Tuesday, November 13, 2012

የሰሞኑ ጦማሮች እፍታ


ጎረቤታችን ኬንያ 40 ሚሊዮን ለማይሞሉ ዜጎቿ 11ሺሕ ጦማሮች/ጦማሪዎች አሏት፡፡ በአገራችን ግን የዚህን ያህል የሚያንበሻብሹ ጦማሮች ቀርቶ ለቁጥር የሚገቡ ጦማሮች ማግኘትም እንደሚቸግር የዚህ እፍታ አዘጋጅ ታዝቧል፡፡ በዚያ ላይ ያሉት ጦማሮችም ቢሆኑ ብዙም የተዋወቁ ባለመሆናቸው ለማግኘት ይቸግራሉ፡፡ እዚህ እፍታ ላይ የቀረቡት ክለሳዎች በአብዛኛው በፌስቡክ በአዘጋጁ የፌስቡክ ገጽ ላይ በቀረበ የጥቆማ እርዳታ የተገኙ ጦማሮች በመሆናቸው ጠቋሚዎቹን በማመስገን መጀመር ተገቢ ይሆናል፡፡  

በዚህ ሰሞን ከተጻፉ ጦማሮች ውስጥ አቤ ቶክቻው በተሳልቆ የጻፈው ‹‹ወይዘሮ አዜብ አደገኛ ቦታማኖነኩ!›› የሚለው ጦማር አንዱ ነው፡፡ አቤ በዚህ ጽሑፉ ‹‹…[መለስ] የአፍሪካ መሪ ናቸው ብለን አምነን ቁጭ ብለን ባለበት በዚህ ሰዓት፤ ወ/ሮዋ ብቅ ብለውመለስ ትግራይን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የቀየሰው ስትራቴጂ ነበር!” ብለው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ተናግረዋል።…›› በማለት በቪዲዮ ምስል የታገዘ መረጃ እያቀበለን በጥቂቱ ተሳልቋል፡፡ ሙሉውን ተሳልቆ እዚህ ያንብቡ፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ ማን ይናገርላት?›› በሚል ርዕስ ደግሞ የጻፈው ‹ጉዳያችን› የተሰኘ ጦማር ነው፡፡ ጽሑፉ የሚያጠነጥነው ለግራዝያኒ ሐውልት በመቆሙ ጉዳይ ዙሪያ ነው፡፡ ጸሐፊው ግራዚያኒ ኢትዮጵያ ላይ ያደረሰውን ሰቆቃ መጽሐፍ አጣቅሰው ያስታወሱት በሚከተለው አንቀጽ ነው፡፡ ‹‹…ጥቅጥቅ ያለ የዝናብ ዓይነት ፍንጣቂ ሲዘንብብን አገሩ በሙሉ እሳት የተያያዘ ይመስል ነበር፡ቡናማ ቀለም ያለው፣ የማይጨበጥ¸ቆዳን አቃጥሎ የሚበላ እንፋሎት ዓይነት የመርዝ ጋዝ ነበር ወታደሮቻችን ላይ የሚዘንብበቸው፡፡ በዚች ቀን ብቻ ቁጥሩን መናገር የሚያሰቅቅ ወታደሮቻችን አለቁ፡፡ ከሁለት ሺሕ ከብቶች በላይም በመርዙ አለቁ፡፡ በቅሎዎች፣ ላሞች፣ በጎችና የጫካው ዱር አራዊት ሁሉ አየሸሹ ወደ ሸለቆው እየሮጡ ወደ ገደል ገቡ፡፡ (ልዑል ራስ ካሳ፣ ላቀች አክሊሉ ገጽ ገጽ 66/68)…›› ሙሉውን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ጠቅ ማድረግ ይበቃል፡፡

ፌስቡክ ላይ በሚጽፋቸው ግጥሞች የሚታወቀው ዮሐንስ ሞላ በቅርቡ በከፈተው ‹የብርሃን ልክፍት› በተሰኘው ጦማሩ ላይ ‹‹ለአገር ጉዳይ ስብሰባ ላይ ነበርኩኝ….›› የሚል ጽሑፍ ጽፏል፡፡ በጽሑፉ በመምህርነት ሥራ እንዳገለገለ ገልጾ ነገር ግን የመምህርነት ሙያ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ መሆኑን እና ፈተና ውስጥ የሚከት መሆኑን በጨዋታ መልክ እንዲህ ጣጥፎታል፡፡ ‹‹….አንዳንድ ጊዜም በሚጠበቀው መልኩ ችግሩን መርዳት አለመቻሌን ሳስብ ጥረቴ እና ጉጉቴ ከንቱ ይሆንብኛል። ስራው ከእኔ በተሻለ የእውቀትና የእድገት ደረጃ ላይ ያለ ሰው እንደሚያስፈልገው ሲሰማኝም ብዙ ጊዜ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ እፅፍና ስጨርስ፥ ከራሴ ጋር ተሟግቼ ሀሳቤን ቀይሬ ቀድጄ እጥለዋለሁ። ይህን የማደርገው ስራውን ላለመተው በመፈለግ አልነበረም። ይልቅስ ተማሪዎቹ ያሳዝኑኛል። ስራውን ብተወው በቦታው የሚተካው ሰው ማንነት ያስጨንቀኛል። ከንቱ ጭንቀት። ቢያንስ ችግሩን (ጉድለቴንም ጭምር) አውቀዋለሁና እስከ ጊዜው ድረስ መቆየቱን እመርጥና ሀሳቤን እለውጣለሁ። ፀዳ ያለ ትምክህት። :) …››


ጸሐፊው በመከተልም በማስተማር ሒደት ውስጥ የገጠመውን አስገራሚ ጉዳይ ‹ወደ ገደለው› በማለት የሚያጫውትበትን ሙሉ ጽሑፍ እዚህ ጠቅ በማድረግ መመልከት ይቻላል፡፡

አዲስ አበባ 125ኛ ዓመቷን ስታከብር መስራቾቿ ተዘንግተው፣ መለስ አላግባብ እየታወሱ ነው በሚል የሚጀምረውን እና ስለአዲስ አበባ መጪው ምርጫ የሚያትተውን ጽሑፍ ያስነበበው ‹የበፍቄ ዓለም› የተሰኘ ጦማር ነው - ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ እና ምርጫዋ›› በሚል መጣጥፍ፡፡ ጽሑፉ ማን ይሳተፋል፣ ማን ያሸንፋል የሚለው ላይ ግምት ካሳለፈ በኋላ ፓርቲዎች የአዲስ አበባ ሰዎችን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልነት እንዲያጩ መክሯል፡፡ ‹‹… አሁን ወደነባራዊው እውነታ እንመለስና ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ተወዳዳሪ እጩዎችን ሲያቀርቡ ሊያስቡበት የሚገባውን ትልቅ ቁም ነገር እናንሳ - አዲስ አበቤዎችን መመልመል፡፡ አዲስ አበባ ወልዳ ባሳደገቻቸው ልጆቿ መመራት አለባት ብዬ አምናለሁ፤ ከኔ ጎን የሚቆሙ ሌሎችም በርካቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ፓርቲዎች እጩዎቻቸው የአዲስ አበባን ነገረ ሁኔታ በቅጡ የሚረዱ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ያደጉ (ወይም ለበርካታ ዓመታት የኖሩባትን) ዕጩዎች እንዲመለምሉ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡…›› ሙሉ ጽሑፉን እዚህ ማንበብ ይቻላል፡፡

ሰብኣዊ የተሰኘ ጦማርም ‹‹ለሕዝባችን በመቆም ሕዝብ ይዳኘን!!!›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ረዥም ጽሑፍ ላይ
‹‹ብዙ ጊዜ ለአፍሪካ ወይም ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ አሜሪካ ምሳሌ መሆን የለባትም የሚሉ ክርክሮች ይሰማሉ፡፡…›› በሚል ይጀምርና አባባሉን ይሞግታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ እንግዳ አይደለንም የሚለው ጸሐፊ ሐሳቡን ማጠናከር የሚጀምረው በሚከተለው አንቀጽ ነው፡፡ ‹‹…ሁሌም ዲሞክራሲን ተለማማጅ እንደሆንን ይነገራል፡፡ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› የሚለው አባባል ተፅዕኖ ካልፈጠረብን በስተቀር ዲሞክራሲን መለማመድ ምን ማለት ነው? በማኅበረሰባችን ውስጥ ዕድር፣ ዕቁብና ሌሎች የመረዳጃ ድርጅቶችን መሥርተው ለዓመታት የዘለቁ ወገኖቻችን ችግሮቻቸውን በመተባበር ሲፈቱ ኖረዋል፡፡ ለሚያቋቁሟቸው መረዳጃዎች ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ እየመረጡ ተዳድረዋል፡፡ በእነዚህ ማኅበረሰባዊ ተቋማት ምክንያት የተፈጠሩ ግጭቶች ወይም አላስፈላጊ ድርጊቶች ጎልተው አይሰሙም፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ሆነው በርካታ ገንዘብና የሰው ኃይል መምራት የቻሉ ተቋማትን ማኅበረሰባችን ማስተዳደር ከቻለ በየደረጃው አገርን የሚመሩ ሰዎችን መምረጥ እንዴት ያቅተዋል? ለዘመናት በመተማመን መንፈስ እየሠሩ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት እነዚህ ተቋማት የረሃብና የድርቅ አደጋ ሲደርስ፣ አገር ስትወረርና በተለያዩ ጉዳዮች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እናውቀዋለን፡፡…››

ሙሉ ጽሑፉን ለማንበብ እዚህ ጠቅ ማድረግ ይቻላል፡፡

በዚሁ የዞን ዘጠኝ ጦማር ላይ ከወጡ ጽሑፎች መካከል ናትናኤል ፈለቀ ‹‹የትምህርት ጥራት ነገር›› በሚል ያሰፈረው ክፍል አንድ ጽሑፍ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ ጽሑፉ የትምህርቱ ዘርፍ በተለይም በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ እየተገዳደሩት ነው ያላቸውን ፈተናዎች ዘርዝሯል፡፡ ‹‹…በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት ላይ ላሉት ችግሮች፤ የተማሪ አስተማሪ እና የመማሪያ መጽሐፍ ጥምርታ እጥረት እና ኢትዮጵያዊ መምህራን በስራ ሁኔታ እና በሚከፈላቸው ደሞዝ ደስተኛ አለመሆን እና የብቃት ማነስ በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡…›› የሚለው ይህ ጽሑፍ ችግሮቹን በተናጠል የሚያብራራበትን ሙሉ ጽሑፍ እዚህ ጠቅ በማድረግ ማንበብ ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment