Wednesday, May 15, 2013

ግንቦት 7 – ታሪካዊ ቀን!


በክፍሉ ታደሰ - (ግንቦት 7 /ኢትዮጵያ፤ እኮ ለምን? እንዴት?/ ከሚለው መጽሐፍ የተቀነጨበ)
 
በግንቦት 7/1997 ምርጫ 524 የምክርቤት ወንበሮች ለምክር ቤት ቀረቡ፡፡ 23 የሚሆኑት በነሐሴ ወር በሱማሌ ክልል ለሚደረገው ምርጫ ወደጎን ተተዉ፡፡
 
ግንቦት 7 በተካሄደው ምርጫ ተሳትፌያለሁ፡፡ ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የተሳተፍኩበትን ነው የማቀርበው፡፡ እኔ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ በሦስተኛ ሰው አድርጌ ታሪኩን ላቀርበው ሞክሬ፤ ራቀብኝ፣ ባዕድ ሆነብኝ፣ የኔ መስሎ አልሰማህ አለኝ፡፡ እናም ታሪኩን በቀጥታ ለመተረክ ወሰንኩ፡፡
 
ግንቦት 7/1997 ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቤቴ ወጥቼ ወደምርጫጣቢያ አመራሁ፡፡ ከምኖርበት ሰፈር ወደምመርጥበት ጣቢያ ለመሄድ ከ15 እስከ 20 ኪ.ሜ. መንዳት ነበረብኝ፡፡ በጠዋት የተነሳሁትም አንድም ቀደም ብዬ ከመረጥኩ በኋላ ከተማውን ተዘዋውሬ ለማየት እንዲረዳኝ በማሰብ ነበር፡፡ ዘጠኝ ኪሜ ያህል ተጉዤ መገናኛ አካባቢ ስደርስ ከአንድ የምርጫ ጣቢያ ፊትለፊት ረዥም ሰልፍ አየሁ፡፡ መኪናዬን ትንሽ ቆም አድርጌ ሰልፉ ምን ያህል ረዥም እደሆነ ለመቃኘት ሞከርኩ፡፡ ሰልፉ እየተጠማዘዘ ቢያንስ 300 ሜትር የሚያክል ቦታ ይዟል፡፡ የተሰለፈውን የሰው ዓይነት ለማየትም ሞከርኩ ዝንቅ ነበር፡፡ ወንድ/ሴት፣ ትልቅ/ትንሽ፣ ወጣት/አዛውንት ሁሉም በትዕግስት ተሰልፈው ይጠብቃሉ፡፡ እንዴት በጥዋት ሊነሱ ቻሉ ብዬ እያሰብኩ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ መገናኛ አደባባዩጋ ስደርስ ወደሰሜን አቅጣጫ ወደሚወስደው መንገድ ወደቀኝ ታጠፍኩ፡፡ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ ወደሚወስደው መንገድ፣ በድሮው አጠራር ወይዝሮል ወደሚባለው መንገድ ወደሚያስገባው አደባባይ ደርሼ ወደግራ ታጠፍኩ፡፡ ከዚህ ቦታ ጀምሮ ምርጫ የማደርግበት ሰፈር እስከምደርስ ድረስ ስድስት ወይም ሰባት የምርጫ ጣቢያዎች አየሁ፡፡ ሁሉም ቦታዎች እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች ተሰልፈው በትዕግስት ይጠባበቃሉ፡፡ እንደዕንቁ ጠብቀው ያቆዩት የምርጫ ካርዳቸውን ከሳጥናቸው ለመጨመር በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡
 
መጀመሪያ እንዳየሁት የምርጫ ጣቢያው ሁሉ ሌሎች ቦታዎችም የተሰለፉት ዓይነት ተመሳሳ ነበር፡፡ ሰው በምርጫው ለመሳተፍ የነበረው ፍላጎት አስገረመኝ፡፡ ረዥም ዘመን በፖለቲካ ትግል ውስጥ ብቆይም ይህን የመሰለ አጋጣሚ አይቼ አላውቅም ነበርና ጥቂት ወራት ወደኋላ ተመልሼ የነበረውን ሁኔታ ለማስታወስ ሞከርኩ፡፡ ምርጫው ሲታወጅ ለመንግሥትም ሆነ ለተቃዋሚ ድርጅቶች አሳሳቢው የነበረው ሒደት ሰው በፖለቲካ ሒደቱ ለመሳተፍ ፍላጎት እያጣ በመሄዱና ተስፋ በመቁረጡ ለምርጫው መመዝገብ ብዙም ፍላጎት ያልነበረው መሆኑ ነበር፡፡ በዚህ የመጀመሪያ ወቅት የመንግሥት፣ የሲቪል ድርጅቶችም ሆነ የተቃዋሚዎቹ ዋና ሥራ ሰው እንዲመዘገብ መቀስቀስና መወትወት ነበር፡፡ በብዙኃን መገናኛ እና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰፊ ቅስቀሳ ሲካሄድ ቆየ፡፡ በቂ ሰው ሊመዘገብ ባለመቻሉ፣ የምዝገባው ጊዜ ሊራዘም ችሏል፡፡
 
የምርጫው ሒደት ከተጀመረበት መስከረም 1997 ጀምሮ ምዝገባው እስከተገባደደበት እስከ የካቲት 6 ድረስ የሁሉም ተቋማት ርብርብ በምርጫ ምዝገባው ላይ መሆኑ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ሌላ ቦታ እንደተጠቀሰው በኢሕአዴግ ዘመን ከ1997 በፊት ብቻ ወደ ስምንት የሚጠጉ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ ሕዝቡ ምረጥ እየተባለ በምርጫዎቹ ተሳትፏል፡፡ ከምርጫዎቹ በኋላ ለውጥ ሲመጣ አላየም፡፡ እናም ለምርጫ ለምን እንደሚቧግት ሊገባው አልቻለም፡፡ ምን አደከመኝ ለውጥ ላይመጣ እያለ ተስፋ እየቆረጠ ሄዷል፡፡ ምርጫ ከንቱ ድካም እንደሆነ ተረድቶ ካልተገደደ በቀር ለመሳተፍ ፍላጎት አልነበረውመ፡፡ ሕዝቡ ፈለገም አልፈለገ፣ ወደደም ጠላ መረጠም አልመረጠ ውጤቱ ገና ከወዲሁ ስለሚታወቅ አብዛኛው ሰው ምን አታከተኝ ብሎ ላለመሳተፍ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ገዢው ፓርቲ ሁልጊዜም አሸንፌያለሁ እንደሚል ይረዳል፡፡ ገዢው ፓርቲ በሕዝቡ ቡራኬ የሥልጣን ዘመኔን አራዝሜያለሁ እንደሚል፣ ቀደም ሲል ጀምሮ ያውቀዋል፡፡ ሕዝቡ ይህንን ቡራኬ ለምን መስጠት እንዳለበት፣ ለምንስ ጉልበቱንና ጊዜውን እንደሚያባክን አልገባህ ስላለው ምርጫን የመድረክ ተውኔት አድርጎ ራሱን ማግለል እንዳለበት ወስኖ ቆይቷል፡፡
 
ለ1997 ምርጫ መንግሥትና የመንግሥት ደጋፊዎች ብቻ ሕዝቡን ለምርጫ እንዲሳተፍ ቢጠይቁት ኖሮ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ጥሪያቸውን ባልተቀበለ ነበር፡፡ ይሁንና ጥሪውን ከተቃዋሚዎችም አንደበት በመስማቱ ተመዘገበ፤ ለማንኛውም ካርዱን ልያዝ የሚሆነውን አያለሁ አለ፡፡ ወደኋላ ላይ እንደምናየው የምርጫ ውድድሩ መልክ እየያዘና እውነተኛ ፉክክር እየታየበት ሲሄድ ካርድ ያላወጡ ብዙ ሰዎች ለማውጣት ወሰኑ፡፡ ይህ የሚሆነው ከየካቲት 1997 በፊት ባለው ጊዜ ሲሆን ከዚያ በኋላ በነበረው ሒደት የተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ ክርክር ብዙዎችን ቢማርክም ጊዜው በማለፉ የምርጫ ካርድ ለማውጣት ቢፈልጉም ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ ካርድ ባለማውጣታቸው የተፀፀቱ በርካታ ናቸው፡፡
 
ወደምርጫ ሒደቱ መለስ ልበልና ምርጫ የማካሄድበት ሰፈር ደርሼ ሰልፍ ያዝኩ ተራዬ እስከሚደርስ ባልሳሳት ሦስት ሰዓት ያክል ተሰለፍኩ፡፡ ቆይታዬን አልጠላሁትም፡፡ ብዙ እንድታዘብ ረዳኝ፡፡ የሕዝቡ አንድ አካል መሆኔ ተሰማኝ፡፡
 
የምርጫ ካርዴን ለማስገባት ተሰልፌ በነበረበት ወቅት ከኋላዬ ተሰልፈው የነበሩ አንዲት ሴት ደግመው ደጋግመው ይናገሩት የነበረው ነገር አስገረመኝ፡፡ ስለምርው ሥነስርዓት፣ ፎርሙ እንዴት መሞላት እንዳለበት፣ ምልክት እንዴት እንደሚደረግ፣ ፎርሙ እንዴት እንደሚተጣጠፍ፣ ወዘተ ቀበሌውን ወክላ አንዲት ሴት ታስረዳለች፡፡ ስለምርጫው ከማስረዳት በስተቀር ምንም የምታደርገው ነገር አልነበረም፡፡ ሴትየዋ የጠራ አማርኛ አትናገርም፡፡ አፏን ያዝ ያደርጋታል፡፡ ይህች ሴት ከቀበሌው ውስጥ ምን ሥልጣን እንዳላት አላውቅም፡፡ ከሌላ ቦታ የመጣች ትሁን አትሁንም ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ከኋላዬ የተሰለፉ አንዲት ሴትዮም ይወቋት/አይወቋትም አላውቅም፡፡ ብቻ ያስገረመኝ ሴትየዋ በተናገረች ቁጥር ‹‹ሰላቢ›› ይላሉ፡፡ አንዲት ቃል ናት የሚተነፍሷት፡፡ ‹‹ሰላቢ››፡፡ ዞር ብዬ ሴትየዋን አየኋቸው፡፡ ደርበብ ያሉ የቤት እመቤት ናቸው፡፡ ለምን ሴትየዋን እንደጠሏት ልረዳ አልቻልኩም፡፡ የግል ፀብ ይኑራቸው አይኑራቸው፣ ወይም ሌላ ምክንያት እንዳላቸው የማውቀው ነገር የለም፡፡ ምን በደለችዎት እና ነው የሚሰድቧት ብዬ ለመጠየቅ ዳዳኝ፡፡ አንተስ ማነህ፣ ምናገባህ ቢሉኝ አልኩ፡፡ ብቻ ድፍረት አጣሁና ጥያቄዬን ውጬ ቀረሁ፤ በጉዳዩ ላይ ትንሽ አብሰለሰልሁ፡፡
 
ምርጫ ያደረግኩበት ሰፈር ውስጥ አብዛኛው ነዋሪ የአማርኛ ተናጋሪ ሲሆኑ፣ በንግድ ሥራ የተሰማሩ በርከት ያሉ ጉራጌዎች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሰፈሩ ትንሽ ከፍ ብሎ በሸማ ሥራ የሚተዳደሩ ጋሞዎች ይገኛሉ፡፡ ሁኔታው ይህ ሆኖ ሳለ የቀበሌው ሊቀመንበር ትግርኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡፡ ምናልባትም የሕወሓት አባል ይሆናሉ፡፡ ስለሌሎቹ የቀበሌው ባለሥልጣናት ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ እነዚህ ሐሳቦች በአእምሮዬ ላይ ብልጭ አሉ፡፡ ከሴትዬዋ ድርጊት ጋርም ላዛምዳቸው ሞከርኩ፡፡ ጉዳዩ የትም ሊወስደኝ የማይችል ስለሆነ ብዙም አልቆየሁበትም፡፡ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማተኮር ጀመርኩ፡፡
 
በምርጫ በተሰለፍኩበት በዚህ ወቅት ብዙ ነገሮችን ታዘብኩ ተማርኩ፡፡ ሲፈልግ ሕዝቡ ሥነስርዓት ከሚገባው በላ ያከብራል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ምርጫው የግሉ አድርጎ ስለወሰደ እንዳይበላሽ ከመንገዱ ወጣ ብሎም እንኳን ሊያስተካክል ይሞክራል፡፡ ሰው ለምርጫ ሳይሆን ለሠርግ ወይም ለሌላ ዓመት በዓል የተጠራ ነበር የሚመስለው፤ ደስተኛ ነበር፡፡ ወጣቶቹም ያ ያልተፈጠረባቸውን ትዕግስት ከየት እንዳገኙት አላውቅም በጨዋነት ተራቸውን ይጠባበቃሉ፡፡ ብዙ እናቶች ተሰልፈዋል፡፡ እጃቸው ባዶ ነው፡፡ ካርዳቸውን አልያዙም እንዴ ብዬ ሳስብ፣ አንዳንዶቹ ከጡታቸው ስር እየመዘዙ ሲያወጡ አየሁ፡፡ ለካርዳቸው የሰጡት ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑ አስገረመኝ፡፡ አዛውንቱ ይህንን ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የተቃዋሚዎች ክርክር እየበረታ ሲሄድ ኢሕአዴግ ካርዶች እየገዛ ነው ተብሎ በከተማው ስለተወራ አዛዋንቱ ለጥንቃቄው ያህል ያደረጉት ይሆናል ብዬ ገመትኩ፡፡
 
ከወለደች 15 ቀናት ብቻ ያስቆጠረች አራስ ልትመርጥ መጣች፤ ታመን ከመጣንበት ተነስተን መጣን የሚሉ በሽተኞች፣ መሄድ ያቃታቸው ሽማግሌዎች፣ ወዘተ ሲመርጡ ማየት አስገራሚ ነበር፡፡ ከምርጫው በፊት በሥራ ጉዳይ ከሀገር መውጣት ነበረብኝ፡፡ ይሁንና በሕይወቴ የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ምርጫ መሳተፍ አለብኝ ብዬ መወሰኔ አስደሰተኝ፡፡ ለረዥም ዘመን ጠፍቶብኝ የነበረው ደስታ ተመልሶ ወደሰውነቴ ሲገባ ታወቀኝ፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ ላገኘውና በቃላት ልገልጸው የማልችለውን ስሜት አገኘሁ፡፡ ይህ ስሜት ምን እንደሚመስል ማወቅ በራሱ ፀጋ ነው ብዬ አልኩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለብዙ ዘመናት የታገለለት መብቱ ሊከበር ይሆን ብዬ እጅግ ደስ አለኝ፡፡ እኔ ያየሁትን እና የሰማሁትን ከጎኔ ያየሁትንና የሰሙትን ከ30 ዓመት በፊት ከጎኔ የነበሩ ጓደኞቼ ምነው በነበሩ ብዬ ተፀፀትኩ፡፡ የወደቁለት ዓላማቸው መሳካቱን ምነው ባዩ  ብዬ አሰብኩ፡፡ በዚህ መሐል ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ለፍርድ ቀርበው የሞት ፍርድ ሲፈረድባቸው ተናገሩ የተባለው ቃል ትዝ አለኝ፡፡ ‹የዘራችሁት ፍሬ ማሸት ጀምሯል›  ብለው ያሉት፡፡
 
ሕዝቡ እጅግ ሰላማዊ ከመሆኑ የተነሳ ለጥበቃ የተመደቡት ፖሊሶች ደከማቸው መሰለኝ ቁጭ አሉ፡፡ ወደሰልፈኛው ብዙም ትኩረት አያደርጉም ነበር፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ አንዳንድ ወጣቶች ሰልፍ ጥሰው ወደፊት ሲሄዱ በዓይናቸው ይከታተሏቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ከቤተሰቦቻቸውጋ ከተወያዩ በኋላ ወደነበሩበት ይመለሳሉ፡፡ ሥራዬ ብዬ ወጣቶቹን ስከታተል ያልተማሩ እናቶቻቸውን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው ለማሳሰብና ለማስረዳት ነበር የሚመጡት፡፡ ወጣቶቹ ሥራቸውን ካከናወኑ በኋላ ምልስ ይላሉ፡፡ ወጣቶቹ ለቤተሰባቸው የማስረዳት ኃላፊነት ሊወስዱ የቻሉት በምርጫው ወቅት ገዢው ፓርቲ ያልተማሩ ሰዎችን ሊያጭበረብር ይችላልና ጥንቃቄ አድርጉ የሚል ማስታወቂያ ለተቃዋሚ ኃይሉ በተደጋጋሚ ስለተሰጠ ሊሆን ይችላል፡፡
 
ግንቦት 7/1997 -  25,605,851 የሚሆን ሕዝብ በመራጭነት እጅግ በርካታ የሚሆን ደግሞ በተባባሪነትና በደጋፊነት ሲፍነቀነቅ ዋለ፡፡ ግንቦት ሰባት አንድ ነገር ይዛ ትመጣ ይመስል ሰው ደስታ በደስታ ሆነ፡፡ ሕዝቡ ግንቦት ሰባት የነገ ብርሃንን አብሳሪና በጫንቃው ተሸክሞ ከሚዞረው ችግር የምታላቅቀው ቀን አድርጎ ነበር የተመለከታት፡፡ በጥቅሉ ግንቦት ሰባት በሚሊዮኖች የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሠርግ ታዳሚ ሆኖ የዋለበት ቀን ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
 
ግንቦት 7 በቁምነገሯ ብቻ ሳይሆን ብዙ ገጠመኞችና ቀልዶች የተስተዋሉባት ቀንም ነበረች፡፡ ብዙዎቹ ገጠመኞች ስለምርጫው ሥነስርዓት ኅብረተሰቡ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያላቸው ግንዛቤ ዝቅ ያለ በመሆኑ ምክንያት የተፈጠሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ገጠመኞች አንድ ሰሞን አነጋጋሪ በመሆናቸው በግል ጋዜጦች ጭምር ሲወጡ ከርመዋል፡፡ በየትኛው ጋዜጣ ላይ እንደሆነ አላስታውስም፡፡ አንድ አዛውንት ሰልፈኛ ወደቆመበት ይሄዱና ‹‹የቅንጅት ሰልፍ የትኛው ነው?›› ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም ሰው አንድ ቦታ ነበርና የተሰለፈው ሰው ሳቀ፤ አዛውንቷ በየዋሕነት ወይም ባለማወቅ ማንን ሊመርጡ እንዳሰቡ አሳወቁ፡፡ ሰውን ያሳቀው ይህ የአዛውንቷ የዋሕነት ነበር፡፡ በአንድ ቀበሌ ውስጥ ስለተፈፀመ አንድ ሁኔታ ሰው ሲያጫውተኝ አዛውንቷ ፎርሙ የሚሞላበት ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ከቆዩ በኋላ ከዚያ ወጥተው ሳጥኑ ወዳለበት ክፍል ይሄዳሉ፡፡ ዞር ዞር ብለው ሲመለከቱ አንድ ሳጥን ብቻ ነው የተቀመጠው፡፡ አንድ ሳጥን ብቻ ነው የተቀመጠው፡፡ አካባቢያቸውን ቢቀኙም ሌላ ሳጥን ሊያዩ አልቻሉም፡፡ ወደአስተባባሪዎቹ ዘወር ብለው ‹‹የቅንጅት ሳጥን የትኛው ነው?›› ይላሉ፡፡ ሰዎቹ ግራ ተጋብተው ዝም ብለው ‹‹እሱ ሳጥን ውስጥ ይጨምሩ›› ይሏቸዋል፤ ሴትየዋ ይናደዳሉ፡፡ ደግመው ‹‹የቅንጅትን ነው እኮ ያልኩህ!›› ይላሉ ወደአንደኛው ዘወር ብለው፣ ሰውዬው መልስ ቢሰጣቸውም ሊያምኑት አልቻሉም፤ ተቆጡ፡፡ ተናገሩት፡፡ ኋላ ላይ ሌሎች ባለሥልጣናት እና የተሰለፈው ሕዝብ ካረጋጋቸው በኋላ ካርዳቸውን ሳጥን ውስጥ ከትተው ሄዱ፡፡
 
ከላይ የዘረዘርኩት የእኔ ገጠመኝ እና በአንድ የምርጫ ቀጠና የታዘብኩት የሕዝቡ ተሳትፎ በመላ ሀገሪቱ ሁሉ ተፈፅሟል፡፡ የሕዝቡ ትዕግስት ድንበር አልነበረውም፡፡ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ችግር ያልነበረ ሲሆን ችግር የተፈጠረባቸው አንዳንድ ቦታዎችም አልጠፉም፡፡ አቶ ኃይሉ ሻወል ‹‹የአዲስ አበባ ምርጫ እየተጭበረበረ ነው›› በማለት ሒደቱ ሳይጠናቀቅ መግለጫ ቢሰጡም ምርጫ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ‹‹ከበድ ያሉ ሕገወጥ አሠራሮች የታዩት በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲሆን መታወቂያ ያለማየትና ለምርጫ ያልደረሱ ወጣቶች ሲመርጡ ተስተውለዋል፡፡›› ይላል በታዛቢነት የተሳተፈው የካርተር ማዕከል፡፡ እንደካርተር ማዕከል በምርጫ ቀንም ሆነ ከዚያ በኋላ የማስፈራራት እና የማስደንገጥ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ የምርጫ ሳጥኖች ያለአግባቡ ከቦታቸው ተነስተዋል፤ ወይም ዋስትና ባለው መንገድ አልተቆለፉም፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች በምርጫ ጣቢያዎች እንዳይገኙ ወይም በቆጠራው ላይ እንዳይኖሩ ተደርጓል፡፡
 
በአጠቃላይ የግንቦት 7/1997 ሕብረ-ብሔራዊ ምርጫ በኢሕአዴግ የ14 ዓመት አገዛዝ እና ይከተላቸው በነበራቸው ፖሊሲዎች ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ያደረጉበት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያደረጉበት እውነተኛ ምርጫ ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment