Monday, December 31, 2012

ያጣናቸው ሰዎች ናፍቆት

በፍቃዱ ኃይሉ

ያጣናቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፤ ግን ቀስ በቀስ ስላጣናቸው አጠፋፋቸው እየቆየ ብቻ ነው የሚገባን፡፡ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ኢሕአዴግ የመሪነቱን ሥልጣን ሲረከብ ብዙ ደርግ ያሰደዳቸው ምሁራንና ባለሀብቶች በሙሉ ተስፋ ወደአገራቸው ተመልሰው ነበር፡፡ ከነዚያ ባለሀብቶች ውስጥ የቀድሞ አለቃዬ ይገኝበታል፤ የሶፍትዌር ኢንጂነሩ፣ የቀድሞ አለቃዬ በዐሥራ ምናምን ዓመት የካናዳ ቆይታው ያጠራቀማትን 4 ሚሊዮን ብር ጨብጦ መጥቶ የሶፍትዌር ኩባንያ መሠረተ… አሁን ኩባንያው ከስሮ በመሟሟት ላይ ሲሆን፤ አለቃዬም በመዓት ዕዳ ተይዟል፤ በሶፍትዌር አምራች ኩባንያነት የተሳካለትን ኢትዮጵያዊ ኩባንያ እና የማንነት ጥናት ብታካሂዱ ጥየቄውም መልሱም ይገባችኋል - የኢሕአዴግ ሰዎች ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ አንድዬነት (economic monopoly) ራዕይ እዚህ ይጀምራል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደጉድ ሲወራለት የነበረው እና በአገራችን የመጀመሪያው የቤት መኪና መገጣጠሚያ የሆነው ሆላንድ ካር ኩባንያ ባለቤት ቤተሰቡን ይዞ ወደቀድሞ የስደት አገሩ ሆላንድ ኮበለለ፡፡ (በነገራችን ላይ መስፍን ኢንዱስትረያል ኢንጂነሪንግ የሚያመርታቸውን ‹‹አዲስ›› በሚል ስም የሚጠሩ አውቶሞቢሎች የትግራይ ክልል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች እንዲሸምቱ መደረጉን ሰምታችኋል?) ዶ/ር ፍስሐ እሸቴንም ከእነዚህ ተርታ አታጡትም፤ የመጀመሪያውን የግል ከፍተኛ ተቋም (እርሳቸው ‹‹ልጄ›› ነው የሚሉት) ለወግ ማዕረግ ካበቁ በኋላ፣ በአንድ ወቅት ‹‹ኢሕአዴግዎችን ‹ለምን እንደሆነ እንጃ› ግን እወዳቸዋለሁ፤›› ብለው በይፋ ለተናገሩት ባለሃብት ሸጠው፣ ኮበለሉ - ምክንያቴ ፖለቲካዊ ጫና ነው ብለዋል፡፡ በርካታ ምሁራን በቃኝ ብለው ወደመጡበት አገር ተመልሰው ሄዱ፡፡ (እዚህች’ጋ ነገሩን በዋዛ ለማፍታታት ያክል ‹‹ሊዮኔል ሜሲ ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ወይ ለደደቢት ተጫወት አሊያም አገርክን ለቀህ ተሰደድ ይባል ነበር›› የሚለውን የከተማ ቀልድ ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ቀልዱ ስደተኞቹን ፍስሐ ተገኝን እና ኤርሚያስ አማረን ሊያስናፍቃችሁ እንደሚችል አይጠፋኝም ሆኖም ቀልዱን አቁሜ ጽሑፉን መቀጠል አለብኝ፡፡)

ከተሰደዱበት የተመለሱት ብቻ አይደሉም መልሰው የሚወጡት፤ እዚሁ በዚሁ ተስፋ ቆርጠው የኮበለሉም ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ስላጣናቸው ሰዎች ናፍቆት ቁጭ ብዬ በዓይን እርግብግቢት አፍታ ያሰብኳቸው ሰዎች እንኳን ወደውስጥ የሚፈስ እንባ ዓይነት ቅሬታ ፈጥረውብኛል፡፡ ለፖለቲካውም፣ ለኢኮኖሚውም… ለሁሉም ስደት መንስኤው የፖለቲካው ሥርዓት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ መናፈቃችን ካልቀረ ፖለቲካው ውስጥ ተስፋ አስጥለውን የነበሩትን ሰዎች እስኪ እናስታውሳቸው፡፡

ብርቱኳን ሚዴቅሳ

ይህች ሴት… ለብዙዎች የሐቀኝነት እና የቆራጥነት ምሳሌ ነበረች፡፡ በወጣትነቷ የነጻ ፍርድቤት ናፍቆት ልቧን ያሸፈታት ይህች ፖለቲከኛ፤ በብሔር ተዋጽኦዋ የሁለት ታላላቅ ብሔሮች ድምር በመሆን በወቅቱ የፖለቲካ ዜማ አንድ ብቻ ሳይሆን ቅይጥ የመሆንን ስሜት እና አበሳ የምታመሰጥር፤ ለብልሹ ሥርዓት እምቢተኛነቷ በምሳሌነት የሚነሳ እና የማይረሳ ነው፡፡ ሴትነትን በሥርዓተ ጾታ ከተሰጠው ብያኔ ያስፈነገጠችው እና መታሰር እና ደግሞ መታሰር ለሚታመኑለት ‹‹ቃል›› እስከሆነ ድረስ ምንም እንዳልሆነ ያስመሰከረች ጀግና፤ ብዙዎች ባገራቸው ተስፋ እንዳይቆርጡ በማድረግ በሩጫ አደባባይ ሳይቀር የሚዘመርላት ሴት ነበረች፡፡ ይህችን ሴት ‹ነበረች› ያሰኛት ግን ይኼው ፖለቲካዊ ሥርዓታችን ነው፡፡ አስመርሮ አሰደዳት፣ አሰደድዶ ዝም አስባላት፡፡

ብርቱኳንን አጥተናታል የሚያሰኘን ለሁለተኛ ጊዜ ‹‹በይቅርታ›› ከተፈታች በኋላ፣ ከአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበርነቷ በፈቃደኝነት ከመልቀቋም ባሻገር፤ ለትምህርት ከተጓዘችበት አገረ አሜሪካም ቢሆን ጠንካራ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት ባለማሳየቷም እስካሁን ባለመመለሷም ነው፡፡ ቢሆንም ሌላው ቢቀር የዓለምን ጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ቀልብ በሳበው የኦባማ የ2008 መመረጥን አስመልክታ… “Yes We Can” በሚል ርዕስ በጋዜጣ ላይ ባሰፈረችው ጽሑፏ ላይ ያስነበበችን አጭር ሕልሟ ብቻ ብርቱኳንን ዘወትር እንድንናፍቃት ያስገድደናል፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

ዶክተሩ አንደበተ ርቱዕ ነው፡፡ አነጋገር ያውቃል - ግርማ ሞገሱ ይናፈቃል፡፡ የአደባባይ ምሁር ነው - የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶችን ማኅበር መስርቶ ከየትኛውም ማኅበር የበለጠ አቅም አጎናፅፎታል፤ ምን ዋጋ አለው - እሱ ሲተወው ማኅበሩም መልፈስፈስ ጀምሯል፡፡ ሀብት አለው - ግን የድሃን ሕመም እንደሚረዳ ያስታውቃል፤ ቤተሰቡን እና ጓዙን ጠቅልሎ  አዲስ አበባ የገባው ሙሉ ተስፋ አዝሎ ነበር፡፡ ‹‹ፖለቲከኝነት በኢትዮጵያ እንደሳት እንደሚፋጅ›› ቢናገርም መሥርቶት የነበረው ፓርቲ ግን በጥቂት ጊዜ ውስጥ በቅንጅት ታሪካዊውን ምርጫ 97 ወልዷል፡፡

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ቤተሰቡን ጠቅልሎ እንደመጣ፣ ቤተሰቡን ጠቅልሎ መልሶ ተሰዷል፡፡ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥርዓት ለመለወጥ ያስኬደኛል ባለው መንገድ ሳቢያም አሸባሪ ተብሎ የሞት ፍርድ ተበይኖበታል፡፡ ዶ/ር ብርሃኑን አጥተነዋል የሚያሰኘን በርግጥም የመረጠው መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ የነርሱ ይሁን አይሁን በቅጡ ያልተረጋገጠውን እና ‹‹እንደግፈዋለን›› ያለውን የሕዝባዊ ኃይል (ሠራዊት) ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ለሚታገል ሁሉ አልተዋጠለትም /ሐሳቡን እንደአማራጭ የሚደግፍ እንኳን እስካሁን አልገጠመኝም/፡፡ ይህም ማለት ‹‹ዶ/ር ብርሃኑ በመጨረሻ ሕዝቡ በማይደግፈው መንገድ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት እየሠራ ነው እንዴ?›› የሚያሰኝ ጥያቄ ላይ ጥሎታል፡፡ ሆኖም ‹የነፃነት ጎህ ሲቀድ› በሚል ርዕስ እስር ላይ ሆኖ በጻፈው መጽሐፉ እና ተስፋው ሁሌም እንድንናፍቀው እንገደዳለን፡፡

እነ ዐብይ ተክለማርያም

እነዐብይ ተክለማርያም አንድ አይደሉም፤ ብዙ ናቸው፡፡ በጋዜጠኝነት እና ጸሐፊነት ሙያቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ማኅበረሰባዊ መነቃቃት እና ተስፋን የፈጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ጸሐፊዎቹ በሕመምተኛው ፖለቲካዊ ሥርዓታችን ስጋት እና እንቅፋትነት ሲሰደዱ ቀስ በቀስ ተሳትፏቸውም እንዲከስም አድርጓቸዋል፡፡ ዐብይ ተክለማርያም የቀድሞዋ አዲስ ነገር ጋዜጣ ፊታአውራሪ ነበር ማለት ይቻላል፤ የትችትን ዋጋ ገኖ እንዲወጣ ያደረገ፣ በዕውቀት የታጨቁ፣ ራዕይ ያዘሉ አጫጭር እና ረዥም ጽሑፎችን አስነብቦን ዓለማዊም ሆነ አገራዊ ዕይታችንን ከፍ ካደረጉልን ጸሐፍት ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ እሱም በወጣበት እንዲቀር ተገዷል፡፡

በፖለቲካችን ሳንካ ከተሰደዱ እና ከሚናፈቁ ጋዜጠኞች መካከል እነ አርጋው አሽኔም የሚዘነጉ አልነበሩም፡፡ ይመራው የነበረውን ስኬታማ የአካባቢ ተቆርቋሪ ጋዜጠኞች ማኅበር በድንገት የተለያየው የመረጃ ምንጩን እንዲናገር በመገደዱ ነበር፡፡ ከተሰደዱ ጋዜጠኞች ውስጥ በአገራዊ ኩነቶች ላይ ከሞላ ጎደል አስተያየታቸውን በተቻለ ፍጥነት እየሰጡን፣ ርቀው እንዳልራቁ ያስመሰከሩት እነ አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው) እና መስፍን ነጋሽ በአንዳንድ ጽሑፎቹ ብሎም አሁን፣ አሁን ደግሞ እነዘሪሁን ተስፋዬ በአዲስ ታይምስ ጽሑፎቻቸው ነው፡፡

እንደዐቢይ ሁሉ እነታምራት ነገራ፣ እነግርማ ተስፋው እና ሌሎችም ብዙ ብዕራቸው የማይነጥፍ ጋዜጠኞች፣ ጸሐፊዎች እና ዝም አንልም ባይ ምሁራኖች… ሁሉም ቀስ በቀስ ከአገራዊ ጉዳይ ተሳትፋቸው ተቆራርጠዋል ወይም ከእኛ ዕይታ ተሰውረዋል፡፡… ነገር ግን በተለያየ ወቅት ፈጥረውት ስለነበረው መነቃቃታችን ሲባል መና’ፈቃቸው አይቀርም፡፡

ምን እነዚህ ብቻ?! የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም በመጠየቃቸው ‹‹ኦነግ›› የተባሉ፣ የሶማሊያን ሕዝብ መብት በመጠየቃቸው ‹‹ኦብነግ›› የተሰኙ፤ አለመሆናቸውን ለማስረዳት እንኳን ግዜ እና ዕድል አጥተው የኮበለሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡

… ያጣናቸው እና የምንናፍቃቸው በስም የዘርዘርናቸውን ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎችም ብዙ…እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ ነገር ግን ሆዳችን ይበልጥ የሚባባው ቀድሞ ላጣናቸው ብቻ ሳይሆን፥ እያጣናቸው ላሉት እና ገና ለምናጣቸውም ጭምር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment