ከአዲስ አበባ ብዙም ርቆ የማያውቅ ሰው ሃያ ኪሎ ሜትር ሲራመድም ቢሆን የጉዞ ማስታወሻ ይጽፋል፡፡
እኔም የዛሬ ሁለት ዓመት እጄን ይዛ ጎንደር
የወሰደችኝ ወዳጄ፣ ዛሬ (ኅዳር 12፤ 2005) ደግሞ መቐለ ወሰደችኝ፡፡ ጉዞዬ ረዥም ነው፤ ገና አክሱም ላሊለባላና ሌሎች ጥቃቅንና
አነስተኛ ቦታዎችን እጎበኛለሁ፡፡ ይህንን ያህል ካስቀናኋችሁ ይበቃል፣ አሁን በጥቅሉ ላስነብባችሁ አቅጄ የነበረውን የጉዞ ማስታወሻ
አላስችል ስላለኝ አመሻሹን የማደሪያዬን መስኮት ሰብሮ የዘለቀ፣ ምንጩ ግን ያልታወቀ ዋይፋይ ተጠቅሜ ጻፍኩት፡፡
ለመናዘዝ ያክል፤ መቐለን ሳስብ መጀመሪያ የሚመጣብኝ ነገር ሕወሓት ነው፡፡ እንዴያው እንዲሁ…
ትንሽ ስጋ እንደመርፌ ትወጋ… የሚለው አባባል በራሱ ኢሕአዴግ ለመቐሌ ሳያዳላ አይቀርም የሚል ጥርጣሬ ሽው እንዲልብኝ አድርጎ ነበር…
ነበር ያልኩት ያለነገር አይደለም፡፡ የመሐመድ ሰልማን ተወዳጅ መጽሐፍ ፒያሳ ‹አደይ መቐለ› ባለው ትረካው ነገሩን ሁሉ ድባቅ መትቶታል፡፡
መቐሌ የምስኪኖች እና አቧራ የዋጣት ከተማ ናት ብሎ ነበር ልበል?!
መቐለ ስገባ ግን ያልጠበቅኩት ነው የገጠመኝ፡፡ ሲጀመር ስፋቷ እንደዚህ አልመሰለኝም ነበር፤
ከሌሎች የክልል ከተሞች አንጻር መቐለ ሰፊ ነች፡፡ ሲቀጥል፣ አቧራ የለባትም - መሐመድ መቼ እንዳያት እኔ እንጃ እንጂ እኔ በተንቀሳቀስኩባቸው
ቦታዎች ሁሉ ውስጥ ለውስጡ ሳይቀር ለዓይን በአማረ የኮብል ስቶን ድንጋይ የተነጠፈች ከተማ ነች - አደይ መቐለ፡፡ እኔ እኮ አቧራ
ሲባል የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ጅማ
ሄጄ ያየሁትን ዓይነት መስሎኛል፡፡
ወደ መቐለ የተጓዝነው በሰላም ባስ ነበር፡፡ ሰላም ባስ ዕድሜ ለፉክክር - የስካይ ባስን የመሳሰሉ
አዳዲስ ባሶችን በአገልግሎት ላይ ያዋለው በቅርቡ ነበር፤ እናም ምቾቱ እምብዛም አልተጓደለብንም፡፡ የመቐለ መንገድ በተለይም ወደትግራይ
ክልል እየተቃረብን በመጣን ቁጥር የተራራው ነገር እያስገረመኝ ነበር፤ እያስገረመኝ ብቻ ሳይሆን እያሳሰበኝም ጭምር፡፡ ኢትዮጵያ
ይሄን ሁሉ ተራራ ተሸክማ ምን ታደርገዋለች? ወይ አርሳው ቀለብ አታመርት፣ ወይ አፍርሳው ከተማ አትቆረቁርበት - ይሄ ‹‹ጋራ ሸንተረርሽ››
እያልን የምንዘፍንላት ዘፈን ልክ ‹‹ድንግልናሽ›› እያልን ምንም ያልተሠራባት፣ ያልተበላባት መሆኑን በተዘዋዋሪ እንምንናገረው ይሆን?
መቐለ የገባነው በማግስቱ ጠዋት ሁለት ሰዓት ነበር፡፡ (የመጀመሪያውን ቀን አላማጣ ላይ ማደር
ነበረብን፤) እንደገባን መዝናኛ ቁርስ ቤት የተባለ የከተማዋ ዝነኛ ቤት ውስጥ የከተማዋን ዝነኛ ቁርስ በላን - ፋታ፡፡ ከዚያ ጉዞ
ወደ አፄ ዮሓንስ 4ተኛ ቤተ መንግሥት፡፡
በነገራችን ላይ የመለስ ፎቶ መቐለን እንደአዲስ አበባ አላጥለቀለቃትም፡፡ ይህንን ቀድሞ መቐለ
ደርሶ የተመለሰ አንድ ወዳጃችንም አጫውቶን ነበር፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄዬ መልስ ያገኘሁ የመሰለኝ የቴክኖ ሞባይል
ማስታወቂያ አንድ ሕንፃ ግድግዳ ላይ በትልቁ በእጅ ተስሎ ስመለከት ነው - ይመስለኛል መቐለ ውስጥ የቢልቦርድ ማተሚያ የለም -
ቢኖርም ውድ ነው፡፡
የአፄ ዮሓንስ ቤተመንግሥት በእድሳት ላይ በመሆኑ በርቀት ከማየታችን በቀር፣ የተመለከትነው
በፎቶ ነበር፡፡ ፎቶው ላይ ድንጋዩ እንደጎንደር ቤተመንግስቶች ተክቦ ስናይ ‹‹ታዲያ የሚታደሰው ለምን በሲሚንቶ ይለሰናል?›› ብለን
ጠየቅን፡፡ ‹‹ቤተ መንግሥቱ በፊት የተለሰነ ነበር፣ ደርግ ነው ልስኑን ያፈረሰው›› አሉን፤ ‹‹ደርግ ቤተ መንግሥቱን በካምፕነት
ተጠቅሞበት›› እንደነበርም ነገሩን፡፡ ሙዚየሙ ውስጥ ከአፄው ዙፋን፣ ባለወርቅ ‹ምላጭ› መሳሪያዎች እና የፈረስና በቅሎ ኮርቻዎች
በቀር ሌሎቹ የራስ ጉግሣ እና ሌሎችም መሣፍንቶች ቁሳቁሶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእዚህንኛው ሙዚየም ጉብኝታችን ረዥም ሰዓት ሊፈጅ
አልቻለም - ጉዞ ወደ ‹ሓውልቲ› - የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት እና ሙዚየም፡፡
የሰማዕታቱ መታሰቢያ
የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት አጠገብ ስንደርስ የሕወሓትን ዋና ጽ/ቤት ተመለከትን፡፡ መጀመሪያ
ላይ አናደደኝ፤ ምክንያቱም የሰማዕታቱ መታሰቢያ ሐውልት እና የሕወሓት ዋና ጽ/ቤት አንድ ጊቢ ናቸው፡፡ ያናደደኝ ደግሞ እንዴት
በመንግስት በጀት የተሠራ አንድ ሙዚዬም የፓርቲ ግቢ ውስጥ (ወይም እንዴት የሕዝብ ሙዚየም ውስጥ የፓርቲ ጽ/ቤት) ይገነባል በሚል
ነበር፡፡ ኋላ ላይ ግን ስመለከት የሚያስደንቀኝ ነገር ተፈጠረ፡፡ ሙዚየሙ የተገነባው በሕወሓት አሠሪነት ነው ይላል ደጃፉ ላይ ያለ
ጽሑፍ፡፡ ወደ ውስጥ የምንገባበትም ትኬት የሚያመለክተው ከአፄ ዮሓንስ ቤተመንግስት ሙዚዬም በተለየ የክልሉ መንግሥት የቱሪዝም ጽ/ቤት
ትኬት አይደለም፡፡ ያስደነቀህ ታዲያ ምንድን ነው ካላችሁ - የሕወሓት አቅም፤ ያንን የሚያክል ሐውልት እና ጊቢው ውስጥ ያሉ ግሩም
ሕንፃዎችን የማስገንባት አቅም፡፡ እዚያው ቆም ብዬ የተቃዋሚዎችን አቅም አሰብኩት - አሳዘኑኝ፡፡
የሰማዕታቱ ሐውልት ያለበት ጊቢ ውስጥ አርብ እና ቅዳሜ ብቻ ፊልም የሚያሳይ የማቲ መልቲፕሌክስ
