Tuesday, June 18, 2013

ኢትዮጵያና ሦስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል


ዘላለም ክብረት


ቀኑ ሚያዚያ 25/1974 ዓ.ም [1] ፤ ሰዓቱ ከሌሊቱ 6፡25፤ ቦታው ፖርቹጋል፣ ሊስበን፡፡ የፖርቹጋል ብሄራዊ የራዲየ ጣቢያ "Grandola Vila Morena" የተሰኝውን ዘፈን በአየር ላይ አዋለ፡፡ ዘፈኑ እንደሌሎች ዘፈኖች እንዲሁ ተደምጦ የሚታለፍ አልነበረም፤ ይልቁንም ዝግጅቱን አጠናቆ ለሚጠባበቀው ወታደር ‹ወደ ፊት› የሚል ፊሽካ ነበር፡፡ ወታደሩም በ12 ሰዓታት ውስጥ የወቅቱን የፖርቹጋል አምባገነን Marcello Caetanoን አስወግዶ፤ በፖርቹጋል አዲስ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመዘርጋት አንድ ርምጃ ወደፊት ተራመደ፡፡ ሰፊው የፖርቹጋል ሕዝብም ሂደቱን በመደገፍ አደባባይ ወጣ ወታደሮቹ በያዟቸው መሳሪያዎች አፈሙዞች ላይም አበባ በማስቀመጥ ለውጡን ሰላማዊ መልክ አስያዘው - The Revolution of the Carnations! አሜሪካዊው የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር Samuel Huntington ሁነቱን ‹‹ሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል የተወለደበት ምሽት›› ይለዋል፡፡ [2]

በዚህ ተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ በማያቋርጥ ሰልፎች ተጨንቃለች፤ በጊዜው በስልጣን ላይ የነበረው ስርዓት ጥገናዊ ለውጦችን ማድረጉን ተያይዞታል፤ አመራሮቹን በየጊዜው ይቀያይራል ሰልፈኞቹ ግን ረክተው ዝም የሚሉ አይደሉም፤ ከታክሲ ሹፌሮች እስከ መምህራን፤ ከነጋዴዎች እስከ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች፤ ከገበሬው እስከ ወታደሩ ሁሉም የየራሱን ምክንያት ይዞ አደባባዮችን ተቆጣጥሯል፡፡ በዚህ መሃል ከሕዝብ ወገን ነን ያለው ወታደር ራሱን በግብታዊነት አደራጅቶ ዙፋኑን ተረከበ፡፡ ነገር ግን በተመሳሳይ ወቅት እንደሆነው የፖርቹጋል ኩነት ሕዝቡ አበባ ይዞ አልጠበቀውም፤ ይልቅስ በተለያዩ የህዝብ ወኪል ነን ባሉ ፓርቲዎች ጥርስ ተነከሰበት፤ ወታደሩም የሕዝብ ወገን እንዳልሆነ አፈሙዘን ወደ ሕዝብ በማነጣጠር ገለፀ፡፡ እናም በፖርቹጋል ተጀመረ ያልነው ‹ሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል›፤ አዲስ አበባ ላይ ፈገግ ብሎ ወዲያው አኮረፈ፤ ከሄደበትም አልተመለሰም፡፡


Third Wave

ሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል የሚለው ስያሜ የመጀመሪያው እና የሁለተኛው የዲሞክራሲ ማዕበላት ተከታይ፤ እንዲሁም ከሁለተኛው የዲሞክራሲ ግሽበት (Second reverse) ተከታይ ነው በማለት ሳሙኤል ሀንቲንግተን ያስረዳል፡፡ ሀንቲንግተን እንደሚያስረዳው የመጀመሪያው የዲሞክራሲ ማዕበል የፈረንሳይ እና የአሜሪካን አብዮት ተከትሎ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለምዕራቡ ዓለም ነጭ ወንዶች የመምረጥ መብት ያጎናፀፈው ወይም ‘Jacksonian Democracy’ እየተባለ የሚጠራው ሂደት ሲሆን፤ በዚህም የመጀመሪያው የዲሞክራሲ ማዕበል ሂደት ወቅት ሙሉ ባይባልም በከፊል 29 ዲሞክራሲዎችን አፍርቷል፡፡ የመጀመሪያው የዲሞክራሲ ማዕበል እስከ 1920ዎቹ መጀመሪያ ቀጥሎ በአውሮፓ በተስፋፋው ፋሺዝም እና ናዚዝም ሀሳብ ምክንያት ወደ ኋላ እንዲሽከረከር ተገዷል፡፡ የመጀመሪያውን የዲሞክራሲ ግሽበት (The first reverse) ተከትሎ የሁለተኛውን ዓለም ጦርነት ማብቃት አስታኮ የተከሰተው ሁለተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል እስከ 1960ዎቹ አጋማሽ ለሁለት አስርት ዓመታት በመቀጠል 36 ዲሞክራሲዎችን እንዳፈራ ሃንቲንግተን ይገልፃል፡፡ እንደ መጀመሪያው ማዕበል ሁሉ ሁለተኛውም ማዕበል የኋልዮሽ ጉዞ ለጥቂት ዓመታት ካደረገ በኋላ ታላቁ እና ዓለማቀፉ ሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበልን ወልዷል፡፡

እንግዲህ ይህ ሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል ነው በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች በመድረስ አምባገነን ስርዓታትን በማናጋት ከ100 በላይ ዲሞክራሲያዊ ስርዓታትን የወለደው፡፡ የሶስተኛውን ማዕበል እንድንናፍቀው የሚያደርገን ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ሰላማዊነቱ ነው፡፡ ሳሙኤል ሀንቲንግተን ‘The Third Wave: Democratization in the Late Twentieth Century’ ባለው ታላቅ ስራው “From the ‘revolution of the carnations’ in Lisbon to the "velvet revolution" in Prague, the third wave was overwhelmingly a peaceful wave.” በማለት የማዕበሉን ዋነኛ መገለጫ ሰላማዊነት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያም የሶስተኛው ማዕበል የተወለደበት ዓመት ላይ በራሷ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት የተገኝችው፡፡

ኢትዮጵያ በሳንፍራንሲስኮ፤ ኢትዮጵያ በኒው ሀምፕሻየር

የ20ኛው ክፍለ ዘመኗ ኢትዮጵያ ካገኝቻቸው ታላላቅ ‹እድሎች› አንዱ እና ዋነኛው ከበለፀገው ዓለም ጋር በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ የነበረውን ጭቁኑን የዓለም ክፍል (The Global South) በመወከል በተለያዩ መድረኮች ላይ መገኝት መቻሏ እና የጭቁኑ ህዝብ አንደበት በመሆን ማገልገሏ ነው፡፡ በርግጥም ይህ እድል እንዲሁ መጣ አልነበረም፤ ይልቁንም ሀገሪቱ ራሷን ከባህር ተሻጋሪው አስገባሪ ተከላክላ መኖሯ እንደ የጭቁኑ ሕዝብ የነፃነት ተምሳሌትነት አሰቆጥሯል፡፡ እንደ ነፃ ሀገርም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር በ1945 ዓ.ም ሳንፍራንሲስኮ፣ አሜሪካ ሲፀድቅ ከበለፀጉ መስራች ሀገራት ጎን የተረሳውን ጭቁን ዓለም በመወከል ፊርማዋን በቻርተሩ ላይ አስቀምጣለች፡፡ እንዲሁም ከቻርተሩ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በኒው ሀምፕሻየር፣ ብሪቶን ውድስ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክን የመሰረተው ጉባኤ ላይ ተገኝታ የምስረታው አካል ለመሆን ችላ ነበር፡፡

ይህ እና በሀገር ደረጃ ከተለያዩ ያደጉ እና ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ጋር በነበራት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ተመልክተን፤ ሀገሪቱ ለዲሞክራሲ ቅርበት (Exposure) እንደነበራት መገመቱ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ በዚህም ምክንያት ራሳችን በጊዜው አስቀምጠን፤ ኢትዮጵያ ከተቻለ በሁለተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል፤ ካልሆነም የሶስተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል ‹ሰለባ› ትሆናለች ብለን መደምደማችን ጤነኛ ድምዳሜ ይሆናል፡፡ ነገር ግን አልሆነም፤ ለምን?
ኢትዮጵያ በሶስተኛው ማዕበል መጀመሪያ ላይ በተመቻቸ ሁኔታ ላይ ተቀምጣ፤ የማዕበሉ ውሽንፍር በትንሹ አዳክሟት እንዴት ከማዕበሉ ሲሳይ ተቋዳሽ አልሆነችም የሚለው ጥያቄ ከፕለቲካ ባህል ጀምሮ እስከ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ባህሪ የሚዘልቅ ሰፊ ጥናትን የሚጠይቅ ስራ ነውና በአጭሩ በዚህ በዚህ ምክንያት ብለን በደፈናው ማስቀመጥ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ለማንሳት እንሞክር፡፡


ልሂቅ ወዲህ፤ ወታደር ወዲያ፤ ሕዝብ በመሃል

የሶስተኛው የዲሞክራሲ አብዩት አንዱ እና ዋነኛው አስተዋፅኦ ሰፊውን ሕዝብ የለውጡ ዋነኛ ተዋናይ ማድረጉ ነው፡፡ ከሊስበን እስከ ካይሮ በዘለቀው የለውጥ ሂደት [3] ሰፊው ሕዝብ በለውጡ ውስጥ አድራጊ እና ፈጣሪ (Maker and Breaker)፤ እንዲሁም ሿሚና ሻሪ (King Maker) በመሆን የነቃ ተሳትፎውን አሳይቷል፡፡ ይሄም ዲሞክራሲያዊ ለውጥን የሚያዋልደው (Midwives of change) ልሂቁ ነው የሚለውን የቆየ እሳቤ ተገዳድሮታል፡፡ አዎ ልሂቁ በዲሞክራሲ ምስረታ እና ማጠናከር ላይ ታላቅ ሚና አለው፤ ነገር ግን ከአምባገነን ስርዓት ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግን ስርዓት በመደገፍ በኩል ከልሂቁ ይልቅ ሰፊው ሕዝብ (The mass) ሁነኛ ቦታን እንደሚይዝ የሶስተኛው የዲሞክራሲ አብዩት ግምገማ ያሳየናል፡፡
የኢትዮጵያን ሁኔታ ስንመለከት ሰፊው ሕዝብ በልሂቃኑ አመራርነት በተደጋጋሚ ወደ አደባባይ ወጥቷል፤ ነገር ግን እንመራሃለን ያሉት ልሂቃኑ ጎራ ለይተው በስሙ ደም ሲያፈሱ ተመልክቷል፤ ሕዝቡን ከአደባባይ ወደ ቤቱ እንዲገባ አድርጎ ወታደሩ የማያውቀውን አመራር በጉልበት ሲይዝ ተመልክቷል፡፡ እናም ሕዝቡ የተሻለ ስርዓትን ፍለጋ መሃል ላይ ቢቆምም ወታደሩ በአንድ ጫፍ ላይ ሲጎትተው፤ ልሂቃኑ ደግሞ በሌላው ጫፍ ሲስቡት፤ ያሰበውን የተሻለ ስርዓት በመሃል ሲሟሟ ለማየትም ችሏል፡፡

የልሂቃኑ በአንድ ፅንፍ መቆም፤ ወታደሩ በሌላ ጫፍ ዙፋን መመስረት ሕዝቡን ከዲሞክራሲው ማዕበል እንዳይጠቀም አድርጎታል ማለት እንችል ይሆን?

ዲሞክራሲን የማያበቅል መሬት

ማዕበሉ ኢትዮጵያን በስሱ ዳስሶ ሳይዋጃት ለማለፉ ሊነሳ የሚችለው ሌላው ምክንያት በሰፊው ባህል፤ በጠባቡ ደግሞ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡ በ1950ዎቹ ገንኖ የነበረው የዲሞክራሲ ምስረታ ፅንሰ ሀሳብ፤ ‹ሀገራዊ ባህሪን› (National Character) ግምት ውስጥ ያስገባ ነበር፡፡ ይሄም ማለት ‹የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ዲሞክራሲያዊ ሊሆኑ አይችሉም፤ ምክንያቱም ‘Asian Values’ አይፈቅዱላቸውምና›፤ ‹አፍሪካዊያን አኗኗራቸው የጋርዩሽ ስለሆነ ለግለሰቡ መብት አይጨነቁም እንዲሁም ህብረተሰቡ በግለሰቡ ላይ አምባገነን እንዲሆን ስርዓታቸው ይፈቅዳልና፤ የግለሰቡ መብት የተከበረባት ዲሞክራሲያዊት አፍሪካን ማለም ስህተት ነው› ወዘተ የሚል የፍረጃ ትንታኔ ነው፡፡ በዚህ ትንታኔ ተመርተንም ወደ ኢትዮጵያ ስንመለከት ከላይ ይወቀሱ የተባሉት ልሂቃን እና ወታደሮች የህዝብ ልጆች ናቸውና፤ መወቀስ ያለበት የህብረተሰቡ ባህል ነው ወይም ኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲን እናጣጥም ዘንድ ባህላችን/የፖለቲካ ባህላችን አይፈቅድልንም ወደሚል መደምደሚያ ይመራናል፡፡ ከዚህም ተነስተን የዲሞክራሲ ማዕበልን ኢትዮጵያዊው ባህል አክሽፎታል ማለታችን መጨረሻው ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡

ይህ እንዳይሆን ‹የሀገራዊ ባህሪ› የዲሞክራሲ ትንታኔ በተደጋጋሚ ሲከሽፍ መመልከታችን ኢትዮጵያዊያን ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሀገራዊ ባህሪ ስላለን ነው ማዕበሉ እኛ ጋር ያልደረሰው የሚለውን መደምደሚያ ፉርሽ ያደርግብናል/ያደርግልናል፡፡

የስነ ሰብ ምሁራን የባህልን ባህሪያት ሲያስረዱ፤ ‹ባህል ያስችላል፤ ይረዳል እንጅ አይወስንም› እንደሚሉ ውሳኔው የየትውልዱ እንጅ የባህሉ አይደለም፤ የሀገራዊ ባህሪ የዲሞክራሲ መረዳትም በጣም ከዲሞክራሲ እንደራቀ በሚገለጸው የአረቡ ዓለም ሳይቀር የራሱን የዲሞክራሲ ማዕበል በማስተናገዱ ‹የማያስችል ባህል የለም› ወደሚለው ብይን ያደርሰናል፡፡ ይህም ማለት ባህል አይከለክለንም፤ ወሳኞቹ ነን ችግሮቹ እንደማለት ነው፡፡ እውን ችግሮቹም፤ የችግሮቹ ሰለባዎችም እኛ ከሆንን ማን ምትሃተኛ ይሆን ማዕበሉን በድግምት የሚጠራልን?

እንደገና

ኢትዮጵያ በሶስተኛው ማዕበል መጀመሪያ ላይ የራሷን የከሸፈ ማዕበል ማስተናገዷ እና አጋጣሚውን መጠቀም ያለመቻሏ ምፀት አስቆጭቶን፤ ለምን ብለን ጠየቀን፤ ምፀቱ ግን ቀጥሎ 2005 ዓ.ም ላይ ያደርሰናል፡፡ በFreedom House ዓለማቀፍ የነፃነት እና ዲሞክራሲ መግለጫ መሰረት ሶስተኛው ማዕበል ከተጀመረበት ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የዲሞክራሲ መፍረክረክ እና መጋሸብ (Breaking down of Democracies) በእጅጉ ጎልቶ የተያበት ዓመት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዚህም በመነሳት ነው አንዳንድ በዲሞክራሲ ዙሪያ የፃፉ ምሁራን ዓመቱን የሶስተኛው ማዕበል ማብቂያ አድርገው የሚያቀርቡት፡፡

በዚህ ተመሳሳይ ወቅት ግን ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ ድንቅ የሚባል ኹነት እያስተናገደች ነበር፤ ሶስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ፡፡ በወቅቱ ሀገሪቱ በሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች አከባበር በኩል ጥሩ የሚባል ደረጃን ይዛም ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ የዲሞክራሲ ማዕበል በደጅ ቆሞ ነበር ለማለት ያስችለናል፡፡ የዓለም ዲሞክራሲ ባለፉት 50 ዓመታት ታላቅ የኋልዮሽ ጉዞ አሳይቷል በተባለበት ዓመት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ደግሞ ወደ ጥሩ ደረጃ ከፍ ብሎ ነበር፡፡ 2005 ግን እንዲሁ አላለቀም፤ ይልቁንም የዲሞክራሲው ማበብ የጥቂት ወራት ሀሴትን ፈጥሮ በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ እስር ቤት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ደግሞ ለሞት ዳርጎ የዓለሙ የዲሞክራሲ ግሽበትን ተቀላቀለ፡፡ ይህም ነው ምፀቱ፤ የዓለም አጠቃላይ የዲሞክራሲ እድገት በተዳከመበት ወቅት የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የከፍታ ምልክቶችን አሳይቶ እንደገና ወደ፤ እንደገና ስብራት ወደ አረንቋ ፡፡

የመንግስት ስለልማት አብዝቶ መናገር፤ በአደባባይ ‹ዲሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው› እያለ፤ የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ግን ‹የልማታችን አደናቃፊ ናቸው› በሚል ግልጽ እና አስደንጋጭ ሁኔታ በማጥላላት እና ወደጎን በመግፋት መሃላውን እንደሻረ እየተመለከትን፤ የዲሞክራሲ አሳላጮች የሚሆኑ ተቋማት ተጠናክረው አለመታየታቸውን እያየን፤ ዜጎች በመብታቸው ላይ ንቃት ማጣታቸውን ስንታዘብ፤ ሶስተኛው ማዕበልን መናፈቃችን ሞኝ ያስብለን ይሆናል፤ ‹የማይመጣውን ጥበቃም› ይሆንብን ይሆናል፡፡ ተስፋ ግን አለ፤ ታሪክ ዲሞክራሲን መደገፉ፤ ለውጥ የማይለወጠው ሀይል መሆኑ እንዲሁም የነፃነት የሰው ልጅ የመኖር ምክንያትነት፡፡

***

[1] በዚህ ፅሁፍ የተጠቀምኩት የጎርጎሮሳዊያኑን የዘመን አቆጣጠር ነው፡፡

[2] የሊዝበኑን ኹነት ከሌሎች መፈንቅለ መንግስቶች የሚለየው፤ የስርዓት ለውጡ ከለውጡ በፊት ከነበሩት መፈንቅለ መንግስቶች በተለየ መልኩ ከጭቆና ይልቅ ዲሞክራሲን ይዞ መምጣቱ ነው፡፡ ይሄም ነው የሶስተኛው አብዩት የውልደት ቦታ ያሰኝው፡፡

[3] ‹ሶስተኛው የዲሞክራሲያዊ አብዮት በ2005 ዓ.ም ገደማ ግሽበት (Recession) አጋጥሞታል፤ እናም ከዚህ ጊዜ ወዲህ የመጣው የለውጥ ሂደት ‘በአራተኛው የዲሞክራሲ ማዕበል’ ውስጥ መካተት አለበት› የሚሉ አንዳንድ ምሁራን  አሉ፡፡ እኔ በዚህ ሀሳብ ከማይስማሙት ወገን በመሆን የአረቡ ዓለም ፀደይም የሶስተኛው የዲሞክራሲ አብዮት አካል እንደሆነ ወስጃለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment