Thursday, June 20, 2013

‹በሲቪል ሶሳይቲ ያደገ ሀገር የለም!› የኢትዮጵያ መንግስት፤ ‹ያለ ሲቪል ሶሳይቲ ድጋፍ የተመሰረተ ዲሞክራሲስ አለን?› እንጠይቅ




ሲቪል ሶሳይቲው ከየት መጣ ያልተባለ ካቴና እጁን ጠፍሮ ሊያስር ወደሱ እየመጣ መሆኑን ተመልክቶ፤ ለመንግስትን ‹እባክህ ካቴናው እጄ ላይ ከመታሰሩ በፊት እንወያይ› የሚል ልመና አቀረበ፡፡ መንግስት ግን ‹እዚህ የተቀመጥኩት ሕብረተሰቡን ከጥፋት ለመከላከል ነው› በሚል ምክንያት ለልመናው እቁብ ሳይሰጥ ካቴናውን ይዞ ወደ ፓርላማ አቀና፤ ፓርላማውም በአብላጫ ድምጽ ሲቪል ሶሳቲው ይታሰር ዘንድ ወሰነ፡፡ ዴሞክራሲያችን እና ፖለቲካችን ‹የተለየ ተልእኮ› ይዘው ሲዘውሩ ከነበሩት ‹የህዝብ ጠላቶች› መካከልም፤ እስሩን የቻሉት ተስፋን ሰንቀው በእስር ላይ ይገኛሉ፤ ያልቻሉት ደግሞ ወደ ሞት አቅንተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ያለፉት 5 ዓመታት የኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲ አጭር የሕይወት ታሪክ ነው፡፡

ቶኮክቪል በአሜሪካ፤ ፑትንሃም በጣሊያን

የ19ኛው ክፍለ ዘመኗን አሜሪካ የወንጀል ስርዓት ለማጥናት ከጓደኛው Gustave Bonninière ጋር በመሆን በአሜሪካ ምድር የተገኝው Alexis de Tocqueville የተልዕኮው ምክንያት የሆነውን የአሜሪካ የወንጀል ስርዓት ለፈረንሳይ እንዴት ሊጠቅም እንደሚችል በሪፖርት መልክ አቀረበ፡፡ ነገር ግን ሪፖርቱ የታሰበውን ያክል አዲስ ነገርን የያዘ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ቶኮክቪል ወደ ፈረንሳይ ከተመለሰ በኋላ በሁለት ጥራዝ የፃፈው ‘Democracy in America’ የተባለው ስራው ዘመን ተሸጋሪ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ተጠቃሽ ሆኖ እናገኝዋለን፡፡ በዚህ ታላቅ ስራው ቶኮክቪል ስለ አሜሪካ የህግ አውጭ አካል፤ ስለ የፖለቲካ ተቋማት፤ ስለ ፕሬሱ ወ.ዘ.ተ ሰፊ ትንታኔን አቅርቧል፡፡ ለአሜሪካ ዴሞክራሲ መጠናከር ዋነኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ተቋማት የሲቪል ሶሳይቲው እና የተለያዩ የዜጎች ማህበራት (Citizens associations) ናቸው፤ በማለትም የነዚህን ተቋማት ወሳኝነት ሲያስረዳ ‹ማህበራት ሁሉም የህብረተሰቡ አካል ስለ ህብረት የሚማርባቸው እንደ ትልቅ ነፃ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡›› በማለት ነው፡፡ ሲቀጥልም “[…] the voluntary association of the citizens might supply the individual exertions of the nobles, and the community would be alike protected from anarchy and from oppression.” እያለ እነዚህ ማህበራት ዜጎች ራሳቸውን ከጭቆና ይከላከሉባቸው ዘንድ የሚጠቅሙ የመብት ጋሻዋች እንደሆኑ ይገልፃል፡፡

ሮበርት ፑትንሃም በበኩሉ ‘Making Democracy Work’ ባለው የጣሊያንን ሕብረተሰብ የዴሞክራሲ መስተጋብር ባጠናበት ስራው፤ ዜጎች በብዛት እና በንቃት በሲቪል ማህበራት ውስጥ ሲሳተፉ፤ የመንግስት ተቋማት ላይ ያላቸው ክትትል (Watchdog role) ይጨምራል፤ በዚህም ምክንያት የመንግስት ተቋማት ውጤታማነት ከፍ ይላል› የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሰናል፡፡

‹የዴሞክራሲው ማዕከል ዜጎች ናቸው› ከሚለው እሳቤ በመነሳት አብዛኞቹ የዘርፉ ምሁራን በዴሞክራሲ ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ ወሳኝ እና ተተኪ የሌለው አካሄድ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ዜጎች የዚህ ተሳትፎ ዋነኛ ተዋናይ ይሆኑ ዘንድ ደግሞ ዜጎች ከመንግስት ተግባራት ጎን ለጎን የራሳቸውን ክትትል እና አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት መንገድ ከመንግስት ነፃ የሆነ፤ በዜጎች ነፃ ፈቃድ የተመሰረተ፤ ራሱን በራሱ ያደራጀ እና ለሕግ ተገዥ የሆነ አካል ያስፈልጋል - ሲቪል ሶሳይቲ፡፡


ዴሞክራሲ ያለሲቪል ሶሳይቲ

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የዴሞክራሲ መነሻው እና መድረሻው ዜጎች ናቸው፡፡ ዜጎች ወግና ስርዓት ያስጠብቅ ዘንድ የሚሾሙት፤ ሲፈልጉም በምትኩ ሌላ የሚተኩበት የዜጎች ‹ሎሌ› የሆነ አካል ደግሞ መንግስት ነው፡፡ እንግዲህ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመንግስት እና የዜጎች ግንኙነት የጌታ እና ሎሌ ነው ማለት ነው፤ ዜጎች ጌታ፣ መንግስት ሎሌ፡፡ ጌታ ለሎሌው ትእዛዝ እንደሚሰጥ ዜጎችም ለመንግስት በህግ የተደነገገ መብት እና ግዴታ ሰጥተው መንግስት ምህዋሩን ስቶ ያለስልጣኑ በዜጎች ሕይወት ላይ ጣልቃ እንዳይገባ ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ክትትል ያደርጉበታል፡፡ ሲቪል ሶሳይቲው እንግዲህ በዜጎች ተመስርቶ መንግስት ሊያከናውናቸው የማይችላቸውን ተግባራት ያከናውናል እንዲሁም መንግስት አጉራ ዘለል ሲሆን ‹ተው ተመለስ› እያለ የጥበቃ ስራን ይሰራል፡፡ በዚህም ምክንያት በዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ አወቃቀር ውስጥ ሲቪል ሶሳይቲው ሰፊና ሁነኛ ድርሻን ይይዛል፡፡

ከዚህ በታች በሚታየው የሶስት የስርዓት አይነቶች ንፅፅር የሲቪል ሶሳይቲውን ድርሻ እንመልከት፡፡


ከንፅፅሩ እንደምንረዳው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት (Democratic System) ውስጥ መንግስት ቁጥብ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ ሲቪል ሶሳይቲው ደግሞ በመንግስት እና በሰፊው ሕዝብ (Parochial Society) መካከል ተሰይሞ የተሳትፎ ድልድይ በመሆን ያገለግላል፡፡ በአምባገነን ስርዓት (Authoritarian System) ደግሞ የመንግስት (Party State) ድርሻ ከፍ በማድረግና የራሱን የሙያ ማህበራት (State controlled associations) በመመስረት ሲቪል ሶሳይቲውን የማያላውስ ጠባብ መንገድ ላይ ያስቀምጠዋል፤ ሲብስም ሲቪል ሶሳይቲው በህቡዕ እንዲንቀሳቀስ ያስገድደዋል፡፡ በፈላጭ ቆራጭ ስርዓት (Totalitarian System) ደግሞ ከናካቴው ሲቪል ሶሳይቲ የሚባለውን ሀሳብ አናገኝውም፡፡


እንግዲህ ዴሞክራሲ የሕዝብ ልህዝብ በሕዝብ ቆመ ስርዓትነቱ የዜጎችን ተሳትፎ ወሳኝ ያደርገዋል፡፡ ያለዜጎች ተሳትፎ ዴሞክራሲ ሊኖር አይችልም ወደ ሚለው ድምዳሜ ያመራናል፡፡ የዜጎች ተሳትፎ ዋነኛ መሳሪያ የሆነው ሲቪል ሶሳይቲ ደግሞ ይህን የዜጎች ተሳትፎ እውን ያደርጋል እና ዴሞክራሲን ያለ ሲቪል ሶሳይቲው ማሰብ ቅዥት ይሆንብናል፡፡


The Ethiopian ‘War’ on the Civil Society


‹ቡርኪናፋሶ ስልሳ ሽህ ሲቪል ሶሳይቲ አለ፤ ነገር ግን ስድስት ሽህ የሚሞሉ የንግድ ድርጅቶች ግን የሉም፡፡ ደቡብ ሱዳን ገና ሪፈረንደም እንኳን ሳታካሂድ ከሁለት ሽህ በላይ ሲቪል ሶሳይቲ ፈልቶባታል፤ ነገር ግን በቅጡ 200 እንኳን የሚሞሉ የንግድ ድርጅቶች እንኳን የሏትም፡፡›› የሚለው ሀሳብ ከመንግስት ሰፈር ምርጫ 97ን ተከትለው ሲሰሙ ከነበሩ ድምፆች ዋነኛው ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ምን ችግር አለው? ብሎ መጠየቁ እዚህ ላይ ተገቢ ይሆናል፡፡ የሲቪል ሶሳይቲው መብዛት በራሱ ጥፋት ሊሆን አይችልም፤ ይልቁንም ለሕግ ተገዥነታቸው እና ነፃነታቸውን አስጠብቀዋል ወይስ ተላልፈዋል? ነው መጠየቅ ያለበት ተገቢ ጥያቄ፡፡ መንግስት ከሲቪል ሶሳይቲው ጀርባ በመሆን የሲቪል ሶሳይቲውን የገንዘብ ምንጭ በማድረቅ ከማጅራቱ ላይ መትቶ ሲጥለው፤ ‹ይህ ገደብ በመብት ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶችን ብቻ ነው የሚመለከተው› ማለቱ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፤ ምክንያቱም ሲቪል ሶሳይቲው በዋናነት የሚፈለግበት መስክ የመብት ጉዳይን በሚመለከቱ ወረዳዎች ነውና - የሰፊው ሕዝብ እና የመንግስት አገናኝ ድልድይ በመሆን፡፡ በተጨማሪም ምንም እንኳን መንግስት ‹ዴሞክራሲ ወይም ሞት› በሚለው አደባባይ መሃላው የምናውቀው ቢሆንም፤ የንግድ ድርጅቶችን መበርከት ታሳቢ አድርጎ ‹በሲቪል ሶሳይቲ ያደገ ሀገር የለም› ሲል፤ ‹ልማትን ጠበቅ - ዴሞክራሲን ለቀቅ› አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ያስረዳናል፡፡


መንግስት በዚህ አላቆመም፤ ሲቀጥል ‹ዴሞክራሲን በጡጦ አንጠባም›፣ ‹ዴሞክራሲ ከዋሽንግተን ወይም ከብራሰልስ የምንገዛው ሸቀጥ አይደለም›፣ ‹የትሮይ ፈረስ ከቅጥሩ አልፎ ወደ ትሮይ ይገባ ዘንድ አንፈቅድም፤ በውስጡ ወታደሮች እንዳሉ እናውቃለንና› ወ.ዘ.ተ የሚሉ መከላከያዎች ሲቪል ሶሳይቲውን ሲከስ የሚያነሳቸው ልምጮች ናቸው፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱን ሲያስቀምጥ ዴሞክራሲና የፖለቲካ ተሳትፎ ለዜጎች እና ለዜጎች ብቻ የሚተው ነው የሚል ነው፡፡ ከምዕራቡ ዓለም የሚመጣው ገንዘብ የዜጎችን መብት ቀምቶ በነሱ ፋንታ ሊያዝ፤ ሊወስን አይችልም የሚል ነው፡፡ ይሄን ሀሳብ ለማፅናትም ሉዓላዊነትን እንደ መከታ ያነሳል፡፡ በርግጥ በዘመናዊው እሳቤ ሉዓላዊነት ጥፋትን መመከቻ ሆኖ የሚቀርብ ጋሻ አይደለም፤ ይልቁንም ዜጎችን ባለመበደል እና የዜጎችን ሉዓላዊነት በማክበር፤ መንግስት የዜጎች ተወካይ ሆኖ በዓለማቀፍ መድረክ የሚታይበት ልብስ እንጅ፡፡ በሉዓላዊነት ሰበብ የተከለከለው ገንዘብ፤ በመብት ዙሪያ የሚሰሩ የራሱ የመንግስት ተቋማት ከምዕራብም ከምስራቅም እንደሚቀበሉና፤ ጥቅም ላይ እያዋሉት እንዳለ ስናይ ደግሞ ነገሩ የበለጠ ብዥታን ይፈጥርብናል፡፡


‘ፃዲቁ’ ሲቪል ሶሳይቲ


ከላይ በመግቢያችን እንደጠቀስነው ከሲቪል ሶሳይቲው ዋነኛ ባህሪያት አንዱ ሕግ አክባሪነት ነው፡፡ ሲቪል ሶሳይቲው ህጋዊ ስርዓቱን ሕግን በመጣስ ለመገዳደር የሚሞክር ከሆነ ያኔ ሲቪል ሶሳይቲው ‹ሲቪል› የሚለውን ስሙን ያጣል፤ ጎራውንም ይለውጣል፡፡ ይህ ለሕግ ተገዥ ያለመሆንም ነው አንዳንድ ሲቪል ሶሳይቲዎችን ወደ ‘Uncivil Societyነት’ የሚመራቸው፡፡ ከዚህም በመለስ ሲቪል ሶሳይቲው በሕግ እና በስርዓት ካልተመራ ራሱን እንደህዝቡ አዳኝ በመቁጠር እና የተቃውሞ ባህልን (Oppositional Culture) በማዳበር የገለልተኝነት ባህሪውን ሊያጣ ይችላል፤ መንግስት ሊመልሰው ከሚችለው በላይ የበዙ ጥያቄዎችን በማቅረብ በተግባር ደረጃ እውን የማይሆኑ ህልሞች ላይ ጊዜውን ሊያጠፋ ይችላል፤ በተጨማሪም በአንድ ሀገር ውስጥ መረን የለቀቁ ብዙ የሲቪል ሶሳይቲ ባለ ቁጥር የፍላጎት እና የአካሄድ አለመጣጣም እንዲኖር በማድረግ ወደ ማህበራዊ ተቀርኖ እና ጽንፍ የያዘ የፖለቲካ ምህዳርን ወደ መፍጠር በማዘንበል ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡


እነዚህን የሲቪል ሶሳይቲው ‹ሀጥያቶች› ለመከላከል እና ለማረም በሚልም የሕግ ማእቀፍ ሊወጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕጉ ሃጣንን ከፃድቃን ያልለየ ሲሆን ሲቪል ሶሳይቲው በአጠቃላይ ሊጫዎት የሚችለውን ዴሞክራሲን የመደገፍ ሚና ያጣል፤ ከዚህም ኪሳራ ዋናኛው ተጎጂ ሰፊው ሕዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት ሲቪል ሶሳይቲውን በህግ ጥላ ስር አውላለሁ በማለት የህግ ማዕቀፍ መዘርጋቱ መልካም ቢሆንም፤ የህግ ማዕቀፉ ‹እኔን የሚተችን ሁሉ አያሳየኝ› በሚል መነሻ ሲሆን ግን ጉዳቱ ለሁሉም ይሆናል፡፡ ሲቪል ሶሳይቲውን ‹ጭጭ› አደረኩት የሚለው የመንግስት ፉከራ፤ ‹እሰይ ቤቴ በመቃጠሉ፤ ከቁንጫው ተገላገልኩ› ከሚለው ‘ደስተኛ’ ሰው የሚለይ አይሆንም፡፡ ቤቱ ቁንጫ ሊያፈራ ይችላል፤ መፍትሄውም ቤትን ማጽዳት እንጅ ፤ ቤትን አቃጥሎ ቁንጫውም ከቤቱ ጋር አብሮ ስለተቃጠለ መደሰቱ፤ ዘላቂ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ሲቪል ሶሳይቲው መንግስትና ሕዝብን የሚያገናኝ ድልድይ ነውና፤ ድልድዩን መጠገን እና ማስተዳደር መልካም ሲሆን ማፍረሱ ግን ከሕዝብ ጋር መቆራረጥ፤ ዴሞክራሲንም ከበር እንደመመለስ ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment