Wednesday, December 5, 2012

ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

ጉዳዩ፡- ሕገ መንግሥቱ በመንግሥት እንዲከበር ስለመጠየቅ

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 74 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትርን ሥልጣን እና ተግባር ሲደነግግ፥ ቁጥር 13 ላይ “[ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ሕገ መንግሥቱን ያከብራል፣ ያስከብራል” ይላል፡፡ ትንሽ ከፍ ብሎ ደግሞ በቁጥር 8 ላይ “የመስተዳድሩን ሥራ አፈጻጸምና ብቃት ይቆጣጠራል፣ አስፈላጊ የሆኑ የእርምት እርምጃዎችን ይወስዳል” ይላል፡፡

እናም እርስዎ በቅርቡ አመራሩን የተረከቡት መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ሕገ መንግሥቱን በመጣስ የመቃወም፣ የመደራጀትና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እንደወንጀለኝነት እንዲፈሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እያደረገ በመሆኑ እና በውጤቱም ብዙ ንጹሐን ዜጎች በሠላማዊ ትግል ተስፋ እየቆረጡ እንዲሳደዱ፣ በፖለቲካው ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርጉ፣ “አሸባሪ” ድርጅቶችን እንዲቀላቀሉ እያስገደደ መሆኑን በመታዘቤ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ልጽፍልዎ ተገድጃለሁ፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ የኢሕአዴግ ብቻ ያልሆነችውን ያክል እርስዎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ መንበር ላይ እስካሉ ድረስ በእኩልነት እና በቅንነት የሚያገለግሉት የኢሕአዴግ ወዳጆችን ብቻ ሳይሆን የኢሕአዴግ ነቃፌዎችንም ጭምር እንደሆነ ይዘነጋዎታል ብዬ ስለማልገምት ላስታውሶት አልደፍርም፤ ነገር ግን በተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች የተተበተበች ድሀ አገር ውስጥ የሚኖር ገዢ ፓርቲ ከደጋፊዎቹ ይልቅ ተቃዋሚዎች ሊኖሩት እንደሚችል መገመት ጥልቅ ምርምር ማድረግ አይጠይቅም፡፡ ይህንን የምናገረው ሕዝብ ሆኜ በሕዝብ ውስጥ የሚነገረውንና የሕዝብን ብሶት እየኖርኩኝ በማየቴ ነው፡፡

ከላይ ከጠቀስኩት እውነት በሚጻረር መልኩ ግን ከላይ እስከታች ድረስ በተዘረጋው የመንግሥት ስርዓት ውስጥ በኃላፊነት የተመደቡ ባለሥልጣናት፣ አስፈጻሚዎች እና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በአገሪቱ ተቃዋሚ የሌለ እስከሚመስል ድረስ ከሰብኣዊ እስከ ቡድን መብቶችን በመጣስ እና በማፈራረስ በገዛ አገራችን የሁለተኛ ዜግነት ስሜት እንዲሰማን እያደረጉን ይገኛል፡፡ በግሌ መንግሥት እና ሹመኞቹ መብትን ለማፈን የሚያወጣውን ወጪ ሕገመንግሥቱን ለማክበር ቢያወጡት አገሪቱ እውነተኛ ለውጥ ታስመዘግባለች ብዬ አምናለሁ፡፡

የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፣

ሕገ መንግሥቱ በመንግሥት እየተጣሰ ነው ስል ያለምክንያት አለመሆኑን ጥቂት ምሳሌዎችን በመጥቀስ እንዳስረዳ ይፍቀዱልኝ፡-

 • አንቀጽ 10 (2) - “የዜጎች እና የሕዝቦች ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡”

እውነታው፡- ሕግ አስከባሪ ፖሊሶች የግለሰቦችን ሰብኣዊ መብት በአደባባይ ይጥሳሉ፣ ሰዎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ማኅበራዊ፣ ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚገቡበት አጋጣሚ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ነው፡፡

 • አንቀጽ 12 (1) - “የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት”

እውነታው፡- የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለየትኛውም የግል መገናኛ ብዙኃን በራቸውን ዘግተው ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች ላይ ሕዝቡ መልስ ከማግኘት ይልቅ በአሉባልታዎች ቅብብል እንዲደናበር ተጨማሪ እንቅፋት እየሆኑ ነው፡፡

 • አንቀጽ 20 (3) - “[የተከሰሱ ሰዎች] በፍርድ ሒደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ በምስክርነት እንዲቀርቡ ያለመገደድ መብት አላቸው”

እውነታው፡- በመንግሥት የሚተዳደሩት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እና ባለሥልጣናትም ጭምር፣ በተለያዩ ጊዜ ክስ የተመሰረተባቸውንም ያልተመሰረተባቸውንም ጋዜጠኞች እና ሌሎችም ተቃዋሚዎች ያውም ‹‹በሽብርተኝነት›› የመወንጀላቸው ነገር የማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ድራማ እየሆነ መጥቷል፡፡

 • አንቀጽ 21 (2) - “[የታሰሩ ሰዎች] ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት መሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው”

ውነታው፡-የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች የፈለጉትን ሰው ጠያቂ እንዳይኖረው፣ ወይም የሚጠይቁትን ሰዎች ማንነት የመገደብ ሥራ በገዛ ፍቃዳቸው በየጊዜው እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ እንደምሳሌም ከዚህ ቀደም ብርቱኳን ሚዴቅሳ በታሰረችበት ወቅት ጠያቂዎች እንዳይጎበኟት ሲከለከሉ በፍርድ ቤት ክስ መስርታ እና በፍርድ ቤቱ መብቷ ተፈቅዶ አልተከበረላትም፤ አሁንም የ18 ዓመት የእስር ፍርድ ላይ የሚገኘውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለመጠየቅ የሚችሉት ቤተሰቦቹ ብቻ እንዲሆኑ አላግባብ በማረሚያ ቤቱ ጥበቆች ተደርጓል፡፡

 • አንቀጽ 29 (2) - “ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ውስን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶቸን ያካትታል፡፡”

ውነታው፡- ይህ አንቀጽ በአሁኑ ሰዓት በገደል ጫፍ ላይ ቆሟል፡፡ ጋዜጦች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየታገዱ ነው፤ ማተሚያ ቤቶች በተለይ የፖለቲካ ጋዜጦችን እየመረጡ እንዳያትሙ በመንግሥት ባለሥልጣናት ጫና እየደረሰባቸው ነው፣ ድረገጾች እና ጦማሮች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይነበቡ እየተደረገ ነው፡፡

 • አንቀጽ 29 (5) - “በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም የመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ያደርጋል፡፡”

ውነታው፡- የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በመንግሥት የሚተዳደሩ ድርጅቶች ሆነው ሳሉ የገዢውን ሐሳብ ብቻ የሚያንፀባርቁ፣ በአንድ ወገን ዘመም ይዘቶቻቸውና የሕዝብን እውነታ በማፈን የሚታወቁ መገናኛ ብዙኃን ሆነዋል፡፡

 • አንቀጽ 40 (4) - “የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመ[ፈ]ነቀል መብታቸው የተከበረ ነው፡፡”

ውነታው፡- በልማት ሰበብ በተለይም በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎችም ክልሎች ለውጭ አገር ዜጎች ለግብርና በሚከራዩ መሬቶች ላይ ነዋሪ የነበሩ ዜጎች በተደጋጋሚ እንዲፈናቀሉ እና ከትውልድ ቀያቸው ርቀው እንዲሰፍሩ እየተደረጉ እንደሆኑ ብዙ ብሶቶች ገሃድ እየሆኑ ነው፡፡

 • አንቀጽ 79 (2) - “በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽዕኖ ነጻ ነው፡፡…”

ውነታው፡- ፍርድ ቤቶች ነጻነት ላይ ሕዝቡ ያለው እምነት ከዕለት ዕለት እየተሸረሸረ ነው፡፡ ነጻ ፍርድ ቤቶች አሉ ብሎ የሚያምን እየጠፋ ነው፡፡ ቀደም ብዬ የጠቀስኳት ብርቱኳን ሚዴቅሳ ዳኛ በነበረችበት ወቅት በዋስትና የፈታቻቸው አቶ ስዬ አብርሃ ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መታሰራቸው ለዚህ የፍርድ ቤቶች ነጻነት ችግር ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡

 • አንቀጽ 87 (1) - “የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ይሆናል፡፡”

ውነታው፡- ይሄ እውነት ነው በሚለው ላይ የሚስማሙ ሰዎች ማግኘት ይቸግራል፡፡ ሠራዊቱ በአናሳ ብሔር አባላት የበላይነት እንደተያዘ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይባስ ብሎ ችግሩን ቀስበቀስ ለመቅረፍ ሲሞከር አይስተዋልም፡፡ እንዲያውም እርስዎ ተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ከተሾሙ 34 ጄኔራሎች ውስጥ 29ኙ የአንድ ብሔር አባላት መሆናቸው ጥያቄው አጋግሎታል፡፡

 • አንቀጽ 89 (2) - “መንግሥት የኢትዮጵያውያንን የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ለማሻሻል እኩል ዕድል እንዲኖራቸው ለማድረግና ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚከፋፈልበትን ሁኔታ የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡”

ውነታው፡- ዛሬ ዛሬ በሀብታሞች እና ድሆች መካከል ያለው የኢኮኖሚ ልዩነት እጅግ እየተጋነነ መጥቷል፡፡ ዜጎች ሀብት ለማፍራት እኩል ዕድል አላቸው ብለው የሚያምኑ እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስደተኛ ወጣቶች በድንበር እያሳበሩ ለሞት እስከመጋለጥ የሚደርሱት ድህነት እየገፋቸው ነው፡፡ ጉዳዩ በጣም የከፋ ቢሆንም መንግሥት ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚሠራው ሥራ አይታይም፡፡

 • አንቀጽ 89 (6) - “የሀገር ልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች በሚዘጋጁበት ወቅት መንግሥት ሕዝቡን በየደረጃው ማሳተፍ አለበት፡፡ የሕዝቡንም የልማት እንቅስቃሴዎች መደገፍ አለበት፡፡”

ውነታው፡- በአገራችን አዋጆች ከወጡ በኋላ ማሳወቅ እንጂ የሚመለከታቸው አካላት ረቂቁን በማውጣት ቀርቶ፣ የወጣው ረቂቅ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የሚደረግበት ልምድ ፈፅሞ አልተዘረጋም፡፡ በከተማ ቤቶች ሊዝ አዋጅ ላይ የነበረው ከፍተኛ ግራ መጋባት እና ቅሬታም ለዚህ ጥሩ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው፡፡

 • አንቀጽ 89 (8) - “መንግሥት የሠራተኛውን ሕዝብ ጤንነት፣ ደህንነትና የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ መጣር አለበት፡፡”

ውነታው፡- ሠራተኛው የሕዝብ ክፍል ወር ጠብቆ በሚያገኛት ምንዳ ለመኖር በሚያደርገው መፍጨርጨር የኑሮ ውድነት መስዋዕት እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት ላለፉት ዐሥር በየጊዜው እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ግዥበት ለመቆጣጠር ለማዋል ሥር ነቀል እርምጃ አልወሰደም፡፡ በዚህም የሠራተኛው ሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ ተንጠልጥሏል፡፡

 • አንቀጽ 102 (6) - “በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት እንዲካሄድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ይቋቋማል፡፡”

ውነታው፡- የምርጫ ቦርድ ነጻነት ከአከራካሪነት ድኖ አያውቅም፡፡ እንዲያውም አሁን እንኳን መጪውን የአዲስ አበባ ከተማ ምርጫ አስመልክቶ 34 የተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ቦርድ ነጻነት ላይ ጥያቄ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አጥጋቢ መልስ ግን እስካሁን አልተሰጣቸውም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣

ከላይ በጠቃቀስኳቸው አንቀጾች ላይ ብቻ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የደረሱትን ሕገ መንግሥታዊ ጥሰቶች ዘርዝሮ ለመጨረስ በጣም ይከብዳል፡፡ መንግሥትዎ ሁሉንም ሕዝቦች በእኩል መንገድ ማገልገል ቢኖርበትም እኩል እያገለገለ ነው ብዬ ግን አላምንም፡፡ ሰብኣዊ መብት አያያዝ እየተሻሻለ ሳይሆን እያሽቆለቆለ እንደመጣ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች ይመሰክራሉ፣ መንግሥት ግልጽነት ይጎድለዋል፣ የገዢው ፓርቲ ነቃፊዎች እንደወንጀለኛ የሚቆጠሩበት አጋጣሚ በዝቷል፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ገደል አፋፍ ላይ ቆሟል፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ለገዢው ፓርቲ ወገንተኝነት ያሳያሉ፣ አርሶ አደሮች ከቀያቸው የሚፈናቀሉት ያለ ፈቃዳቸው እንደሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ፣ ፍርድ ቤቶች ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ ነጻ ናቸው የሚለውን የሚያምነው የሕዝብ ቁጥር እየተመናመነ ነው፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከአንድ ብሔር ተዋፅኦ የመገንባት ነገር ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል፣ የኢኮኖሚያችን ስርዓት ለሁሉም እኩል ዕድል አልሰጠም የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ነጻ ነው በሚለው ላይ የማይስማሙ ወገኖች በዝተዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች እና ችግሮች የተከሰቱት የመንግሥት ኃላፊዎች ሕገ መንግሥቱን ለማክበር ቁርጠኝነት ስለሚያንሳቸው ነው፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች ሕገ መንግሥቱን በቁርጠኝነት ባለማክበራቸው ሳቢያ ሌሎችም ዜጎች ሕገ መንግሥቱ ላይ ያላቸው ጠንካራ እምነት እንዲሸረሸር እያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጉዳዩን አንገብጋቢነት በመረዳት ሕገ መንግሥቱን የማስከበር ቆራጥ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲጀምሩ እለምንዎታለሁ፡፡

ከሕገ መንግሥቱ አክባሪዎች አንዱ፣

በፍቃዱ ኃይሉ

No comments:

Post a Comment