Thursday, June 7, 2012

ልማታዊ ጋዜጠኛነት ወይስ ይሁንታን ማምረት?

በዚህ ጽሁፍ የማቀርብላችሁ ርዕሰ ነገር ልማታዊ ጋዜጠኝነትን ይመለከታል፡፡ አዲስ ጉዳይ መጽሄት በተከታታይ እትሞቿ ስለ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የተለያዩ ሰዎችን ሙግት ይዛ ቀርባ ነበር:: መጽሄቷ አንጋፋ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑትን አቶ ማእረጉ በዛብህን ቃለ መጠይቅ በማድረግ እና በመቀጠልም የኝህኑ መምህር ጽሁፍ ‹አንዳንድ ነጥቦች ስለ ልማታዊ ጋዜጠኝነት› በሚል ርዕስ ለአንባቢ አቅርባለች:: ከቃለ መጠይቁም ሆነ ከቀረበው ጽሁፍ በመነሳት በሀገራችን ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚባለው የጋዜጠኝነት ዘውግ እየተተገበረ ነው ማለት ያዳግታል የሚል ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን:: በእውነቱ ከሆነ የአቶ ማእረጉ አቋም የኔም አቋም ነው:: ከዚህም ባሻገር የፍትሑ አምደኛ ኃይለመስይቀል በሸዋምየለህ ደግሞ ‹‹በኢትዮጵያ የነጻው ፕሬስ እየተደመደመ ነውን?›› እያለ ይጠይቃል:: ነገር ግን በዚህ በሳቸው ጽሁፍ አነሳሽነት ሁለት ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ዝምድና ያላቸው ወጣቶች ‹‹የለም፤ የአቶ ማእረጉ ድምዳሜ ስህተት ነው›› ይሉናል :: እንዳውም ‹‹አቶ ማእረጉ ሆነ ብለው እውነታውን ለመካድ በመሻት ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ የለም የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ካልደረሱ በቀር፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊካድ በማይቻል ሁኔታ የልማታዊ ጋዜጠኝነት ውስን ዘውጎች በመንግስት መገናኛ ብዙሐን እና በአንድ አንድ FM ራዲዮን ጣቢያዎች እየተተገበሩ ናቸው›› ሲሉ የክርክር ነጥባቸውን አቅርበዋል::

የነዚህ ሁለት ወጣቶች አቋም የነሱ ብቻ አቋም አድርጌ አልመለከተውም:: የመንግስትም አቋም እንደሆነ አምናለሁ:: አለመታደል ሆኖ እንጂ መንግስት ለዲሞክራሲ መጎልበት እንዲህ መሰረታዊ ፋይዳቸው ላቅ ያሉ ጉዳዮችን አደባባይ አውጥቶ ሕዝባዊና ምሁራዊ ክርክሮች እንዲካሄዱ ከመፍቀድም አልፎ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት ግን አልሆነለትም፤ ወደ ምክንያቶቹ አልሄድም የጽሁፌ ትኩረት አይደለምና። የግል መገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ ጥቂቱ በሀገር ውስጥ ግማሹ ከሀገር ውጪ በመሆን እንዲህ ያለውን ጉዳይ በተንጠባጠበ እና አልፎ አልፎ በሚነሳ የአምድ ማሟያነት ከክርክር ባለፈ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም በሰፊው ለመስራት በሞከሩ ነበር: ምንም እንኳ የእስካሁኑ ሙከራቸው ቢያስመሰግናቸውም፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው/አይደለም የሚለው ክርክር በልማታዊ ጋዜጠኝነት ኀልዮቶች ላይ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም:: በእርግጥ የ”ልማታዊ” ጋዜጠኝነት ኀልዮቶችን ፋይዳ እና መገለጫዎቹን የ”ልማታዊ” ጋዜጠኞችን ስነ ምግባር እና ሌሎችንም ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር ቅርበት ያላቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በሙሉ መነጋገርም መወያየትም ተገቢ ነው:: ነገር ግን ይህን የመሰለ ሀገራዊ አብይ ጉዳይ በኀልዮት ደረጃ ብቻ ተወያይቶ ወይም “ምናምን” ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፤ በሚባለው ራድዮ ጣቢያ አንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ ምንትስ ስለሚባል ሰፈር ወጣቶች ድህነትትን ለመዋጋት በማህበር ስለመደራጀታቸው ሰምቻለሁ:: ምንትስ በሚባለው FM ራድዮ ዜጎች ያለ ፍርሃት በስነተዋልዶ ጤና ሲወያዩ ሰምቻለሁ፣ አይቻለሁ፤ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ማውራት ይችላል ለሚሉ ባልዳረባዎቼ እኔ ልላቸው የምችለው ነገር ቢኖር እነዚህ የክርክር ነጥቦች የየዋህነት አልያም የጅልነት ወይም ደግሞ አውቆ የተኛ ዓይነት የመከራከሪያ ነጥቦች ናቸው:: ምክኒያቱም ልማታዊ ጋዜጠኝነት በኀልዮት ደረጃ እንኳ በቅጡ ያልተደላደለ ወጥ የሆነ የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር የሌለው ከምዕራባዊያን የጋዜጠኝነት ባህል እንኳ በምን እንደሚለይ ጥርት ባለ ሁናቴ ሳይታወቅ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ያለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ነው ብሎ በችኮላ ከመደንገግ በፊት የሀገራችንን የሚዲያ መልክዐ ምድር(Media Landscape)፣ ህጋዊ ዳራቸውን እና ጋዜጠኞቻችን ሙያቸውን እየተገበሩ ያሉበትን አውድ በሚገባ ዘርዘር አድርጎ ማየቱ ይቀድማል ብዬ ስለማምን ነው:: ከዚህም ባሻገር የመገናኛ ብዙሃን የሥራ ባህል እና የጋዜጠኝነት ልምድ ትንተና ባንድ አገር ውስጥ ካላቸው ተጨባጭ ኹኔታ ነው መጀመር ያለበት። እስቲ ተጨባጩን የአገራችንን የመገናኛ ብዙሐን የሥራ ባህል እና የጋዜጠኝነትን ስራ አንኳር ነጥቦች በወፍ በረር እንቃኛቸው፦

የኢቴቪ ልማታዊነት ሲጠየቅ

በሀገራችን የሚዲያ መልክዐ ምድር ላይ የሚገኙትን እድሜ ጠገብ እና ሰፊ ጂኦግራፊያዊ ተደራሽነት ያላቸውን የመገናኛ ብዙሃን፦ ኢቴቪ፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ እና አዲስ ዘመንን ጨምሮ በየክልሉ የሚገኙትን የመገናኛ ብዙሐንን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው መንግስት ነው:: ይህም በአዋጅ የተረጋገጠለት መብቱ ነው:: ነገር ግን መንግስትም ይሁን ግለሰብ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የትኛውም የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ትርፍን ከማጋበሻነት በተጨማሪ የባለንብረቱን የፖለቲካ አቋም ማራመጃ ለመሆን ምቹ ነው:: በዚህ ጉዳይ ላይ የመገናኛ ብዙሃንን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ(Poletical Economy of the Mass Media) በመተንተን እውቅ የሆኑት ኖኦም ቾምስኪን እና ኤድዋርድ ሄርማን በ 1988 “ይሁንታን ማምረት” (Manufacturing Consent: The Political Economy of the Mass Media) በሚል ርዕስ ካሳተሙት መጽሃፍ የፕሮፓጋንዳ ሞዴል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሀገራችንን የመገናኛ ብዙሃን መልክዐ ምድር እና የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ በደንብ አድምቶ ስለሚገልጽልኝ ዋቤ አድርጌ ከዚህ እንደሚከተለው እጠቀስዋለሁ (ትርጉም ራሴ)፦

“መሰረታዊ የሀብት እና የፖለቲካ ስልጣን ክፍፍል መዛነፍ በሰፊው በሚስተዋልባቸው ሀገራት መገናኛ ብዙሐን ስልታዊ በሆነ ዘዴ የሚስተዋለውን አለመመጣጠን የማድበስበስ ታላቅ ሚናን ይጫወታሉ:: በተለይም የስልጣን መዘውሩን የሚቆጣጠሩት ጥቂት ቢሮክራቶች ከሆኑ እና ሞኖፖላዊ የመገናኛ ብዙሐን ቁጥጥር የሰፈነበት ስርዐት ከሆነ በተለይ ደግሞ ሕጋዊም ሆነ ሕገ ወጥ (ጭማሪ ከራሴ) የቅድመ ምርመራ አሰራርን የሚያበረታታ ከሆነ የመገናኛ ብዙሐን ስልጣን ላይ ለሚገኙት ልሂቃን ጥቅማቸውን ማስጠበቂያ መሳሪያ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው:: (ገጽ 1፤ 1988)

ይህ ማለት ደግሞ መንግስታት የህዝቡን አስተያየት በመገናኛ ብዙሐን በኩል በሚገባ ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ዕድል ይፈጥርላቸዋል ማለት ነው:: በዚህም መሰረት መንግስታት በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙትን መገናኛ ብዙሐን በመጠቀም ህዝቡ ወይም ጋዜጠኛው በራሱ ተነሳሽነት የመረጠውን ርዕሰ ጉዳይ ወይም በወቅቱ እየሆነ ያለውን እንገግጋቢ የመገናኛ ብዙሐንን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ወደ ጎን በመተው የራሳቸውን እጀንዳ ማራጋቢያ እና የኢኮኖሚ ጥቅም ማስጠበቂያ ያረጉታል ማለት ነው::

ለጥቄ ይህንን በምሳሌ ላስረዳ ተከተሉኝ:: በሀገራችን የሚዲያ መልክዐ ምድር ላይ ከላይ ከጠቀስኩት የቾምስኪ እና የሄርማን ኀልዮት አንጻር በግሉም ሆነ በመንግስት የመገናኛ ብዙሐን የሚስተዋሉ የባለቤትነት ቁጥጥር ምሳሌዎችን በደምሳሳው ልጠቃቀስ:: ላካሄድ እንዲያመቸን ከስርጭት ሽፋን ተደራሽነት እና ስለ መንግስት መገናኛ ብዙሐን በዓይነ ህሊናችን ስናስብ ሁልዜም ድቅን ስለሚልብን የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ፊት አውራሪ ከሆነው ኢቴቪ ልጀምር:: መንግስት ኢቴቪን ልክ እንደ ሐረር ሰንጋ ገመድ በአንገቱ ላይ አስሮ ወደ ፈለገበት እንደሚነዳው ከሚያሳብቅበት የመገናኛ ብዙሐን ቀዳሚው ነው:: በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ላይ የፍልስፍና ዲግሪ ጽሁፋቸውን የጻፉት ኖርዊያዊው ቴርዬ ስካርድል (Terje S. Skjerdal) በ2008 “Conflicting professional obligations among government journalists in Ethiopia” በሚል ርዕስ ካሳታሙት የጆርናል ጽሁፍ በመጥቀስ የክርክር ነጥቤን ላጠናክር ለነገሩ የኢቴቪን የመንግስት አፍነት ለማስረዳት ምስክር መጥቀስ አያሻውም:: ከወቀሳ ለመዳን ግን (Terje) ቴርዬ የጆርናል ጽሁፍን ሲጽፍ በማስረጃነት የተጠቀመውን ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የኢቴቪ የእንግሊዝኛ ዴስክ ከፍተኛ ረፖርተር በህዳር 2000 የኢትዮጵያ የፕሬስ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ስለነበረው የፕሬስ አዋጅ የተቃውሚ ድምጾችን ያካተተ የዜና ዘገባ በመስራቱ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚንስትር ከነበሩት ከአቶ በረከት ስሞኦን የደረሰበትን ጫና እንዲህ ያስረዳል (ትርጉም ከራሴ)፦

“የፕሬስ አዋጁ በጣም አፋኝ ነው የሚል አስተያየት የሚሰጡ በርካታ ሰዎች እራሱ አቶ በረከት ስሞኦን በሚመራው በፕሬስ አዋጁ ዙሪያ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ በሰፊው ይደመጡ ነበር:: በመሆኑም በማታው የዜና እወጃ ሰዐት በዚህ ዙሪያ ባዘጋጀሁት የዜና ዘገባ ላይ የነዚህን ሰዎች እስተያየት አካትቼ አቀረብኩ::”

“በማግስቱ ግን እዛው ኢቴቪ ሕንጻ ላይ ይገኝ ከነበረው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ስልክ ተደውሎ ተጠራሁ:: ሚንስትሩ በሰራሁት የዜና ዘገባ ተበሳጩብኝ:: ለምንስ እንዲህ ዓይነት ዜና እንደሰራሁ ጠየቁኝ:: እኔም ዜናው ባላንስ እንዲኖረው ወይም ሚዛናዊ እንዲሆን ነው ስል ያለ ምንም ፍርሐት ላስረዳችው ሞከርኩ:: እሳቸው ግን ይህ የባላንስ ወይም የሚዛናዊነት ጉዳይ አይደለም:: ይህ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን እንደ መሆኑ መጠን መስበክ ያለብህ ሰለመንግስት ነው:: አሉኝ”::(ገጽ 6፤ 2008)

ሌላ ምሳሌ ልጨምር:: መሐመድ ሰልማን በ2011 ፒያሳ መሃሙድ ጋር ጠብቂኝ በሚል ርዕስ ካሳተመው የወጎች እና የመጣጥፎች መድብል መንግስት በመገናኛ ብዙሐን ላይ ያለውን ቁጥጥር እና የቾምስኪን እና የሄርማንን ኀልዮት ስነ ጽሁፋዊ ለዛ ባለው መንገድ ስለሚያስረዳልኝ ኢቴቪ እና ተዛማጅ ትዝታዎቼ ከሚለው መጣጥፍ የኢቴቪ የዜና ቀመር የሚለውን ቃል በቃል እንደሚከተው ገልብጨዋለሁ::

“ኢቴቪ አንድን ዜና ዘለግ ላለ ጊዜ እያቦካ የመጠቀም ባህል አለው:: ለምሳሌ ከአላማጣ ማይጨው መንገድ ሊሰራ ነው ብለን ብናስብ ከሚሰራው መንገድ ይልቅ ዜናው እንደሚረዝም በዚህ መልክ ማየት እንችላለን:: በትንሹ ከአንድ መንገድ አሥር ዜናዎች ይፈለፈላሉ::

  1. ከአላማጣ ማይጨው የሚደርሰውን የጠጠር መንገድ ወደ አሥፋልት ለማሳደግ የሚያስችል ብድር ከቻይናው ማክሲም ባንክ ተገኘ።

  2. ከአላማጣ ማይጨው የሚደርሰውን መንገድ ለመስራት ከቻይናው ሲራቢሲ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተካሔደ::

  3. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደውን መንገድ ለመጀመር የመሰረት ድንጋይ ተጣለ::

  4. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ ተጀመረ::

  5. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው ተባለ::

  6. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በመጓተቱ ነዋሪዎች ተቸገርን አሉ::

  7. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ 65 በመቶው ተጠናቀቀ::

  8. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ተባለ:

  9. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ::

  10. ከአላማጣ ማይጨው የሚወስደው መንገድ ግንባታ በመጠናቀቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ደስታቸውን ገለጹ::


ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ዜና በ10 ተመንዝሮ ሲቀርብለት 10 ጎዳናዎች የተሰሩለት ስለሚመስለው “ይህ መንግስት ምነኛ ልማታዊ ነው” ሲል ይገረማል::” (ገጽ 73/74 2004) የህዝብ ይሁንታን ማምረት ይሉሃል ይህ ነው:: ውዱ ባልደራባዬ መሐመድ ሆይ የኖኦም ቾምስኪን እና ኤድዋርድ ሄርማን የፕሮፖጋንዳ ሞዴል ኢትዮጵያዊ በሆነ ትንትና ለማስረዳት ስራዬን ምነኛ አቀለልክልኝ?!

ከዚህ ባሻገር የመንግስት ጠንካራ የባለቤትነት ቁጥጥር በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋልበት ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንደ የአዲሱ ዘመን የመገናኛ ብዙሐን አውታር የሚቆጠረው የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ነው:: ከቴሌኮም አገልግሎቶች መሃከል የሞባይል ስልክ አገልግሎት እና ሌሎችም የመረጃ መረብ ወይም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ከ85 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በብችኝነት የሚያቀርበው አትራፊው እና ብቸኛው የኢትዮጵያ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ነው:: ስለ ቴሌኮም የአገልግሎቶት ጥራት መጓደል ተጠቃሚው በሚገባ ስለሚያውቀው በዚህ ጽሁፍ ምንም አልልም:: በዚህ ላይ ተጠቃሚው ለቴሌኮም አገልግሎቶች የሚከፍለው ዋጋ እጅግ ውድ መሆኑን የ2011 የFreedom Houseን ሪፖርት ጠቅሶ ነብዩ እያሱ ስደት በጋዜጠኛው ዓይን በሚለው አዲስ መጽሃፉ ላይ ዘግቧል:: (ገጽ 312፤ 2004):: በአንጻሩ ግን ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሰፊው ይተገበርባቸዋል በሚባሉት እንደ ህንድ ባሉ ሀገራት የቴሌኮም አገልግሎቶች የዜጎችን አሳታፊነት በማሳለጥ ዜጎች ለልማት ብቻም ሳይሆን ለመልካም አስተዳደር እና ለግልጽነት መጠናከር የድሮዎቹ የመገናኛ ብዙሐን ተብለው ከሚጠሩት እንደ ሬዴዮ እና ቴሌቪዥን ሁሉ ኅብረተሰብን በመቅረጽ ለሀገር እድገት የማይተካ ሚና ይጫወታሉ፡፡

ከላይ የተቀሱት ማሳያዎች በኢትዮጵያ ሚዲያ መልክዐ ምድር ላይ አድራጊ ፈጣሪ መንግስት መሆኑን ያረጋግጥልናል:: እላይ በጠቀስኩት የቾምስኪ እና የሄርማን ሀልዮት መሰረት ደግሞ መንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር በሚያሳድርባችው ሀገራት መገናኛ ብዙሐን የህዝብን ይሁንታ በማምረት ሥራ ነው የሚጠመዱት:: ይህንንም ሥራቸውን (ይሁንታ ማምረትን) የዳቦ ስም አውጥተውለት ልማታዊ ጋዜጠኝነት ይሉታል እንጂ ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚባል ነገር የለም፤ ለኔ ባሀገራችን የሚድያ መልክዐ ምድር ላይ ዛሬ የሚስተዋለው ከዚህ ብዙም የሚለይ አይደለም:: አቶ ማእረጉም ለማለት የፈለጉት ይህንኑ ይመስለኛል:: እስቲ አሁን ደግሞ ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሐን ሕግ አንፃር ምን ይላል::

ልማታዊ ጋዜጠኝነት ከህግ አንጻር ያስኬዳል?

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ዜጎች ዘርፈ ብዙ ከሆኑ የመገናኛ ብዙሐን መረጃን የማግኘት እና የመሰላቸውን አስተያየት የመያዝ መብታቸው ተረጋግጦላቸዋል:: በተለይ ደግም በአንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 5 መሰረት በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ መገናኛ ብዙሐንም እንኳ ቢሆኑ የአስተሳሰብ እና የአስተያየት ብዙሐነትን (Diversity of Expression and Opinion) ማረጋገጥ አለባቸው:: በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ የተደረጉበት ምክንያት ይህንኑ ለማድረግ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ የመገናኛ ብዙሐን እና የመረጃ ነጻነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 መገናኛ ብዙሐን በነጻነት ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በድጋሚ አረጋግጧል:: እዚህ ላይ እንዲተኮርበት የምፈልገው ነጥብ ታዲያ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙሀን እና የነዚሁ ድርጅቶች ምንደኛ ጋዜጠኞች የአስተሳሰብ እና የአስተያየት ብዙሐነትን በተግባር ለማረጋገጥ መትጋት አለባቸው እንጂ በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም ራሳቸውን እንደ ሀገር ገንቢዎችም ሆነ እንደ መንግስት አጋሮች በመቁጠር ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 5 ያረጋገጠውን ዲሞክራሲያዊ መብት እንዲጣስ ተባባሪ መሆን የለባቸውም:: ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትልልቅ መንግስታዊ አጀንዳዎችን ለሀገሪቱ ብቸኛና መለኮታዊ መፍትሄ አድርገው ያቀርባሉ መንግስትን የሚተቹ ዜጎችን ደግሞ ትችቱ ለምን እንኳ እንደተሰነዘረ ቀርበው እንዲያስረዱ ሳያደርጉ የሀገር ጠላቶች እና መርዶ ነጋሪ እንደሆኑ ተደርገው ይቀርባሉ:: ከሕጉ አንጻር ግን ይህ የመብት ጥሰት እንጂ ልማታዊ ጋዜጠኝነት አይደለም:: ለኔ አንድ ጋዜጠኛ በከፍተኛ የሞያ ልቀት እና የስነ ምግባር ብቃት ያለ መንግስትም ሆነ ያለ ቱጃር ተጽእኖ በነጻነት ስራውን ከሰራ እሱ ጋዜጠኛ ነው:: ከፈለጋችሁ ልማታዊ የሚል ቅጥያ ልትጨምሩበት ትችላላሁ::

ነጻ የግል መገናኛ ብዙሃንስ?

በግል የመገናኛ ብዙሐንም ቢሆን የተጋነኑ “ልማታዊ” ዜናዎች ባይስተዋልባቸውም:: በማስታወቂያ አስነጋሪዎች ተጽእኖ ምክኒያት ማስታወቂያዊ ዜናዎችን፣ ማስታወቂያዊ ዶክመንተሪዎችን እና ሌሎችንም ፕርግራሞች (Adevertorials) ማየትም መስማትም እየተለመደ መጥቷል:: በኤፍ ኤሞቻችንም ሆነ በጋዜጦቻችን አንዳንድ ዘገባዎች ላይ እነዚህን ክፉ የጋዜጠኝነት ተግዳሮቶች አልፎ አልፎ አያለሁ:: ስም ሳልጠቅስ ምሳሌ ልስጥ፤ አንድ ማንትስ የሚባል ወፍ ዘራሽ ቱጃር BIKS የሚባል ብስኩት ፋብሪካ በቅርቡ ከፍቷል ወይም አለው እንበል:: ይህ ወፍ ዘራሽ ቱጃር ብስኩቱን በገፍ መሸጥ ይፈልግ ስለነበር ማስታወቂያ ማሰራት ያስባል:: ከተማው ውስጥ ያሉት የማስታወቂያ ለፋፊ ድርጅቶች በደቂቃ ታይታ/ተሰምታ ለምታበቃ ማስታወቂያ ዋጋቸው የሚቀመስ አልሆነለትም:: በዚህ ላይ ማስታወቂያ ማስታወቂያ ነው:: በአጋጣሚ አንድ ቀን ይህ ባለሀብት ማንትስ ልማት ማህበር ባዘጋጅው ቴሌቶን ላይ አንድ ሁልግዜ በራዲዮ ድምጹን እየሰማ ባካል ግን የማያውቀውን ትንታግ ልማታዊ ጋዜጠኛ ይተዋወቃል:: አጋጣሚውንም በመጠቀም ለልማታዊ ጋዜጠኛው ማስታወቂያ ማሰራት ፈልጎ ዋጋው አልቀመስ እንዳለው ይነግረዋል መፍትሄ ካለውም እንዲያማክረውም ይጠይቀዋል:: ጋዜጠኛውም የሆነ አካባቢ ስለሚኖሩ ምንዱባን ያአኗኗር ችግር የሚመለክት የራዲዮ ዶክመንተሪ ለመስራት እያሰብኩ ነው ይህንን ፐሮግራም በአነስተኛ ዋጋ ስፖንሰር አድርግና ስለ BIKS ብስኩት ፋብሪካ ሰፋ ያለ እና ተከታታይ የዜና ዘገባ ላቅርብልህ የሚል የልማታዊ ጋዜጠኝነት ሞያዊ ምክሩን ሰጠው:: በዚህም ተስማሙ ባለጸጋውም ከፍተኛ ከሆነ የማስታወቂያ ወጪ ከመዳኑም ባሻገር በቀላል ወጪ የኩባንያውን ስም በተጋጋሚ ማህበራዊ ችግሮችን ከሚፈቱ ልማታዊ ሀገር በቀል ኩባንያዎች ተርታ ተሰለፈለት:: ህዝቡም ይህንን ልማታዊ ባለጸጋ ለሀገር አሳቢ ለደሀ አዛኝ አድርጎ ስለሚያስበው ብስኩት ሲገዛ ሁልግዜም የBIKSን ነው::

እዚህ ላይ ግን የማስታወቂያ አስነጋሪ ባለሀብቶች የዜና ሽፋን ስጠኝ እና ማስታወቂያ ልስጥህ ተጽእኖ የትም ሀገር ላይ ያለ ተጸእኖ ስለመሆኑ ዋቤ መጥቀስ አያሻውም ቢሆንም ግን እንደኛ የፋይናንስ ነጻነታቸው እጅግ ፈታኝ እና እስቸጋሪ የሚሆኑባቸው የግል መገናኛ ብዙሀን በሚገኙባቸው ሀገራት ማስታወቂያዊ ዜናዎችን በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም መስራት መፍትሄ የሌለው መሆኑን እገነዘባለሁ:: የሀገራችን በተለይ የህትመት የግል መገናኛ ብዙሐን እለት እለት እያሻቀበ የመጣውን የህትመት ዋጋ ለመቋቋም ሲሉ በዚህ ዓይነት ተጽእኖ ውስጥ መግባታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው:: ነገር ግን አሁን በሀገራችን በህትመት ላይ የሚገኙትን በተለይ ከፋይናንስ ተጽእኖ ውጪ ያሉትንም ፖለቲካዊ ጫናዎች ተቋቁመው በነጻነት ያለ ፍርሀት የጋዜጠኝነት ስራቸውን ለሚሰሩ ምስጋና ቢያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም:: እኔም ለስራቸው መገን እላለሁ::

ማጠቃለያ

የሀገራችንን የሚድያ መልክዐ ምድር በአንድ ተራራ እንመስለውና ይህንን ተራራ ለሁለት የሚከፍል ትልቅ ሸለቆ አለ ብለን እናስብ:: ከተራራው ግርጌ እስከ ጫፉ ድረስ ያለውን ምቹ እና ገላጣ ስፍራ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን የሚባሉ መጥቀስ ቢያስፈልግ፦ ኢቴቪ፣ የኢትዮጵያ ራዲዮ፣ አዲስ ዘመን፣ ሄራልድ፣ FM97.1 አሁን ደግሞ በየክልሉ ያሉ የመንግስት አዳዲስ የክልል “ኢቴቪዎች” እና የግል ወይም ነጻ የሚል ቦሎ ለጥፈው በልማታዊ ጋዜጠኝነት ስም በመዝናኛ እና ስፖርታዊ አደንዛዥ ወሬዎች አየሩን የተቆጣጠሩ የሰፈሩበት ሲሆን ተራራውን ለሁለት በሚከፍው ትልቅ ሸለቆ ውስጥ ደግሞ በመሰናክሎች የተተበተቡ ከህዝብ ጋር ለመገናኝት ወደ ተራራው ገላጣ ስፍራ ለመውጣት ሙከራ ሲያደርጉ በሸለቆው ዳር እና ዳር የቆሙ እና ሰፊውን የተራራ ከፍል የማያስደፍሩ ሰዎች መልሰው ወደ ሸለቆው የሚከቷቸው ራሳቸውን የነጻው ፕሬስ አባላት እያሉ የሚጠሩ በተራራው ገላጣ ስፍራ የሚገኙት ደግሞ የግል ሚዲያ እያሉ የሚጠሯቸው የሚገኙበት የተራራው ክፍል ነው:: በዚህ ዓይነት የሀገራችን የሚዲያ መልክዐ ምድር ታዲያ ሊኖር የሚችለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት ወይስ የጋዜጠኝነት ጣዕረ ሞት?

------

የዚህን ጽሁፍ አቅራቢ በendalk2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

 

2 comments: