Wednesday, June 20, 2012

የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ አወዛጋቢነት

የቴሌኮም ማጭበርበር ሕጉ አወዛጋቢነት የሚጀምረው ‹‹አዋጁ ፀድቋል፣ አልፀደቀም?›› የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ስንጀምር ነው፡፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ በግንቦት 18፤ 2004 እትሙ ‹‹አዋጁ ፀድቋል›› ብሎ ቢዘግብም ለገዢው ፓርቲ በሚወግኑ ጽሁፎቹ የሚታወቀው ጦማሪ ዳንኤል ብርሃነ ደግሞ ገና ‹‹የመጀመሪያውን የንባብ ደረጃ ማለፉ ነው›› ይላል፡፡ ፍኖተ ነፃነትም በበኩሉ በሰኔ 12፤ 2004 እትሙ ‹‹ፍርሀት የወለደው የቴሌ አፋኝ ረቂቅ ሕግ›› ባሰኘው ጽሁፉ ገና ረቂቁ በፓርላማ እንደቀረበ ነገር ግን ከፓርላማችን ያለፈ ልምድ መረዳት እንደሚቻለው ‹‹የቀናት ጉዳይ ነው እንጂ መጽደቁ እንደማይቀር›› ያትታል፡፡

በአገራችን ረቂቅ ሕጎች የሚመለከተው ሕዝብ’ጋ በግልፅ ሳይደርሱ በጭምጭምታ ይቆዩና ድንገት በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ሕግ የመሆናቸው የተለመደ ድራማ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ይለወጣል ብሎ መገመት ሞኝነት ነው፡፡ ይሄም ጽሁፍ በጭምጭምታው እውነታነት እና በረቂቅ ሕጉ ዙሪያ መጠነኛ ትንታኔ ይሰጣል፡፡

በቃሉ ኃይሉ (ስሙ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል የተቀየረ) በስካይፕ የሚያወራው ከሚናፍቃቸውና ባሕር ማዶ ከሚኖሩ፣ እሱን ለማግኘት ኮምፒዩተር ላይ ቁጭ ብለው ከሚጠብቁት ጓደኞቹ’ጋ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹እኔ እስከማስታውሰው ድረስ›› አለ ለዞን ዘጠኝ አስተያየቱን ‹‹እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፤ ምንም ዓይነት ሕግ ሲወጣ ብወደውም ብጠላውም እታዘዝለት ነበር፡፡ አሁን ግን በስካይፕ ማውራት ሕገ-ወጥ ከሆነ ከጓደኞቼ እና ከሕጉ መምረጥ ሊኖርብኝ ነው፡፡ ጓደኞቼን ከሕጉ የማስበልጥበት ምክንያት እስካሁን አይታየኝም፡፡›› በቃሉ ይህንን የተናገረው አዋጁ ስካይፕ መጠቀምን በወንጀልነት ፈርጆታል የሚለውን ወሬ ከሰማ በኋላ ነው፡፡

‹‹የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጁ›› ከስያሜውና ከትርጉም ክፍሉ ውጪ 18 አንቀጾች ብቻ አሉት፡፡ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልክ ማስደወልም ሆነ ሌሎች የቴሌኮም አገልግሎቶችን ያለ ኢትዮ ቴሌኮም እውቅና መስጠት የማይቻል መሆኑ ድሮም በሕግ የተደነገገ ቢሆንም አሁን የዚህ አዋጅ መውጣት አስፈላጊ የሆነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማሕበራዊ ደረገጾች ላይ እያደገ የመጣውን ፀረ-አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት ለመገደብ እንደሆነ ብዙዎች መጠራጠር ጀምረዋል፡፡ የአዋጁ መግቢያ ላይም እንዲህ የሚል ይነበባል፡፡ ‹‹…የቴሌኮም ማጭበርበር ከኤኮኖሚ ኪሳራውም ባሻገር ዋና የደህንነት ስጋት በመሆኑ…›› ህግ አውጪው በረቂቅ አዋጂ ከኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ባለፈ ለሃገር ደህንነት ማሰቡን በግልጽ ይናገራል፡፤(በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አዋጁ የተጣቀሰው ከእንግሊዝኛው ቅጂ ሲሆን ትርጉሙ የዞን ዘጠኝ ነው፡፡)

ኢሕአዴግ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚያደርገው ቅጥ ያጣ ጥበቃ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ትችቶቹን በሐሳብ ማሸነፍ እንዳቃተው ያሳብቃል፡፡ በጥቅሉ የመረጃ መረብን እና በዋናነት ማሕበራዊ ድረገጾችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱት የመረጃ ምንጮች እንደ ዶ/ር ዳኛቸው አባባል ‹‹የመረጃ ኦና.›› (Information Vacuum) ለመፍጠርና አውራ ፓርቲው ‹የሕዝብ› መገናኛ ብዙሐንን በመጠቀም የሚያጮኻቸው ወደአንድ አስተሳሰብ ያዘነበሉ መረጃዎች ለሚፈጥሯቸው የገደል ማሚቱ ድምጾች እንቅፋት ሆነዋል፡፡


ከቻይና ምን መማር?
‘ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ’ የተባለ የጋዜጠኞች ድንበር የለሽ ቡድን ቻይናን ‹ከኢንተርኔት ጠላቶች› አንዷ እንደሆነች ያስቀምጣታል፡፡ የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ልኡካን ቡድን ደግሞ በአዲስ አበባ ለሚገኘው አቻው - ኢሕአዴግ በብዙሐን መገናኛ እና ኢንተርኔት አስተዳደር  ዙሪያ ያካበተውን ልምድ አካፍሎ ተመለሰው በቅርብ ጊዜ እንደሆነ በገዢው ፓርቲ ድረገጽ ላይ የሰፈረው ዜና ያስረዳል፡፡

ቻይና ‹‹የምዕራቡ ዓለም የመረጃ ነፃነት ባሕል የአገሬን ባሕል ያጠፋል›› በሚል ስም ለበርካታ ብዙሐን መገናኛ በሯን ዘግታለች፡፡ ለቻይና ብቻ ተብሎ የተዘጋጀው ጉግል አንዳንድ የኮሙኒስት ፓርቲን የሚያስቀይሙ ቃላቶችን እንዳይፈልግ ተደርጎ በልኳ ተሰፍቶላታል፡፡ ፌስቡክና ትዊተርም ታግደዋል፡፡

የቻይና የፍቅር ልጅ የሆነችው ሃገራችን ከቻይና በቀሰመችው ልምድና ቴክኖሎጂ የቪኦኤና የዶቼቬሌን ሬዲዮ ጣቢያ ማፈኗን መንግስቷ አምኗል፡፡ በርካታ ድረገጾችም ታግደዋል፡፡ አንድ የዞን ዘጠኝ አባል በግሉ ባደረገው ቅኝት 65 ነፃ ድረአምባዎች፣ 14 የፓርቲ እና ለፓርቲ የሚወግኑ ድረአምባዎች፣ 37 ጦማሮች፣ 7 የበይነመረብ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች እና 37 የፌስቡክ ቡድን ገጾች በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ መደረጋቸውን አረጋግጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አዲሱ አዋጅ በመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አርቃቂነት ለፓርላማ የቀረበው፡፡ ‹አዲሱ አዋጅ ምን ዓይነት በቀላሉ ትርጉማቸው ሊጠመዘዝ የሚችሉ አንቀጾች አሉት? የማሕበራዊ ድረገጽ እንቅስቃሴዎችን እንዴት ያውካቸዋል? ሐሳብን በነፃ ከመግለጽ መብት አንጻርስ አዋጁ እንዴት ይታያል? ስካይፕና ጉግል ቶክን የመሳሰሉት በVoice over Internet Protocol (VoIP) የሚጠቀሙ አገልግሎቶችን ሕገወጥ ያደርጋቸው ይሆን?› የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ እና ለማብራሪያ ክፍት የሆኑ አንቀጾችን ከዚህ በታች እንጠቃቅሳለን፡፡

አወዛጋቢዎቹ አንቀጾች
በአዋጁ ክፍል አንድ በተለዩ ቃላት ትርጉሞች ላይ የሚከተሉትን ያስቀምጣል፡፡ አንቀጽ 2 ላይ ‹‹የቴሌኮሙኒኬሽን ቁሳቁስ ማለት ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት የዋለ ወይም ሊውል የታቀደ ዕቃ፤ መገጣጠሚያ (accessories) እና ሶፍትዌሮችን ጨምሮ ማለት ነው፡፡›› ይላል፡፡ አንቀጽ 1 ላይ ‹የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት› የሚለውን ሲተረጉም በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚቀርቡ ጽሁፎች እና ምስሎች ከአገልግሎቱ እንደሚካተቱ ጠቁሟል፡፡ ሶፍትዌሮችን በዚህ ትርጉም ውስጥ በማካተት የተከታይ አንቀጾችን ትርጉም በዚያ መልክ እንድናይ ያስገድደናል፡፡

ክፍል ሁለት፣ አንቀጽ 3 ‹‹ሚኒስትሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር የትኞቹ የቴሌኮሙኒኬሽን ቁሳቁሶች፣ አምራቾች፣ ገጣጣሚዎች፣ አስመጪዎች ፈቃድ እንደማይሹ ይገልጻል፤ ደንብ ያበጃል›› ይላል፡፡ ይህም በሚኒስትሩ (ሚኒስትሩ የሚባለው የኢንፎርሜሽን እና ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው፡፡) ያልተዘረዘሩ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ተጠቃሚውን በወንጀልነት እስከ 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና እስከ 40,000 ብር በሚደርስ ቅጣት፣ አስመጪ እና አከፋፋይ ድርጅቶችን ደግሞ ‹‹..ከ10 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከ100,000ብር እስከ 150,000 ብር የሚደርስ ቅጣት..›› ሊያስከትልበት እንደሚችል ረቂቁ ይደነግጋል፡፡

የዚህ አንቀጽ ለትርጉም ክፍት መሆን የምንጠቀምባቸው የበይነመረብ ማሰሻዎች (Internet browsers)፣ ሶፍትዌሮች (skype, google talk…)፣ የስልክ ቀፎዎች (blackberry, iPhone, Android ስልኮች፣ ወዘተ…)፣ እና ሌሎችም ዓይነት በሚኒስትሩ ይወሰናሉ፣ ካልተወሰኑ ደግሞ ለመጠቀም ፈቃድ ያስፈልጋል የሚል አንድምታ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡(የጆሮ ማዳመጫ /head set/ የተጠቀመ ሰው ያልተፈቀደ መሳሪያ ገጣጥሞ ተጠቀመ ቢባል ሊስቀጣው ነው ማለት ነው እስከሚል የተለጠጠ ትርጉም ድረስ ሊወስደን ሁሉ ይችላል::)

አንቀጽ 6(1) ደግሞ ‹‹ማንም የቴሌኮም መረብን ወይም መሳሪያን በመጠቀም በፀረሽብርተኝነት አዋጅ 652/2001 መሰረት የሽብር መልዕክት ቢያሰራጭ ወይም በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት የሚያስጠይቅ አጸያፊ መልዕክት ቢያሰራጭ… ከ3 እስከ 8 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከ30,000 እስከ 80,000 ብር ድረስ ይቀጣል›› ይላል፡፡በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰውን ወንጀል መፈጸም በዚህ ህግ ቢካታትም ባይካተትም ማስጠየቁ የማይቀር ሆኖ ሳለ በድጋሚ የተለየ ሽፋን መስጠቱ የህጉን አስፈላጊነት እንድንጠይቅ ያስገድደናል፡፡

አንቀጽ 13 ‹‹የቴሌኮም ማጭበርበርን ለመከላከል፣ ለመመርመርና ለመቆጣጠር ብሔራዊ የቴክኒክ ሥራ ቡድን ከሚመለከታቸው አካላት ተውጣጥቶ ይቋቋማል፡፡››

አንቀጽ 14 ‹‹ፖሊስ የቴሌኮም ማጭበርበር ተከስቷል ወይም ሊከሰት ይችላል ብሎ ባመነ ጊዜ ከፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መጠየቅ ይችላል፡፡›› ይህም የአንድ ሰው የስልክ ንግግር፣ አጭር የጽሁፍ መልዕክቶች፣ የኢሜይል መልዕክት ልውውጦች እንደአስፈላጊነታቸው የሚበረበሩበትን የሕግ አግባብ ይሰጣል ማለት ነው፡፡ መንግስት የኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ ለአገሪቱ ደህንነት የሚያሰጉ ነገሮች ካሉ መቆጣጠር አለበት የሚለው ነጥብ ላይ መስማማት ቢቻልም የግለሰቦችን ነፃነት በተራ ፍራቻ ማሳጣት ግን ከሰብአዊ መብት ጥሰት ውስጥ ሊመደብ ይችላል፡፡

