Tuesday, February 12, 2013

ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር የረታ ይቅርታ!



በፍቅር ለይኩን

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ጓደኞቿና የነፃነት ትግሉ አጋሮቿም፡- ‹‹እናዝናለን ኤሚፍቅርሽ፣ ርኅራኄሽ፣ ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት መከበር ያለሽ ጽኑ አቋም በልባችን ለዘላለም ይኖራል፡፡ ትግላችን እንዳቺ ያሉ የእውነት፣ የፍትሕ ጠበቃዎችንና ሐቀኞችን በአጥፍ ጨምሮ ይቀጥላል፡፡ ኤሚ እንወድሻለን፣ ሁሌም እናስታውስሻለን! አንቺ የዘረኞችን የመለያየት ግንብ የናድሽ ጀግናችን ነሽ፣ አንቺ በልባችን ውስጥ ለዘላለም ሕያው ነሽሞት በአንቺ ላይ ስልጣን የለውም፣ ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ያሸነፈሽ የሕዝባችን ታላቅ ሰማዕት ነሽና …!›› በማለት ወደ ትውልድ አገሯ አሜሪካ በእንባና በመሪር ሐዘን ሸኟት፡፡
                                                   
ውቧ፣ ማራኪዋና ከዓለማችን አስር ምርጥ ከተሞች ተርታ የተመዘገበችው የደቡብ አፍሪካዋ የኬፕታውን ከተማ የደቡብ አፍሪካ የታሪክ፣ የቅርስ፣ የባህልና የፖለቲካ ማዕከል ናት፡፡ የድኅረ ምረቃ ትምህርቴን የተከታተልኩባት ኬፕታውን ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል አፍሪካውያን ያለፉበትን ውስብስብ የታሪክ ጉዞ የሚያስቃኙ፣ የጥቁር ሕዝቦችን የአይበገሬነትና የነፃነት ተጋድሎ የሚዘክሩ በርካታ ቅርስና ሕያው አሻራ ያላት ታሪካዊ ከተማ ናት፡፡

ኬፕታውን ታላቁ አፍሪካዊ የነፃነት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለ27 ዓመታት የተጋዙባትን ቀዝቃዛውን የአትላንቲክ ውቅያኖስንና የከተማይቱን ግርማና ውበት የሆነውን የቴብል ማውንቴንን ተንተርሶ የተገነባው የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት የሚገኝባትም ናት፡፡

ይህን ለዘመናት በርካታ አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ለሰው ልጆች ነፃነትና ሰብአዊ መብት ሲሉ የተጋዙበትን የሮቢን ደሴየት ግዞት ቤት/ወኅኒ ቤት በየቀኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎችና አጥኚዎች፣ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ ታላላቅ የሆኑ የዓለማችን የፊልም እንዱስትሪዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ዝነኞችና ባለ ጠጋዎች ይጎበኙታል፡፡ እናም የደቡብ አፍሪካዋ ‹‹እናት ከተማ›› ኬፕታውን የቱሪስቶችና ውብ የመዝናኛ ከተማም ጭምር ናት፡፡

በዩኒቨርስቲ ቆይታዬ በትምህርት ክፍላችንና የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሙን ነፃ የትምህርት ዕድልና አጠቃላይ ወጪያችንን የሸፈነልን የሮቢን ደሴየት ሙዚየም፣ በኬፕታውን የሚገኙትን ቤተ መዘክሮችን፣ የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ተጋድሎ የሚያንጸባርቁ ታሪካዊ ቦታዎችንና ቅርሶችን መጎብኘት እንድንችል ዕድልን አመቻችቶልን ነበር፡፡ በዚህ ዕድልም ከጎበኘኋቸውና በማስታወሻ ደብተሬ ከመዘገብኳቸው አስደናቂ ስፍራዎች መካከል አንዱ ለዛሬ ጽሑፌ መነሻ ሆኖኛል፡፡

እኔና የክፍል ጓደኞቼ ጉብኝታችን ፕሮግራሞች ውስጥ ካየናቸው የአፓርታይድ አገዛዝን ጭካኔና ክፋት ከሚዘክሩ ታሪካዊ ቦታዎች በኬፕታውን ከተማ የሚገኘው የጉጉሌቱ ታውን ሺፕ አንዱ ነው፡፡ ይህ ታውን ሺፕ/መንደር በአብዛኛው ጥቁሮች የሚኖሩበት ነው፡፡


እነዚህ በአራቱም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የጥቁር አፍሪካውያን መንደሮች በደቡብ አፍሪካውያን ሕይወት ዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት የተወው ጠባሳ ገና ፈፅሞ የሻረ እንዳልሆነ ማረጋገጫን የሚሰጡ ናቸው፡፡ እስከአሁንም ድረስ ጥቁር አፍሪካውያኑ የሚኖሩባቸው እነዚህ መንደሮች ድህነትና ጉስቁልና በእጅጉ የሚንጸባረቅባቸው መሆናቸው የሕዝቦቻቸው ኑሮ ይመሰክራል፡፡  

በዚህች በጉጉሌቱ የድኆች መንደር ውስጥ ነዋሪዎቿና ሥራ አጥ ወጣቶቿ ካሉበት አስከፊ ድህነትና ጉስቁልና በመጠኑም ቢሆን ለማውጣትና እገዛ ለማድረግ በአሜሪካውያን ቤተሰቦች የተቋቋመ አንድ ፋውንዴሽን አለ፡፡ በጉብኝታችን ወቅት ስለዚህ ፋውንዴሽን ማብራሪያ የሰጠን አስጎብኚያችን የፋውንዴሽኑን አመሰራረት ታሪክ እንዲህ ሲል አጫወተን፡፡ እኔም በማስታወሻዬ የዘገብኩትንና በዚህች ድህነትና ወንጀል በተንሰራፋበት የጥቁሮች መንደር ‹‹ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ስለረታው›› አስደናቂ የእርቅ/የይቅርታ ድንቅ ታሪክ ላስነብባችሁ ወደድኹ፡፡

ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል በ1970ዎቹ እና በ1980ዎቹ  መጨረሻ አካባቢ ላይ እጅጉን የተፋፋመበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ያገኙ ደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ተማሪዎች ትግሉን ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ያሻገሩበትን ትልቅ ዕድል ፈጥሮ ነበር፡፡

በዚህ በኬፕታውን ከተማ በዋነኝነት ለክልሶች፣ ለኢንዲያንስ (Colors and Indians) እና ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች የመማር ዕድል እንዲያገኙ በተቋቋመው የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ፣ ከአሜሪካን ካሊፎርኒያ ኮሌጅ በFulbright Scholarship ዕድል አግኝታ የመጣች አንዲት በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ነጭ አሜሪካዊ ወጣት በዩኒቨርስቲው ያለውን የተማሪዎችን ፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴና ትግል ለማጥናት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ ለአስር ወራት ቆይታ ለማድረግ መጥታ ነበር፡፡

ኤሚ የተባለችው ይህች አሜሪካዊት ሴት በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ከጥቁር ተማሪዎች ጋር ለመተዋወቅና አጋርነቷን ለመግለፅ ብዙም ጊዜ አልወሰደባትም ነበር፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተማሪዎቹ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ዋና የትግል አጋርም ለመሆን በቃች፡፡ የፀረ አፓርታይድ ትግሉንም በሐሳብና በሞራል መደገፉን ተያያዘችው፡፡ በተጨማሪም ከአፍሪካውያን ተማሪዎች ጋር ስለ አፍሪካውያን የነፃነት ትግልን በተመለከተ ሰፊ ውይይትና ጥናት ማድረጓንም ቀጠለች፡፡ ከአፓርታይድ አገዛዝ ወደ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት በሽግግር ወቅት ለነበረችው ደቡብ አፍሪካም የምትችለውንና የአቅሟን ሁሉ አድርጋለች፡፡ 

ኤሚ ከተማሪዎቹ ጋር ያስተሳሰራት የፀረ አፓርታይዱ ትግል ይበልጥ ወንድማዊና እህታዊ የሆነ ቤተሰባዊ ወዳጅነትን አተረፈላት፡፡  እናም ኤሚ አፍሪካውያን ጥቁር ተማሪዎች በሚኖሩባቸው በተከለሉ የጥቁሮች መንደሮች እየተዘዋወረች የዘረኛውን የአፓርታይድ መንግሥትን አስከፊና ዘግናኝ ጭቆና በዓይኗ ለመታዘብና ምስክር ለመሆን ቻለች፡፡

ጭቆና፣ ድህነት፣ መከራ፣ ጉስቁልና፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ የዘረኛው አፓርታይድ መንግሥት ክፉ ተግባርና ግፍ አባሳቸውን በሚያስቆጥራቸው በእነዚህ የድሆች ከተማዎች ውስጥ ያለውን ዘግናኝ ሕይወት ኤሚ በአዕምሮዋና ብዕሯ መከተቡን በሚገባ ተያያዘችው፡፡
 
የሚሊዮኖች የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የፍትህ ያለህ ዋይታና እሪታ በሚሰማባቸው የጥቁሮች መንደር ያለውን ዘግናኝ እውነታ የታዘበችው ኤሚ፡- ይህ ግፍ፣ ይህ ኢ-ሰብአዊነትና ጭካኔ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ፀረ አፓርታይድ ትግልና ታጋዮች ያላትን አጋርነት በይበልጥ እንድታጠናክር አደረጋት፡፡ ኤሚ በሳምንቱ መጨረሻና በበዓል ወቅት ለእረፍት ወደቤተሰቦቻቸው የሚሄዱትን ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ በመኪናዋ በመሸኘት ጭምር ከእነርሱ ጋር ብዙ ጊዜዋን ታጠፋ ነበር፡፡

ታዲያ ከሰብአዊነት ከመነጨ ፍቅርና ርኅራኄ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ተማሪዎች ድጋፏን ስትሰጥ የነበረችው ኢሜ በአንድ ወቅት የትምህርት ቤት ጓደኞቿንና የትግል አጋሮቿን ለመሸኘት ለጥቁሮች ብቻ ወደተከለለ የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የድሆች መንደር ወደሆነችው ጉጉሌቱ እንደበፊቱ ሁሉ አገር ሰላም ነው ብላ መኪናዋን በማሽከርከር ትመጣለች፡፡

ጓደኞቿን ከመኪናዋ አውርዳ የምትቸኩልበት ሌላ ጉዳይ የነበራት ኤሚ መኪናዋን አዙራ በፍጥነት ወደ ከተማ ለመመለስ ስትነዳ ሳለች በመንገዷ ላይ ሁከት ከታከለበት ሰልፍ ውስጥ ራስዋን አገኘችው፡፡ ከሰልፉ መካከል የወጡ ሁለት ወጣቶችም መኪናዋን እንድታቆም አጭርና ቀጭን ትዕዛዝን አስተላለፉላት፡፡ ኤሚ በወጣቶቹ ትዕዛዝ በጥቂቱም ቢሆን ግራ ተጋባች፡፡

ይሁን እንጂ ኤሚ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ የመሰላት ጥቁሮች ለነፃነታቸው የሚያደርጉትን ትግል በመደገፍ በመቆሟ አድናቆታቸውንና ምስጋናቸውን ሊገልፁላት መስሎአት የወዳጅነት ፈገግታን በተሞላ መንፈስ ሰላም አለቻቸው፡፡ ያ በኤሚ ፊት የታየው ከፍቅርና ከርኅራኄ የመነጨ ፈገግታዋ ግን በእነዚህ ወጣቶች ዘንድ በምላሹ ጥላቻን ያነገሰ ቅፅበታዊ የሆነ ግብታዊ ስሜትን ፈጠረ፡፡

እናም እነዚህ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ወጣቶች በዛ በነጮቹ የአፓርታይድ ዘረኛ ስርዓት አራማጆች ለጥቁሮች ብቻ ተከልሎ በተሰጣቸው ምስኪን መንደራቸው ይህችን ነጭ ወጣት ሴት ማየታቸው በእጅጉን አናደዳቸው፡፡ እናም በውስጣቸው የሚንቀለቀለውን ንዴትና በቀል በኤሚ ላይ ለማዝነብ ፈጣን እርምጃ ወሰዱ፡፡ የኤሚ ተማጽኖና የማንነት ኑዛዜ ሰሚን አላገኘም፡፡

ወጣቶቹ ኤሚን በመኪናዋ ውስጥ እንዳለች በድንጋይ በመውገር ያን የፍቅርና የርኅራኄ ፈገግታዋን በበቀል ደም አጨልመውትና አጠልሽተውት እግሬ አውጪኝ በማለት ከአካባቢው ተሰወሩ፡፡ በደም ተጨማለቀችውን ሴት ፖሊስ ደርሶ ወደ ሐኪም ቤት ይዟት ቢሄድም ሕይወቷን ለማትረፍ አልተቻለም ነበር፡፡ እናም ኤሚ በዚህ ዓይነት ያልተጠበቀ መጥፎ አጋጣሚ ሕይወቷ አለፈ፡፡

ባልታሰበና ባልተጠበቀ አጋጣሚ ኤሚ ለነፃነታቸውና ለሰብአዊ መብታቸው በምትታገልላቸውና አይዞአችሁ በምትላቸው ጥቁሮች ወንድሞቿ እጅ ሕይወቷ አለፈ፡፡ ገዳዮቿም በፖሊስ ተይዘው ወኅኒ እንዲወረወሩ ተደረገ፡፡ ይህን ዘግናኛ አጋጣሚ የሰሙና ያዩ ጓደኞቸዋ ሀዘናቸው እጅጉን የመረረ ነበር፡፡ የትግል አጋራቸውንና የልብ ጓደኛቸውን ያጡት የዌስተርን ኬፕ ተማሪዎች- የትግል አጋሮቿ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ ሐዘናቸውን ለመግለጽ ልዩ ፕሮግራም በማድረግ ኤሚን፡-

 ‹‹እናዝናለን ኤሚፍቅርሽ፣ ርኅራኄሽ፣ ለሰው ልጆች ነፃነትና መብት መከበር ያለሽ ጽኑ አቋም በልባችን ለዘላለም ይኖራል፡፡ ትግላችን እንዳቺ ያሉ የእውነት፣ የፍትሕ ጠበቃዎችንና ሐቀኞችን በአጥፍ ጨምሮ ይቀጥላል፡፡ ኤሚ እንወድሻለን፣ ሁሌም እናስታውስሻለን! አንቺ የዘረኞችን የመለያየት ግንብ የናድሽ ጀግናችን ነሽ፣ አንቺ በልባችን ውስጥ ለዘላለም ሕያው ነሽሞት በአንቺ ላይ ስልጣን የለውም፣ ሞትን በሕይወት፣ ጥላቻን በፍቅር ያሸነፈሽ የሕዝባችን ታላቅ ሰማዕት ነሽና …!›› በማለት ወደ ትውልድ አገሯ አሜሪካ በእንባና በመሪር ሐዘን ሸኟት፡፡

ከጥቂት ዓመታት በኋላ የእነ ኤሚና የሚሊዮኖች ደቡብ አፍሪካውያንና የሰው ልጆች ነፃነት ተቆርቋሪ የሆኑ ሕዝቦች መራር ትግል በስተመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ የአፓርታይድ ስርዓት ከደቡብ አፍሪካ ምድር ተገረሰሰ፡፡ የፀረ አፓርታይድ ትግሉ ዋና መሪ በሆኑት በኔልሰን ማንዴላ ግንባር ቀደምትነትም በአዲሲቷ ደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ እርቅና መግባባት እንዲወርድ ታወጀ፡፡

ለዚህም ማንዴላ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ለ27 ዓመታት ግዞት፣ ለሕዝባቸው መከራ፣ እንግልት፣ ስደትና ሞት ምክንያት የሆነውን የአፓርታይዱ ዘረኛ መንግሥት መስራችና ዋና አቀንቃኝ ወደሆኑት ወደ ሟቹ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቤት በመሄድ በሕይወት የሚገኙትን ባለቤታቸውን፣ ዘረኛው የአፓርታይድ ስርዓት በርሳቸውና በሕዝባቸው ላይ ላደረሰባቸው የሰው ልጅ ሕሊና ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ለሆነው ግፍና መከራ በፍፁም ልብ ይቅርታ ማድረጋቸውን ለዓለም በይፋ ገለጹ፡፡

ዓለም በአንድ ድምፅ፡- ‹‹ብራቮ ማንዴላ! የሰላም አባት፣ የፍቅር ተምሳሌት፣ የይቅርታ መዝገብ…!›› ሲል አሞካሻቸው፡፡ ይህን የፍቅርና የእርቅ መንገድ ሚሊዮኖች ደቡብ አፍሪካውያን ዘረኛው አፓርታይድ መንግስት ትቶባቸው ካለፈው ህመማቸው፣ ስብራታቸውና ቁስላቸውም ጋር እየታገሉም ቢሆን ‹‹ዳዳ/ማዲባ›› ወይም ‹‹ታላቁ አባታችን›› የሚሏቸውን የማንዴላን ‹‹የሰላምና የእርቅ መንገድ›› ቆርጠው ሊከተሉት ወሰኑ፣ የብዙዎችም ልብ ለፍቅርና ለይቅርታ ጨከነ፡፡

በዚህም ለቂምና ለበቀል፣ ለክፋት፣ ለጥላቻና ለእርስ በርስ እልቂት ከሰገባቸው የተመዘዙ የበቀል ሰይፎች ወደ ሰገባቸው ተመልሰው በአንፃሩ ደግሞ በዚህች የእግዚአብሔር ስጦታ በሆነች ውብና ባለ ጠጋ የአፍሪካ ምድር- በደቡብ አፍሪካ እርቅና ሰላም ይወርድ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችና ተሟጋቾችን፣ ታዋቂ ሰዎችን ጭምር ያቀፈ የእውነት አፈላላጊና የእርቅ ኮሚሽን (Truth and Reconciliation Commission) በይፋ ተቋቋመ፡፡

ይህ የደቡብ አፍሪካ የእውነት አፈላላጊና የእርቅ ኮሚሽንም በአፓርታይድ ዘመን የደረሱትን የመብት ጥሰቶች፣ ጭፍጨፋ፣ እልቂትና ግፍ በመመርመር በበዳይና በተበዳይ መካከል ሰላምና እርቅ እንዲወርድ፣ እንዲሁም የትላንትና ቁስሎች በቂም በቀል ሳይሆን በይቅርታና በካሳ እንዲዘጉ ትልቁን ኃላፊነትና ታሪካዊ የሆነ ድርሻ ወሰደ፡፡

በዚህም የትላንትና የጭቆና፣ የክፋት፣ የጥላቻ፣ የእልቂትና የደም ዘመን ምዕራፍ ተዘግቶ በአገሪቱ አዲስ የሆነ የእርቅና የሰላም ታሪክ እንዲፃፍ አደረገ፡፡ ከዚህም የተነሳ አዲሲቱ ደቡብ አፍሪካ ነጭ፣ ጥቁር፣ ክልስ፣ ህንድ…ወዘተ ሳይባል ሁሉም በሰላምና በአንድነት የሚኖሩባት Rainbow Nation የሚል ቅጽል ስምንና ክብርን አተረፈች፡፡

ወደ ታጋይዋ ኤሚ ታሪክ ፍፃሜ ስንመለስ ደቡብ አፍሪካ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ካደረገች በኋላ በአፓርታይድ ዘመን በደቡብ አፍሪካውያን ሕዝቦች ላይ የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያ፣ እሥራትና ግፍ ለማጣራት በተቋቋመው የእውነትና የእርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን  በተደረገላቸው ግብዣ ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት የኤሚ ወላጆች ሚ/ር ፒተርና ወ/ሮ ሊንዳ በልጃቸው ሞት ምክንያት የተከሰሱ ወጣቶች በተገኙበት በተካሄደው ችሎት ለልጃቸው ገዳዮች ፍፁም የሆነ ከልብ የመነጨ ይቅርታ ማድረጋቸውን በፍቅር ገለፁ፡፡

ዕድሜ የተጫጫናቸው የኤሚ እናትና አባት በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ገና አሁንም ከባድ የሆነ ድህነት፣ የሥራ አጥነትና ወንጀል በተንሰራፋባት በምስኪኗ ጉጉሌቱ የፍቅርና የይቅርታ ሀውልትን ለማቆሙ ወደዱ፡፡ የአፓርታይድ ዘረኛ መንግስት ትቶት ያለፈው መጥፎ አሻራው ባልጠፋባት በዚህች መንደር መካከል ወደተቋቋመው ፋውንዴሽን በእጁ እየጠቆመን አስጎብኚያችን አንዳንች ልዩ ስሜት የተጫነው በሚመስል ቃላቶችና የሰውነት እንቅስቃሴ ትረካውን እንዲህ ቀጠለልን፡-

የኤሚ ወላጆች በችሎቱ ፊት ባሰሙት ውሳኔያቸው ለልጃቸው ገዳዮች ፍጹም የሆነ ይቅርታ ማድረጋቸውን በይፋ ገለጹ፡፡ ለሟች ልጃቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድም ልጃቸው በድንጋይ ተወግራ በሞተችበት አካባቢ ለመንደሩ ነዋሪዎችና ሥራ አጥ ወጣቶች እንዲሆን በራሳቸው ገንዘብ በግፍ ለተሠዋችው ለልጃቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የኤሚ ፋውንዴሽንን አቋቋሙ፡፡ የኤሚ ገዳዮችም በዚሁ ፋውንዴሽን ውስጥ ዋና ሠራተኛ መሆናቸውንም ልብ ይሏል፡፡

ይሄ ፋውንዴሽን ለልጃቸው፣ ለምስኪኗ ሰማዕት ኤሚ የበቀል ደም በፍቅርና በይቅርታ ይደመደም ዘንድ የተቋቋመ መሆኑን አስጎብኚያችን ሲተርክልን ብዙዎቻችን በስሜት ተውጠንና ዓይናችን እንባ አቅርሮ ነበር፡፡ አንድና ብቸኛ ልጃቸውን በሞት የተነጠቁት የኤሚ አባትና እናትም ለልጃቸው ገዳዮች እናትና አባት እንደሚሆኑላቸው ጭምር ነበር ከልብ በሆነ ፍቅር ያበሰሯቸው፡፡ አስጎብኚያችን እጅግ ልብ የሚነካውን ታሪክ መተረኩን ቀጥሏል . . .፡፡

በጉብኝቱ መካከል የነበሩ አብዛኞቹ ሴት ተማሪዎችም እንባቸው መንታ ሆኖ በጉንጫቸው ላይ ሲወርድ በግልፅ ይታይ ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በዚህች በድሆች መንደር ‹‹ለፍቅርና ለእርቅ›› በቆመው ፋውንዴሽን ሕንፃ ላይ ዓይናቸውን ለደቂቃ ሰክተው ጥልቅ የሆነ የአሳብ ባሕር ውስጥ የገቡ ይመስሉ ነበር፡፡ አስጎብኚያችን ትረካውን ጨርሶአል፤ ሁኔታው ግን ከእኛው ጋር ቃላት ሊገልፀው በማይችል ጥልቅና በልዩ ስሜት ውስጥ አብሮን የነጎደ ይመስል ነበር፡፡

ይህን አስደናቂ የፍቅር/የእርቅ ገድል ታሪክ ከምመዘግብበት ማስታወሻዬ ላይ እንዳቀረቀርኩ ሕሊናዬ፡- የራሴን፣ የወገኖቼንና አገሬን የእርስ በርስ መበላላት ዘግናኝ ታሪክ፣ የቂም፣ የበቀልና የጦርነት ታሪክ ወደፊትና ወደኋላ እያጠነጠነ ነበር፡፡ ከሰላሙ፣ ከፍቅሩ፣ ከአንድነቱና ከእርቁ ታሪካችን ይልቅ የመበላላት፣ የቂም፣ የበቀልና የመለያየት ዘግናኝ ታሪካችን በዓይነ ሕሊና ገዝፎ ታየኝ፡፡ እናም ካቀርቀርኩበት ቀና ስል ዓይኔ ያረገዘው ትርጉም አልባ የሚመስል የእንባ ዘለላ ቁልቁል ወርዶ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ጠብ ሲል ተመለከትኩኝ፡፡

በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ዛሬም ምስክር ሆኖ ያለው የደረቀው እንባ የኤሚንና የወላጆቿን የነፃነት ተጋድሎ፣ የእውነትና የፍትሕ ራባቸውን፣ ድንበርና ዘር ያላጋደውን የፍቅራቸውን ታላቅነትና ሕያውነት በአንክሮት ያሳስበኛል፡፡ በእውነትም ይህ በኬፕታውን በጉጉሌቱ የጥቁሮች መንደር በኤሚ ስም የተቋቋመው ፋውንዴሽን በፍቅር ስለፍቅር በተከፈለ መስዋእትነት፣ የይቅርታን ታላቅነት በተግባር ለመተረክ የቆመ ሕያው ምስክር፣ ዘመን አይሽሬ ቅርስ መሆኑን ሁላችንም በጉብኝቱ የነበርን ከተለያዩ ሀገራት የመጣን ተማሪዎች በአንድ መንፈስ በአንድ ቃል ያረጋገጥን በሚመስል መንፈስ ዓይን ለዓይን ተያየን፡፡

ሁላችንም በዛች ቅፅበት በኤሚ ሰማዕትነት፣ በወላጆቿ የፍቅርና ይቅርታ ቋንቋ ከልብ የተግባባን መሰልን፡፡ ሕሊናችን መልሶ መላልሶ ኤሚን፣ ፒተርን፣ ሊንዳን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን… በዛች ድህነት፣ ጉስቁልና፣ ሥራ አጥነትና ወንጀል በተንሰራፋባት የጥቁሮች መንደር በጉጉሌቱ ለፍቅርና ለእርቅ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የቆመውን የኤሚን ፋውንዴሽን ያሰላስል ጀመር፡፡

ልባችንም አንደበታችንም በዚህ ሕያው የፍቅር ገድል የተረታ መሰለ፡፡ እናም ከጉብኝታችን ጉዞ መልስ የኤሚንና የወላጆቿን የፍቅር/የይቅርታ ታላቅ ገድል በመቀባበል እየተረክን ነበር ወደ ዩኒቨርስቲያንችን ቅጥር ግቢ በአድናቆትና በአግራሞት ተሞልተን የተመለስነው፡፡ 

የካሊፎርኒያዎቹ ሚ/ር ፒተርና ወ/ሮ ሊንዳ የልጃቸው ክቡር ሕይወት በብዙ እልፎች ሕይወት የሚተካውና መንፈሷ ሊያርፍ የሚችለው ገዳዮቿን በመበቀል ሳይሆን በይቅርታ መሆኑን በተግባር ያሳዩበት ይህ የፍቅር ገድል ታሪክ ዛሬም ድረስ በውስጤ ይደውላል፡፡ እነዚህም ቤተሰቦች በደላቸውን በሌላ በደል፣ በቂም በቀል ሳይሆን ከልብ በመነጨ ይቅርታ በበጎ ካሳ በፍቅር ደመደሙት፡፡ በእርግጥም ይቅርታ የተሰበረንና የቆሰለ ልብን ሊጠግን የሚችል፣ መዓዛው የሚያውድ፣ መልካም የፍቅር ዘይትን ማፍሰስ ካልቻለ ሙሉ ይቅርታ ሊሆን አይችልም፡፡

በወቅቱም ይህን የኤሚን ቤተሰቦች ፍቅር፣ ርኅራኄና ይቅርታ የታየበትን ሰላማዊ የሆነ የእርቅ እርምጃ አንድ የደቡብ አፍሪካ ታዋቂ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ገልፆት ነበር፡-

Today, rather than having their lives subsumed in bitterness, Amy's parents are leading important, constructive lives as part of the great South African reconciliation effort. They keep Amy's spirit alive as a living memory, and they feel hope rather than anger. Strictly from the standpoint of their own self-interest, the Biehls are better off than if they had refused to forgive.

እውቁ የነፃነት ታጋይና የሰላም አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ በኤሚ ድንገተኛና አሳዛኝ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፡-

"She made our aspirations her own and lost her life in the turmoil of our transition as the new South Africa struggled to be born in the dying moments of apartheid. Through her, our peoples have also shared the pain of confronting a terrible past as we take the path of reconciliation and healing of our nation."

ፍቅርን ያብዛልን! ሰላም፣ እርቅና አንድነት ለእናት ምድራችን ለእማማ ኢትዮጵያችን ይሁን! አሜን ይሁን!!

ሰላም! ሻሎም!
---
ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው befikir12@yahoo.com ወይም fikirbefikir@gmail.com መጠቀም ይችላሉ፡፡

No comments:

Post a Comment