Saturday, May 28, 2016

‹የሥልጣን ባለጌ› ያሳደገው የእኔ ትውልድ


ዮሴፍ መርጉ የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነው፡፡ ዮሴፍ ብቻ ሳይሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ ዮሴፍ “ከዚህ በኋላ በኢሕአዴግ ተስፋ ማድረግ፤ በራሱ ተስፋ መቁረጥ እንደሆነ አድርጌ እወስደዋለሁ” በማለት መፍትሔ ይሆናል የሚለውን ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ አንብቡት፡፡

ከ1996 አንስቶ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ መሰጠት የጀመረው ‹የሥነ-ዜጋ›
ትምህርት በፖለቲካ ንቃቴ ላይ በቀላሉ የማይገመት አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ በአጋጣሚ ይሁን ሆን ተብሎ ባላውቅም መምህራኑ ሥነ-ዜጋንና የታሪክ ነክ ትምህርቶችን ደርበው እንዲይዙ በመደረጉ በመንግሥትና አስተዳደር ግንዛቤዬ ላይ ደማቅ አሻራን አሳርፏል፡፡ እንዲህ፣ እንዲህ እያለ እየዳበረ የመጣው የፖለቲካ ግንዛቤዬ ከፍ እያልኩኝ ስመጣ በተለያዩ መጽሐፍት ታግዞ፤ ብሎም የበይነ-መረብ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መናኘቱ ስሜቴን በአደባባይ የመግለጽ ድፍረቱንና አጋጣሚውን ፈጠረልኝ:: ብዙም ነገር እንዳውቅም ሆንኩኝ፡፡

1983 እኔ የተወለድኩበት ዓመት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ.) ወደ ሥልጣን የመጣውም በዚሁ ዓመት ነው:: ዘንድሮ በ2008 የብር ኢዮቤልዩውን የሚያከብረው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የእሱን መንግሥት ብቻ በማውቀው በኔ እንዴት ይታያል የሚለውን እስኪ እንመልከት::

ማወቅ ዕዳ ነው። አንድ ሰው በማወቁ የተለያዩ የስሜት ፈረቃዎችን ለማስተናገድ ይገደዳል። በትውልድ ዘመኔ አንድ መንግሥት ብቻ ማየቴና በአንጻሩ ደግሞ የምዕራቡ ዓለም በነጻ ምርጫ የተለያዩ መንሥታትን ማየት መቻላቸው የፈጠረውን ነገር ማወቄ የተለያዩ ስሜቶችን ሰጥቶኛል። አንድ መንግሥት ያለገደብ በሥልጣን ላይ መቆየቱ ‹የሥልጣን መባለግን› ከመፍጠር ውጭ ለአገሪቱ የሚፈጥረው ነገር የለም። ይህንንም ለማረጋገጥ አፍሪካን ለረጅም ጊዜ ያስተዳደሩና እያስተዳደሩ ያሉ መንግሥታትን ማየት ብቻ ብቂ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የምዕራቡ ዓለም አገራት ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሔድ ባሻቸው ጊዜ የፈለጉትን መንግሥት መቀያያር ይችላሉ፡፡። በውጤቱም አንዱ መንግሥት የሰነፈበትን ተተኪው መንግሥት እየሠራ እንዲያልፍ፤ ይህም ብቻ አይደለም ተተክቶ ያለፈው መንግሥት የጎበዘበትን አዲሱ መንግሥት በተሻለ ሁኔታ በማስቀጠል አልፏል። እያለፈም ነው።

ይህንንና መሰል ሁነቶችን ሳስብ በትውልድ ዘመኔ አንድ መንግሥት ብቻ ማየቴ እኔም እንደ ዜጋ፤ አገሬም እንደ አገር የተለያዩ መንግሥታት፤ የተለያዩ ክኅሎቶችን የማጣጣም ዕድል ማጣት ከሚፈጥረው ቁጭት ጋር ጭምር ነው፡፡ የኔም ትውልድ ፖለቲካን በፍላጎት ሳይሆን በቁጭት የሚገባበት ረመጥ ሆኖበታል:: እዚህ ድምዳሜ ላይ ያደረሱኝን የታሪክ አጋጣሚዎች እንመልከት::

በ1990 የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ መግባቱን ተከትሎ ‹ለኤርትራ መንግሥት ምን ዓይነት የአፀፋ ምላሽ ይሰጥ?› በሚለው ላይ የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕ.ወ.ሓ.ት) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሁለት ጎራ በመሆን የተለያየ አቋም ይይዛሉ:: ይኽም የአቋም ልዩነት በስየ አብርሃና በመለስ ዜናዊ በኩል የጎላ ከመሆኑም ባሻገር የእርስበርስ መተማመን ላይ የማይናቅ ጥላሸትን ፈጠረ:: ጊዜ ሊያስታርቀው ያልቻለው የሁለቱ ግለሰቦች መቃቃር ፓርቲውን ለሁለት መሰንጠቅ የዳረገው ሲሆን፤ በሽኩቻው መጨረሻም ‹የነስየ ቡድን› የፓርላማ አባልነት በዚያውም ያለመከሰስ መብታቸውን በመንጠቅ ተጠናቀቀ:: ይኽም አልበቃ ብሎ “ስየ አይተኛልኝ” ብሎ ያሰበው መለስ እነስየ ከፓርላማ በተሰናበቱ በአራተኛ ቀን “ስየን እግር ተወርች ያስርልኛል” ያለውን የሙስና ‹ካርድ› በመምዘዝ ያለበቂ ማስረጃ ዘብጥያ እንዲወርድ አድርጎታል:: ከዛ በኋላም ባለው የፓርቲው አባላት መጠየቅ ሲጀምሩና የሐሳብ ልዩነት ሲያሳዩ ይኸው የሙስና ‹ካርድ› እየተመዘዘባቸው ለእሥር ሲዳረጉ ተመልክተናል:: ይኽም የታሪክ አጋጣሚ በፓርቲው ውስጥ አዳዲስ ሐሳቦችን ማስተናገድ እንዳይቻልና ዴሞክራሲም ከውስጥ ይመነጫል ተብሎ እንዳይታሰብ አድርጓል:: ፓርቲው የውስጥ ቅራኔዎች የሚፈታበት አግባብ ከውጪ ሆኖ ለተመለከተው፤ ፓርቲውን መቀላቀል ማለት በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ከመጠርነፍ ባለፈ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት መቻል እንዳልሆነ ይረዳል::

እንግዲህ በሕይወት ዘመኔ ያየሁት አንድ መንግሥት፤ ‹ኢሕአዴግ› ዴሞክራሲን ከውስጥ በመነጨ ያሰፍናል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል ይህን ያህል ካልኩኝ፤ በማስከተል ደ'ሞ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፈን ከሱ ባንፃሩ የሚንቀሳቀሱትን ፓርቲዎች በምን መልኩ ያስተናግዳል የሚለውን ትዝብቴ እንደሚከተለው ላስቀምጥ::

የኢሕአዴግ መንግሥት ለሁለተኛ ጊዜ ባካሄደው የ1992 ምርጫ አንዳችም ተአማኒነት በማጣቱ፤ ባናቱም በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሳቢያ ኢሕአዴግ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቱና የተፈጠረውም ቀውስ ድርጅቱን ከፋፍሎ በማዳከሙ፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ሒደት ችግር ውስጥ እንዳለ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ጆሯቸው ላይ ተኝተው የነበሩት ፈረንጆች እንኳን መረዳት ሲጀምሩና፤ በዚህም ምክንያት የተወሰነ ማሻሻያዎች (Reforms) ሲጠይቁ፤ ኢሕአዴግ ”ከዚህ በፊት በአንጃው (እነስየ አብርሃን መሆኑ ነው) ተወጥሬ ነው ለውጥ ማምጣት ያልቻልኩት አሁን ግን አደርገዋለሁ::” ብሎ ቃል ገባ::

የተገባው ቃል የፈጠረው የፖለቲካ ምኅዳሩ መሻሻል ለ1997 ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አባሎቻቸውን እንዲሰባሰቡ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀሰቅሱና እንዲያደራጁ ዕድል ሰጠ:: ይህ የመንግሥት ተስፋ ሰጪ ቃል መስጠት ቀደም ብሎ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ይሳተፉ ከነበሩት ፖለቲከኞች ባሻገር ለአዳዲስ ፓርቲዎች መፈጠርና በተለያየ የሙያ ዘርፍ ላይ አገሪቱን ሲያገለግሉ ከነበሩት ምሁራን በተጨማሪ በውጪ ያሉትንም ወደ ፖለቲካው የመሳብና የመሳተፍ ዕድል ፈጠረ:: በነዚህ ምሁራን ከተፈጠሩ ፓርቲዎች ውስጥ ‹ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ› አንዱ ነው::

ኢሕአዴግ በአገሪቱ ሚዲያ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመከራከር የከፈተው መድረክ ከራሱ ይልቅ ተቃዋሚዎችን በእጅጉ ጠቅሟል:: የምርጫው ቅስቀሳ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት፤ ኢሕአዴግ የከፈተው ቀዳዳ ለሽንፈትና ለውድቀት እንደዳረገው ሲረዳ የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፍቶት ነበር:: በተለይ በአዲስ አበባ የታየው የሕዝብ እንቅስቃሴ ዕንቅልፍ ነስቶት ገንዘቡን እየበተነ የኢሕአዴግ የንብ ምልክት የነበረባቸው ፖስተሮች:፣ በራሪ ወረቀቶች፣: ቲሸርቶችንና ሌሎች የቅስቀሳ ቁሳቁሶችን በማደል አዲስ አበባን አጥለቅልቋት ነበር:: ሆኖም የሕዝቡን አመኔታ አጥቶ የነበረው የኢሕአዴግ አመራር በመጨረሻም ከሽንፈት ሊያመልጥ አልቻለም:: መሸነፉንም ከመቀበል ይልቅ የምርጫውን ውጤት በማጭበርበር አሳፋሪ ተግባር ፈፅሟል:: ይህንንም የተረዱት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ስምንት የመደራደሪያ ነጥቦችን በማስቀመጥ እነሱ እንዲሟሉላቸው ጠየቁ:: ያ የማይሆን ከሆነ ግን ለሕዝቡ ሠላማዊ የተቃውሞ ጥሪም እንደሚያሰሙ ያሳውቃሉ:: ሁኔታዎች ባላሰበው መልኩ የሄዱበት የኢሕአዴግ መንግሥትም በመጨረሻ የቅንጅት ፓርቲዎችንና ጋዜጠኞችን በማሰር በአሜሪካ ምክር ቤትም ሆነ በአውሮፓ ኅብረት የተወገዘበትን ድርጊት ፈፀመ::

የነጻነት እና የዴሞክራሲ ልፈፋው ከአፋዊነት ያላለፈ መሆኑን ከመነሻው ጀምሮ ማየት የቻሉት ጥቂቶች ባይሆኑም፤ በምርጫ ‘97 የኢሕአዴግ ቡድን አፋኝነትና ፀረ-ዲሞክራሲያዊነት ሊደበቅ በማይችል ደረጃ ለሁሉም ተጋልጧል፤ የቅንጅት መሪዎችና አባላት፣ ጋዜጠኞችና የሲቪክ ድርጅት ተወካዮች ከዚህ ፍጅት ጋር በተያያዘ ‹ሕገ-መንግሥቱን በኃይል ለመናድ› ሞከሩ በሚል ተወንጅለው ‹ወሕኒ› ሲወረወሩ፤ በአባሪነት የተከሰሱትና የተሰደዱት የነጻው ፕሬስ አባላት ጥቂት አይደሉም:: ሁኔታውን እጅግ አሳዛኝ የሚያደርገው፤ መንግሥት የገባውን ቃል ተከትለው ወደ ፖለቲካው የገቡ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ለእስርና ለከፍተኛ እንግልት መዳረግ ነበር::

ይህን መሰሉን ግፍ በአገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ላይ የፈፀመ መንግሥት “ከንግዲህ ለማንስ ይመለሳል?” የሚል ጥያቄም ፈጥሮ አልፏል:: ለኔም ቢሆን ዴሞክራሲ ከፓርቲው ‹ኢሕአዴግ› ውስጥ መመንጨት እንደማይችል ካረጋገጥኩበት የታሪክ አጋጣሚ በተጨማሪ፤ ይህኛው የታሪክ አጋጣሚ ደ'ሞ ከኢሕአዴግ ባንጻሩ መቆምና የቆሙት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን ያህል ፈታኝ ሁኔታ እንዳለባቸው አስገንዝቦኛል::

ከላይ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን ሊያመጣ እንደማይችል እንደማሳያነት የተጠቀምኳቸው የታሪክ አጋጣሚዎች እንዳሉ ሆነው፤ የቅርብ የቅርቡን እናውራ ቢባል'ኳ ብዙ ተስፋ አስቆራጭ ሁነቶችን እናገኛለን:: ለአብነት ያህል በ2007 ምርጫ መዳረሻ፤ ብቃት ያላቸውንና ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ይፈጥሩብኛል ብሎ ያሰባቸውን የሰማያዊ፣ የአንድነትና የአረና ፓርቲ አመራሮችን የክርክር ሒደት የሚስተናገድበት ወቅት መቃረቡን ተከትሎ ለእሥር ዳርጓቸዋል:: በሚያሳዝን ሁኔታ አመራሮቹን ከምርጫው በኋላ ፍርድ ቤት በነጻ አሰናብቷቸዋል:: ከዚሁ ምርጫ አንድ ዓመት በፊትና በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተነሳበትን ተቃውሞ ለማስቆም የወሰደው ርምጃም በመቶዎች የሚቆጠሩትን ሕይወት ሲነጥቅ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለእስር ዳርጓል::  ከዚህ በተጨማሪም የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላነሳው ጥያቄና ለጥያቄው መፍትሔ አፈላላጊነት በተመረጡት ኮሚቴ ላይ የተወሰደው የእስር ርምጃም ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው፡፡

ለፓርቲው የማይመቹ ጥያቄዎችን በሚያነሱት ላይ ከላይ የጠቀስኳቸውን ርምጃዎች ለመውሰድ ያስቻለው ዘንድ፣ የ‹ሙስና ካርድ›ን እንደማጥቂያ የሚመዝ ሲሆን፤ ከፓርቲው ውጪ ያሉትን ደ'ሞ የ‹ሽብርተኝነት› ካርድን እየመዘዘ እያስወገደ ይገኛል:: እነዚህን ሁለት ‹ካርዶች› እንደተፈለገው መለጠጥ እንዲችሉ ተደርገው የተዘጋጁ የሕግ መዋቅሮች ስላሏቸው፤ የሚፈለገውን ‹የመንግሥቱን ሥልጣን የማስጠበቅ› ሥራ በሚገባ ማሳካት አስችለዋል::
ይህ ከሆነ በኋላ በኢሕአዴግ ተስፋ ማድረግ፤ በራሱ ተስፋ መቁረጥ እንደሆነ አድርጌ እወስደዋለሁ::

ታዲያ ዴሞክራሲ በምን መልኩ ይመጣል? ለሚለው ጥይቄ መልሴ “ሁሉን ዐቀፍ በሆነ መልኩ ክፍተቶችን በሙሉ በመጠቀም የሕዝቡን ንቃት በማጎልበትና ሕዝቡም የሚገኙትን አጋጣሚዎች ሁሉ ወደ ለውጥ መቀየር የሚችል እንዲሆን አድርጎ በማዘጋጀት ነው” የሚል ነው የእኔ መልስ::

No comments:

Post a Comment