Thursday, May 30, 2013

“አፍንጫ ሲመታ፥ ዓይን አያገባውም”!


አዎ! ዛሬ ዛሬ አፍንጫ ሲመታ ዓይን አያለቅስም፡፡ አፍንጫ ሲመታ አፍንጫ ብቻ ነው የተመታው፡፡ የአፍንጫ መመታት ለዓይን ጉዳዩ አይደለም፡፡ አንተ ቤት ሲንኳኳም እኔ ቤት አይሰማም፡፡ እኔ ጋር የሚሰማ እኔ ጋር የተንኳኳ እንደሆን ብቻ ነው፡፡ ባለቤት ሰጮህ ጎረቤት አይሰማም፡፡ ጩኸቱ ጩኸት ብቻ ነው፡፡ እሪ በከንቱ! አዎ ይህ ዓይነት ዝመት የሕዝባችን እውነት እየሆነ መጥቷል፡፡ በየጥጋጥጉ ለራስ ብቻ የመሮጥ ግዴለሽነትና ምን አገባኝ ባይነት መንፈስ አድፍጧል፡፡ አንዳንድ ዘመን የራሱ መንፈስ አለው፡፡ ከሌከላው ጊዜ የተለየ በጎም ይሁን ጥሩ የራሱ ቀለም ይኖረዋል፡፡ ይሄንንም ዘመን አስተውሎ ለተመለከተ ሰው የኅብረተሰባችንን በምን አገባኝነትና በግድ የለሽነት ድቅድቅ ውስጥ እየተዋጡ መሄድ መለየት አይሳነውም፡፡ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉም በዚህ ምን አገባኝ መንፈስ ዋግ ተመትተዋል፡፡ ለትንሽ ትልቁ የኑሮ ፈሊጡ ሆኗል፡፡ እዚህ ጋር ይህንን መንፈስ አድምቆ ሊያሳይ የሚችለውን የኑረዲን ኢሳን ግጥም እንውጣው፡፡ 

     ‹‹እኔን ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ 
     እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደ በግ 
     የተሰኘ ግጥም ልጽፍ አሰብኩና 
     ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና፡፡››

ይህ ግጥም የዚህ ዘመን ስዕል ነው ፡፡ የግጥሙ ተናጋሪ ሕዝቡን ቀፍድዶ የያዘውን ሕፀጽ ለመተቸት ነበር አነሳሱ ነገር ግን በምን አገባኝነት ባይነቱ ስፋትና ጥልቀት የተነሳ እሱንም እዛ መንፈስ ውስጥ ዳግም ሲቀላቀል እና ተደላድሎ ሲቀመጥ እናየዋለን፡፡ 

ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ መተጋገዝ መተያየት አለሁ ባይነት---- እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አብረው የሚነሱ እሴቶች ነበሩ፡፡ ደቦ፣ ጂጊ፣ ወንፈል፣ የሚባሉ በኅብረት የመተጋገዝና የመሥራት ማኅበራዊ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዛሬ እነኚህ ምን ደረጃ ላይ ላይ ናቸው? ምን ያህል እድሮች ሰው ሲሞት ከመቅበር የዘለለ ሥራ ይሠራሉ? ምን ያህሉ አጠገባቸው በቁም ለሞተው ይገዳቸዋል - ግለሰቦችስ ቢሆኑ "የያዙትን አንጠልጥሎ ያልቻሉትን ጥሎ" ከማለፍ ውጪ እርስ በእርስ ይተያያሉ? የያዙትን ይዘው ለማለፍ ሲሞክሩ የጣሉትን ዞሬው ያያሉ --- ዝቅ ብለው ያነሳሉ? ይሄን የሚያደርጉ የሉም እያልኩ አይደለም! ብዙው ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ሰፊው ክፍል በምን አገባኝ ባይነቱና በግድየለሽነት መንፈስ የተዋጠ ነው፡፡ ነገ ያሉትን ጥቂቶች ምን አገባኝ አስብሎ ስላለማስቀመጡ እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ማኅበራዊነት፣ አብሮነት፣መረዳዳት ችግር መካፈል --- ወደ መቃብር እየተጓዙ ያሉ ያለፈው ዘመን ዘይቤዎች ወደ መሆን ደርሰዋል፡፡ ----- የራሳችንን ቆሻሻ ማራቃችን እንጂ ሌላውን ማቆሸሻችንን ከቁብ አንቆጥረውም፡፡ የኛ መቆም እንጂ የሌላው መውደቅ ግድ አይሰጠንም፡፡ በድጋፋችን መቆም የሚችሉ ብዙዎች እያሉ እጃችንን ነፍገናቸዋል፡፡ በኅብረት ያልቆምንባት የመጀመርያዋ ቅጽበት፤ ያልተጋገዝንበት የመጀመርያዋ ሰዐት የስብራታችንና የውድቀታችን አዋጅ መሆኗን አርቆ ማየት ተስኖናል፡፡ 

“ነግ በኔ” ነው…

በአንድ ወቅት፣ ሦስት በሬዎች ከለምለም መስክ ላይ ሳር ይግጣሉ፡፡ በመሀል አንበሳ ወደነሱ መጣ፡፡ የአንበሳውን መምጣት ሲያዩ እራሳቸውን ለማዳን አጠገብ ለአጠገብ በመቆም እራሳቸውን ለመከላከል ተዘጋጁ፡፡ አንበሳው ሁለቱን በሬዎች እንዲህ አላቸው" እንድትበሉ ሚያደርጋችሁ ቀዩ በሬ ነውና እሱን አሳልፋችሁ ስጡኝ እናንተን አልነካችሁም" አላቸው፡፡ ተስማሙ፡፡ አንበሳው ቀዩን በሬ ወሰደ፡፡ እንዲሁ በሁለተኛው ቀን ተመልሶ መጣ፡፡ ሁለቱ በሬዎች እራሳቸውን ለመከላከል ቀንዳቸውን አሹለው ጎን ለጎን ቆሙ፡፡ አንበሳ "ነጩን በሬ አሳልፈህ ከሰጠኸኝ አንተን አልነካም" አለው፣ ለጥቁሩ በሬ፡፡ ተስማማ፡፡ ነጩን በሬ ወሰደው፡፡ በሦስተኛው ቀን ጥቁሩ በሬ አገር አማን ብሎ ሳር ሲግጥ አንበሳው መጣ፡፡ በሬው በድንጋጤ የሚገባበት ጠፋው፡፡ "ሁለት ጓደኞቼን አሳልፌ ሰጥቼህ ልትበላኝ?" ጠየቀ በፍርሃት፡፡ አንበሳውም "አንተን የበላሁህ እኮ ቀዩን በሬ እንድወስድ በፈቀድክባት ቅጽበት ነው፡፡" ብሎ ቀጨም አድርጎ አጣጣመው፡፡ 

ለጊዜያዊ ራስን ማዳን ሌላውን ማጋፈጥ ነገ ራስን ማጥፋት ነው፡፡ የነገን ችግር ተካፋይ ለዛሬ ጊዜያዊ ችግር መገበር አይወጡት ችግር በገጠመ ጊዜ ችግር ተካፋይን ማጣት ነው፡፡ በምን አገባኝና በግድለሽነት ውስጥ ያለው ትልቁ ትርፍ ይኸው ነው፡፡ አንገትን እንደሰጎን አሸዋ ውስጥ መቅበር አያዋጣም፡፡ መሰበራችን ከራስ ለራስ በላይ አሻግሮ ማየት በተሳነን ቅጽበት ነው፡፡ 

መንግሥት ስለዜጎቹ ግድ የለውም፡፡ ሲነኩት ለመኮርኮም የሚሮጥበትን ያህል ፍጥነት ዜጎቹ ሲቸገሩ ለመድረስ ጊዜ የለውም፡፡ የሕዝቡን ጩኸት ለመስማት ጊዜ ያለው አይመስልም፡፡ አሁን አሁን እንደውም ከነጻው ፕሬስ ነጻ የሆነች ሀገር ለመፍጠር የሚፈልግ ይመስላል፡፡ ለምን ለሕዝቡ ለቅሶ ግድ የለውማ! የግል ሚዲያዎች የሕዝቡን ብሶት ከማሰማት በላይ ምን ፋይዳ አላቸው? በማን አፍንጫ መመታት የማን ዓይን ያለቅሳል? እስከመቼ "ሁለትም ሦስትም ሆናችሁ በስሜ ስትሰበሰቡ ብቻ በመሐከላችሁ እገኛለሁ" እያለ እንደሚዘልቅ መልስ የለም፡፡ የሚቃወሙትን ከሚደግፉት ዕኩል በአንድ ዓይን የሚያይበት፣ ስለእነሱ ይገደኛል የሚልበት ቀን ይናፍቃል፡፡ ግለሰቦች ስለሀገር ግድ የላቸውም፡፡ ከቤት ውስጥ ልጅ ያገባኛል ቢል "አንተ ምን አገባህ አርፈህ ተቀመጥ" እያሉ ቤተሰቦቹ የመንፈሳቸው እስረኛ ያደርጉታል፡፡ "ጎመን በጤና" ይነግሩታል፡፡ "ፈሪ የእናቱ ልጅ ነው" ያሰርጹበታል፡፡ "ከራስ በላይ ንፋስ፣ ንፋስ" ሲሉ ያጠምቁታል፡፡ እሱም የምን አገባኛቸው አቀንቃኝ ይሆናል፡፡ ጨለማውን አብሮአቸው ብርሃን ይላል፡፡ ነጋዴው የሸማቹ ጩኸት አይሰማውም፡፡ አከራዩ የተከራዩ እሮሮ አይቆረቁረውም፡፡ ነግ በኔ የለም፡፡ ኅብረት የለም፡፡ ኅብረት የሌለው ጩኸት ተራ የድምፅ ብክነት መሆኑን መገንዘብ አቅቶናል፡፡ መንግሥት በራሱ ሚዲያዎች ላይ ከዕውቀትም ሆነ ከጋዜጠኝነት ስነምግባር የፀ ጋዜጠኞች በሚያቀርቧቸው ፕሮግራሞች የሚፈጠረው ማኅበራዊ ቀውስ አያሳስበውም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን ባዮች የምርጫ ሰሞን ብቅ ብለው ከመጥፋት ውጪ እርስበርሳቸው እንኳን ኅብረት ኖሯቸው አያውቅም፡፡ የተንሸዋረረ ፖለቲካቸውን ከማውራት አልፈው ዝቅ ብለው ሕዝቡን አይመለከቱም፡፡ ለሕዝባችን ይላሉ እንጂ ሕዝቡን በቅጡ አያውቁትም፡፡ ጩኸቱን አይጮሁለትም፡፡ የራሱን ጩኸት እራሱ ይጩህ ይመስላል! በማን አፍንጫ መመታት የማን ዓይን ያለቅሳል?

የምናገባኝ መንፈስ የሰፈነበት ሕዝብ ታላላቅ ሰዎች አይኖሩትም፡፡ የታላላቅ ሰዎች ታላቅ መንገድ ለሌሎች ግድ ማለት ነው፡፡ ለራስ ብቻ ኑሮ ለራስ መሞት ደመነፍሳዊ የእንስሳት ባሕሪ እንጂ ሰብኣዊ አይደለም፡፡ አንስታይን "ትክክለኛው ሕይወት ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የኖርነው ነው፡፡ አልያ ግን ኖርን አይባልም" የሚል እምነት ነበረው፡፡ የታላቅነቱም ሚስጢር ይሄው ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ እየወረረን ባለው ለራስ ብቻ ኑሮ ለቁሳዊ ነገሮች ተቅበዝብዞ የማለፍ አባዜ በአንድ ኮንዶሚንየም (የጋራ ቤት) ውስጥ አንድ ግድግዳ እየተጋሩ በዓይን የማይተዋወቁ ሶዎችን እስከመታዘብ አድርሶናል፡፡ ይህን የተረዱ የቀን ሌቦች የተዘጋ ቤት ከፍተው እየገቡ የቤት እቃ ጭነው እስከ መሄድ ደርሰዋል፡፡ ሰው ቁሳዊ ብቻ አይደለም መንፈሳዊም ነው፡፡ ስጋዊ ምቾት ሁሉ መንፈሳዊ እርካታን አያተርፍም፡፡ የዚህ ሁሉ ግድየለሽነታችን ምንጩ ቁሳዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ የብዙ አሜሪካውያን ሕይወት እንዲህ ነው፡፡ መሮጥመሮጥብቻ ለራስ ጊዜ የሌለበት! ሩጫ፣ ነገ አዲስ ቴሌቪዢን፣ አዲስ መኪና፣ አዲስ ኮምፒውተር፣ ለመግዛት መሮጥመሮጥሞት! መሥራት መልካም ነው፡፡ ሀብትም መልካም ነው፡፡ እዛ ውስጥ ጠፍቶ መቅረት ግን የሰውን ልጅ መንፈሳዊነት አድቅቆ "ለቁስ ስለቁስ" የሚኖር እንስሳ ያደርገዋል፡፡ 

አዎ! ያገባኛል ባይነታችን እየሞተ ነው፡፡ አንዳንዴ እኔ ያገባኛል ማለት "ሌላው አያገባውም" ማለት የሚመስላቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህም ቢሆን ምን ያገባኛል ከሚለው አስተሳሰብ ያልተለየ ጠማማ ዕይታ ነው፡፡ በተለይ መሪዎቻችን የዚህ ስሜት ተጠቂዎች ናቸው፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ "ኢትዮጵያ ያለ እኔ ምንም አይደለችም፡፡ ዕድሏ ከእኔ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እኔ ነኝ የማደርሳት፡፡ ካለኔ ትኖራለች ብለህ አታስብ፡፡" እስከማለት መድረሳቸው ኦቶባዮግራፊ (ሕይወቴ ታሪክ) በሚለው የተክለ ሀዋርያት ተክለ ማርያም መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶአል፡፡ መንግሥቱ /ማርያምም ቢሆን "ከእኔ በላይ ሀገር ወዳድ" የሚል ነበር፡፡ 

ዛሬም ቢሆን ኢሕአዴግ "ከኢሕአዴግ ውጪ አማራጭ የለም" እያለን ነው፡፡ የብዙኃኑን ከማልቀስ ውጪ ያልሆነ ሕይወት ወርዶ ያየ ይመስል! ኢትዮጵያዊ ኅብረት እየሞተ ነው፡፡ ወደ ነበር እያደገ ነው፡፡ የገዛ አፍንጫችን በተመታ ዓይናችን እንባ የለውም፡፡ ዓይናችን እስኪመታ እንጠብቃለን፡፡ መረን የለቀቀ ግላዊነታችን በዚሁ ከቀጠለ ማጣፊያው ያጠረ የከፋ ጦስ ነው ይዞብን የሚመጣው፡፡ ኅብረት በሌለበት ተሰባሪው ብዙ ነው፡፡ ኅብረት በሌለበት ወዳቂው እልፍ ነው፡፡ ኅብረት በሌለበት ጉዞ ሁሉ፥
    
    
    
    
    
ነው፡፡ ቁልቁለት ሲወርዱት ቀላል ነው፡፡ ዳግም ሊወጡት በፈለጉ ጊዜ ነው ክብደቱ!.... እናም በአያያዛችን ዘልቀን አንወጣውን ከፍታ በራሳችን ላይ ከምንፈጥር እንተያይ! በኅብረት እንቁም! ለአንተ አፍንጫን መመታት የእኔ ዓይን እንባ ይኑረው! የቤትህ መንኳኳት ለቤቴ ይሰማ! የጎረቤቴን ጩኸት ጆሮዬን ይስማው! እንዲሁም ጩኸቴ ላንተ ይሰማ!

1 comment:

 1. እኔ ምን አገባኝ ?
  “እኔ ምን ቸገረኝ
  ፀሐይ ብትወጣ ባትወጣ
  ታበራልኛለች የ—መላጣ”
  በሀገር ብቻ አደለም ሲቀለድ በፀሐይ
  ሁሉን በእየፊናው ችላ ማለቱን ሳይ
  ተጠያቂው ማነው? እየተብከነከንኩ
  ስሜቴ ቢነካም ኮራሁ ንፁህ እንደሆንኩ
  ውጪ ወጣሁና አልኩ ምን አገባኝ
  ባንዳ ዘር የለኝ ለሀገሬ መታረድ ቢላዋ አልሳልኩኝ
  ተው በለው!ይሄ ምንአገባኝ! ይሄ ምንቸገረኝ!
  አንዴ ካመለጠ እንዳማረ አይገኝ።
  ^^^^^^^^^^^^^^^^^

  ReplyDelete