(ክፍል፩)
እነዚህ የግል ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ለግለሰብ የተጻፉ፡፡ተወዳጅ ባይሆኑም እንኳን አንዳንድ የስደተኛ ታሪኮች አያጡም፡፡ከስደት ጅማሬየአንስቶ እስከ ገጠመኞቼ ድረስ ያለውን በተከታታይ ላጫውታሁ እሞክራለሁ፡፡፡ሲጀመር
‘ትልቁን ነው መያዝ ያለብህ!’ ቁጣ ባዘለ ድምፀት ተናገረች።
‘ትንሿንም የምይዘው ይሁንልሽ ብዬ ነው’ አልኳት ረጋ ብዬ።
‘ታዲያ የቱን ልትተው የቱን ልትይዝ ነው? ይሄም፣ ይሄም፣ ያም፣ያም ሁሉም ይጠቅምሃል’ አለች ወደ ልብሶቹ፣ መፅሃፎቹ፣ ስጦታዎቿና እህቷ ለመንገደኛ ብላ ወዳዘጋጀችው ስንቅ ተራ በተራ እያመለከተች።
‘አንቺና እህትሽ በሎንችና የሚሰደድ ሰው አይታችሁ ስለማታውቁ አልፈርድባችሁም ግን ሁሉንም አልይዝም፣ ልያዝም ብል መያዝ አልችልም’ አልኳትና የምይዛቸውን ጥቂት ልብሶች በሃሳቤ መምረጥ ጀመርኩ።
‘መኪና አይደል እንዴ የሚሸከመው? ካልሆነልህም መንገድ ላይ ብትጥለው ይሻላል’አለች በእንባ በተጋረዱ አይኖቿ እያየችኝ።
‘መኪኖቹ ስለሚፈጥኑ ከሰው ውጪ ከባድ ነገር መጫን አይፈልጉም’ በየመንገዱ ችግር ሲከሰት አይደለም እቃ ሰው እያወረዱ እንደሚጥሉ ብነግራት የባሰ ሃሳብ ውስጥ እከታታለሁ ብዬ ስለሰጋሁ ነበር እንዲህ ያልኳት።
‘ከዚችማ ባዶ’ጅህን ብትሄድስ?’ ግራ እንደተጋባች ትንሿን ሻንጣ ከፈተቻትና አጠገቧ ተቀመጠች።
ልንለያይ አንድ ቀን ብቻ ቀረን። እሁድ ጠዋት ጉለሌ አካባቢ ያለችው ቤታችን ውስጥ ለብቻችን ሆነን የምይዘውን ነገር ከአንድ ትንሽ ሻንጣ እንዳያልፍ አንዱን እንጥላለን ሌላውን እናነሳለን። ያን ያዝይህን ያዝ ትላለች፤ ሁሉንም እንድይዝም ትፈልጋለች። እኔ ደግሞ አልይዝም እላለሁ። ደልቶኝ አደለም የምሰደደው፤ የምሄድበት አገር ተቀባይ የለኝም። ክርክር ደምቋል። ከቤቱ ጋር፣ ከስጦታዎቿ ጋር፣ እቤቱ ውስጥ ካሉት እቃዎች ጋር፣ ከመፅሃፍቶቹ ጋር፣ ከባሕል እቃዎቹ ጋር፣ ከሁሉም ነገር ጋር የነበረን ትስስር ወደ ሶስት አመት ሆኖታል ስለሆነም ሁሉን ነገር ይዤ እንድሰደድ ትፈልጋለች።
እኔ ብቻዬን ከዚህ ሁሉ ትዝታ ውስጥ መኖር አልችልም ግማሹን ይዘህልኝ ሂድ ነበር የመከራከሪያ ነጥቧ። ይህ ግን ሰዎችን ፈርቶ ለሚሮጥ ሰው የሚሆን ክርክር አልነበረም። ያየችውን ሁሉ፣ የያዘችውን ሁሉ፣ያስታወሰችውን ሁሉ እንድይዘው ትፈልጋለች። ሁኔታዋን ሳየው አልቅስ አልቅስ አለኝ። የጭንቀቷን ልክ ስገነዘብላል አትሂድ አትሂድአለኝ። ግን ምንም ማድረግ አልችልም ነበርና ጨከንኩ።
‘እና ይሄንንም ይዘህ አትሄድም?’ በልብ ቅርፅ የተሰራችውን ቀይ ውብ ትንሽ ትራስ አንስታ እያሳየችኝ በልምምጥ ጠየቀችኝ።
ያንን ቤት ጥለን ካልወጣን የምንላቀቅ አልመስልህ አለኝ። እጇን ይዤ ከቤት አስወጣኋትና ኮሪደሩ ላይ አቆምኳት። ‘እዚሁ ቆመሽ ጠብቂኝ አምስት ደቂቃ ብቻ’ አልኳትና አለኝ የምትላቸውን ውብ አይኖቿን በየተራ ስሜ ወደቤት ገብቼ ቤቱን ከውስጥ ቀረቀርኩት። ስልኬን አወጣሁና ለላዳ ታክሲ ደንበኛዬ ደወልኩ፤ ፈጥኖ እቤት እንዲመጣ ነገርኩት።
ያስፈልገኛል ብዬ ያሰብኩትን ጥቂት ልብስና ጥቂት መፅሃፍ ትንሿ ሻንጣ ውስጥ ከተትኩ። በሩን ስከፍተው እዚያው በተደገፈችበት ግርግዳ ተንሸራትታ ወለሉ ላይ ተቀምጣ እየጠበቀችኝ ነበር። ቦርሳዋንና ሹራቧንአቀበልኳትና ተመልሼ ወደ ውስጥ ገባሁ። ግራ እየገባት ታስተውለኛለች። ከዚያም ይዤው የምሄደውን የራሴን ሻንጣ ያዝኩና ከቤት ወጣሁ።
እንሂድ ብያት ሻንጣዬን መጎተት ጀመርኩ። ከጎን ከጎኔ እየተራመደች በመደነቅ ታየኛለች ከዚያም ‘ወዴት ነው የምንሄደው’ አለች።
‘ዝም ብለሽ ተከተይኝ’ አልኳትና ቀደም ብዬ የጠራሁት ላዳ ታክሲ ውስጥ ገባን። የታክሲ ሹፌሩን ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠሁት በኋላ‘ መገናኛ ነው የምንሄደው ታውቀዋለህ አይደል?’ አልኩት። ሹፌሩ የማታ ማታ ደንበኛችን ነበር። የእኔንም የጓደኛዬንም ቤት ያውቀዋል፡፡ ስንደርስ ሻንጣዬን አውርጄ ወደ ጓደኛዬ ቤት ገባን። እየሰረቀች የምታየውንሻንጣ ከፊታችን ራቅ አድርጌ አስቀመጥኩ።
ዐሥራ አንደኛው ሰዓት
ልንለያይ ሰዓታት ብቻ ናቸው የቀሩን። እሁድ ማታ መገናኛ አካባቢ ካለው የጓደኛዬ ቤት ውስጥ አብረን አመሸን። ስንት ነገር እያለ ፈዘን እንዲችው ስንተያይ አመሸን። ትልቅ ቤት ውስጥ ለብቻችን ተቀምጠን መተያየት ብቻ። በሥሥት እየተያየን አምላክ በሰላም እንዲያገናኘን አባታችን ሆይ ብለን ልሸኛት ከቤት ተያይዘን ወጣን። በቀላሉ እንደማንላቀቅ ስለምናውቅ አንድ ስምምነት ተስማምተናል። የተስማማነው እሷ ታክሲ ውስጥ ስትገባ እኔ ወደኋላ እንድመለስ ነበር። እየተያየን መለያየት ስለሚከብደን። ከመገናኛ ወደ ፒያሳ የሚሄደው ታክሲ ውስጥ ስትገባ ወደኋላ አትዪ የሚለውን ምክሬን ተግባራዊ አድርጋ ሳትዞር ሰተት ብላ ገባች። እኔ ግን እያየኋት ስለነበር መቅረት ከበደኝና ተከትያት ገባሁ።
‘እንዴ ወዴት ልትሄድ ነው? አልጨረስንም እንዴ?’ እያለች በመግባቴ ያልተደሰተች ለመምሰል ጥረት ብታደርግም ከአይኗ የነበረው የሚያንፀባርቅ ፈገግታ የደስታዋን መጠን ያሳብቅ ነበር። ከጎኗ ተቀመጥኩና አቀፍኳት።
ሁሉ ነገር ፍጥንጥን ስላለብን የምናደርገው ነገር ሁሉ እንደህልም ትዝ ይለኛል እንጂ ምንም በውል አይታሰበኝም። ወደቤት በደመነፍስ ደግመን ተመለስን። በሩን ከፍታ እንደገባች ማልቀስ ጀመረች።ያልያዝኳቸውን ልብሶችና እቃዎች ተራ በተራ እያነሳች ‘ይሄንንም ትተኸዋል? ይህንንም? ታዲያ ምንድን ነው ሻንጣዋ ውስጥ ያለው?’ ሁኔታዋን ሳይ ምንም አላማረኝም፤ ወደ ውጭ ወጣሁና ለእህቷ ደወልኩ። መሄጃዬ ሰዓት ስለደረሰ ቶሎ እንድትመጣልኝና እንድትገላግለን ለመንኳት።
ወደቤት ስመለስ በጉልበቷ ተንበርክካ አልጋው ላይ ተደፍታ ታለቅሳለች። ‘ሂድ ያልኩህ ውሸቴን ነው! ካለ አንተ አዲሳባ ትበላኛለች! እኔ አልችልም...!’ ስሰማቸው የከበዱኝንና ከውስጥ የሚወጡ ብዙ ብዙ አረፍተ ነገሮች ለፍራሹ ትነግረው ነበር።
አልጋው ላይ ተቀመጥኩና እንደምንም ቀና ሳደርጋት አይኖቿ ሌላ ሆነዋል። እነዛ በማንም ሰው ላይ የማይገኙ አይኖች ደፍርሰው ከእንባ ውጪ ሌላ ነገር እያፈሰሱ ነበር። ምሬት፣ ጭንቀት፣ ፍራቻ፣ ተስፋ መቁረጥ። ይህን ሳይ አገሬን ረገምኩ። ኢትዮጵያዊነቴን ኮነንኩ። ኢትዮጵያዊ ባልሆን ይህን የሚጣፍጥ የሕይወት ክፍል ትቼ እሰደድ ነበር? ከእኔና ከእሷ ፍቅር በላይ የሆነው ችግር ከየት መጣ? ችግሩን የፈጠሩት ይህን የእኔንና የእሷን ሕይወት ያውቁት ይሆን? ቢሯቸው ገብተው የሚጭሯት ብጣሽ ደብዳቤ ከፍቅር በላይ የሆነ ችግር እንደሚፈጥር ያስቡት ይሆን? ለኔ የተፃፉት ደብዳቤዎች በዊንስተን ስሚዝ ላይ ከተለቀቁት አይጦቹ ባይወዳደሩም ለመሸሽ ግን ተዘጋጅቻለሁ። ካስገቡኝ በኋላ ዊንስተን "Do it to Julia!" እያለ እንደጮኸው ላለመጮህ ጥያት ልሄድ ተነስቻለሁ። አስገብተውኝ መፋቀራችንን ከሚያጠፉት መሰደድ ይሻላል። ተለያይተን ከቀረንም እንዳፈቀርኳት ይሻላል። (ዊንስተን ስሚዝ 1984 የተባለው ትንቢት ተናጋሪ ልብ-ወለድ መፅሃፍ ላይ የሚገኝ የጆርጅ ኦርዌልገፀ-ባህሪ ነው፡፡)
‘እሺ ልቅር የኔ እናት? ልቅር? ቅር ካልሺኝ እቀራለሁ! ደግሞም እንዲህ እየሆንሽ እያየሁሽ ጥዬሽ አልሄድም፤ በቃ ቀርቻለሁ፤ ባይሆን ትንሽ ጊዜ ያስፈልገናል ስለዚህወደ ሓረር ወይ አዋሳ አብረን እንሄድና እዚያ ትንሽ እንቆያለን። በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ወር እሄዳለሁ አይዞሽ በቃ አይዞሽ’ እያወራኋት አገጯን ይዤ የበለጠ ቀና አረኳት።
ሁለት እጆቼን አርዝሜ ሁሉነገሯን አቅፌ ወደራሴ አስጠግቻታለሁ። መቼም እንደዚህ አቅፌያት አላውቅም። ባሳለፍኳቸው የስራ ዓመታት ያወቅኩትና የሰራሁት ለስደት ባይዳርግም ዕድሌ ከሚሰደዱት ተርታ አሰልፎኛል። የኖርኩት ኑሮና የሰራሁት ሥራ ትክክልም ይሁን ስህተት ለዛሬ አሳልፎ ሰጥቶኛል። ዛሬም የመረጥኩት መንገድ ትክክል ይሁን ስህተት ለነገ ማንነቴ ወሳኝ እንደሚሆን አውቃለሁ። ግን ሳስብ ውዬ ሳስብ ባድርም ሌላ አማራጭ እንዳይታየኝ ተጋርዶብኛል። ስለዚህም ይህችን የመሰለች ፍቅር ትቼ ልሰደድ ሆነ። አቅፌያት እንዲህ እያሰብኩ በር ተንኳኳ። እንባዋን እያደራረቀች በር ልትከፍት ተነሳች። ከተቀመጥኩበት አልጋ ላይ ሳልንቀሳቀስ ፈዝዤ ተጎልቻለሁ። በር ያንኳኳችው ታላቅ እህቷ ነበረች።
እንደገባች ቦርሳዋን ወርውራ ወገቧን ያዘች ‘ትላቀሳላችሁ እንዴ? ስንለያይ እንዳንቸገር ብላችሁ መሄድህን ካወቅህ ጀምሮ፤...አዎ ከእሮብ ጀምሮ ቤት ዘግታችሁ አልነበር? ታዲያ ምን ተገኘና ዛሬ እንዲህ የሚያደርጋችሁ? አንቺ በኋላ እንነጋገራለን! አንተ?’ ወደኔ አፈጠጠች። ‘ቤተሰቦችህን የተሰናበትከው መቼ ነው? ጠዋት ነው ዓይደል ደረስ ብለህ የመጣኸው? እንደቤተክርስቲያን ተሳልመሃቸው መጣህ አይደል? አበዛችሁት እሺ! ወንድ አይደለህ እንዴ ምን እንዲህ ያደርግሃል? አሁን ተነስና ፊትህን ታጠብ መሄጃህ ደርሷል’ እንዳዘነችልን ያስታውቅባታል። የውሸት ቁጣዋን ስትጨርስ የተዝረከረከውን ቤት ማስተካከል የወዳደቁትንእቃዎች ማነሳሳት ጀመረች።
* * *
ስንለያይ የሆንነውን ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እገረማለሁ። በውስጣዊ ፈገግታ ራሴን እየታዘብኩ ፈገግ ብያለሁ። እንደህፃን ልጅ በጉልበት አላቀውን የተለያየንበትን ቀን ሁልቀን አስታውሰዋለሁ።
በስደት አገር መኖር ስጀምር እሷን ወደዚህ አገር ለማምጣት እያሰብኩ ኑሮዬን መግፋት ጀመርኩ።እስከምንገናኝ በስልክ ማውራታችንን ቀጠልን። ቢያንስ በቀን አንዴ መገናኘት ግድ ሆነ። መቼ ነው የምንገናኘው የሷ የዘወትር ጥያቄ ነበር፤ መቼ ነው የምመጣው ሳትለኝ አድራ አታውቅም።
እየቆሁ ስሄድ በስደት ምድር ላይ የማየው ነገር እኔ ያልጠበቅኩትን ነበር። በየቀኑ ስለ ስደትና ስደተኛ ረጃጅም እውነተኛ ታሪኮችን መስማትጀመርኩ፤ ያልተፃፉ ተውኔቶችን ማየት ጀመርኩ። እኔን የታየኝን የስደት አስከፊ ገፅታ በስልክ አውርቻት እንደማልዘልቀው ተረዳሁ። እኔ የታየኝን እሷም እንዲታያት ማድረግ አለብኝ ብዬ ባሰብኩ ጊዜ ብቸኝነቴን ድል እንደነሳሁት ቆጥሬ ተደሰትኩ።የስደትን እና የስደተኛውን ሕይወት ልፅፍላት ተነሳሳሁ።አስከፊውን የውጭ አገር ኑሮ ሳልደብቅ በወረቀት ላይ ላወራት ቆረጥኩ። ለምን አሁኑ ለመምጣት የቋመጠችለትን ምድር ቀድሜ አላሳያትም ብዬ ተነሳሁ።ወደ ገበያ ወጣሁና አንድ ደልደልና ረዝም ያለ ደብተር ገዛሁ።
እያስደነገጥኩና እያስገረምኩ የነገርኳትን ነገሮች በስልኩ ውስጥ አብራርቼ ስለማልጨርሰውና የሷንም ውሎ መስማት ስለምፈልግጥሩ ዘዴ የቀየስኩ መሰለኝ። ከዚያም ሁሉን ነገር በግልፅ አብራርቼ የምነግራት ደብተሯ ላይ ሊሆን ሆነ። ‘ከስደት ወዲያ ሁሉም እኩል ይሆናል’ የሚለው ንንግግር ያልተሰደደ አይገባውምና‘ ሁላችሁም እኩል? እዛ ያለው ስደተኛ በሙሉ ተምሯል እንዴ? እንዴት አንድ አይነት ስራ ትሰራላችሁ? ሁላችሁንም ተመሳሳይ ቤት ውስጥ?’ እያለች ለምትጠይቀው ጥያቄ በውድ በሚሞላ የስልክ ካርድ ማስረዳት እጅግ ስለሚከብድ ደብተሯ ጥሩ መናገሪያ መንገድ ሆነችልኝ። ስለሆነም ዋና ዋናውን ወግ አውርተን ስናበቃ የተራረፉትን በስፋት እያብራራሁ ልፅፍላት ተነሳሳሁ።
የስልኬን ሰዓት አላባክንም። እንዲያውም በማብራሪያ ደብተሯ ላይ ጎጃም አዘነውን አዲስ አበባ አስፋልት ላይ ጥሎ እዚህ የደረሰውን ጠመንጃውን፣ ሜዲትራኒያንን ከሊቢያ ተንደርድሮ አውሮፓ ላይ ለማረፍ ሲዘል የፊት ጥርሱ የወለቀበትን የማያስቀውን ፍልፍሉን፣ አስራ ስምንት አመት ዴስክ ላይ ተቀምጦ ያጠራቀመውን እውቀቱን አቅፎ የተኛውን ብኩን ምሑር፣ አውቆ ቀዋሾቹን ወንድሞቻችንን፣ እያዩን እና እየታዘቡን ፌንት ሰራን የሚሉትን እንስቶቻችንን እና የሌሎችንም ታሪኮችን እንድነግራት በር ከፈተልኝ።
ዘወትር በየምሽቱ ስልክ ደወዬላት የተመደበልኝ ደቂቃዎች ሲያልቁ በሃሳብ መዋለልና መነጫነጭ ነበር። ያኔ ግን የስልክ ወሬያችን ሲቆም ወደ ደብተሩ ለመዞርና ያልተቋጩ የስልክ ወሬዎችን ጨምሬ ሌሎች ታሪኮችን ልነግራት ተነሳሳሁ። ደብተሩን የገዛሁ ቀን ማታ ጥቂት አውርቻት የዘጋሁትን ስልክ አልጋው ላይ አሽቀንጥሬ ሳበቃ ደብተሯን አነሳሁት። ከዚያም መጠሪያ ስም አወጣሁለት። የመጀመሪያውን ገፅ አልፌ ሁለተኛው ገፅ መሃል ላይ ‘እስክትመጪ!’ ብዬ በትልቁ ፃፍኩና ወደ ሚቀጥለው ገፅ ተሻገርኩ። ከዚያን ቀን ጀምሮ ማታ ማታ የገጠመኝን፣ ያወቅሁትንና ያየሁትን ነገር መፃፍ ጀመርኩ።
(ይቀጥላል)
-----
ጸሐፊውን ለማግኘት እባክዎ በኢሜይልአድራሻቸው tizusola@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡
No comments:
Post a Comment