Sunday, June 10, 2012

ጋዜጦቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ - አንድ

(የሳምንቱ ጋዜጦች ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3፤ 2004)

በአጭር ጊዜ ውስጥ ተነባቢነት ያተረፈውና በአንድነት ፓርቲ አሳታሚነት ማክሰኞ ገበያ ላይ የሚውለው ፍኖተ ነፃነት በመላው ሃገሪቱ ሰፊ የመረጃ መረብ ስላለው ሁሌም ዜናዎቹ ትኩስና ያልተሰሙ ናቸው፡፡ በዚህ ሳምንትም ከዜናዎቹ ውስጥ እነዚህ ነበሩበት፡-

‹‹…በጎንደር ፖሊስ የሟቾችን አስከሬን በመኪና መሬት ለመሬት አስጎተተ….

‹‹… የዜና ምንጮቻችን እንደሚሉት ‹አቶ ሽንኩ ከፍያለውና አቶ ዳኛቸው የተባሉ ሁለት ግለሰቦች ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርገው ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው መሬት ለመሬት ሲጎተት ውሏል› ብለዋል፡፡….››

‹‹…በቤንች ማጂ ዞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገደሉ….

‹‹… የፍኖተ ነፃነት ምንጮች ባደረጉት ማጣራት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመው [ለአራት ወራት የፀጥታ ችግር የሰፈነበትን] አካባቢውን ለማረጋጋት ሞክረዋል፡፡… በዚህ የኃይል እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተገደሉ [ምንጮች] አስረድተዋል….››

‹‹…የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር የመተዳደሪያ ደንቡን አፀደቀ….

‹‹… በምስረታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፕሬስ አሳታሚዎች ማህበር (ኢፕአማ) ሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2004 ባካሄደው ስብሰባ የመተዳደሪያ ደንቡን አፀደቀ….››

‹‹…ግንቦት 20ን ለማክበር 120 ሚሊዮን ብር መውጣቱ ተጠቆመ….

‹‹… [የፍኖተ ነፃነት ምንጮች] እንደሚሉት ‹ሰዎችን ጋብዞ ላመጣ አንድ ሺ ብር፣ ለፎረም አባል 600 ብር፣ ለቀበሌ ቀስቃሽ 300 ብር፣ ለሰልፈኛ መቶ ብር እየተከፈለ የተሰበሰበ ነው፡፡ ለዚሁ ማስፈፀሚያ የሚውል ለኦሮሚያ ብቻ 30 ሚሊዮን ብር መመደቡን› ያስረዳሉ፡፡ ….››

የፈቴሌ እማሬ እና ፍካሬ (ፍኖተ ነፃነት፤ በነብዩ ኃይሉ) ያስነበበን ትንታኔ ደግሞ ስለስልክ መጠለፍ ያወጋናል፡- ‹‹… በአንዳንድ የስልክ ልውውጦች ላይ የራስህን ድምጽ መልሰህ የምትሰማበት፣ ከሌሎች ስልኮች በተለየ በአድ ድምጽ የምትሰማበት፣ የሦስተኛ ወገን ንግግር በጣልቃ የሚሰማበትና የሚቆራረጥበት ሁኔታ ስልክ መጠለፉን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው፡፡… ባለሙያዎች እንደሚሉት ቴሌ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እያጋጠሙት ያሉት ችግሮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው የኔትወርክ መጨናነቅ ድርጅቱ ለጠፋ ተግባር የሚጠቀምባቸው በአድ መሳሪያዎች ጠንቅ እንደሆነ ይናገራሉ…››

* * *


የጋዜጠኛ ስንዱ አበበ አስገራሚ ቃለ ምልልስ ከየኛ ፕሬስ ጋዜጣ ጋር፤ ቀንጨብ፣ ቀንጨብ እያረግን እንመልከተው፡-

‹‹ጥንቆላ ለልማት መዋል ቢችል ኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ ታመጣለች›› ይላል ርዕሱ!

‹‹… ብዙ ኢትዮጵያውያን ችሎታ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ግን ችሎታቸውን ለክፋት ነው የሚያውሉት፡፡ ለምን? እኔ አሁን እንዲጠየቅልኝ የምፈልገው ይሄንን ነው፡፡…

‹‹… እኔ እንግዲህ ጋዜጠኛ ነበርኩ፡፡ ነፃ ጋዜጣ ሲመሰረት ጀምሮ ከነበሩት ሰዎች አንደኛዋ ነበርኩ፡፡ አንዱ ጋዜጣ ጥሩ ነገር ሲያወራ ሰምተሃል? አሉባልታ፣ ክፋት፣ የሰው ስም ማጥፋት፡፡ እንድታድግ፣ እንድትቀየር፣ የተሳሳትከውን ነገር እንኳ ሲጽፉ የሚፅፉበት መንገድ በክፋት ተወሳስቧል፡፡ ክፋት በዝቷል፡፡ ለምን ይህን ያህልስ እንከፋፈላለን? ክፋት ምን ያደርጋል? ግን ችሎታህን ለክፋት መጠቀም በጣም መርዛማ መርዛማ አኗኗር ነው፡፡ ቫይብሬሽኑን ራሱ መርዛማ አድርገውታል፡፡ የመጀመሪያው ተጠያቂ ደግሞ ሚዲያው ነው፡፡…

‹‹… በማጂክ የምንኖር መሰለኝ እኮ! ሰርተህ ምንም የለም፡፡ እኔ አሁን ዘጠኝ መጽሃፍ አትሜያለሁ፡፡ ላይፌን ደሞ እየው፡፡ ምንድን ነው ይሄ? ምንም ማለት ነው፡፡ ምን ሆኖ? የት ሄደ? የሰራኹት ገንዘብ የት ሄደ? ያ ሁሉ ስራ ምንድን ነው የሆነው? ብትለኝ ላስረዳህ አልችልም፡፡ ውልብልብ ነው… ሁሉም ሰው ገብቶታል ይሄ፡፡…

‹‹… በመንግስት በኩል ለምሳሌ እንየው ብንል ማተሙን አትከለከልም፡፡ ግን ማከፋፈል ላይ ይይዙሃል፡፡ ሜጋ አይገባም ካሉህ አለቀ፡፡ በስንት ቡክ ሾ ልትሸጥ ነው ሜጋ ካልገባህ፡፡ ስለዚህ ያከስሩሃል፡፡…

‹‹…[ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ጋዜጠኝነት] መጥፎ የሆነ ህዝብ የሚመራ መድረክ ስለሆነ ህዝቡንም ምን ያህል ክፉ እንዳደረግነው አስብ፡፡ እና በጣም ያሳፍራል፡፡ እና ጋዜጠኛ መባል፣ ቃሉንም መባሉንም አልፈልገውም፡፡ ስለነበርኩም አሁን ላይ ይደብረኛል፡፡…

‹‹… ብዙ ጊዜ ደግሞ ጋዜጦቹ ማተም የሚፈልጉት አሉባልታ ነው እንጂ እውነት የተደከመበት ስራ አይደለም፡፡…

‹‹… ስታየው ያለንበት ሁኔታ ተመሰቃቅሏል፡፡ ሃይማኖቶቹም ተመሰቃቅለዋል፡፡ ፖለቲካውም ተመሰቃቅሏል፡፡ ምንድን ነው ስትል ‹‹ሞስትሊ›› ጥንቆላ የሚባለው ጠልሞስ፣ ዛር፣ ደብተራ… እንግዲህ እነኚህ በአግባቡ ያልፈተሽናቸው ኢትዮጵያውያን እሴቶች ናቸው፡፡ አሁን አሉ? የሉም? መጠናት አለበት፡፡ ግን እኔ አሁንም ባለው ሁኔታ ላይ ጥንቆላ ለልማት መዋል ቢችል ኢትዮጵያ ፈጣን ለውጥ ታመጣለች፡፡…

‹‹… እናድናለን ይላሉ፡፡ ያጎራሉ፤ ከሁሉ ነገር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ - የያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ከጥንቆላ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሴክተሮች ተጠንተው ለልማት የሚውሉበት መንገድ ካለ መንግስት ይህን ቢመረምር ይሻላል የሚል አቋም አለኝ፡፡…››

‹‹… እኔ የሰራኋቸው መጽሃፎች ወደፊት ገና ትንታኔ ይፈልጋሉ፡፡ በአዋቂ ሰዎች፣ ዩኒቨርስቲዎ ፔፐር ይሰሩባቸዋል፡፡ ይደርሳል፡፡ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከአምስት ስድስት ዓመተ በኋላ የኔ መጽሃፎች በጣም እንደሚፈለጉ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ቀን ለማየት ፀጥ ብሎ ራስን አክብሮ መኖር፡፡››

* * *


መሰናዘሪያ  በበኩሉ የዶ/ር ኃይሉ አርአያን ምስል ከሽፋን ገጹ ላይ ይዞ ወጥቷል፡፡ ዶ/ሩ ለጋዜጣው ሲነግሩት እንዲህ ብለዋል፤ ‹‹… የአንድ አምባገነን ግለሰብ መለወጥ ምንም ለውጥ አያመጣም

‹‹… የልማት ማዕከሉ ሰው ነው፡፡ አንድ ነገር አደገ ሲባል የሰውን ህይወት መለወጥ አለበት… የዕለትተዕለት ኑሮውን ካላሻሻለው ዋጋ የለውም፡፡ … ያለነፃነት የተሟላ ልማት ሊኖር አይችልም፡፡ ውሸት ነው ቀጣይ የሆነ ዘላቂ ልማት ሊኖር አይችልም፡፡…››

* * *


ሪፖርተር በረቡዕ እትሙ ‹‹… የኤርትራ ጦር በባድመ አንድ ትምህርት ቤትና አንድ አውቶቡስ አቃጠለ›› የሚል ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡

‹‹… ባለፈው እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በባድመ ግንባር የሚገኘው የኤርትራ ጦር ኃይል በከባድ መሣርያ (ተወንጫፊ) ባደረሰው ጥቃት፣ ‹‹ባድመ ቀዳማይ ብርኪ ቤት ትምህርቲ›› (ባድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት) ሙሉ ለሙሉ በመቃጠሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡…››

‹‹መለስ በምስክርነት ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው›› የሚል ዜና ያስነበበን ደግሞ ኢሕአዴግ ሲቀነስ መለስ ምን ይሆናል? የሚል ጥያቄ ሽፋን ገጹ ላይ ይዞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ነው፡፡ ስለመለስ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲዘረዝር፡-

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የቀድሞ የህወሓት አመራሮች ለምስክርነት መቐለ ከተማ ፍ/ቤት ሊጠሩ ነው፡፡ አመራሮቹ ለምስክርነት የተጠሩት የህወሓት መስራች ከነበሩት አንዱ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ላይ አቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን የስም ማጥፋት ክስ ተከላከሉ በመባላቸው ነው፡፡…››

አቶ አስገደ ‹ጋሃዲሦስት› በተባለው መጽሃፋቸወ ምዕራፍ 29 ላይ የቀድሞ የህወሓት የፀጥታና ደህንነት አባልን ስም አጥፍተዋል በሚል በአቃቤ ሕግ ለቀረበባቸው ክስ ነው… መከላከያ ምስክር የጠሩት፡፡

‹‹… አቶ አስገደ በመከላከያ ምስክርነት ከጠሯቸው የመከላከያ ማስረጃዎች መካከል አቶ መለስ ዜናዊ፣ አምባሳደር ሙሉጌታ አለምሰገድ (ነዋሪነታቸው በጣሊያን) አቶ ስብሃት ነጋ፣ አቶ መኮንን (የአባታቸው ስም ለጊዜው ያልታወቀ)፣ አቶ ወልደስላሴ አብርሃ (በትግራይ የሚገኙ)፣ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ፣ አቶ ፍሬው ተስፋሚካኤል (በደቡብ ሱዳን ጁባ የሚገኙ)፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ አባይ ፀሃዬ፣ አቶ ስዬ አብርሃ (በአሜሪካ ሃርቫርድ ዩንቭስቲ የሚገኙ)፣ አቶ ስዩም መስፍን (ቻይና በአምባሳደርነት የሚያገለግሉ)፣ አቶ አርከበ እቁባይ፣ አቶ ኪሮስ አቡዬ፣ አቶ አክሊሉ ኪዳነማርያም (በአድማስ ኮሌጅ አዲስ አበባ የሚገኙ) እና ሦስት የመከላከያ ጄኔራሎች ይገኙበታል…››

ሰንደቅ እንደቀጠለ ነው…

‹‹የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ባለስልጣናት የኢሕአዴግ አቻዎቻቸውን አሰለጠኑ…

‹‹… አምስት አባላት ያሉት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ዓለም አቀፍ አባላት [በአቶ ሴኮቱሬ ለሚመራው] ለኢሕአዴግ አቻቸው….በብዙኃን መገናኛ አቅም ግንባታ፣ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት አስተዳደርና በኢንተርኔት አስተዳደር [ቻይና] ያላትን ልምድ በስልጠናው ተመርጠው ለተገኙ የኢሕአዴግ ከፍተኛ የአመራር አባላት አካፍለዋል፡፡…

‹‹… ቻይና ፌስቡክን ጨምሮ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማፈን (ጃም በማድረግ) በዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ተቃውሞ የሚቀርብባት ሲሆን በሃገሪቱ የሚዲያ አፈና እና የጋዜጠኞች መብት የማይከበርበት መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡››

* * *


‹የዋጋ ግሽበቱ እና የ‹‹መለኖሚክስ›› [የመለስ-ኢኮኖሚክስ] ክስረት› በሚል ርዕስ የኢኮኖሚ ምሕዳሩን ቅኝት በፍትሕ ጋዜጣ ላይ ያቀረበው ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ‹‹… በየሦስት አልያም አራት ቀናት ውስጥ አንዱን ምንም ምግብ እቤት ውስጥ የማይኖርበት ጊዜ የተለመደ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥመኝ ለልጆቼ ምንም የሚበላ ነገር እንደሌለ እነግራቸዋለሁ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የተገኘ ጊዜ ደግሞ አንዷን እንጀራ አራት ቦታ ቆርሼ፣ ትንሽ ሽሮ ፈሰስ አደርግና እንዲቃመሱ አደርጋቸዋለሁ፡፡ አሁን እግዚአብሔር ይመስገን ህፃናቱ ያለውን ችግር እየተረዱ መጥተዋል፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ምግብ አምጪ እያሉ አያስቸግሩኝም፡፡…›› ያሉ የኢኮኖሚው መገለጫ ንግግሮችን ከጥናቶች አሰባስቦ አቅርቧል፡፡

ፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝም በበኩሉ ‹የጠፋው ትውልድ እና የታህሪር ናፍቆት› በሚል ርዕስ በጻፈው ጦማሩ ‹‹… የባልቻ አባት ሳፎ እንጂ አባ ነፍሶ አይደለም የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ሳይሆን ይህች ሀገር እስከመቼ ድረስ እንዲህ በግለሰቦች የተናጠል ትግል ህልውናዋ ሊጠበቅ ይችላል?...›› በማለት ምሁራኑ እንኳን ፈርተው የሸሹትን ‹‹ብቸኛ ታጋይነቱ››ን አወድሷል፡፡ ተመስገን ስለ ‹ያ ትውልድ›፣ ስለ ‹አምላጭ ትውልድ› ሐተታ ካቀረበ በኋላ ‹ታህሪር ናፋቂ› ስላለው ትውልድ ሳምንት ለመመለስ ቃል ገብቶ ተሰናብቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት የ‹‹ቃሊቲው ምስጢሮች›› ላይ የሰላ ትችቱን የሰነዘረው ብርሃኑ ደቦጭ በዚህ ሳምንት ደግሞ ‹‹ባለቀለተ ጉዳይ ፍርድ ቤት ከመከራከር ለሕዝብ ዳኝነት አንድ መጽሐፍ መጻፍ፤ የሲሳይ አጌና መጽሐፍ አንድምታ›› በሚል ርዕስ ለዘብ ትችቱን አቅርቧል - በፍትሕ ጋዜጣ!

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞችን በታዘቡበት የሰላ ትችታቸው ‹‹…የዛሬዎቹ ‹ታዲያስ አዲስ›፣ ‹የፍቅር ክሊኒክ›፣ … የመሳሰሉ የኤፍ.ኤም ፕሮግራሞች በየእለቱ የሚረጩት መርዝ የትውልዱን ስነምግባር ሸርሽሮ ከስሩ ነቅሎ እስከሚጥለው፣ ሀገራችን በእውቀትና በስነምግባር የታነጸ ዜጋ ማጣትዋ በግልጽ እስከሚታይ ስንት ዓመት ይፈጃል?...›› ሲሉ ‹ዘመኑ እኮ የኤፍ.ኤም ነው› በሚል ርዕስ ፍትሕ ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ በምሬት ጠይቀዋል፡፡

* * *


አዲስ አድማስ ነፃ አስተያየት በተሰኘው አምዱ ‹‹የመንግስት ወከባ ከፍርሃት የማያላቅቅ የሕልም ሩጫ›› የሚል ሰፊ ሐተታ አስነብቧል፡፡ ‹‹… ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የያዙ ስራአጦች እየበዙ ነው፣ ቁጥራቸው በ5 ዓመት ውስጥ በ3 እጥፍ ይጨምራል፣ የትራንስፎርሜሽኑ እቅዱ 2 ዓመት ሊሞላው ነው፤ ነገር ግን በርካታ እቅዶች በተያዘላቸው ጊዜ አልተሰሩም፣ የስራ ፈላጊ ከተሜዎቹ ቁጥ በ330ሺ ይጨምራል፤ ሩብ ያህሉ ብቻ መደበኛ የስራ እድል ያገኛሉ፡፡ የገጠር ሕዝብ በየዓመቱ በ2ሚ. እየጨመረ ነው፤ የዝናብ እጥረት ሳይኖርም ከ12ሚ. በላይ ሰዎች ተረጂ ናቸው…›› እያለ የመንግስት እቅድንና አፈፃፀምን ይተቻል፡:

‹‹..     ይድረስ

ለወዳጄ፡-

እንደምን ሰንብተሃል እኛ ባለንበት እግዚአብሄር ቸርነት ደህና ነን፤ መቼም ወቅት ፈቅዶ ለብዙ ትውልዶች ያህል ተራርቀን ብንኖርም ያገሬ ታሪክ የጀግኖች ታሪክ መቼም አይዘነጋም ብዬም አልነበር… እናም ይሄውልህ በእናንተው ዘመን ደግሞ ብላቴናው ቴዎድሮስ ካሳሁን ‹‹ጥቁር ሰው›› ብሎ ታሪካችንን ብድግ አደረገዋ!

       እንግዲህ ምን ትላለህ? ከሆነልህማ የፊታችን ማክሰኞ ከአመሻሹ 12 ሰዓት ላይ ከቤተመንግሥታችን ዝቅ ብሎ ከሚገኘው ሂልተን ውቴል ብቅ በልና ጠበል ፀዲቅ ቅመስ፤ ስናወጋ እናመሻለን

       አደራ እንዳትቀር

       ያልመጣህ እንደሆነ ግን ማርያምን እቀየምሃለሁ፡፡

       ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ግንቦት 28/2004 ዓ.ም. ›› - የቴዲ አፍሮ ‹ጥቁር ሰው› ሙዚቃ ቪዲዮን ለማስመረቅ የተዘጋጀው የጥሪ ወረቀት ላይ የተጻፈ ጽሁፍ (አዲስ አድማስ)

* * *


ነጋድራስ ጋዜጣ ‹‹በጽንፈኝነት የተቃኘች ሃገር›› በሚል በደሳለኝ ስዩም ባቀረበው ሰፊ ሐተታ ሃይማኖተኞችን፣ የገዢው ፓርቲንና ወገኖችን፣ ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጦችንና ፕ/ር መስፍንን ሳይቀር በማስረጃ እያስደገፈ ተችቷል፡፡ ከጽሁፉ ጥቂት ለመጨለፍ ያክል፡- ‹‹…በመገናኛ ብዙሃን ኢንዱስትሪ ውስጥ መካከለኛ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ጭልጥ ያሉ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና የኢሕአዴግ አቀንቃኝ የሆኑ የመንግስት ብዙሐን መገናኛዎች እና ጭልጥ ብለው ምንነቱ ያልታወቀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚደግፉ /ኢሕአዴግን በመጥላት ላይ ብቻ የተመሰረቱ/ ብዙሐን መገናኛዎች በየራሳቸው ጽንፍ ላይ ቆመዋል፡፡…››

የጋዜጦቹ ርዕሰ አንቀጽ

ሌላም፣ ሌላም

  • በአዲስ አበባ በቤተ-ክርስቲያን ይዞታ በተቀሰቀሰ ግጭት የሁለት ሰው ህይወት አለፈ፡፡ - ፍትሕ

  • በጋዜጠኛ ርዕዮት ላይ የይግባኝ አቤቱታ ክርክር ሊጀመር ቀጠሮ ተያዘ - ፍትሕ

  • አቶ አስገደ ‹‹የመከላከያ ምስክሮቼን ለማሰማት ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ገጠመኝ›› አሉ - ፍትሕ

  • ‹‹ገመና ድራማ ተተራመሰ፤ ተፈሪ አለሙና መሰረት መብራቴ ጀማነሽ ሰለሞንን ተከትለው ራሳቸውን አገለሉ›› - የኛ ፕሬስ

  • ጋዜጠኛ አበበ ገላው በደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል - አዲስ አድማስ

  • ‹‹ስለ ካሴቱና ስለፕሮግራሙ የምሰጠው አስተያየት ባይኖረኝም ክሊፑ በጣም አሪፍ ነው፤ የሠሩት ልጆች መመስገን አለባቸው፡፡›› - የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ (አዲስ አድማስ)


ቀልድ

‹‹ማርሻል ቲቶ የዩጎዝላቪያ መሪ በነበሩበት ጊዜ ነው አሉ፡፡ ቲቶ የደህንነት ሚኒስትራቸው ራንኮቪክን አስከትለው በከተማዋ ጉብኝት ያድረጋሉ (የሥራ ልትሉት ትችላላችሁ፡፡) መጀመሪያ ወደ አንድ ወላጅ አልባ ህፃናቱ ያሉበትን ሁኔታ ለማሻሻል በሚል 10ሺ ዲናር ይለግሳሉ - ቲቶ፡፡ በመቀጠል ጋብቻ ሳይመሰርቱ የወለዱ እናቶች መጠላያ ይሄዱና 15ሺ ዲናር ይሰጣሉ - የእናቶቹንና የህፃናቶቻቸውን የአኗኗር ሁኔታ ለማሻሻል በሚል፡፡ የቲቶ ቀጣይ ጉብኝት ወህኒ ቤት ነበር፡፡ እዚያ ደግሞ 80ሺ ዲናር ሰጡ - የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል በማዘዝ፡፡…. ቲቶ ለወህኒ ቤቱ ባደረጉት የበዛ ልግስና የተገረሙት የደህንነት ሚኒስትራቸው፤ ‹ለምንድን ነው የእስረኞች አያያዝ እንዲሻሻል ያን ሁሉ ገንዘብ የሰጠኸው?› ሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ ቲቶም ሲመልሱ፤ ‹ክፉ ቀን ቢመጣ እኔና አንተ ማረፊያችን የት ይመስልሃል? የህፃናት ማሳደጊያ ተቋም፣ የእናቶች መጠለያ ወይስ ወህኒ ቤት?››› በማለት የጻፈው በብዕር ስሙ ኤሊያስ የአዲስ አድማስ ፖለቲካ በፈገግታ› አምደኛ ነው፡፡ በጽሁፉ ‹‹…አዲስ አዋጅም በሉት መመሪያ ሲወጣ ከዕለታት አንድ ቀን እኔም ላይ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ቢቀር እንኳን መጠርጠር ክፋት የለውም…›› ብሏል፡፡

በመጨረሻም ስፖርት

‹‹በበርካታ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ባለመሳተፏ የተረሳችው ኢትዮጵያ በዘንድሮው የ2012 የአውሮፓ ዋንጫ ስሟ የሚጠራበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ በመጪው አርብ ሰኔ 1 ቀን 2004 በሚጀመረውና ፖላንድ እና ዩክሬን በሚያስተናግዱት የአውሮፓ ዋንጫ ለቼክ ሪፐብሊክ ብሔራዊ ቡድን ከሚሰለፈው ቴዎዶር ገብረስላሴ ጋር ኢትዮጵያም መጠራቷ አይቀርም፡፡…›› - ሰንደቅ፡፡

No comments:

Post a Comment