Sunday, June 24, 2012

ጋዜጣ እና መጽሄቶቻችን ከሰኞ እስከ ሰኞ - ሦስት

(ከሰኔ 11 እስከ ሰኔ 17፤ 2004)

የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት በልዩ ዝግጅት ለማክበር ደፋ ቀና እያለ ያለው ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ በዓይነቱ የተለየ ‹‹የንድፈ ሐሳብና የፖሊሲ ትንተና መጽሄት›› ሊያሳትም እንደሆነ የሚነግር ዜና ይዞ ወጥቷል፡፡ ‹‹.. በዓይነቱ የተለየ የንድፈ ሐሳብና የአማራጭ ትንተና የሚቀርብበት መጽሄት ለማሳተም ዝግጅት መጨረሱን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ለዝግጅት ክፍላችን አስታወቀ፡፡ ‹ዳንዲ› የሚል ስያሜ የተሰጣት መጽሄቷ ሙሉ ለሙሉ የንድፈ ሐሳቦችና አማራጭ የፖሊሲ መነሻ የሚሆኑ ሐሳቦች የሚተነተኑባት መሆኗ ተነግሯል፡፡

* * *


‹‹የመንግስት ገንዘብ ለሚያባክኑ መ/ቤቶች ከፍተኛ በጀት ተመደበ›› ያለው ደግሞ የኛ ፕሬስ ጋዜጣ ነው፡፡ ‹‹ከፍተኛ የመንግስት ገንዘብ ባለማወራረድ ዋና ኦዲተር ለመሰከረባቸው መስሪያ ቤቶች ከበፊቱ የበለጠ ከፍተኛ በጀት እንደተመደበላቸው ተጠቆመ፡፡›› ካለ በኋላ ባለፈው ዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ያባከኑትን መ/ቤቶች ሲዘረዝር ‹‹… መከላከያ ሚኒስቴር፣ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የመቀሌ ዩንቨርሲቲ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የመቀሌ ጤና ሳይንስ፣ የአይደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመንግስትን ገንዘብ ያለበቂ ማስረጃ ወጪ በማድረግና ሳያወራርዱ በመቅረት በዋና ኦዲተር ጥቁር መዝገብ ውስጥ እንደገቡ አረጋግጧል፡፡›› በተመሳሳይ ዜና ፍኖተ ነፃነትም የመጪው ዓመትን በጀት ‹‹ለአፈና የሚውል በጀት›› ሲል ወርፎታል፡፡

* * *


‹‹የየመኑ ፕሬዘዳንት ሳላህ አዲስ አበባ መሽገዋል?›› የሚል መካከለኛ ሐተታ ይዞ የወጣው መሰናዘሪያ ‹‹…የብዙዎች ግምት ሳላህ ከእይታ የተሰወሩት ለደህንነታቸው በተፈጠረው ስጋት ሳይሆን ቀደም ሲል ስልጣን ላይ እያሉ ለሕዝባቸው እኔ በፊት በየቀኑ ጫት እቅም ነበር፡፡ አሁን የምቅመው በሳምንት አንድ ጊዜ ነው ስለዚህ እናንተም የእኔን አርአያ ተከተሉ በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ መሽገው ሱሳቸውን እያወራረዱ ነው ወይም ከሕዝብ በዘረፉት ገንዘብ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ሱሳቸውና ፍላጎታቸውን እያጣጠሙ እንደሆነ የሚገልፅ ነው፡፡…››

* * *


ሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹ዳኞች የፍርድ ቤት ተገልጋዮን በቁጣ ማሸማቀቃቸው ጥያቄ አስነሳ›› የሚል ዜና በረቡዕ ዕትሙ የፊት ገጽ ላይ ይዞ ወጥቷል፡፡ በዝርዝሩም ‹‹…በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የተለያዩ የክስ ሒደቶችን የሚያስችሉ ዳኞች በተገልጋዮ ላይ በሚያደርሱት ቁጣ፣ ተገልጋዮቹ በችሎቱ የተገኙበትን ጉዳይ ሳያስረዱ ተሸማቅቀው እንደሚመለሱ ተገለጸ፡፡..›› እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህ የተገለጸው ከሕዝብ በቀረቡ ጥያቄዎች እንደሆነ በዜናው ላይ ተገልጧል፡፡

* * *


ሰንደቅ ጋዜጣ ‹‹ተማሪዎችን በውጤት ያንበሸበሸው የአ.አ.ዩ. ባልደረባ ቅጣቱን እየጠበቀ ነው›› ሲል ዘግቧል፡፡ ‹‹በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና የስነ-ትምህርት ፋኩሊቲዎች ውስጥ የተማሪዎች ሪከርድና ማኅደር ክፍል ሰራተኛ ሆኖ የ18 ተማሪዎችን ውጤት ከዲፓርትመንቱ መምህራኖች በመቀበል አሻሽሎ ወደሬጅስትራር አስተላልፏል ሲል የፌዴራሉ የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚስን ዐቃቤ ሕግ ክስ የመሰረተበት አቶ ሰለሞን ኩምሳ….. የሰውም ሆነ የሠነድ መከላከያ ማስረጃ የለኝም በማለቱ የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት.. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡››

* * *


ተመስገን ደሳለኝ ፍትህ ጋዜጣ ላይ ‹‹ፍትህን እና አልሻባብን ምን አገናኛቸው?›› ባለው መጣጥፉ ላይ ካልታወቀ እራሱን የአልሻባብ ወኪል ብሎ ከፍትህ ጋዜጣ ጋር ውል እንደነበረው ለማስመሰል በፍትህ ኢሜይል መልዕክት ስለላከ ሰው ጽፏል፡፡ ‹‹… እንደምታውቀው ለ30 ተከታታይ እትሞች 24,000 የአሜሪካን ዶላር ከፍለንሃል፡፡ አሁን ግን አልሻባብ ዕቅዶቹን ለመፈፀም የስልት ለውጥ አድርጓል፡፡ ስለዚህም 11,200 የአሜሪካን ዶላር የሚሆነውን የ14 እትሞች ክፍያ ለአልሻባብ እንዲመለስ እንፈልጋለን፡፡…›› የሚል እና ሌላም፣ ሌላም ይዘት ያለውን ደብዳቤ ተመስገን የተቀነባበረ ሴራ እንደሆነ ማረጋገጫ ያላቸውን ነገሮች ከዘረዘረ በኋላ ‹‹… ስርዓቱ እዚህ ድረስ ወርዶ ለመወንጀል እየሞከረ ያለው ሀገራችንን ጥለን እንድንሄድ አልያም ራሳችንን በዝምታ እንድንሸብብ ከሆነ፤ የሚሰማ ካለ አቋማችንን በተደጋጋመ ማሳወቃችንን ብቻ አስታውሶ ከማለፍ ውጪ አማራጭ የለውም፡፡..›› ብሏል፡፡

* * *


‹‹ዶ/ር እሌኒ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ›› የሚል ዜና በፊት ገጹ ያስነበበው አዲስ አድማስ ‹‹… የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩት ዶ/ር እሌኒ ገ/መድህን፣ የሥራ ማስፋፊያ ዕቅዳቸው ተቀባይነት ማጣቱን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን ሥራ አስፈፃሚዋ ከነበራቸው ኃላፊነት ለቀዋል፡፡ ዶ/ር እሌኒ በምርት ገበያ መስራችነታቸው ዓለምአቀፍ እውቅናና ሽልማቶች እንዳገኙ የሚታወቅ ሲሆን ድርጅቱን ለመመስረትና ለመምራት አብረዋቸው እንዲሠሩ በዓለምአቀፍ መመዘኛ ቀጥረዋቸው የነበሩ ዘጠኝ ባለሙያዎችም ከሳቸው ጋር ለቀዋል፡፡ የደርጅቱን ሥራ ለማስፋፋት ከመንግስት ጋር ውይይት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን የተናገሩት ዶ/ር እሌኒ፣ አንዳንድ ዋና ዋና እቅዶች እንደከሸፉ ለሮይተርስ ገልፀዋል፡፡…. በዶ/ር እሌኒ ምትክ የአቢሲኒያ ም/ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ አንተነህ አሰፋ የተሾሙ ሲሆን፣ ኩባንያው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሲሰሩና ልምድ ሲቀስሙ የነበሩ የአገር ውስጥ ተቀጣሪ የማኔጅመንት ባለሙያዎች፣ አመራሩን ተክተው ይሰራሉ ተብሏል፡፡…››

* * *


ላይፍ መጽሄት ‹‹‹ጥቁር ሰው› ለሚኒልክ፣ ‹ስቴድ›ስ ለማን ተዘፈነ?›› በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ ላይ የብርቱኳን ሚዼቅሳን ምስል አስቀምጦ ለርሷ እንደተዘፈነ ተከራክሯል፡፡ እንደማስረጃ ያስቀመጠው ‹‹…ቃል እንዲህ ሆነ እንዴ…›› የሚለውን ሐረግ ሲሆን ይህንንም ያለው ብርቱኳን ለሁለተኛ ጊዜ ከመታሰሯ በፊት ‹‹ቃሌ›› ብላ የጻፈችውን ደብዳቤ በማጣቀስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹…ቃል እንዲ ሆነ እንዴ…›› ካለ በኋላ በደበሰባሳው ‹‹…በሃገሬ…›› የሚል ዜማ ያሰማል በማለት ክርክሩን አጠናክሯል፡፡

* * *


የቴዎድሮስ ተ/አረጋይን ቃለ ምልልስ በአዲስጉዳይ የሚያነቡ ከBBC - Hardtalk ጋር ያመሳስሉታል፡፡ በዚህ ሳምንት አቦይ ስብሃትን አነጋግሯቸዋል፡፡ ‹‹አቦይ ስብሃት ከኢሕአዴግ ፊትና ኋላ›› የሚል ርዕስ ከተሰጠው ምልልሳቸው ውስጥ እየቀነጫጨብን እንመለከታለን፡-

‹‹… በ60ዎቹ አጋማሽ ላይ እዚህም እዚያም ትግል ነው፡… የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በተሻለ ብቃት ተንትኖ የተነሳ ኅወሓት ብቻ ነበር ብል ትክክል ነኝ፡፡››

‹‹… [ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ስለመልቀቃቸው] በሁሉም ሐሳቦች እንግባባለን ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም አለመግባባቱ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንድለቅ የሚያደርገኝ አይደለም፡፡…››

‹‹… [የግል ፕሬስ ላይ ስለመጻፋቸውና ለቃለምልልስ ስለመገኘታቸው] ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ስለ ሀገሩ የመናገር፣ ሐሳብ መስጠትና ለውጥ የማምጣት ዕድል እንደተሰጠው እኔም እሱን እያደረግሁ ነው፡፡ ሐሳቤን መግለጽ ደግሞ መብቴም ግዴታዬም ነው፡፡…››

‹‹…[ሐሳባቸውን መግለጽ ስለሚፈሩ ምሁራን] ሐሳብ የሌላቸው ወይም እልም ያሉ አድርባዮች ይሆናሉ - እነዚህ ምሁራን፡፡ በተረፈ ግን ስህተትም ቢሆን ዝም ከማለት ተናግሮ ሐሳብን ማስተካከል ይሻላል፡፡…››

‹‹…[ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገር ውስጥ የግል ሚዲያ ቃለ ምልልስ ስለአለመስጠታቸው] ይሄን ጥያቄ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢመልሱት ይሻላል፡፡…››

‹‹… ኢህአፓዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ ፕሮግራም አልነበራቸውም፡፡…››

‹‹…የሽግግር ዘመን መንግስት ሊመሰረት በነበረ ጊዜ ቀንና ሌሊቱ [መገንጠል እንፈልጋለን የሚሉትን] በልመና ነበር ያሳለፍነው፡፡…››

‹‹…ባለፉት መንግስታት በተሰራበት ግፍ አሁንም ሕዝቡ ያለው ምሬት ቀላል አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱና ልማቱ ካልተፋጠነ ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡…››

‹‹…የአማራም ሕዝብ ቢሆን በስሙ ተነገደ እንጂ አልተጠቀመም፡፡…››

‹‹…[‹እስከ መገንጠል› ከሚለው አንቀጽ ሌላ ስለማስገባት] አንተስ ሌላ አማራጭ የነበረ ይመስልሃል? በርካታ ድርጅቶች ወዲያው ለመገንጠል ነበር የፈለጉት፡፡… ይህም ሁሉ ሆኖ እኮ ነው እነኦነግ ጥለው የወጡት፡፡››

‹‹…[በግንቦት 20 ወንድም ወንድሙን እንዴት እንደገደለው ስለማውራት] ብሔራዊ አንድነታችንን ስለሚያጠናክር በደንብ መነገር አለበት…››

‹‹…[ስላለፈው በደልና እልቂት ማውራት ስለማቆም] ገና መቀጠል አለበት፡፡ መቼም ማብቃት የለበትም፡፡…ግንቦት 20 ሲደርስ እንደነገሩ ይወራል እንጂ ገና በብቃት አልተነገረም፡፡››

‹‹…ልጆች ከህፃንነታቸው ጀምሮ የነበረው ግፍ መረዳት አለባቸው…››

‹‹…ሲስተሙ መስተካከል አለበት እንጂ ዛሬም ነገም ከመቶ ዓመት በኋላም መነገር አለበት ነው የምለው፡፡…››

‹‹…‹ጠላት› የሚለው ቃል፣ ‹የውጭ ጠላት›፣ ‹የሃገር ጠላት› ተብሎ መለየት አለበት የለበትም የሚለው አንፃራዊ ነው፡፡ ይህን የስነልሳን ሰዎች ሊያጠኑት ይችላሉ፡፡… ለሌላውም ሰው ቢሆን የነበረውን ስርዓት ማየትና የመጣውን ለውጥ ማሰብ እንጂ ቃል ላይ አተኩሮ መንገፍገፍ የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡…››

‹‹… [የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም አደጋ ላይ ስለመሆን አለመሆኑ] ነፍጠኛ ሳይሆን ሰራተኛ ትግሬ ወደሌላ ብሔር እየሄደ ነው፣ አማራም ነፍጠኛ ሳይሆን ሰራተኛ ሁኖ ወደሌላ እየሄደ ነው፡፡… አጀማመሩ አበረታች ነው፡፡… ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በአስተዳደር፣ በአመለካከት የአያያዝ ችግሮች አሉ፡፡…››

‹‹ሙስና አለ፡፡››

‹‹…ከቁጥጥር ውጭ የወጣ ሙስና የለም፡፡…››

‹‹የሀገሪቱ እድገት መኖሩ ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡…››

‹‹…የከተማው ሕዝብ ኑሮው እየከበደው ሄዷል፡፡… ይህ ግንዘቤ ተወስዶበት፣ ምክንያቱ  ታውቆ የማስተካከል እርምጃ እየተደረገ ነው፡፡…››

‹‹…የዋጋ ግሽበቱ ደመወዝተኛውን ወደማይጎዳበት ሁኔታ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነኝ፡፡››

‹‹…[በኢሕአዴግ ውስጥ ስለግለሰቦች መጉላት] የበላይነቱን ለማረጋገጥ ብሎም ከሥርዓቱ በላይ ለመሆን ያሰበም እንቅስቃሴ የጀመረም የለም፡፡… አንዳንዶቻችን ተገደን ከወረስነው የሰው አምልኮ አመለካከት በህሊናችን የማሰብ የበላይነት ጎልቶ ታይቶን ሊሆን ይችላል፡፡…››

‹‹…በእኔ አመለካከት አባይን የደፈረው መለስ ይቅርና ኢሕአዴግም አይደለም፡፡››

‹‹…ኢሕአዴግ በፈጠረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም… የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው ደፈሩት የምለው፡፡››


ሌላም፣ ሌላም

  • በኢትዮጵያ የግብረ-ሰዶማውያን ቁጠር 16ሺ ደረሰ፤ አንድ ግብረሰዶማዊ 75 የወንድ (የወሲብ) ጓደኛ አለው፡፡ - የኛ ፕሬስ

  • 1.5 ሚሊዮን ካሬ መሬት ተዘረፈ - መሰናዘሪያ

  • ኢትዮጵያ ከወርቅ ሽያጭ ሪከርድ የሰበረ ትርፍ አገኘች - መሰናዘሪያ

  • ከስድስት ጊዜ በላይ የትራፊክ ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃዳቸውን ሊነጠቁ ነው - ሪፖርተር (ረቡዕ)

  • ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ጨምሮ የቀድሞ የኅወሓት ባለስልጣናትን ለምስክርነት ለማጓጓዝ 20,000 ብር ተዋጣ - ሰንደቅ

  • አንድነት የረሃብ አድማ ያደረጉ ታሳሪዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠየቀ - ሰንደቅ

  • በቴዲ አፍሮ በከፈትኩት የፌስቡክ አካውንት የአበሻ ሴቶችን ታዘብኳቸው - ቃልኪዳን

  • እነ እስክንድር ነጋ ለውሳኔ በድጋሚ ተቀጠሩ - ፍትህ


‹‹…. የዕለቱ የቀኝ ዳኛ ሁሴን ይመር፣ ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙን መርምሮ አለማጠናቀቁን ገልፀው ለውሳኔ ለሰኔ 20 ቀን 2004 ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡…››

  • የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እግር ሊቆረጥ ይችላል ተባለ - ፍትህ

  • ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለምስክርነት አይቀርቡም - ፍትህ


‹‹…አቃቤ ሕግ… የተከሳሽን መከላከያ ምስክሮች ማድመጥ እንደማያስፈልግ ከገለፁ በኋላ በአቶ አስገደ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለሐምሌ 26 ቀን 2004 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡…››

ስፖርት

‹‹ሉሲዎቹ›› የአትሌቶቻችንን ገድል ለመድገም የቻሉ ጀግኖች ሆነዋል፤ ቀዳማይት እመቤት አዜብ መስፍን የበላይ ጠባቂ ሆነዋል - የኛ ፕሬስ

የመጽሄትና ጋዜጦቹ ርዕሰ አንቀጾች

  • የ2005 ረቂቅ በጀትና የኢሕአዴግ የብልጭልጭ ኢኮኖሚ - ፍኖተ ነፃነት

  • አዲስ አበባን የወጠረ የመንግስት ዝምታ - የኛ ፕሬስ

  • ለምግብ ዋስትና በጀት አለመያዙ ለዋጋ ንረቱ አለመታሰቡን አጉልቶ ያሳያል (ዜጋ ሁሉ የበይ ተመልካች እየሆነ መቀጠሉ አሳሳቢና አደናጋሪነቱ መቋረጥ ይገባዋል) - መሰናዘሪያ

  • መንግስት የግል ዘርፉን ይደግፍ! ያበረታታ! - ሪፖርተር (ረቡዕ)

  • የአዲስ አበባ 125ኛ በዓል ከማክበር ባሻገር - ሰንደቅ

  • ፍትህ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የህዝብ ድምፅ ነች - ፍትህ

  • በሰንዓ የኢትዮጵያን መከራ - ላይፍ

  • በስብሰባ ብዛት የበለፀገች ሀገር - ቆንጆ

  • ‹‹ልማት እንደምስማር ከላይ ወደታች የሚመታ ሳይሆን እንደ እንጉዳይ ከመሬት የሚፈላ ነው›› - የድሬደዋ ገበሬ - አዲስ አድማስ

  • ኢሕአዴግ ራሱንም አገርንም ከማፈሪያነት ይጠብቅ! - ነጋድራስ

  • ነፃው ፕሬስ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው - ኢትዮ ቻናል

  • ዓሣውን ለማግኘት ወንዙን ማድረቅ!? - አዲስጉዳይ

  • ኢትዮጵያ በአይምሬው የሙስና ቫይረስ ተጠቅታለች - ሪፖርተር (እሁድ)

No comments:

Post a Comment