ተቀባይ ሁሌም ይኖራል::

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የተማረውን ስደተኛ እንይ:: አንድን የህክምና ባለሙያ ለማስመረቅ ቢያንስ በድሮው ካሪኩለም ሰባት አመት፣ በአሁኑ ስድስት አመት ያስፈልጋል:: በነዚህ አመታት የህክምና ትምህርቱን ለማሳካት የሚያስፈልገውን አጠቃላይ ወጪ ብናሰላው በትንሹ 1 ሚሊየን እስከ 1.5 ሚሊየን ብር ድረስ ይወጣበታል:: ነገር ግን ስንቶች ናቸው ይህ ሁሉ ገንዘብ ከወጣባቸውና ከተማሩ በኋላ ሀገራቸውን ጥለው የወጡት? ይህ ሙስና አይደለምን? ይህ በሌሎች የሙያ ዘርፎችም ተመሳሳይ ነው:: ሃገሪቱ በከፍተኛ ክፍያ አስተምራቸው የሃገራቸው መንገድ በቻይና ባለሙያ ሲሰራ እነርሱ ግን የአውሮፓን መንገድ የሚቀይሱት ሙሰኞች አይደሉምን? የሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መሪ እያጡ ወይም ብቁ አስተማሪ እያጡ እነርሱ ግን አውሮፓና አሜሪካ ተሰደው የሚያስተምሩት ሙሰኞች አይደሉምን? ለትምህርት ጥራቱ ማሽቆልቆል የየራሳችን አስተዋፅኦ ሊኖረን የቻለውም በዚህ የተደበቀ ሙስና አይደለምን? የሙስና ትግል ስናነሳ ትግሉ ከሁላችንም ቤት ሊጀምር ይገባዋል:: ሙስናን ሁላችንም ልንጠየፈው ይገባናል:: መንግስት ወይም የፓርቲ አባላት ብቻ ሙስናን እንዲፀየፉ አንጠብቅ ወይም አንስበክ:: እኛስ? ስንቶቻችን ነን ለሃገራችን ያልከፈልነው ገንዘብ እንዳለብን የምናውቀው? ሃገራችን እኛን ለማስተማር ያፈሰሰችውን ገንዘብ ይዘን እንደጠፋን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ሀገራችን እኛን ለማስተማር ያወጣችውን ገንዘብ ዘርፈን ለባእድ ሀገር በነፃ ያስረከብንስ ሙሰኞች አይደለንምን?

3)  የዳያስፖራ አንድነትና ትዕግስት

በመጨረሻም አንድነትንና ትዕግስትን በተመለከተ ትንሽ ልበል:: በበርካታ ግዜያት እንደምናየው ዳያስፖራዎች ስለ አንድነት እንዲሁም ብንከፋፈል ስለሚደርስብን ጉዳት ይተነትኑልናል:: ነገር ግን ማነው አንድነትን ያጣው? ከላይ ያነሳኋቸው የፍረጃ አይነቶች የሚመነጩት ወይም ተጧጡፈው የሚገኑት በዳያስፖራው እንጂ ሃገር ቤት ባለው አይደለም:: አንዳንዴ ሲታይ ዳይስፖራዎች የሚያነሷት ኢትዮጵያ እንደ ኢቲቪዋ የተለያየች እንደሆነች ሊሰማን ሁሉ ይችላል:: "ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር" የሚል መፈክር እያሰማ ሌላውን ብሄር ሙልጭ አድርጎ የሚሰድብ እና የሚያንኳስስ ሰው ያለው ዳያስፖራ ውስጥ ነው:: ኢትዮጵያ ለዘላለም ልትኖር የምትችለው ብሄር ብሄረሰቦቿ ተስማምተውና ተከባብረው ሲኖሩ እንጂ ተሰዳድበው አይመስለኝም:: ዳያስፖራው ወቅታዊውን ንፋስ እየተከተለ የሚነፍስ ፖለቲከኛ ብቻ ነው:: አፉ የጣፈጠ ቀጣፊ ሲያወራለት ተከትሎ የሚጓዝ ነገር ግን የተወሰነ ርቀት ላይ ሲደርስ እርሱ የሚያስበውን ካልተናገረለት ያንን ሰው አፈር ካላስገባሁ ለማለት የሚፈጥን ፖለቲከኛ ያለው ዳያስፖራ ውስጥ ነው:: መዋደድን፣ መከባበርን፣ በሃሳብ ተለያይቶ በሰለጠነ መልኩ መነጋገርን ዳያስፖራው ሊማር ይገባዋል:: ለፍቅርም፣ ለጥላቻም መፍጠን ሃገርን ይጎዳል እንጂ የትም ሊያደርስ አይችልም:: መንግስትን በፍረጃው እየከሰሱ ከመንግስት እጅግ በላቀ መልኩ ፈራጅ ሆኖ መገኘት ምን የሚሉት ስልጣኔስ ነው? ዳያስፖራው ተፈረጅኩ ብሎ ሰልፍ እንደሚወጣው ሁሉ እርሱ እንዲፈርጅ የሚያፈቀድለት ምክንያት አይታየኝም:: ተስማምቶ፣ ተግባብቶ ለመነጋገር ዳያስፖራችን ገና እንጭጭ እድሜ ላይ እንዳለ ለመረዳት አንዱን የፌስቡክ አክቲቪስት ጓደኛ አድርጎ አስተያየት ሰጭዎችን መታዘብ ብቻ በቂ ነው:: ከተቻለም ፓልቶክ ላይ ገባ ብሎ 10 ደቂቃ የሚባለውን መስማት በቂ ነው:: ስብሰባ ጠርቶ ማስጨብጨብ ወይም ከስብሰባው በኋላ "የርሱ ብሄር እንዲህ ነው" "የርሷ ብሄር እንዲህ ነው" እያሉ እርስ በእርስ መንኳሰስ አንድነትን አያሳይም:: ሃገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ በምንም መልኩ ይህንን አይነት ድርጊት አያደርግም:: እናም ዳያስፖራ ሆይ አንድነት አለኝ ትለን ይሆን? ትዕግስትስ አለኝ ትለን ይሆን? መከባበርስ አለኝ ትለን ይሆን? በሰለጠነ መልኩ ልዩነትን አክብሮ መወያየትስ እችላለሁ ትለን ይሆን? እራስህን መርምር::

ሳጠቃልል:- ሁላችንም ባለንበት ወይም በተሰማራንበት ሙያ ላይ ሆነን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት እንችላለን:: ጋዜጠኛ "ዋሽ" ሲባል "አልዋሽም" ብሎ መተባበር እንጂ መሸሽ ውሸቱን አያቆመውም:: ፖሊስም "ግደል" ሲባል "ወንጀለኛን ለህግ አቀርባለሁ እንጂ አልገድልም" ብሎ መተባበር እንጅ ስልጣንን ማስረከብ መፍትሄ መንደማይሆን ዳያስፓራው ሊያስተምር ይገባል:: ባለስልጣንም "ዋሽ" ወይም "አስገድል" ወይም "ሃገር ሽጥ" ሲባል መሸሽ ወይም "ስልጣናችሁን አልፈልግም" ማለት መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚዎችም "የውሽት ምርጫ ነው" እያሉ ማማረር ሳይሆን "አስተካክሉት" ማለት አለባቸው:: ተቃዋሚ ለመሆን ብቻ መስራትንም ማቆም አለባቸው:: በስልጣን ላይ ያለው መንግስት አነሰም በዛም ባለው ፖሊሲ መሰረት እንደሚሰራ እናውቃለን:: በስመ ተቃዋሚነት የተሰሩ ስራዎችን ጭፍልቅ አርጎ እንዳልተሰራ መስበክ መቆም አለበት:: የተሰራውን ጠቅሶ ያልተሰራውን እንዲሰራ መጠየቅ መፍትሄ ይሆነናል:: የዳያስፖራ ሰልፍም የሚያጠነጥነው ሁሌም በተቃውሞ እንጂ አማራጭን ታሳቢ ያደረገ አይደለም:: አማራጭ ማሳየት ሳይቻል ዝም ብሎ መቃወም በራሱ መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚዎቹ ለመቃወም ብቻ ሳይሆን አማራጭ ፓርቲ ሆኖ ለመቅረብ መስራት አለባቸው:: ገዥው ፓርቲም "የተለመደ ውንጀላ ነው" እያለ ገንቢ አስተያየቶችን ከመግፋት ይልቅ አስተያየቶቹን ገምግሞ ገንቢ የሆኑትን ወስዶ ሌላውን መተው መልመድ አለበት:: "አንተ ከዚያ ነህ አንተም ከነዚያ ነህ" እያለ መፈረጁን ማቆም አለበት:: እየተፈራረጅን የትም መንቀሳቀስ አንችልም:: አንድ ሰው ተቃወመም፣ ደገፈም በሙያው ግን ሀገራዊ ግዴታውን መወጣት አለበት:: ተመሪም ሆነ መሪ ፍረጃን አቁሞ ለሃገር ለመስራት መፎካከር አለበት:: የተማርነውም እስኪ ከትንሿ ሃላፊነታችን እንጀምር:: የሙያ ሃላፊነታችንን ምን ያህል እንደተወጣን እንፈትሸው:: እስኪ ወደፊት ትምህርቴን ስጨርስ ምን ማድረግ ነው ያሰብኩት እንበል:: ከዛም የፍተሻውን ውጤት ከሃገርና ከህዝብ ፍቅር አንጻር እንመዝነው:: የራሳችንን ምቾት ለማሳካትና ለባዕድ ሃገር ለመስራት እየተሯሯጥን በይስሙላ ብቻ ሀገርን መቃወም ፍይዳ ያለው አይመስለኝምና ራሳችንን እንመርምር:: ዳያስፖራ የሚልከው ገንዘብ እጅግ ብዙ ነው እያልንም ራሳችንን አንሸውድ:: ሃገርን ከፓርቲ እንለይ:: በመጨረሻም ዳያስፖራ ሆይ እራስህን መርምር:: የቆምክ መስሎህ ከሆነ ተዘናግተሃል:: አበቃሁ::

ጸሐፊውን ለማግኘት jhnb4775@gmail.com ይጠቀሙ::

1 comment:

  1. rejem tsehufe ..gen yalbeseleche....geleb nate ....generalization is not a solution.

    ReplyDelete