Wednesday, December 12, 2012

የሰሞኑ የጦማሮች እፍታ


  በማሕሌት ፋንታሁን

የፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም ኦፕን ሳሎን ጦማር ‹ሱዛን ራይዝና ሶስቱ የአፍሪካ እርኩሶች[ Susan Rice and Africa’s Unholy Trinity]› በሚል ፅሁፋቸው በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሱዛን ራይዝ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች ጋር ለሁለት አስርት አመታት ስታሽቃብጥ እንደነበረ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ሶስቱ እርኩስ መሪዎች የተባሉትም የአምባሳደር ሱዛን ምርጫ የሆኑት--የሩዋዳው ፖልካ ጋሜ፣የኡጋዳው ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የኢትዮጵያው መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ በሶስቱ ሃገራት በለፉት ሃያ አመታት የነበራትን ታሪካዊ ግንኙነት በዝርዝር አሰቀምጠውታል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ 

 

‹ኢህአዴግ ህገመንግስቱን መቼ መቼ ነው የሚጠቀምበት… ለአመትባሉ ይሆንን!?› የሚለን ደግሞ የአቤቶኪቾው ጦማር ነው፡፡ በዚሁ ጦማሩ በዞን ዘጠኝ ኢ-መደበኛ የጦማሪያን ቡድን ስለተዘጋጀውና “ህገ መንግስቱ ይከበር” በሚል መፈክር ስላነገበው ዘመቻ፣ መድረክ ኢህአዴግ ሕገመንግስቱን በመጣሱ ሊከሰው መሆኑን እና ሌሎች ከህገመንግስቱ ጋር ተያያዥ ሆኑ ጉዳዮችን አስነብቦናል፡፡ ሲያሽሟጥጥም እንዲህ ብሏል፡፡ “መድረክ፤ ‹ኢህአዴግ ህገመንግስቱን ጥሷል› ብሎ ፍርድ ቤት ሊገትረው እንደሆነ ሰምተናል። ጥሩ ሀሳብ ነው። እስቲ ‹ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ› የሚለው ብሂል መቅረት እና አለመቅረቱንም በዛው “ቼክ” እናድርገው።” ሙሉውን ለማበብ እዚህ ይጫኑ፡፡ 

ዘ ሊትል ቴስ የተሰኘ ጦማር ‹ ትናንሽ መንግስታት ብሶቴ….› በሚለው ፅሁፉ ፀሃፊው የቀበሌ መታወቂያ ለማግኝት ወደ ቀበሌ ጎራ ባለበት ወቅት የታዘበውን ያካፈለን ሲሆን ብሔርን በተመለከተ ቀበሌዎች ያላቸውን አሰራር ተችቷል፡፡ ብሔርን በተመለከተም ጓደኛው ያጫተውንም ሲነግረንም እንዲህ ብሏል፡፡ “ከአመት በፊት ጓደኛዬ ስራ ለማግኘት ሲል ፎርም ያስሞሉት የነበሩ ሰዎች ብሔሩን እንዳስቀየሩት አጫውቶኛል፡፡ እሱ ምክንያቱ ደግሞ በጣም አስቂኝ ነበር፡፡ ወጥሮም ተከራክሮ ነበር ሁኔታው ግን የእንጀራ ጉዳይ ነበር እና ተቀብሎ ወጣ፡፡ ስራውንም አገኘ፡፡  ብሔር የቀየረበት ምክንያት ደግሞ ለእናንተ ብሔር የተመደበው ኮታ ስለሞላ  ስራውን ከፈለክ እንደዚህ ተብለህ መፃፍህ ግድ ነው፡፡ ተብሎ ነው፡፡” ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡     

ካፋ ፎር ፍሪደም የሚባለው ጦማር ደግሞ ‹በ2012 ዓለም አቀፍ የአገሮች የሙስና ሰንጠረዥ፤ የኢትዮጵያ ገጽታ በጨረፍታ› በሚል ርዕስ ዓለም አቀፉ የጸረ-ሙስና የአገራትን የመልካም አስተዳደር ይዞታ የሚከታተለው ተቋም Transparency International ዓመታዊውን የዓለም አገሮች የሙስና ደረጃ ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን ኢትዬጵያ ከ 177 ሃገራት 113ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን እና 2012ቱን ዓመታዊ የአሮች ገጽታ በመግቢያቸው የቃኙት  ካናዳዊቷ  የድርጅቱ ሊቀመንበር Labelle «ሙስና በከፋባቸው አገሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝም ያንኑ ያህል የከፋውን መስመር ይይዛል፤» ማለታቸውን በፅሁፉ ገልጧል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ

ከበደ ካሳ የተሰኘው ጦማር  ‹አዲስ ራዕይ › በሚል ርዕስ ስለ አዲስ ራዕይ መፅሄት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዞአል፡፡ “እዉነቱን  ለመናገር  የኢሕአዴግ  የንድፈ  ሃሳብ  መፅሄት  የሆነችዉ  አዲስ ራዕይ  መፅሄት  ዋና አዘጋጅ  ታላቁ  መሪ  መለስ  ዜናዊ  እንደነበር አላዉቅም ነበር፡፡ በርግጥ መለስ  ዜናዊ  በተለያዩ  መድረኮች ከሚያራምዳቸዉ  አቋሞች  ጋር  የሚመሳሰሉ  ፅሁፎችን በመፅሄቷ  ስመለከትና  በይዘቷና  በአቀራረቧ  ካላት  ብስለት  አንጻር  በመመዘን  ‘ሰዉየዉ’ ፅፏት ይሆንን  ብዬ  መጠርጠሬ  አልቀረም፡፡ ዋና  አዘጋጇ  መለስ መሆኑን  ርግጠኛ  መሆን የጀመርኩት  ግን  የዚህ  አመት  የመጀመሪያዋ  ልዩ  እትም  የገበያ ማስታወቂያ/commercial ad/ በኢትዮጵያ  ቴሌቪዥን  ሲነገር  ነዉ፡፡” ፅሁፉ ስለ አዲስ ራዕይ መፅሄት የፃፈውን ሙሉውን ለማግኘት እዚህ ላይ ተጫኑ፡፡


ይሔው ጦማር ‹እዉቅና እና እዉቀት፤ ዱባ እና ቅል› በሚል አርዕስት ሰሞኑን በኢቲቪ ተላልፎ በነበረውና ሴቶች በማስታወቂያ ላይ የሚጫወቱትን ሚና በሚል የመወያያ ርዕስ  ፕሮግራም ላይ የተሰማውን ሃሳብ በፅሁፉ አስፍሯል፡፡ “የሴቶችን ገላ ለምርት/አገልግሎት ማሻሻጫ መጠቀምም የማስታወቂያዎቻችን ችግር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በአስተዋዋቂዋ አማላይ ዉበት ተማርከን ምርቱን/አገልግሎቱን እንድንገዛ የሚፈልጉ ነገር ግን ስለሸቀጡ የማይነግሩን አሉ ነዉ ያለዉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ፡፡ እነዚህ ቅሬታ ያዘሉ አስተያየቶች የተሰነዘሩባቸዉ የማስታወቂያ ባለሙያወችና አስተዋዋቂዎች ታዲያ የየራሳቸዉን ምላሽ ይዘዉ ቀርበዋል፡፡ እኔን የሳቡኝና ቅሬታዬን እንዳቀርብ የገፋፉኝ ታዲያ የተሰጡት መልሶች ናቸዉ፡፡” ብሎ ቅሬታዎቹንና የራሱን ሃሳብ የገለፀበትን ሙሉ ፅሁፍ እዚህ ላይ ተገኙታላችሁ፡፡

‹የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች መጨመር ሕገ መንግሥታዊነት?????›  የሚል  ፅሁፍ ያስነበበን የሚኒሊክ ሳልሳ ጦማር ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ስለ ሦስት ም/ጠ/ሚኒስቴር ሹመትና ሕገመንግስታዊነት፤ ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚናገረው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ አንቀጽ 75 በመጥስ ስለ ወቅታዊውን ጉዳይ ዳሷል፡፡ ሙሉውን ለማግኘት እዚህ ላይ ተጫኑ፡

 

ይሄው ጦማር  በኢትዮጵያ መንግስት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የኦነግ አባል  ሆነዋል  በሚል  በተከሰሱት  በቀለ  ገርባ፣ ኦልባና ለሊሳ፣ ወልቤካ ለሚን  ላይ  እና ሌሎች በአሸባሪነት ክስ በተመሰረተባቸው ሰዎች ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን ፅፏል፡፡  “1ኛ. አቶ በቀለ ገርባ – በ8 ዓመት እሥር 2ኛ. ኦልባና ለሊሳ – በ13 ዓመት እስር 3ኛ. ወልቤካ ለሚ – በ7 ዓመት እስር 4ኛ. አደም ቡሳ – በ3 ዓመት እስር፣ 5ኛ. ሀዋ ዋቆ – በ8 ዓመት፣ 6ኛ. መሀመድ ሙሉ- በ 10 ዓመት እስር 7ኛ. ደረጀ ከተማ – በ8 ዓመት እስር፣ 8ኛ. አዲሱ ሞክሬ – በ10 ዓመት እስር 9ኛ ገልገሎ ጉፋ – በ12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከሁለት እስከ አራት ዓመት ለሚደርስ  ጊዜም ህዝባዊ መብታቸው ፍርድ ቤቱ መሻሩም ታውቋል።” ሙሉውን እዚህ ላይ በመጫን ታገኙታላችሁ፡፡ 

 

በዚሁ በዞን ዘጠኝ ጦማር ደግሞ ባሳለፍነው ሳምንት አራት ጦማሮች የተፃፉ ሲሆን ከነዚ ውስጥ ሶስቱ ‹ሕገ መንግስቱ ይበር› በሚል ለሶስት ቀን የቆየው የበይነመረብ ዘመቻ ቀናት በተከታታይ ለንባብ የበቁ ናቸው፡፡

 

በዘመቻው የመጀመሪያ ቀን የወጣው  የበፍቃዱ ኃይሉ “ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ” የተሰኘው ፅሁፍ ሲሆን በሕገ መንግሥቱ የጠቅላይ ሚኒስትርን ተግባር የተጠቀሰባቸውን ቦታዎችና ተግባር ደብዳቤውን ለመፃፍ የተገደደበትን ምክንያት እንዲህ ያስረዳል፡፡ “አንቀጽ 74 ፥ ቁጥር 13 ላይ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል” ይላል፡፡ ትንሽ ከፍ ብሎ ደግሞ በቁጥር 8 ላይ “የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል፡ እናም እርስዎ በቅርቡ አመራሩን የተረከቡት መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የመቃወም፣ የመደራጀትና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደወንጀለኝነት እንዲፈሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እያደረገ በመሆኑ እና በውጤቱም ብዙ ንጹሐን ዜጎች በሠላማዊ ትግል ተስፋ እየቆረጡ እንዲሳደዱ፣ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ፣ “አሸባሪ” ድርጅቶችን እንዲቀላቀሉ እያስገደደ መሆኑን በመታዘቤ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ልጽፍልዎ ተገድጃለሁ፡፡” በማለት ተጣሱ የሚላቸውን አንቀፆች እና ነባራዊውን ሁኔታ በዝርዝር አከቷል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

በዘመቻው ሁለተኛ ቀን የተፃፈው ደግሞ የዘላለም ክብረት ‹ሕገ መንግስታዊነት› የተሰኘው ፅሁፍ ነው፡፡ የሕገመንግስት አስፈላጊነት እና ፅንሰሃሳብ፣ የሕገመንግስት ዓለማና ተግባር፣ ሕገመንግስት ያለሕገመንግስታዊነት የነበረበትን የንጉሡን ዘመንን እንዲሁም አሁንም ተመሳሳይ ችግር የሚታይበት ኢህአዴግ መንግስት እንዴት ሕገመንግስት እንደማይከበር እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችንም አካቷል፡፡ ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ 

በሶስተኛው እና በመጨረሻው የዘመቻ ቀን ‹ሰብኣዊ መብቶች፣ ሕገ-መንግሥቱ እና መንግሥት› የሚለው ፅሁፏን የስነበበችን ሶሊያና ሽመልስ ናት፡፡ ሶሊያና በዚህ ፅሁፏ ሰብዓዊ መብትን የሚመለከቱ አንቀፆች በሕገመንግስቱ መካተታቸውን ነገር ግን ተግባር ላይ የመዋል ችግር እንዳለባቸው፣ የተናቁ አንቀፆችን ዝርዝር እና የተጣሱበትን ሁኔታዎች እንዲሁም መፍትሔ ያለችውን ያስቀመጠችበት ሲሆን ሙሉው እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

ሌላው በዚሁ የዞን ዘጠኝ ጦማር ትላንት የወጣው በፍቃዱ ‹ስለለውጥ› በሚል በተከታታይ እያቀረበ ያለውን ፅሁፍ ሲሆን በዚህኛው ክፍል ደግሞ “ስለለውጥ፤ አብዮት ወይስ አዝጋሚ-ለውጥ?” ይለናል፡፡ በፍቃዱ በዚህ ፅሁፉ ስለ አብዮትና አዝጋሚ ለውጥ ምንነት፣ ለውጥ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በማሕበራዊ፣ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶችም ላይ እንደሚያስፈልግ፣ የፈረንሳይ አብዬቶች እና በኢትዬጵያ ስለታዩ አብዮቶች እንዲሁም የአብዮትና የአዝጋሚ ለውጥ ባህሪያትን በዝርዝር የፃፈበት ሲሆን ሙሉውን እዚህ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡

 

መልካም ንባብ! 

 



 

 

 

 






ዘ ሊትል

ብሶቴ

ዘ ሊትል

 

 

 

 

 

No comments:

Post a Comment