Wednesday, June 19, 2013

ወቸው ጉድ አቶ መለስንና ማንዴላ ደግሞ ማን አንድ አደረጋቸው!?

በፍቅር ለይኩን

እሑድ ዕለት ብሔራዊ ቡድናችን ችሎታ ሲደምር ዕድል ተጨምሮ የደቡብ አፍሪካን ብሔራዊ ቡድን (ባፈና ባፋናን) 2-1 በኾነ ወጤት አሸንፎ ከምድቡ በ13 ነጥብ አንደኛ በመኾን ወደዐሥሩ የአፍሪካ ቡድኖች ለመቀላቀል ችሏል፡፡ ከጨዋታው ጋር በተያያዘ ያስተዋለችውንና ስሜቷን ብዕርተኛዋ ሶሊያና በሚጥም ውብ ቋንቋ በአጭሩ አካፈላናለች፡፡ ከድሉ በኋላ ስለተሰማው አሳፋሪና አስደንጋጭ ስለኾነው የፊፋ ክስ ነገር አሁን ማንሳት አልፈልግም፡፡
ዋና ጉዳዬ ስለዛ አይደለምና፡፡ ሶሊ ባነሳችው ሐሳቦች ላይ ተመርኩዤ፣ በእሑዱ ዕለት ጨዋታ ያስተዋልኩትን ትዝብትና በስታዲየሙ ስለተሰቀለው የአቶ መለስና የማንዴላ ምስል፣ እንዲሁም ስለ ማንዴላ ጤንነት መልካም ምኞትን ስለሚገልጹት ባነሮች ጥቂት ነገሮችን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በጨዋታው ዋዜማ ቅዳሜ ዕለት ለግል ጉዳዬ በስታዲየም አካባቢ ነበርኩ፡፡ በአዲስ አበባ በስታዲየምና በአካባቢው በእጅጉ ያስደመሙኝና ያስደነቁኝ ያስተዋልኳቸው በርካታ ነገሮችም ነበሩ፡፡

የቅዳሜ ማምሻውንና እሑድ ዕለት በአራቱም አቅጣጭ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም የሚያመሩትን ዋና ዋና የመዲናይቱን አውራ ጎዳናዎችን ሁኔታ ለታዘበ ‹‹መንገዶች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ያመራሉ›› ዓይነት ሁኔታን የተላበሱ ነበር የሚመስሉት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ለ2014ቱ ብራዚል ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚጠብቁት ጨዋታዎች መካከል ከደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን (ከባፋና ባፋና) ጋር የሚያካሒደውን ወሳኝ የኾነውን ጨዋታ ለመመልከት እሑድ ዕለት በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝቶ ነበር፡፡

ከጨዋታው ዋዜማ ጀምሮ የአዲስ አበባ ስታዲየምና አካባቢው እጅግ የተለየና ውብ የኾነ ድባብን ተላብሶ ነበር፡፡ በስታዲየምና በአካባቢው እንዳስተዋልኩት በርከት ያሉ ነጋዴዎች የዋልያዎቹን መለያ ማልያ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ፣ አረጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የደመቁና ያሸበረቁ የእጅ ጌጦች፣ ጃንጥላዎች፣ ባርኔጣዎች … ወዘተ ገበያም በእጅጉ ደርቶ ነበር፡፡

በጨዋታው ዋዜማ ዕለተ ቅዳሜና ጨዋታው በተካሔደበት ዕለተ እሑድ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የፍቅር፣ የአንድነት፣ የነፃነት ተጋድሎና የብሔራዊ ኩራት መለያ በኾነው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ባንዲራ ዳግም የተሞሸሩ ነበር የሚመስለው የአዲስ አበባን ስታዲየምና የአካባቢውን ትዕይንት አስተውሎ ለታዘበ ሰው፡፡ ልዩ በኾነ ብሔራዊ ስሜትና ኢትዮጵያዊነት ኩራትና መንፈስ፣ በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ያሸበረቁ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም ሲተሙ ማየት በራሱ ልዩ የኾነ ስሜትን የሚየጭርና በደስታ የሚፈነቅል ትዕይንት ነው፡፡

ጎሰኝነትና የብሔር ፖለቲካ ቅም ስቅሏን ለምታይና የኢትዮጵያዊነት ስሜት በደበዘዘባት ምድራችን እንዲያ የኢትዮጵያዊነትን ሚያንቀላፋ እንጂ የማይሞት ሕያው መንፈስ እንዲህ ድል ነስቶ ወጥቶ ከማየት ውጭ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖራል ብላችኹ ነው ወገኖቼ … ?!  

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለይም ደግሞ ከሠላሳ ዓመታት ናፍቆት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የቻሉትን የዋልያዎቹን ድል ከሰማን በኋላ፣ የእግር ኳሱ ስፖርት ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን የአንድነት መንፈስና ብሔራዊ ኩራት ከፍ ያደረገና ዳግም የአንድነታችንን ውል ኪዳን እንድናድስ ምክንያት እንደኾነን እያስተዋልን ነው፡፡   

ዋልያዎቹ ከባፋና ባፋና ጋር ያደረጉትን ወሳኝ ፍልሚያ ለማየት እግር ኳስ አፍቃሪው ሕዝብ ከምሽት ጀምሮ ነበር የሌሊቱ ብርድ፣ ውርጭና ዝናብ ሳይበግረው ወረፋ መያዝ የጀመረው፡፡ ከአጎራባች የአዲስ አበባ ከተሞች ሳይቀር አዳራቸውን በስታዲየሙ አካባቢ በማድረግ ረጅሙን ወረፋ ታግሠው ትኬት በመቁረጥ ዋልያዎቹን ለመደገፍ የመጡ በርካታ ደጋፊዎች እንደነበሩም ዐይተናል፣ ሰምተናልም፡፡ በእርግጥ ጭንቅንቁን፣ ግፊያውንና ረጅሙን ሰልፍ ታግሶ፣ በለስ ቀንቶት ግጥሚያውን በአካል ተገኝቶ ለማየትና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድጋፉን ለመስጠት ወደ ስታዲየም ከገባው በዐሥር ሺሕዎች ከሚቆጠረው ሕዝብ ይልቅ በውጭ የቀረው ሕዝብ በእጥፍ የሚበልጥ ነበር፡፡

አዲስ አበባ ስታዲየም ለመግባት ዕድሉን ያላገኙ በርካታ ደጋፊዎችና እግር ኳስ አፍቃሪዎች ጨዋታውን ለመመልከት በመስቀል አደባባይና በኢትዮጵያ ሆቴል አቅራቢያ በተሰቀሉ ስክሪኖች ላይ ጨዋታውን ለመከታተል በርካታ ደጋፊዎች በሆታና በጭፈራ አካባቢውን አድምቀውት ነበር፡፡ ደመና የተጫነው በሚመስለው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚውለበለበው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ባንዲራ፣ ፊታቸውን በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ ያስወቡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የፈጠሩት ልዩ ሕብር ለአካባቢው እጅግ የደመቀ ውበትን ነበር የፈጠረለት፡፡

እኔ ለግሌ ጉዳይ በተገኘኹበት በኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ የሚገኘው ስክሪን ግን ብዙዎች ተስፋ እንዳደረጉት የዋልያዎቹና የባፋና ባፋና ጨዋታ ቢጀመርም ጨዋታውን ሊያስተላልፍ አልቻለም፡፡ በጩኸት፣ በሆታና በጭፈራ የጨዋታውን መጀመር በጉገት ሲጠባበቅ የነበረው እግር ኳስ አፍቃሪም በተንቀሳቃሽ ስልኩ ጨዋታውን እያዳመጠ ጨዋታው እኮ ተጀምሯል ለምን አያሳዩንም በሚል ወደ ተቃውሞና ጩኸት ውስጥ ገባ፡፡ ጨዋታው በተሰቀለው ስክሪን ግን መተላለፍ አልጀመረም፣ ደቂቃዎች መንጎድ ጀመሩ፡፡ ወዲያው ጩኸቱ ወደተቃውሞና ቁጣ የተቀየረ መሰለ፡፡

በርካታ ደጋፊዎችና ወጣቶችም በአቅራቢያ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድ/ት በመሮጥ ኢቲቪ ሌባ፣ ኢቲቪ ሌባ፣ ሌባ … ሌባ…! የሚለው ድምፅ አካባቢውን ማወክ ጀመሩ፡፡ የሚወረወሩ የውኃ ፕላስቲኮችና ተቃውሞዎችም ተበራከቱ፡፡

በስክሪን ጨዋታውን እንከታተላለን ብሎ ከየቤቱ የወጣው ደጋፊም እጅግ ተበሳጭቶ ቁጣውን ማንጸባረቅ ጀመረ፡፡ ብዙም ሣይቆይ ከመስቀል አደባባይ በሚገኘው ስክሪን ጨዋታውን ለማየት የወጡ ሌሎች ደጋፊዎች ከወደ መስቀል አደባባይ በኩል ወደአምባሳደር አካባቢ በመምጣት ሌሎች ደጋፊዎችን ተቀላቀሏቸው፡፡ አካባቢው በጩኸትና በተቃውሞ ለጥቂት ደቂቃዎች የአካባቢውን ሰላም አናጋው፡፡

በዚህ መካከልም እነዚህ ስሜታቸው እጅጉን የተጎዳው ወጣቶች ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ያገኙትን አንድ የአንበሳ አውቶቡስ መስታወቱን በድንጋይ በመሰባበር የቁጣቸው ማብረጃ እንዳደረጉት ዐይቻለኹ፡፡ እንዲሁም ከመስቀል አደባባይና ከኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ በተሰቀለው ስክሪን ጨዋታውን ለማየት የወጡ፣ ጨዋታውን በየቤታቸውና በየመዝናኛው ለማየት የጓጉ በርካታ ሰዎች ታክሲ ለማግኘት ያደርጉት የነበረው ግርግርና በመንገድ ላይ ሲያልፉ በነበሩ መኪናዎች ላይ በኃይል ለመውጣት ሲያደረጉ የነበረው ሩጫ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭም ነበር፡፡

ለወትሮው የተለያዩ ጨዋታዎችን ሲያስተላልፉ የነበሩ ስክሪኖች በዛን ቀን ለምን ይህን ወሳኝ ጨዋታ ለማስተላለፍ ቸል እንዳሉ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ እነዚህ በአደባባይ ተሰቀሉ ስክሪኖች ጨዋታውን እናያለን በማለት ወደ አደባባይ የወጣው ሕዝብ ስሜት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ መቸለሳቸው ብዙዎችን አሳዝኖአል፡፡ የአውሮፓን ፕሬሜየር ሊግና ውድድሮች ለማስተላለፍ የማይደክመው ስክሪን የዋልያዎቹን ወሳኝ ጨዋታ፣ ያ ሁሉ ሕዝብ እንዲያ ከየአቅጣጫው ተሰባስቦ በጉጉት ሲጠባበቀው እንዲህ መጨከኑ ብዙዎችን ያነጋገረና ያሳዘነ እንዲያም ሲል ያስቆጣ ጉዳይ ኾኖ ነበር፡፡

ቢያንስ የሚመለከተው ክፍል ጨዋታውን በስክሪን እንደማያስተላልፍ አስቀድሞ በመግለጽ ሕዝቡ ተረጋግቶና ሳይደክም ከቤቱ ተቀምጦ ጨዋታውን ይመለከትበት የነበረበትን አጋጣሚ ማሳጣቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ ሌላው ስፓርት የሰላም፣ የወንድማማችነት፣ የሕዝቦች አንድነት መገለጫ መድረክ መኾኑን የታዘብኩበትና ለኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ምስጋና ሊቸራቸው ይገባቸዋል ወዳስባለኝና ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ወደኾነኝ ሌላኛው ጉዳዬ ልለፍ፡፡
የብሔራዊ ቡድናችን/የዋልያዎቹ ደጋፊዎችና እግር ኳስ አፍቃሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ የማንዴላን ምስል የያዘ ባነር ከፍ በማድረግ ለማንዴላ ያላቸውን ክብርና ፍቅር የገለጹበት ሁኔታ ደቡብ አፍሪካውያን ተጫዋቾችንና ደጋፊዎችን ጭምር እጅግ ያስደሰተ ክስተት ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ውስጥ ቀዳሚ ስፍራና ከፍተኛ ስም ያላቸው ኔልሰን ማንዴላና አገራቸው ደቡብ አፍሪካ በእግር ኳሱ ዓለም ሲነሡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡

ዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት በአፍሪካ ዋንጫና በዓለም ዋንጫ እንዳይሳተፍ ከፍተኛ የኾነ እንቅስቃሴ በማድረግ ሌሎችንም አገራት ጭምር በማስተባባር ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያና የአፍሪካ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንና የወቅቱ ፕሬዝዳነት የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በዚህ መድርክ ከአቶ መለስ ይልቅ የአቶ ይድነቃቸውና የማንዴላ ምስል አብሮ ቢታይ ትክክለኛና እጅግ የተለየና ትርጉም ያለው በኾነ ነበር፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በአያሌው የብሔር ፖለቲካ ለተጫነው ለዘረኛው ለአቶ መለስና ለመንግሥታቸው ጀርባቸውን እንደሰጡና እንዲያ እንደ ነፍሳቸው የሚወዷትንና የሚያከብሯትን ኢትዮጵያን ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ለመጎብኘት እንደተጠየፉ መወሰናቸውንና መቆየታቸውን አሳምረን እናውቃለን፡፡ በአምልኮተ መለስ የተለከፉ የሚመስሉ ካድሬዎች አቶ መለስን ከማንዴላ ምስል ጋር ይዘው መውጣታቸው ‹‹ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ ጠጋ›› የሚለውን አገሪኛ ተረት እንድንተርትባቸው ያስገድደናል፡፡ እነዚህ ባገኙት መድረክ ሁሉ የአቶ መለስን ‹‹ሁሉን ቻይነት›› ሊነግሩን የማይደክሙትንና የማይታክታቸውን ሰዎች ሐይ ባይ ምነው ጠፋ ጎበዝ!?    

በእሑድ ዕለቱ በአዲስ አበባ ስታዲየም የታየው ይህ ለማንዴላና ለደቡብ አፍሪካውያን ሕዝቦች ማንዴላ እንዎድዎታለን!፣ ፈጣሪ ለጤንነት እንዲመለስልዎትና ረጅም ዕድሜን እንዲያድልዎ እንጸልያለን! ማንዴላ እግዚአብሔር ይባርክዎ! … ወዘተ የሚሉ መልእክቶቹን የሚያንጸባርቁት ባነሮች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች በሕዝቦች መካከል የሚያስፍነውን የአንድነት፣ የሰላምና የወንድማማችነት መንፈስ በተግባር ያሳየ እንደኾነ ነው ብዙዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ የተሰሙት፡፡ ደቡብ አፍሪካውያን ተጨዋቾችና ደጋፊዎችም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ክብር ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግኖችን የሚያከብርና የሚያወድስ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ መኾኑንም በሰላማዊው የስፖርት መድረክ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ በተግባር በማሳየት ጨዋነቱንና አፍሪካዊ ማንነቱን በማሳየት ብዙዎችን አስደንቋል፣ አስደምሟልም፡፡ በአንፃሩ ግን እምብዛም የማይተዋወቁትንና የየቅል የኾነ የፖለቲካ መርኽ የነበራቸውን አቶ መለስንና ማንዴላን በአንድነት ማስቀመጥና ለመግለጽ መሞከር ከማስተዛዘብም በላይ አላዋቂነት ይመስለኛል፡፡

ፋኖው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ በማንዴላ/በማዲባ የትግል ሕይወት ላይ እምብዛም ወይም ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የላቸውም ማለት ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አቶ መለስና ኔልሰን ማንዴላ በተለይ የተገናኙባቸው ምንም ዓይነት መድረኮች አለመኖራቸው ሁለቱ ፖለቲከኞች ምንም ዓይነት የጋራ የፖለቲካ አካሔድ እንደሌላቸው ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

ለመኾኑ እነዚህ ሰዎች ማንዴላ/ማዲባ እንዲያ በነፍስ የሚወዷትን፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማና ልዩ ሰንደቅ በሚል ስሟን አንስተው የማይጠግቧትን፣ ናፍቆታቸውና ስስታቸው የኾነችውን ኢትዮጵያን በዘመነ ኢህአዴግ አንዴም እንዳልጎበኟትና አቶ መለስንም በተለይ አግኝተዋቸውም ኾነ አነጋግረዋቸው እንደማያውቁ ብንነግራቸው ምን ይሉ ይኾን …! ታዲያ በምን ሒሳብ ነው መለስንና ማንዴላን ጎን ለጎን አድርጎ የሌለና ያልኾነ ታሪክ ለመጻፍ እነዚህ ወገኖቻችን አብዝተው የሚደክሙትና የሚጥሩት … ወይ ነዶ አሉ … ?!?!

ድል ለዋልያዎቹ! ክብር ለኢትዮጵያ ሕዝብ!

ረጅም ዕድሜ ለማንዴላ! ረጅም ዕድሜ ለሰው ልጆች ነፃነት፣ ፍትሕና መብት ለታገሉና ለሚታገሉ ሁሉ!

ሰላም! ሻሎም!

No comments:

Post a Comment