Tuesday, May 14, 2013

የአንደኛ ዓመት ማስታወሻ፤ ሽቅቡም ቁልቁሉም!

‹ዞን ዘጠኝ እንዴት ተመሠረተ? ለምን ተመሠረተ? ለምን ዞን ዘጠኝ ተባለ?...› እና ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ባሳለፍነው ዓመት በዞን ዘጠኝ የፌስቡክ ገጽ በብዛት ያስተናገድናቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እነሆ ‹ዞን ዘጠኝ› የሚለውን ስም አውጥተን ጦማሩን (ብሎጉን) የፈጠርንበትን ቀን (ግንቦት 5/2004) አንደኛ ዓመት በማስመልከት ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡

በመጀመሪያ እንዲህ ነበር

በሊባኖስ ቤይሩት በአሠሪዎቿ ድብደባ የደረሰባት የዓለም ደቻሳ ሞት ብዙ የማኅበራዊ አውታር ኢትዮጵያውንን አስቆጣ፡፡ ይህ ምሬት ፌስቡክን እንደማህፀን ተጠቅሞደጉ ኢትዮጵያዊ’ የተሰኘው ቡድን ወለደ፡፡ በአጋጣሚ የተወሰኑ የዞን ዘጠኝ አባላት እነዚህ ስብስብ ውስጥ ተገኘን፤ እንዲሁ አጋጣሚ! አንዳንዱ ለሰላምታ፣ አንዳንዱ ሲያልፍ ሲያገድም አንዱ ደግሞ የዓለም ጉዳይ አስቆጭቶት፡፡

የዓለምን ደቻሳን ቤተሰቦች (ልጆች) ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰብና የመሳሰሉት ሥራዎች ሲጠናቀቁ የደጉ ኢትዮጵያ ቡድን አባላት መካከል ጥቂቶቹ ከሌሎች የፌስቡክ ወዳጆች ጋር ወትሮም አየር (በይነመረብ) ላይ በተመሳሳይ ሐሳብ ዙሪያ ሲያወሩ የሚተዋወቁት ሰዎች ነበሩና እየተገናኙ መወያየታቸውን ቀጠሉ፡፡ ይህ መቀራረብ ተጨማሪ ቀጠሮዎችን ወለደ፡፡ በጠፋችው ከተማ አዲስ አበባ እንደመስቀል ወፍ አልፎ አልፎ የሚካሄዱ የፖለቲካ ውይይቶች መከታተል ጀመርን፡፡ ይህ ተከታታይ ግንኙነት ሌላ ሐሳብ ይዞ ብቅ አለ፡፡ በጣም ትንሽ፣ ግን መሰባሰብ የሚፈልግ ሐሳብ፡፡ ለምን በየቦታውን በየብሎጉ የምናወራውን ሰብሰብ አድርገን ወደ አንድ ቦታ አናመጣውምየሚለው ሐሳብ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በመጠየቅ ወደ ቃሊቲ በመሄድ ታገዘ፡፡ የቃሊቲው ጉዞ ብዙ መነቃቃትንና የዞን 9ኝን ስም ወለደ፡፡

ስሙ የተገኘው እንዲህ ነው፤ በወቅቱ ከእስረኞች መሐል በማንኛውም ሰው መጠየቅ የሚችሉትን ርዕዮት ዓለሙንና ከእርስዋ ጋር በተመሳሳይ ክስ የተከሰሱ እስረኞችን ለነርሱ በተከለለው ዞን 8 ስናዋራቸው ሒሩት ክፍሌ ‹‹እናንተስ፣ ዞን 9 እነዴት ነው?›› ብላ ጠየቀችን፡፡ በተደናገረ ስሜት ደህና ነን ብለን ስንመልስ ርዕዮትእኛ እዚህ ያለነው እኮ ውጪ ያላችሁትን ትልቁ እስር ቤት ዞን 9 ውስጥ ነው ያላችሁት ነው የምንላችሁ› ብላ አብራራችልን፡፡ ከሰዓታት በኋላ ስም ስንፈልግለት የነበረው የጦማሪዎች ቡድን ስም ተገኘለት - ‹‹ለምን ዞን 9 አንለውም?›› አለ ከመካከላችን አንዱ፤ በፈገግታ አፀደቅነው፡፡ ከዚያ ተጀምረው ወደ ነበሩት ምንና እንዴት እናድርግ ውይይቶች ተመለስን፡፡


ዞን9 ስሙን ከማግኘቱ ቀደም ብሎ ስናነሳቸው ከነበሩት ጉዳዮች መካከል አንዱ በአገሩ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ወጣት መቀነስ ነበር፡፡ ያገባኛልን ማምጣት በእኛ አቅም የማይሳካ የማይታሰብ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ባቅማችን እንደሚያገባን በመናገር የድርሻችንን ለመሞከር ስንነሳ የመጀመሪያው ዓላማ ተበታትኖ የሚታየውን የበይነ መረብ ውይይት መልክ ወዳለው ተዋስኦ ለማምጣት የሚሞክር አለፈመደብ (‹ፕላትፎርም›) ለመፍጠር መሞከር ነበር፡፡ ይህ ሙከራ የተለያዩ ጦማሮች እና የማኅበረሰብ ሚዲያ ገጾች ላይ የሚንጸባረቁትን ሐሳቦቻችንን ወደ አንድ ማምጣት ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይህ የመጦመር ሒደት ግን ከግል አራማጅነት ባሕርያችን ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ገባን፡፡ ዞን9 ላይ ጦማር የሚጽፉ ዘጠኛውያን በግላቸው የየራሳቸውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚጠቀሙ አራማጆች መሆናቸውን አልቀየረውም፡፡

ይህ ዞኑን ወደኹለተኛው የአራማጅነት ሚናው እንዲመጣ ውይይት ከፈተ፡፡ ይህ ረዘም ያለ ውይይትራሳችንን እንደምንድን ነው የምንቆጥረው?› ከሚለው ጥያቄ አንስቶ የአራማጅነት ሚና በቡድን እንወስዳለን ስንል ምን ማድረግ እንችላለን ማለታችን ነው እስከሚለው ድረስ ውይይቶች ተደረጉና ቅርጽ ያላቸው የአራማጅነት ዘመቻዎች ዕቅድ ተወለደ፡፡ ይህ ዘመቻዎችን የማቀድ ሥራ ሲጠናቀቅ ሌሎች ተጨማሪ ዓላማዎችን ለቡድኑ ሰጠ፡፡ የበይነመረብ ዓለሙ ሌሎች ሠርተው የሚያቀብሉትን ሐሳቦች እና አጀንዳዎች ይዞ ስለሚጓዝ በተቃራኒው አጀንዳዎችን የማቀበል እና የማስቀመጥ ዓላማዎችን ይዞ እንዲነሳ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት ነበረን፡፡ በመሆኑም የበይነ መረብ ውይይቶችን በአጫጭር ጽሑፎች እና በአርቲክሎች በማስደገፍ ዘመቻዎች ማካሄድ ውይይቱን ቅርጽ የመስጠት ድርሻችንን ከማጠናከሩም በተጨማሪ የበይነመረብ ሐሳቦች የመነጋሪያ አጀንዳዎች መሆን ጀምረዋል፡፡

የቡድኑ አባላት ከተለያየ የሙያ /ትምህርት/ ዘርፍ አቅጣጫ፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሰባሰብን መሆናችን እና በአገሪቱ ፖለቲካ ላይም የተለያዩ የምንስማማባቸውም የምንከራከርባቸውም ሐሳቦች መኖራቸውን የቡድኑ ዋነኛ ጥንካሬ አድርገን እንድንወስደው አድርጎናል፡፡ በሌላ በኩል በአጋራችን የሚፈታተነን ያልዳበረው የትችት ባሕላችን፣ የፈለግነውን ያክል እንዳንጓዝ እና እንዳንናገር በመገደቡ ረገድ ተለቅ ያለ ፈተና ነበር ማለት እንችላለን፡፡  

ጦማሮቻችን

በጣም በተገደበ አቅምና በትርፍ ጊዜ የሚዘጋጁት እነዚህ ጦማሮች ከዞን ዘጠኛውያን ውጪ አንባቢዎችንም ጭምር ወደ ጽሑፍ ማምጣት ችለው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በግላችን ሐሳባችንን እንደፈለግን ከምንገልጽባቸው የግል መንገዶቻችን ወጥተን በከፊል ተቋማዊ እና ቡድናዊ ሐሳቦች ማምጣትን አስለምደውናል፡፡ ኃላፊነት የምንወስድባቸው ሲያሰኘን የማናጠፋቸው እና ከግል ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጽሑፎችን እና ሐሳቦችን ማንፀባረቅ ምንም ደካማ ጎናችን ቢሆንም ሙከራው አስተምሮናል ብለን አናምናለን፡፡ በተለያዩ ተግዳሮቶች የተነሳ እየተቆራረጡይን አልገቡም እንጂ የሚዲያና የጦማሮች ዳሰሳ ሙከራዎቹም እንደሙከራ የተማርንባቸው ነበሩ፡፡ የግል ኑሮ ውጣ ወረድና ዕቅድ ወደኋላ ያንጓተተው የአንድ ዓመት የጦማሮች ዕቅዳችን በዘመቻዎች ላይ ግን የተሻለ ውጤቶችን አስመዝግቧል ማለት ይቻላል፡፡

በዓመቱ በአጠቃላይ በጦማራችን ላይ 160 ያህል ጽሑፎች የታተሙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከ20 በላይ የሚሆኑትን የጻፉት የዞናችን አባል ያልሆኑ ወዳጆች ናቸው፡፡ ከነዚህ ጦማራችን ላይ ከታተሙት መካከል ገሚሱን ለሕትመት ሚዲያው (መጽሔቶች) ማበደራችንንም አስተውለናል፡፡

ዘመቻዎች

ከግል የአራማጅነት ባሕርያችን ወደ ቡድን ሲመጡ የወለዱት የበይነመረብ ዘመቻዎችን የማካሄድ ዕቅድ በአመዛኙ የማኅበረሰብ ሚዲያው የፈጠረውን ዕድል ተጠቅመው በይነመረብ አራማጅነትን መልክ የሰጡ ነበሩ ለማለት እንደፍራለን፡፡ እስካሁን ከተደረጉት ሦስት የበይነ መረብ ዘመቻዎች (ሕገ መንግስቱ ይከበር፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለሁሉም እና ዲሞክራሲን ተግባራዊ እናርግ፤ የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ) በይዘትም በማስተባበርም የተማርንባቸውና ከአንደኛ ሌላኛው እንዲሻል ጥረት ያደረግንባቸው ነበሩ፡፡ በዚህ ረገድ ከጦማራች ተከታታዮች ዕኩል እኛም አብረን እያደግንና የምናልመው ለውጥ አካል እየሆንን መጥተናል ማለት ይቻላል፡፡

ዘመቻዎቹ ከትችት የማያመልጡ፣ ጉድለትም የማያጣቸው ቢሆኑም ቢያንስ ቢያንስ ሐሳቦቹን ለውይይት በማቅረብና ሁሉም ወገኖች የሚያወሩበት አንድ አጋጣሚ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ፍርሐት በባሕያችን ውስጥ በሰረፀበት በዚህ ዘመንዘመቻዎቹ መሳተፍ መነቃቃት እና ፍርሐትን የመጋራት ስሜት በመፍጠር ጤናማ ሐሳቦችን ወደ ማንሸራሸር የሚደረገውን ቀሰስተኛ ጉዞ ትንሽም ቢሆን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ የደረሱን አስተያየቶች እና የዘመቻው ተሳትፎ ምስክሮች ነበሩ፡፡ እስከ አሁን በነበሩት ዘመቻዎች በፌስቡክ ብቻ ከ50,000 በላይ ሰዎችን በአንድ ዘመቻ መድረስ የተቻለበት ሆኗል፡፡ በትዊተር ደግሞ ኢምፕሬሽኑ እስከ 80,000 የደረሰበት ጊዜ አለ፡፡ የዘመቻዎቹ ዓላማ በተለይ ርዕሶቹ ላይ ማሰብ፣ ሐሳብን መግለጽና መነጋገር መቻል ሲሆን በሒደቱ የሚያዳምጡ አካላትንም በግልጽ ለመንገር አጋጣሚውን መጠቀምም ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡

ጥያቄዎችና ትችቶች


አራማጅነትን የሚለውን ስያሜ የሰሙ አንዳንዶችእንዴት ራሳቸውን አራማጅ› እያሉ ይጠራሉ የሚል ጥያቄንም አንስተዋል፤ የአራማጅነትን ትርጉም ማየት መልሱን ቀላል ያደርገዋል፡፡ አራማጅነት ስንል በተመረጡ ርዕሶች ዙሪያ ተደጋጋሚ እና የታሰበባቸው ድምፆችን ማስተጋባት ሲሆን ያንን አድገናል ብለን እናስባለን - ድምፃችን መሰማቱ፣ ሐሳባችን መገዛቱ ጉዳይ ላይ ያለው ክርክር እንዳለ ሆኖ፡፡ ‹‹ከአንድ ወገን ፓለቲካ ማራመድ›› እስከ ‹‹ፓርቲ ፖለቲካ›› ድረስ የተተቸንበት ጉዳይ ነው፡፡ ጦማርን እንደአራማጅነት እንደመደበ አለፍ መጠቀማችን  መጠን የምናነሳቸው የፓለቲካ ሐሳቦች የአንድ ወገን ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ የአራማጅት ክፋቱም ይኸው ነው፡፡ አራማጅት የተጎተተውን ወደፊት ማምጣት ከሆነ ያልተጎተተውን ሐሳብ ላይ ማራመድ አይቻልምና የተቀየማችሁ በዚህ መልኩ ተረድታችሁ ይቅር በሉን፡፡ እኛ ሕዝባዊ ተዋስኦ፣ ምክንያታዊ ሙግት እና በአገር ጉዳይ ያገባኛል ባይነትን ለማበረታታት እና ለማነቃቃት የቻልነውን የምናደርግ እንጂ ምንም ዓይነት የፓርቲ ፖለቲካ የመጫወት ሕልም የለንም፤ ሆኖም ያገባኛል የምንልባቸው ጉዳዮች ፖለቲካ ነክ እንደመሆናቸው አሁን ከዚህኛው፣ በኋላ ከዚያኛው ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሌላኛውጋ የሚመሳሰል አጀንዳዎችን ባነሳን ቁጥር ከተለያዩ ቡድኖች ጋር እኛን እንደወገንተኛ ማየት መጨረሻው ስህተት እንደሚሆን ግን ሳናገረጋግጥ አናልፍም፡፡

ደካሞች ነበርን

የመነቃቃት (‹ኢንስፓይሬሽን›) እጥረት የእኛም ድካም ምንጭ ነበር፡፡ መነቃቃት ማጣታችንን ለመገዳደር ብዙ ሞክናል - የወደቅንበት ትልቁ ፈተናችን ሆኖ ዓመቱ አለፈ እንጂ፡፡ የጦማሮች መቆራረጥ፣ የውይይት ሐሳቦቸን አንስቶ በጋራ ለማውራት መሞከር ጀምረን የወደቅንባው ፈተናዎች ናቸው፡፡ ጠፍተን ብቅ ስንል ፊት የማይነሱን ወዳጆች ባይኖሩን ኖሮ ደግሞ አንድ ዓመት መቆየትም አስቸጋሪ ይሆንብን ነበር፡፡ የተለያዩ የተሰፉ ሐሳብን የማካፈል ሙከራዎችንም ጀምረን አልዘለቅንባቸውም፣ የ‹‹መክሸፍ››ን ተከታታይ ጽሑፍ ጅማሬዎች፣ ተከታታይ የሚዲያና የጦማር ዳሰሳዎችጨምሮ ሌሎችንም ማስታወስ ይቻላል፡፡ ታቅደው ባደባባይ ባይወሩም በኛው ድካም የትም ያልደረሱ ሥራዎችም ብዙ ናቸው፡፡ ቋሚ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሐፍትን አሳጥሮ በዳሰሳ መልክ ማቅረብም የታሰበበት ነገር ግን ያልተነገረና የወደቅንበት ፈተና ነው፡፡ ሳንናገርወደቅንበት ከነብዛቱ ያለፉትን 12 ወራት መዝለቃችን የወዳጆቻችንን ደግነት ያሳያል፡፡ ምስጋና ለዞን ዘጠኝ ነዋሪዎች!

በመጀመሪያው ጽሑፋችን ‹‹የሚያገባውን ትውልድ ፍለጋ…›› ያገባናል ብለን ጀምረናል፡፡ ይህች ሙከራ ትንሽ መሆኗ አያጠራጠርም፡፡ ጥቂቶችን ካስወራች፣ አንዳንዶችን ካወያየች፣ ሌሎችን በየፍላጎታቸው ዙሪያ እንደኛው ዓይነት ኢ-መደበኛም ይሁን መደበኛ ቡድን ለመፍጠር ካነሳሳች ስኬት አጠገብ ባትደርስም ከስረናል ብለን እንዳናስብ ይረዳናል፡፡ አንዱን ዓመት ያያችሁንን፣ ያነበባችሁንን፣ ያበረታታችሁንን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡ በአካሄዳችን የተከፋችሁብንም ጥያቄ የሆነባችሁን ሐሳብ ጭምር እንድታካፍሉን ተጋብዛችኋል፤ መልስ ካለን እንመልሳለን፣ መልሱ መሻሻል ከሆነም ለመስተካከል እንጥራለን፡፡ በድጋሚ እናመሰግናለን!

1 comment:

  1. እንኳን ለዐመቱ በሰላም አደረሳችሁ! ያልደረሱም ያለፉም አሉና ... ሥም ይወጣ እሥር ቤት ይከተላል እቤት አሉ። ሙከራችሁ ሁሉ የሚደነቅ የሚበረታታ ነው። እንግዲህ በቁም የታሠረ ዞን ፱ ከሆነ አሳሪው ዞን ፲ እንደተፋጠጠ ነው፡ ወደ ዞን ፰ መቀነስ ጀምሯል፡በኢህአደግ የኢኮኖሚ ዕድገትና ባለሥልጣን የሚቀንስበት ዘመን!? ለማናቸውም እናንተ ይመቻችሁ በርቱ በለው! ከሀገረ ካናዳ

    ReplyDelete