ሲኒማ ቤት እና የሰማዕታቱ መታሰቢያ ሙዚየም አለ፡፡ ወደሙዚየሙ ገባን ሙዚዬሙ በአቅርቦቱ በአራት ቢከፋፈልም በይዘቱ ግን ፎቶ እና
መገልገያ ቁሳቁሶች የሚታዩበት ነው፡፡ የሚገርሙ ጥንታዊ መሳሪያዎች (ጦርነቱ የተካሄደው በምንሊክ ጊዜ ነው እንዴ - የሚያስብሏችሁ)፣
የሬዲዮ ማሰራጪያዎች፣ ሌሎች ቁሳቁሶች እና በርካታ ተራኪ ፎቶዎች ሙዚየሙ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ፎቶዎቹን ስመለከት ሆነ ብዬ እፈልግ የነበረው የአቶ ስዬን እና የአቶ መለስን ፎቶ ነበር፡፡
ብዙዎቹ ታጋዮች ተሰብስበው፣ አፈር ለብሰውና እና ተጎሳቁለው (እየተሳሳቁም፣ በሥራ ላይ ተሰማርተውም ቢሆን) በጋራ የተነሷቸው ፎቶዎች
ውስጥ መለስ የሉም፡፡ መለስ ፌስቡክ ላይ ከምናውቃቸው አንዳንድ የብቻዎቻቸው ፎቶዎች እና ከሁለት ስብሰባዎች ውስጥ በቀር ሌላ ቦታ
የለም፡፡ አቶ ስዬ ግን ከናካቴው የሉም፡፡ ሌላው የገረመኝ ግን የ1977 የምሁራን ስብሰባ የተባለ ፎቶ ላይ የአቶ በረከት ስምኦንን
ፎቶ ማየቴ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ከአቶ በረከት ያቺ ፎቶ በቀር ሁሉም ሰዎች የሕወሓት እና የሕወሓት ብቻ ናቸው፡፡
‹የትሮይ ፈረስ› የሚል መጽሐፍ ላይ አንድ ኤርትራዊ ምሑር ‹ለኤርትራ ሕዝብ የሚበጀው ሰላምና
ዕርቅ ነው› በሚል የጻፉትን መጽሐፍ ሽፋን መሳሪያ ባፍጢሙ ተደፍቶ አበባ በቅሎበት ነበር፤ የዚህን መጽሐፍ ምላሽ መለስ ‹የኤርትራ
ሕዝብ ትግል ባፍጢሙ አይደፋም› በሚል ሲጽፉ ጠብመንጃውን በሽፋን ገጻቸው አቃንተውታል ሲል አስነብቦናል፡፡ ያቺን የመለስ ምላሽ
የተባለችውንም መጽሐፍ ስመለከታት ሰውነቴን ብስጭት ውርር ሲያረገኝ ታወቀኝ፡፡ ዘራፍ አይባል ነገር፡፡
BefeQadu what you have seen is a completely improved roads and alleys but Mohammed is right when he describe Mekelle,it was like he said now a days kobele stone and Bajaje changed most of the main cities though l agree the change might be beyond imagination.
ReplyDeleteBefeQadu, I am not sure what the purpose of your writting is but you have aevery right to write what you want. One thing was left on purpose or not knowing, that is the Myrtyrs Hawelti was built by all of us Tigrains inside and outside the country. I know for a fact Tigraians in the Daiaspora sent millions of dollors.
ReplyDeleteThank you
CV
ReplyDelete