Saturday, May 28, 2016

“እኔ… ተስፋ የለኝም?”



መልዕክተ ዓብይ የ25 ዓመት ወጣት ስትሆን፤ በኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ዘመን ተወልዳ አድጋለች፡፡ በሌላ አነጋገር መልዕከተ አንዳንዶቹ ‘The EPRDF Generation’ የሚሉት ትውልድ አባል ነች፡፡ መልዕክተ ብቻ ሳትሆን ስልሳ አምስት በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ወዲህ የተወለደ ሲሆን፤ ይሄም ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛውን ይሸፍናል፡፡ መልዕክተ በዚህ ዕድሜዋ የፖለቲካ መነቃቃቷን ጨምራ በስርዓቱ ያላትን ‹ተስፋ› እንዲህ ታስነብበናለች፡፡ እስኪ አንብቧት፡፡

“ፖለቲከኛ አይደለሁም፤ ፖለቲካ አይመቸኝም፡፡ የኔ የመኖር ዓላማ፤ መጀመሪያ እኔ እራሴን እና ቤተሰቤን ካለሁበት ችግር ማላቀቅ ነው፡፡ ፖለቲካ የደላው እና ኑሮን ያሸነፉ ሰዎች ችግር እንጂ የኔ አይደለም፡፡ እኔ ምን ያገባኛል?”

ይህ እስከቅርብ ጊዜ የነበረኝ የፖለቲካ አመለካከት ነበር፡፡ በርግጥ አሁን ላይ በፊት ከነበረኝ
አስተሳሰብ የተለየ አመለካከት እየተፈጠረብኝ መመጣቱ በራሱ ረዥም ሒደት ነው፡፡ ፖለቲካ የሁሉም ሰው የሕይወት ሕልውና እንደሆነ እየገባኝ ነው መሰል የማየውም የምስማውም የምኖርውም ብቻ ባጭሩ እኔም ሆንኩ ማንም ሰው ‘ከፖለቲክሱ’ ነጻ ሆኖ መኖር እንደማይችል የገባኝ አሁን ነው:: በ25 ዓመቴ:: ያሳዝናል:: ያደለው በ25 ዓመቱ የሆነ ለውጥ በራሱ ላይም ሆነ በቤተሰቡ ከዛም አልፎ ለሀገሩ ያበረክታል፡፡ እኔ ግን  በ25 ዓመቴ ገና ምንም እንደማያቅ ሕፃን ልጅ የፖለቲካ ፅንሰ ሐሳብ እዲገባኝ ‘ሀ’ ብዬ ለመጀመር እየተነሳሁ ነው፡፡ ለዚህ ግን ተጠያቂው ማን ይሆን?

አባቴ ይሆን?

አይ፤ የኔ አባት የ14 ዓመት ልጅ እየለሁ ነበር በሞት የተለየኝ፡፡ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ግን የቻለውን እና ያኔ በእኔ አቅም ልረዳው የምችለውን ይነግረኝ እና ያስተምረኝ ነበር፡፡ እሺ ታዲያ ማነው?

እናቴ ትሆን?

እናቴማ እኔን ለማሳደግ ደፋ ቀና ትበል ወይንስ ስለእኔ የፖለቲካ እና የሕይወት አመለካከት ትጨነቅ? በዚያ ላይ እንደሚታወቀው  የኛ እናቶች ከሕይወት ተሞክሯቸው ፖለቲካን በሩቁ ብናይላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እናም፣ እናቴ ላይማ አልፈርድም፡፡

መምህሮቼ ይሆኑ?

መምህሮቼ? ለምን እንደዚህ ዓይነት አመለካክት እንዲኖረኝ አድርገው አሳደጉኝ? በተለይ የሥነ-ዜጋ መምህሮቼ ለምንድን ነው የተሻለ አመለካከት እና አሰተሳስብ እንዲኖረኝ አድርገው እና የእውነትም ከዚያ ትምህርት ማግኘት የነበረብኝን ዕውቀት ያላስቀሰሙኝ? ለምንድን ነው ያለሁበት ስርዓት ብቻ ትክክል እና ያለፉት ስርዓቶች ላይ ጥላቻ ብቻ እንዲኖረኝ አድርገው ያስተማሩኝ? አሁን አሁንማ ሲገባኝ እነሱ የማያምኑብትን ሐሳብ እኔ እንዳምንበት ሲያደርጉ እንደነበር ነው የሚሰማኝ:: ይገርመኛል፡፡

በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ እኔ ፈልጌውም ይሁን ተገድጄ ያለሁበትን እንዳመሰግን እና ለእኔ ኑሮ ማለት ዳቦን ፈልጎ ማግኘት እና ለመብላት የሚደረግ ሩጫ ብቻ እንደሆነ እንዳስብ እና እንድኖር ተገድጄ ነው ያደግኩት፡፡ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ምርጫ እንኳን ያወቅኩት በ1997 በተደረገው የምርጫ ዘመቻ ላይ ነበር፡፡ ያኔ 14 ዓመቴ ሲሆን የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ እንደነገርኳችሁ እንኳን ያኔ እስከ ቅርብ ጊዜ የነበረኝ አመለካከተት የተሳሳተ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው ያደርገው የነበረ እንቅስቃሴ፤ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ የነበረው ግድያ፤ በተለይ ደግሞ አባቴ ታሞ ተኝቶ የነበረ ቢሆንም እንኳን የምርጫ ካርዱን ለመውሰድ ተደግፎ ሄዶ መምጣት እና ማታ ማታ ያባቴ ጓደኞች ያደርጉት የነበረ ውይይት እና ክርክር፤ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ይደረጉ የነበሩ የምረጡኝ ዘመቻ፤ ውስጤ የሆነ ነገር ሲፈጥር ትዝ ይለኛል፡፡ እውነት ለመናገር ብዙ የሚገባኝ ነገር አልነበረም፡፡ ያው አሁን ሲገባኝ ምንም እንዳላውቅ ተደርጌ 9ኛ ክፍል መድረሴ ይመስለኛል ነገሮች በቀላሉ እንዳገቡኝ ያደረገኝ፡፡ ብቻ  ምን አለፋችሁ፤ ደስ የሚል ነገር ነበረው፡፡ ያቺ ጊዜ እኔም አባቴን ስላለፈው እና ስለአሁኑ ስርዓት ለመጀመሪያ ግዜ አንዳንድ ጥያቄዎችን የጠየቅኩበት እና አባቴም በጊዜው በሚገባኝ እና ባቅሜ መጠን ያወራኝ ቢሆንም፤ ‹አይገባትም› ብሎ ይሁን በሌላ ምክንያት የምፈልገውን ያህል ብዙም እዳላወራኝ አስታውሳለሁ፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ፣ አባቴ ለምርጫውም ሳይደርስ እኔም ከሱ ማወቅ ያለብኝን ሳላውቅ በሞት ተለየኝ፡፡ እናም ለእኔ ያ ጊዜ በሕይወቴ ውስጥ ሰለኢትዮጵያ ፖለቲካ የነበረኝን ግንዛቤ በትንሹም ቢሆን የቀየረ ነበር ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ በዘመኑ ቋንቋ ‘97 የፖለቲካ የቃና ለውጤ ነበር፤ “ ‘97 ውስጤ ነው!” እንደማለት ነው፡፡

ከአባቴ ሞት በኋላ ለቤተሰቤ ሕይወት ትንሽ አስቸጋሪ ስለነበር ያ ውስጤ ተፈጥሮ የነበረ የማወቅ ፍላጎት ጭላንጭል ብርሐን የሕይወት ውጣ ውረድ ከሚፈጥረው ጨለማ መብለጥ አልቻለም ነበር እና ጠፋ፡፡ እንዳልኩት ያ ብርሃን ከውስጤ የጠፋ ቢመስለኝም ሁሌም ግን በማያቸው ነገሮች ውስጤ ጥያቄ ይፈጠር ነበር፡፡ 10ኛ ክፍል ላይ ውጤት ያልመጣላቸው አብሮ አደጎቼ ከዚህ በኋላ ዕጣ ፋንታቸው ምን ይሆን? ብዬ አስብ ነበር፡፡ ይህች አገር ታዳላለች ማለት ነው? እነዚህ ልጆች የሷ አይደሉም ማለት ነው? እኛ በቀን ሲበዛ ሦስቴ ካልሆነ ግን አንዴ ለመብላት ስንፍጨረጨር ሌሎች ልጆች በክረምት የእረፍት ጊዜያቸው ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ ሳይ፣ ‹ይህ እንዴት ይሄ ሊሆን ቻለ?› ብዬ ማሰቤ አልቀረም፡፡ ያኔ ግን ይሄ ሁሉ የስርዓቱ ችግር መሆኑ አይገባኝም ነበር፡፡ ለምን ቢሉ እንዲገባኝ ተደርጌ እያደኩ ስላልነበር፡፡ መንግሥት ማለት እኔን በነጻ እያስተማረ እና የአባቴን የጡረታ ብር እየሰጠ የሚያኖር አካል እና ባለውለታዬ እንደሆነ እንዳስብ ተገድጄ ስለነበር መሰለኝ፡፡

ከፍ ብዬ ‹ላቅመ ዪኒቨርስቲ› ስደርስ እና ዩንቨርስቲ ስገባ፤ የቤተሰብ ተስፋ እኔ እንደሆንኩ እና ከእኔ ብዙ እንደሚጠበቅ አስብ ስለነበር ‹ፖለቲካ› ብሎ ነገር ለእኔ ሩቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሌም የማየው በብሔርና በሃይማኖት መከፋፈል፤ ይባስ ብሎም የአዲስ አበባ ልጆች እንኳን በ‹ከማን አንሼ› በመጡበት ሰፈር እና ትምህርት ቤት መቦዳደን ውስጤን ያሳዝነው ነበር፡፡ እንዴት አድርገው ውስጣችንን እዳበላሹት ሳስብ የእውነት ያመኛል፡፡ ነው ወይስ ይህ ነገር በፊትም ነበር?

ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ ወደዩንቨርስቲ ስመለስ የነበርኩበት ‹ዶርም› ውስጥ አዲስ ጓደኛ አፈራሁ፡፡ ጓደኛዬ ለሀገሯ ያላትን ፍቅር ሳስብ ይገርመኛል፡፡ ደስም ይለኝም ነበር፡፡ ከብዙዎች ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ጥቂቶችን ማየት ደስ ይላል፡፡ እናም ከዚህች አዲስ ወዳጄ ጋር በብዙ ጉዳዮች ላይ እንወያይ ነበር፡፡ ትውልዱን እንዴት እደቀረፁት፤ ስለራሱ ብቻ የሚያስብ ግላዊነት የሚያመዝንበት አስተሳሰብ፤ ምን አልባትም በዛ ከተባለ የእኔ ብሎ ለሚያስባቸው ሰዎች እንጂ ለሰፊው ማኅበረሰብ እና አገር ብሎ ማሰብ ኋላቀርነት፤ ብሎም የማያዋጣ ነገር እንደሆነ እንዲያስብ የተገደደ ትውልድ፡፡ በቃ ፈሪ እንዳደረጉን እና በዘመናቸው ተወልደን (ማለትም በነሱ ስርዓት ውስጥ ብቻ ተወልደን ማደጋችን) ‹ፖለቲካና እሳት በሩቁ› እንድንል፣ መኖር ከፈለግን ‹ከፖለቲካ ነጻ ሆኖ መኖር› የሚል አስተሳሰብ ውስጣችን እንዲኖር ብቻ በሚፈልጉት መልኩ ቀርፀው እንዳሳደጉን እናወራ ነበር፡፡

ብቻ ምን አለፋችሁ ባጭሩ ፈሪ ሆኜ ነው ያደኩት፡፡ የምኖረውም እንደዛው ነው፡፡ በጣም ከጥቂት ልጆች ጋር ካልሆነ በቀር ስለ ስርዓቱም ሆነ ስለ ‹ፖለቲካ› እንዳላወራ ተገድጃለሁ፡፡ እርስበርስ እንዳንተማመን፤ እንድንፈራራ፤ በሁሉ ቦታ እነሱ እና እነሱ ብቻ  እንዳሉ እንድናስብ፤ እርስ በእርሰ ‹ኧረ አንቺ ልጅ ልኑርበት›፣ ‹ኧረ ልማርበት›፣ ‹ኧረ ለቤተሰቤ ልኑር›… እየተባባልንና እየተሸነጋገልን እንድንኖር አድርገው ቀርፀውናል፡፡ በቃ ዲሞክራሲን በቃል እንዳናውቀው የተደረግን ምስኪኖች፡፡

አንድ ጊዜ ዩንቨርስቲ እያለሁ ያጋጠመኝን ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የክፍላችን ተወካይ የነበረ ልጅ ለሦስት ዓመታት ሲያገለግለን ቆይቶ አራተኛ ዓመት ላይ ግን ‹ከክላስ› በኋላ እንደሚፈልገን ነግሮን፤ “ከዚህ በኋላ በቃኝ፣ ደክሜያለሁ፡፡ ከሥልጣኔ ወርጃለሁ” አለን:: ስለዚህ ሌላ ተወካይ እንድንመርጥ  ነገረን፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር እንግዲህ እራሴን እና ሌሎችን የታዘብኩት እሱና በወቅቱ ረዳት ተወካይ  የነበረችው  አንድ ሌላ የክፍላችን ልጅ የምርጫውን ሒደት ለማካሄድ ቆመው በመጀመሪያ ለምርጫ በቂናቸው የምንላቸውን ከሴት ሦስት ከወንድ ሦስት  እንድንመርጥ ዕድል ሰጡን፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ ግማሹ ክፍሉን ለቆ ለመሄድ ቸኩሏል፣ ግማሹ ‹ያለምጣል›፣ ግማሾቹ አይደሉም ሌላውን ሊወክሉ፤ ከራሳቸው ጋር እንኳ በቅጡ የሚያወሩ የማይመስሉ ልጆችን ይጠቁማሉ፡፡ በጣም ጥቂቱ ብቻ በትክክል ይከታተሉ ነበር፡፡ ከነሱ ይልቅ ግን የሚቀልደው ይበዛ ነበር፡፡ ለዛውም የቀረውን ጊዜ በነዚህ በሚመረጡ ልጆች እንደሚወድቅ እያወቅን እንቀልድ ነበር፡፡ ብቻ በብዙ ልፋት ምርጫው ተካሄደ፡፡ እናም አንድ በግትርነቱ ፣ በአልማጭነቱ እና ከራሱ ሐሳብ በቀር ለሌላው ግድ የማይሰጠው ልጅ ተመረጠ፡፡ ተበሳጨሁ፡፡ ታዲያ ይሄ ልጅ ግማሽ ዓመቱን ሲያሳርረን ከረመ፡፡ በሱ ፈቃድ ክላስ ሲቀይር፣ ‹ሀንድአውቶችን› በአግባቡ ሳይሆን ለሚያውቃቸው እና ለዶርሙ ልጆች ሲያድል፤ ሌላም ሌላም እያደረገ ሲያተክነን ከረማት፡፡ ስለእውነት የእጃችንን ስላገኝን ደስ ነበር ያለኝ፡፡ ከነአባበሉስ ‘Every nation gets the government it deserves’ አይደል የሚባለው? (እኛም የሚመጥነን የክፍላችንን ተወካይ ነበር ያገኘነው፡፡)

ከዚህ ክስተት በኋላ ከራሴ ጋር ሳወራ ውስጤ የተፈጠረው ጥያቄ ‹ለምንድን ነው ለምርጫው ግድ ያልሰጠን? እዚህ የማንም አስገዳጅነት እና ጣልቃ የማይገባበት ምርጫ ላይ የቀለድነው ለምንድን ነው? ስለምርጫ ያለን አመለካከት የተበላሸ የሆነው ለምን ይሆን? ቧልተኛ የሆንነውና ቀልድ ወዳድ ያደረገን ማን ይሆን?› ብዬ ሳስብ ‹የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ› እንደሚባለው ስለማናውቀው የዲሞክራሲ መብት እና ምርጫ ስለምን ግድ ይሰጠናል? የትኛው የምርጫ ስርዓት ሲከበር አይተን? የትኛው ምርጫ ለውጥ ሲያመጣ አይተናል? ምርጫ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ እያየን አድገን ከዚህ ሌላ እንዴት እድናስብ ይጠበቅብናል? በምርጫ ከሥልጣን መውረድ እና ወደሥልጣን እንደሚወጣ በቃል እንጂ በተግባር አናውቅ፡፡ ያለው ስርዓት የማይነካ እና የማይደፈር እንጂ፤ በምርጫ ማውረድን አናውቅማ! ስለዚህ ለምን በጓደኞቼ ላይ ለምን እበሳጫለሁ? ወደን ሳይሆን ተገደን መሆኑ የገባኝ ያኔ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተወልዶ ማደግ እንዴት አስፈሪ ነው፡፡

ከላይ እደገለጽኩት፣ በቃ እንደሚመስለኝ ያሰሩን ልንፈታው የማንችል በሚመስል በተወሳሰበ የማንነት ገመድ ነው፡፡ በምን አገባኝነት፣ በራስ ወዳድነትና በእኔነት አስተሳሰብ የታጠርን ሁነን አድገናል፡፡

በጣም የሚገርመኝ ይህ ስርዓት በተፈጥሮ እንዲሁም ከቤተሰቦቻችን ያገኘነውን ሕልውና እንኳን ነው የቀየረው፡፡ ማንነቴን በመጥፎ ሁኔታ ነው የቀየሩት፡፡ አንዳንዴ ከእኔ አስተሳሰብ እና አመለካከት ውጪ የነበሩ ነገሮችን ማሰብ መጀመሬን ሳስተውል ማመን ያቅተኛል፡፡ እንደ ‘97ቱ የኛ ሰፈር የምርጫ ኮሮጆ ለእኛ በሚያስቡ በሰዎች ተከበን እንኳን ሳናውቀው እንጭበረበራለን፡፡ ይባስ ብሎ ወደ ሥራ ዓለሙ ስገባም የነሱ ነገር ካከተመ እንደቆየ በመገመት ለራሳችን ከመቸውም በላይ አዝን ጀምሬአለሁ፡፡

ነገር ግን አሁን ላይ ትንሽ ጭላንጭል ይታየኛል፡፡ ጭላጭሉን ሙሉ ብርሃን ለማድረግ ወደሱ መጠጋት ይኖርብናል፡፡ በቃ፣ እኔ በዚህ ስርዓት ላይ ጥላቻ እንጂ ተስፋ የለኝም፡፡ እሱንም ቢሆን ከነሱ ነው የተማርኩት፡፡

No comments:

Post a Comment