Friday, June 22, 2012

ህግ ምርኩዝ ነው ዱላ ?

ዘላለም ክብረት

ህዝብ አብሮ ሲኖር ግጭት ሊያስወግደው የማይችለው ነገር ነው፡፡ የሰዎች የእርስ በእርስ ግንኙነት እስካለ ድረስ ግጭት አለ፡፡ በግጭቱ ጉልበተኛው አሸንፎ ተሸናፊውን እንደፈለገ ይቀጣል ማለት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እንግሊዛዊው የስነ መንግስት ሊቅ Thomas Hobbes ‘State of Nature’ የሚለው ወይም ጉልበተኛ የሚገዛበት ደካማ የሚጠቃበት እና Hobbes “ life is solitary, poor, nasty, brutish, and short” ብሎ የገለፀው ሀሳባዊ አለም ነው፡፡

ይህ እንዳይሆን ህዝብ ስምምነት ላይ ደረሰ ይሄንም ስምምነት በልቦናው ፈረመ 'መንግስት' የሚባልም አካል መሰረተ፡፡ ይህ አካልም ከህዝቡ ጉልበት ተቀንሶ ጉልበተኛን ይቀጣ ዘንድ ተሰጠው እንዲሁም ይህ መብት እንዳለው ሁሉ የህዝቡን ሰላም የማስጠበቅም ግዴታ ተሰጠው፡፡ ማን ? መንግስት የተባለው አካል፡፡

ታዲያ መንግስት በጦር በጎራዴ ብቻ ሰላምን አያሰጠብቅም ይልቅስ ሰላማዊ መሳሪያውን ይመዛል ይሄም መሳሪያ የመንግስት ህግ ነው፡፡ ህዝቡም ያከብረው ዘንድ ይወዳል ወይም ይገደዳል፡፡ ስለዚህ የመንግስት ህግ ማለት መንግስት ህዝብ ከራሱ የተፈጥሮ ስልጣን ቀንሶ መንግስት ለተሰኝው አካል ስለሰጠው መንግስቱ ይሄን የህዝብ አደራ ለመጠበቅ የሚቀርብ በትር ነው፡፡

በመሰረቱ የኢትዮጵያም ታሪክ በዚህ የመንግስት ህልዮት ይገዛል፡፡ ነገሩ የሚበላሸው መንግስት የተባለው አካል የህዝብን አደራ በልቶ ሌላ ዳቦ መጋገር ሲጀምር ነው፡፡ የህዝቡን ዳቦ በልቶ የራሱን ሽልጦ ሲያነጉት ነው መከራው፡፡

መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር የህዝብን ሰላም እና ጥቅም ለመስጠበቅ ህግ ያወጣሉ፣ ይከለክላሉ፣ ያስጠብቃሉ፡፡ ይሄም እውነት በጠነከረ ሁኔታ አሁን ባለንባት ኢትዮጵያ ገዝፎ ይታያል፡፡

ለምሳሌ ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ከፀደቀበት ህዳር 1987 ዓ.ም ወዲህ፡

- ወደ 750 የሚደርሱ አዋጆች፣
- ከ200 በላይ ደንቦች፣
- በሽዎች የሚቆጠሩ መመሪያዎች ወጥተዋል፡፡

እነዚህ ህጎች በአጠቃላይ መብትን ማስጠበቂያና ግዴታን መስጫ ናቸው፡፡ እንደ ሁሉም የህግ ባህሪያት፡፡ አስገራሚ የሚሆነው ጉዳይ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ የሚወጡ ህጎች ብርታት እና ሀይል ነው፡፡

የፕረስ ህጉ አዋጅ ቁጥር 590/2000 ፣ የሙያ ማህበራት ህግ አዋጅ ቁጥር 620/2000፣ የፀረ-ሽብር ህግ አዋጅ ቁጥር 652/2001፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ አዋጅ ቁጥር 662/2001፣ የሊዝ ህግ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ብለን የዋነኛዎቹን ብርቱ ህጎች መዘርዘር ይቻላል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ደግሞ በረቂቅ ደረጃ ያለ የሁሉንም ሰው በር ሊያንኳኳ የሚችል አዲስ የህግ ረቂቅ የቴሌኮም ህግ በሂደት ላይ ይገኛል፡፡

እንግዲህ ለጨዋታችን ይሄን ረቂቅ ህግ ከፀረ-ሽብር ህጉ ጋር አብረን እንመልከተው፡

- ማሞ እና ብሪቱ አዲስ ሙሽራዎች ሲሆኑ የፍቅራቸው ሙቀት አልበርድላቸው ብሎ የሚያደርጉትን አሳጥቷቸዋል:: ለዚህም ይመስላል ማሞ ህዝብ ይወቀው፣ ይመልከተው ብሎ ከብሪቱ ጋር ሲቃበጡ እና የጭናቸው ፍም በጋለበት ወቅት እያደረጉት ያሉትን ድርጊት ምስል የፌስቡክ ገፁ ላይ የለጠፈው፡፡ ግማሾቹ ጓደኞቹ ምነው ማ ሞ ! ሲሉት ግማሾቹ ደግሞ ኧረ ማሚሻ ቀወጥሽው ሎል ምናምን ብውለታል፡፡

በአዲሱ ረቂቅ የቴሌኮም አዋጅ አንቀፅ 6 መሰረት ማንኛውም ሰው ፀያፍ የሆነ ነገርን ማንኛውንም የቴሌኮም መሳሪያ ተጠቅሞ ለህዝብ ያሳወቀ ከሆነ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 640 የተደነገገው ቅጣት እንዳለ ሁኖ ከ 3 – 8 ዓመት ያስቀጣል፡፡ እንግዲህ ህጉ ከፀደቀ አቶ ማሞንም መልካም የእስር ወቅት ለማለት እንገደዳለን እንዲሁም ሞቶ በክር መታሰር ነው ክፉ ስምንት ዓመት እማ ስምንት ቀን ናት ብለን ለማፅናናት እንወዳለን፡፡

- አያንቱ የዩንቨርስቲ ትምህርቷን ጨርሳ በአንድ የመንግስት ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ለሁለት ዓመታት ካገለገለች በኋላ በአንድ የምስራቅ አውሮፓ ሀገር ነጻ የትምህርት ዕድል ታገኛለች፡፡ ማንንቷን እና የቋንቋ ችሎታዎን ለማረጋገጥ በሚል ዩንቨርስቲው አያንቱን በ Skype ለሚደረግ የ30 ደቂቃ ቃለ መጠይቅ ይጋብዛታል፡፡ አያንቱም በተቀጠረችበት ሰዓት ሰፈር ውስጥ የሚገኝ አንድ ኢንተርኔት ካፌ ውስጥ ተገኝታ ቃለ ምልልሱንም በድል ትወጣለች፡፡ የማረጋጋጫ ደብዳቤም ይደርሳታል፡፡

በአዲሱ የቴሌኮም አዋጅ አንቀፅ 10 ንኡስ ቁጥር 4 መሰረት ማንም ሰው እያወቀም ሆነ በቸልተኝነት በኢንተርኔት የሚደረግን የስልክ ወይም የፋክስ ጥሪ ያደረገ ከሆነ ከ3 ወራት እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ይቀጣል፡፡

እንግዲህ ይህ ረቂቅ አዋጅ ከወጣ እህት አያንቱ ወደ ትምህርት ከመሄድ ይልቅ ወደ እስር ቤት መሄዷ እውን ይሆናል፡፡

እሱ እንዳለው ያ ሎሬቱ <<ሰው ይማራል አንድም በሳር ሀ ብሎ አለያም በአሳር ዋ ብሎ፡፡>>

- ዳርጌ ፌስቡክ ላይ ነው ውሎ አዳሩ፡፡ የሆነ ቀን ነሸጥ ሲያደርገው "አልሻባብ ድሬዳዋን ተቆጣጠረ ይሄም የጫትን ዋጋ ሊያንረው ይችላል" ብሎ ይለጥፋል:: በጉዳዩ የተደናገጡት ፌስቡካዊያን ጨኸታቸውን ያሰማሉ፡፡

በፀረ ሽብር ህጉ ማኝኛውንም የሽብር ድርጅት መደገፍ እንዲሁም ህዝብን ሊያሸብሩ የሚችሉ መረጃዎችን የለቀቀ አሁን ደግሞ በረቂቁ የቴሌኮም አዋጅ ማንኛውንም የቴሌኮሚኒኬሽን መሳሪያ ተጠቅሞ አሸባሪ መልዕክት ያስተላለፈ ሰው እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

እንግዲህ ዳርጌም የዚሁ አንቀፅ ተሸላሚ ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥ ዳርጌ "ፅሁፉን የፃፍኩት ጓደኞቼን አሰደንግጨ April the Fool ለማለት ነው" እንደሚል አይጠረጠርም፡፡

Thomas Hobbes ከመቃብር ቀና ብሎ ይሄን ቢመለከት የስነ መንግስት ትንታኔውን ያሻሽለው ይሆን ወይስ  Sometimes, the state of nature can be the case even if there is a Law, since an unjust law is not a law at all” ይላል? እኛም  መንግስት ከሕዝብ ኃይል ተቀናንሶ የተሰጠውን በትር አደራውን ሳይሆን ሌላ ነገር ሲጠብቅበት ባየን ጊዜ Is Rule by law a Rule of Law? ብለን እንጠይቃለን::

No comments:

Post a Comment