Sunday, November 4, 2012

ልፈራ የሚገባኝ “ሕይወቴን ያለክብር እንዳልመራ” ነዉ እንጂ “ክብር የተነፈገዉ ሕይወቴን እንዳላጣ አይደለም፡፡”

ፍቃዱ አንዳርጌ

ዞን 9 በተባለዉ የመወያያ መድረክ ላይ ብዙ ጠቃሚ ሃሳቦች በተለያዩ ፅሃፊዎች እየተነሱ ሲብራሩና ለዉይይት ሲቀርቡ እከታተላለዉ ይበል የሚያሰኝም ነዉ :: እንደ አስተያየት ግን በየጊዜዉ የሚነሱ ሃሳቦች እንደ ቆዳ እየለፉ ማለፍ እንዳለበት ይሰማኛል፡፡
ዛሬ እኔም የማህሌት ፋንታሁንየፍርሃት ዘመንየሚለዉን መጣጥፍ አንብቤ ከሃሳቧ ላይ ሃሳቤን መጨመር ፈለኩ - ማህሌት በፅሁፏ የዘረዘረቻቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትምተማሪዎች፣ሰራተኞች ፣አሰሪዎችና ባለሃብቶች ፍርሃት መር ኑሮ ለመኖራቸዉ ተማሪዉ ተመርቆ ስራ አጥ እንዳይሆን፣ ሰራተኞች የስራ ዋስትናቸዉን፣ እድገት እና የትምህርት እድል የሚያገኙት በመፍራት ስለሆነ፣ አሰሪዎች ከቀዳሚ አለቆቻቸዉ ሞገስን እና ጥቅማጥቅምን ያገኙ ዘንድ እነሱዉ እራሳቸዉ ፈርተዉ ሰራተኞችን የፍርሃት ሀሁ ማስቆጠር ስላለባቸዉ እና በቁስ ቀዳሚነትም ያመኑት ባለሃብቶችም ቢሆኑ ጣሪያ የሌለዉ ፍላጎታቸዉ ይሞላ ዘንድ የፍርሃት መንፈስ ይጠናወታቸዋል፡፡ብላለች፡፡

እኔም ሁሉም ሳይፈልግ ወደ ፍርሃት ዓለም የሚያደረገዉ ጎዞ መነሻዉ የእዉቀት፣የምክንያት እና ፍላጎት ያለመመጣጠን እንደ ሆነ እና መጨረሻዉምየፍርሃት ማህበረሰብ”(fear society) መፈጠር ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ ፡፡ በፍርሃት እሳቤ የተከበበ ማህበረሰብ ደግሞ የተቃወሰ ማህበራዊ ስሪት ስለሚኖረዉ ለመጪዉ ትዉልድ ሊያስተላልፈዉ የሚችል ባዶ የፍርሃት መንፈስን ብቻ ነዉ፡፡ እዉቁ ፈላስፋፕላቶየሰዉ ልጅ የተስተካከለ፣ ጤናማ እና ከፍርሃት የፀዳ ምክንያታዊ ስብዕና ይኖረዉ ዘንድ ሊሟሉ ይገባል ያላቸዉን ነገሮችን ዘርዝሯል፡፡ እኛምፍርሃትከስነ ልቦና ስሪታችን ጋር የተያያዘ ስለሆነ የሊቁን ስራ በከፊል እንመልከተዉ እንዲህም ይላልየሰዉ ልጅ አካለዊና ስነ ልቦናዊ ስሪቱ የተስተካከለ ሊሆን ግድ ይለዋል፡፡ የሰዉን ልጅ የነፍስ ሁነት ከሶስት ከፍሎ ማዬት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያዉምክንያታዊክፍል ሲሆን አንድ ሰዉ እንዲጠይቅ፣ እንዲያዉቅ ፣እንዲከራከር እና ሃሳቡን እንዲገልፅ የሚያደርግ ክፍል ሲሆን፤ ሁለተኛዉመንፈሳዊ ክፍልየሚለዉ ሲሆን ደግሞ አንድ ሰዉ መልካም ፈቃዱን የሚሰጥበት እና የፍርሃት እና የድፍረት ስሜቱ የሚብላሉበት ክፍል ነዉ፡፡ ሶስተኛዉ ፍላጎትን መሰረት ያደረገዉ ፍላጎታችን የሚርመሰመስበት ክፍል ሲሆን የምግብ፣የመጠጥ፣የወሲብ፣ የሃብትና መሳሰሉ ፍላጎታችን ማንፀባረቂያ ክፍል ነዉ፡፡ይቀጥልናምየአንድ ሰዉ የተስተካከለ ስብዕና ይኖረዉ ዘንድ የእነዚህ ክፍሎች የተመጣጠናና የተስማማ አካሄድ ሊኖራቸዉ ግድ ነዉይለናል፡፡
እዚህ ላይ ዋናዉ ነጥቡ የሰዉ ልጅ ለማይገደቡ ፍላጎቶቹ ብቻ አዳሪ እንዳይሆን፣ በአጉል ፍርሃት ተሸብቦ ድንጉጥ እንዳይሆን ምክንያትን የማቅረብ አቅሙ ሊጎለበት ግድ ይለዋል፡፡ ምክንያታዊነት ወደ መድረክ ሊመጣ የሚችለዉ ደግሞ ጥልቅ ወደ ሆነዉ የእዉቀት ዉቅያኖስ በመማር፣በማንበብ ፣በመጠየቅ እና በመከራከር ስንገባ ብቻ ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ ጥቅሙንና ፍላጎቱን ብቻ በማስቀደም ምክንያትን ገሸሸ በማድረግ መንገዱን የጀመረ እንደሆነ አሁንም መዘበራረቅ ሊከሰት ይችላል፡፡ ዋናዉን ጉዳያችንፍርሃትንነጥለን ያየነዉ እንደሆነ እንድንፈራ ያደረገን ነገር ፅኑ የመኖር ምኞት፣የቁስ ሰቀቀን፣ በስራ እጦት ያለመሰቃየት፣የሰዉ ፊት ላለማየት፣የደረጃ እድገት፣ብቸኝነትን መፍራት እና መሰል ስሜት ነዉ፡፡ እነዚህን ዝርዝር እና ግልፅ የፍርሃታችን ምንጮች ግን በፍርሃታችን የተነሳ ከምናጠዉ ነገር ማለትም የማወቅ፣ያወቅነዉን ነገር የመጠየቅ፣በሰዉነታችን ያገኘናቸዉን ሰብዓዊ መብት ከማጣት አንፃር በምክንያታዊ እይታ ሲመዘኑ ዉሃ አይቋጥሩም፡፡ ለዚህም ነዉ የፍርሃታችን መነሾ የፍላጎታችንና የምክንያታዊ መሆን አለመመጣጠን የሚሆኑት፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ የተማሪዎችን፣መምህራንና ሰራተኞችን ፍርሃታቸዉን እንደ ገቢ ምንጫቸዉ እና የፍላጎታቸዉ ማሟያ እንዲመለከቱ ያደረገበትን ሁኔታ አንስተን መመልከት እንችላላን፡፡

ተማሪዎችና መምህሮች

አዎ ተማሪዎቻችን የፍርሃት ቆፈን ይዟቸዋል፡፡ በድህነት ተምረዉ ፣ተመርቀዉ ስራ እንዳያጡና የቤተሰብ ሸክም እንዳይሆኑ ይሰጋሉ፡፡ ለስጋታቸዉ ማሳለጫ ይሆናቸዉ ዘንድም ሳይፈልጉ የፍርሃት መንገድን ይዘዉ ይሸመጥጣሉ፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ያልን እንደሆነ መልሱን ሩቅ ሳንሄድ ከነባራዊ ሁነቶች መረዳት እንችላላን፡፡ አብዛኛዉን የተማሪ ክፍል ያየን እንደሆነ ከሚማርበት የትምህርት ዘርፍ የዘለለ ወደ ሞራላዊ ልዕልና የሚያደርስ የማወቅ፣የመጠየቅ እና የማንበብ ልምዱ ከዜሮ በታች ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ የዕለት ዉሎዉን በአዉሮፓ እግር ኳስ የሆሊዉድን ፊልም ሰንጠረዥ መዉጣት መወረድ ሲነታረክ የሚዉልን ተማሪ ምክንያት አንስተህ ከፍራትህ ተፋታ ማለት ትንሽ ምፀት ይሆናል፡፡ይሄ ደካማነቱም ፍርሃትን ወልዶ በራስ አለመተማመንን ገንብቶ ለአምባገነኖች በቀላሉ እንዲበረከክና በወጥመዳቸዉ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ ይሄ ጉዳይ የዓለም ዉራነታችን የሚያሳየን ደግሞ አዉሮፓዎችና ምዕራባዊያኖች እዚህ አለማቀፋዊነት ደረጃ የደረሱት በእዉቀት ተጠምቀዉ፣በምክንያት ዓለም እየኖሩ ፍርሃትን ገፈዉ የሚገባቸዉን በመጠየቅ መሆኑን ስንገነዘብ ነዉ፡፡

መመህሮቻችንም የዚህ ፍርሃት ሰለባ ናቸዉ፡፡አንድ ሁለት የትምህርት ዓይነት ይይዙና ከዚያ ባለፈ ያላቻዉን ጊዜ ወገባቸዉ ላይ ሽርጥ አሸርጥዉ የፑል ዲንጋይ ሲደልቁ የሚዉሉ፣ከተማሩት ትምህርት የዘለለ ወንዝ የሚያሻግር እዉቀት ማነስ የተጠናወተዉ እንግዲህ መሸ ወደ ምሽት ቤት ልዉጣ እያሉ የቢራ ጠርሙስ ጨብጠዉ ሌቱን በንባብ ሳይሆን በዳንኪራና በቧልት የሚያነጉ መምህሮች አያሌ መሆናቸዉን ስንመለከት በምክንያት የሚሞግት መመህር ሆይ ወዴት ነህ? እንድንል ያደርገናል፡፡ እንደ ገቢ ምንጭ ብቻ የሚጠቀምበትን መመህርነት ላለማጣት ተማሪዎችን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር እያገናዘቡ ማስተማር ህልም ይሆንበታል፡፡ እንደ ማሳያ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ያጋጠመኝን ጉዳይ ላንሳ መመህሩ ክፍል ዉስጥ በሚያስተምርበት ሰዓት ከተማሪዎች ጥያቄ ይቀርብለታል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጥያቄዉ ፖለቲካዊ ይዘት ነበረዉ፤በራሱ የሚተማመን ትዉልድ የመፍጠር ሃላፊነት የነበረበት መምህር መልስ ግን ሁላችንም ቅር ያሰኘና እኛም እንደ እርሱ ማሰብ እንዳለብን በሚያመላክት አነጋጋርይሄ ፖለቲካ ነዉ እንለፈዉነበር ያለዉ፡፡ ተማሪዉ ከፍርሃት ይላቀቅ ዘንድ የመምህሩ ደፋርነትና ምክንያታዊነት ወሳኝነት ነበረዉ፡፡ ግን ሳይሆን ቀረ እኛም ፍርሃት ፍርሃት ሲለንይሄ ፖለቲካ ነዉእንለፈዉ ማለት ጀመርን፡፡

የመንግስት ሰራተኛዉ መደብ

በቤተሰብ፣በሰፈር፣በቀሌ፣በጎጥና በሃገር ደረጃ የቁስ አካል ቀዳሚነት በነጋሪት እየተነገረ ከሰራተኛዉ መደብ ሰብዓዊነትን ያማከለ እንቅስቃሴ ላይታሰብ ይችላል፡፡ ይህ በቁስ ሰቀቀን የሚባትልን የማህበረሰብ ክፍል የአምባገነኖችን ወጥ የሆነ አስተሳሰብ እንዲይዝ በሚደረግበት ጊዜ ፍርሃት የራሱ ሆነ ሚና ይኖረዋል፡፡ አብዛኛዉ የሰራተኛዉ ክፍልም ከዩኒቨርሲቲ፣ከኮሌጅና መሰል የትምህርት ተቋሞች እንደተመረቀ በተማረበት ትምህርት መስክ የመቀጠር እድሉ የጠበበ ስለሆነና የትምህርትን፣የንባብን ምዕራፍ እንደተዘጋ አድርጎ ስለሚያስብ ስራ እንደጀመረ በማግስቱ ምን እንደተማረ ወዴት እንደሚያመራ ግራ ይገባዉና ዘልማዳዊ ኑሮን ይገፋል ፡፡ ቢሮ ዉስጥና በመስክ በተዘረጉ ቢሮክራሲዎች ይታሰርና እርምጃዉን ባለበት ይረግጣል፡፡ የእድሜ መጨመርና እራስን በኢንፎርሜሽን፣በንባብ አለማሳደጉ ዛሬ ላይ ተቀምጦ ከሁለትና ከሶስት ዓመት በኋላ ስለሚያደርገዉ የመቶ እና ሁለት መቶ ብር ጭማሪ ተስፈኝነት፣ ይቺንም እድገት ላለማጣት የማይሆነዉን ሆኖ መታዬትና ፍርሃት ብቅ ማለት ይጀምራሉ፡፡ እድገቱም ቢቀር የያዙትን ላለማጣት የሚደረግ የመፍጨርጨር ጉዞ ፡፡

በአጠቃላይ የፍርሃታችን መነሻ ያየነዉ እንደሆነ በክብር መኖርን፣ በሰብዓዊነታችን ያገኘናቸዉን መሰረታዊ መብቶች እንዳናጣዉ ከምንሳሳለት ሕይወት፣ቁስ፣ከስራ ተራ መገፋትን ፣ግዞት መዉረድ ጋር ስናነፃፅረዉ ስለሚያንስብን ነዉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለዉ ደግሞ ፍላጎታችን በምክንያት ባለመመራቱ ነዉ፡፡ አንድ ሰዉ በሕይወት መኖርን ሲመኝ አብሮ በክብር፣ሰብዓዊነቱ ተክብሮ ሊኖር ግድ እንደሆነ ማመን ስንችል ነዉ ከፍርሃት ነፃ የምንሆነዉ ፡፡ አንድ ሰዉ በስራዉ ላይ እንዲቆይ ከፈለገ መብቱ እስከተከበረ ድረስ እንጂ መብቱ ሳይከበር ስራ ላይ መቆየቱ አግባብ እንዳልሆነ ስንረዳ ነዉ ፍርሃትን የምናስወግደዉ፡፡  እኔ ልፈራ የሚገባኝሕይወቴን ያለክብር እንዳልመራነዉ እንጂክብር የተነፈገዉ ሕይወቴን እንዳላጣ አይደለም፡፡እንዲህ ነዉ ደግሞ የመኖር ፍላጎት በምክንያት ሲሟሽ፡፡

No comments:

Post a Comment