Wednesday, February 20, 2013

ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል እና ለአቶ በረከት ስምኦን


ለተከበሩ አቶ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ የኮሙኒኬሽን እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር፣
ለተከበሩ አቶ በረከት ስምኦን፤ በሚኒስትር ማዕረግ፣ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣

ከ20 ዓመታት በፊት ፓርቲዎቻችሁ - ሕወሓትም ሆነ ብአዴን - ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ሕይወታቸውን የገበሩለትን ጦርነት ያካሔዱት፥ ኢትዮጵያውያን ‹‹ጀርባቸውን ሳይመለከቱ›› በነጻነት አመለካከታቸውን እና ሐሳባቸውን እንዲያንፀባርቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብዙዎች ደማቸውን ያፈሰሱለት፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ የተሰየመለት (አንቀጽ 29) ‹‹የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት›› ከኢትዮጵያውያን እጅ ቀስ በቀስ አፈትልኮ እየወጣ መሆኑ ቢያሳስበኝ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡

ደብዳቤዬን መስመር ለማስያዝ እንዲመቸኝ ከኔ የተሻለ የምትረዱትን ነገር በማስታወስ ልጀምር፡፡ ኢትዮጵያ ከ80 ሚሊዮን የሚልቁ ሕዝቦች፣ ከ80 የሚልቁ ብሔሮች እና ብሔረሰቦች፣ በርካታ ሃይማኖቶች፣ እምነቶች እና ባሕሎች ያሏት አገር ናት፡፡ ሁሉም የየራሱ የሆነ ነገሮችን የሚረዳበት መንገድ ያለው ይህ ብዝኃ-ሕዝብ በፓርላማ ውስጥ ባለ አንድ ፓርቲ ሙሉ ድምፅ እና አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አማራጭ ሐሳብ ብቻ ሊወከል ፈፅሞ አይችልም፤ ስለዚህ ሕዝቦች ሐሳባቸውን በነጻ የሚገልፁበት ሌሎች አማራጮች ያስፈልጓቸዋል፡፡ እነዚህ አማራጮች ጋዜጣና መጽሔቶችን፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኖችን እንዲሁም አዲሱ ብዙኃን መገናኛ (new media) በመባል የሚታወቀውን በበይነመረብ ላይ ባሉ ድረአምባዎች፣ ጦማሮች እና ማኅበራዊ አውታሮች ላይ ዜጎች የሚያሰፍሯቸውን አስተያየቶች እና ሐሳቦች ያካትታል፡፡

በአሁኑ ወቅት በርካታ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያወሩ መጽሔቶች እና ጥቂት የማይባሉ የስፖርት ጋዜጦች ለሕዝብ የሚደርሱ ቢሆንም፣ ማዕከላዊ ትኩረታቸውን ፖለቲካ አድርገው የሚጽፉ ሳምንታዊ ጋዜጦች ቁጥር ግን እየተመናመነ መጥቶ ከ10 በታች ሆኗል፤ ከነርሱም ውስጥ ገሚሱ ከተመሰረቱ 5 ዓመት የማይሞላቸው ሲሆን እንደሌሎቹ ከዚህ በፊት በተለያዩ ምክንያቶች ከስመው እንደቀሩት እልፍ ጋዜጦች መጥፋታቸው አይቀርም የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ይህ እንግዲህ የፕሬስ ነጻነት በአገራችን ከተጀመረበት ጊዜ አንጻር ሲታይ በየቀኑ ሁለት፣ ሦስት ጋዜጦች ከሚወጡበት እና የተለያዩ ሐሳቦች ከሚንሸራሸሩበት፣ በቀን ምንም ነጻ ጋዜጣ ላይወጣ ወደሚችልበት (ሰኞ እና ኀሙስን መጥቀስ ይቻላል) ጊዜ ዝቅ ብለናል ማለት ነው፡፡

ሁለት የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን አንዱ ትኩረቱን ከማኅበራዊ ጉዳዮች ሳያርቅ፣ ብዙዎች እንደሚሉት ‹‹ከመንግሥት ጋር ሳይጋጭ›› ለመዝለቅ እየሞከረ ሲሆን ሌላኛው ሙሉ ለሙሉ የሚያንፀባርቀው የገዢውን ፓርቲ ሐሳብ እና ርዕዮተ ዓለም ብቻ በመሆኑ አማራጭ ድምፅ ብሎ ለመጥራት ከባድ ነው፡፡ በተጨማሪም፤ አንድም የግል ቴሌቪዥን እስካሁን አልተፈቀደም፡፡

ሕገ-መንግሥቱ በአንቀጽ 29 (5) ላይ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፡፡›› ብሎ ቢደነግግም በተግባር የሚታየው እውነታ ግን ተቃራኒው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚያሰራጫቸው አራት ቴሌቪዥኖች፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ኤፍ ኤም 97.1 እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ የሚያሳትማቸው ጋዜጦች በሙሉ ለገዢው ፓርቲ የሚወግኑ፣ ተቃራኒ ሐሳብ የሚያመነጩ ወገኖችን የሚያፍኑ እና ፍርደገምድል የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ መሆናቸውን ማንም ከሕዝብ የወጣ መንገደኛ አስቁመው ቢጠይቁት ይመሰክራል፡፡

አዲሱ ብዙኃን መገናኛን በመጠቀም የሚቀርቡ ዜናዎች እና መረጃዎች ቀልጣፋ እና በቀላሉ የመሰራጨት አቅም ያላቸው ቢሆኑም፤ መንግሥት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠቱ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚጽፉ፣ ራሳቸውን የድረገጽ ዜና እና መረጃ አገልግሎት ለመስጠት በሕጋዊ መንገድ ያስመዘገቡ ያገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማት የሉም፡፡ ይሁን እንጂ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎቻችን የመሠረቷቸው በርካታ ድረገጾች እና አገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንም በትርፍ ሰዓት ሊጽፉባቸው የመሠረቷቸው በርካታ ጦማሮች አሉ፡፡ እነዚህ የሕዝብ አስተያየቶች፣ እና አማራጭ ምክረሐሳቦች የሚንጸባረቁባቸው ጦማሮች እንኳንስ መንግሥትጋ ደርሰው ለስህተቶቹ የእርምት እርምጃ እና ለብሶቶቹም ምላሽ ሊሰ’ጥባቸው ቀርቶ ከጸሐፊው በቀር ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ አንድም ዜጋ ሳይደርሱ እንዲቀር ድረገጾቹ ከስር፣ ከስር እየታገዱ ይገኛሉ፡፡

ክቡራን ሚኒስትሮች፣

ኢትዮ-ቴሌኮም ‹‹ኢትዮጵያን ከመጪው ዘመን ጋር የማገናኘት›› ሕልሙን የሚፈፅመው በተቀላጠፈ እና ነጻ የመረጃና ተግባቦት አገልግሎት እንጂ በከፊል በተገደበ ተግባር ሊሆን አይችልም፡፡ የብሮድካስት አገልግሎት የገዢው ፓርቲን አቋም ብቻ ለይቶ እያሰራጨ ሕዝቡን በአንድ አስተሳሰብ ብቻ ለመቅረፅ የሚያደርገው ሙከራ ከስነምግባርም ሆነ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ከሚያስብ ሕሊና አንጻር ተገቢ አይደለም፡፡

መንግሥት የፕሬስ ነጻነቱን የሚያፍንባቸው በርካታ መንገዶች ናቸው፡፡ በብሮድካስት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የሕትመት ፈቃድ ለማውጣት የሚሄዱ የድርጅት ወኪሎች በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ምክንያት ይከለከላሉ ወይም ተሰላችተው እንዲቀሩ ተከታታይ እና የተራዘሙ ቀጠሮዎች የሚሰጥበት አስተዳደራዊ በደል ይደርስባቸዋል፤ (የቀድሞው ‹አውራምባ ታይምስ› ጋዜጠኞች ተሰብስበው የመሠረቱት አሳታሚ በዚህ መንገድ አዲስ ጋዜጣ ማሳተም ሳይችል ቀርቷል)፡፡ ማተሚያ ቤቶችም ቢሆኑ ፈቃድ የተሰጣቸውን ጋዜጦች ‹‹በበላይ አካላት ትዕዛዝ›› እንዳይታተሙ ያግዳሉ፤ (የፍትሕ ጋዜጣን እግድ መጥቀስ ይቻላል)፡፡ አዲስታይምስ መጽሔትም በብሮድካስቱ ባለሥልጣን ፈቃዱ እንዳይታደስ ተከልክሏል፡፡ በመንግሥት በጀት የሚተዳደረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሳንሱር የሚከለክለውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ (29/3/ሀ) የሚጋፋ የሥራ ውል ያስፈርማል፤ ሌላኛው የመንግሥት ይዞታ ቦሌ ማተሚያ ቤትም በተመሳሳይ መንገድ አንድ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ እና ሌሎች የስፖርት ጋዜጦችን ብቻ ይዞ የፖለቲካ ጋዜጦችን ‹‹ሥራ ይበዛብኛል›› በሚል ሰበብ እንዳይታተም ያደርጋል፡፡

ጥቂት የማይባሉ የግል ማተሚያ ቤቶች ያሉ ቢሆንም፣ ሁሉም ሊባል በሚቻል መልኩ አንድን ጋዜጣ ለአንዴ ብቻ ካተሙ በኋላ ደግመው አያስተናግዱም፡፡ ይህም የሚሆነው ‹‹በመንግሥት ወይም ባለሥልጣናት ጫና›› እንደሆነ አሳታሚዎቹ በተደጋጋሚ የገለጹት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህም በላይ፣ ጋዜጠኞች እየታሰሩ ነው፤ ሌሎችም በመንግሥት አካላት ጫና አገራቸውን እየለቀቁ ለመሰደድ ተገደዋል፡፡  ይሄ ደግሞ በቀሪዎቹ ጋዜጠኞች ላይ ራሳቸውን እና ሐሳባቸውን ሳንሱር እንዲያደርጉ፣ ዜጎች በየተገናኙበት ብሶታቸውን ‹ሌላ ሰው ሰማኝ አልሰማኝ› በሚል ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው በሹክሹክታ እንዲያወሩ የሚያደርግ ፍርሐት ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡

ብዙ ጋዜጦች በታገዱበት እና ቀሪዎቹም ‹‹መንግሥትን የማያስከፉ›› ይዘቶች ላይ በሚያተኩሩበት በዚህ ጊዜ ዜጎች ብሶታቸውን የሚተነፍሱበት እና መረጃዎችን የሚያገኙባቸውን ሌሎች አማራጮች መፈለጋቸው የማይቀር ነው፡፡ ለዚህም ነው በተለያዩ የድረአምባ ጦማሮች እና የማኅበራዊ አውታሮች ላይ የውይይት መድረኮችን የሚከፍቱት፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ማኅበራዊ አውታሮችም በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ እየታገዱ ነው፡፡ ለእገዳው የተለያዩ ኃላፊነቱን ሊወስዱ የሚችሉ ቢሮዎች ቢኖሩም፣ ዋናው ግን የተሌኮም አገልግሎቱን በብቸኝነት የሚመራው ኢትዮ-ቴሌኮም ነው፡፡

የኢትዮ-ቴሌኮም የመረጃ ማጥለል ሥራ፣ በግል ባደረግነው የማጣራት ሙከራ ብቻ ከ200 በላይ ድረአምባዎችን እና ጦማሮችን በኢትዮጵያ እንዳይነበቡ አግዷል፡፡ ይህ እገዳ ሲደረግ ምንም የተሰጠ መግለጫ ባይኖርም መንግሥትን ‹‹የሚያስቀይሙ›› ሥራዎች ላይ መሆኑ በግልጽ ያስታውቃል፡፡ ሌላው ቀርቶ፣ ዓለም አቀፎቹ የሲኤንኤን፣ ቪኦኤ እና አልጄዚራ ድረአምባዎች በተለያዩ ጊዜ ባቀረቡት መረጃ ምክንያት የመዘጋት እና እንደገና የመከፈት ዕጣ ቀምሰዋል፡፡ ይህንን የተመለከተ ዜጋ ምናልባት የሚታገዱት የመረጃ ምንጮች ለሕዝብ ደኅንነት የሚያሰጉ መረጃዎችን የያዙ ይሆናል ብሎ ሊያስብ ይችላል፤ ነገር ግን የሚታገዱትን ገጾች መረጃ ላነበበ እውነታው አያሻማም፤ ገጾቹ የሚያቀርቡት መረጃ እና ዕውቀት ቢሆንም መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ/ትችት ግን የማይሸሽጉ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ ለማኅበረሰብ ደህንነት የማይበጁ፣ ከሕዝቡ ባሕልና ወግ ጋር የማይሄዱ የሚባሉትን የልቅ ወሲብ ቪዲዮ እና ምስል የሚያቀርቡ ድረገጾች - አንዳቸውም አለመታገዳቸው ሌሎቹ ድረአምባዎች የሚታገዱት ለማኅበረሰቡ ታስቦ እንዳልሆነ መልዕክት ይሰጣል፡፡

ስለዚህ ክቡራን ሚኒስትሮች፣

መንግሥት የዜጎችን ሐሳቦች፣ ጋዜጦች እና ጦማሮች በተደራጀ መልኩ እያሰሰ እና እያነበበ የሕዝቦችን ብሶት እና ችግር ተረድቶ ለመፍትሔው መረባረብ ሲኖርበት፣ ዜጎች መረጃዎቹን እንዳያወጡ እንቅፋት መሆንን ከመረጠ በየት በኩል ኃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻለዋል? መንግሥት በምሳሌነት የማያሳየውን ሥርዓት ከሕዝቡ እንዴት መጠበቅ ይቻለዋል?

እንግዲህ እነዚህን ጥያቄዎቼን በቅን ልቦና ተረድታችሁ ለጥያቄዎቼ ሁሉ መልስ እንደምትሰጡኝ በማመን የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 29 (2) በመጥቀስ ደብዳቤዬን እቋጫለሁ፡-
‹‹ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው፡፡ ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሐሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል፡፡››

ሕገ-መንግሥቱ ይከበር፤ የአመለካከትና ሐሳብን በነጻነት የመያዝና የመግለጽ መብት ይከበር!


ሐሳባቸውን የመግለጽ ነጻነታቸውን ከተነፈጉት ዜጎች አንዱ፣

በፍቃዱ ኃይሉ

1 comment:

  1. ሰዎቹ መስማትም፤ ማየትም ካቆሙ ውለው አድረዋል። ሳያውቁ ሳይሆን በራሳቸው ላይ የጠመጠሙት የሐሰትና የተንኮል መዓት መውጫ ቀዳዳ ሳይነሳቸው አልቀረም። “ጅብ የነከሰች አህያ” ሆነዋል።
    ለማንኛውም በግለሰቦች (በሚንስትሮች) የሚሰጥና የሚነጠቅ ነፃነት ያለ አይመስለኝም። ግን ማስታወሱ ችግር የለውም።
    የካናዳው ከበደ ነኝ

    ReplyDelete