Monday, December 24, 2012

የደሞዝ Vs. የጠብሽ* ሰሞን
አነጋገራችንን፣ አካሄዳችንን፣ አበላላችንን፣ አስተያየታችንን ባጠቃላይ የምናደርገውን ማንኛውም እንቅስቃሴ ላይ ቀጥጠኛ አስተዋፅኦ ካላቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛው በኪሳችን ያለው ገንዘብ ዋነኛው ነው፡፡ ገንዘብ ከምናገኝባቸው አንዱ መንገድ ደግሞ ተቀጥሮ መሥራትና ወር ሲያልቅ የሠራንበትን ክፍያ/ደሞዝ ማግኘት ይገኝበታል፡፡ አብዛኛው በከተማ አካባቢ የምንኖር በዚህ መስመር ውስጥ እንገኛለን፡፡

ደሞዝ ተቀብሎ ቀጣዩን የደሞዝ ቀን እንደ ምፅአት ቀን በጉጉት የማይጠብቅ ካለ ይህ ሰው ከደሞዙ ውጪ ሌላ ተጨማሪ ገቢ አለው ወይም አንድ ቀልድ ላይ እንደሰማሁት በአስማት ነው የሚኖረው ማለት ነው፡፡ ደሞዛችን እዛው እንዳለ ወይም በተወሰነ ጭማሪ… ብቻ ኑሮ ግን በብዙ እጥፍ ጨምሮ መኖር መቻላችን እውነትም አስማተኛ ያስብላል፡፡ እንደየደረጃው ይለያይ ይሆናል እንጂ አብዛኛው ደሞዝተኛ ደሞዝ ከተቀበለ በኋላ ካሉት የተወሰኑ ቀናት ውጪ ለመጪው የደሞዝ ቀን ስንት ቀን እንደቀረው በመቁጠር፤ ቀሪውን ጊዜ በብድር እንዴት እንደሚያሳልፍ በማውጠንጠን፤ የሰቀቀን ኑሮ መኖሩን የተለማመድነው ይመስላል፡፡

የደሞዝ ሰሞንና የጠብሽ ሰሞን እንደየሰው ይለያያል፡፡ በአብዛኛው ደሞዝ ከተቀበሉ ከ10-15ኛው ቀን በኋላ ሰሞነ ጠብሽ ይገባል፡፡ ደሞዝ የተቀበሉ እለትም ደሞዟ ብድር ብቻ ከፍላ የዕለቱለት ጠብሽ የሚጀምርበት አጋጣሚም አለ፡፡ የበዓል ወቅቶች እና ጳጉሜ ወር “የጠብሽ” ወቅትን ከሚፋጥኑ/ከሚያረዝሙ ምክንያቶች ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የጳጉሜ ወር ግን ለምን ደሞዝ እንደሌላት ሁሌም ይገርመኛል፡፡ በዛ ላይ የአዲስ ዓመት ወጪ ተጨምሮበት አስቡት፡፡


የደሞዝ ሰሞን 1

የደሞዝ ሰሞንን አስታከው የሚመጡ ወጪዎች ብዛታቸው አይጣል ነው፡፡ በመሥሪያ ቤት ለተለያዩ ጉዳዮች የሚሰበሰቡ መዋጮዎች፣ በየመሥሪያ ቤቱ እና ካፌው እየዞሩ እርዳታ የሚጠይቁ እና  የመንገድ ላይ ለማኞች የሚበዙት በዚህ በደሞዝ ወቅት ነው፡፡ መንገድ ላይ የተለያዩ ዕቃዎችን ለሽያጭ ይዘው የሚወጡ ነጋዴዎችም ከሌላው ቀን በተለየ መንገዱን ሞልተው የምናያቸውን ደሞዝተኛን የሚያባብል እና የሚያግባባ ቃላት በመጠቀም ሸቀጦቻቸውን እንድንገዛ ሲታትሩ የሚታዩት በዚሁ በደሞዝ ወቅት  ነው፡፡ እኛም አዎንታዊ ምላሻችንን አንነፍጋቸውም፡፡

የደሞዝ ሰሞን 2

ከቤተሰብ፣ ጓደኛ እና በአካባቢያችን ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ይጠብቃል፡፡ ሰላምተኞች፣ ደውሎ ጠያቂ፣ አስታዋሽ እና እንገናኝ ባዮች እና  አሰባሳቢዎች እኛ ነን፡፡ ከፋይ ወይም ከፋይ ለመሆን ልባዊ የሆነ ተነሳሽነት እናሳያለን፡፡ ሲያወሩን በጥሞና እናዳምጣለን (የተሰበሰበ ቀልብ ይኖረናል)፡፡ ድንገት የሚያውቁት ሰው ካለ በማለት አካባቢን እያስተዋሉ መሄድ፡፡ (ምክንያቱም ገንዘብ በኪስ አለ፤ ሻይ ቡና እንበል ቢባሉ ቢያንስ ወጪን ተጋርቶ ለመክፈል ቢበዛ ደግሞ ለመጋበዝ ይችላሉ፡፡)

የደሞዝ ሰሞን 3

የሌለን ነገር ግን ሊኖረን ይገባል የምንለው ነገር ይበዛል፡፡ በተለይ ልብስ፣ ጫማ፣ መጽሐፍ፣ የቤት ቁሳቁስ…እና የመሳሰሉት ከዝርዝራችን ውስጥ የመካተት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በመንገዳችን ያገኘነው መገበያያ ቦታ ወይም ሥራዬ ብለን እገበያው ቦታ በመሄድ የምንፈልገው ነገር እንዳለ እናያለን፡፡ እናማርጣለን፡፡ ልንገዛም ላንገዛም እንችላለን ነገር ግን ለማየትም እንኳን ቢሆን የምንሄደው የደሞዝ ሰሞን ነው፡፡ ይህ አምሮታችን የበዛ ከሆነና ያማረንን ሁሉ የምንገዛ ከሆነ የጠብሽ ሰሞንን ያለጊዜው እንዲመጣ ያፋጥናል፡፡

የደሞዝ ሰሞን 4

ለቀን ወጪያችን መጠንቀቅ አይታይብንም፡፡ የእግር መንገድ እንጠላለን፡፡ አውቶብስ፣ ሃይገር ባስና ሌሎች ታሪፋቸው ዝቅተኛ የሆኑ ትራንስፖርቶችን አንጠቀምም፡፡ የምንመገብበት ምግብ ቤት ከሌላው ቀን ደረጃው ከፍ ያለ ይሆናል፤ ምሳ ከቤት ቋጥሮ መምጣት ይረሳና የምግብ ቤቶች ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡  

የደሞዝ ሰሞን --ሌሎች

በየሳምንቱ የሚወጡ ትኩረታችን የሚስቡ ጋዜጦችን እና መፅሄቶችን ገዝቶ ማንበብ፡፡ የሚያዝናንን ነገር ለምሳሌ እንደ ፊልም እና ቲያትር ማዘውተር፡፡ መጠጥ፣ ሲጋራ፣ ጫት እና የመሳሰሉ ሱሶችን በምርጫችን ማስተናገድ፡፡ እራስን ማዝናናት፡፡ ‹‹ቺክ›› ለመጥበስ ወይም ፍቅረኛን ለማግኘት ማቀድ እና ተግባራዊ ማድረግ፡፡ በዚሁ ወደጠብሽ ሰሞን እንሸጋገር…

የጠብሽ ሰሞን 1

ደሞዝተኛ ደሞዙን ጨርሶ ቀጣዩ ደሞዙ እስከሚደርስ ያለውን ጊዜ ለማሳለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይጠበቅበታል፡፡ ከዛ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ተበድሮ ያን የጠብሽ ጊዜ በቁጠባና በማብቃቃት ጥበብ ማሳለፍ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ደሞዝተኛ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አበዳሪዎች እንዲኖሩት ከሚሠራው ሥራ ባልተናነሰ ተግቶ መሥራት አለበት፡፡ አበዳሪዎች ቋሚ ወይም የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መ/ቤቱ የገንዘብ ሰብሳቢ ካለውና ገንዘብ ሰብሳቢ የሆነው ሰው ወይም ጓደኛ ከሆኑ  ብዙም ሳይጨናነቁ ብድር በቀላል የማግኘት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡  ‹አበዳሪ ሲያበድር የሰጠ ይመስለዋል› የምትለዋ አባባልም በተበዳሪ የተፈጠረችና በጠብሽ ወቅት በአበዳሪና ተበዳሪ ግንኙነት ተደጋግማ የምትጠቀስ ናት፡፡

የጠብሽ ሰሞን 2

ከጓደኛ ጋር ያለንን ግንኙነት እንቀንሳለን፣ ለወሳኝ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ስልክ አለመደወልን እንመርጣለን ወይም ሚስድ ኮል እናደርጋለን፣ ጓደኞችን ለማግኘት ብዙም ደስተኞች አንሆንም፣ ከማንኛውም ሰው ጋር ባንገናኝ እንመርጣለን፣ ብዙ ጊዜ ስልካችንን ልናጠፋ እንችላለን፣ ሰዎች ሲያወሩን ቀልባችንን ሰብስበን አናዳምጥም፣ በራስ የመተማመን መንፈሳችን ይቀንሳል፡፡

የጠብሽ ሰሞን 3

በጣም አስቸኳይ እና በእለቱ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር የምንገዛው አዲስ ነገር አይኖርም፡፡ አዲስ የሚገዙ ነገሮችን አይናችን እንዳያይ መከልከል ባንችልም ለአእምሮአችን ግን ያየነው አዲስ ነገር እንዴት እንደማያስፈልገን፤ ባለን ነገር መቆየት እንደምንችል፣ ከለው ሰው ተውሰን መጠቀም እንደምንችል እና የመሳሰሉ ምክንያቶችን እንነግረዋለን፡፡

የጠብሽ ሰሞን 4

ወጪያችንን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ዋጋው ረከስ ያለ ቤት ተመርጦ መመገብ ይጀመራል፡፡ አውቶብስ፣ ሃይገር ባስና የመሳሰሉትን ዝቅተኛ ታሪፍ ያላቸውን የትራንስፖርት መንገዶችን እንጠቀማለን፡፡ የተወሰነ መንገድ በእግር ልንጓዝ እንችላለን፡፡ ምሳ ቋጥረን መምጣታችንን እንጀምራለን፡፡ እነዚህን ስናደርግ ግን ጠብሽ ሰሞን ላይ በመሆናችን እንዳልሆነ ለማሳወቅ የተለያዩ ምክንያቶችን ስንሰጥ ይሰማል፡፡ ለምሳሌ የምግብ ቤቱን፡- ‹ምግቡ እኮ ያው ነው ዋጋው ብቻ ነው፡፡ የዚ የዚ….›፡፡ የትራንስፖርቱን፡- ‹ከታክሲ እኮ ቀድሞ የሚደርሰው ባስ ነው፡፡ በዛ ላይ ቀጥታ ሰፈሬ ያደርሰኛል…›፡፡ በእግር መጓዛችንን ደግሞ ለጤንነት ወይም ክብደት ለመቀነስ ጥሩ ነው ብለን እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ምሳ ቋጥረን ስንመጣ ‹የሆቴል ቤት ምግብ እኮ ጥሩ አይደለም፡፡ በምን እንደሚሠሩት አይታወቅም፡፡ ምንም ቢሆን እቤት የተሠራ ይሻላል፡፡….› እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች እንሰጣለን እንጂ የተበደርናትን ብር አብቃቅተን እስከ ደሞዝ ለመድረስ የምናደርገው እንደሆነ አንናገርም፡፡

የጠብሽ ሰሞን--ሌሎች

ጋዜጣ እና መጽሔት ገዝተን እናነብ የነበርን ወደ ኪራይ እንገባለን፡፡  የገዛ ወይም የተከራየ ሰው ተውሰን ልናነብም እንችላለን፡፡ ፊልም እና ቲያትር ማየት አያምረንም፡፡ መዝናናት አይታሰብም፡፡ የሱስ ነገር ስለማይሆንልን ተጋባዥ የምንሆንበትን አጋጣሚ እናመቻቻለን፡፡ በተወሰነም ፍላጎታችንን እንገድባለን፡፡ ፍቅረኛን ለማግኘትና ‹‹ቺክ›› ለመጥበስ ይህን ወቅት አንመርጠውም፡፡

እነዚህን ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገሮችን እየሆንን እና እያደረግን፤ ሁለቱ ወቅቶች እየተፈራረቁ ሲገዙን ወሩ ያልቃል፡፡ በዚህ ተመሳሳይ ዑደትም ቀናት ወራትን፤ ወራት ዓመታትን እየሆኑ ጌዜዎች ያልፋሉ፡፡

በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ በሁለቱ ወቅቶች የሚኖረን አስተሳሰብ የተለያየ ነው፡፡ በተለይ የገንዘብ አወጣጥ መርሓችን በሁለቱ ወቅቶች ፍፁም አይገናኝም፡፡ የጠብሽ ሰሞን በምንከተለው የገንዘብ አወጣጥ ቀመር እየተመራን ሙሉ ወሩን ማሳለፍ ብንችል የት በደረስን ብዬ አስብና እሱን ለማሰብ ግን የጠብሽ ሰሞን ጭንቅላት እንደሚጠይቅ ትዝ ሲለኝ እተወዋለሁ፡፡ ልክ ይህን ጽሑፍ ለጻፈፍ የጠብሽ ሰሞን ጭንቅላት እንደጠየቀኝ ሁሉ ማለት ነው፡፡

ረጅም እድሜ ለአበዳሪዎቻችን!
-----
* ጠብሽ - በኢ-መደበኛ (‹‹የአራዳ››) አነጋገር ዘይቤ ባዶ ኪስ ወይም የችግር ሁኔታን ይገልጻል፡፡

No comments:

Post a Comment