Friday, February 1, 2013

እግርኳሳችንና ተግዳሮቶቹ …………


በፍስሃ ተገኝ

እግርኳስ እኛነታችንን እንድናውቅ ይረዳናል። የምንኖርባቸው ከተሞች የእለት  እለት ህይወቶች የሆኑት ንግዶች፣ ጩኸቶች፣ ኳኳታዎች፣ ውበቶችንእና አስቀያሚዎችን ያንጸባርቃል። እግርኳስ ማንነታችንን አጋነን እና አትርፈን የምናሳይበት ምልክት ነው። ሰዎች የአንተን ማንነት እና ህይወትበምታሳየው እግርኳስ ውስጥ መመልከት ይችላሉ። እግርኳስ ጠንካራ፣ ሀይል ያላቸው እና ሁላችንም በአንድነት የምንጋራቸውን ምስሎች ማንጸባራቂያውብ ነገር ነው” በማለት የተናገረው አርጀንቲናዊው የቀድሞው የአለም ዋንጫ ባለቤት እና “የእግርኳስ ፈላስፋው” በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ሆርጌ ቫልዳኖ ነበር።

የእግር ኳስ ፍቅራችን……

የእግርኳስ ጨዋታዎችን ለመመልከት በሚል ከትምህርት ቤት አምልጠን ወጥተን ስታዲዬሞች ስንሄድ የነበረው፣ ማታ ቴሌቭዥን ያላቸው ጎረቤቶች ፈልገን እግርኳስን ለማየት ወላጆችን ለማታለል አልጋችን ውስጥ ሰው የተኛ ለማስመሰል ትራስ ደብቀን በመስኮት በመውጣት የምንነጉደው፣ መኪና እያጠብን ያገኘነውን ገንዘብ በማጠራቀም እና ከቤተሰብ የተቀበልነውን የኪስ ገንዘብ ለስታዲዬም መግቢያ ትኬት መግዣ በሚል እስከሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ስንሰበስብ የነበረው፣ ገንዘብ ከሌለን ደግሞ ስታዲዬሞች መግቢያ በሮች ወይም ከተንበሪዎች (ከሀረር አካባባቢ ከሆኑ) አጠገብ በመቆም ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ያህል እስኪቀሩት ጠባቂ ፖሊሶችን አይን አፍጠን እያየን በልጅ ፊት ቋንቋ የምንልማመጠው እግርኳስ ጨዋታን ለማየት እና ልንገልጸው የማንችለውን መንፈሳዊ እርካታን ለማግኘት ነበር።

እነዚህን ነገሮች ስናደርግ ታዲያ ተቺዎች፣ እንቅፋቶች እና አላጋጮች አላጋጠሙንም ማለት አይደለም። ግን  “ደግሞ ለሞተ እግርኳስ እና ለቅሪላ” እያሉ ሲያሾፉብን የነበሩ ሰዎች ታዲያ ድንገት ያ አስተያየታቸው በሀገራዊ ፍቅር እና ስሜት ተቀይሮ እግርኳስን ከእኛ ጋር እያጣጣሙ ሲያዩ እና የራሳቸውን አስተያየቶች ሲሰጡ ማንበብ፣ መስማት እና መመልከት በእውነትም የዚህ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ትልቁ ክስተት ነበር ማለት ይቻላል። በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ተካፋይ የነበረው እና ከዛምቢያ ጋር አቻ ተለያይቶ፣ በቡርኪና ፋሶ እና ናይጀሪያ ብሄራዊ ቡድኖች ተሸንፎ ከውድድር ውጪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሜዳ ውስጥ ያደረጋቸው እንቅስቃሴዎች የሀገሪቷን እግርኳስ ለረጅም ጊዜ ሲከታተል ለነበረ ተመልካች አዲስ ባይሆንም ለበርካቶች (ኢትዮጵያዊያን ለሆኑ እና ላልሆኑ) ግን አስደናቂ እና ጭራሽም ያልጠበቁት አይነት ነበር። ያ ፈጣን አጭር ኳስ ቅብብል፣ ከአምስት ሜትሮች ባነሰ ርቀት ላይ በቆሙ ሁለት እና ሶስት ተጨዋቾች መካከል ጠባብ ቦታዎችን በመጠቀም የሚደረጉት አንድ-ሁለት ቅብብሎሽ፣ የቆሙ (የቅጣት ምት እና የማእዘን ምቶች) ኳሶችን የማጥቃት እና የመከላከል ችግሮቹ፣ አስደናቂ የግል ችሎታዎች እና ያልተገራ እና ተፈጥሯዊ የሆነው ጥበብ  ለማየት ጊዜውን እና አቅሙን ሲሰዋ የነበረ ኢትዮጵያዊ የእግርኳስ አፍቃሪ በሙሉ ያለምንም ማቋረጥ ሲያያቸው የሰነበቱ ክስተቶች እና ሂደቶች እንደሆኑ ያውቃል።

ታዲያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሜዳ ላይ ባሳየው እንቅስቃሴ የተገረሙት እና ሀገሪቷን በስፖርቱ አለም በሩጫው ብቻ ያውቋት የነበሩ የጨዋታ አስተላላፊዎች (commentators) እና ተንታኞች (pundits) በአንድነት ማለት ይቻላል ተጨዋቾቹ ራሳቸውን ሜዳ ላይ ለመግለጽ አለመፍራታቸው፣ ለእይታ ቀላል እና ማራኪ በሆነው አጭር ኳስ አጨዋወታቸው በመገረም አድናቆታቸውን ማፍሰስ ጀመሩ። እነዚህ አድናቆቶች ታዲያ (ከገለልተኛ ወገኖች የተሰሙ በመሆናቸው) በስሜት እና በሀገር ፍቅር ወኔ ብሄራዊ ቡድኑን ለመደገፍ ለወሰነው በፊት እግርኳሱን ይከታተል ላልነበረው ኢትዮጵያዊ ልክ እንደአስቴር አወቀ ሰረቅራቃ ድምጽ ለጆሮው የሚጣፍጡ ሙዚቃዎች ነበሩ።

የክለቦች ችግር በአህጉራዊ ሜዳ

በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ባየነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጨዋወት ብንደሰትም በርካታ የዘርፉ ባለሞያዎች “ነገር ግን” ብለው የሚጀምሩት ትችት የበፊቶቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች እና ክለቦች ላይ ይሰነዘሩ ከነበሩት ትችቶች ጋር ተመሳሳይነት ነበራቸው። በተለይ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ ክለቦችም ሆኑ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የተጫወቱ የውጪ ሀገሮች ተጋጣሚ ቡድኖች አሰልጣኞች በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡድኖች ላይ ከሚያቀርቧቸው ትችቶች መካከል ታክቲክ ላይ ወይም የጨዋታ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ኳስን ለመቀበል ወደክፍት/ባዶ ቦታ መሮጥ፣ የሜዳውን ስፋት እና ርዝመት ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚቆምባቸውን ቦታዎች ማወቅ፣ ከቡድን አባል ጋር መቀናጀት፣ ኳሱን ለመቀበል ክፍት ቦታዎች ላይ መገኘት፣ በራስ እና በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ኳስን በበላይነት መቆጣጠር፣ እንቅስቃሴዎችን ኳስ እግር ስር ከመግባቷ በፊት ቀድሞ ማንበብ፣ መቼ ኳስን ማቀበል እና በግል እያንከባለሉ መሄድ እንዳለባቸው ትክክለኛ እርምጃን መውሰድ፣ ኳስን ለጓደኛ ሲያቀብሉ እና ሲያንከባልሉ ከተጋጣሚ ቡድን ተጨዋች እይታ/ንባብ መሸፈን፣ የተጋጣሚ ቡድን ሊጠቀምበት የሚችለውን አደገኛ ቦታ እና ሰው መከላከል እና መሸፈን የሚሉት በዋናነት የሚጠቀሱ የታክቲክ ስርአቶች ቀድሞም ቢሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ቡድኖች ላይ በተደጋጋሚ የሚታዩ ታሪካዊ ችግሮች ናቸው። እነዚህን ክፍተቶቻችንን ይዘን ለአህጉራዊ እግር ኳስ መምጣታችን በ29ነኛ የአፍሪካ ዋንጫ በሚገባ ታይቷል፡፡

ጥንካሬያችንና ጉድለቶቻችን

ሜዳ ውስጥ ባሉት እንቅስቃሴዎች ላይ ብቻ አተኩረን የኢትዮጵያ እግርኳስ የሚደነቅባቸውን እና የሚተችባቸውን ነገሮች ነጣጥለን ብናይ የሚደነቅባቸው ነገሮች ግለሰቦች በተፈጥሮ ያገኟቸውን (ያለአሰልጣኝ ወይም አስተማሪ ሊገኙ የማይችሉ) ችሎታዎች ሲሆን፣ የሚተችባቸው ደግሞ በትምህርት እና በስልጠና ሊያገኙቸው በሚችሏቸው ነገሮች ላይ ነው። ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች አብዛኞቹ አጨዋወታቸው ኳስን በመያዝ ላይ የተመሰረተ እና ለአይን የሚማርክ እንቅስቃሴ ቢሆንም ተጋጣሚ ቡድንን ለማሸነፍ ግን በቂ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል። እ.አ.አ በ1907 ዓ.ም የእንግሊዙ ኖርዝሀምተን ክለብ አሰልጣኝነት የተረከቡት ኸርበርት ቻፕማን በጊዜው “እግርኳስ ጨዋታን ለማሸነፍ ኳስን በቁጥጥር ስር ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ ኳሱን የት እንደተቆጣጠርከው እና የተቆጣጠርክበት ሁኔታዎች ወሳኝነት አላቸው” በማለት የተናገሩት ለምን የሀገራችን ተጨዋቾች በዚህ በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ቢሆን ኳሱን ቢቆጣጠሩም ያንን ቁጥጥራቸውን ወደውጤት መቀየር በተደጋጋሚ እንደተቸገሩ ፍንጭ የሚሰጥ ነው።

Inverting the Pyramid የተሰኘው በእግርኳስዊ አጨዋወት ታክቲክ ላይ ያተኮረ መጽሀፍን የጻፈው ብሪታኒያዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ጆናታን ዊልሰን “አንድ ቡድን የራሱን እግርኳሳዊ ፍልስፍና ሜዳ ላይ ለማሳየት ከሁለት ነገሮች መካከል አንዱን መምረጥ አለበት” ይላል። “ወይ ኳሱን መቆጣጠር እና ተጋጣሚው ቡድን እንዲጫወት በፈቀደለት ክፍት ቦታ ላይ መጫወት አለበት፣ አሊያም ደግሞ መከላከልን በመምረጥ የራሱ ሶስተኛው የመከላከያ ሜዳው ክፍል ከኳስ ጀርባ የሚቆሙ የሰዎችን ቁጥር በማብዛት ኳስን ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ አምኖ መጫወት።” ኳስን ይዞ የሚጫወተው “proactive” ቡድን ሲሆን፣ ኳሱን የሚከላከለው ደገም “reactive” በመባል ይታወቃል።

የቀድሞው የጣሊያኑ የኤሲ ሚላን ክለብ ታላቅ አሰልጣኝ አሪጎ ሳኪ በአንድ ወቅት ዘ ጋርዲያን (The Guardian) ጋዜጣ ላይ የጣሊያን እግርኳስ አምደኛ (columnist) ከሆነው ፓውሎ ባንዲኒ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በተለይ አጨዋወታቸው ኳስን በመቆጣጠር (possession football) ላይ ያተኮሩ ቡድኖች ውጤታማ ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እሳቸው ኤሲ ሚላን ውስጥ የተገበሩትን እና በዚህ አጨዋወት ዘዴ ዝነኛ የሆኑት የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም እና የስፔኑ ባርሴሎና ክለቦችን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ የተናገሩት ኳስን መቆጣጠር/አጭር ኳስ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት ያላቸው የኢትዮጵያ ቡድኖች (ብሄራዊ እና ክለቦች) ለምን ውጤታማ ለመሆን እንደተቸገሩ በግልጽ የሚያብራራ ነበር።

