Friday, November 30, 2012

የጉዞ ማስታወሻ፤ ሥልጣኔ ወደላይ እና ወደታች



አክሱም ከአዲስ አበባ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር ያውም በመኪና፣ ያውም ያንን ጠመዝማዛ መንገድ ለተጓዘ ሰው አንድ ሺሕ ነገር መጠበቅ አያስገምተውም፡፡ ጥያቄው ‹በምስል እና በተንቀሳቃሽ ምስል ያየነውን፣ ተጽፎ ያነበብነውን በአካል ሲያዩት እንዳሰቡት ይሆናል ወይ?› ነው፡፡

ከመቐለ ወደ አክሱም ስንጓዝ ውቕሮ (ከጠበቅናት በላይ የደመቀች ከተማ)፣ አዲግራት፣ አድዋ (ከጠበቅናት የደበዘዘች) ከተማን አቆራርጠናል፡፡ አድዋ ከተማ ጦርነቱ የተደረገበት ተራራ ሥር የባንዲራ መስቀያ እና የመታሰቢያ ጽሑፍ የተጻፈበት እምነበረድ ነገር መኖሩን በመኪናው ፍጥነት አስተውያለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ሰሞን ብዙ ተወርቶለትና ገንዘብ ተሰብስቦለትም የነበረው የአድዋ ተራራ ላንድማርክን ፍለጋ ዓይኔን ወደላይ ባንከራተትም ማየት አልቻልኩም፤ አብረውኝ የነበሩትን የአገሬው ሰዎችም ብጠይቃቸው የሚያውቁት ጉዳይ የለም፡፡

አክሱም ከተማ የዕድሜዋን ያክል አይደለችም፡፡ ጎስቋላነቷ ገና ከደጃፏ ያሳብቃል፡፡ እንዲያውም አካባቢውን የምታውቀው ወዳጃችን እንዳጫወተችን ከሆነ ከፎቅ አቅም እንኳን አብዛኛዎቹ የተገነቡት ከ2000 ወዲህ ነው፡፡ ማረፊያችንን ካመቻቸን በኋላ ወደአክሱም ሐውልቶች መጓዝ ጀመርን… አዲሱ የአክሱም ከተማ እና አሮጌው የተያያዙ ናቸው ከአዲሱ ወደአሮጌው የጥቂት ደቂቆች የእግር ጉዞ በማድረግ ይደረሳል፡፡ ያቺው ወዳጃችን ‹‹የአሁኗ አክሱም የበፊቱ አክሱም ላይ ነው የተገነባችው›› የሚባል አባባል እንዳለ ነገረችን፤ ቢቆፈር ከስር የሚወጣ ጥንታዊ ከተማ አይጠፋም በሚል ዓይነት፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን ፊት ለፊታችን አየነው - አክሱምን ቆሞ አየነው፣ የአክሱም ሐውልቶችን ቆመው አየናቸው፡፡


ከተተከለ ጀምሮ እንደቆመ ያለው የአክሱም ሐውልት ትንሽ በመዝመሙ መወጠሪያ በአንድ ጎን ተደርጎለታል፡፡ ሌላኛው ደግሞ ከሮም በፊታውራሪ አመዴ እና ሌሎችም ትግል የመጣው፣ እንደታጠበ ዓይነት አዲስ መልክ ይዞ በግርማ ሞገስ አጠገቡ በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ቆሟል፡፡ ሌላኛው እና ትልቁ የሚባልለት ደግሞ ከአዲሱ ጥቂት ሜትሮች ፈቀቅ ብሎ ተሰባብሮ ተኝቷል፡፡ ተሰባብሮ የተኛው ውፍረቱ ሲያዩት ከሁለቱም እጅግ የገዘፈ እንደሆነ ያሳብቃል፡፡ የቆሙት ሐውልቶች በጥቂት ስኩዌር ሜትሮች ስለታጠሩ መጠጋት አይቻልም፡፡ ከወደቀው አክሱም ስር ዋሻ ነገር አለ፡፡ የዋሻው ኮርኒስ ላይ ያሉት ግዙፍ አለቶች እንዴት እንደተቀመጡ የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ሰዎች ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

ቀጠልን፤ እዚያው ጊቢ ውስጥ ያለውን ሙዚየም ጎበኘነው፡፡ ጥንታዊ የአክሱም ዘመን ቅሪቶች (ሳንቲሞችን ጨምሮ) እዚያው ይገኛሉ፡፡ በስተመጨረሻም በትግራይ ክልል የሚገኙ ቅርሶችን የሚያስተዋውቅ ቪዲዮ መመልከት ይቻላል እና በጉጉት ቁጭ አልን፡፡ ቪዲዮው የተዘጋጀው ለውጭ አገር ቱሪስቶች በመሆኑ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው የሚተረከው፡፡ ገና ሲጀምር የትግራይን ካርታ ለይቶ ቀይ አቀለመውና… ትግራይ The Open Air Museum ነች አለ፤ እውነት ነው፡፡ ተራራዋ፣ ታሪካዊ ቦታዎቿ ብዙ ናቸው፡፡ ትግራይ ከኤርትራ፣ አማራ፣ አፋር እንደምትጎራበትም ተናገረ፡፡ በመቀጠልም… ትግራይ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ አልፋና ኦሜጋ መሆኗን ነገረን፡፡

በቪዲዮ አስቀየሙኝ

በትረካው ላይ አድዋ ይጠቀሳል - የአድዋ ጦርነትን የመሩት ምኒልክ እና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ቦታ የላቸውም፤ 120 ከድንጋይ የተፈለፈሉ ቤተ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ጠቅሶ ትግራይ የኢትዮጵያ የክርስትና ዋና ከተማ ናት ይላል - ላሊበላስ?... ከዘመናዊ ከተሞች መቐለ በዕድሜ ትልቋ ናት ይላል - የምር? አጤ ዮሓንስ ከነገሥታት ሁሉ ጀግናው መሆናቸውንም ነገረን፡፡…. አንደኛ እና ትልቅ የሚሉትን የመሳሰሉ ቃላት የተጠቀሱበትን አገባብ መቁጠር ያታክታል፡፡ እንኳን ትልልቅ እና አንደኛ ነገሮች በዙ - ደስ ይላል ችግሩ ግን በጥቅሉ ይሄ አይደለም፤ እኛ ሁሉንም ቅርሶች እንደኢትዮጵያዊነታችን የኛ ብለን ልንጎበኛቸው ኪሎሜትሮች አቋርጠን ስንሄድ የትረካው ሙሉ መንፈስ ግን ታስቦበት በሚመስል መንገድ እየጎበኘነው ያለነው የትግራይ ሀብትን እንጂ የኢትዮጵያን እንዳልሆነ ነገረን፡፡ እኔ በበኩሌ ሙዴ ወዲያው ነው የተጨረበው! በእንግሊዝኛ Belongingness አሳጡኝ ብለው ይገልጽልኝ ይሆን? እንዲያም ሆኖ ግን የባለግርማ ሞገሱን ተራኪ ድምጽ የት ነበር የማውቀው እያልኩ እያሰላሰልኩ ነበር - በመጨረሻ ተከሰተልኝ፡፡ ለካስ የድኅረ ምርጫ 97ን ብጥብጥ ተከትሎ ኢሕአዴግ ለኤምባሲዎች እና ዲፕሎማቶች የላከው የቪዲዮ ሲዲ ላይ ይተርክልን የነበረው ድምፅ ነው፡፡ መቐለ - የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም ውስጥ ካየናቸው የትግሉ ወቅት ጽሑፎች መካከል በትግርኛ የተጻፈ ‹የኢትዮጵያ ታሪክ ማስተካከያ› አይቻለሁ፤ ሁሉንም ብስጭቴን ትቼ ጉብኝቴን በመቀጠሉ ላይ ያተኮርኩት፣ የአገሬውን ሕዝብ መስተንግዶ እና እነዚህ ዓይነቶቹ የመከፋፈል ዘመቻዎች የአንድ ቡድን ዒላማዎች መሆናቸውን ለራሴ በማስታወስ ነው፡፡

ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስትያን ከሐውልቱ ፊት ለፊት ትገኛለች፡፡ ከቤተ ክርስትያኑ ፊት ለፊት ለቲዎሎጂ ኮሌጅነት እየተገነባ ያለ ሕንፃ ቀድሞ የነበረውን ውበት እንደጋረደው ያስታውቃል፡፡ ሁሉም ሰው መጎብኘት የሚችለው አፄ ኃይለሥላሴ ያሠሩትን ቤተ መቅደስ ነው፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦት አለበት የሚባለው ቤት እና ጥንታዊው ቤተ ክርስትያን ግቢ ውስጥ ሴቶች መግባት ስለማይፈቀድላቸው እኔም የጾታዬን አበርክቶ አንዴ ግቢውን በመዞር እና ፎቶዎች በማንሳት ተጠቀምኩበት፡፡

ግማሽ ቀኗ እንዲህ ስላለቀች ወደመቐለ በማግስቱ ጠዋት ልናደርገው ያቀድነውን ጉዞ ወደ ከሰዓት በኋላ አራዘምነው፡፡ በማግስቱ የአጤ ካሌብን ቤተ መንግሥት ለመጎብኘት ስንፈልግ ባጃጆች በሙሉ ‹‹ሩቅ ነው፣ ኮረኮንች ነው›› እያሉ 200 ብር እያሉ ካስቸገሩ በኋላ በመጨረሻም ለደርሶመልስ በ150 ብር ተስማምተን ጥቂት ኮረኮንቹን እንዳሻቀብን አጤ ካሌብ ቤተ መንግሥት ስር እንደደረስን ተነገረን፤ በእግርም ብንመጣ15 ደቂቃ እንደማይፈጅብን እያሰብን በመቆጨት፣ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መረብ ወንዝን ያቀፈውን ተራራ (የኤርትራ ድንበር) አሻግረን እያየን ወደ ቤተ መንግሥቱ ዘለቅን፡፡ ቤተ መንግስቱ እስከ ሦስት ፎቅ የሚረዝም ቢሆንም አሁን ግን ከመሬት በላይ ያለው ጥቂት ፍርስራሽ ብቻ ነው፤ ሆኖም ከመሬት በታች ያለው ክፍል አሁንም ድረስ በሕይወት አለ፡፡ ለማንቀሳቀስ ቀርቶ ለማሰብ የሚከብዱ ትልልቅ ድንጋዮች የምድር ስሩ ቤት ኮርኒስ እና ግድግዳ ሆነው ተጋድመዋል፤ ቆመዋል፡፡

ጥንታዊ ቤተ መንግሥቶቹ

አጤ ካሌብ ጦረኛ ንጉሥ እንደመሆናቸው ከመሬት ወለል ስር መኖሪያ መገንባታቸው አያስገርምም፡፡ ነገር ግን የዛሬ 1400 ዓመት ወደኋላ እንዲያ ዓይነት ቤተ መንግሥት ማነጽ መቻላቸው የሚያስገርም ነው፡፡ በዚያ ላይ ማብራሪያ እንደሰጡን ሽማግሌ ከሆነ ሌላም ተቆፍሮ ያልወጣ የምድር ቤት ምድር ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን ነገሩን፡፡ ግድግዳው ላይ ወደታች የተሳሉ ቀስቶች እያሳዩ፡፡ ይገርማል፤ የሳቸው ንግግር ቤተ መንግሥቱ እንዴት እንደተገኘ የሰማሁትን ታሪክ አስታወሰኝ፡፡ አንድ ገበሬ ሲያርስ ድንጋይ ይገጥመዋል፡፡ ድንጋዩን ሊፈነቅለው ሲሞክር የተገነባ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ለከተማው መስተዳድር ያመለክትና መስተዳድሩ በባለሙያዎች ሲያስቆፍሩት ያንን የሚያክል ቤተ መንግሥት ተገኘ፡፡ ታዲያ የሚያስገርመኝ ነገር፤ ያ ቤተ መንግስት በ14 መቶ ዓመቶች ውስጥ አፈር ሲለብስ፣ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች እና ባለ ሦስት ፎቁ ቤተ መንግሥት እንዴት ፈረሰ? እንዴት ስለአጤ ካሌብስ ስለሌሎቹ ነገሥታቶቻችን ያሉንን ያክል (የተጻፈው ቢቸግር) አፈታሪኮች አይኖሩንም?

ከዚያ መልስ ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደተገነባ የሚታመነው የንግሥተ ሳባ ቤተ መንግሥት ነበር ወደሚባለው ፍርስራሽ አመራን፡፡ ወደዚያ የሚወስደውም መንገድ ኮረኮንች ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት እና የከተማው መስተዳድር ለነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች መንገድ በመዘርጋት ገቢውን ማሳደግ እንዳለበት ለምን እንደዘነጋ በማሰብ ተገረምኩ፡፡ ቤተ መንግሥቱ ከካሌብ በጣም የሚሰፋ እና ብዙ ክፍሎች ያሉት ነው፡፡ ሆኖም ከወገቡ በታች ፈርሷል፡፡ ይሄንኛው ከካሌብ ቤተመንግሥት የሚለየው ምድር ውስጥ ክፍሎች ስለሌሉት ነው፡፡ የሚመሳሰለው ደግሞ ከምድር በላይ ያሉት ካቦች አደራደር ነው፡፡ ካቦቹ የተደረደሩት ወደላይ ከፍ ባለ ቁጥር በእርከን በእርከን በመሆኑ በመሬት ስበት የመናድ ዕድሉን ያጠብባል፡፡ እናም አሰብኩት፤ አገነባባቸው የመሬት ስበት የሚያመጣውን የመናድ ዕድል በሚቋቋም መንገድ በመሆኑ እነዚህ ሕንፃዎች የፈረሱት በሰው ሰራሽ መንገድ እንጂ በተፈጥሮ አይሆንም፡፡

ከሰዓት በኋላ ወደመቐለ የሚመለስ መኪና ብንፈልግም ማግኘት አልቻልንም፡፡ ወደመቐሌ የሚሄደው ‘ቅጥቅጥ’ ስላመለጠን ማግኘት የምንችለው ከአክሱም የአድዋ፣ ከአድዋ የአዲግራት፣ ከአዲግራት የመቐለ እንደሆነ ተነገረን - ያውም ከቀናን፡፡ ተጨማሪ ቀን የማደር ዕቅድ ስላልነበረን ተስፋ ቆረጥን፡፡ ዐሥር ሰዓት ላይ እወስዳችኋለሁ ያለ ለሥራ የመጣ የመንግሥት መኪና ሾፌርን መጠበቅ ጀመርን፤ ለቀጭን ጉዳይ በሄደበት የውሃ ሽታ ሁኖ በመቅረቱ ግን ለሁለተኛ ቀን አክሱም አደርን…ደግነቱ በማግስቱ ሌሊት ዐሥር ሰዓት ላይ ሁለት ባልደረቦቹን ጨምሮ መጣ፡፡

ከአክሱም ወደ መቐለ የተመለስንበት መኪና ውስጥ ያሉ የትግራይ ክልል መንግሥት ሠራተኞች ወሬያቸው በሙሉ በፖለቲካ የተቃኘ ነው፡፡ ቋንቋው ትግርኛ በመሆኑ በቅጡ አልሰማሁትም እንጂ ብዙ ቁም ነገር ሳያመልጠኝ አይቀርም፡፡ እየሾለኩ ጆሮዬ ከገቡ ቃላት ውስጥ HR2003 በተደጋጋሚ ሲነሳ ነበር፤ አድዋ ላይ ስንደርስ አንዱ ‹‹አባባ ተስፋዬ አድዋ መጥተው ‹የዛሬ አበባዎች፣ የነገ ካድሬዎች››› አሉ ብሎ አሳቀን፡፡ በየመሐሉ የመለስ ስም ተደጋግሞ ይነሳ ነበር፤ አጠገቤ የተቀመጠው እንዲያውም ‹‹የአዲስ አበባ ሕዝብ በመለስ ሞት ከማንም በላይ ማዘኑን›› ነገረኝ፡፡ በትግርኛ ሲያወራ ደግሞ ቡልቻ ‹‹ለመከላከያ ለምን 4 ቢሊዮን ብር ተመደበ?›› ብለው ሲጠይቁ መለስ ‹‹አገር እኮ በጾምና በጸሎት አትጠበቅም›› ብሏል ብሎ በሳቅ አዝናናቸው፡፡

ቴዲ አፍሮ በትግራይ

በጉዞዋችን ላይ የምንሰማው የኤርትራ ሙዚቃ የነበረ ቢሆንም የቴዲ አፍሮን የመጨረሻ አልበምም ሹፌሩ ከፍቶልን ነበር፡፡ ወዲያው የጨዋታው አቅጣጫ ወደቴዲ አፍሮ ተሸጋገረ፡፡ ቴዲ አፍሮ ቀብር ላይ ተገኝቷል እንዴ ብለው ጠየቁኝ፡፡ ‹‹አይ ቀብር ላይ አልተገኘም፤ የተገኘው ቤተ መንግሥት ነው፡፡›› አልኩኝ፡፡ ‹‹እዚያማ ሰድበውታል አልተባለም እንዴ?›› አለኝ አልፎ አልፎ ብቻ በውይይቱ የሚሳተፈው ሹፌር፡፡ ሰምቼ ነበር፤ ግን ለምን እንደሆነ ሳላውቅ ካድኩኝ፡፡

ቴዲ አፍሮ አንዴ ትግራይ ማዘጋጃ ውስጥ ኮንሰርት አዘጋጅቶ እሱም ከተገኙት 16 ሰዎች ውስጥ አንዱ እንደነበር ጋቢና የተቀመጠው ልጅ ነገረን ‹‹እኔም ራሱ በሰው ተጋብዤ ነው የሄድኩት›› በማለት፡፡ ከኔ ጎን የተቀመጠው ደግሞ ‹‹ገዛ ገረሥላሴ (የመቐሌ ባሕላዊ ጭፈራ ቤት ነው) መጥቶ ያቃል ግን ማን ይገባለታል?›› ሲል የአዲስ አበባውን ጣኦት አጣጣለው፡፡

ጨዋታው ቀጠለ፤ ‹‹እሱ ግን ምንድነው አስመራ፣ አስመራ የሚለው… ለምን አክሱም አይልም? ለምን ጎንደር አይልም?...›› ከጎኔ ያለው ጠየቀ፡፡ ከጋቢና ያለው ‹‹የቴዲ እናት አባት ኤርትራዊ ናቸው፤ አዲ ቋላ ነው የተወለዱት›› ብሎ ማብራሪያ ሰጠ፡፡ በጥቅሉ ግን ከወሬያቸው መንፈስ እንደተረዳሁት ከሚወዱት ኤርትራ ዘፈን ወዲህ የሚያደምጡት እሱኑ ነው፤ እንዲያው ብቻ ግራ የገባቸው አቋሙ ከማን ጋር እንደሆነ ነው፡፡ ምክያቱም ‹‹እሱ ቆይ ለምንድን ነው ከሌሎቹ አርቲስቶች ጋር አንድ ላይ የማይሆነው… ሌሎቹ ለመለስ ቀብር እንትን ሲሉ ነበር…›› ብለዋል፡፡ ‹እንትን› ያሉት ምን እንደሆነ አላወቅኩም፡፡

በመንገዳችን መሐል የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሚባለው የነጃሺ መስጊድ ጋር ከፍተኛ አከባበር አየን፡፡ ምንድን ነው ስንል ለካስ ኅዳር 15 ቀን በያመቱ መስጊዱ የቆመበት ሰደቃ አለ፡፡ ወይ ትግራይ - እውነትም ክፍት ሙዚየም፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን ያንን ፈታኝና ጠመዝማዛ መንገድ በኤርትራ ጉዳይ (በነገራችን ላይ ከአፋቸው የማይነጠለው የኤርትራ ወሬ ትግራዋዮች ዛሬም እንደሚናፍቋት ያሳብቅባቸዋል)፣ በወያኔና ደርግ ጦርነት እና በመለስ ሙገሳ ወሬዎች ያንን አስፈሪ አቀበት እና ጠመዝማዛ መንገድ ፉት ብለነው መቐለ ተገኘን፡፡ በተመከርነው መሠረት ወደላሊበላ ጉዟችን መቀጠል ነበረበትና የላሊበላ መኪና ነገ ጠዋት ለመያዝ ዛሬውን ወልዲያ መግባት አለብን፤ መኪና ከየት ይምጣ ለሚለው ጥያቄ ጀብደኛ መልስ አገኘንለት፡፡ 90 ኩንታል ከኋላው የጫነ አይሱዙ ውስጥ ተሳፈርን፡፡

የአይሱዙው ሾፌር ዮሐና የምትባል ከተማ ላይ በፌዴራል ፖሊሶች የተዘጋ መገንጠያ መንገድ 100 ብር ጉቦ በመክፈል አስከፈተ፡፡ ለምንድን ነው ስንለው፤ ‹‹መንገዱ እስከአላማጣ ያለውን ዳገት የሚያቀል አቋራጭ ነው ግን ገና ግንባታው እስኪያልቅ ማቋረጥ ስለተከለከለ ነው በጉቦ የምንጓዘው አለ፡፡ ከሁለት ሰዓት በላይ እንደተጓዝን ትራፊክ አዲሱ መንገድ ላይ ቆሞ ጠበቀን፤ ሾፌሩን ሦስት መቶ ብር ቀጥቶ አበሳጨው፡፡ እንደምንም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት መብራት ጠፍቶባት ‹ከፊል ጨለማማ› የሆነችው ወልዲያ ደረስን፡፡

ከወልዲያ ወደላሊበላ የተሳፈርነው በሚኒባስ ነው፡፡ ሚኒባሱ ወደ ባሕርዳር የሚወስደውን መንገድ ጥሎ ወደላሊበላ የሚገነጠለው ጋሸና የተባለች ከተማ ላይ ሲሆን ከዚያ በኋላ ያለው 64 ኪሎሜትር ውስጥ 60 ያክሉ ፒስታ በመሆኑ ከመንገጫገጩ ባሻገር ከመኪናው ስንወርድ አቧራ ላይ ኳስ የተጫወተ ሰው መስዬ ነበር፡፡ የዓይኖቼ ሽፋሽፍት ላይ ሳይቀር አቧራ ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን የላሊበላ ከተማ ነገር ነው፡፡ ከላይ ለአክሱም ከተማ ጎስቋላ የሚለውን ቃል በመጠቀሜ ከጎስቋላ የከፋ ቃል ላገኝ ባለመቻሌ ሳልገልጸው አልፋለሁ፡፡

ዕድገተ አክሱም ወ ላሊበላ

የዚህን ጽሑፍ ዋና ርዕስ የሰጠሁት የአክሱም ስልጣኔ ከመሬት በላይ የላሊበላ ደግሞ ወደ መሬት ስር የሚለውን ተንተርሼ ነበር፡፡ ሳስበው ግን የሚከተሉት ሁለት አንቀጾችም ቢጨመሩ ተገቢ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የትግራይ ከተሞች ማማር የጀመሩት ከሦስት ዓመት ወዲህ መሆኑን አብሮኝ ተሳፈረ ያልኳችሁ የነገረኝ ሲሆን ኢሕአዴግ በ97 አዲስ አበባ ላይ ቅንጅት እንዳስደነገጠው፣ በ2002 ደግሞ አረና ትግራይ ላይ ሳያስደነግጠው አልቀረም፡፡ ዞሮ ዞሮ የትግራይ ከተሞች አድገዋል ልላችሁ ነው፤ ይህን ስል የተጋነነ ምስል እንዳትይዙ ከሌሎች ከተሞቻችን አንፃር መሆኑን እወቁልኝ፡፡ ለመንደርደሪያ ያክል ወደአክሱም ስንሄድ ያገኘነው አንድ ሰው ስለአክሱም ‹‹እያደገች ነው›› ያለንን እና ወደላሊበላ ስንሄድ ከጎኔ የተቀመጠው ደግሞ በራስ ተነሳሽነት ‹‹ዘላለም የማያልፍላት ከተማ›› ብሎ የተማረረውን ንፅፅር አስቀምጬላችሁ ልጀምር፡፡

ከአዲስ አበባ ስወጣ አክሱምን እና ላሊበላን የመጎብኘት ዕቅድ ነው የነበረኝ፡፡ አክሱም ለመድረስ እና ወደ ላሊበላ ለመድረስ በብዙ የገጠር ከተሞች ውስጥ ማረፍም ማለፍም የግድ ነውና በዚያ ሒደት ውስጥ ሳልፍ የተመለከትኩትን ሳልናገር ማለፍ ይከብደኛል፡፡ መቐሌ እንደደረስኩ በመቐሌ መደነቄን ቀድሜ ተናግሬያለሁ፡፡ ከመቐሌ ወደ አክሱም ስሄድ እና ስመለስ ያረፍኩባቸው እና ያለፍኩባቸው ከተሞች ሁሉ ተስፋሰጪ የዕድገት አዝማሚያ የሚያሳዩ፣ በተለይም ደግሞ በየመሃሉ የምናያቸውን መንገደኞች ጨምሮ (እጃቸውን በተማጽኖ ከሚያውለበልቡት የተጎሳቆሉ አሮጊቶች በቀር) ሁሉም ነቃ ያሉ እና ከተሜነት የሚነበብባቸው ናቸው፡፡ ካየሁት መገመት እንደምችለው ትግራይ ወደ ከተሜነት እያመራች ነው፡፡

በተቃራኒው ግን ወደ ላሊበላ ለመጓዝ ደምቢያ ስንደርስ ከተማዋ ዓይን የሚገባ ነገር የሌላት መሆንዋ ብቻ ሳይሆን መኪና እንዲፈልጉልን የምንነግራቸው ደላሎች ሁሉ ‹ሞባይል› የላቸውም፤ መቐሌ ግን ሁሉም ባለሞባይል ናቸው፡፡ አብረውን የተሳፈሩት ሁሉ ባላገርነታቸው የሚጎላ ከተሜዎች ናቸው፤ ጋሸና የተባለችው ከተማ ስንደርስ ደግሞ ከቤቶቹ ቁጥር የጫት ቤቶቹ ቁጥር የሚበዛ ይመስላል፡፡ ብቻ ልዩነቱ የሕንፃ ብቻ ሳይሆን የሰውም ነው፡፡ ከመቐሌ ወዲያ ያሉት ተስፋ ሰጪ ስልጣኔ ላይ ሲሆኑ ከዛ ወዲህ ያሉት ሁሉ ደግሞ እስካሁን ከባላገርነታቸው መላቀቅ አልቻሉም፡፡ የከተሞች እና ከተሜነት መስፋፋት ለአንድ አገር ዕድገት አመላካች አይደለም ብሎ የሚከራከረኝ ይኖር ይሆን? (ይህ እንግዴህ የድህነቱን ልዩነት ሳናነሳው ካለፍን ነው፡፡)

ለዚህ ልዩነት ምክንያቱ ምን ይሆን ተባባልን - ከጓደኛዬጋ፡፡ ምናልባት የትግራይ ክልል አስተዳደሮች በጀታቸውን ባግባቡ ስለሚጠቀሙ? ከሆነስ ሌሎቹ ለምን እንደነሱ አልተጠቀሙም? ምናልባት እነሱ በመንግሥት እምነት ስላላቸውና መንግሥትም በነርሱ እምነት ስላለው ጠንክረው ስለሚሠሩ እና መንግሥትም የሚሠሩ ሰዎችን በፖለቲካዊ አመለካከት ሳይሆን በሥራ ችሎታ ስለሚሾም? ወይስ… የእነርሱ ሹመኞች እና የንግድ ሰዎች አቅም ስለናረ የከተሞቻቸውን ሕዝባዊ እና ንግዳዊ እንቅስቃሴ አሳድጎት ነው? መልስ አልነበረንም፡፡

ላልይበላን በጨረፍታ

ስለላልይበላ ጉብኝቴ ትረካ ሳስብ የጨነቀኝ እንደፖርቹጋላዊው ጎብኚ መታመን ያቅተኛል ብዬ አይደለም፤ ያየሁትን በትክክል መግለጽ ይቸግረኛል ብዬ ነው፡፡ የአክሱም ታሪክ ያስጎመዣል ቅሪቱ (በአካል የሚጎበኘው) ግን አንጀት አያርስም፡፡ የላሊበላ ደግሞ ተቃራኒ ነው፡፡ የሚወራው ነገር ሲታይ ከሚፈጥረው ስሜት እና አግራሞት አንጻር የሚገለጽ አይደለም፡፡ አንድ ግዙፍ ድንጋይ ወደታች ተፈልፍሎ ሕንፃ ሲወጣው፣ ሕንፃው ፎቅ እና ውስብስብ ዲዛይን ሲኖረው፣ አንዱ ክፍል ገብተው ሌላኛው ውስጥ ሲገቡ እንደገና አዲስ ሲሆን፣ ሕንፃው የተሰራው ደግሞ ከ839 እስከ 813 ዓመታት በፊት መሆኑን ሲያስቡት፣ ‹‹ወቸ ጉድ›› ያስብላል፡፡

አንዳንዶቹ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት (ሕንፃዎች፤ በተለይ በቡድን አንድ እና ሁለት ውስጥ ያሉት) በፀሐይና ዝናብ መፈራረቅ ምክንያት መሰነጣጠቅ ስለጀመሩ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ማኅበራዊ እና ባሕላዊ ድርጅት (UNESCO) ጣሪያ ተገንብቶላቸዋል፡፡ አንዳንዶቹ ምሰሦዋቸው በመፍረሱ በተጠረቡ ድንጋዮች ካብ ተተክተዋል - ሆኖም ግን አብዛኛው ሕንፃ እንዳለ አለ፡፡ የላሊበላ ኤርፖርት በቀን ሦስቴ (አንዳንዴም አራቴ) በረራ እንደሚያስተናግድ እና አብዛኞቹም ቱሪስቶች መሆናቸውን አስጎብኛችን ነግሮናል፡፡ እኛም እንዳየነው አክሱምን ሊጎበኙ ከሚመጡ እጅግ የበዙ የውጭ ዜጎች ጉብኝቱ ላይ አግኝተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን የሚያርፉበት ደህና ደረጃ ያለው ሆቴል ያላት ጥሩ ከተማ ነች ለማለት አይቻልም - ላሊበላ፡፡ የእውነት ቢታሰብበት የቱሪዝም ገቢዋ ብቻ ከተማዋን ማሳደግ ያቅተዋል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡

እኛ በጣም የለመድነውና ሁሌም ስለላሊበላ ስናስብ የሚመጣልን የቤተ ጊዮርጊስ ምስል ነው፡፡ እሱ እንግዲህ የመጨረሻው የንጉሥ ላሊበላ ሥራ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የተሠራውም ቤተ አማኑኤልም የሚያስገርም ጥበብ ግድግዳው ላይ ተሠርቷል፡፡ በስፋት ትልቁ የሆነው የቤተ መድኃኔዓለም እና የመጀመሪያ ሥራው የሆነው ቤተ ማርያም ውስጣዊ ዲዛይኖች ጥበብ ዓይን አያስከድንም፡፡ የሚገርመው የሁሉም ቤቶች ውጪያዊና ውስጣዊ ዲዛይኖች አይመሳሰሉም፡፡ ምናልባት አብዛኛዎቹን የሚያመሳስላቸው ነገር ካለ የውስጥ ምሰሦዎቻቸው እርስ በርሳቸው ሲጣመሩ የሚመሠርቱት የአክሱም ሐውልት አናትን የመሰለ ዲዛይን ነው፡፡

ጀብዱ ለሚወድ ሰው መተላለፊያ ዋሻዎቹ ከሆኑት ውስጥ ረዥሙንና በድቅድቅ ጨለማ የተሞላውን መተላለፊያ ያለመብራት ማቋረጥ ግሩም አማራጭ ነው፡፡ አንዴ መብራት አብርቼ ካየሁት በኋላ… ጣሪያው ከአናቴ እንደሚርቅ፣ መሬቱም ድፍን እንደሆነ አይቼ… በዚያ ድቅድቅ ጨለማ ለመራመድ አንዴ ጣሪያውን ዳበስ፣ አንዴ ቀኜን፣ አንዴ ግራዬን ዳበስ ከዚያ በቀኝ እግሬ መሬቱን መታ፣ መታ አድርጌ አንድ እርምጃ፣ አሁንም ድጋሚ እንደዚያ እያልኩኝ አቋረጥኩት፡፡ በዓይናችን ላይ ያለን እምነት እንደዚህም አጋጣሚ ታስቦኝ/ተገልጦልኝ አያውቅ!

ውቅር አብያተ ክርስትያናቱን በጥድፊያ ባለችን ግማሽ ቀን ጎብኝተን/ሳንጠግበው ስንጨርስ ወደ ሙዚየሙ ወሰዱን፡፡ ሙዚየሙ ሕንፃዎቹ ሲጠረቡ አገልግለዋል ተብላ ከምትታሰብ አንዲት መጥረቢያ እስከ የመስቀል፣ የአልባሳት፣ አትሮኖሶች እና በርካታ የብራና ጥንታዊ መጽሐፎች ድረስ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ንጉሥ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናቱን ከመጥረቡ በፊት እንጨት ፈልፍሎ የሠራቸው አምሳያዎች/ሞዴሎችም ይገኛሉ፡፡

በመጨረሻም ነገሬን ከዚህ በላይ ሳላስረዝመው የምላችሁ ቢኖር አንድ ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁለት ይከፈላል፡- ላሊበላን የጎበኘ እና ያልጎበኘ ተብሎ፡፡ ቶሎ ጎብኙት እና ከቆጫችሁ እከሰሳለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment