(ክፍል ፫)
ጥገኝነትና አውሮፓ!
ውዴ ሆይ! በስልኩ ውስጥ እዚህ አገር መረረኝ ልምጣ ማለትሽ ገርሞኛል።
ወደ አውሮፓ መምጣት ስለተቻለ ብቻ አይመጣም። መምጣት ያለብሽ ጥገኝነት ለመጠየቅ ከሆነ እንዴት እንደምትኖሪ ልንገርሽ። አውሮፓ
ለጥገኝነት ጠያቂዎች የምቾት ውስጥ ፍዳዎችን አዘጋጅታ ትጠብቃቸዋለች። እዚህ ከመጡ በኋላ የሚገጥማቸው ማለቂያ የሌለው ፈተና ሆዳቸው
ስለማይራብና ጉሮሯቸው ስለማይደርቅ ይለይባቸዋል። ድሮ ከሚያውቁት ፈተና ስለሚለይ ወይም ፈተናው በምቾት የተቃኘ ስለሚሆን ከፍዳው
ለመውጣት ያዳግታል። ለማንኛውም ስለአውሮፓ የጥገኝነት የህልም መንገዶች አንዳንድ ነገሮች ልበልሽ።
አውሮፓ እንደ አንድ በጎሳና በጎጥ እንደተከፋፈለች አገር ትመሰላለች።
በተለይ European Union (EU) ተብሎ ለኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ትብብር የተመሰረተው 27 አገሮች አባል የሆኑበት የአንድነት ስብስብ አንድ አስመስሏቸዋል። ይህ ህብረት ከመመስረቱ በፊት የአህጉሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መዘውር እንግሊዝ ለንደን ላይ እንደነበረ ይነገራል። ከዚህ ህብረት ምስረታ በኋላ ግን ከእንግሊዝ ተፅእኖ ተላቆ ወደ ቤሊጅየሟ ዋና ከተማ ብራስልስ ተዛውሮ በጀርመንና በፈረንሳይ ፊታውራሪነት እየተዘወረ ይገኛል።
በዚህ በአውሮፓ ‘ምክንያት አልባ ሆነሽ’ ብትሰደጅ ፈተናው እጅግ
ከባድ ይሆንብሻል። ስለሆነም በስደት አገር ላይ ፈተናሽ ከሌሎቹ አገሮች ስደተኞች አይሎ ከራስሽ አልፎ ቤተሰቦችሽን አንዳንዴም እዚህ
ከመጣሽ በኋላ ትወልጂና ምንም የማያውቁትን ልጆችሽን ሲያንገላታ ይታያል።
ምክንያት ሳይኖርሽ ወይም ከመንግስት ሳትጣዪ ወደአውሮፓ ከምትመጪ እዛው ብትቀሪ ወይም ወደ አጎራባች አገሮች ብትሄጂ
ይመረጣል። ጎረቤት አገራትንና የአረቡን ዓለም ለማቆራረጥና አውሮፓ ለመድረስ የከፈልሺው መስዋዕትነት በዜሮ ሲባዛብሽ ይበልጡኑ ተስፋ
ስለምትቆርጪ እዛው በነበርሺበት ሰርተሽ ብትኖሪ ይመረጣል። አውሮፓ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች የብክነት ቦታ ስለሆነ፤ በስጋዊ ምቾት
እየኖርሽ ተስፋ መቁረጥ ከባድ ይሆንብሻልና።
ማሩን አምርሮ ወተቱን አጥቁሮ በግፍ ሕዝብን የሚጨቁንን አምባገነናዊ ስርዓት ለመጣል የታገለ ሰው እንደ ብርቱካን፣ እንደ አንዷለም፣ እንደ እስክንድር አይነት ዜጋ እና ከነዚህ የነፃነት መሪዎች ጋር የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል ብለው፣ በፓለቲካ ድርጅት ታቅፈው፣ በማህበራት ተደራጅተው ለወገን በደል የሚቆረቆሩ፣ ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ ሰዎች፣ ስለ እኩልነት የሚፅፉ፣ ስለነፃነት የሚጨነቁ እና በተለያየ ስልት መንግስትን የሚታገሉ ዜጎች ብለውት ብለውት አልሆን ሲላቸውና ወደ አዘቅቱ ሊጣሉ ሲሉ ራሳቸውን ለማዳን ቢፈረጥጡና ስደት ቢመርጡ አይገርምም።ታግለው ሞክረው ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች ምክንያት ስላላቸው በስደት መዳረሻቸው የሚሰማቸውና ጥገኝነት የሚሰጣቸው መንግስት አያጡም።
ሌላው ደግሞ ከዓንባ-ገነኖች ወገን የሆነና፤ መንግስታዊ ስልጣኑን
ለበጎ ነገር ሲጠቀምበት ኖሮ፣ በስልጣኑ እየተከለለ መንግስት እንዲወድቅ ለሌሎች ጋር በስውር ሲሰራ የነበረ፣ የመንግስትን ጭቆና
ጠልቶ ለሕዝብ ወግኖ አምባገነኖችን ሲያዳክምና ለተቃዋሚዎች መረጃ ሲሰጥ የኖረ፣ ሕዝብን ለማገልገል የገባውን ቃል አጥፎ የሚዘርፍን ስርዓት ለመጣል ከሌሎች ጋር ሲያብር የተገኘ፣ የአገር ሃብት ሲዘረፍ እያየ ዝም ስላላለ ወደ አዘቅቱ ሊጣል ቀን የተቆረጠለት ተቆርቋሪ ሳይቀድሙት ነቅቶ አገር ጥሎ ቁርበት ጠቅሎ ቢሰደድ በሞያው፣ በማዕረጉ እና በስራው ምክንያት በመሰደዱ በደረሰበት አገር ላይ የሚሰማው ጆሮ አያጣም።
በቅርብ ዘመድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምክንያት ከመንግስት ሰዎች ዛቻና
ማስፈራሪያ የሚደርሰው የቤተሰብ አባል ይኖራል፤ በአባት የፖለቲካ ተሳትፎ ተሳቦ መደፈር በልጅ ወይም በሚስት ላይ ሊከሰት ይችላል፤
ከቤተሰብ አንዱ የሚያኪያሂደው እንቅስቃሴ ለሌሎቹ የመታሰር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በተለይ እንደኢትዮጵያ አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴን
ለመግታት ሰበብ የሚፈረክባቸው አገሮች ላይ እንዲህ አይነቱ ጥቃት ይስተዋላል። እናም የዚህ አይነት ጥቃት ሰለባ ከሆንሽ ጠባሳሽንና
ሌሎች መረጃዎችሽን ይዘሽ ስትሰደጂ አዛኝ መንግስታት ይረከቡሽና ቁስልሽ እስኪጠግ እንክብካቤ ይደረግልሻል ወይም ይደረግልሃል። ይህም
እንግዲህ አንዱ የስደት ምክንያት መሆኑ ነው።
በተጨማሪም የጥገኝነት ደረጃን ሊያጎናፅፍ የሚችል ጉዳይ ውስጥ የሚመደበው
አጓጉል ሃጢያት የተጠናወተውና በማሕበረሰቡ ያልተፈቀዱ አስነዋሪ ድርጊቶችን ሲያዘወትር የተገኘ ሰው የሚደርስበትን መገለልና ጥቃት
በመሸሽ አገር ጥሎ ቁርበት ጠቅሎ ቢፈረጥጥ የሆነውን ነገር በተግባር ማስረዳት ስለሚችል ሰሚዎቹ ያምኑትና የተደላደለ ኑሮ ሊሰጡት
ይችላሉ።
ነገር ግን እንዲሁ ውጭ አገርን እንደ ፅድቅ ቆጥሮ ለስደት መነሳት
የማይወጡት ማጥ ውስጥ መዘፈቅን ሊያስከትል ይችላል። ለዚህ ንግግሬ መነሻ የሆኑኝ ባለፉት ተከታታይ ወራት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች
ያገኘኋቸው ስደተኞችና በተለያዩ ምክንያቶች የረገጥኳቸው የአውሮፓ አገሮች ውስጥ የታዘብኳቸው የአበሻው ወገኖችሽ ኑሮዎች ናቸው።
እና አንቺም እንደበርካቶች እጣ ክፍልሽ ስደት ሆኖ የሚዘገንነው የወገን ስቃይ ሳይገጥምሽ አውሮፓ ገባሽ እንበልና የሚገጥምሽን የስደት ህይወት ታሪክ እንጀምር። በየትኛውም መንገድ፣ ከየትኛውም የኑሮ ደረጃ ላይ ነይ ልክ አውሮፓ እንደገባሽ ተቀባይ ያስፈልግሻል። ወዳጅ ዘመድ ትፈልጊና አንድ ቦታ ታርፊያለሽ። አንድ ቀን ታርፊና ለራስሽ ቃል የገባሽውን ማሰላሰል ትጀምሪያለሽ። ሰርተሽ ልትበለፅጊ፣ አገርሽ ላይ የነበረውን የቁጥ ቁጥ እድገት በፍጥነት ልትከውኚ፣ በድህነት ያጎነበሱ ቤተሰቦችሽን ቀና ልታደርጊ፣ ዲያስፖራ ተብለሽ ወደ አገርሽ ቶሎ ተመልሰሽ የቀደሙት ከስደት ተመላሾች የሸለሉትን ሽለላ ለመድገም እያልሽ ታሰላስያለሽ።
ተቀባይ አግኝተሽ የስደት ይህወትሽን ሀ ብለህ ትጀምሪያለሽ ማለት ነው። ነገር ግን ልክ እንደደረስሽ የሚጠብቅሽ ነገር ያላሰብሽው ሆኖ ታገኚዋለሽ። በተቀበለሽ ሰው የሚነገርሽ ታሪክ የሥራ፣ የገንዘብና ብልፅግና ሳይሆን አንቺ ሰምተሺው ያማታውቂው ‘እጅ የመስጠት’ ታሪክ ይሆናል። ይህን ስትሰሚ ግር ትሰኚና ‘ምንድን ነው እጅ መስጠት? ለማን ነው እጄን የምሰጠው? እጅ መስጠት እኮ መማረክ ማለት ነው፤ ታዲያ ማን ነው የሚማርከኝ?’ እያልሽ የጥያቄ መዓት ትጠይቂያለሽ። ከዚያም ጆሮሽ የሚሰማው ጥገኝነት የማግኘትና ያለማግኘት ታሪክ ይሆናል። የሚነገርሽ የጥገኝነት ታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የቅብብል
ታሪክ ስለሆነ በደንብ ላይገለፅልሽ ይችላል። ስለጥገኝነት የተደነገገውንም ሕግ ማንም ላይነግርሽ ይችላል።
እንግዳ ሆነሽ ባረፍሽበት አካባቢ የምታገኚያቸው የአገርሽ ሰዎች አብዛኞቹ
አዲስ መሆንሽን እንዳወቁ የሚያነሷቸውና የሚጥሏቸው የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። ስላንቺ በተነሳ ቁጥር የድርጅቶቹ ስም፣ ጥገኝነት
ሰጪዎቹ የሚከተሉት ነባራዊ ሁኔታ እና የአንቺ ማንነት በስፋት መዳሰስ ይጀምራል። አንቺ በተከሰትሺበት ወቅት ጥገኝነት ሰጪዎቹ በአንዱ
ድርጅት ላይ ተመስርተው ጉዳያቸውን ላቀረቡ ሰዎች አውንታዊ ምላሽ ከሰጡ የአንቺም የስደት ጉዞ ታሪክ ወደዚህ ድርጅት እንዲሆን ይወሰንብሽና
ስለ ድርጅቱ ውስጠ ሚስጢር እንድታጠኚ ይነገርሻል። ተፅፎ የተሰጠሽንም የድርጅትና የግለሰብ ቁርኝት የራስሽ አድርገሽ እንድትወስጅው
ማጥናት ትጀምሪያለሽ። ነፍጥ አንግተው መንግስትን የሚወጉ ድርጅቶች አንዱ ከደረሰሽ ስለድርጅቱ ማብራራት ይጠበቅብሻል። በየት በኩል
እንደተዋጋ፣ ምን ምን ጉልህ ክስተቶች እንደተፈጠሩና ያንቺ ድርሻ ምን ላይ እንደነበር ማብራራት በቃለ መጠይቅ ወቅት ዋናው ስራሽ
ይሆናል።
ያልጠበቅሺውን ጉድ ሲያወሩብሽ ኧረ ወደመጣሁበት ቁምነገር እንግባ ብለሽ ልትወተውቺ ትችያለሽ። ግን ማንም አይሰማሺም። አንቺ የመጣሺው ሰርተሽ ለመክበር ነበር፤ የመጣሺበትን ቁም ነገር ትተው ያላሰብሺውን እስኪበቃሽ ይነግሩሻል። እነሱ እውቀት አላቸው አንቺ ምንም አታውቂምና በቃ ሁሉም ሲያገኝሽ ያለ የሌለ እውቀቱን ይዘራብሽ ይጀምራል። ይህ ሁሉ ሰው እንዲያ ሲያወራ ስታዪ ትደነቂ ይሆናል ነገር ግን እንደነሱ ለማውራት ውለሽ ማደር አይጠበቅብሽም፣ እንደነሱ ለመደስኮር ጥቂት ጊዚያት ብቻ ይበቁሻል። ለማንኛውም ከሁሉም መካሪዎች አንደበት ውስጥ case የምትለዋን ቃል ሺ ጊዜ ትሰሚያታለሽ። ወጣ ገባ እያሉ case መረጥሽ፣ caseሽን አጠናሽ፣ caseሽን ከአመጣጥሽ ጋር አቀናጀሽ? አመጣጥሽን ወሰንሽ? እየተባልሽ የእንግድነት ጊዜሽን ታገባድድጂና እጅ ለመስጠት ትነሺያለሽ።
በተመከርሺው መሰረት ኬዝሽን ሰርተሽ ለሳምንታት አዲስ ማንነት አብጅተሽ
ቆይተሽ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ትሄጃለሽ። አዲስ ማንነት ማለት ብዙ ብዙ ለውጥ አድርገሽ ማለት ነው። ለውጦቹ የትምህርት ደረጃሽን፣ ቤተሰብሽን፣
ስራሽን፣ ያደግሺበትን ሰፈር አልፎ አልፎም ዜግነትሽን ቀይረው በመጨረሻ አዲስ የመጠሪያ ስም ያላብሱሻል። ይህ አዲስ ማንነት የመኖሪያ
ፍቃድ አግኝቶ ለመኖር ወሳኝ እንደሆነ ስለተመከርሽ ደረጃ በደረጃ በደንብ አድርገሽ ታጠኛለሽ። አዲስ ስም ሲሰጥሽ እንዳይረሳሽ የቅርብ
ዘመድሽን እንድታደርጊ ትመከሪና ወደድ ያደረግሺውን አንዱን ለራስሽ ትሰጫለሽ ወይ አንዱ አምባ-ገነን የፈለገውን ይሰጥሽና እንዳትረሺው
ሸምድጅ ይልሽል።
ማንነትን መደበቅ በየት ከአገር እንደወጣሽና የየትኛዋን አገር ቪዛ
እንደተጠቀምሽ እንዳይታወቅብሽ ይረዳል በሚል እሳቤ ነው። አንድ ሰው ከአገሩ ሲወጣ በቦሌ በኩል፤ በሰላማዊ መንገድ ከሆነ አገሩ
ላይ ለመኖር ምንም የሚያግደው ነገር እንደሌለ ይታመናል። ከመንግስት ጋር ቁርሾ ቢኖረው በቦሌ በኩል ሲያልፍ ዝም አይሉትም ተብሎ
ይታሰባል። አንዳንዴ መንግስት የማሪያም መንገድ የሚሰጣቸው ስደተኞች ቢኖሩም አብዛኛው ግን በሰላም እንደማያልፍ ያስባሉ። ስለዚህ
ማንነትሽን ከስር ከመሰረትሽ መንግለሽ ካልጣልሽ ይነቁብሽና የመኖሪያ ፍቃዱን ለዘለዓለም አይሰጡሽም ሲሉሽ የተባልሺውን ታደርጊያለሽ።
ወደ ፖሊስ ስትሄጂ በስርዓት ይቀበሉሻል። ግን አብዝቶ መምከር የሚወደው
ስደተኛው ወገንሽ ፊትሽ እንዳይፈታ፣ አንደበትሽ እንዳይከፈት አስፈራርቶ ስለሚልክሽ ግንባርሽን አኮማትረሽ አንደበትሽን ለጉመሽ ጆሮሽን
አሹለሽ የጥገኝነት መንገድሽን ትጀምሪያለሽ። ሁሉም እንዳንቺው በያረፈበት ቤት ተመሳሳይ የማንነት ማስተካከያ ተደርጎለት እንደመጣ
በዚህ ጉዞሽ ከምታገኚያቸው የአገርሽ ልጆች ትረጃለሽ። ከስም ጀምሮ እስከ ባህርይ ድረስ ሰው ሁሉ አዲስ ይሆንብሻል። ቀስ በቀስ
ግንባርሽ ይፈታል፣ አንደበትሽ ይከፈታል ከዚያም ሁሉ ነገር ወደነበረበት ይመለስና ስምሽ እና ዜግነትሽ እንደተቀየረ ይቀራል።
ለፖሊስ እጅ ከሰጠሽ በኋላ ወደ መጠለያ ጣቢያ ያስገቡሻል። የምትላኪበት
የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ እንደየ አገሩ ይለያያል። እንደጀርመን አይነት በስደተኛ ብዛት የተጥለቀለቁ ትልልቅ አገሮች ሲቀበሉሽ በግዴለሽነት
ያስተናግዱሻል። የአገርህ ዜጎች ተሰብስበው በአንድ ወደሚኖሩበት መጠለያ ይልኩሽና መኖር ትጀምሪያለሽ። ጥቂት ስደተኛ የሚሄድባቸው
የስካንዴነቪያ አገሮች ደግሞ ከተለያዩ አገር ዜጎች ጋር አብረሽ በጋራ እንድትኖሪ ትገደጃለሽ። ብዙ አይነት ቋንቋ የሚናገሩ የብዙ
አገር ዜጎች አብረውሽ ሊኖሩ ይችላሉ። ታዲያ በነዚህ መጠለያ የምታገኚው አሕዛብ caseን እንደ አውራ ቃል አድርጎ ጥቂት ቃላትን አብዝቶ ይጠቀማል።
ስደተኛውን አሕዛብ ብዬ የጠራሁት ለመፍረድ ደፍሬ ሳይሆን አንድም ስለሕይወቱ አንድም ስለውሸቱ ነው። ሕይወቱ ምን ሆነ? ያልሺኝ እንደሆነ፤ የስደተኛው ህይወት አስከፊ መሆኑን የቀደሙት አሕዛብም ሕይወት እንደዚሁ እንደነበር ለማመላከት ሲሆን ተሰዶ ስሙን፣ ዜግነቱን፣ ማንነቱን በመቀየር ያልዋሸ ባለመኖሩ ደግሞ አትዋሽ የሚለውን ሕግ እያንዳንዱ ጥሷልና ነው።
የአብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት የስደተኛ አቀባበል ይመሳሰላል። ለፖሊስ እጅ ትሰጪና የውጭ ዜጎችን ጉዳይ ወደሚያየው ቢሮ ትሻገሪያለሽ። ይህ ቢሮ ከአገርሽ ለመሰደድ ያስቻለሽን ችግር ይጠይቅሽና ወደ መጠለያ ጣቢያ ይልክሻል። እዛ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተቀምጠሽ ያቀረብሺው የጥገኝነት ማመልከቻ ተቀበይነት እንዳገኘ ወይም ውድቅ እንደተደረገ ይነገርሻል። ጥገኝነት የጠየቅሺው ጣልያን፣ ግሪክ ወይም ስፔን ከሆነ የፈረንጅ አገር የጎዳና ተዳዳሪ እንድትሆኚ ልትገደጂ ትችያለሽ። ኢኮኖሚያቸው ክፉኛ ስለተቃወሰ እነዚህ አገሮች ለስደተኛ ደንታ የላቸውም። አሰልፈው መዝግበው ሲጨርሱ ወደጎዳና ይለቁሻል። ጀርመን፣ ቤልጅየም፣ ስዊድን፣ ወይም ኖርዌይ ከሆኑ ደግሞ ምቾቱ ቢለያይም ጥሩ የሚባል የስደተኛ እንክብካቤ ይደረግልሻል።
በ2011 ብቻ 302.445 ጥገኝነት ጠያቂዎች 27 የአውሮፓ አገሮችን በር አንኳኩተዋል። ከነዚህ ውስጥ 19% በፈረንሳይ 17.6% በጀርመን 11.3% በጣልያን፣ 10.5% በቤልጅየም፣ 9.8% በስዊድን የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ሲያስገቡ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊዘርላንድ፣ ሆላንድና ኮስትሪያም እንዲሁ በዛ ያለ ስደተኛ የሚገባባቸው አገሮች ናቸው። በዚሁ አመት ወደአውሮፓ ምድር ገብተው ወይም ከአንዱ አውሮፓ አገር ወደአንዱ ተሸጋግረው ጥገኝነት ከጠየቁት ስደተኞች ውስጥ ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ የተሰጣቸው 237410 ጥገኝነት ጠያቂዎች ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 25% የሚሆኑት ብቻ ጉዳያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ የተቀሩት ጉዳያቸው ውድቅ ሆኖ ከአገር እንዲለቁ የተነገራቸው ናቸው።
ሰዎች ከቀያቸው ወደ ከተማ ሊፈልሱ ይችላሉ፣ ክትመት ዓለም-ዓቀፍ ሂደት በመሆኑ ምክንያት። ከአገር ወደ አገር መሰደድ ግን ከዚህ ይለያል። ሃላፊነታቸውን በትክክል መወጣት ባልቻሉ መንግስታት ምክንያት በሚፈጠሩ ችግሮች ሕዝቦች አገራቸውን ጥለው ለስደት ይዳረጋሉ። ጦርነት፣ ሁከትንና ብጥብጥ፣ ዋስትና የሌለው ኑሮ፣ የአጥፍቶ ጠፊዎችን ፍንዳታ፣ ፖለቲካዊ ችግር፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና በአገራቸው የወደፊት እጣ ተስፋ ማጣት ምክንያት በተለያዩ አለም አገራት የሚገኙ ሕዝቦች አገራቸውን እየጣሉ ለስደት ይዳረጋሉ። በ2011 ወደ አውሮፓ ብዙ ስደተኛ ካስመዘገቡ አገሮች ቀዳሚዎቹ አፍጋኒስታን፣ ሩሲያ፣ ፓኪስታን፣ ኢራቅ፣ ሰርቢያ፣ ሶማሊያ ሲሆኑ የአፍጋኒዝታን ወጣቶች አገራቸውን ጥሎ በመሰደድ ቀዳሚ ናቸው፤ በዚሁ አመት ብቻ 30000 ስደተኞች በአውሮፓ ተመዝግበዋል። ከአፍሪካ በዛ ያለ ቁጥር ከሚሰደድባቸው አገሮች ውስጥ ቀዳሚዋ ሶማሊያ ስትሆን ናይጀሪያ፣ ኮንጎ (ዛየር)፣ ኤርትራ እንደቅደምተከተላቸው ይከተላሉ።
ከነዚህ አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ጥቂት የሚባል ስደተኛ ጥገኝነት ለመጠየቅ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ይገባል። አንቺ በአንዱ መንገድ አንድ የአውሮፓ አገር ጥገኝነት ትጠይቂና መኖር ትጀምሪያለሽ። በዚህ ኑሮሽ የተለያዩ ሂደቶችን ታልፊያለሽ። የመጀመሪያው የጥገኝነት ማመልከቻሽን ማቅረብና ውጤቱን መጠበቅ ይሆናል። ይህ እንደጉዳይሽ ጥልቀት እስከ ሁለት አመት ሊወስድ ይችላል። አዎንታዊ መልስ ከተሰጠሽም ከማሕበረሰቡ ጋር ተሰባጥረሽ አብረሽ መኖር ትጀምሪያለሽ። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚሰጠው መልስ አሉታዊ ነው። የአገርሽ መንግስት በነዚህ አውሮፓ አገሮች የውጭ ግንኙነት ስራን በባለስልጣናቱ አማካኝነት በትጋት ይሰራል። በየአገሩ የሚገኙት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ አካላት ዋንኛ ስራቸው እንደሌሎቹ አገሮች ዜጎቹን ከጥቃት መጠበቅና የአገሪቱን መልካም ገፅታ ለሚኖሩበት አገር ማሳወቅ አይደለም። የነዚህ ባለስልጣናት ዋነኛ ስራ የእርዳታ ግንኙነትን ማጠናከር፣ አንቺንና ወገንሽን ለስደት የሚዳርጋቸው አገራዊ ችግር ፖለቲካ ሳይሆን ኢኮኖሚ እንደሆነ መስበክና በውጭ አገር ተደራጅተው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን ዜጎች ማዳከም ነው።
ይህም የጥገኝነት ጥያቄሽ ተቀባይነት እንዳያገኝ የአገርሽ መንግስት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት ያሳያል። በዚህ ምክንያት አንቺም ከአገርሽ የተሰደድሺበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ችግር ስለሆነ ትባይና የጥገኝነት ማመልከቻህ ውድቅ ይደረግብሻል። ሙሉ በሙሉ ውድቅ ከተደረገብሽ ቡኃላ አገር ለቀሽ እንድትወጪላቸው በሚያስፈራራ ደብዳቤ ይነግሩሻል። አገር ለቀሽ ውጪ የሚለውን ማስፈራሪያ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የተነሳ አንድ ስደተኛ ሶስት ምርጫዎች አሉት። ወደአገርቤት መመለስ የመጀመሪያው ሲሆን የቀሩት ሁለቱ አማራጮች ደግሞ ስደትን አጠናክሮ ይዞ ወደ ሌሎች አገሮች መጓዝን የሚጠይቁ ናቸው።
----
----
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው
ethioswe13@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡
No comments:
Post a Comment