Thursday, November 1, 2012

ወጣት ሴት የመሆን ጣጣ




እኛ ሴቶች በተወሰነ ጊዜ በቋሚነት የምንገናኝ ሴት ጓደኞች  አይጠፉንም፡፡ የከተማዋ ካፌዎች ውስጥ የሚሆነው ይህ ቆይታችን በተለይ ወደ ሥራው ዓለም ከገባን ወዲህ ስለወንዶቻችን (በተለመደው አጠራር ባሎቻቸን) እና  በዚያው  ዙሪያ ስላሉ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሲሽከረከር ይቆያል፡፡ ፓለቲካ ያልተቀላቀለበት፣ ጠንካራ ማኅበራዊ ችግሮች የማይወሩበት እና ቀላል ጨዋታ የሚመስለው ይህ  ቆይታ  ከባድ የማይመስሉ ነገር ግን የወጣት ሴቶችን ሕይወት እና አኗኗር የሚያመሳቅሉ ጉዳዮችም ይነሱበታል፡፡ የሚለያዩ የማይመስሉ ጥንዶች ሕይወት “ውይ we break up እኮ”  በሚል ቀላል የትካዜ ቃል የሚጠናቀቅበት፣ “surprise…………… guys am engaged………..’’ የሚል ጬኸት የሚደመጥበት፣ አልፎ አልፎም አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ “I think am pragenat ምን ይሻለኛል” ተብሎ የሚተከዝባቸው ናቸው፡፡ ወደ “በሰለ ወጣትነት” ከገባንበት ጊዜ አንስቶ የወጣት ሴቶች ችግሮች በውበታቸው እየተሸፈኑ ወይም እየተለመዱ ሳይሆን አይቀርም መነጋገሪያ ሲሆኑ ሰምተንም  ተወያይተንባቸውም  አናውቅም፡፡ በዛ ቢባል የቁሳቁስ ፍቅርና የቸልተኝነት ነገር እያነሳን ሴቶቻችንን ማማረር ነው፡፡


ወጣት ሴት መሆን ጣጣ ነው፡፡ አመቱ ከመፍጠኑ አንስቶ የሚጠበቅብን አበዛዙ አብዛኛውን ዓመታት ባልሰከነ ውዥንብር ውስጥ እንድንከርም ያደርገናል፡፡ በዚህ ላይ የማኅበረሰቡ ግልጽነት ያጣ ጫና እና ማስፈራሪያ ለአንዲት ወጣት ሴት የመረጃ ምንጯ ጓደኞችዋ ብቻ፣ ትክክል የሚሆነውም ብዙዎቹ ጓደኞችዋ ያደረጉት ነገር ይሆናል፡፡ በትምህርት ቤት እና ከቤተሰብ ጥብቅ ቁጥጥር በአንጻራዊነት ነጻ በሚኮንባቸው በነዚህ ዓመታት የቦይ ፍሬንድ ምርጫ እና ውዝግቡ፣ የማግባት አለማግባት እና የዕድሜ ነገር ሐሳቡ ሁሉ ቀላል ቢመስሉም መስመር ካለው (focused) የሐሳብ መስመር በተደጋጋሚ ሲያናጥቡ እና ለብዙ የሚጠበቅ አቅም ያላቸውን ሴቶች ከተለመደው መንገድ ሲያስቀሩ ይስተዋላል፡፡

የመምሰል  ጣጣ

ወጣት ሴት ሆኖ ወጣት ሴቶችን አለመምሰል ችግር ነው፡፡ ሁላችንም ከአለባበስ ጀምሮ እስከ አስተሳሰብ ድረስ እንድንመሳሰል ይጠበቅብናል፡፡ ወንዶች እንዲጋብዙን ዝግጁ ሆኖ መገኘት፣ የተመጠኑ የሴት ልጅ ዕውቀቶች ላይ ብቻ ማተኮር እና መመሳሰላችንን የሚያፈጥኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ እንድናተኩር መደረጋችን ግድ ነው፡፡ የሴት ጓደኛው በአለባበስ፣ በአወራር፣ በመግባባት ዘዬ ዘመናዊ ሴቶቸን እንድትመስል የማይፈልግ እና የማይገፋፋት ወንድ የለም፡፡ በመሠረቱ በዚህ ዕድሜ ብዙ ሚና የሚኖራቸው የወንድ ጓደኞች ራሳቸው ልዩነትን በፍጹም አይቋቋሙም፡፡ ከለመዱት የሴቶች ዓይነት ወጣ ያለች ሴት ስትገኝ የግንኙነት መስመሩ ብዙም ሳይቆይ የሚቋረጥበት ጊዜ የሚበዛውም ለዚያ ነው፡፡ “ኧረ  ሴት ልጅ ምሰይ? የምን ጎረምሳ መምሰል ነው?” የሚሉ ወላጆችም ቀላል አይደሉም፡፡ የጓደኛ እና የጎረቤት ልጆች እንደምሳሌ እየተጠሩ የመመሳሰልን አስፈላጊነት ከወላጆቻቸን ጀምሮ እስከ ወንድ ጓደኞቻችን ድረስ እንመከራለን፡፡ በዚህም ምክንያት መሆን የምንፈልገውን እና የምናስበውን ሳይሆን ወንዶቻችን እንደንሆን የሚፈልጉትን ነው እየሆንን ያለነው፡፡ ለምሳሌ ብንጠቅስ፡- ወንዶች ወፍራም የሆነች ሴት ስለማትመቻቸው ወይም ምርጫቸው አይደለችም ብለን ስለምናስብ እኛ ሴቶች ክብደት ለመቀነስ፣ ለመክሳት እና ቦርጭ ለማጥፋት ከረሃብ አድማ ያልተናነሰ የአመጋገብ ዘየ ስንከተል ይስተዋላል፡፡ ከልክ በላይ መወፈር አግባብ ነው እያልን ሳይሆን ‹ወንዶች ስለማይመቻቸው› ግን መሆን አልነበረበትም፡፡
የዕድሜ ጣጣ እና ፍርሐቱ



ታዲያ በዚህ ጊዜ ወጣት ሴት የመሆን ጣጣው አንዱ የትኛው ነው ትክክለኛው ወንድ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ግንኙነት መጨነቅ፣ የትኛው ይሆነኛል ብሎ ማሰብ እንዲሁም ገፋ ሲል ይሄኛው የመጨረሻው ይሁን ብሎ መመኘት ያጋጥማል፡፡ በዚህ የፍቅር ግንኙነት መልኩን ቀይሮ  ቅልጥ ያለ ስሌት ወደመሆን በተጠጋበት ዘመን የመጨረሻውን ሰው ፍለጋ ሐሳቡ ቀላል አይደለም፡፡ የማኅበረሰብ አወቃቀራችን ከተወዳዳሪነት ይልቅ ዕድሜ ላይ ያተኮረ ከመሆን አለመላቀቁ እና ከወላጆቻቸንም አልፎ እኛ ላይ መጋባቱ  ደግሞ ሐሳቡን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ሴት ልጅ አይደለሽ በዕድሜሽ አትቀልጂ፣ በሴት እድሜ እንዲህ ይቀለዳል እንዴ የሚሉ አባባሎች ከእናቶቻችን ጀምሮ እስከ ጓደኞቻችን ድረስ ይዘወተራሉ፡፡ ምንም እንኳን የሴት ልጅ ዕድሜ በተፈጥሮው የሚያስቀምጣቸው ገደቦች ቢኖሩም ከልክ ላለፈ ፍርሐት ተዳርገው ብዙ ሲጠበቅባቸው በፍጥነት የዕድሜ ውድድር ውስጥ ገብተው ሰጥመው የቀሩ ሴቶች ቀላል አይደሉም፡፡ በዚህ ላይ ማኅበረሰባዊ ግዴታ ሲጨመርበት ከዕድሜ ጋር ያለው ሩጫ ቶሎ ተጀምሮ ቶሎ ይጠናቀቅና ለረዥም ጊዜ የሚቆየው ውጤቱ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህንን ማኅበረሰባዊ ግዴታ ያልተወጡ ወይም የተለየ አቅጣጫ የያዙ የሚመስሉ (ቢያንስ ለጊዜው ያልተሳካላቸውም ቢሆኑ) ወጣት ሴቶች የግል ፍርሐታቸውን ማኅበረሰቡን እና አቻ ግፊትን የመቋቋም ጣጣ ይጠብቃቸዋል፡፡

የግል እሴት እና ማኅበረሰባዊ ጥበቃን (social expectation) የማስታረቅ ጣጣ

ብዙ የከተማ ወጣት ሴቶች በልጅነት ጊዜ የነበሩን የመረጃ ዕድሎች ሰፊ እንደመሆናቸው መጠን በተቻለ መጠን የተለያዩ መረጃዎቻችን ላይ ተመሰርተን ሕልሞቻችን እናስቀምጣለን፡፡ ከዚያም ከፍ ሲል ጠንካራ እሴቶችን ልናዳብር እንችላለን፡፡ እነዚህ እሴቶች መሪ ለመሆን ማለም፣ የተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ ለመገኘት ማሰብ፣ የትምህርት እና የሌሎች ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጠንካራ እሴቶች በመካከለኛ የወጣትነት ዘመን  ላይ ሲደረስ በከፍተኛ ተግዳሮቶች እና በተለመዱ ትዳርን የመጨረሻ የሴት ልጅ ስኬት አድርጎ በሚያይ ማኅበረሰባዊ እሴቶች ውስጥ ይዋጣሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በሀገራችን ሴት ልጅ በተማረች እና በበቃች ቁጥር ስኬታማ የቤተሰብ እና የትዳር ሕይወት የመመስረት እድሏ ይቀንሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የትዳር አጋርዋን የምትፎካከርበት ገቢ ማምጣት ከቻለች እና ቤተሰብዋን እስከደገፈች ድረስ በተለያዩ መስኮች የምታርገው እንቅስቃሴ ላይ ጎልታ መታየት ከትዳር በፊት ከሆነ ለሰከነ ኑሮ የማትሆን እና ለቤት አመራር የማትሆን ከትዳር በኋላ ከሆነ ደሞ ቤተሰባዊ ኑሮዋ ላይ ጠንካራ ትርጉም ያለው ሥራ ያለው እንቅስቃሴ የማታደርግ ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ይህ የግል እሴት የመኖር ሙከራን ከሌሎች ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ጋር አጣምሮ የማየት ማኅበረሰባዊ አባዜ ለብዙ ታላላቅ ቁም ነገሮች ሕልም የነበራቸው ሴቶችን የትዳር ስኬታማ ብቻ አድርጎ አስቀርቶዋቸዋል፡፡ ይህንን ለማስታረቅ በሚደረግ ትግል የሚያልፈው ጊዜ ደግሞ ሌሎች ፍርሐቶች እየወለደ መጨረሻ ላይ ከምንም ሳልሆን ቀረሁ የሚል ቁጭት ውስጥ ወድቀው የሚቀሩ ሴቶች ቀላል አይደለም፡፡

የወንዶቻችን ነገርስ ቢሆን?

ወንዶቻችን በቃል ሲነገር ጠንካራ ሴት፣ ራዕይ ያላት በጠንካራ ገቢ የተደገፈች ምኞታቸው እንደሆነች ቢወራም በተግባር ግን ወደ ጠንካራ ጉዳዮች የምትሳብ ሴትን ለመቅረብ የመድፈር ሙከራቸው በጣም አናሳ መሆኑን የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊያን ሴቶችን ጨምሮ የብዙ ተመሳሳይ ሴቶች ይመሰክራሉ፡፡ ራስዋን በሚገባ መግለጽ የምትችልን ሴትን በተግባር የሚፈሩ ምናልባትም ከቀረቧት በኋላ ደግሞ ተመሳሳይ እንድትሆን ተጽእኖ የሚያሳድሩ ወንዶች በአብላጫው ይገኛሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በተለይ የሐሳብ ልዩነት የምታበዛ ምክንያት የምትደረድር የምትጠይቅ ከተለመዱ ጉዳዮች ወጣ ባሉ ሐሳቦች  የምታስብ  ከሆነ ደግሞ የወንወዶቻችን የንግግር ፉከራ ከንግግር የማያልፍ እንደሆነ ለማስመስከር ቀላል ይሆናል፡፡ (የፍልስፍና እና የፖለቲካ መጽሐፍትን የምታነብ፣ ስለሜክ አፕ የማታወራ  ሴት ሲያዩ የሚፈረጥጡም አይጠፉም) ታዲያ አንዳንድ ወንዶቻችንን የሴቶችን አበሳ ከሚያበዙ ጉዳዮች ጎራ ቢመደቡ መጨከን ይሆናል?

የተፈጥሮና የባሕል ተፅዕኖ

ተፈጥሮና ባሕል ለሴትም ለወንድም የተለያየ ኃላፊነቶችን ሰጥቷል፡፡ በዚህም መሰረት ሴት ልጅ በተፈጥሮ ልጅ በሆዷ ተሸክማ መውለድ እና የማጥባት ስራ የሷ ብቻ ነው፡፡ ይህን ምንም ልናደርገው የማንችለው የተፈጥሮ ኃላፊነት ነው፡፡ ባሕላችን ደግሞ ሴት ልጅ ከጋብቻ በፊት የወሲብ ግንኙነት መጀመር እንደሌለባት ይሰብካል፡፡ ከነድንግልናዋ ብታገባ ተመራጭነት አለው፡፡ ድንግልና በአብዛኛው ሴት ልጅ ከዚያ ቀደም ከወንድ ጋር ግንኙነት አለመፈፀሟን  ማረጋገጫ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ለወንድ ግን ተመሳሳይ ማረጋገጫ ማግኘትን ተፈጥሮ አትፈቅድም ወይም አልሰማንም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፈገግ የሚያሰኙ ገለጻዎችንም እናስታውሳለን፡፡ ‹ድንግልናዋን አስወሰደች/ወሰደ›፣ ‹ድንግልናዋን አስረከበች/ተረከበ› እና የመሳሰሉ ገለጻዎች ሴቷን እንደሰጪ ወንዱን እንደተቀባይ ስለሆነም የተቀበለው አካል ብቻ እንደሚጠቀም ሰጪ ደግሞ ተጎጂ ተደርጎ የመቁጠር ባሕል በተለምዶው ይታያል፡፡ ይህ ባሕል ከድንግልናው በኋላ በሚኖሩ ግንኙነቶች በቆመ ጥሩ ነበር፡፡ እኛ ሴቶች ከወንዶች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ወቅት የወሲብ ግንኙነት ማድረጋችን ወንዶች እንደተጠቀሙብን የሚታሰብበት በተለይም ግንኙነቱ በሚቆምበት ወቅት ሴቷ እንደተበደለች የመቁጠር አስተሳሰብ ሌላው አስቸጋሪ ማኅበረሰባዊ ጣጣችን ነው፡፡ ይህ ግን ፍፁም ስህተት እና መቅረት ያለበት አስተሳሰብ እንደሆነ ከጋብቻ በፊት ወይም ያለጋብቻ የሚመጣ ልጅ መኖር እንደሌለበትም በማኅበረሰባችን የተደነገገ ሕግ ነው፡፡ ከዚህ ሕግ ውጪ የሆነች ሴት ደግሞ ከማኅበረሰቡ የሚጣልባትን ቅጣት ትቀበላለች፡፡ ይህን ቅጣት ሽሽትም ብዙ መሆን የማይገባቸው ነገሮች ይሆናሉ፡፡ ከዛ ውስጥ አንደኛውና ዋነኛው ያለዕቅድ የተረገዘን ፅንስን ለማስወረድ የሚደረግ ጥረት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እርግዝና በመከሰቱ ምክንያት ብቻ ያለዕቅድና አብራ ለመኖር ከማትፈልገው ጋር ወደ ትዳር ሕይወት መግባት ነው፡፡ ይህ ቀላል ሊባል የማይችል እና በማኅበረሰብ ለሴት ልጆች ብቻ እንዲጋፈጡት የተሰጠ ጣጣ ነው፡፡
ሴት ልጅ የወሲብ ፍላጎት እና ተነሳሽነት እንደሌላት ተደርጎ የሚቆጠረውም የዚሁ ተፅዕኖ ውጤት ነው፡፡ ሴት ልጅ ወሲብን ስትፈጽም የተሰጣትን ተያያዥ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቶች አብራ ስለምታስታውስ የማርገዝ ያለማርገዝ የማኅበረሰቡ ውስጥ የወሲብ ባሕሏን ተከትሎ የሚመጡ ኃላፊነቶችን ማሰብ  ከወንዱ እኩል ወሲብን እንዳታጣጥም እና እንዳትናፍቅ (ከወንዱ እኩል ነው ያልነው) መንስኤ ሆኗል፡፡

ስርአተ ጾታዊው ውዝግብ… በሌለ ነገር? (In the middle of nowhere?)

በዚህ ጊዜ ወጣት (ከተሜ) ሴት መሆን ከእናቶቻችን እና ከተለመደው በተለየ የማኅረሰባዊ ልምድ በተለይ ለተለያዩ የአኗኗር ስልቶች እና መረጃዎች ቅርብ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ነገር ግን ከተለመደው የማኅበረሰባዊ የሴት ልጅ ኃላፊነቶችን መቀበል እና የማንቀበላቸው ላይ በተግባር የመቃወም አጣብቂኝ የዚሁ ዕድሜ ጣጣ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ዘመናዊነትን እና ባሕላዊ ኃላፊነትን አጣምረው የሚይዙ ሴቶችን ማግኘት የወደፊቱ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ተግዳሮት ነው፡፡ በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የምንገኝ ወጣት ሴቶች እንደፊልም እኩዮቻችን በተግባር ዘመናዊ መሆንን በመፈለግ እና የሚጠበቅብንን ጠንካራ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት አለመረዳት ውስጥ ወድቀን እንገኛለን፡፡ ካፌዎች ውስጥ ሲዝናኑ መዋል እና የቤት ጓዳን በአግባቡ ማስተዳደር አብረው ማስኬድ የቸገራቸው ብዙ እህቶችን ማየት በተዛባ መልኩ ለዓመታት ሲሰጥ የነበረውን  የስርአተ ጾታ ጽንሰ ሐሳብ በተግባር ለማየት ሁነኛ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ በዚህ የተዛባ እና በንባብ ባልተደገፈ የስርአተ ጾታ ዕውቀት ያለፉ ወጣት ሴቶች የሴቶችን ማኅበረሰባዊ ሚና ባለመረዳት ባሕላዊውንም ቤተሰባዊ ኃላፊነትም ሆነ ዘመናዊውን ከቤት ውጪ ያሉ ጠንካራ የሥራ እና የኢኮኖሚያዊ የበላይነት ሳይዙ መሐል ሜዳ ላይ የመቅረት ዕጣ ፈንታ ያጋጥማቸዋል፡፡

እነዚህ የተለያዩ ጣጣዎች መሐል የሚያልፉ ወጣት ሴቶች ግን በቁሳዊ እና ብልጭልጭ ፍላጎቶቻቸው ሲታሙ ሲተቹ እንጂ እየተባባሰ የመጣውን የውስጣቸውን ውዝግብ ያስተናገዱ ችግሮችን በሚዳስሱ ውይይቶች ሲካተቱ ሰምተን አናውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ስለኛ ስለሴቶች የሚናገሩት ወይም የሚጽፉት ወንዶች በመሆናቸው የዘረዘርናቸው የኛ ብቻ ጣጣዎች ትኩረት ተሰጥቶአቸው ስለጉዳዩ ግንዛቤው እንዳይኖር አድርጓልም፡፡

እስቲ ምንያህሎቻችን ነን ቡቲክ በር ላይ፣  ካፍቴሪያዎች ውስጥ እና ባጠቃላይ በዙሪያችን የምናያቸውን እና የምናቃቸውን ወጣት ዘመናዊ ቆነጃጅት በዚህ መልኩ ለመረዳት ሞክረን የምናውቀው?

6 comments:

  1. great thought! Thanks for sharing

    ReplyDelete
  2. great thought! Thanks for sharing

    ReplyDelete
  3. መጨከን ይሆናል!!!
    Meleketachehu betam yasdenekal! Bezuhanu bota yemayesetewen .... Endihe zerezer kelebech aderegachehu maskemetachehu ,,, nurulen endele asgededongal!
    Soli & Mahi bertu!!!

    ReplyDelete
  4. Wow best analysis. Please write more and more on zis type of untouchable/ misunderstood social issues. Go forward

    ReplyDelete
  5. I like this post and last time I read article about how to date Ethiopian women..on www.ethiojoke.com .it was funny and interesting

    ReplyDelete
  6. you made an exceptional observation and experience as you put it,l couldn't agree more in most of your points but in the same manner l couldn't get when you said "zemenawe sate" please l need some explanation from the writers..keep on walking and stronger...

    ReplyDelete