ታላላቅ ቡድኖች ኳስን እና ቦታን የመቆጣጠር አላማ ያለው ተመሳሳይ አይነት ባህሪ አላቸው። መቼ የያዛቸውን ተጨዋች ማምለጥ እንዳለባቸው እናመቼስ የተከፈተ ቦታን መቆጣጠር እንዳለባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሁልጊዜ ማሰብ ያለባቸው እና እርምጃዎችን/ውሳኔዎችን መውሰድ ያለባቸው ግንከተጋጣሚያቸው ቡድን ሳይሆን ከቡድናቸው ተጨዋቾች እና እንቅስቃሴ በመነሳት መሆን አለበት።”ነበር ያሉት አሪጎ ሳኪ

እግር ኳስ በጣም የተወሳሰበ ስፖርት ነው። ስታጠቃ በተጨዋቾችህ መሀል ያሉት ርቀቶች ትክክለኛ መሆን አለባቸው። ጊዜ አጠባበቅህ እና አጠቃቀምህልክ ሊሆን ይገባል። የያዘህን ተጨዋች ማስለቀቂያ ትክክለኛ መንገድ ሊኖርህ ይገባል። እነዚህ ነገሮች ከሌሉህ የምትጫወተው እግርኳስ ፍሰትአይኖረውም። ብዙውን ጊዜ ቡድኖች ቡድን ከመሆን ይልቅ ዝም ብለው የተጨዋቾች ስብስብ ሆነው ይቀሩና በአንድነት መንቀሳቀስ ሲቸገሩ ታያለህ።ሲሉ  ማብራሪያ ሰጥተው ነበር በአፍሪካ ዋንጫው ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ሆነ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ቡድኖች ሜዳ ውስጥ ሲገቡ የትኛውን የአጨዋወት ዘዴ መቼ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በግልጽ ከማየት ይልቅ ድንገት በአጋጣሚዎች ከ proactive ወደ reactive ሲቀያየሩ እና ያንንም በአግባቡ ሳይፈጽሟቸው ሲቀሩ ነው የሚታዩት።ይህ በስልጠና የሚገኙ ክህሎቶችን ያለማግኘት በአፍሪካ ዋንጫ የታየ ችግራችን ነበር፡፡


አስተዳደራዊው ነገር

እነዚህ በስልጠና የሚገኙ የላቁ እግርኳሳዊ እውቀቶች በተጨዋቾቻችን እና በአሰልጣኞቻችን አእምሮ ውስጥ እንዲኖሩ እና ብሎም ሜዳ ውስጥ እንዲተገበሩ ለማስቻል ደግሞ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ያለበት ከእግርኳስ ሜዳው ውጪ ያለው እና ነገሮችን የማመቻቸት ሀላፊነት ያለበት አስተዳደራዊ ክፍል ነው።

በእኔ አይን ውስጥ የእግርኳስ ሜዳ ጫካ ማለት ነው የሚለው ቫልዳኖ እዛ ጫካ ውስጥ ዛሬም ድረስ የሚካሄዱት ነገሮች ከዛሬ መቶ አመታትበፊት ይካሄዱ ከነበሩት ጋር ተመሳሳይነት እንዳላቸው ይናገራል። “ከመቶ አመት በፊት ይጫወት የነበረ አንድ አጥቂ ኳስን ይዞ ወደተጋጣሚጎል ሲደርስ ‘ምን ማድረግ አለብኝ’ ብሎ የሚያስበው ልክ ዲስቴፋኖ፣ ፔሌ፣ ማራዶና እና ሊዮ ሜሲ በተመሳሳይ አጋጣሚ ከሚያስቡት ጋርተመሳሳይነት አለው። እየተለወጠ ያለው ግን የጫካውን ዙሪያ የከበቡት ነገሮች ናቸው።

እነዚህ ቫልዳኖ “ከጊዜ ወደጊዜ ይለዋወጣሉ” ያላቸው ጫካውን/ሜዳውን የከበቡት ነገሮች ዘመናዊ የእቃ-አቅርቦቶች፣ ስልጣኔዎች፣ ሳይንሳዊ እና ፍልስፍናዊ አጨዋወቶች፣ ታክቲኮች፣ የገንዘብ ድጋፎች እና የስፖርት ገበያዎች እና አስተዳደሮች ናቸው።

ብዙዎቻችን ሜዳ ላይ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የሚሰሯቸውን ስህተቶች በአይናችን ስለምናያቸው ብቻ ለሽንፈት እና ለእግርኳሱ ድክመት የቀጥታ ተሳታፊዎቹን እንደምክንያት እያቀረብን ረጅም ጊዜ ሰንብተናል። ታዲያ ይህ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ጊዜያት ከተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ጀርባ ተደብቀው የእግርኳሱን አደረጃጀት እና ሂደት ወደኋላ እየጎተቱ ድንገት ብልጭ የሚሉ ውጤቶች ሲገኙ ልክ “የአብዮቱ ዋና መሰረቶች ነን” በሚል ትቢት እራሳቸውን በዋናነት በማስቀመጥ ስለ “ጠንካራ ሰራተኛነት፣ ስፖርትን ከታች ከህጻናት ጀምሮ ማስፋፋት፣ ህብረት፣ ስታዲዬም መገንባት፣ እግርኳሱ ላይ መዋለ-ነዋይ ማፍሰስ” የመሳሰሉ የሚያብረቀርቁ ወሬዎችን በማውራት እያጭበረበሩ መኖራቸውን ከተያያዙት አመታት አልፈዋል።

ከ12 አመታት በፊት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ወጣቶች እግርኳስ ሻምፒዮናን አስተናግዳ አራተኛ ደረጃን አግኝቶ በማጠናቀቁ አርጀንቲና ላይ በተካሄደው የአለም ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን በሻምፒዮናው ላይ በታላቁ ሆላንዳዊ አሰልጣኝ ሉዊ ቫን ሀል ይመራ ከነበረው የሆላንድ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደረገውን እንቅስቃሴ ጨምሮ ያሳያቸው ድንቅ ብቃቱ በሀገሪቷ ህዝብ ላይ ልክ የአሁኑ የአፍሪካ ዋንጫው ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድን የፈጠረውን አይነት ስሜት እና ተነሳሽነት መፍጠሩን የተገነዘቡ “እግርኳሳችንን በጋራ ለማሳደግ ቆርጠን መነሳት አለብን” የሚለው፣ ተቆርቋሪ መስሎ መታየት የሚፈልገው ፖለቲከኛ እና የስፖርቱ የበላይ ሀላፊ አጋጣሚውን በመጠቀም ሊያደርጉት የማይችሉትን የተጋነኑ ቃልኪዳን መግባቱን፣ የእግርኳስ ፌዴሬሽኑም “ኢትዮጵያ ልክ እንደሩጫው ሁሉ ስሟ በእግርኳሱም አለም ላይ ይገናል” የሚለው ንግግሩን ማስተጋባቱን ተያይዘውት ቃሎቻቸው በተግባር ሳይሆን በሌሎች ቃሎች ታጅበው ይሄው 12 አመታት አለፉ እና እንደገና በተመሳሳይ ተነሳሽነት በተጨዋቾች እና በጥቂት የቡድን አባላት ጥረት የተገኙትን ውጤቶች ተገን አድርገው እንደገና የሚያብረቀርቁ ወሬዎቻቸውን አሁንም እያወሩልን ነው።

ለኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃሪ ትእግስት አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ትግስተኛ ህዝብ የሚመኘው እና ማየት የሚፈልገው ግን የሚመለከታቸው የስፖርቱ የበላይ ሀላፊዎች በአሸናፊነት ጀርባ ላይ ተንጠልጥለው ለመታየት ጥረት ለማድረግ ከሚያወጡት ጉልበት ላይ ግማሹን እንኳን ቆጥበው ቃል ሲገቡልን የነበሩትን እና አሁንም እየገቡልን ያሉትን ሩብ ያህሎቹን እንኳን ተግባራዊ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ ያላቸውን አቅም እና ችሎታ ተጠቅመው የአቅማቸውን ያህል በመጣር ቢያንስ የሀገሪቷ እግርኳስ “አለሁ” ብሎ በአፍሪካ እግርኳስ ውስጥ ስሙን እንዲያስተጋባ እና ህዝቡም በአንድነት በታላቅ ደስታና ስሜት ለአጭር ጊዜም ቢሆን እንዲቦርቅ ላስቻሉት ተጨዋቾች የሚገባቸውን ክብር እና አድናቆት ሊሰጣቸው ይገባል።

No comments:

Post a Comment