Friday, February 8, 2013

የታክሲዎቻችን ነገር
ከሌላው የኑሯችን ሳንካ ባልተናነሰ የአዲስ አበባ ከተማ ታክሲዎች አሠራር ተጠቃሚዎችን ማማረር እና ማበሳጨት ሥራቸው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከረዳትና ከሹፌር ጋር አተካሮ ሳይገጥም የሚሄድ ተሳፋሪ ያለበት ታክሲ ውስጥ መገኘት መታደል ነው፡፡ ባለታክሲ ስል ሾፌርንም ረዳትንም በጅምላ ወይም በተናጠል ማለቴ ነው፡፡ የፀቡ መንስኤ ሁል ጊዜ ባለታክሲ ነው  ብዬ አላስብም ተሳፋሪም  ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የዛሬ ርዕሴ  ባለታክሲዎችን የሚመለከት ነው፡፡

ባለቤት፣ ሹፌርና ረዳት

የታክሲ ሥራ ዋና ተዋናይ ሲሆኑ፤ ሁሉም አንድ የሚያረጋቸው የቀን ገቢያቸው ከፍ የሚልበትን ማንኛውንም መንገድ መጠቀማቸውና ለተሳፋሪም ርህራሄ የሌላቸው መሆኑ ነው፡፡ የታክሲ ባለቤት ሹፌር በሚሆንበት ጊዜ ረዳቱ ለከፍተኛ ቁጥጥር አደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ ሹፌሩ ተቀጣሪ በሚሆንበት ጊዜ ግን በአብዛኛው ሹፌርና ረዳት በመመካከርና በመረዳዳት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡ ረዳቱ የታክሲው ባለቤት የሚሆንበት ጊዜም አለ፡፡ ወይም የታክሲው ባለቤት ሹፌር ይቀጥርና የራሱ የቅርብ ሰው የሆነ ረዳት ይመድባል፡፡ (የባለቤቱ ዘመድ የሆኑትን ረዳቶች ሹፌሮች ‹‹ዕንባ›› ነው የሚሏቸው፤ ዕንባ ጠባቂ እንደማለት፡፡) ይህም ለሒሳብ ቁጥጥር ያመቸዋል፡፡ በሁለቱም መንገዶች ረዳቱ ሹፌሩን ሲመራ እና ሲያዝ ይስተዋላል፡፡ አብዛኛዎቹ ረዳቶች ሹፌር የሆነ ወቅት ያክል ከረዱ በኋላ የሹፌርነትን የሥራ መደብ ይይዛሉ፡፡


እነሱ ብቻ ተናጋሪ

ተሳፋሪን የሚተቹ እና የሚወቅሱ ጥቅሶችን ታክሲ ውስጥ ለተሳፋሪ ዕይታ በሚያመች መልኩ የሚለጥፉትን ነገር ባየሁ ቁጥር እኛም እኮ እንደነሱ የልባችንን የሚናገር ጥቅስ ለጥፈን ታክሲ ውስጥ መግባት ብንችል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንጀታችን እያረረም ቢሆን አንብበን ዋጥ አድርገናት እንሄዳለን እንጂ መልስ ለመስጠት ሞክረን አናውቅም፡፡ ከሚለጥፏቸው ጥቅሶች ውስጥ እስቲ እነዚህን ላስታውሳችሁ፡፡

 •  የታክሲ ከሌለህ ወርደህ በባስ ሂድ
 • ባለጌና ዋንጫ ከወደአፉ ይሠፋል
 • ሰው አካውንት ይከፍታል፤ አንዳንዱ አፉን ይከፍታል
 • ማስቲካ የሚታደል መስሏችሁ አፋችሁን እንዳትከፍቱ
 • ጤነኛ ካልሆኑ መውረጃዎ ደርሷል
 • የቤትህን አመል እዛው!!!
 • ለካፌና ለላዳ ብዙ ይከፍላሉ፤ እኛ ሲሳፈሩ ለምን ይጨቃጨቃሉ


በተጨማሪም እነሱ ያሉት ነገር ካልሆነ ተሳፋሪን በመስደብ እና በማመነጫጨቅ ሰላማቸውን ያሳጧቸዋል፡፡ ተሳፋሪዎችም ወይ እየሰሙ ዝም ይላሉ፤ ቢመልሱላቸውም ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ አይኖራቸውም፡፡ አለፍ ሲልም እስከመማታት ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ 

የሚመሩበትን ሕግ የሚጥስ ሌላ ሕግ ማውጣት

የታክሲ ሥራን የሚቆጣጠር አካል የሚሰሩበትን መስመር እና በመንገዱ የርቀት  መጠን የዋጋ ታሪፍ ባወጣው ደንብ መሠረት መሥራት እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ እነሱ ግን እንዳሻቸው ከተቀመጠላቸው መመሪያ ጋር የሚፃረር አዳዲስ ሕግ እና ደንብ እራሳቸው እያወጡ ያለአንዳች መሳቀቅ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፡-

 • ከመነሻ የተሳፈረ ተሳፋሪ የሚወርደው የትም ሆነ የትም የረጅሙን ርቀት ታሪፍ መክፈል አለበት
 • የሚሄድበት መስመር ታፔላው ላይ ተለጥፎ እያለ፤ ሲጭን ግን መስመር ቆራርጦ እና ተሳፋሪው የሚሄድበትን/የሚወርድበትን ቦታ ጠይቆ የተስማማውን ማሳፈር
 • መሽቷል፣ በመንገድ  ተጨናንቋል እና ተቆፋፍሯል ሰበብ ከታሪፉ በላይ አላግባብ  ማስከፈል
 •  ደርቦ ማስቀመጥ ግዴታ ነው አለበለዚያ ሌላው አማራጭ ከታክሲው መውረድ

ለደንባቸው አለመገዛት እና ሙሰኝነት

ታክሲዎች የሚነሱበት ቦታ እና ተሳፋሪዎች በብዛት የሚወርዱበት ወይም የሚጫኑበት አካባቢዎች ላይ ተራ በማስከበር ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች ዕይታ በመሰወር ተሸሎክሉከው ለማለፍ ይጥራሉ፡፡ እንዲህ የሚያደርጉት ለተራ ሚከፈለውን ክፍያ ላለመክፈል ሲሆን ይህን ክፍያ ላለመክፈልም አንዳንዶቹ አስከባሪዎቹ ካሉበት ቦታ ጥቂት ወደፊት ወይም ወደኋላ ሄደው የተራ ሳይከፍሉ ይጭናሉ፡፡ አንድ ወቅት ተራ አስከባሪዎች ይህን ችግር ለመቆጣተር በቲኬት መሥራት ጀምረው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ብዙም ግን አልዘለቁበትም፡፡ ያው አዲስ አሠራር ጀምሮ ወዲያውኑ መተው ለአገራችን ብርቅ አይደለም፡፡

ሙሰኞች ናቸው የምልበት ምክንያት ደግሞ፤ ሰልፍ ያለበትም ሆነ የሌለበት ቦታ ሹፌሩ ወይም ረዳቱ የሚውቀው ሰው ሳይሰለፍ እና ሳይጋፋ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ቅድሚያ የመስጠት ተግባር የሚፈፅሙት ታዲያ ለሚውቁት ተሳፋሪ ብቻ አይደለም፡፡ ቀልባቸው ለወደደው ሰውም ቅድሚያ የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በብዛት ይሄ ዕድል የሚገጥማቸው ሴቶች ናቸው፡፡ በተለይ ውብ እና ዓይን ገብ የሆኑቱ፡፡ ቀጠን ሰብሰብ ያሉ ተሳፋሪዎችም አብዛኛውን ጊዜ ተመራጮች ናቸው፡፡ በአንፃሩ ወፍራም የሆኑ ተሳፋሪዎች ሦስተኛ ሰው ለመጨመር ወይም ኋላ መደዳ ከሆነ ደግሞ አራተኛ ሰው ለመጨመር ስለማያመቹ ባለታክሲዎች አይመርጧቸውም፡፡ ከዚህ ቀደም በተከራካሪነት ወይም በተጨቃጫቂነት (መብታቸውን የሚያስከብሩም ሊሆኑ ይችላሉ) የሚያውቋቸውን ተሳፋሪዎች አይጭኑም፡፡                   

መልስ አለመስጠት

አሁን አሁን መልስ መጠየቅ በተለይ በሳንቲም ቤት እንደ አሳፋሪ ተግባር እንደሆነ እየቆጠሩት እና እያስቆጠሩት ነው - ባለታክሲዎች፡፡ ካልተጠየቁ መልስ አይሰጡም፡፡ በተቻላቸው አቅም ያረሳሳሉ፡፡ ሲጠየቁም ሳንቲም የለም የሚል ምክንያት በመስጠት ወይም መጀመሪያውኑ ሳንቲም እንደሌላቸው  በመንገር  መልሱን የሚያስቀሩበትን መንገድ ይፈጥራሉ፡፡ መልስ የሚጠይቅ ተሳፋሪ እንደ ጠላታቸው፤ የማይጠይቀው ደግሞ እንደ ወዳጃቸው አድርገው ይወስዳሉ፡፡

ባጠቃላይ ግን ሒሳብ ለመሰብሰብ እንደሚቸኩሉት መልስ መስጠት ላይ ይዘገያሉ፤ ባይመልሱም ደስታቸውን አይችሉትም፡፡

ጭካኔ እና የበዛ እራስ ወዳድነት

ተሳፋሪን የሚያቋሽሽ እና የሚያዋርድ ስድብ መሳደብ ይቀናቸዋል፡፡ ትልቅ አይሉ ትንሽ ሲሳደቡ መሳቀቅ እንኳን አይታይባቸውም፡፡ መልስ ለጠየቃቸው ተሳፋሪ እንኳን ስድብ እና ማመነጫጨቅ የሚቀናቸው ባለታክሲዎች አሉ፡፡ ተሳፋሪዎች ለያዙት ዕቃ የሚጠይቁት ክፍያ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ ምንም ቦታ ለማይይዝ ዕቃ የሚጠሩት ብር ምን ያክል ለተሳፋሪዎች እንደማያስቡና ጨካኝ መሆናቸውን ያሳብቃል፡፡ አጭር መንገድ ለሚሄድ ተሳፋሪ የረጅም ርቀት ሒሳብ ሲጠይቁ ሕፍረት እንኳን አይሰማቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት ተሳፋሪ ልከራከር ቢል “ማን ግባ አለህ”፣ “ተናግሬ ነው ያስገባሁት”፣ “እኔ መች እዚህ ቦታ ጠራሁ” (ዘልሎት አይሄድ እንግዲህ ይታያችሁ)፣ “ብር ከሌለህ የለኝም አትልም?”፣ “ከሌለህ በባስ አትሄድም” እና የመሳሰሉት ውርጅብኞች ይከተሉበታል፡፡

ኧረ ከዚህም የበለጠ በከተማችን ስላሉ ታክሲዎች ብዙ መባል ይችላል! ላሁን ግን ይበቃኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በታክሲዎች ተግባር ያልተማረረ ካለ እርሱ የባለታክሲው ዘመድ፤ ሳይሰልፍ፣ ሳይጋፋ እና መንገድ ሳይቆራረጥበት የሚሳፈር ወይም የመኪና ባለቤት መሆን አለበት፡፡

በተረፈ ታክሲዎቹ በማን አለብኝነት፣ በምን ታመጣላችሁ  እና ከኛ ውጪ አማራጭ የላችሁም በሚል የንቀት መንፈስ እኛን ማማረራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ታዲያ እነዚህ ትናንሾቹ ኢሕአዴግ መር መንግሥት መባል ያንሳቸው ይሆን?
-----

No comments:

Post a Comment