ህጉ በአጠቃላይ ካሉበት መሰረታዊ ገደቦች (limitations) መካከል ዋና ዋናዎቹ የግለሰቦችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሃገር ደህንነት ስም መንጠቁ፣ ለትርጉም ክፍት የሆኑ ሰፋፊ ሃሳቦችን ማጠቃለሉ እንዲሁም የህጉን አስፈላጊነት በሚገባ ሊያሳምን አለመቻሉ ናቸው፡፡

ከሌሎች የተለመዱ ሕጎች በተለየ የማስረጃ ሁኔታን የዳሰሰው ይህ አዋጅ ለወትሮ ከምንጠቀምባቸው የማስረጃ አይነቶች በተጨማሪ ተቀባይነት ያላቸውን ተጨማሪ የማስረጃ አይነቶች ይጨምራል፡፡ይህ ከመሰረታዊ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ጋር እና ከመሰረታዊ የወንጀል ህግ ጋር መታረቁ ያልተገጋገጠ የማስረጃ ስርአት በህጉ ትግበራ ወቅት ታርሞ ይተገበራል ማለት ዘበት ነው፡፡

ከኢንተርኔት ወደ ስልክ መደወልን፣ ያልተፈቀዱ ሶፍትዌሮችን መጠቀምን፣  እንዲሁም የጽሁፎችን ይዘትን በብዙ ከሚወቀሰው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ጋር ማቀላቀሉ ህጉን ከተጸፈበት በላይ አላማ  እንዳለው ሌላ ምስክር ነው፡፡ ወደ ስልክ መደወል እና ማስደወልን የሚከለክለው የህጉ አንቀፅ አስር  ከተከለከሉ ሶፍት ዌሮች ጋር ተደምሮ የኢንተርኔት የድምጽ ንግግርን ወደ ወንጀልነት ይቀይረዋል፡፡

VoIP (Skype, Google Talk…) በሚኒስትሩ ይፈቀዱ ይሆን?

የቀድሞዋ አዲስ ነገር መራኄ ኤዲተር መስፍን ነጋሽ በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹Promote then criminalize!› በሚል ርዕስ ባሰፈረው አጭር የስዕል ማብራሪያ ላይ (ምስሉ እዚህ ጦማር መግቢያ ላይ ይታያል) ከሁለት ቀን በፊት በሚኒስትሩ ድረገጽ ላይ VoIPን (Voice over Internet Protocolን) የሚያስተዋውቅ ይዘት ያለው መልዕክት ተለጥፎ እንዳገኘ (ያ ገጽ አሁን በሌላ ይዘት ተተክቷል) በምስል አዘጋጅቶ እና የመጀመሪያው መስመር ላይ "ስለ VoIP ሰምታችሁ የማታውቁ ከሆነ የረዥም ርቀት የስልክ ጥሪዎችን የምታደርጉበትን መንገድ ለመቀየር ተዘጋጁ" የሚል ነገር እንዳነበበ ጠቅሶ ጽፎ ነበር፡፡ መስፍን ነጋሽ ይህንን ሁኔታ ከረቂቅ አዋጁ አንፃር በመታዘብ አገልግሎቱን እያስተዋወቁ፣ ተጠቃሚዎቹን ወንጀለኛ ከማድረግ የተቀነባበረ ሴራ ለይቶ እንደማያየው ተናግሯል፡፡

የሚኒስተሩ ድረገጽ በፍጥነት በሌላ ጽሁፍ መተካቱ አዋጁ እውነትም VoIP ኢላማ አድርጎ ተነስቷል ብሎ ለመጠርጠር እንደ አንድ ግብአት ሊቆጠር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል እ.ኤ.አ. በ2002 የቴሌሴንተር አገልግሎት ፈቃድን በተመለከተ በወጣው መመሪያ አንቀጽ 13(2) ላይ VoIP (ከኮምፒዩተር ወደ ኮምፒዩተር የሚደረግ የድምጽ ግንኙነት ጨምሮ /ስካይፕን ያካትታል/) የተከለከለ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የተለያዩ ኢንተርኔት ካፌዎች ስካይፕን በይፋ ሲጠቀሙ እንጂ በወንጀል ሲከሰሱ የታየበት አንድም መረጃ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢቴቪ የሕዳሴው ግድብን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ በስካይፕ ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል እያለ ሲያስተዋውቅ መክረሙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

በመሆኑም መመሪያው እያለ፣ የፀረ-ሽብርተኝነቱም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እያሉ አዲሱ ‹የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅ› እዚያ የተካተቱትን ሕግጋት ደግሞ መውጣቱ ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አለመሆን የእነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋት ተከትሎ እያደገ የመጣውን ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው የሚለውን መላምት ያጠናክረዋል፡፡ ለዚህም እንደዋቢ መጥቀስ የሚቻለው በረቂቁ ላይ ‹‹መንግስት በሕዝቡ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ…››፣ ‹‹… አፀያፊ ጽሁፎች›› የሚሉ አሻሚ እና ሰፊ ትርጉም የሚኖራቸውን ሐረጎች መጠቀሙ የአዋጁ ኢላማ በተለይ ማሕበራዊ ድረገጾች ላይ በሚደረጉ የግል ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለስጋት የሚጥሉ ሆነዋል፡፡

ሚኒስትሩ VoIPን ከሚከለከሉ አገልግሎቶች መካከል እንደሚያስቀምጣቸው ለመጠርጠር የሚያበቃ ሌላም ምክንያት አለ - የገዢው ፓርቲ የቅርብ ሚዲያ እና "ህግ አውጪው"  በመባል የሚታማው ሬድዮ ፋና፡፡ የዜና መጽሄት በተሰኘው ፕሮግራሙ ሬዲዮ ፋና የረቂቅ አዋጁ መንፈስ ሁሉንም ዓይነት VoIPን የሚጠቀሙ አገልግሎቶችን ለማገድ የወጣ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል:: በተለይ (በፕሮግራሙ ላይ) አንድ የምክር ቤት አባል የአዋጁን አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲናገሩ ኢትዮ ቴሌኮም እንደስካይፕ ያሉ በኢንተርኔት ስልክ የማስደወያ ሶፍትዌሮችን በሕግም ሆነ በቴክኖሎጂ ቁጥጥር ስር ማድረግ እንዳለበት አስረድተዋል:: አዲሱ የቴሌኮም አዋጅ ረቂቅ ደግሞ ለቴሌ ይህን ሕጋዊ ዳራ ይፈጥርለታል::

አዋጁ ከኢትዮ ቴሌኮምም በላይ በድብቅ የኢንተርኔት ማጥለል (Internet filtration) ሥራ በመስራት የሚታማውን የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲን (INSAን) ነፃ ያወጣዋል - የረቂቁ አንቀጽ 13 ‹የቴክኒክ የሥራ ቡድን›መቋቋም የሚለው ከለላ በማስቀመጥ፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት እየተዘዋወርን ያነጋገርናቸው ጥቂት የኢንተርኔት ካፌ አገልግሎት ሰጪዎች ከወዲሁ (አዋጁ ከመጽደቁ እና በነጋሪት ጋዜጣ ከመውጣቱ በፊት) የስካይፕ እና ማንኛውንም የድምጽ (Voice over IP) አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ለመረዳት ችለናል፡፡

ዳንኤል ብርሃነ ከላይ ባጣቀስነው ጦማሩ ላይ ‹‹ስካይፕ በሕግ እንደማይታገድ የጥብቅና ባርኔጣዬን አስይዤ እወራረዳለሁ›› ሲል ከተከራከረው በተቃራኒ መደምደም እንደሚቻለው፣ አዋጁ አሁን አሁን እያቆጠቆጠ የመጣው በበይነመረብ ላይ ሐሳብን በነፃ የመግጽ ፍላጎት ላይ ክፉ ጥላ መጣሉ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች የአዋጁ ብቸኛ ዓላማም ይኸው ነው ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ከወዲሁ እየገለፁ ነው፡፡ ውጤቱን ለማየት ግን አዋጁ (በፓርላማ ክርክር እና የጋለ ውይይት?) ፀድቆ  የተግባር እርምጃው እስኪጀመር ጥቂት ወራት ብቻ መታገስ በቂ ይሆናል፡፡

No comments:

Post a Comment