Wednesday, June 26, 2013

#ስንፍና፤ ባሕላችን ነው እንዴ?



ሁሉም ሰው የለውጥ ምኞት አለው፣ ሁሉም ሰው የለውጥ ምኞቱን እውን ማድረግ የሚችልባቸውን አማራጮች ከሞላ ጎደል ያውቃቸዋል፣ ሁሉም ሰው ግን ለውጡን እውን የማድረግ አቅም የለውም፡፡ ጥቂቶች ናቸው ይህንን ማድረግ የሚችሉት፡፡ ዋነኛው ምክንያታቸው ደግሞ ስንፍና ነው፡፡ የስንፍና ተቃራኒው ጉብዝና ነው እንበልና - ጉብዝናቸውን ከስንፍናቸው ማስበለጥ የቻሉ ሰዎች ብቻ ለውጦችን ማስመዝገብ ይችላሉ ብለን መጣጥፉን በድምዳሜ እንጀምረው፡፡

ከላይ ‹ጉብዝናን ከስንፍና ስለማስበለጥ› ያወራኋትን ነገር ‹‹ለመግቢያ መግባቢያነት›› እንድደግማት ፍቀዱልኝ፡፡ ጉዳዩ አወዛጋቢ ቢሆንም ሰዎች ሁሉ በጥቅሉ /በመሠረታዊ ነገራቸው/ አንድ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥልቀቱ እና ስፋቱ ይለያይ እንጂ፣ በትምህርትና በልምምድ ብሎም በኑሮ አጋጣሚ ይዳብር/ይሳሳ እንጂ ሁሉም በሰብኣዊነታቸው የሚጋሯቸው ባሕርያቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ስንፍና እና ጉብዝናን ነው መርጬ ላወራበት የፈለግኩት - በተለይ ስንፍናን፡፡ ሆኖም በማወራበት ጊዜ ሁሉ ፍፁም ስንፍናን (ወይም ፍፁም ጉብዝናን) እያሰብኩ እንዳላወራሁ እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ፤ የሌለውን ከየት አመጣዋለሁ?!

ስንፍና - የኢትዮጵያውያን ባሕል?

ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ስነሳ ገና ‹‹ኢትዮጵያውያን የስንፍና ባሕል አለብን›› የሚል ስጋት እየተጫጫነኝ መሆኑን አልደብቃችሁም፡፡ ጥያቄው፤ ይህ ሰብኣዊ ባሕርይ ባሕል ሊሆን ይችላል ወይ? ባሕል ሊሆን የሚችል ከሆነስ ኢትዮጵያውያን ስንፍናን ባሕል አድርገውታል ወይ? ኢትዮጵያውያን ባሕል አድርገውታል/አላደረጉትም ለማለትስ ሁሉንም በአንድ መጨፍለቅ እንችላለን ወይ? (ለምሳሌ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ጉራጌው… ሁሉ በየራሱ የሥራ ባሕል ውስጥ የሚኖር ስለሆነ አንድ ዓይነት የስንፍና/ጉብዝና ባሕል ይኖረዋል ወይ? የክርስትያን ሙስሊሙስ የሥራ ባሕል አይለያይም ወይ?...)

ጥያቄዎቹን ባወጣሁ እና ባወረድኳቸው ቁጥር የመመለስ አቅሜ ውሱን እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ ሆኖም ጥያቄውን ማንሳት በራሱ ወደመልሱ የሚያመራ ነውና መጻፌን አላቋረጥኩም፡፡

ባሕልን ከሚፈጥሩት በርካታ ቅንጣቶች መካከል ተፈጥሮ ዋነኛው ነው፡፡ ማኅበረሰቦች የሚሰፍሩባቸው አካባቢዎች እና የአካባቢው ተፈጥሯዊ ሁኔታ (ለምሳሌ፤ የዝናብ ሁኔታ፣ የወንዝ ውኃ መኖር አለመኖር፣ የመሬቱ አቀማመጥ ለእርሻ የሚመች መሆን/አለመሆኑ፣ መሬቱ የሚያበቅለው የእህል ዓይነት…) ሁሉም ተደማምረው ከሚበሉት ምግብ፣ ምግቡን እስከሚያዘጋጁበት ዘዴ፣ መኖሪያ ጎጇቸውን ከሚቀልሱበት ዘይቤ እስከ ትወፊትነት የዘለቁ ልምድና ባሕሎቻቸውን ይወስናሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ የሚሠሩ የድንጋይ ቤቶች፣ በመሐል አገር የሚገነቡ የጭቃ /እና እንጨት/ ቤቶች፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚሠሩ ተንቀሳቃሽ የኬሻ ቤቶች እና ወዘተ… የአካባቢያዊ ተፈጥሮ አመጥ ናቸው፡፡ በተመሳሳይም በሰሜን የሚበሉ የጥራጥሬ ፍጭ ውጤቶች፣ በደቡብ የሚበሉ የረዥም ጊዜ ሒደት (processed) የምግብ ውጤቶች (ለምሳሌ ቆጮ) የዚሁ የተፈጥሮ ሰጥ ባሕል ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህ መነሻ ነው ቤት ለመሥራት፣ ምግብ ለማዘጋጀት እና በሌላውም ለመትጋት የሚያበቁ የግል ባሕርያትን ባሕል ይጫናቸዋል ለማለት የምጣደፈው፤ የስንፍና ባሕሪን እንደየባሕሉ ጎልቶና ላልቶ ሊታይ ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ ያቆመኝ ይኸው ግንዛቤዬ ነው፡፡

በዚሁ ዕሳቤና ድምዳሜ ተንተርሼ ሰሜን አካባቢ ያለው የተፈጥሮ ሞጋችነት (ማለትም የምድራዊ አቀማመጡ ወጣገባነት እና ድንጋያማነት…) ለአካባቢው ነዋሪዎች የትጋት ባሕርይ/ባሕል እንዲይዙ አድርጓቸዋል ብዬ አምናለሁ፣ ወደመሐል አገር ስንመጣ ደግሞ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የመሬቱ ገራምነት እና በአመዛኙ ጠፍጣፋ አቀማመጥ፣ በቂ ውኃ የመኖሩ አጋጣሚ እና ሌሎችም ተደማምረው የአካባቢው ነዋሪዎች ከፈጠራ ይልቅ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ የሆነ ማኅበረሰብ (ማለትም ተፈጥሮ የሰጠችውን የምግብ ውጤት እንደወረደ የመመገብ፣ እና የአኗኗር ዘዬውም ከዚያውጋ የተወዳጀ እንዲሆን /ወተትና የወተት ውጤቶች ምሳሌ ናቸው/) አድርጓል ብዬ አምናለሁ፡፡ በምስራቃዊ ሰሜን ኢትዮጵያም የምንመለከተው በአንድ ቦታ ረግቶ አለመቀመጥ፣ በእንስሳት ውጤቶች ምግብ ብቻ መኖርና ሌሎችም ተፈጥሮ ለአካባቢው የሰጠችው ሁኔታ የፈጠረው ባሕል ነው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ለም የሆኑ እና ከዓመት ዓመት የሚቆዩ ፍራፍሬዎችን፣ እና አትክልቶችን የሚያመርቱት (ደቡቦች) ደግሞ የተፈጥሮ ውጤቶቹን እንዲሁ ከመመገብ ይልቅ በብዙ ሒደቶች ውስጥ እንዲያልፉ (እሴት እንዲጨምሩ) የሚያደርጉበት የአመጋገብ ዘይቤ ማምጣታቸው ደግሞ ተፈጥሮ ገር ብትሆንም እንደየባሕሉ ሠርተው ተፈጥሮ የሰጠቻቸው ላይ ጨምረውበት የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ይኖራሉ ለሚለው በር ይከፍትልናል፡፡

እንግዲህ አባባሌ የ13 ወር ፀጋ ‹የ13 ወር ስንፍናን› አብሮ አጎናፅፎን ይሆናል የሚል ነው፡፡ በጥቅል ዕይታ ክረምቱ እጅግ የማይቀዘቅዝ፣ በጋው እምብዛም የማይሞቅ፤ መሬቱ ወንዝ ሳያስቀልስ ከሰማይ በሚወርድ ዝናብ የሚለማ መሆኑ በራሱ የጠንካራ ሠራተኝነት ባሕርይ ነፍጎ ስንፍናን ባሕላችን አድርጎብናል ባይ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ተፈጥሯዊ ምቾታችን የፈጠረው ስንፍና ብቻ ነው የተፀናወተን የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሌሎችም ባሕላችን ያዳበረው ነገር አለ ባይ ነኝ፡፡

ስንፍናን የሚያበረታቱ ባሕሎቻችን

እኔ በማውቃቸው ማኅበረሰቦች፣ ባነበብኳቸውና በሰማኋቸው የምረዳቸው ባሕሎቻችን እና ልምዶቻችን ስለስንፍናችን አዎንታዊ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ይነግሩኛል፡፡ ለዚህም ማረጋገጫ ይሆኑኛል በሚል የሚከተሉትን ከ’ሀ’ እስከ ‘ሐ’ ዘርዝሬያለሁ፡- 

(ሀ). ለየብቻ ሠርተው፥ በደቦ ይበሉታል!

ኢትዮጵያውያን ‹ሲበሉ እንጂ ሲሠሩ አይተባበሩም› የሚለው አባባል ታዋቂ አባባል ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚታይም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ደቦ የሚለው ቃል የእርሻ ምርቶችን በጋራ ለመሰብሰብ ሲሠሩ የሚጠቀሙበት ቢሆንም ይህ ባሕል በተለዩ አጋጣሚዎች (በተለይ እህሉ ቶሎ እንዲሰበሰብ የሚያስገድድ ተፈጥሯዊ አደጋ /አንበጣ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ…/ ሲመጣ እና በመሳሰሉት እንጂ ሁልጊዜም የማይሆን) በመሆኑ እና፣ በጋራ መሰብሰቡም ቢሆን የአንድ ሰውን፣ ከዚያም የሌላኛውን እንጂ በጋራ ሠርቶ በጋራ ማምረት የሚባል ልምድ ስለሌለ በደቦ ከመሥራት ይልቅ በደቦ የመብላት ልምድ አለን ቢባል ይሻላል፡፡ ነገር ግን በጋራ የመብላት ልምድ እንጂ የመሥራት ልምድ የለንም ሲባል በተናጠል የመሥራት ልምድ አለን ማለት አይደለም፡፡ በጣም ጠንካራ ሠራተኞች የሚባሉት ገበሬዎቻችን እንኳን በዓመት የሚሠሩት በአማካይ ሦስት ወራት ነው፡፡

በደቦ መብላት ምናልባት ጥሩ ባሕላችን ሊሆን ይችላል፤ መተሳሰባችንንም የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የስንፍናችን መሠረት ሆኗልም ብዬ ለመከራከር የሚያበቃ ምክንያት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያውያን ባይሠሩም እንኳ በልተው ያድራሉ የሚባለው በዚህ ባሕላችን ሳቢያ ነው፡፡ አንዱ የሠራውን ባሕሉ ብቻውን ቢበላ እንደስስታምና ስግብግብ እንዲቆጠር ስለሚያደርገው ማካፈሉ አይቀርም፡፡ ይህ ‹ሶሻሊስታዊ› ጽንሰ-ሐሳብ ያለው ባሕል፣ የሠሩት ሰዎች ካልሠሩት የበለጠ የተለየ ምን እንዳገኙ ስለማይነግራቸው በተለይ ስንፍናን አሸንፎ (ጎብዞ) መሥራትን ያስጠላቸዋል፡፡ (በርግጥ ሰው የሠራውን ተካፍሎ መብላትና፣ በራስ የሠሩትን አካፍሎ መብላት ዕኩል በራስ የመቆም ስሜት አይሰጡም፡፡)

ይህ ባሕል ነው ዛሬ በየከተማው በረዥሙ በተዘረጉ ቤተሰቦች (extended families) እና ወዳጅነቶች ውስጥ የምናገኛቸው፡፡ ከቤተሰብ ውስጥ አንዱ ሌት ተቀን ሠርቶ ብዙ ሀብት ቢያፈራ እንዲሁ ያለምንም ውልና ስምምነት የሱን ያክል ሀብቱን ለማፍራት ያልደከሙትን ሰዎች የመደገፍ እና የሀብቱን ፍሬ የማካፈል ባሕላዊ ግዴታ ይጣልበታል፡፡ ይህ ማለት ጎብዞ በመሥራቱ በሕይወቱ ላይ ለውጥ ከማስመዝገብ ይልቅ በስንፍና የደኸዩትን የቤተሰቡን አባላትም ቢሆን በመደገፍ ለውጥ ማየት ሳይችል ይቀራል፡፡ ያኔ በሰነፉ የቤተሰቡ አባልና በራሷ/ሱ ጉብዝና መካከል ያለው ልዩነት ይደበዝዝበታል፡፡ ይኸው ድጋፍ እና ማካፈል የሚያስፈልገውን ብቻ ለይቶ የማያውቀው ልምድ እና ባሕል ነው በርካታ ጥገኞችን፣ በርካታ ለማኞችን እንድናፈራ ያደረገን!

(ለ). ስም ያሰጣሉ (calling them names)

ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ሠራተኝነት ማኅበረሰባዊ ዕውቅና (recognition) የሚያሰጠው በጣም አልፎ፣ አልፎ ነው፡፡ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ብረት አቅልጠው ማረሻ ሞፈር የሚሠሩለትን ገበሬው ‹ቀጥቃጭ› ይላቸዋል - በስድብ፡፡ ሸክላ ሠርተው ምግብ ማብሰያ የሚያቀርቡትን ሌላም፣ ሌላም ብዙ የመሥራት ጥበብ የሚያፈሩትን ሞረቴ፣ ቡዳ፣ ባለእጅ እያለ ይሰድባቸዋል፡፡ ይህም የነዚህ ባለሙያዎችን ጥበብ መውረስ በራሱ ስም የሚያሰጥ በመሆኑ በተቻለ መጠን ከዚያ መሸሽን አስፈላጊ የሚያደርግ ባሕል ነው፤ ትውፊታዊ ጥበበኛነታችን ያሳጣንም ይህና ይህ መሰሎቹ ጎጂ ባሕሎች መሆናቸውን አምናለሁ፡፡

ዛሬም በራሱ ጠንካራ ባሕርያትን እና ባሕሎችን የሚያበረታታ ቋንቋዊ ልምድ እንዳለን እጠራጠራለሁ፡፡ የጉራጌ ማኅበረሰብ አባላት ከምንም ተነስተው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችንመሥራት የሚችሉ በርካታ ምሳሌዎችን አሳይተውናል፡፡ ሆኖም አሁንም ‹‹ስስታም›› የሚለውን ቃል ለመተካት ‹‹አንተ ጉራጌ›› ሲባል መስማት የተለመደ ነው፡፡ ስስታምነት እና ጥሩ የቁጠባ ባሕልን እና ምክንያታዊ የገንዘብ አወጣጥ ባሕልን ለይቶ እና አምኖ መቀበል የሚቸግረን ዛሬም ብዙዎች አለን፡፡

የጉራጌ ማኅበረሰብ የዕቁብን ልምድ ሲተገብር እና በተለያዩ ዘርፎች ስኬታማ ሲሆን፣ በገጠርም አረንጓዴ አካባቢ አቅፎ የተቀመሙ (ወራት በሚፈጅ አዘገጃጀት የተሰናዱ) ምግቦችን ሠርቶ ለመብላት የመቻሉ ጉዳይ ጠንክሮ የመሥራት ሥር የሰደደ ባሕላዊ ድጋፍ ቢኖረው ነው ብዬ አምናለሁ፤ ጉዳዩ ሰፊ ጥናት ቢጠይቅም እኔ በመደዴ ምልከታዬ የምደመድመው ግን ልዩነት የጉብዝና ባሕላቸው የስንፍናውን በመብለጡ መሆኑን ነው፡፡

(ሐ). ምትሐተኛ ያሰኛሉ

በአገራችን የተሳካለት ነጋዴ ሲገጥማቸው ሰዎች ይሄ ‹‹ምን ዓይነት መተት አሠርቶ ነው?›› ወይም ደግሞ በዘመንኛው ‹‹ጉቦ ከፍሎ ነው…›› እንጂ… ‹ምን የተለየ ነገር ሠርቶ ነው?› ብሎ የሚጠይቅ ሰው ማግኘት ይከብዳል፡፡ ‹ሰዎች ጎብዘው በመሥራት የሆነ ደረጃ አይደርሱም፤ በሆነ ምትሐት እንጂ› ብሎ የማሰቡ ነገር ሳናስበው ውስጣችን ሰርጾ ባሕል ሳይሆንብን አይቀርም፡፡

እነዚህ ጥቅል ነገሮችን ጠቃቀስኩ እንጂ የችግሮቹ መሠረቶች ብዙ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ሃይማኖትንም መጥቀስ ቢያስፈልገን፣ በዓላትን ማክበር በሚባል እስካሁንም ባልቀረ ቀኖናዊ ድጋፍ በሌለው  እምነት ብዙ የሥራ ቀናት በስንፍና ይባክናሉ (መጽሐፍ ቅዱስ በተለይ በብሉይ ኪዳን ስንፍናን የሚተች መሆኑን በማሰብ ነው ቀኖናዊ ድጋፍ የለውም የምለው)፡፡ ከዚያም በላይ ሃይማኖቶች ሠርቶ ከመክበር ይልቅ ተካፍሎ መብላትን ያበረታታሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ሃይማኖተኛ እንደመሆናቸው የምክሩ ውጤት የመሆን ዕድል አላቸው፡፡ በርግጥ በዚህ ረገድ እስልምና ጠንክሮ ሠርቶ ሀብትና ንብረት የማፍሪያ መንገዶችን በቁራን ላይ ደንግጎ ያስቀምጣል (ቢያንስ ሀብታም መሆንን አያነውርም)፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ጥቂቶች ቢጎብዙም የብዙኃኑ ስንፍና የጥቂቶቹን ጉብዝና ቀርጥፎ ይበላዋል ስለዚህ - ኢትዮጵያውያን ሰነፍ ነን!

ብዙዎቻችን የገዛ ቢሯችንን ጠረጴዛ እንኳን ማጽዳት የሚከብደን/የሚሰለቸን፣ ያነሳነውን ዕቃ በቦታው መመለስ የሚከብደን፣ የጀመርነውን ንባብ/ጽሑፍ መጨረስ ዳገት መውጣት የሚሆንብን፣ ሐሳባችንን እንኳን ሳይቀር ማስረዳት የሚታክተን፣ በቀጠሮ ሰዓት መድረስ የማይሆንልን - ፈረንጆቹ the devil is in the detail (ገመናው ዝርዝሩ ውስጥ) ነው እንዲሉ ስንፍና ይዞን ነው፤… ጥቃቅኖቹ ስንፍናዎቻችን ለትልቁ ኪሳራችን መጋቢ ነው፡፡ 

በዚህ ስንፍናችን ደግሞ አገር ቀርቶ ጥሩ ቤተሰብ መገንባት ይከብዳል፡፡


No comments:

Post a Comment